Archive | January 3, 2014

ከወያኔ ጋር ክርክር አጉል ጉንጭ ማልፋት

ከወያኔ ጋር ክርክር አጉል ጉንጭ ማልፋት
Alemayehu Tibebu/German/
እንደው አሁንስ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቀቢጸ ተስፋ እንዲህ ሲለፉ ሳይ በጣም እያሳዘኑኝ መጡ፡፡ ድሮ እናቴ ስትነግረኝ “ለማይገባው ሰው ነገርን መንገር ድንጋይ ላይ ውሃ ማፍሰስ ነው“ ትለኝ ነበር እውነትዋን ነበር፡፡
ገዥው መንግስት ላለፉት ሃያ ሁለት አመታት ሲያስተዳድር አንድም ቀን ቀጥተኛና ፍትሃዊ ነገርን ሳይናገርና ሳይሰራ እንዲሁም በየጊዜው በሚለዋወጡት ህጎቹ ምክንያት ብዙ ንፁሃን ዜጎች ለእስር፣ ለእንግልት፣ ለስደት እና ለሞት በመዳረግ ይኧው አሁንም አለ፡፡
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ነገር ባለፈው በኢቲቪ ኢህአዴግ እና የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ጸረ ሽብር ህጉ ክርክር ይሁን ልብ መድረቅ ሲያደርጉ ተመልክቼ ስለነበር የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሚያነሱት ግልጽና አሳማኝ ነገር ኢህአዴግ ተብየዎቹ እንደው ድርቅ ሲሉ ሳይ እኔ ለነሱ ልቤ ድክም አለ፡፡
እኔ እኮ የሚገርመኝ ገዥው ፓርቲ አንዳንዴ እንኩዋን የዋህ ቢሆን ወይም የዋህ መምሰሉ እንደ ተሸናፊነት ከቆጠረው ብልጥ ሆኖ የሰው ሃሳብ ቢሰማ ምን ነበረበት፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያነሱት ሃሳብ የህዝብን ጥቅም ማእከላዊ ያደረገ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ አመራር እንዲሰፍን ለማድረግ ከመፈለግ አንፃር ነው፡፡ ለምን የነሱን ሃሳብ እንደ ሰይጣን ሃሳብ ሲንገረው እንደሚያንገሸግሸው አላውቅም::
ለምሳሌ በዋነኝነት የጸረ ሽብር ህጉ ከነ አሜሪካና ከነ እንግሊዝ ቃል በቃል ስርአተ ነጥቡ ሁላ ሳይቀር ተቀዳ አሉን እንደ እኔ ሲጀመር ህጉ መቶ ፐርሰንት አያስፈልግም ፣የወንጀል መቅጫ ህጉ ውስጥ ያሉት አንቀጾች ይህን ችግር መከላከል ያስችላሉ ህገ መንግስቱም ቢሆን በቂ ነው ባይ ነኝ፡፡ እንደእኔ እንደእኔ በሌላም መንገድ ቢሆን ኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር ህግ ቢያስፈልጋት እንኩዋን በጥቅም /በተግባር ላይ የዋለበት መንገድ ግን አግባብ አይደለም፡፡(እኔ የጸረ-ሽብር ህግ ስል ህገመንግስታዊ መብቶችንና ግድታዎችን አጉልቶ የሚያሳዩ ህጎች ማለቴ ነው እንጂ ገዢው ፓርቲ የስልጣንና የአፈና ማስፋፊያ መሳሪያ ማለቴ አይደለም) ጎማ ሳይፈነዳ አራት ኪሎ አራት ቦምብ ፈነዳ ብሎ ህዝብን ሚያሸብር አይነት ነጻነት አይደለም፡፡

ህጉን አሸባሪዎችን ለመቆጣጠርና ለመቅጣት ይበል እንጅ መላውን በኢትዮጵያን ህዝብ ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉትንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለስጋት ህዝቡም ከነዚሁ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንዳይሰራ እንዳይሳተፍ በማስፈራራት በውጥረት ከተውታል፡፡
እነዚህ ሽብርተኞች የተባሉት ኦነግም ይሁን የግንቦት ሰባት መሪዎች እኮ በፊት ከኢህአዴግ ጋር ሽርክ የነበሩ እና ባሁኑ ሰአት ግን በፖለቲካው ጤና ማጣት የተነሳ አሸባሪ ተብለው የተሰየሙ ናቸው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ጸረ-ሽበር ህጉ ገዢው ፓርቲ የራሱን የአፈናና የአገዛዝ ስርአት ለመጠበቅ እንጂ የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ የታለመ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡የገዢው ፓርቲ ጥቅምና ስልጣን ለማስጠበቅና ለመከላከል ፤የሰላ በዕራቸውን በመጠቀም በእውነትና በምክንያት ላይ ተመስርተው አግባብ የሆነ ጥያቄና ትችት የሚያቀርቡበትን እንደ እስክንድር ነጋ፣ ዕርዮት አለሙ ፣ ውብእሸት ታየ ያሉ ጋዜጠኞችንና የፍትህና የነጻነት ድምጾችን ለማሳደድና ለማፈን ነው እየተጠቀመበት ያለው፡፡የዜጎች ማፈኛ እንጂ የዜጎች መጠበቂያ አልሆነም፡፡በጸረ ሽብር ህጉ ገዢው ፓርቲ ጠያቂ እንጂ ተጠያቂ አልሆነም፡፡መቃወምና መስተካከል አለበት ብዬ የማስበው እንዲህ አይነቱ ነገር ነው፡፡
አነድ ሰው በኑሮ መወደድ ተማሮ ተቃውሞ ቢያቀርብ ህዝቡን ለአመጽ እና ለሽብር አነሳሳ ብሎ ለእስር መዳረግ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ደግፎ ስለነሱ ቢያወራ ከአሸባሪዎች ጋር ተባበረ አወራ ተሳተፈ ……. ወዘተ በማለት ድራማውን በማቀነባበር ሰው ባልዋለበት አውሎ የስልጣን ዘመኑን ለማርዘም እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡
በጣም የገረመኝ ደግሞ እኮ አሜሪካና እንግሊዝ ካወጡት ህግ በተሻለ መቀመጥ የሚችል ህግ ነው፥ ብሎ የወያኔ ካድሬ ሲናገሩ ሳይ እንዴ እነዚህ ሰዎች የውነት ከልባቸው ነው? ግን ምን አለበት ትንሽ እንኩዋን ቢያፍሩ እንደው አንዱ እንኩዋን ከመሃላቸው “አረ በህግ“ የሚል የለም? የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያነሱትን ሃሳብ አንዳንዴ እንኩዋን አይ ይሄንን እንኩዋን ልክ ናችሁ ብሎ ማለት ምን አለበት ቢችሉ?
በ 1997 ዓም የተከሰተው የምርጫ ነገር ቢያስደነግጣቸው ከዛ በሁዋላ የትም ቦታ የሚደራጅን እና በህዝብ ተቀባይነትን ያገኘ ተቃዋሚ ፓርቲን ማቀጨጭ እና በታትኖ ማጥፋት ዋና አላማው አድርጎታል:: በህገ መንግስት የበላይነት አመካኝቶ አዋጁን በማውጣት በህግ በመጠቀም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመግፈፍ ለራሱ ህልውና ስልጣኑን ለማቆየት እየተጠቀመበት ይገኛል::
እንግዲህ ይህ ግልጽ ነው እንኩዋን አንድ ሃገር ለማስተዳደር የተቀመጠ መንግስት እና ማንም ሰው ሊረዳው እና ሊገባው በሚችል መንገድ ሃሳባቸውን ቢያቀርቡም “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም“ እንዲሉ ጉንጭን ከማልፋት ውጭ እርባና ቢስ ሆንዋል፡፡
ለዚህም ይመስለኛል ይህንን የተረዱት እንደ ግንቦት ሰባት ያሉት እና ሌሎች ጥቂት ፓርቲዎች ከሰላማዊ ትግል ይልቅ ወደ ሃይል እርምጃ የተሸጋገሩት በመነጋገር መፍትሄ ከማይፈልግ የማፍያ መንግስት ጋር ስለ ሰላማዊ የህዝብ ምርጫና ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መንገር አጉል ጉንጭ ማልፋት ነው ስለዚህ እኔ በበኩሌ ከቃላት ካልዘለለ ክርክር ወተን ሃይላችንን አጠናክረን ወደ ትጥቅ ትግሉ መግባት የመጨረሻ መፍትሄ መሆኑን እናገራለሁ እኔም ተሳታፊ ነኝ፡፡

የመቀለ ወጣቶች ከህወሓት መሪዎች ጋር ተጋጩ

የመቀለ ወጣቶች ከህወሓት መሪዎች ጋር ተጋጩ
———————————————–

ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 24, 2006 ዓም በኮብልስቶን ስራ የተሰማሩ (ና ለመሰማራት በማህበራት የተደራጁ) የመቀለ ወጣቶች በመቀለ ከተማ ማዘጋጃቤት አዳራሽ ተሰብስበው ነበር። የተሰበሰቡበት ምክንያት በጨረታ የተወዳደሩበት የኮብልስቶን ግንባታ መሰረዙ ሊነገራቸው ተብሎ ነበር።

ባለፈው ዓመት በኮብልስቶን ስራ የተሰማሩ ወጣቶች አብዛኞቹ መክሰራቸው ይታወሳል። የከሰሩበት ምክንያት ደግሞ ለኮብልስቶን ስራ ተብሎ ከዓለም ባንክ የተከኘ ገንዘብ በሐላፊዎች አለ አግባብ መመዝበሩ ነበር። የኮብልስቶን ገንዘብ የሰረቁ ባለስልጣናት መታሰራቸው ይታወሳል።

አሁን በወጣው ጨረታ መሰረት ግን ለስርቅ የሚሆን የሚተርፍ የኮብልስቶን ገንዘብ አይኖርም። በዚህ ምክንያት የህወሓት መሪዎች ጨረታው ለመሰረዝና ሌላ አዲስ ጨረታ ለመክፈት ወስነዋል። ወጣቶቹም የህወሓት መሪዎች የወሰዱት እርምጃ ክፉኛ ተቃውሞውታል። ወጣቶቹ ለጠየቁት ጥያቄ ተገቢ መልስ ባለመግኘታቸው ስብሰባው ረግጠው ወጥተዋል። የአደራሹ በር በመዝጋት ስብሰባው ረግጠው እንዳይወጡ ጥረት የተደረገ ቢሆንም አልተሳካም።

ወጣቶቹ ነገ ጠዋት (ዓርብ) ወደ ክልል ቢሮ ተሰባስበው ይሄዳሉ። የክልል መንግስት መፍትሔ ካልሰጣቸው የተቃውሞ ሰልፍ እስከማድረግ ይደርሳሉ።

ይህ የኮብልስቶን ጉዳይ ባብዛኞቹ የትግራይ ክልል ከተሞች ትልቅ አጀንዳ ሁኗል።

(ኮብልስቶንም … ንትርክ በዛባት)

It is so!!!1074891_501448586602754_1044490877_o

በጀግኖች አባቶቻችን ና እናቶቻችን ደም ተከብራ የኖርች አገር በክሃዲዎች አትደፈርም።

New Picture
ወቅታዊ የአገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ(ኢህአግዘ) የተሰጠ መግለጫ
በጀግኖች አባቶቻችን ና እናቶቻችን ደም ተከብራ የኖርች አገር በክሃዲዎች አትደፈርም። ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላላት ክብር እና ማንነት ጀግኖች አባቶቻችን በከሰከሱት አጥንት እና ባፈሰሱት ደም ነው።
ለጠላት የማይንበረከከው እና ማንንም የማይፈራው የኢትዮጵያ ጀግና ከፋሺስት ኢጣልያ ጋርም ቢሆን አንገት ለአንገት ተናንቀው በጦር በጎራዴ ይችን ሃገር ባላት ቅርጽና ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ አቆይተዋታል። አሁን ግን የደም መስዋእትነት የተከፈለበትን ይህንን መሬት ሃገር እናስተዳድራለን ባሉ ወረበሎች ስትበጣጠስ እና ስትቆራረስ ማየት ያማል።
ይቺ ሀገር ባንዲራዋ በየ ዳር ድንበሩ የተውለበለበላት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ባንዲራዋን ጨርቅ ሳይሉ በደማቸውና ባጥንታቸው አጥር አጥረው ያኖርዋት ፣ ጀግኖች አትሌቶች ድል አድርገው ላባቸውን እና እንባቸውን እያወረዱ ባንዲራውን ከፍ አርገው የሚያስከብርዋት ፣ ሃገር ማለት ባልታወቀ ሰንሰለት ከልብ ጋር የታሰረ የማትተው፣ የማትሰለች ፣ ካንቺ በፊት እኔን ያርገኝ የተባለላት ፣ በፍቅርዋ ተነደፈው ስንቱ በብእራቸው የተቀኙላት፣ በድምጻቸውም የፎከሩላት ፣ ሰአሊው በቡርሹ ቀባበቶ ያሳመራትን ሃገር የወያኔ ወረበላ ቡድን ኤርትራን አስገንጥሎ ለሻብያ መስጠቱ ሳያንሰው ዛሬ ደሞ ሌላ ጉድ ስንሰማ እውነት ሃገር እንዲህ በሽፍታ መንግስት እንዲህ መበጣጠስዋ ቢያቆስለን ድምጻችንን ለማሰማት ተነሳን።
በ 1881 ዓ/ም ሚኒሊክ ድንበሬ ይሄ ነው ብለው ለአለም መንግስታት ከበተኑ በሁዋላ ሌላ ምንም አይነት ህጋዊ ውል ያልተፈረም ሲሆን ባሁኑ ሰአት ግን ለሱዳን የወያኔ ወረበላ ቡድን ከመተማ እስከ ጋምቤላ ጠረፍ ድረስ ከ1 ሺ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ቁመትና ከ40-50 ኪሎ ሜትር ጎን በላይ ያለዉን ሰፊ ታሪካዊ ለም መሬት አሳልፎ በመስጠት ላይ እንዳለ ይታወቃል። ሥለዚህ ወገኔ ወያኔ ዳር ደንበር የማካለልም ሆነ የየመሸጥ ሞራልም ብቃትም የለውም» እኛ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ዘብ ከምንታገለበት ጉዳይ ዋናው የሃገራችንን ዳር ድንበር አንዲት ክንድ እንኩዋን ለሌላ ቆርሶ እና አሳልፎ ላለመስጠት ነው። ይህ ለሱዳን ሊሰጥ የታሰበው መሬት ማለትም ከ 1901 እስከ 1904 የተሰመረው /Gjuhen/ የሻለቃ ጉሄን መስመር ሲሆን ይህንን መስመር በኢትዮጵያ በኩል ማንም ያልተስማማበት እና እውቅና ያላገኘ ነው። ነገር ግን መሰሪው የወያኔ መንግስት ህዝቡ ሳያውቅ ውስጥ ውስጡን ስራውን እየሰራ ደሃው ገበሬ በሃገሩ መሬት ሲያርስ ሰው ድንበር ገብተህ ተብሎ በሱዳን ወታደር መከራውን እያየ ነው። የደሃው ለም መሬት ከመነጠቅ አልፎ ሰፊው የደን እርሻችን እንዲሁም ብርቅየ የዱር አራዊቱ ሁሉ ሳይቀር ለሱዳን ቆርሰው እየሰጡ ይገኛሉ። ሟቹ የወያኔ ወረበላ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው መለስ ዜናዊ ኤርትራን ለሻዕብያ አሳልፎ ለመስጠት በአለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በ 1983 ዓም ሃገሬን ቆርሳችሁ ለሌላ ስጡልኝ በማለት ለተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ በመጻፍ እንዲሁም በሃሰት ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት በማለት ህዝቡ ሳይጠየቅ ሬፈረንደም እንዲደረግ በማድረግ ህዝብን
ከህዝብ ወገንን ከወገን አለያይቶ እንዲሁም ሃገራችንን ያለ ባህር በር እንዲቀር አደረገ። ከዛም በሁዋላ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ተነካ ቢባል ከ 80 ሺህ ህዝብ በላይ በባድሜ ጦርነት አለቀ። በአሁኑ ሰአት ደሞ የባሰ ብለው ይህንን መሬት ማለትም ከመተማ እስከ ጋምቤላ ከ1 ሺ 600 ኪሎ ሜትር በላይ ቁመትና ከ40-50 ኪሎ ሜትር ወደውስጥ ለሱዳን ለመስጠት መደራደር ይህ ወሮበላ ሃገር ሻጭ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን ህብረተሰቡ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን። መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች :- ይህ የወረበሎች ጥርቅም በሳዓውዲ አርብያ ወገይኖቻችን ሲታርዱ አያገባኝም ያለ የጠላት ቅጥርኛ በመሆኑ ባለን አቅም እና ሃይል ተባብረን ከስሩ ነቅለን በፍጥነት ካልጣልን ህዝብን ከህዝብ አባልቶ ድንበርዋን ለጠላት ሸጦ እንዲሁም ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር እንዳትኖር በታትኖና ቆራርሶ የባሰ ችግር ወደ ማመጣት እንደሚሄድ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሀገር ፍቅር ፣ አንድነት ፣ ባንዲራ ፣ ጀግንነት እና የሀገር ታሪክ ለወያኔ ስርአት ከተረት ያላለፈ ነገር ቢሆንም እኛ የኢትዮጵያ ልጆች ግን ህመምዋ የሚያመን ጩኧትዋ የሚሰማን የድሃው ህዝብ መፈናቀል መገፋት እና ከቅየው መባረር እንቅልፍ የሚነሳን በየበርሃውና በየስደት አለም ገብቶ ያለ ሃገር እና ያለ ወገን የቀረው ንጹሁ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶት እረፍት የሚነሳን ነገር በመሆኑ ይህንንም ነገር በጽኑ በመቃወም ለለውጥ የምናደርገውን ትግል በባሰ እልህ እና ቁጭት እንደሆነ ማሳወቅ እንፈልጋለን። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሆኖ ይህንን ከፋፋይ መንግስት ለመጣል ባንድነት እንነሳ ስንል የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ዘብ ጥሪውን ያቀርባል ። ”ከጀግኖች አባቶቻችን የተረከብነውን አደራ በትግላችን እናስከብራለን!!!” የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ ሁሉም ለናት አገሩ ዘብ ይቁም።
ታህሳስ 24 2006 ዓም

በደቡብ ክልል የይርጋ ጨፌ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ

በደቡብ ክልል የይርጋ ጨፌ መምህራን የስራ ማቆም አድማ አደረጉ
ታህሳስ ፳፫( ሃያ ሦስት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መምህራኑ አድማውን የጀመሩት ያለፍላጎታችን ለአባይ ግድብ ማሰሪያ ደሞዛችን እየተቆረጠብን ነው በሚል ነው። መምህራኑ ለይርጋ ጨፌ ከተማ አስተዳደር፣ ለጌዲዮ ዞንና ልክልሉ ትምህርት ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ” ከ ሀምሌ 2005 ዓም ጀምሮ ለህዳሴ ግድብ የሚቆረጠው ገንዘባችን እኛ ያለፈቀድነውና ያልተስማማንበት በመሆኑ ጥቅምት 28፣ 2006 ጀምሮ ስራችንን በአግባቡ እየሰራን የመብት ጥያቄያችንን ለሚመለከተው ሁሉ ስናቀርብ በመቆየታችን ታህሳስ አንድ በዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢነት የከተማው ከንቲባ ፣ የከተማው ትምህርት ዩኒት ሃላፊ በተገኙበት አቆራረጡ አግባብነት የሌለውና የመምህራንን መብት የጣሰ መሆኑን በውይይቱ ተረጋግጦ ከታህሳስ ጀምሮ የሚቆረጠው ገንዘብ እንዲቆም፣ መወሰኑን” አስታውሷል። ድብዳቤው “ነገር ግን የከተማው አመራር እንደተለመደው በመዋሸት እንዲቆም የተወሰነው ገንዘባችን እንዲቆረጥብን አድርጓል” ይላል።
ድብዳቤው አያይዞም ” የታህሳስ ወር የተቆረጠበን ተስተካክሎ እንዲከፈለን፣ ከሀምሌ 30 ፣ 2005 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ 5 ወራት የተቆረጠብን ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲመለስልን፣ ከዚህ ቀደምም ያለፈቃዳችን እየተቆረጠብን ያለው የኢች አይ ቪ መዋጮ እንዲቆም እየጠየቅን ከዛሬ ማለትም ከታህሳስ 22 ቀን 2006 ዓም ጀምሮ ስራ ማቆማችንን እንገልጻለን፤ የታህሳስ ወር የሚመለስልን ከሆነ ግን ወደ ስራ ገበታችን ተመልሰን እየሰራን ከዚህ ቀደም የተቆረጠውን የ5 ወር ገንዘባችንን ደግሞ እስከ ታህሳስ 25 2006ዓም በትእግስት የምንጠብቅ ሲሆን ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን አሁንም ስራችንን ለማቆም የምንገደድ እና ለሚመለከተው የበላይ አካል የምንሄድ መሆናችንን ከወዲሁ እናሳውቃለን” ብሎአል። በትምህርት ቤቱም ይሁን ከትምህርት ቤት ውጭ ለሚፈጠሩ ችግሮች መምህራኑ ተጠያቂዎች ያለመሆናቸውን ገልጸዋል።
ደብዳቤውን ተከትሎ መምህራኑ ያስራ ማቆም አድማውን ተማሪዎችን በማሰናበት መጀመራቸውን ተከትሎ መስተዳድሩ ዛሬ የታህሳስን ወር ለመክፈል መገደዱን ዘግይቶ የደረሰን ዜና ያመለክታል።
በደቡብ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን ያለፈቃዳቸው የሚቆረጥባቸውን ገንዘብ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

በህወሀት ውስጥ የሚገኙ አክራሪ የሚባሉት ቡድኖች የመከላከያ አዛዥነቱ ከህወሀት እንዳይወጣ ለማድረግ ሲጥሩ መክረማቸው ተሰማ

በህወሀት ውስጥ የሚገኙ አክራሪ የሚባሉት ቡድኖች የመከላከያ አዛዥነቱ ከህወሀት እንዳይወጣ ለማድረግ ሲጥሩ መክረማቸው ተሰማ
ታህሳስ ፳፬( ሃያ አራት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በመከላከያ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ አዛዦች ለኢሳት እንደገለጹት የህወሀት ባለስልጣናት ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ለመተካት የተሻለ ቦታ ላይ የነበሩትን ጄ/ል አበባው ታደሰን አድማ ለማድረግ አስበዋል በሚል ሰበብ ማእረጋቸውን እንደያዙ የሚሰጣቸው ሃላፊነት እንዲቀነስና ከውድድር ውጭ እንዲሆኑ አድርገዋል። ለዚህም ስራ ጄኔራል ማሞ ሀይለማርያም እና ጄኔራል ሰሐረ መኮንን ተባባሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሶስቱ ጄኔራሎች “ጄኔራል ሳሞራ የኑስ በመከላከያ ውስጥ ያለውን ሙስና ለመከላከል ብቃቱ ጎሏቸዋል በሚል እንደተነጋገሩና ጉዳዩ በወታደራዊ ደህንነት መምሪያ ክፍል ሲታይ ቆይቶ በመጨረሻም ይፋ ተደርጎ” ሶስቱም ጄኔራሎች በያዙት ማእረግ ሃለፊነታቸው ቀንሶ እንዲሰሩ ተወስኖባቸዋል። ይሁን እንጅ ጄ/ል ሞላ እና ጄ/ል ሳህረ ከጄኔራል አበባው ጋር በአድማው የተሳተፉት ሆን ተብሎ ጄ/ሉን ከስልጣን ተፎካካሪነት ለማስወጣትና ፍትሀዊ ውሳኔ የተላለፈ መሆኑን ለተቀሩት የሰራዊቱ አባላት ለማሳየት መሆኑን ወታደራዊ ምንጮች ገልጸዋል።
ጄ/ል ሳሞራን ይተካሉ ተብለው የሚታሰቡት በቅርቡ የሌ/ጄ ማእረግ ያገኙት ጄ/ል ዮሃንስ ገብረመስቀል ናቸው። የተለያዩ ወታደራዊ አዛዦችን በማነጋገር ስለነበረው ሙሉ ድራማ ከዜናው በሁዋላ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን።

የፕሬስ ነጻነት አስከፊ ከሆነባቸው 10 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት ተባለች

የፕሬስ ነጻነት አስከፊ ከሆነባቸው 10 አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት ተባለች

ሲፒጄ የፕሬስ ነጻነት አደጋ ውስጥ የወደቀባቸው 10 የአለም አገራት በማለት በግንባር ቀደምነት ያስቀመጣቸው አገሮች ብራዚል፣ ኢኳዶር፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ራሺያ፣ ሶማሊያ ፣ ሶሪያ፣ ቱርክ እና ቬትናም ናቸው።’

ኢትዮጵያ የጸረ ሽብር ህግ በማውጣት ጋዜጠኞች በእስር ቤት እንዲማቅቁ ማድረጓን በዚህ ድርጊቷም ከኤርትራ በመቀጠል የሁለተኛነት ስፍራ መያዙዋ ተጠቅሷል።’

አምና 4 ጋዜጠኞች ፣ ከ2007 ጀምሮ ደግሞ በድምሩ 49 ጋዜጠኞች አገራቸውን ጥለው መሰደዳቸውን፣ ከአለም አገራት ጋር ሲተያይ አገሪቱ በሶስተኛ ደረጃ እንድትታይ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በአገር ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች የሀይለማርያም ደሳለኝ መንግስት በፕሬስ ላይ የሚታየውን አፈና ይለውጠዋል ብለው እንደማያስቡ ሲፒጄ ገልጿል።