Archive | January 5, 2014

የጨቅላዎች ሁካታ !

minilik1-202x300

 

ከቴዎድሮስ ሐይሌ(tadyha@gmail.com)
ምንሊክ መጓዙን የምትጠይቁኝ፤
ፊትም አላለፈ ኋላም አይገኝ።
ካለፉት ሳምንታት ወዲህ የማንነት ቀውስ ዋግ እንደመታው አገዳ ያኮሰሳቸው የበታችነት ስነልቦናቸውን ታሪክ በማፍረስና ጀግኖችን በመዝለፍ የሚጠገን የመሰላቸው አንዳንድ ተማርን ነን ባይ ደካሞች ዛሬን በድቅድቅ የባርነት ጨለማ አሳራቸውን እያዩ ፤ በራሳቸው ላይ የተጫነውን የአገዛዝ የጭቆና ቀንበር ለማንሳት ብርቱ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ወደኋላ ተጉዘው የነጻነትን ብርሃን ፤ የዘመናዊነትን ጎዳና፤ የአንድነትን መሠረት ከወረሪና ከተስፋፊ ቅኝ ገዠ አውሮፓውያን በብርቱ ታግለው የክብርን አክሊል፤ የኩራትን መንፈስ ያወረሱንን ደጋጎቹን አባቶች የሚያንጓጥጥ ከስደት ፤ ከረሃብና ፤ ከውርደት በዚህ ዘመን እንኳ ለራሱ መቀዳጀት ያልቻለ ደካማና ልፍስፍስ ህብረተሰብ ጀግኖች አባቶቻችንን ለመዝለፍ ሲንጠራራ ይበልጥ እየተዋረደ መሆኑን እንኳ አለመረዳቱ የሚያሳዝን ከመሆን አልፎ የዛችን ታላቅ ሃገር ኢትዮጽያዊ ዜጋ መጻዊ ሕላዌ ፈተና የሚደቅን በሌሎች ሃገሮች የታየው አይነት የእርስ በእርስ መተላለቅን የሚጋብዝ አደገኛ አካሄድ የጥቂት ጨቅላዎች ሁካታ ነው በሚል ልናልፈው ብንሞክርም እንኳ የዚህ የጥፋትና የጥላቻ ግብረሃይል ሃገሪቷን በሚመራው ወገን የጀርባ ድጋፍ ያለው በመሆኑ አሁን ባለው የጽንፈኝነት መንገድ ከቀጠለ የሚያስከትለው አደጋ ቀላል ባለመሆኑ በነዚህ ጨለምተኞች ዙሪያ ወገንን የማንቃት እንቅስቃሴ እንዲያግዝ ሁሉም የበኩሉን ማለት ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ ።
ውሃን ድንጋይ ያናግረዋል አበው እንዲሉ በአሮጌ የታሪክ ቡልኮ ተጀቡነው ዘመኑን መዋጀት ያልቻሉት በትላንትና የቅናትና ጥላቻ ችንካር ላይ ተቀርቅረው ዘመን ተቀባብሎ የለወጠውን በሃውርታዊ ውህድ ህብረተሰብ ለመበታተን በተጋነነና ሁን ተብሎ በተፈበረከ የጥላቻ ድርሰት ታውረው ለከፋፍለህ ግዛው ፋሽስታዊ የወንበዴዎች አገዛዝ ህዝብ ስቃዩ እንዲረዝም እያደረጉ ያሉት የምሁር ደንቆሮዎች ዘመናቸውን የፈጁበት የጥላቻ ጉዞ ጡረታም ሲወጡ ሊተዋቸው አለመቻሉ እጅግ የሚያሳዝን ከመሆኑም በላይ የግማሽ ክፍለ ዘመን የከሸፈና የዘቀጠ አስተሳሰባቸውን ለትውልድ ለማውረስ የተጀመረው መቃብር የመቆፈር ፖለቲካ አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ ትርምስ የመፍጠር አላማ ያነገበ በመሆኑ አጀንዳቸው ውሃ የማይቋጥርና ፤ ለጆሮ የሚቆረፍድ ቢሆንም ልካቸውን እንዲያውቁና አደብ እንዲገዙ ለማድረግ እውነቱን ይነገራቸው ዘንድ ስልጡን በሆነ መንገድ መንገሩ ተገቢ ነው።
ታላቁን ገናናውንና በጥቁር ሕዝብ ዘንድ የነጻነት ጮራ ፈንጣቂ ሞራሉ ለተሰበረው ውርደት
እንደመጎናጸፊያ ለደረበው ተስፋው ተሟጦ በባርነት እንደ እንስሳ እየተረገጠ መኖርን ህይወቱ አድርጎ
አያሌ ዘመናትን ለተሻገረው ድፍን የአፍሪካ ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት በመሆን የአባቶቹን ታሪክ የደገመው
ጀግናው የጣሊያን ጌታ የንጉሶች ንጉስ (King of Kings) የሆነው እምዬ ምንሊክ በማንም ወፍ ዘራሽ
መደዴ የባንዳ ልጆችና የማንነት ቀውስ ባኮሰሰው ታሪክ በራዠ እንደ ጥጃ መለመላውን ከመሄድ ሱሪ
እንኳ ያጠለቀለትን ጥቁሩን አንበሳ ሲሰድብ ዉሎ ሲሰድብ ቢያድር ሀውልት ቢያቆም ድርሳናት ቢጠረዝ
አንዲት ጋት ያህል ክብሩን ሊቀንስ የማይችል በመሆኑ በዚህ የክፋት አቦከብሬ የጫጫታ ተግባር
ለተጠመዳችሁ መድረሻቸው ሃፍረት ነው።
የገናናውን ታላቅ የጥቁር ሕዝቦች ንጉስ የእምዬ ሚኒሊክ መቶኛ አመት እና የታላቁ አፍረካዊ
የነጻነት ታጋይ የማንዴላ እረፍት መገጣጠም ያጫራቸው የሃሳብ ንትርኮች ውስጥ በራሳችን ሃገር ዜጎች
ምኒልክን በማሰነስ ማንዴላን የማወደስ ስራ የተጠመዱ የእንግዴ ልጆች የዘነጉት ወጣቱ የጥበብ ሰው
(እድሜውን ያርዝምልን በጥበብና በማስተዋል አምላክ ያቆይልን) ጥቁር ሰው በሚለው የሙዚቃ አልበሙ
ያሰፈረውን ታላቅ አባባል ልዋስና ‘’ የፊቱ ከሌለ የለም የኋላው ‘’ እንዳለው የማዴላን የትግል መንፈስ
ያጠነከረው ሞራሉን የገራው ጥቁር የነጭ አሽከር ነው የሚለውን ዘመናት የተሻገረውን ክፉ መንፈስ
እንዲሰበር የረዳው ነጭም ጥቁርም እኩል በአርአያ እግዚያብሄር የተፈጠረ እኩልነትና ነጻነት የመቀዳጀት
መብት ያለው ሰብዓዊ ፍጡር መሆኑን ከማን ተማረ ፈር ቀዳጁስ ማን ሆነና ! ለመሆኑ ከጥቁር የአፍሪካ
አሃጉር ከኢትዮጽያ በስተቀር ማነው ነጻ የነበረው ከመላው የእስያ የአፍሪካና የካሪቢያን ሃገራት ውስጥ
የትኛው መሪ ነው የአውሮፓን ቅኝ ገዠ ወራሪ ሃይል አሸንፎ ያንበረከከው ከምኒሊክ ሌላ ማን የሚጠቀሰ
አለ ነው፤ ለዚህ ነው ሚኒሊክ የኢትዮጽያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ፋና ወጊ ነው
የሚያስብለው ። የማንዴላ ብርታት ፤ የነማርቲን ሉተር ኪንግ ሞራል ፤ የነማርኮስ ጋርቪ ፤ የነጆሞኬንያታ
፤ የነነኩሩሃማ በጭቆናው ዘመን ለነበሩት ተራማጆችና ፓን አፍሪካኒስቶች የትግል መነሻ የሞራላቸው
መዳረሻ አድዋ ላይ የተገኘው አኩሪ ድል እኮ ነው። ይህ ዛሬ ባሪያ ነበርን ተረገጥን ጡታችን ተቆረጠ ፤
ሱሪያችን ወለቀ ፤ ተዋርደን ነበር ወዘተ የሚሉት መቃብር ቆፋሪ የድኩማን ግሪሳዎች የራሳቸው አልበቃ
ብሎ ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ የቆረፈደ አሮጌ የተረት ቡልኮ ለመጨመር መመኮራቸው ሃገር ወዳዶች
ተረድተው ይህን ሴራ የፖለቲካና የዘር ልዩነት ሳንል ማክሸፍ ካልተቻለ ሊፈጥረው የሚችለው አደጋ ቀላል
አለመሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል ።
እነዚህ የመቶ አመት ሂሳብ ለማወራረድ በቧልት የተሞላ የታሪክ አዛባ የሚዝቁት ጥቂት
የትላንት እስረኞች የዛሬም ተጨቋኞች ስለህብረተሰብ ጥንቅር ስለ ስነመንግስትና በአለም ውስጥ ያሉ
ሃገራት በምን አይነት መንገድ የዛሬውን ቅርጽ ይዘው እንደወጡ ሊያውቁ የሚችሉበት የእውቀት አድማስ
እንኳን ለምሁራን ለተራው ዜጋም ሊጠፋ የማይችል እውነት ሆኖ እያለ ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት
በተዛባ መልኩ እየተረኩ ያለው አደገኛ ተረት ውሎ አድሮ እንወክለዋለን የሚሉትን ወገን አንገት
የሚያስደፋና የማያኮራ የማይጠቅም በመሆኑ ከድርጊታቸው ቢታቀቡ መልካም ነው ። የአሁኒቷ አለም
ሃገራት ከሞላ ጎደል አሁን የያዙትን ቅርጽ ይዘው እንዲገኙ ያደረጋቸው በጦርነትና በወረራ በተደረገ ደም
አፋሳሽ በሆነ ወታደራዊ ንቅናቄ የመሆኑ እውነት በታሪክ የታወቀ ነው። በኢትዮጽያም የሆነው ይህው
ነው። የኢትዮጽያ ደግሞ ከሌሎቹም በተለየ መልኩ የግዛት ወሰኗ ሰፊውን የአፍሪካን ቀንድ ያካለለ
እንደነበር አያሌ የታሪክ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ኢትዮጽያ የግዛት ወሰኗን አስከብራና ነጻነቷን
ጠብቃ ከመኖሯም በላይ ፍትህ የተጓደለባቸውን ህዝቦች ቀይ ባህር ተሻግራ የአሁኒቷ የመን ሃገረ ናግራን
የሚኖሩ ወገኖችን ለመታደገ በአፄ ካሌብ ዘመን የተደረገው የድል ዘመቻ ኢትዮጽያ የአካባቢው ግዛቶች
ባለቤት ከመሆኗም በላይ በአካባቢው ጂኦ ፖለቲካ ላይ የበላይነት የነበራት ሃያል ሃገር እንደነበረች ከታሪክ
የሚረዳ ወገን አጼ ሚኒሊክ ከሰሜን ወደ ደቡብ ያደረጉት እንቅስቃሴ የቀደምት የአባቶቻቸውን የወሰን
ግዛት የማስከበርን ታሪካዊ ሃላፊነት መወጣት እንጂ የዛሬዎቹ የፋሽስትና የባንዳ ርዝራዦችና ነጭ አምላኪ የታሪክ አተላዎች እንደሚቀባጥሩት የሚኒሊክ የደቡብ ወታደራዊ ንቅናቄ ወረራና ሌላ ሃገር ላይ የተደረገ ዘመቻ አለመሆኑን በብዙ ማስረጃ አቅርቦ ለመከራከር አዳጋች ባይሆንም የተጀመረው የጥላቻ ዘመቻ ኢትዮጽያዊነትን የካደ ስልጡን ውይይት የማያስተናግድ በጠባብነት የተመራ ጨለምተኝነት የነገሰበት በመሆኑ ሂደቱን በጥንቃቄ መከታተል ተገቢ ይመስለኛል።
የዛሬዎቹ የማንነት ቀውስ የደፈጠጣቸው በበታችነት የስነልቦና ደዌ የተጠቁት የምናባዊቷ ኦሮሚያ ደቀመዛሙርት በወያኔው የጥላቻና የተንኮል ታሪክ ጸሃፊ ተስፋዬ ገብረዓብ በተባለ ሃሳዊ ተፈብርኮና ተደርሶ የተሰጣቸውን የውርደት መድብል ታሪክ ብለው ትውልዱን በማደናገርና በቂም በቀል ተነስቶ እርስ በእርስ እንዲተላለቅ የጀመሩት ዘመቻ አስተዋዩ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪኩንና ማንነቱን በቅጡ የሚያውቅ በመሆኑ በከሰሩ ኦነጎችና በተንበርካኪ የወያኔ ሎሌዎች የተጀመረው ሃገር አፍራሽ ዘመቻ ባለመተባበር እንደሚያከሽፈው የሚያጠራጥር ባይሆንም ይህን የባርነት መንፈስ የተጫናቸውን ታሪክ አርካሽ አልጫ ስብስብ ወደ ቀልቡ እንዲመለስ ለማስገንዘብ ጥቂተ ማለቱ ተገቢ ሲሆን ከዛ ባለፈ በወያኔ ምርኮኛ የደርግ አስር አለቆች የሚመራው ድኩማኑን የህወሃት አገልጋይ ኦህዴድ ሆነ ከ50 አመታት በላይ የአንድ ትውልድ እድሜ ያስቆጠረው ጡረተኛው የኦነግ ቡድን በአንድ ቀን ጀንበር መቶ ሃያ ሺ ጦሩን ያስማረከ ልፍስፍስና የተበታተነ የምሁር ሃይል በሚኒሊክ መቃብር ላይ ጡረታውን ላማስከበር የጀመረውን የጅል የወሬ ዘመቻ ፍጻሜው ከመሳቂያነት የማያልፍ በመሆኑ አጀንዳው ሳይንዛዛ በአጭር ዘግቶ የዚህን እኩይ ሴራ ቀማሪ በሆነው የወያኔን አገዛዝ ወደ ማስወገድ ትኩረታችንን ማድረጉ ላይ ሁሉንም ወገን ግንዛቤ ሊጨብጥ ይገባል።
ወገኖቼ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነጻ ከወጡ የአንደ ትውልድ ዘመን እንኳ ያልሞላቸው ሃገራት በአስተዳደር በኢኮኖሚና በስልጣኔ በልጠውን እኛ ግን ቢያንስ ሃሰባችንን እንኳ በነጻነት መግለጽ የማንችልበት ረሀብተኛ ስደተኛና በሃገሩም እስረኛ በሆንበት የውርደትና የጉስቁልና መቀመቅ ውስጥ መከራራችንን እያየን ያለን ህዝብ ሆነን ክብርን ኩራትን ሰው የመሆንን ጸጋ ትተውልን ያለፉትን አባቶች መልካም ስራቸውን አንግበን መጥፎ ስራቸውን ለታሪክ ትተን ከወደቅንበት ለመነሳት እጅ ለእጅ ተያይዘን መቆም ሲገባን በዘርና በጎጥ ተቧድኖ የእንካሰላምታ ግብግብ መግጠማችን ክብር የተውልንን አባቶች መስደብ ምን የሚባል ፖለቲካ ነው! ፋይዳውስ ምንድን ነው? ዛሬ በዚህ ዘመን ምን የተቀዳጀንው ነገር አለና ነው? ያሳዝናል በዓለም ቁጥር አንድ ከሆነ በምጽዋት ህይወቱን ከሚገፋ ህብረተሰብ የማይጠበቅ እንደ ህዝብ አሳፋሪ የታሪክ ጠርዝ ላይ ቆመናል። አፄ ሚሊክን በምንም አይነት ልሳን ብንሰድብ የጥቁር ሕዝብ ንጉስ የመሆናቸውን እውነት የአውሮፓ ሃያላንን የማንበርከኩን ሃቅ ማንም ቅናትና የበታችነት ስነልቦና የተጫናቸው እንጭጮች ጫጫታ ሊፍቀው አይችልም። ሃይለስላሴን ለማዋረድ የተነሳው ትውልድ ራሱ ተዋርዶ እርስ በእርስ ተባልቶ ማለቁን አይተናል። የተረፈውም ያራገበው አብዮት ተቀልብሶና ተሸንፎ በቁሙ በውርደትና በእስር ማቆ አይቶታል። ሃይለስላሴ ግን ከማክበርም አልፎ የሚያመልካቸው የጥቁር ሕዝብ እንዳይኖር ከቶስ ማድረግ የሚችለው ማነው? በዋልጌ ዜጋው የተዋረደው የሃይለስላሴ አጥንት እንደ አማልክት እንዲከብር ራስ ተፈሪያውያንና የካሪቢያንና የአፍሪካ ሕዝቦች ልብ ውስጥ የኩራት ሃውልቱን አኑሮ ይኖራል። በዘረኞችና በበታችነት ስነልቦና እስረኞች ንጉሰ ነገስት ሃይለስላሴ ብርቱ ጥረትና ትግል ለመመስረት የበቃው የአፍሪካ ህብረት የዚህን የአፍሪካ ኩራትና ሃዋርያ በገዛ ሃገሩ ሃውልቱ እንዳይቆም ቢደረግም ውለታቸውን ባልዘነጉ መላው ጥቁር ሕዝቦች የማይዘነጋ አሻራ ከማኖሩም በላይ በናይሮቢ ኬንያ በስሙ ጎዳና ተሰይሞ (Haile Selassie Avenue) ስሙ እንዳይጠራ ማስቀረት የሚችለው ማን ነው?።
የሻብያ ፍጥረት የወያኔ አሽከር የሆኑት አንዳንድ በአሮሞ ስም የሚነግዱት ተንበርካኪ የእንግዴ ልጆች ሳይወለድ የሞተው ሊሳካም ከቶም የማይችለው ተምኔታዊው የጽንፈኞቹ የህልም አለም ምናባዊቷ
የኦሮሚያ ሉዓላዊነት እንደለመዱት በአሶሳ በወተር በአርባጉጉ በአሰቦት ሰውበላው ድርጅታቸው ኦነግ አሮጊቶችና ሴቶች ላይ የፈጸመውን የጭካኔ ተግባር እንደግመዋለን የሚለው የሜንጫ ፉከራቸው በዚህ ዘመን ለመድገም መሞከሩ ሊያስከትል የሚችለው ዋጋ ቀላል አለመሆኑን የሚረዱት ይመስለኛል ። ከዛ ባለፈ መቶ አመት ወደ ኋላ ተጉዘው የጀመሩት ተረትና እያቆሙ ያለው የተንኮል ሃውልት የሚኒሊክን ስም የሚያጎድፍ ከመሰላቸው በጣም ተሳስተዋል። ንጉስ ሚኒሊክ ጠላቱም የመሰከረለት ጀግናና ለአሸነፋቸው ምህረትን ማድረግ ልምዱ ያደረገ ለመሆኑ ለተሸናፊው ንጉስ ጦና እና ለምርኮኛው የፋሽስት ጣሊያን ጀነራሎች ያሳየው ምህረትና ደግነት ዓለም የመሰከረለት በመሆኑ ሚኒሊክን ለማሳነስ ጡት ቆረጣ የከተቱት ኦነጎች የዘነጉት ያለና የነበረ አጉል ባህልና ታሪካቸው እና ያፈሰሱት ደም ያልደረቀ በብዙ ማስረጃ የተደገፈ መረጃ ያለ በመሆኑ አጀንዳው ወደእናንተ ተመልሶ ክስም ሆነ ክርክር ለመክፈት ከበቂ በላይ በመሆኑ ባለፈ ጉዳይ መነታረኩ ሊጠቅማችሁ እንደማይችል ወገናዊ ምክሬንም ልገልጽ እወዳለሁ።
ታሪክ እንምዘዝ ከተባለም አይጠቅምም እንጂ ብዙ ነገሮች ማንሳት ይቻላል። እዚህ ላይ ከመቶ አመት በፊት በነበረው የአመለካከት ኋላ ቀርነት አንጻር በዘመኑ ይካሄድ ከነበረው አስገራሚ ነገር አንደ መጽሄት ላይ ያነበብኩትን ብቻ ጠቅሼ ማለፍ እወዳለሁ ፤ የጅማው ባላባት አባ ጅፋር በአስተዳደራቸው ዘመን አምስት ባርያ (በአምስት ሰዎች) በአስራሁለት ሶሎግ ውሻ እንደለወጡ የሚነገር ታሪክ ተጽፎ አይቻለሁ። ይህ ማለት እኝህ የጅማ ባላባት ከዘመኑ ከነበረው የአስተሳሰብ ሚዛን አንጻር እንደታላቅ ወንጀል ሊቆጠርና ሊያወግዛቸው የሚሞክር የዚህ ዘመን ሊቅ ቢኖር መሣቂያ ከመሆን አያልፍም። በዚያ ዘመን ባርያ መሸጥና መለወጥ ፋሽን የነበረበት የሰው ልጅ የአመለካከት አድማሱ ያልሰፋ በነበረበት በዚያ ግዜ የተደረጉትን በዛሬ ሚዛን እንለካ ከተባለ ማለቂያ ወደሌለው ትርምስ የሚከት በመሆኑ ታሪክን ለ ታሪክነቱ መተው ይገባል። ይህን መንገድ የተከተሉት የዛሬይቱ ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ትላንት የጥቁር ሕዝቦች የቁም መቃብር የሰቆቃ ምድር እንዳልነበረች ዛሬ ያንን አሮጌ ታሪክ ወደኋላ ትተው በፍቅርና በአንድነት የዓለም መሪ የሆኑበት አቅም ገንብተዋል ። ትላንት በጥቁር ወንድሞቻችን በባርነት ሰንሰለት ታስረው የገነቡት ቤተመንግስት ታሪክ ተለውጦ በቆዳ ቀለም ይሰጥ የነበረው የመሪነት ቦታ የሃሰብ የበላይነት መሰረት ባደረገ ዘመናዊ መስፈሪያ መለካት በመቻላቸው ያ ርኩስ ታሪክ ተሽሮ ይህው ተምሳሌትነቱ ለዓለም ያንጸባረቀው የፕሬዘደንት ኦባማ ምርጫ አይተናል። ኦባማ ኦቫል ቢሮ ውስጥ ተሰቅሎ የሚታየው የጆርጅ ዋሽንግተን ፎቶ ከተሰቀለበት የቆየው ለኦባማ ነገድ ለጥቁር አፍሪካውያን የተመቸ ሆኖ አልነበረም ፤ እንዲያውም ጆርጅ ዋሽንግተንና የቀደሙት ዝነኞቹ የሜሪካ መንግስት ቀራጮች አብዛኞቹ የባሪያ አሳዳሪዎች እንደነበሩ የሃገሪቱ ታሪክ ሰነድ ውስጥ በይፋ ተቀምጦ ይገኛል። ዛሬ ዲሞክራት መሆን የመሰልጠን ምልክት የመሆኑን ያህል ከዛሬ መቶ አመት በፊት የባሪያ አሳደሪ መሆን እንደ ዘመኑ አመለካከት የጨዋነት መግለጫ ነበር። ነጻነቱን ያስከበሩለት ክብሩን የጠበቁለት የዛሬው የኔ አልጫ ትውልድ የሚዘለፉት የፖለቲካ ጨቅላዎች የሚያውካኩባቸው የትላንት መሪዎቻችን ይህን አይነት ተግባር ያልነበራቸው ጀግንነትን ከሃይማኖት የተላበሱት የኢትዮጽያ ነገስታት የባሪያ ንግድን በአዎጅ ከልክለው ስለመኖራቸው ታሪክ ምስክር ነው።
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን አጀንዳ በመፈብረክ የስልጣን እድሜውን ለማርዘም የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ የተረጋገጠለትና ማናቸውንም አይነት እርምጃ በመውሰድ ለስልጣኑ ሕልውና ዘብ በመቆም ሃይማኖትን በሃይማኖት ብሄርን በብሄር በማናከስ የመጣበትን ተጽዕኖ ለማለፍ ዛሬን ብቻ በማየት ሃገር አፍራሽ በሆነ ተግባር የተጠመደው ታሪክ አርካሹ የሱዳን አሽከር የአረብ አገልጋይ የሆነው የወያኔ ማፍያ ቡድን ሰሞኑን ከጀርባ በመሆን ተላላኪዎቹን መቃብር እንደ ፍልፈል እያስቆፈረ የሚኒሊክን ዘመን አስታኮ የተጀመረው የፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተጠናክሮ የቴዲ አፍሮን የፍቅር የሙዚቃ ጉዞ ለማደናቀፍ ስፖንሰሩን ቢራ ጠማቂ ድርጅት በተጽዕኖ ስር በማዋል ጥቂት ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞችን በማነቃቃት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ወያኔዎች ያስደሰታቸው መሆኑን ከልሳኖቻቸው የሰሞኑ ዘገባ መረዳት
ይቻላል። አበው የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዲሉ ወያኔዎች ኦሮሞውን በአማራው ላይ በማነሳሳት በዳር ተመልካችነት የሰላም ግዜ ለማግኘት እያቀናበረች ያለችው ሴራ በቀጣይ ምን ሊያስከትል እንደሚችልና የሚነደው እሳት ራሷን ወያኔንም ጭምር ይዞ ሊያወድም የሚችል መሆኑን ያልተረዱት የጥላቻ መንፈስ አይናቸውን የጋረዳቸው ወያኔዎች አማራውን ለማስጠቃትና ምኒልክን ለማወረድ የተነሳውን መንጋ ጽንፈኛ በልምድ ታጅቦ ወደ እነሱ የዘርና የሃይማኖት አጀንዳውን ይዞ ወደ እነሱ ሊመለስ እንደሚችል አለማረዳታቸው ምን ያህል የወያኔን የፖለቲካ ዘገምተኛነት የሚያሳይ ነው።
የተጀመረው ጉንጭ አልፋ ፖለቲካ መሬት ከረገጠ የጥላቻው ቅስቀሳ ወደ ግጭት ካመራ የአማራው ህዝብ ላለፉት 22 አመታት ታግሶና ችሎ እንደተቀመጠው የሚፈጸምበትን ጥቃት ዝም ብሎ እንደማያየው ሊረዱት ይገባል። አማራው በታሪኩ ራሱን ሲከላከል የኖረና ሃገሩንም ከሌሎች ወንድሞቹ ኢትዮጽያውያን ጋር በጋራ እንደጠበቀ ሁሉ ዛሬ ትጥቁን ፈቷል አልተደራጀምና በቀላሉ ልናጠቃው እንችላለን በሚል መንገድ የሚቃጣበትን ጥቃት ሕልውናውን ለማስጠበቅ ማናቸውንም ዋጋ ከፍሎ በአሸናፊነት እንደሚወጣ የማያጠራጥር ቢሆንም ፤ ይህ ህዝባዊ ቁጣ ከተቀጣጠለ ለማንኛውም ኢትዮጽያዊ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር የሚተርፍ ሰደድ እሳት እንደሚያስነሳ ቅን የሆነ ዜጋ ተገንዝቦ ይህን የክፋትና እርስ በእርስ እንድንጫራረስ የተሰጠንን ርኩስ አጀንዳ በግዜ አደብ እንዲይዝ መደረግ የሚገባው ጥረት ማድረግ በሁሉም ጽንፎች ያሉ ወገኖች እርጋታ እንዲያደርጉና በተለይ ወጣት ምሁራኖች በዚህ የወንድማማቾች ፖለቲካዊ ጡዘት ለማርገብ ከስሜት ባሻገር ስልጡን የሆነ ውይይት በየማህበራዊ መድረኮች በማድረግ ሰላም ለማስፈን የሚቻለውን ማድረግ ይኖርብታል።
ኢትዮጽያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን

አቶ አያሌው ጎበዜ ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንትነታቸው ለምን ተነሱ?

 

January5/2014
ከአቡዛብር ተገኝ

ፋክት መፅሄት (በታህሳስ 2006፣ ቁጥር 26 እትሙ) የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ አያሌው ጎበዜ በምን ምክንያት ከስልጣን እንደ ተነሱ ያሰፈራቸውን መላምቶች አንብቤያለሁ፡፡ ብዙዎቹ በግምትና በይሆናል ላይ የተመሰረቱ ከመሆናቸውም በላይ ለግለሰቡ ከፕሬዝዳንትነት መነሳት በዋና ምክንያትነት ሊመደቡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ለመፃፍ መነሳቴ፡፡

አቶ አያሌው ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንትነት የተነሱበት ዋና ምክንያት ምንድነው?

ከዜናው ሀሳብ በመነሳት በአንድምታ የምንረዳው እውነታ ስላለ፣ በኢቲቪ ከቀረበው የአቶ አያሌው ዱላ የማቀበል ዜና ልጀምር፡- በኢቲቪ ዜና መሰረት አቶ አያሌው ጎበዜ ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንትነት ስልጣናቸው የተነሱት በፍቃዳቸው ነው፤ “በቃኝ፣ ዱላውን ላቀብል” ብለው፡፡ እንኳንስ ከክልል ፕሬዝዳንትነት ስልጣን ላይ ይቅርና ከተራው የሹመት ስልጣን (ለምሳሌ ምክትል ቢሮ ሀላፊ፣ ከዚያም ዝቅ ሲል “ፕሮሰስ ኦውነር”) ላይ በራሱ ፈቃድ “ልውረድ” ያለን የፖለቲካ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ “‘በቃኝ’ ካልክማ እሰዬ” ብሎ ቶሎ የመልቀቅ ልምድ የለውም፤ ኢህአዴግ እንደ ገብስ ቆሎ ሳያሽ የማውረድ ባህል የለውም፡፡ ኢህአዴግ፣ አፍ አውጥቶ “ሹሙኝ-ሹሙኝ” ያለን ወይም በጣም “በሚያስበላ” ሁኔታ እንዲሾም የቋመጠን ሰው የስልጣን መንበሩ የማያቀምሰውን ያህል፣ “ስልጣን በቃኝ” ያለን አባል፣ ተንደርድሮ አያወርድም – ለዚያውም የክልል ፕሬዝዳንት ያህልን ሰው፣ ለዚያውም አስቸኳይ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ ጠርቶ፡፡

አያሌው ጎበዜ

ስለሆነም ኢቲቪ አቶአያሌው ጎበዜ በራሳቸው ፈቃድ “የመተካካት መርሁ በ’ኔም ላይ ይተግበርልኝ” ብለው ከፕሬዝዳንትነታቸው ስለመልቀቃቸው የነገረን ዜና ታእማኒነት የሌለው፣ የተለመደ የኢህአዴግ ድራማ ለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው ማሳያ ግለሰቡ አስቸኳይ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ ከስልጣን በለለቁበት እለት፣ ሙሉ አምባሳደር ሆነው የመሾማቸው “ትንግርት” ነው፡፡ የአማራው ክልል የምክር ቤት አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ የተጠራው፣ በአቶ አያሌው የቀረበውን “የመተካካት መርሁ በ’ኔም ላይ ይተግበርልኝ” ጥያቄ አዳምጦ ካመነበት ከፕሬዝዳንትነታቸው ሊያነሳቸው፣ ካላመነበት ደግሞ ጥያቄውን ውድቅ ሊያደርግ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ጥያቄያቸውን በመሰረታዊ ሀሳብነት ተቀብሎ ከፕሬዝዳንትነታቸው የሚያነሳበትን ወቅት ግን የተወሰነ ጊዜ ሊያራዝም ይችላል፡፡

ከአምባሳደርነት ሹመታቸው የምንረዳው ግን ሁሉም ነገር ቀድሞ ያለቀ መሆኑን ነው፡፡ ግለሰቡ መነሳታቸውም፣ መሾማቸውም ያለቀ ነገር ነበር፡፡ መቼም ምክር ቤት ተብዬው የመወሰን ሙሉ ቀርቶ እንጥፍጣፊ ስልጣን እንኳን ቢኖረው፣ በአምባሳደርነት የተሾመን ግለሰብ ከፕሬዝዳንትነት ስለማውረድ፣ አለማውረድ ጉዳይ እንዲወያይ ባልተደረገ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር አቶ አያሌ ጎበዜ ከፕሬዝዳንትነታቸው እንዲነሱ ለምክር ቤቱ ሀሳባቸውን ካቀረቡበት እለት በፊት አምባሳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ስለሆነም ቢያንስ በዚያች እለት ግለሰቡ ሁለት ጥምር ስልጣን በትከሻቸው ላይ ነበር – የአማራ ክልል ፕሬዝዳንትም፣ በቱርክ የኢትዮጵያ ሙሉ አምባሳደርም ነበሩ፡፡ ስለዚህም የአማራው ክልል ም/ቤት አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ ተጠርቶ ሲወያይ የነበረው፣ ቀድሞውኑ ከፕሬዝዳንትነቱ በተነሳና አምባሳደር ሆኖ በተሸመ ግለሰብ (አቶ አያሌው) ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ (የኢህአዴግ ድራማ እንዴት ደስ ይላል¡)

ድራማው ግን በዚህ አያበቃም፡፡ አቶ አያሌው ለምን ከፕሬዝዳንትነታቸው እንዲነሱ ተደረገ? ፋክት መፅሄት ከተወሰኑ መላምቶች አንፃር በማየት ስለግለሰቡ አነሳስ ምክንያት ለማቅረብ ሞክራለች፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ መላምቶች የተሳሳቱና እጅግ የተጋነኑ ስለሆነ፣ እኔ ለክልሉ ባለስልጣናት ካለኝ ቅርበት አንፃር የተወሰኑት ላይ ማስተካካያ ለመስጠትና ለግለሰቡ ከስልጣን መነሳት ዋናውን ምክንያት ለመጠቆም እፈልጋለሁ፡፡

አቶ አያሌው ከስልጣን የተነሱት ለሱዳን ከተሰጠ የወሰን አካባቢ ቦታ ጋር የተያያዘ መሆኑን አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊትም አቶ አያሌው “አልፈርምም አለ” ተብሎ መናፈሱ ይታወቃል፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ አቶ አያሌ በዙሪያቸው ያሰባሰቧቸው የወንዝ ልጆች በስፋት የለቀቁት ተራ ፕሮፓጋናዳ ነው፡፡ አንደኛ መለስን እንኳንስ “የቁርጥ ቀን ልጅ” በሚፈለግበት እንዲህ ባለው ሁኔታ ቀርቶ፣ ቀላል በሚባሉት ጉዳዮችም “ይህን እኔ አልሰራም” የሚል ባለስልጣን ኢትዮጵያ አልነበራትም (ያማ ቢሆን ኖሮ፣ የተሸከምነው መከራ በግማሽ እንኳን በቀነሰልን ነበር)፡፡ እንዲያውም አቶ መለስ በአንድ ወቅት አቶ አያሌውን “አንተ የማትጠቅም፣ የማትጎዳም ነህ” ብለው በመተቸታቸው በድርጅቱ ትልልቆቹ አባላት ውስጥ ዜናው በስፋት ተናፍሶ ነበር፡፡ ባጭሩ አቶ አያሌው “እምቢ” የማለት ወኔው የላቸውም፡፡ (በሱዳኑ ፊርማ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሳተፉ የተደረገው፣ ሙስሊም ስለሆኑ/ኢስላማዊ ዳራ ስላላቸው የሱዳኖችን ስነልቦና “ለመግዛት” ኢህአዴግ የቀየሰው ስልት ከመሆን አይዘልም፣ ወደ አንዳንድ አረብ አገራት ዲፕሎማቶችን ሲመድብ ተመሳሳይ መንገድ ስለሚከተል፡፡)

እና አቶ አያሌው ለምን ከፕሬዝዳንትነታቸው እንዲነሱ ተደረገ? የአቶ አያሌው ከፕሬዝዳንትነት መነሳት ለብዙዎች ድንገታዊ ሊመስል ይችላል፤ አንደኛ አቶ አያሌው “የመተካካት መርሁ በ’ኔም ላይ ይተግበርልኝ” ብለው እንዲጠይቁና ይቺው ቃላቸውም ሳትጨመር-ሳትቀነስ በኢቲቪ እንድትተላለፍ ተደርጓል፡፡ ሁለተኛ “ከስልጣን አውርዱኝ” ጥያቆያቸውን ያየው ም/ቤት ጉዳዩን የተወያየበት በ“አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ” ነው፡፡ ሆኖም ግን ሀቁ ሌላነው፡፡ (እነዚህ ግርግሮች ሌላው የድራማው አካል ናቸው)፡፡

አቶ አያሌውን ከፕሬዝዳንትነት የስልጣን ኮርቻ የማንሳቱ እቅድ የተዘረጋው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር (አቶ መለስ) በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ አቶ መለስ በመሩትና ባህር ዳር ላይ በተካሄደ የኢህአዴግ ስብሰባ ላይ አቶ አያሌ ተገምግመዋል፡፡ በዋናነት የቀረበባቸውና የተቀበሉት ክስም በክልሉ ባሉ የተለያዩ የስልጣን/የሹመት እርከኖች ላይ የራሳቸውን አካባቢ ሰዎች እጅግ በተደራጀ መንገድ ማሰባሰባቸው ነው፡፡ አንዳንዶች ሂደቱን “ጎጃማይዜሽን” ይሉታል፤ ሌሎች ደግሞ “ማርቆሳይዜሽን” በማለት ይጠሩታል፡፡

አቶ አያሌው ሹመት የሚሰጡበት ቀመር በጣም ግልፅ ነው፡፡ እሳቸው ከመጡበት ከደብረ ማርቆስና አካባቢው የተማረ ከተገኘ ያለ ምንም ጥርጥር ይሾማል፡፡ ማርቆሴ እያለ ሌላ ሰው በምንም ሁኔታ አይሾምም፡፡ ማርቆሴ ከጠፋ፣ የአቶ አያሌው ሁለተኛው የሹመት ቀመር ስራ ላይ ይውላል፤ ጎጃሜ የሆነ ሰው ተፈልጎ ይሾማል፡፡ ማርቆሴ ሁሉ ጎጃሜ ቢሆንም፣ ጎጃሜ ሁሉ ግን ማርቆሴ አይደለም፡፡ ሆኖም ማርቆሴ ያልሆነ ጎጃሜን መሾም፣ ጎንደሬን፣ ወሎዬን ወይም የሰሜን ሸዋ ሰው ከመሾም እጅግ የተሻለ ነው፤ ምክንያቱም ጎንደሬም፣ የሸዋ ሰውም ሆነ ወሎዬ መቼም ቢሆን ጎጃሜ አይደለምና፡፡ ይህ የአቶ አያሌው የሹመት ቀመር ከስልጣን በሚወርዲት ላይም ስራ ላይ ይውላል፤ ባብዛኛው ከስልጣን የሚወርድ ተሿሚ ማርቆሴ ወይም ጎጃሜ አይደለም፤ ባጋጣሚ ነገሩ ከፍቶ ከስልጣን ከተነሳም ወይ የተሻለ ቦታ ይሰጠዋል፤ ካልሆነም በያዘው ደረጃና ደመወዝ የአቶ አያሌው አማካሪ ሆኖ ይሾማል (ፉገራ በሚወዱ ካድሬዎች አነጋገር Recycle Bin ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ማለት እንደ ገና የሚሾምበት ጊዜ አለ ማለት ነው፤ አቶ አያሌው ማዘናጋት የሚገባቸውን ካዘናጉ በኋላ፡፡ የቀመሩን ዘረኝነት (racist) ልብ ይሏል፡፡)

ይህም በመሆኑ አሁን በአማራ ክልል ርእሰ ከተማ -በባህር ዳር- ብዙዎቹን የመንግስት ተቋማት የሚመሩት ባለስልጣኖችና ምክትሎቻቸው፣ ዝቅ ሲልም የምክትሎቹ ምክትሎች (ፕሮሰስ ኦውነር፣ መምሪያ ሀላፊ፣ ወዘተ) በዚህ የአቶ አያሌው የሹመት አሰጣጥ ቀመር ወደ ስልጣን የመጡ ናቸው፡፡ ይህ የአቶ አያሌ የሹመት ቀመር በቀጥታ በማይመሩት በባህር ዩኒቨርስቲ ጭምር ስራ ላይ እየዋለ እንደ ሆነ ይነገራል፤ ዩኒቨርስቲው በፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር የሚመራና ያሉት መምህራንም ከአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች የተገኙ ሆነው እያለ፤ የፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶችና ዲን ስልጣን (ወረድ ሲልም ከፕሮግራም ሀላፊ) በአብዛኛው በመጀመሪያ ደረጃ በማርቆሴዎች፣ ከዚያም በጎጃሜዎች “ቡድን” እንዲያዝ ተደርጓል፡፡ የአቶ አያሌው የጎጠኝነትና የዘረኝነት እጅ ይሄን ያህል ረጅም ነው፡፡

ይህ ድርጊታቸው ማለትም ክልሉን የጎጠኞች አምባ ማድረጋቸው አቶ አያሌውን ክፉኛ አስገምግሟቸዋል – በአቶ መለስና በሌሎቹም የኢህአዴግ ቁንጮ አባላት፡፡ ሆኖም አቶ መለስ በሀይል የወቀሷቸውን፣ የሰደቧቸውን፣ ያንቋሸሿቸውን ያህል አቶ አያሌውን ሮጥ ብለው ከስልጥን ማንሳት አልሆነላቸውም፡፡ በአቶ አያሌው ድርጊት “የበገኑትን” ያህል የይስሙላውን የአማራ ክልል ም/ቤት አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባ አስጠርተው ግለሰቡን ከፕሬዝዳንትነታቸው በማስወረድ “የትምህን ግባ” ማለት አልቻሉም፡፡ ያን የመሰለ ባለ ራእይ መሪ ይህን ማድረግ ለምን ተሳነው?

ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡ አቶ አያሌው ዙሪያቸውን ያሰለፉት የጎጥ ሀይል ቀላል አይደለም፡፡ ከላይኛው የክልል ካቢኔ ጀምሮ፣ የቢሮ ሀላፊዎች፣ ምክትሎቻቸው፣ ከምክትሎቹ ስር ያሉ ሌሎች ሀላፊዎች ከ95 በመቶ በላይ ከፍ ሲል የተገለፀውን የአቶ አያሌውን የሹመት ቀመር ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ (እዚህ ላይ ከምክትል ቢሮ ሀላፊዎች በታች ባለ የስልጣን ሹመት ላይ አቶ አያሌ ቀጥተኛ ሚና የላቸውም፡፡ ሆኖም በሹመት ቀመራቸው ያመጧቸውን የራሳቸውን የወንዝ ልጆች በሳቸው ቀመር እንዲመሩ ማድረግ አይሳናቸውም፤ አድርገውታልም፤ ተገምግመውበታልም፡፡)
ስለሆነም አቶ አያሌውን በድንገት እንደ ሙጀሌ ፍንቅል ማድረግ አደጋ እንዳለው ኢህአዴግ አመነበት፡፡ እዚያ ክልል ላይ የሰፈረውን አብዛኛውን ባለስልጣን አስኮርፎ ክልሉን መምራት (እንደፈለጉ ማሽከርከር) እንደማይቻል ኢህአዴግ ልብ አለ፡፡ ምናልባት ቅሬታው ስር ሰዶ በተለይም ደብረ ማርቆስ ወደሚገኘው ህዝብ ሊደርስና ያልተፈለገ መነሳነሳት/ብጥብጥ ሊያስከትል እንደሚችል እነመለስ ሰጉ፡፡ ስለሆነም ግለሰቡን በረጅም ጊዜ ለማውረድ መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆነ፡፡

እናም በክልሉ መስተዳድር መዋቅር ውስጥ የሌለ አደረጃጀት ኢህአዴግ ፈጠረና ከፕሬዝዳንቱ ሰር ሁለት ምክትሎች እንዲኖሩ ተደረገ፡፡ ሁለቱ ምክትሎችም በአቶ አያሌው ዙሪያ ካሰፈሰፉት የጎጥ ቡድኖች ውጭ እንዲሆኑ ተደረገ፤ አቶ አህመድ አብተውና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሆነው ተሸሙ፤ ሁለቱም ከወሎ፡፡ ስለሆነም አቶ አያሌው የነበራቸው ያሹትን የማድረግ ስልጣን በእጅጉ ተገድበ፤ ባጭሩ ተንሳፈፉ፡፡

የተዘረጋውን ጠንካራ የማርቆሴ መዋቅርና የአቶ አያሌውን ተፅእኖ የማዳከሙ ስራ እንደ ተሳካ ሲታወቅ የይስሙላው የአማራ ክልል ም/ቤት ተጠራ፤ የይስሙላውን የአቶ አያሌው ዱላ ላቀብል የሚል ምክንያት አዳመጠ፤ አፅድቅ የተባለውን አፀደቀ፡፡ በቃ- የሆነው ይኼው ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢቲቪ በአንድ የዜና ስርጭት ላይ፣ የአቶ አያሌውን ከስልጣን መውረድ “ካረዳ” በኋላ፣ ወዲያው በማስከተል በሙሉ አምባሳደርነት መሾማቸውን “ማብሰሩ” ሰውዬው ከፕሬዝዳንትነት በመነሳቱ ቅር የሚላቸውን መገኖች (የማርቆሴ ቡድን) ስሜት ለማከም መሆኑን ልብ ይሏል፤ ኢህአዴግ እንዲህ ነው መፍራት ሲጀምር ልክ የለውም፣ መድፈር ሲያበዛ ልክ እንደሌለው ሁሉ፡፡

ሌላው ለአቶ አያሌው ከስልጣን መሳነት እንደ ተጨማሪ ምክንያት ሊቀርብ የሚችለው፣ የምስራቅ ጎጃም በተለይም በሞጣ የአዲስ አበባ መንገድ አቅጣጫ ያለው ህዝብ ተደጋጋሚ ቅሬታና አቤቱታ ነው፡፡ የአዲስአበባ-ሞጣ-ባህር ዳር የጠጠር መንገድ በአስፋልት እንዲሰራ የአካባቢው ህዝብ ለዘመናት ጠያቄ ሲያቅርብ ኖሯል፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር – አቶ መለስ – ለህዝቡ ቃል የገቡ ቢሆነም እስካሁን ድረስ የመንገድ ስራው ሊጀመር አልቻለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ፣ የአካባቢው ህዝብ እንደሚናገረው፣ አቶ አያሌው ናቸው፤ “አቶ አያሌው በስልጣን እያለ የኛ መንገድ አይሰራም” በማለት ቅሬታቸውን በምሬት ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ሁሉ ወጥተዋል፡፡ ግን አቶ አያሌው ለምን ችክ ብለው መንገድ ግንባታውን ያሰናክላሉ?

የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን እንደሚሉት የሞጣው መንገድ መሰራት ከአዲስ አበባ-ባህር ዳር ያለውን ርቀት ቢያንስ በ70 ኪሎ ሜትር ስለሚያሳጥረው፣ በነባሩ መስመር ማለትም በቡሬ በኩል ባሉት ከተሞች ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅኖ ይኖረዋል፤ ያለ ጥርጥር ብዙዎቹ ተሸከርካሪዎች በሞጣው መስመር ስለሚሄዱ የቡሬ መስመር ነጋዴዎች በተለይም ሆቴሎች ገቢ ትርጉም ባለው ሁኔታ ማሽቆልቆሉ አይቀሬ ነው፡፡ ደብረ ማርቆስ ያለችው ደግሞ በዚሁ የቡሬ መስመር ነው፡፡ አቶ አያሌው ደግሞ ከዚህች አካባቢ ምሁራን ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ ጋር ያላቸው ፍቅር ወደር የለውም፡፡ እናም ለጎጣቸው ሲሉ የጎረቤታቸውን ጎጥ መልማት ሲከላከሉ ነው የኖሩት፡፡

እና ኢህአዴግ እኒህን ሰው ከስልጣን ማንሳት ይነሰው?

የከተማ አብዮት! – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

 

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ከሩሲያውያኑ ቦልሼቪክና ሜንሼቪክ አንስቶ፣ የእኛዎቹ ኢህአፓና መኢሶን በፊት-አውራሪነት እስከ ተሳተፉበት ድረስ ያሉ በደም የጨቀዩ አብዮቶች በሙሉ በከተሞች የተካሄዱ ሲሆን፣ አብዛኛው አጋፋሪዎቻቸው ደግሞ ልሂቃኖች እንደነበሩ በጉዳዩ ዙሪያ የተፃፉ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ይሁንና እነዚህ አብዮቶች (የተሳኩትም ሆነ የከሸፉት) ሰላማዊውንና ህጋዊውን መንገድ የተከተሉ ባለመሆናቸው ዛሬም ይዘገንናሉ፤ ለወደፊቱም ባልተደገሙ ያሰኛሉ፡፡ ስለምን ቢሉ? ግድግዳው ላይ የተቸከቸከው ፅሁፍ እንዲህ የሚል ምላሽ ያስነብባልና፡- በጭቁን ሕዝብ ስም የብዙሀኑን ቤት አፍርሰዋል፤ ሀገርና ታሪክ ለመቀየር የማይሳናቸው አፍላ ወጣቶችን እርስ በእርስ አጫርሰዋል፤ ‹አንቱ› ሊባሉ የሚችሉ ምሁራንን በአንድ ጀንበር ወደ ትንታግ ነፍሰ-ገዳይነት ቀይረዋል፤ ክስረቱም ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል… 

በርግጥም ያ ወቅት መደማመጥ፣ መነጋገር፣ መወያየት፣ መቻቻልን… የመሳሰሉ ምክንያታዊ እሴቶች ህቡዕ ገብተው፤ መጯጯኽ፣ መነቋቆር፣ መፈራረጅ፣ መገዳደል… የገነኑበት ነበር፤ ለዚህም ይመስለኛል ሀገር ሊረከብ የተዘጋጀ አንድ ትውልድ፣ በተኮረጀ ርዕዮተ-ዓለም፣ ባልጠራ ፕሮግራም እቅሉን ስቶ ‹ማርክስ እንደፃፈው›፣ ‹ሌኒን እንዳብራራው›፣ ‹ማኦ እንዳስተማረው›፣ ‹ሆጃ እንደመከረው›… በሚል ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ስቶ-በማሳት፣ ሀገር ምድሩን የጦር አውድማ አድርጎ ማለፉ የትላንት የቁጭት ትዝታ የሆነብን፡፡ በአናቱም ዛሬ ‹‹ነፃ አወጣናችሁ›› እያሉ ጃሎታ የሚመቱት የኢህአዴግ መሪዎች ከዚሁ ምንጭ የተቀዱ፣ ግና በቃላት ስንጠቃና በጎሳ ጠባብ አስተሳሰብ የተለዩ የትውልዱና የመንፈሱ ተጋሪ በመሆናቸው፣ የሁነቱ ‹ታሪክ›ነት ለተሰዉት እንጂ፣ ለእነርሱ ‹ሀገር እየመራንበት ነው› የሚሉበት ‹ፖለቲካ› ነውና፣ የነገይቷ የምንወዳት ኢትዮጵያችን መፃኢ ዕድል ገና ከእርስ በእርስ ግጭት ስጋት አለመላቀቁን ያመላክታል፡፡ በዚህ ፅሁፍም የምንዘመርለት የ‹አትነሳም ወይ?› ድምፅ አደገኛውን ስርዓት የመቀየሪያው ጊዜ አሁን በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ግን እነኢህአፓ ተቸንፈው የተሰናበቱበትም ሆነ ኢህአዴግ ድል አድርጎ የመጣበት መንገድ ለዘመኑ መልካም ተሞክሮ ሊሆን ይችላል እንደማለት አይደለም፤ ምክንያቱም በእኔ እምነት የእነርሱ ‹ፋኖ ተሰማራ…› ጊዜው በበየነበት ሙዚየምና የታሪክ ትምህርት ክፍል ውስጥ ብቻ ካልተገደበ ጉዳቱ በቀላሉ የሚጠገን ካለመሆኑም ባለፈ፣ የምንመኘውን ለውጥ ሊያመጣ አይችልምና ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ለትውልዱ ክቡድ ጥያቄ ስኬታማነት መንገድ መሪ አብርሆት መሆን የሚችሉ የደም ግብር ያልጠየቁ፣ ፍፁም ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ በከተሞች ተካሂደው ሀገርና ህዝብ ያለ ብዙ ኪሳራ በአሸናፊነት የወጡባቸው በርካታ አብነታዊ አብዮቶች (እንደ አረቡ ፀደይም ሆነ እንደ አውሮፓውያኑ ጆርጂያና ዩክሬን ብርቱካናማ-አብዮቶች) መኖራቸው እውነት ነው፤ እንዲሁም በእነርሱ መንፈስ መቀደስ፣ በእነርሱ ፀበል መጠመቅ የአምባገነኑንና የበደለኛውን ሥርዓት እድሜ ለማሳጠር የሚያበረታ ኃይል ማስረፁ እውነት ነው፡፡

ከተማን እንደ ጠላት

የ‹ያ ትውልድ› የጠብ-መንጃ ትንቅንቅን በድል የተሻገረው ኢህአዴግ (ከልቡ አምኖበት ባይሆንም) ይህንን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለው በተለይም ለአርሶ አደሩ ጥቅም መሆኑን በአገኘው አጋጣሚ ሳይናገር አያልፍም፡፡ በግልባጩ ደግሞ የከተማ ነዋሪዎችን ‹ጠላት› አድርጎ በመፈረጅ ሲገነግን ተደጋግሞ ተስተውሏል፤ በርግጥ የዚህ መግፍኤ በብሔር እና በሀይማኖት የከፋፈለውን ሕዝብ፣ በመደብም ለያይቶ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ ለማድረግ እና በየአምስት ዓመቱ በሚያካሄደው የይስሙላ ‹ምርጫ› ኮረጆ ገልብጦ ሲያበቃ የፈረደበት ምስኪን አርሶ አደር ‹መርጦኛል› ለሚለው የተለመደ ሰበቡ ‹ይጠቅመኛል› በሚል ለማመቻቸት ‹አዛኝ ቅቤ…› ተቆርቋሪ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይህም ሆኖ ድርጅቱ ይህንን የማጭበርበሪያ ስልት በደደቢት በረሃ ራሱ የቀመረው ነው ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ገፊ ጭብጥ ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ምክንያቱም በአንዳንድ የዓለማችን ሀገራት የፖለቲካውን ኃይል ከጨበጡ በኋላ በሕዝባቸው ላይ ነጋሪት ጎስመው ሞትን ከነዙ፣ ስቃይን ከረጩ እርኩሳን መሪዎች (ፓርቲዎች) ድርሳናት ቃል-በቃል የተገለበጠ መሆኑን የሚያስረግጡ (በስነ-አመክንዮ) የተቀኙ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላልና፤ እንደምሳሌም አንዱን በአዲስ መስመር እንምዘዘው፡-

የ‹ኬመር ሩዥ› መንገድ

በተለምዶ ‹ኬመር ሩዥ› (Khmer Rouge) በመባል የሚታወቀውና አክራሪ ኮምኒስታዊ የገበሬዎች ድርጅት እንደሆነ የሚነገርለት ‹‹Communist Party of Kampuchea /CPK/›› እ.ኤ.አ ከ1975-1979 ዓ.ም ድረስ፣ በወጣት የገበሬ ሠራዊት ታግዞ በካምቦዲያ መንግስታዊ ሥልጣን ተቆናጥጦ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ጨካኝና አፍቃሪ ቻይና የሆነው የፓርቲው ሊቀ-መንበር ፖል ፖትም (Pol Pot)፣ ማኦ ዜዱንግ ‹‹የሀገሬን ኢኮኖሚ ያሳድግልኛል›› በማለት ያረቀቀውንና በግብርና ላይ የሚያተኩረውን ‹‹Great Leap Forward›› ፕሮግራም፣ ‹‹Super Great Leap Forward›› በሚል ተቀጥላ እንደወረደ በመኮረጅ ‹‹ሙሉ የካምቦዲያን ሕዝብ ወደ ‹እርሻ መር-ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ› (Agrarian Society) እቀይራለሁ›› ብሎ ያደረገው ሙከራ ወጪ-ኪሳራን ያወራረደው ሁለት ሚሊዮን ዜጎቹንለህልፈት በመዳረግ እንደ ነበር የታሪክ መፃህፍት ያትታሉ፡፡

ከሁሉም የከፋው ግን ፖል ፖትና ጓዶቹ ‹‹እውነተኛ ዜጋ ገበሬ ብቻ ነው›› በማለት የከተማ ነዋሪዎችን በጠላትነት ከፈረጁ በኋላ ‹‹ማህበረሰባችንን ለማንፃት›› በሚል የቁም-ቅዠት ምዕራባዊ አስተሳሰብ የተንፀባረቀበትን ማንኛውንም ጉዳይ፣ የከተማ ሕይወትን፣ ኃይማኖትን፣ ትምህርትን፣ አንድ ብርም ቢሆን በግል መያዝን… በአዋጅ ማገዳቸው ነበር፤ እንዲሁም ኢምባሴዎችን፣ ጋዜጣና ቴሌቪዥን ጣቢያን ዘግተዋል፤ በሁሉም የሀገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎችን በማፈናቀል ወደ ገጠር አግዘው፣ በግዳጅ የእርሻ ሥራ ላይ አሰማርተዋል፤ ከዋና ከተማዋ ‹ፈኖሞ ፔንህ› (Phnom Penh) ብቻ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች ወደ ገጠር በእግር እንዲጓዙ በመገደዳቸው ሃያ ሺህ የሚሆኑት በጉዞ ላይ ወድቀው እንደወጡ ቀርተዋል፤ ገጠር የደረሱትንም ቢሆን ‹የግድያ ወረዳዎች› እያሉ በሚጠሯቸው የእርሻ ሥራ ላይ አሰማርተው ለአንድ ሰው በነፍስ ወከፍ በየሁለት ቀኑ አንዴ 180 ግራም ሩዝ ብቻ በመስጠት በረሀብ፣ በበሽታ፣ ብስቅየት እና በግድያ እንዲያልቁ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም አገዛዙ በቬትናም ጣልቃ ገብነት እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም በኃይል በመወገዱ፣ ፖል ፖት ከእነተከታዮቹ ሀገሩ ከታይላንድ ወደምትዋሰንበት ጠረፍ አካባቢ በመሸሽ፣ የትጥቅ ትግል እንደአዲስ ጀምሮ ለረዥም ዓመታት ከታገለ በኋላ፣ እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም እርጅና ተጭኖት በህግ ቁጥጥር ስር በዋለ፣ በዓመቱ ከልብ ጋር በተያያዘ ህመም ምክንያት ህይወቱ ማለፉ ይታወቃል (በነገራችን ላይ ይህ ድርጅት የሽምቅ ውጊያ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ በኋላ የተጠናከረበትን ምስጢራዊ መንገድ ጨምሮ የተከተለው ስልት
ከሞላ ጎደል ከኢህአፓና ህወሓት አፈጣጠር ትርክት ጋር ተመሳሳይነት አለው)

ኢህአዴግ እንደ ‹ኬመር ሩዥ›

ከሁለት አስርተ ዓመታት የሥልጣን ቆይታም በኋላ፣ የከተማ ነዋሪዎችን በጠላትነት ካሰፈረበት ጥቁር መዝገቡ ላይ መሰረዙ ያልሆነለት ኢህአዴግ ‹እንደ ኬመር ሩዥ ሁሉንም የጭካኔ ተግባራት በአደባባይ ፈፅሟል› ተብሎ ባይወነጀልም፣ ተመሳሳይ ስልቶችን በመኮረጅ በረቀቀ መንገድ አለዝቦ መተግበሩን ግን መካድ አይቻልም፡፡ እንዲሁም የሁለቱ ድርጅቶች ዋነኛ ልዩነት ወደ እንዲህ አይነቱ የጥላቻ ጠርዝ የተገፉበት ምክንያት ይመስለኛል፤ ይኸውም ፈላጭ ቆራጩ ፖል ፖት በከተሜው ላይ የከፋ ቂም የቋጠረበት መነሾ፣ ከገበሬ ቤተሰብ መገኘቱን ጨምሮ፣ ከአስተዳደጉ ጋር በሚያያዙ ‹ህመማቸው-ህመሜ› በሚል ሲባጎ የተቋጠረ ሲሆን፣ መለስና ጓዶቹ ደግሞ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም በማስላት ብቻ መሆኑ ነው፤ መቼም መሬት የረገጠውን እውነታ ተመልክቶ የሀገሬ አርሶ አደር ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በዘለለ፣ ከከተሜው የተለየ የመልካም አስተዳደርም ሆነ የመሰረተ-ልማት ተጠቃሚ አለመሆኑን መረዳቱ አዳጋች አይደለም፡፡
የሆነው ሆኖ የኢህአዴግ ‹ፀረ-ከተሜነት› እንዲህ በግላጭ አፍጥጦ የወጣው ከምርጫ 97 በኋላ ነው፤ በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ፣ ድርጅቱ በከተሞች መሸነፉን ከገለፀ በኋላ፣ በገጠር ሙሉ በሙሉ ስለተሳካለት መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የመራጭ ድምፅ ማግኘቱን አውጇል፤ ይህንንም ተከትሎ ግንባሩን ያልመረጡ የከተማ ነዋሪዎች በተቀነባበረ ሴራ የጥቃት ዒላማ መሆናቸውን የሚያመላክቱ በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በተለይም በድህረ-ምርጫው ከተሜውን ዒላማ ያደረጉ በስራ ላይ የዋሉ አፋኝ ህጎች እና ፖሊሲዎችን ጨምሮ በደባ የተፈፀሙ መንግስታዊ ጥፋቶችን ዘርዘር አድርገን እንያቸው፡፡
መሬትን በተመለከተ የወጣውን የሊዝ አዋጅ በቀዳሚ ምሳሌነት እናንሳው፤ ፓርቲው በ1987 ዓ.ም ባፀደቀው ህገ-መንግስት የመሬት ፖሊሲውን አንዱ ዕማድ አድርጎ በማካተቱ፣ የመንግስት ጭሰኝነትን (Tenants of the state) በገጠሩ ክፍል ሲያሰፍን፣ የመሬት ከፊል ባለቤትነትን ደግሞ ለከተሞች እንዲፈቅድ አድርጎት ነበር፡፡ እናም የግል ይዞታን መሸጥ (መንግስት ለሚፈልጋቸው ‹‹ልማቶች››ም ሆነ በሊዝ ለመቸብቸብ ዜጎችን የማፈናቀል መብት ከማግኘቱ ውጪ) እስከ 97ቱ ድህረ-ምርጫ ድረስ ተፈቅዶ የዘለቀበት ሂደት፣ በዚህ የሊዝ አዋጅ በመሻሩ የተነሳ፣ ነዋሪው መሬት በመሸጥ ሊያገኝ ይችል የነበረው ገቢ ተጨምቆ ወደ መንግስት ካዝና እንዲሻገር ሆኗል፡፡ የዚህን አዋጅ ‹ፖለቲካዊ ንባብ› ውስጥ የምናገኘው ጭብጥ፣ በከፊልም ቢሆን መሬት ላይ የቆመውን የሀብት መሰረት በመናድ፣ የተቃውሞ ኃይሉ የድጋፍ መዕከል እንደሆነ ያመነውን የማህበረሰብ ክፍል ክፉኛ ማድቀቁን ስንረዳ ነው፡፡ አዋጁን እንለጥጠው ካልን ደግሞ ግንባሩ በገጠሩ ያነበረውን የዜጎች የመንግስት ጭሰኝነት በጠመዝማዛ መንገድ፣ በተለይም በአዲስ አበባ የመፈጸም ዕቅዱ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡

የኢህአዴግ ከተማንና ከተሜዎችን የመፍራት አባዜ ከጫካ ትግሉ ጋርም በረዥሙ የሚተሳሰር ነው፡፡ በወቅቱ በጥላቻ ከመተያየት አልፎ ደም የተቃባቸው ኢህአፓን መሰል ኃይሎች መሰረታቸው ከተሞች ላይ እንደነበረ ይታወቃል፤ በአናቱም በትግሉ መጠናቀቂያ ዋዜማ እና ማግስት ሊገዛለት ያልቻለው (ማማለሉ ያልተሳካለት) ልብ በተለይ የአዲስ አበቤዎችን ነበር፤ በ1980ዎቹ መጀመሪያም ፓርቲው አንገት ላይ ታንቆ ሊደፋው የነበረው ዋነኛ ጉዳይ፣ ብሔር ተኮር ስርዓቱ ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ ሲያገኝና የብሄር ፖለቲካ ብቸኛው የድጋፍም የተቃውሞም ተዋስኦ እንዲሆን መደረጉ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መንፈስ ከተገራው የአዲስ አበቤ ብሔር ዘለል ማንነት ጋር እንዲህ በፊት ለፊት መጋጨቱ፣ ከተማይቱን በወረራ የያዛት እስኪመስል ድረስ በጥላቻ እንዲዘምቱበት አነሳስቷል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የመጣው የአሰብ ወደብን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲካለል የመፈለግ የከተሜዎቹ ግፊት ነው፡፡ ጦርነቱ ሲያበቃና የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ ሲገደዱ የነዋሪው ቁጣ ብርቱ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ይህ እውነትም ሌላኛው ፓርቲውን ቂም ያስቋጠረ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በድህረ-ምርጫ 97 የፀደቀውና አፋኝነቱ በተግባር የተረጋገጠው የሲቪል ማህበረሰቡን የሚመለከተው አዋጅም ‹የብዙዎች ተቋማት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የወጣ ነው› በማለት ከየአቅጣጫው ይነሳ የነበረውን የተቃውሞ ውግዘት አጣጥሎ፣ በሥራ ላይ ባዋለበት ዓመት በርካታ ተቋማትን ከማፈራረሱ አኳያ፣ መጀመሪያውንም ለእንዲህ አይነቱ ክፉ እርምጃ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ወደሚል ጥርዝ ይገፋል፡፡ በተጨማሪም ያለፉትን ሃያ ሁለት ዓመታት ሙሉ በአይኑ መዓት የሚያያቸው ምሁራን፣ የነፃው ፕሬስ አባላት እና
በየዘመኑ ከባድ ተግዳሮት የፈጠሩበት የተቃውሞ ስብስቦች ጠንካራ መሰረት በከተማይቱ ውስጥ መሆኑ ጥላቻ እና የጭካኔ እርምጃዎቹን አብዝቶታል፡፡

ሌላው አገዛዙ በከተሜዎች (በሸማቾች) ላይ ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ የሚያሳዩት፡- ከምርጫው በኋላ ጤናማ ያልሆነ የዋጋ ንረት በከፋ ደረጃ ማሻቀቡ፣ ፍትሃዊ ያልሆኑ የተለያዩ የግብር ህጎች በእንጀራ እና ሽንኩርት ቸርቻሪዎች ላይ ሳይቀር መተግበራቸው ነው፡፡ በተለይም ካለፉት ስምንት ዓመታት ወዲህ የተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ዋነኛ አባባሽ ኃይል የምግብ ዋጋ መናር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ የምግብ ዋጋ መናር በዋነኝነት ቋሚ ደሞዝ ተከፋዩ የከተማ ነዋሪው ተጎጂ መሆኑን የስርዓቱ ባለስልጣናትም ይቀበላሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ከሁለት ወራት በፊት በ‹‹አዲስ ዘመን›› መፅሄት የተጠየቀው የፋይናስና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ‹‹በ2006 ዓ.ም የሚጨመር ደሞዝ አይኖርም›› ከማለቱ ባለፈ ‹‹ነገ ይችን አገር ወደተሻለ የሚያደርስ በጎ መስዋዕትነት ነው›› ሲል በከተሜው መከራ ላይ አላግጧል፡፡ በርግጥ ይህ ሁሉ መዓት ከመውረዱ በፊት በ1998 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ራሱ አቶ መለስ በደቡብ ክልል ወደምትገኘው ይርጋለም ከተማ ድረስ ሄዶ የሙዝ አምራች አርሶ አደሮችን ሰብስቦ ካነጋገረ በኋላ፣ እንዲህ ለፍተው የሚያገኙትን ምርት ለከተሜው በርካሽ መሸጣቸው አግባብ አለመሆኑን ቀስቅሶ ዋጋውን በአራት እጥፍ እንዲጨምሩ በማድረጉ የተፈጠረው የገበያ እጥረት፣ ምንም እንኳ መልሶ አምራቾቹን ሰለባ ቢያደርግም፣ ኩነቱ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቀጣይ ዕቅድ የሚያመላከት ነበር፡፡

በከተሞች ውስጥ እየተደረገ ያለው ‹‹የሰፈራ ፕሮግራም››ም (Urban Resettlement) አንዱ ሊነሳ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ ዕቅድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተሻለ የመኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ እንደሆኑ ማየት እንችል ይሆናል፡፡ ጥያቄው የሚነሳው ግን፣ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎችን ከሌሎች የፈረሱ የከተማዎቹ ክፍሎች ከሚመጡት ጋር በአንድ አዳብሎ በኮንዶሙኒየም ቤቶች አጥሮ የማስቀመጡ አንደምታ ላይ ነው፡፡ የዚህ ዕቅድ ክፉ ገፅ የሚገባን በረዥም የአብሮነት መስተጋብር (ሶስት መንግስታትን መሻገር የቻለ የአንድ አካባቢ ነዋሪነት) የተገነባው የጋርዮሽ ፖለቲካው አረዳድ እና የእርስ በእርስ ፍፁም መተማመን፣ 97ን ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች በተነሱ ተቃውሞዎች ወጥ ምላሽ እንዲሰጡ ማደፋፈሩን (አራት ኪሎን የመሳሰሉ አካባቢዎች) አስታውሰን፣ በመልሶ ማስፈሩ ደግሞ የአንዱን አካባቢ ነዋሪ በታትኖ ወደተለያዩ ሳይቶች መውሰዱን ስንመለከት ነው፤ ይህ መራራ እውነታም የገዥዎቻችን ጥላቻ ስር የሰደደ መሆኑን እና የአምባገነናዊ ስርዓቱን ዕድሜ ለማራዘም ያለመ እንደሆነ ይጠቁመናል፡፡
(ስርዓቱ በከተሜዎች ላይ የሰረፀበትን ጥልቅ የጥላቻ ፅንፍ እንዲህ ከተመለከትን፣ የከተማ አብዮት፣ ማኦኢዝም ከሚያዘው ከገጠር ከሚነሳው ብረታዊ ትግል ጋር ያለውን ልዩነት፣ በአረቡ ፀደይ ተሞክሮ በመንተራስ መፈተሹን፤ እንዲሁም የኢህአዴግ ግድፈቶች (Achilles’ heel) የከተማ አብዮትን ለማስነሳት ያላቸውን አስተዋፅኦ፣ በአደባባይ ሊያሰባስቡ የሚችሉ ጥያቄዎች ምን ቢሆኑ የተሻለ ነባራዊውን እውነት ያንፀባርቃሉ… የሚሉትን ጉዳዮች እና መንገዱን ስለሚመሩ የሚችሉትን መልከአ-ቡድኖች ማንነት ሳምንት እመለስበታለሁ)

“መሪዎቻችን ነጻ ናቸው! ፍትህ ለወኪሎቻችን! እያልን ትግላችንን እንቀጥላለን” – ከድምጻችን ይሰማ የተላለፈ ወቅታዊ ጽሑፍ

“መሪዎቻችን ነጻ ናቸው! ፍትህ ለወኪሎቻችን! እያልን ትግላችንን እንቀጥላለን” – ከድምጻችን ይሰማ የተላለፈ ወቅታዊ ጽሑፍ

 ታህሳስ 27/2006

ባለፉት ሁለት አመታት ያሳለፍነው የትግል ወቅት በፍሬዎቹም ሆነ በመስዋእትነቶቹ ብዙ ያሳየን ክስተት አለ፡፡ ከነዚህ አንዱ ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙ ‹‹ወኪሎቼ›› ብሎ ሊተማመንባቸው የሚችላቸውን ሰዎች በአንድ ድምጽ መርጦ ወደመንግስት ዘንድ መላኩ ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ገና ተቃውሞውን ማሰማት በጀመረ በሳምንታት እድሜ ውስጥ ይህን መሰል ውክልና እውን ማድረጉ አስገራሚም አስደናቂም ሆኖ አልፏል፡፡
muslim1
‹‹ኮሚቴዎቻችን ወኪሎቻችን ናቸው!›› የሚለው ቃል መፈክር ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም መሬት ላይ የወረደና የብዙሀኑን ሙስሊም ህይወት የሚነካ ተግባራዊ ትርጉም አለው፡፡ እንዲሁ ከሜዳ የተገኘ ውክልናም አይደለም፡፡ ይልቁንም የኮሚቴዎቻችን ውክልና ባህላዊውን አካሄድም፣ ብቃትንም፣ ህጋዊነትንም፣ ሃይማኖትንም ሆነ ህብረ ብሄራዊ ስብጥርን ያገናዘበና የሁሉንም መስፈርት ያሟላ ድንቅ የህዝባዊ ድምጽ ውጤት ነው፡፡

ህዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ ሲኖረው ችግሩን ለመንገር፣ ብሶቱን ለማሰማትና መፍትሄ ለመፈለግ ከመካከሉ መልካም የሚላቸውን ሰዎች መምረጡ ለዘመናት የቆየ አገራዊ ባህላችን ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሰዉን ብሶት ለማሰማት ባለስልጣናት ጋር የሚሄድ አካልን ማክበርም እንዲሁ ከማህበረሰባዊ እሴቶቻችን አንዱ ነው፡፡ እንኳንስ የራስ ህዝብ ወኪል ይቅርና የጠላት ሀይል መልእክተኛ እንኳን ሰብአዊ በሆኑ ማህበረሰባት ዘንድ ሁሉ ይከበራል፡፡ ኮሚቴዎቻችን የተወከሉበት ስርአት ከግምት ካስገባቸው ነጥቦች አንዱ ደግሞ ይኸው ድምጽን በወኪሎች የማሰማት የዘመናት ልማድ ነበር፡፡ አዎን! የኮሚቴዎቻችን ህዝባዊ ውክልና ከሚጸናባቸውና ተቀባይነት ካስገኙለት መሰረቶች አንዱ ይኸው ነው፡፡ ህዝቡ ብሶቱን ለመግለጽ ተሰበሰበ፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ ተነጋገረ፡፡ ‹‹መንግስትን ማናገር አለብን›› የሚል ውሳኔ ላይ ሲደርስ አፍ ሆነው ችግሩን ሊያስረዱለት የሚችሉ ሰዎችን መረጦ ሀላፊነት አሸከመ፡፡ ሲመርጥ ዝም ብሎ አልነበረም፤ እንደህዝብ የውክልናቸው ቅቡልነት መሰረት የሆኑ ነጥቦችን አገናዝቦ እንጂ!

ከቅቡልነታቸው መሰረቶች አንዱ የኮሚቴዎቻችን ብቃት ነበር፡፡ ህዝቡ በተለያዩ መድረኮች ያውቃቸዋል፡፡ በተሰማሩባቸው ዲናዊ ዘርፎች የነበራቸውን አስተዋጽኦ፣ የማስተባበር ብቃት፣ የንግግር ተሰጥኦና የዳበረ እውቀት በሚገባ ያውቃል፡፡ ድምጽ ሊሆኑለት ዘንድ ምሉእ ብቃትን የተላበሱና የዘመኑንም ቋንቋ መናገር የሚችሉ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ በመሆኑም በፊርማው ወክሎ ሲልካቸው ሃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚችሉ በመተማመን ነበር፡፡ ይህንን ደግሞ ተግባራቸውም ታሪክ ሆኖ መስክሯል፡፡ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ባልታወቀ ሁኔታ ህዝቡን ሰላማዊ፣ ጽኑና የሰለጠነ ትግል እንዲያደርግ ማስቻላቸውንና አገራዊ መነቃቃት መፍጠራቸውን ያልታዘበ የለም፡፡

ሃይማኖት ሌላው የቅቡልነት መስፈርት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ይከበራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ እንደኢትዮጵያ አገራችን ህዝቡ ሃይማኖተኛ በሆነበት አገር ደግሞ ለሃይማኖት አባቶች የሚሰጠው ማህበራዊ ክብር የበለጠ ይገዝፋል፡፡ ከትናንሽ የቤተሰብና የትዳር ጸብ አንስቶ እስከትላልቅ አገራዊ ጉዳዮች ድረስ የሃይማኖት አባቶች የሽምግልናም የገሳጭም ሚና አላቸው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በህገ ወጡ መጅሊስና መንግስት ጋብቻ የሚደርስበትን ችግር ለመፍታት ሃይማኖት አባቶችን መምረጡ በእርግጥም ተገቢ ነበር፡፡ ኮሚቴዎቻችን ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ የሃይማኖት አባቶች፣ ሰባክያንና ምሁራን ነበሩ፡፡ ይህን እንከን የለሽ ውክልና እንደምን መካድ ይቻላል?
muslim dim
ህጋዊነት ሌላው የውክልናቸው ቅቡልነት መስፈርት ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በአወሊያ መስጊድ ተሰባስቦ ለሁሉም ግልጽ በሆነ ሁኔታ ተመርጠዋል፡፡ የምርጫ ሂደቱ እንከን የለሽ የነበረ ቢሆንም በርሱ ብቻም አልተብቃቁም፡፡ የሁሉም ስም ዝርዝር ተጽፎ በሰፈረበት ወረቀት ላይ እያንዳንዱ ፔቲሽን ፈራሚ ስሙንና አድራሻውን እያስገባ ሶስቱን ጥያቄዎች መንግስት ዘንድ እንዲያደርሱለት ወክሏቸዋል፡፡ ፔቲሽኑ በተጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ከመላው አገሪቱ ከ800 ሺህ በላይ ሙስሊሞች ፈርመው ውክልናቸውን አጽድቀዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የክልል ሙስሊሞችም አወሊያ መስጊድ ድረስ የጁምአ ተቃውሞዎች ላይ በአካል በመገኘት ህዝባዊውን ጥያቄ ለማድረስ የወከሏቸው መሆኑን በይፋ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ድብቅ ታሪክ ሳይሆን በቪዲዮ ጭምር የተቀረጸና የመንግስት አይኖችና ጆሮዎች ባሉበት በግላጭ የተፈጸመ ነው፡፡ ታዲያ ይህን እንከን የለሽ ውክልና እንደምን መካድ ይቻላል?

ኮሚቴዎቻችን ታስረው ክስ እስከተመሰረተባቸው ጊዜ ድረስ በመንግስትም ዘንድ ውክልናቸው ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ መሆኑ የማንዘነጋው ትውስታ ነው፡፡ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ባለስልጣናት የካቲት 26/2004 ከኮሚቴዎቻችን ጋር በይፋ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ኮሚቴዎቻችን የተወከሉበትን ፔቲሽን በእለቱ ያቀረቡ ሲሆን ባለስልጣናቱም ውክልናቸውን አጽድቀውና መጅሊሱ ኮሚቴዎቹን ‹‹አሸባሪ›› ብሎ መፈረጁን ኮንነው፣ ይልቁንም ተቃውሞውን ሰላማዊነቱን አስጠብቀው በማቆየታቸው አመስግነው ነበር፤ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ያልሰጡ ቢሆንም! ‹‹እናንተን አሸባሪ ማለት አብሯችሁ የተወያየውን መንግስት በአሸባሪነት መፈረጅ ነው›› እስከማለትም ደርሰው ነበር፡፡ ታዲያ ዛሬ ውክልናቸውን ቢክዱት ከቶ ምን ይፈይዳል?

መንግስት የኮሚቴዎቻችንን ውክልና ንዶ በአሸባሪነት መኮነኑ በህዝብም ሆነ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አንዳችም ድጋፍ አላገኘም፡፡ ‹‹የህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ሳይሆን አሸባሪዎች ናቸው›› ይላል መንግስት፤ ይህን ሲል ግን ብቻውን ነው፡፡ ሳር ቅጠሉ ይቃወመዋል፡፡ ህዝቡ ይቃወመዋል፡፡ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ይቃወመዋል፡፡ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ይቃወሙታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በግትርነት መግፋቱን ቀጥሏል… መንግስት ባንድ በኩል…. ቀሪው ሁሉ ደግሞ በሌላ በኩል!!!

መንግስት ያንንም አለ ይሄንን እኛ ወኪሎቻችንን እናውቃቸዋለን! ድምጾቻችንን እንለያቸዋለን! እስከመጨረሻም ከጎናቸው አንለይም! ‹‹መሪዎቻችን ነጻ ናቸው! ፍትህ ለወኪሎቻችን!›› እያልን ትግላችንን እንቀጥላለን …. እስከድሉ ደጃፍ ድረስ!

ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ልጃቸው ተከሰሱ

የቀድሞ ፕሬዚዳንት  ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ልጃቸው ተከሰሱ

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ልጃቸው ተከሰሱ

  •  05 January, 2014
  • Written by  ሠላም ገረመው

ቤት ያገኘላቸው የኮሚሽን ሠራተኛ  360ሺ ብር አልተከፈለውም
ውል ፈርሶብኛል ያሉ ሌላ አከራይ የ2.4 ሚሊዮን ብር ካሣ ጠይቀዋል
የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት የሚከራከርለት የህግ ባለሙያ የለውም
ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ የመኖሪያ ቤት አፈላልጐ ያከራያቸው የኮሚሽን ባለሙያ አቶ አንተነህ አሰፋ፤ 360 ሺ ብር የአገልግሎት ክፍያ አልተከፈለኝም ሲል በፕሬዚዳንቱና ልጃቸው ላይ ክስ መሠረተ፡፡
ክሱ፤ ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ የፕሬዚዳንቱን ጽ/ቤትና የጽ/ቤቱ ሃላፊ ወ/ሮ አማረች በካሎን፣ የጽ/ቤቱ ባልደረባ ወ/ሮ አምሣለ ፋንታሁንንና የፕሬዚዳንቱን ልጅ ወ/ሮ መና ግርማን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡
ከሣሽ አቶ አንተነህ፤ ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ለፍ/ቤት  በጽሑፍ ባቀረበው ማመልከቻ፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባለፈው መስከረም ወር ከስልጣን ሲወርዱ የገቡበትን ባለ 3 ፎቅ መኖሪያ ቤት አፈላልጐ በወር 400 ሺህ ብር እንዲከራዩ ማድረጉን ጠቅሶ፤ ለእሱ የሚገባው 360ሺ ብር የኮሚሽን ክፍያ እንዳልተከፈለው ገልጿል፡፡ የአገልግሎት ክፍያውን የመክፈል ሃላፊነት የማን እንደሆነ ለማወቅ መቸገሩን የጠቆመው ከሳሹ፤ ከ5ቱ ተከሣሾች ውስጥ ሃላፊነት ወስዶ ክፍያውን የሚፈጽመው ማን እንደሆነ ፍ/ቤቱ እንዲያጣራለት ጠይቋል፡፡ አስር በመቶ የኮሚሽን ክፍያው ከመስከረም ወር ጀምሮ ከሚታሰብ የ9 በመቶ ወለድና የክስ ሂደት ወጪዎች ጋር ተደምሮ ይከፈለው ዘንድም ለፍ/ቤቱ አመልክቷል፡፡
ክሱ የደረሰው የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ የህግ ድጋፍ ለመጠየቅ ለፍትህ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ፤ ለኮሚሽን ባለሙያው ሊከፈል የሚገባው ገንዘብ፣ የመንግስትን ጥቅም ስለሚጐዳና ጽ/ቤቱም በራሱ ለመከራከር የህግ ባለሙያ ስለሌለው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወክሎ እንዲከራከርለት ጠይቋል፡፡
የመኖሪያ ቤት ፍለጋውን ከመጀመሩ በፊት የፕሬዚዳንቱ ወኪል ከሆነችው ከልጃቸው ወ/ሮ መና ግርማ ጋር የኮሚሽን ክፍያ ውል መፈራረሙን የጠቀሰው ከሳሹ፤ ክፍያውን በወቅቱ ባለማግኘቱ  ህዳር 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ፤ በ5 ቀን ውስጥ ክፍያው ካልተፈፀመ ክስ እንደሚመሰርት ማስጠንቀቁን አስታውሷል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤትም፤ ተከሣሾች መልሳቸውን የፊታችን ረቡዕ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በማዘዝ የክሱን ቀጣይ ሂደት ለመስማት ለጥር 27 ቀጥሯል። በሌላ በኩል ቀደም ሲል በ530 ሺ ብር ቤታቸውን ለፕሬዚዳንቱ መኖሪያነት ለማከራየት ከተስማሙ በኋላ፣ ውል ፈርሶብኛል ያሉት አቶ ኤልያስ አረጋ፤ ቤቱን ለማሳደስና ለተያያዥ ጉዳዮች ያወጧቸውን የተለያዩ ወጪዎች በመጥቀስ፣ የ2.4 ሚሊዮን ብር ካሣ እንዲከፈላቸው ለፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በደብዳቤ ያሳሰቡ ሲሆን ይህ ካልተፈፀመ ግን መብታቸውን በህግ ለማስከበር እንደሚገደዱ  ገልፀዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ በአሁኑ ሰዓት በኃይሌ ገ/ስላሴ ጐዳና፣ ከአክሱም ሆቴል ጀርባ መንግስት በተከራየላቸው ባለሦስት ፎቅ መኖርያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ቤቱ የመዋኛ ገንዳ ያለውና ባለብዙ ክፍሎች እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቤቱ ከእሳቸው በፊት ለኬንያ ኤምባሲ ተከራይቶ ነበር፡፡  የመንግስት ባለስልጣናት በጡረታ ሲገለሉ የሚኖራቸውን መብት የሚደነግገው አዋጅ፤ ፕሬዚዳንቱ ከ4-5 መኝታ ክፍሎች ያሉት መኖርያ  ቤት እንደሚያገኝ ቢገልጽም የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በጣም ውድና ከ20 ክፍሎች በላይ ያሉት መኖርያ ቤት መከራየቱ ሲያነጋግር መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶን በጉዳዩ ዙርያ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸው “ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ስለሆነ ምላሽ ልሰጣችሁ አልችልም” ብለዋል፡፡