“ለአፍሪካ ቀንድ ሠላም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መመለስ አለበት” – ረ/ፕሮፌሠር መድኅኔ ታደሠ


Medhane Tadesse 1

“ለአፍሪካ ቀንድ ሠላም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መመለስ አለበት”

“የመለስን ያህል ስልጣን የያዘ ሠው አለመኖር ብዙ ነገሮችን ሸግግርና ጥያቄ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል”
ረ/ፕሮፌሠር መድኅኔ ታደሠ

ረዳት ፕሮፌሠር መድኅኔ ታደሠ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች በተለይ በግጭት አወጋገድ አጥኚና ተመራማሪ ናቸው፤ በመገናኛ ብዙሃን በመቅረብ በሚሰጡት ትንታኔም ይታወቃሉ፡፡ “Horn of African Veteran Political Analyst” በማለት የውጪ ሃገር መገናኛ ብዙሃን ይገልጿቸዋል፡፡ ረ/ፕ መድሃኔ ከሥራ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አብላጫ ጊዜያቸውን በውጪ ሃገራት ነው የሚያሳልፉት፤ ባለፈው ሳምንት ከደቡብ ሱዳን እንደተመለሱ በወቅታዊ የሃገር ውስጥና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ዙሪያ ከሎሚ አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሎሚ፡- ረ/ፕ መድኅኔ እንኳን በሠላም ተመለሱ፤ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት ዋና ትኩረትዎን ምን ላይ አድርገው በመስራት ላይ ነዎት?
ረ/ፕ መድኅኔ፡- እንኳን ደሕና ቆያችሁኝ፡፡ በዋነኛነት በአፍሪካ የፀጥታ ችግሮችና ግጭት አፈታት ዙሪያ ከተለያዩ መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የማማከር ስራ ነው የምሠራው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጠመድኩበት ስራ የአፍሪካ ህብረት የፀጥታ ዘርፍን ስትራቴጂ ማዳበር ነበር፡፡ ትኩረቱ የአፍሪካ መንግስታት የፀጥታ ተቋማትን ማሻሻል ነው፡፡ የአፍሪካ ሃገራት ካሉበት በጣም የወደቀ የማይመች አሠራር መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ሲል አፍሪካ ለዚህ የሚሆን ዕቅድ አልነበራትም፡፡ የአፍሪካ ህብረትም ዕቅዱ ያስፈልገው ነበር፡፡
የአሕጉሪቱ መንግስታት የየሃገራቸውን የደህንነት፣ ፖሊስና መከላከያ ኃይል የመሳሰሉ የፀጥታ መዋቅሮቻቸውን ለህዝብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው፡፡ እነዚህ የግጭት መንስዔም የችግር ምንጮችም ናቸው፡፡ ስለሆነም አዋጁ ተረቆ ካልጸደቀ በቀር አፍሪካ ውስጥ ሠላምና ዲሞክራሲ ሊመጣ አይችልም በሚል እሳቤ ይሄንን ሃሳብ ከሚጋሩ ጓደኞቼ ጋር ሆነን አጀንዳውን ቀረጽን፡፡ የየሃገራቱን ነጣጥለን ከመመልከት በአሕጉር ደረጃ በተለይ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት አወቃቀር እንዲሻሻል ማድረግ አለብን ብለን በመነሳት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለዚህ የሚሆን መነሻ ሃሳብና ግብአት አስቀምጠን በአማካሪነት ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ሥራው ተጠናቆም የመሪዎች ጉባዔ አፅድቆታል፡፡

ሎሚ፡- በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በሚያስተምሩበት ወቅት የአፍሪካ ግጭት ተመራማሪ እየተባሉ ነበር የሚጠሩት፤ በመፅሐፎችዎም ይኽ ተጠቅሷል፤ እነዚህን የጥናት ውጤቶች ጠቅለል አድርገው ቢገልጹልን?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- አብዛኞቹ መፅሃፎቼ ከታተሙ ከ10 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ አንዱ የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው ትልቅ ተፅዕኖ የፈጠረው መፅሀፍ በአፍሪካ ቀንድ በማተኮር በ“አል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ” ዙሪያ የፃፍኩት ነው፤ የሶማሊያ አክራሪ ቡድኖች ምንጭ፣ እድገት እና አፈጣጠር ላይ ያተኮረ ነው፤ ሶማሊያ በዚህ ከቀጠለች አክራሪዎቹ ወታደራዊ የበላይነት የሚጨብጡበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ከ10 ዓመት በፊት ነበር የፃፍኩት፤ የተባለው ሆኖ “ኢስላሚክ ፍርድ ቤቶች ሕብረት”፣ “አልሸባብ” መጡ፤ ይሕን እና ከምንጫቸው አንስቶ ወደ ዓለም አቀፍ ጂሃድ እንቅስቃሴ ምስረታ ድረስ የሚኖረውን ሂደት እንዲሁም በሶማሊያ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚጠቁም መጽሐፍ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያም ጣልቃ እስከመግባት ደረሠች፡፡
ሌላኛው መጽሐፌ የናይል ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ውሃ እንዲሁም የሱዳንና ግብፅ ነዳጅ ዘይት ወሳኞቹ የትስስር ክንፎች ወይም የግጭት ምንጮች ይሆናሉ ነው የሚለው፡፡ ይሕም ረጅም ዓመት ሆኖታል፡፡ በአጠቃላይ ወሳኝ ናቸው የሚባሉ የአፍሪካ ቀንድ ዘመን ተሻጋሪ ግጭቶችን፣ መፍትሔዎችን፣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚጠቁሙ ስራዎች ላይ ነበር ያተኮርኩት፡፡

አሁንም ድረስ እዚያው ላይ ነው እየዳከርን ያለነው፡፡ ወይ መንግስታቱ አይሠሙም፤ አለያም ምንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ ስላልቻሉ ችግሮቹ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ በርግጥ ችግሮቹ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ በመሆናቸው እንኳንስ በአንድ መንግስት ቀርቶ በአራትና አምስት መንግስታት ላይቀረፉ ይችላሉ፡፡ የአባይ ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይ… ለዘመናትና ለትውልዶች የሚቆዩ ይሆናሉ፡፡ ችግሮቹ በአንዴ ይፈታሉ ማለት ባይቻልም የመፍትሄ አቅጣጫውን ማስቀመጥ ግን ይቻላል፡፡ የኤርትራም ጉዳይ እንደዚያው ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ከአስር ዓመት በፊት ያደረግኩትን ጥናት በኢ.ሲ.ኤ መድረክ አቅርቤ ነበር፡፡

በጥናቱ የውሃ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ውስጥ አደገኛ እየሆነ እንደሚሄድ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ህዝብን ሊፈትን የሚችል ኃይል ሊኖረው እንደሚችል ጠቁሜያለሁ፡፡ በተለይ በሃይማኖት ረገድ የሳዑዲው “ዋህቢያ” ያለውን ጥንስስ፣ የሃይማኖት ግጭት በአምስት አመት ውስጥ ሊፈጥር እንደሚችል ነበር ያ ፅሁፍ የሚያብራራው፡፡ ያኔ መንግስት አልተቀበለውም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የሆነው እየታየ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ችግሮች ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡ ችግሩ አሁንም በተለያየ መልኩ የሚታይበት ሁኔታ ነው ያው፡፡

ሎሚ፡- ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ከቀድሞው መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ የከፋ መሠነጣጠቅ ውስጥ እንደገባ በተለያዩ ወገኖች ይገለፃል፡፡ እርስዎ ስለዚህ ጉዳይ ምን መረጃ አለዎት?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- የከፋ መሠነጣጠቅ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከመለስ ሞት በኋላ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ሃገሪቷም ሌላ ሽግግር ውስጥ ነው የገባችው፡፡ ኢትዮጵያ ሽግግር ላይ መሆኗን ያለመረዳት ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ ልክ ከደርግ በኋላ እንደነበረው ሽግግር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የመለስን ያህል ከፍተኛ ስልጣን የነበረው ሰው አለመኖር ብዙ ነገሮችን ሽግግርና ጥያቄ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ ስልጣን የማሸጋገሩና የማጠናከሩ ጉዳይ አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ፍፃሜ ላይ አልደረሠም፡፡ በዚህ ውስጥ በፓርቲው፣ በመከላከያው፣ በፀጥታ ተቋማትም ብዙ ሂደቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሂደቶቹ አንድ መልክና ቅርፅ አልያዙም፡፡ ይህ እንግዲህ የተለያዩ ኃይሎች ፍላጎቶች የሚንጸባረቅበት ስለሆነ እየተከታተሉ ማየት ነው የሚሻለው፡፡

ሎሚ፡- ኤርትራ (በተለይ ኢሳይያስ አፈወርቂ) ከኢትዮጵያ ጋር በኮንፌዴሬሽን የመዋሃድ ሃሳብ እንዳላቸው፣ ሆኖም ግን በኢህአዴግ በኩል ፈቃደኝነቱ እንደጠፋ አቶ አብርሃም ያየሕ በቅርቡ በበተኑት ሠፊ መጣጥፋችው ገልፀዋል፤ አሁንም ሆነ በቀደመው ጊዜ በኤርትራ በኩል እንዲህ ያለ ሃሳብ ቀርቦ ነበር?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- ይሄ ሃሳብ የነበረው በነፃነት ትግሉ ወቅት ነው፡፡ እንዲያውም ህዝባዊ ግንባር ሃርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) የኢትዮጵያን ወይም የደርግን ሠራዊት የማሸነፍ ዕድሉ ብዙም የሚያስተማምን ስላልነበር፣ ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ሲፈጅ ኮንፌዴሬሽንን እንደ አንድ አማራጭ በፖሊሲያቸው ውስጥ ያስገቡበት ሁኔታ ነበር፡፡ የጦርነቱ መልክ ከሽሬው ውጊያ በኋላ ስለተቀየረ ነበር ወደ ግልፅ የመገንጠል አቅጣጫ የገቡት፡፡ አፄ ኃ/ስላሴም ሆኑ የደርግ መንግስት ለድርድር ቀርበው ቢሆን ኖሮ ሻዕቢያ የኮንፌዴሬሽንን አማራጭ ሊቀበል የሚችልበት ዕድል ሠፊ ነበር፡፡ ሆኖም በተጠቀሰው ምክንያት አጀንዳው ተቀየረ፡፡

አሁን እንደገና ሃሳቡ ቀረበ ከተባለም ሌሎች ጉዳዮች መታየት አለባቸው፡፡ አንዳንዴ አቶ ኢሳይያስ የማያደርጉትን የመናገር ነገር ይታይባቸዋል፡፡ ሲያሻቸው ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እንገዛለን ይላሉ፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያ ካልፈረሠች የኤርትራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብሩህ አይሆንም ይላሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጪ ኤርትራ ///// ናት ይላሉ፡፡ አሁን ወደተጠቀሰው ግንዛቤ መምጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ ሃገር ናት፡፡ ለትልቅ ሃገር ደግሞ ክብር ይገባል፡፡ ከዚህች ትልቅ ሃገር ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን ማጠናከር ለኤርትራ ጠቃሚ ነው፡፡ ቢዘገዩም ይሄን መገንዘባቸው በራሱ መልካም ነው፡፡

ከዚያ በፊት ግን በርካታ ነገሮች መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁለቱ ሃገራት እርስ በርሳቸው የሚተነኳኮሡበትና የሚናቆሩበትን ማስቀረት፣ አንዳቸው የሌላኛውን ሃገር አማፂ ቡድን መደገፋቸውን ለማቆም ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ በሁለቱ ሃገራት የመሬት ውዝግብ አለ፤ ኮንዴዴሬሽኑ በዋናው ጉዳይ መተማመን ላይ ከደረሱ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ ኤርትራ ለራሷም ለጎረቤቶቿም ስትል በወሳኝ መልኩ ትጥቅ ማስፈታት አለበት፡፡ ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ወደ ኮንዴዴሬሽኑ መግባት የሚሆን አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ኤርትራ ምን ልትሆን እንደምትችል መገመት አያዳግትም፡፡ ሃሳቡ መምጣቱ መልካም ነው ቢባልም የሚስተካከሉት ጉዳዮች ግን መቅደም ይኖርባቸዋል፡፡
Medhane Tadesse
ሎሚ፡- ኤርትራ የአፍሪካ ቀንድን እንደምታተራምስ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ገልጿል፤ እንደዚህ አይነት ድርጊት ውስጥ ለምን ገባች ይላሉ? የሚፈጠረውስ ትርምስ ራሷን አይጎዳትም?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- ጎድቷታል እንጂ፡፡ የኤርትራ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ጥላቻ እና በቀልን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች በደፈጣ ጥቃት የመገዳደል ባሕል አልተቀረፈም፤ የኤርትራ የውጪ ግንኙነትና የፀጥታ ፖሊሲም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል እንጂ፣ ኃላፊነት የሚሠማውና ጥቅሙን ለማስከበር የሚንቀሳቀስ ሃገር የውጪ ፖሊሲ አይደለም፡፡ ቂም እና ጥላቻው የተፈጠረው ኤርትራ ለራሷ ከነበራት አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡ ኤርትራ ስትፈጠር መሪዎቿ በአፍሪካ ቀንድና በቀጠናው ራሳቸውን አድራጊ ፈጣሪ አድርገው መመልከታቸው የፈጠረው ተጽዕኖ ነው፡፡ ደርግን በማሸነፋቸው ነፃ ሲወጡ ወታደራዊ የበላይነት መጨበጣቸውን እንደ ትልቅ እሴት ይዘው ነበር የተነሱት፡፡ ወታደራዊ የበላይነቱ ተሠሚነት፣ የኢኮኖሚ የበላይነትና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ስለሚያመጣ የኤርትራን ተሰሚነት በዓለም ጭምር ከፍ ያደርግልናል ብለው አመኑ፡፡ ሆኖም ደርግን ያሸነፉት በኢትዮጵያውያን ትብብር እንጂ ለብቻቸው አልነበረም፡፡ ለራሳቸው የነበራቸው ገፅታ ግን የኤርትራን ፖሊሲና ወታደራዊ አቅጣጫ ለመወሰን የሚያበቃቸው አድርገው ወሰዱት፡፡ “አይበገሬነቱን፣ አሸናፊነቱን” የሰበኩለት ወታደራዊ አቅማቸው ግን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ድምጥማጡ ጠፍቶ ዜሮ ገባ፡፡ ዋነኛ መመኪያቸውም በዚያ ጦርነት ተናደ፡፡ ይሕም በጣም ክፉኛ ጎዳቸው፡፡ አሁንም ግን ከዚያ መውጣት አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ የበቀልና የጥላቻ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲን እያራመዱ ነው፤ በኢትዮ-ሶማሊያ ውጊያ የዚያድ ባሬ መንግስት የፈጠረው አይነት የበላይነት ስሜት ነበር ያደረባቸው፡፡ ይሕ አጀንዳቸውና ስነ ልቦናቸው ተሻሽሎ የሚታይ አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎች ጎረቤት ሃገሮች ጋር ለመጋጨት የበቁት፡፡ የኤርትራ መሪዎች እድሜያቸው እየገፋ በመሆኑ አሁን መለወጥ ይችላሉ የሚሉ አሉ፡፡ ይለወጡ እንኳን ቢባል የፖለቲካ አደጋ አለው፡፡ በተለይ “ለህዝባዊ ግንባር ሃርነት ኤርትራ”፡፡

ኢሳይያስ አፈወርቂ ህዝቡን መሳሪያ በማስታጠቅና በወታደሩ በመተማመን ኤርትራ ውስጥ የዴሞክራሲን ለውጥ አፍነው ይዘዋል፡፡ የዴሞክራሲና የሕገ መንግስት ጥያቄ ሲነሳባቸው ይሕንን መግታት የቻሉት “ወረራ ላይ ነን፣ የኤርትራ ደሕንነት ለአደጋ ተጋልጧል፣ አሠብን ሊወስዱብን ነው፣ ነፃነታችንን ልናጣ ነው” የሚለውን ፕሮፓጋንዳ በመጠቀም ነው፡፡ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሠላም ከፈጠሩ በሃገራቸው የዴሞክራሲና የሕገ መንግስት ጥያቄ እንደሚነሳባቸው ያውቁታል፡፡ ይሕንን ደግሞ አይፈልጉትም፡፡ ከመጠን በላይ የታጠቀው የኤርትራ ሠራዊት ወደየቤቱ መመለስ አለበት፡፡ ያንን ለመመለስ አቅሙም የላቸውም፤ የፖለቲካም ስጋታቸው አይሎም በብሔራዊ ውትድርና እና በጦር ሠራዊት ውስጥ የከፋ ብዙ የሠብዓዊ መብት ጥሠት እንዲፈጸም ያደርጋሉ፡፡ ሕዝቡን እንደ ህብረተሠብ ገድለውታል፡፡ የኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥያቄዎችን ማዘግየት የሚችሉት ደግሞ በዚህ በከበባና በጦርነት ስሜት ሲቀጥሉ ብቻ በመሆኑ በዚሁ ገፍተውበታል፡፡

ሎሚ፡- ከዕድሜ መግፋት ባሻገር የኢሳይያስ ጤንነት እንደተቃወሰ ይነገራል፡፡ እንዲያውም ስልጣናቸውን ለወታደራዊ መኮንኖች አለያም ለልጃቸው ለመስጠት እንዳሠቡም እየተገለጸ ነው፡፡ ከኢሳይያስ በኋላ ኤርትራ ምን ልትመስል ትችላለች?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- እንደ ግብፅ እና ሌሎች የሠሜን አፍሪካ ሃገራት ጦር ሠራዊቱ ነው የተደራጀና የታጠቀውን ኃይል የያዘው፡፡ ሆኖም ግን ሠራዊቱንና ህዝቡን መነጠል አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የሠራዊቱ አባል ከሕዝቡ የወጣና ህዝቡ ውስጥ ስለገባ ተቋሙን ብቻውን ነጥሎ ማቆም አይቻልም፡፡ ከአቶ ኢሳይያስ በኋላ ሠራዊቱ የኃይል የበላይነቱን ሊቆጣጠር ይችላል፡፡ ሆኖም ግን እርስ በርሱ የሚግባባ፣ መደበኛ አወቃቀር ያለው ወታደራዊ መንግስት መጠበቅ ይከብዳል፡፡ ከአቶ ኢሳይያስ በኋላ ቢያንስ አራት ከበዛም አምስት የጦር አበጋዞች የሚቆጣጠሩት፣ እርስ በርሱ የሚጋጭ የመሬትና የህዝብ ሽንሸና ይኖራል፡፡ አቶ ኢሳይያስም እያሉ ጄኔራሎች ናቸው ክልሎችን የሚቆጣጠሩትና የሚያስተዳድሩት፡፡ እነዚህ ጄኔራሎች እርስ በእርሳቸው አይስማሙም፤ በተጨማሪም በህገ ወጥና የወንጀል ዝንባሌ ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል፡፡ ከአቶ ኢሳይያስ በኋላ እነዚህ እርስ በራሳቸው የማይስማሙ፣ የተለያዩ አካባቢዎችን የሚቆጣጠሩ፣ ህገወጥ ኢኮኖሚን የሚመሩ የጦር ጄኔራሎች የሚቆጣጠሩት ሃገር ስለሚሆን እንደ ሶማሊያ ባይሆን ተቀራራቢ ነገር የሚታይ ይመስለኛል፡፡ ጄኔራሎቹ እስከ ሲናይ በረሃ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ኤርትራዊያንን በ/// መልክ የሚቆጣጠሩ የጦር አበጋዞች ያሉበት ሃገር ነው፡፡ ወታደራዊ ተቋምን ይዘው የወንጀል ተግባር የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ አሁንም ወንጀለኞች ሆነው፣ ኢሳይያስ በማይኖርበት ጊዜ ደግሞ ነፃ ወንጀለኞች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

ሎሚ፡- ሽብርተኝነት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ስለመሆኑ ከመንግስት ወገን የሚሠጠውን መግለጫ እንዴት ተከታተሉት?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- ሽብርተኝነት የሁሉም ሃገር ስጋት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የተለየ አይደለም፡፡ ምናልባት ኢትዮጵያ ከነበራት ታሪካዊ ቦታ ለአካባቢው ካላት ተፅዕኖ እና የራሱዋን የሃይማኖት ጥንካሬዎች አንፃር ምናልባት አንዳንድ ፅንፈኛ ተመራማሪዎችና አስተማሪዎች አላማ ልትሆን ትችላለች፡፡ በአጠቃላይ ግን ኬንያ እንዳየነው ነው ለዚህ አይነት ነገር የተጋለጠች ነች፡፡ ኢትዮጵያ ጋር የተገናኘ የራሱ መልክ ቢኖረውም እንደዛም ሆኖ ግን ሽብርተኝነት ስንዋጋ መጀመሪያ ውስጣችንን ሠላም ፣ ዴሞክራሲ ቅድሚያ ሠጥተን ነው፡፡ ህዝቡን አሠባስቦ አስፈላጊውን ነፃነትና ፍትህ አስፍኖ፣ የዴሞክራሲ ሞዴ ሆኖ አጠቃላይ ህዝን አንቀሳቅሶ ፅንፈኞችን መዋጋት ደንብ ነው፡፡ ከዛ ውጭ እነዚህን ሁኔታዎች ሳያደርጉ ሽብርተኝነትን እንዋጋልን ማለት ጊዜያዊ ነው፡፡ እንጂ ዘላቂ አይደለም፡፡

ሎሚ፡- ከአመታት በፊት ከመንግስት ጋር (ከፌደራል ጉዳዮች) ጋር ስብሰባ ሲያደር የነበሩ የሙስሊም ማህበረሠብ ተወካዮች በፀረ- ሽብር በህጉ መከሠሳቸውን እንዴት ተከታተሉት?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- እኔ ቀደም ብዬ ካልኩት ጋር ነው የማያይዘው የፀረ ሽብር ህግ የሃገሪቱ የውስጥ ሠላም አንድነት ዴሞክራሲ መንካት የፀረ ሽብር ህጉ የፖለቲካ ምህዳሩን ማጥበብ የለበትም፡፡ የፀረ ሽብር ህጉ የመናገር የመፃፍ የመንቀሳቀስ፣ የመጠይቅ መብቶችን መገደብ የለበትም ይሄ ከሆነ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች የፖለቲካ መጠቀሚያ ነው የሚሆነው ይሄ ላለመሆኑ እርግጠኝ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ብዙ መሻሻል ያለባቸው ህጎች አሉ፡፡ ይቺ ሃር በሠላም፣ በአንድት፣ በዴሞክራሲ ጠንካራ ሆና የምትቀጥልበት መንገድ እነዚህ ሸብበው የያዙ ህጎችን ማፍረስና መለወጥ ይጠይቃል፡፡ ይሄ ለሃገሪቱ ለህዝብም ለመንግስትም አይጠቅምም ይቺ ሃገር የአካባቢውንና የአፍሪካ ጦርነትን ልትጎናፀፍ የምትችለው የራሱን ጤናማ የሆነ የፖለቲካ ሲስተም ልትገነባ ስትችል ብቻ ነው፡፡ በኢኮኖሚ በፓን አፍሪካኒዝም ብቻ መዝፈን አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ መሪነት ወሳኙ የዴሞክራሲ ተምሳሌት መሆን የዴሞክራሲ ተምሳሌት ለመሆን ሠላምን ለማስፈን ዋናው እንቅፋት እንደዚህ አይነት ህጎች ናቸው፡፡ እነዚህ ህጎች መቀየር አለባቸው፡፡ መንግስት ከዚህ ትንሽ አስተሳሰብ ወጥቶ ሠፋ ወዳለው መንገድ ለማሰብ እንደዚህ አይነት ነገሮችን እያሻሻሉ እንቅፋት የሆኑትን በሁደት እየጠረገ መሄድ አለበት፡፡

ሎሚ፡- የአሠብ ወደብ ለኢትዮጵያ የሚሠጥበት አለም አቀፍ ህግ እንዳለ የአለም አቀፍ ህግ ባለሞያዎች ይገልፃሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ደግሞ ይሄን ሃሳብ ለማንሳት የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ ወደብ ሊኖራት አይገባም? ከተቻለስ አሠብን የመመለስ እንቅስቃሴ ማድረግ ይቻላል?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- ወደብ ሊኖራት አይገባም ብቻ ሳይሆንም ኢትዮጵያ የተወሰደባት ወደብ ማግኘት አለባት፡፡ ነበራት ወደም ብዬ ገልጨዋለሁ የአባ ተፋሠስ ጥያቄ የምስራቅ አፍሪካ የብሔርና ቋንቋዎች ስብጥር ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ የወደብ መጠቀም የቀደብ ጥያቄ ዝም ብሎ አንድ መንግስት ስለመጣ የሚቀየር ነገር እንዳይመስልህ አይቀየርም ዘላለማዊ ነው ይሄ እስካልተፈታ ድረስ ሃሮች ሠላማዊ አይሆኑም አካባቢው ከግጭት አይወጣም፣እድገትም የለም፣ ለኢትዮጵያ ኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ለአካባው ሠላምም ቢሆን የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በተለይ ቀይ ባህርን ከወሠድክ የኢትዮጵያን ነገስታት የኢትዮጵያን መሪዎች ጥያቄ ነው፡፡ የቀይ ባህር ጥያቄ የትግራ መሳፍንቶች እንጂ የኤርትራ መሳፍንቶች አያውቁትም ነበር፡፡ ስለሲህ አጀንዳው የኢትዮጵየን ጂኦግራፊው አሁን በወሠነላቸው ሁኔታ ባህሩን ተቆጣጠሩት ማለት የነሱ ሆኖ ይቀጥላል ማለት አይደለም፡፡ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሄ ትልቅ ሃገር ነው፡፡ የባህር በር ጥያቄን ሳትመልስ የኢኮኖሚ እድገት፣ የኢኮኖሚ ትብብር፣አካባቢያዊ ትስስር፣ ሠላም አይገኝም፡፡ ኤርትራዊያንም መገንዘብ አለባቸው ይገነዘቡታል የሚል እነት አለኝ፡፡ አንድ ባህርን ለብቻህ ስለተቆጣጠርክ ጥቅም የለም፡፡ ሰላምም አያመጣም፣ እድገትም አያመጣም ፡፡ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት ለኤርትራዊያን ፍይዳ የለውም፣ የኢኮኖሚ ጠቀሜታውን አይደለም እየወራሁ ያለሁት ለኢትዮጵያ የባህር በር ተዘግቶባት ኤርትራ ለብቻዋ ልተበለፅግና፣ ሠላም ልታገኝ አትችል፡፡ ኃላፊነት የሚሠማው መንግስት እስካለ ድረስ ህዝቡ በዚህ ደረጃ የሚረዳው ነው፡፡ የሚመለስኝ ዝም ብሎ ሽርሽር ጥላቻና በቀል የፈጠፈው ስሜት ነው ጤናማነት ያለው አዕምሮ ለረጅም ጊዜ በትውዶች የሚመነዘር ፖሊሲ ሊሆን አይችልም፡፡

ሎሚ፡- በኢትዮጵያ በተለይ በመንግስት ባለስልጣናት ዘንድ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል የሚባለው ሙስና እንዴት ተመለከቱት? ችግሩን ለማስወገድስ ምን መደረግ አለበት?

ረ/ፕ መድኅኔ፡- ያው እኔ ብዙ ጊዜ እዚህ ስለሌለሁ ይህንን ነገር አላውቀውም ግን ምንድነው አንድ የሚያስፈራኝ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ የማውቃቸው ብዙ የአፍሪካ ሃገሮች እንደ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ ሙስና ለረጅም ጊዜያት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በትንሽ ደረጃ ላይ ነበር፡፡ የእነርሱን የሙስናና የጉዳት ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን የፈጀብን ጊዜ በጣም ፈጠነ፣ በዚህ ፍጥረነት ከተጓዝን ግን በጣም አደገኛ ነው፡፡ ናይጄሪያና ኬንያን የተመለከተ ኧረ የኢትዮጵያ የሙስና ደረጃ ኧረ በ7 አመት ከደረሰበት በጣም አደገኛ ነው እና እኛም ሃገር ያሠጋናል ማለት ነው፡፡ ከነእርሱ በላይ ሌላም ሙስና እንደስርዓት የበላይ ደረጃ ላይ እንዳይደርሰ መቆጣጠር ነው፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ከደረስን በጣም ከባድ ነው፡፡ የበላይነት ብቻ ሳይሆን ሙስና ከፖለቲካ ጋር ከተያያዘ ሌላው ሶስተኛ አደጋ ነው፡፡ አራተኛው ከተሣሠረም ከፍተኛ አደጋ ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ አራት ነገሮች ያሠጉኛል፡፡ ዝርዝሩን ግን አላውቀውም፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s