Archive | January 8, 2014

በጀግኖች አባቶቻችን ና እናቶቻችን ደም ተከብራ የኖርች አገር በክሃዲዎች አትደፈርም።

We Need Freedom

New Picture
ወቅታዊ የአገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ(ኢህአግዘ) የተሰጠ መግለጫ
በጀግኖች አባቶቻችን ና እናቶቻችን ደም ተከብራ የኖርች አገር በክሃዲዎች አትደፈርም። ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላላት ክብር እና ማንነት ጀግኖች አባቶቻችን በከሰከሱት አጥንት እና ባፈሰሱት ደም ነው።
ለጠላት የማይንበረከከው እና ማንንም የማይፈራው የኢትዮጵያ ጀግና ከፋሺስት ኢጣልያ ጋርም ቢሆን አንገት ለአንገት ተናንቀው በጦር በጎራዴ ይችን ሃገር ባላት ቅርጽና ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ አቆይተዋታል። አሁን ግን የደም መስዋእትነት የተከፈለበትን ይህንን መሬት ሃገር እናስተዳድራለን ባሉ ወረበሎች ስትበጣጠስ እና ስትቆራረስ ማየት ያማል።
ይቺ ሀገር ባንዲራዋ በየ ዳር ድንበሩ የተውለበለበላት ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ባንዲራዋን ጨርቅ ሳይሉ በደማቸውና ባጥንታቸው አጥር አጥረው ያኖርዋት ፣ ጀግኖች አትሌቶች ድል አድርገው ላባቸውን እና እንባቸውን እያወረዱ ባንዲራውን ከፍ አርገው የሚያስከብርዋት ፣ ሃገር ማለት ባልታወቀ ሰንሰለት ከልብ ጋር የታሰረ የማትተው፣ የማትሰለች ፣ ካንቺ በፊት እኔን ያርገኝ የተባለላት ፣ በፍቅርዋ ተነደፈው ስንቱ በብእራቸው የተቀኙላት፣ በድምጻቸውም የፎከሩላት ፣ ሰአሊው በቡርሹ ቀባበቶ ያሳመራትን ሃገር የወያኔ ወረበላ ቡድን ኤርትራን አስገንጥሎ ለሻብያ መስጠቱ ሳያንሰው ዛሬ…

View original post 423 more words

ከኦነግ ጋር በተያያዘ ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል 45ቱ በእስራት ተቀጡ

 

Fird Bet

    • በአሸናፊ ደምሴ/ ሰንደቅ ጋዜጣ

በትምህርት ተቋማት ላይ ቦምብ በማፈንዳት፤ በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ላይ በደረሰው የ2 ሚሊዮን ብር ዝርፊያ በመሳተፍ፣ አብያተ-ክርስቲያናትን በማቃጠል፣ አባላትን በመመልመልና አመፅ በማነሳሳት የኦሮሚያ ፌዴሬሽንን ከህገ-መንግስቱ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ከኢትዮጵያ ግዛት ለመገንጠል ሲንቀሳቀሱ ይዣቸዋለሁ ሲል የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ ክስ ከመሰረተባቸው 69 ተከሳሾች መካከል 45ቱ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከ3 እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሲቀጡ 18 በነፃ ተሰናበቱ።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ከትናንት በስቲያ (ሰኞ) ባስቻለው ችሎት፤ የፈፀሙት ድርጊት በንባብ ሲቀርብ እንደተሰማ ነው ተከሳሾቹ በኬኒያ፣ በሶማሊያና በኤርትራ በመዘዋወር የጦር ስልጠናን በመውሰድና የአባላትን ቁጥር ለመጨመር ከመስራት በተጨማሪ በሀገር ውስጥና በውጪ ከሚገኙ ሰዎች የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ወይም ኦነግ ለተሰኘውና መንግስት አሸባሪ ብሎ በሰየመው ቡድን ስም የገንዘብ ዝውውር ሲያደርጉ እንደነበር ተዘርዝሯል።

በተለይም 1ኛ ተከሳሽ ተሻለ በከሺ፤ በ1998 ዓ.ም በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ላይ በተካሄደው ዝርፊያ ከግብረአበሮቹ ጋረ በመሳተፍ መንግስት 2 ሚሊዮን ብር እንዲያጣ ከማድረጉም በተጨማሪ በአንድ ትምህርት ቤት ላይ ቦምብ በመወርወር ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል። ሌላኛው ተከሳሽም በኦሮሚያ ቆሬ መንደራደዩ በሚባል አካባቢ ከኦነግ አባል በተሰጠ ትዕዛዝ በ1996 ዓ.ም አብያተ ክርስትያናትን አቃጥለው ሰው ገድለዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝሩን ያስረዳል። ተከሳሾቹ መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ በማሴር፤ ገንዘብ በማሰባሰብና መሳሪያ በመግዛት፤ አባላትን በመመልመልና በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት የሽብር ቡድኑን አላማ በመደገፍ ሲንቀሳቀሱ ነበር ሲል ዐቃቤ ሕግ ያስረዱልኛል ያላቸውን ከሃምሳ በላይ የሰውና የሰንድ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

የግራ ቀኙን ሀሳብ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሾቹ የፈፀሙትን ወንጀል ያብራራው የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ የደረሰውን ውድመት በዝርዝር የሚያሳይ ካለመሆኑ መነሻነት የወንጀሉን ደረጃ መካከለኛ ነው ሲል ያስቀመጠው ሲሆን፤ ይህም ቢያንስ እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት ያስቀጣ እንደነበር በማስታወስ ተከሳሾቹ ያቀረባቸውን በርካታ የቅጣት ማቅለያዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የቅጣት ውሳኔው መዘጋጀቱን አትቷል።

ሰኞ ዕለት የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎትም ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በአግባቡ ካየ እና የተከሳሾቹንም የመከላከያ ማስረጃዎችና የቅጣት ማቅለያዎችን ከመረመረ በኋላ ቀደም ላለው ጊዜ 18 የሚሆኑትን ተጠርጣሪዎች ነፃ ናችሁ ሲል በብይን ያሰናበታቸው ሲሆን፤ የሁለት ተከሳሾች ጉዳይ ደግሞ ለብቻው ተነጥሎ በመታየት ላይ ነው ሲል አስረድቷል። በተቀሩት 45 ተከሳሾች ላይም የጥፋተኝነት ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ከ3 እስከ 12 ዓመታት በሚደርስ ፅኑ እስራትና 40 በሚደርሱት ላይም ከ2 እስከ 3ዓመት የሚደርስ የህዝባዊ መብት እገዳ ጥሎባቸዋል።

ምንጭ ሰንደቅ ጋዜጣ

የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ወታደራዊ ጥቃት ፈፀመ

በሀገራችን ላይ የተንሠራፋውን አምባገነናዊ ሥርዓት ገርስሶ ለመጣል የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የትጥቅ ትግል በማካሄድ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ የሚወስዳቸውን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃዎች አጠናክሮ በመቀጠል በታህሳስ 23 ቀን 2006 ዓ/ም በሰሜን ጎንደር በላይ አርማጭሆ ወረዳ ልዩ ስሙ ገራርዋ ባምብላ ወንዝ በተባለው ቦታ መሽጎ የአካባቢውን ህብረተሰብ ሲያሰቃይና ሲያንገላታ ከነበረው የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር እና ከፀረ-ሽምቅ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ባደረገው ውጊያ 24 የጠላት ወታደሮችን ገድሎ 11 በማቁሰል የግንባሩ ሠራዊት አንፀባራቂ ድል አስመዝግቧል፡፡ በዚሁ ዕለትም በተደረገው እልህ አስጨራሸ ውጊያ የወያኔ 24ኛ ቴዎድሮስ ክ/ጦር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የሚደርስበትን የተኩስ ናዳ መቋቋም ተስኖት ሙትና ቁስለኛውን እያዝረከረከ እግሬ አውጪኝ በማለት መፈርጠጡን ታውቋል::

ይህ በእንዲሀ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት በጠላት ላይ ባስመዘገበው ከፍተኛ ወታደራዊ ድል መደሰታቸውና ወደፊትም ሀገራዊና ሕዝባዊ አላማን አንግቦ የህብረተሰቡን እምባ በማበስ ግንባር ቀደም በመሆን ለሀገርና ለወገን ደራሽነቱን እያስመሰከረ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊትን በመደገፍ የቆመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ግንባሩ በተከታታይ ጊዜያቶች የሚወስዳቸው ወታደራዊ ጥቃቶችና የሚያስመዘግባቸው አንፀባራዊ ድሎች የወገንን አንጀት በማራስ በአንፃሩ ደግሞ የጠላትን አንገት በማስደፋቱ እጅግ ደስተኛ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም የአካባቢው ህብረተሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የጀግና አቀባበል ያደረጉለት ሲሆን ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከግንባሩ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡debirhan.com

16 things you may not know about Ethiopia

ethiopia

Delightful reading at: Ethiopian Folk Tales

1) In Ethiopia it is now 2006, we use the Julian calendar with 13 months a year. New Year’s Day is on 11th September and theye celebrate Christmas on 7th January. Each of 12 months all have 30 days, the balance of 6 or 7 days depending whether it is a leap year is the 13th month
2) As Ethiopia is near the equator it gets daylight at 6am and dark by 6pm every day all year. We tell the time as 12 hours by day and another 12 hours for night. 7am is then 1 o’clock day, 8pm is 2 o’clock night. Arranging a meeting can be confusing!
3) The oldest humanoid skeleton dated over 6 million years ago, is from Ethiopia.
4) Frankincense comes from Ethiopia. One of the three kings to witness Jesus birth is reputed to have been an Ethiopian, bringing the Frankincense.
5) There were Jews living in Ethiopia centuries before Christ and Christianity came to Ethiopia in the third century AD. The original Ten Commandments or Holy Ark of the Covenant is reputed to be in Axum, Northern Ethiopia – where it is closely guarded.
6) Lalibela, deep in the mountains in the centre of Ethiopia country, has a collection of eleven 13th century underground rock-hewn churches – reputedly built by many angels. A World Heritage site often termed the eighth wonder of the world.
7) Ethiopia was the only African country to defeat an European power (Italy) in the 1896 “Scramble for Africa” . Ethiopia is the oldest independent African state & was never colonised.
8) Ethiopia is as big as France & Spain together, with an estimated population of over 80 million – although reputed to have more livestock.
9) Half of the country is mountainous and over 6,000 feet – that is twice as high as the highest mountain in the UK, Ben Nevis. Other parts are actually below sea level.
10) Before Emperor Haile Selassie was crowned, he was called Duke (Ras) Tafari. This is the source of the name of the Rastafarians, who revere him as the direct descendant of King Solomon. “Haile Selassie” means Holy Trinity. 11) The alphabet used in Ethiopia is derived from Hebrew and Sabean and is called G’eez. It has nearly 300 letters – including seven vowels. All spelling is phonetical.
12) The Queen of Sheba journeyed from Ethiopia in the 9th Century BC to see King Solomon in search of knowledge and is recorded as saying “Learning is better than treasures of silver and gold, better than all that has been created on earth…and afterwards what can be compared to learning?”
13) The Greeks and Persians called Ethiopians the “Habasha” meaning the burnt people. An earlier name for Ethiopia was Abyssinia (said to be derived from Habasha), meaning land of the burnt people.
14) Coffee, grown on trees, originated in Ethiopia – in the region of Kaffa.
15) The Blue Nile rises in NW Ethiopia joining the White Nile (from Uganda) at Khartoum, Sudan and providing over 85% of all the water in the Nile flowing through Egypt.
16) In 14 Nov 1879 Ethiopian Prince Alemayehu, (orphaned son of Emperor Tewodros) died in Leeds, UK allegedly of pneumonia. He was being cared for by Queen Victoria and is the only non British royal to be buried in the Royal Chapel at Windsor Castle.

ቴሌ ከቻይናው ዜድ ቲ ኢ እና ከሃዋዊ ጋር ያደረገውውል ከፍተኛ ትችት ቀረበበት

1174818_622638514434901_856846903_n
ቴሌ ከቻይናው ዜድ ቲ ኢ እና ከሃዋዊ ጋር ያደረገውውል ከፍተኛ ትችት ቀረበበት
የአለማችን ከፍተኛው ተነባቢ የቢዝነስ ጋዜጣ ወል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው የሞባይል ኔት ወርክ ችግር መሰረታዊ ምክንያቱ ከሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ጋር የተደረገው ስምምነት ግልጽነት የጎደለው መሆኑ ነው።
የአለም ባንክ የምርመራ ክፍል ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ መንግስት የራሱን የግዢ መስፈርቶች መጣሱን ገልጿል።
መንግስት በኩባንያዎች መካከል በቂ ወድድር እንዲኖር የማድረግ ሃላፊነት ቢኖርበትም ይህን ሃላፊነቱን ባለመወጣት ከቻይናው ዜድ ቲ ኩባንያ ጋር የረጅም ጊዜ ኮንትራት ተፈራርሞአል።
በ2013 የወጣ የአለም ባንክ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ከዜድቲ ጋር ኩባንያ ጋር ያደረገውን ስምምነት እንዲፈትሽ ጠይቋል።
መንግስት በቅርቡ ከዜድቲ ጋር ብቻ የነበረውን ኮንትራት በማቋረጥ፣ ከዜድ ቲ ኢ እና ሃዊይ ከሚባለው ኩባንያ ጋር አዲስ ውል ተፈራርሞአል። የዜድ ቲኢ የኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ጂያ ቼን በአገሪቱ የኔት ወርክ ችግር መኖሩን ቢገነዘቡም ፣ ችግሩ የተፈጠረው በመስመሮች መቆራረጥ፣ ቴሌ በቂ ጥገና ባለማድረጉና የአሌክትሪክ ሲቲ አቅርቦት ችግር ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የዜድ ቲን ወጪ ለመሸፈን ከፍተኛ የሆነ የሞባይል ዋጋ እንደሚያስከፍል ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ቴሌን በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ስራ አስኪያጆች አሁን የሚታየው የኔትወርክ ችግር እንዳይፈጠርና ቴሌም ሙሉ በሙሉ በአንድ ኩባንያ ስር እንዳይወድቅ መሟገታቸውን ለጋዜጣው ገልጸው ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ግን ሊቀበሉት ፈቃደኛ አልነበሩም ብለዋል።
የመንግስት ከፍተና ባለስልጣናት የቀድሞ የቴሌ ባለስልጣናት ከዜድቲ ጋር የተደረገውን ውል እንዳያጋልጡ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ይህንን ተከትሎም ወደ እስር ቤት እንደላኩዋቸው ጋዜጣው ዘግቧል።

“ከሀብታም ቤት ጥብስ፣ ከድሀ ቤት ጥቅስ…”

  • Written by  ኤፍሬም እንዳለ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ ልደቱ ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁማ!
እንግዲህ የበዓል ሰሞን አይደል… ያው ያለው “ፏ!” ይላል የሌለው “ዷ!” ይላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን ስሙኝማ…እሷዬዋ የዓመት ፈቃድ ነገር ወጣችና ሰው ሳያያት ከረምረም ብላ ትመጣለች፡፡ እናላችሁ… ስትመጣ ‘የቅቤ ቅል’ መስላ፣ ተመችቷት ነበር፡፡
ታዲያላችሁ… ወዳጆቿ “እንዴት ነው ነገሩ እንዲህ ያማረብሽ፣ ምን ተገኘ?” ምናምን ይሏታል፡፡ እሷም ከሀብታም ዘመዶቿ ዘንድ እንደ ከረመች ትነግራቸውና…ልጄ፣ “ከሀብታም መጠጋት ነው የሚያዋጣው…” ትላለች፡፡ እነሱም “ሀብታም ምን ያደርግልሻል፣ ይልቅ ከቢጤዎችሽ ከእኛ ጋር መሆኑ ነው የሚያዋጣው…” ምናምን አይነት ‘የክብር ማስጠበቂያ’ ክርክር ያመጣሉ፡፡
እሷም እነሱ ቤት የምታገኘውንና ሀብታም ቤት የምታገኘውን ልዩነት ስትነግራቸው ምን ብትል ጥሩ ነው… “ከሀብታም ቤት ጥብስ፣ ከድሀ ቤት ጥቅስ አይጠፋም፡፡”
የእውነት እኮ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ጥቅስን የመሰለ ‘ቀን አሳላፊ’ አለ እንዴ! ልክ ነዋ…ኪሳችን ተራግፎ ውስጡን ብል ሲበላው፣ “እንዴት አደራችሁ” ለማለት ሂሳብ የምንጠየቅ እየመሰለን ስንሳቀቅ፣ ዕድሜ ለጥቅስና ለተረት…ምን እንል መሰላችሁ…“ያጣም ያገኝና ያገኘም ያጣና፣  ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!” አለቀ፡፡ በተረት መልክ የመጣ ‘ፓራሲታሞል’ በሉት! የዚችኛዋ ተረት ኮሚክነቷ ምን መሰላችሁ…ይኸው “…ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!”  ስንል ስንት ዘመናችን ሆኖ…አለ አይደል…. የምንታዘበው እስኪመጣ ገና እየጠበቅን ነው!
ልጄ እንደ ዘንድሮ ከሆነ…አይደለም ቁልቁል መውረድ፣ ላይ የወጣው ሁሉ “ባትጋሩኝ!” እያለ ‘ገዢ መሬቱን’ እያጠናከረ ‘በእኛ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት’… ከተረታችን ጋር ረስተውናል፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን አንድ የምትገርመኝ ተረት አለች…“ሀብታም ለሰጠ የድሀ እንትን አበጠ” ምናምን የምትል፡፡ አሁን…ጭንቅላት፣ ትከሻ፣ አንገት የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎች እያሉ…አለ አይደል… እዛ ድረስ ‘ቁልቁል’ መውረድ ለምን አስፈለገ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“ያጣም ያገኝና…” የሚለውን ለመሞከር ችግሩ ምን መሰላችሁ…መሰላሉ የለማ! ‘ብልጦቹ’ መሰላሉን ከወጡበት በኋለ  ገፍተው ከመሬት ያጋድሙታል መሰለኝ፣ መሰላል አጥቶ የሚንከራተት መአት ነው፡፡ በእርግጥ ሲወረድ በምን እንደሚወረድ ራሱን የቻለ ጥያቄ ቢሆንም ገና ለገና ስለ‘መውረድ’ አይወራም፣ እዚህ አገር እኮ ያለውም የሌለውም ኑሮን በኪሎ ሜትር ማስላት ትቶ በሚሊ ሜትር እየደመረና እየቀነሰ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንዳወራነው አንዳንዴ ሰዉን ስታዩት “ነገ” የሚባል ነገር የሌለ ነው የሚመስለው፡፡
“መሰላሉን ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ…” ምናምን የሚል ዘፈን ይቀናበርልንና በየኤፍ.ኤሙ. ኮምፐልሰሪ ምናምን ነገር ይሁንልን፡፡ (ልክ ነዋ… ኤፍ.ኤሞችን ስናዳምጥ አንዳንድ ጊዜ ዘፈኖች ብቻ ሳይሆኑ ዘፋኞቹም ‘ቢያንስ አንዴ’ እንዲሰሙ ሰርኩላር ነገር ያለ እየመሰለን ቸግሮናላ!)
እናማ…እኛ ግን ጥቅስ መጥቀሳችንን፣ ተረት መተረታችንን እንቀጥላለን፡፡ ልክ ነዋ…ያለመሳቀቅ ልንጠቀምባቸው ከምንችልባቸው ነገሮች መሀል ዋናዎቹ ጥቅሶችና ተረቶች ናቸዋ! ለዛውም ቢሆን ‘ኤዲት’ የተደረጉትን!
እና እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ…የሆነ ዝም ያለ ነገር አልበዛባችሁም! ልክ ነዋ…የሚጮህ ነገር ቢኖር፣ ወይ አዲስ የመዝሙር አልበም ሲያስተዋውቁ፣ ወይ “ሎተሪ ግዙ” ስንባል፣ ወይ “ለአቶ እከሌ መታከሚያ የአቅማችሁን አዋጡ…” ምናምን ሲባል ነው፡፡ መአት የምንነጋርባቸው ከእለት ኑሯችን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን … ነገርዬው ማን ማንን አምኖ ይናገራል ነው ነገሩ፡፡ እንደ ድንገት አምልጦን ሹክ ያልነው ነገር፣ ዙሪያውን ተሽከርክሮ በመጨረሻ ለእኛው ሲነገረን… አለ አይደል…
“ተናግሮ አናገረኝ ይወደኝ ይመስል፣
ሄዶ ተናገረ የላኩት ይመስል”
ብለን እንተርታለን፡፡ አሁን ‘መተረት’ ባንወድ ኖሮ ይቺን ማደንዘዣ ከየት እናገኛት ነበር! እንኳንስ ቤታችን ጥቅስ አልጠፋ!
ያቺ የለመድናት…
“ከእንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ፣ ከአፍ የሚለቅም”
ብለን ተርተን ‘ጭጭ’ ነው፡፡ ምን ይደረግ…‘ሄዶ ተናጋሪ’ ሲበዛ ከቤታችን ‘የማይጠፋውን ጥቅስ’ ለቀም አድርገን ማስታገሻ እናደርገዋለን፡፡
“ዝምታ ለበግም አልበጃት
አሥራ ሁለት ሆነና አንድ ነብር ፈጃት”
የምትለው ተረት…አለ አይደል…የሆነ እርፍና ነገር ቢኖራትም ያለችው ግድግዳችን ላይ ሳትሆን እንጨት ሳጥናችን ውስጥ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…አለ አይደል… “የዛሬውን አያድርገውና…” እያልን በሉካንዳ በኩል ባለፍን ቁጥር በናፍቆት ‘ሽንጥና፣ ታናሽ’ ላይ ዓይኖቻችንን እንተክላለን፡፡ አሀ… መቶ ብር ሦስት ኪሎውን ‘ሻሽ የመሰለ’ ሥጋ ከፋሽኮ ቪኖ ጋር ገዝተን ለቡና ይተርፈን የነበረበት ጊዜ ትዝ ይለናላ! አሁንስ?…አሁንማ ፓሪስ የሚታየው የፒካሶ የስዕል ዓውደ ርዕይና ዶሮ ማነቂያ የሚታየው የሥጋ ‘ዓውደ ርዕይ’ አንድ ሆኖብናላ! ብናጉረመርም ምን ይፈረድብናል! ይሄኔ ነው ተረት የማስታገሻ ሚናዋን የምትወጣው…
“ቁርበት ምን ያንጓጓሃል ቢሉት ባያድለኝ ነው እንጂ የነጋሪት ወንድም ነበርኩ አለ”
የምንንጓጓ ቁርበት መሆናችንን ብቻ አትዩብና! የእውነት ግን እኮ ብዙዎቻችን የምር ቁርበቷን መስለናል! እነ እንትና…ምነው ደብዘዝ አላችሁብኝሳ! ችግር አለ እንዴ!
እናላችሁ… እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ…መቼም ሁልጊዜ እንደምንለው ዘንድሮ እርስ በእርስ መተማመን ቀንሶ የለ! እናላችሁ…አይደለም የማናወቀው ሰው ሲያደናቅፈው “እኔን ድፍት ያድርገኝ…” ምናምን ሊባል የቅርባችን ሰው እንኳን አደናቅፎት ሲንገዳገድ “አንተ ሰውዬ ጭራሽ ደንባራ ሆነህ ቀረኸው…” ምናምን መባባል እየለመደብን ነው፡፡ እናላችሁ…“እባክህ አንድ ችግር ገጥሞኝ…” ለሚለው ሰው እኔ ወንድምህ እያለሁ ምናምን ከማለት ይልቅ…ችግሩ ይጋባብን ይመስል እንሸሻለን፡፡ እናማ ዕድሜ ለ‘ተረት ወዳጅነታችን’… ተረት አናጣለትም…
“ውሀ ለሚወስደው ሰው በትርህን እንጂ እጅህን አትስጠው”
እንልና…በትርም ስሌለን “እንደ ፍጥርጥርህ…” ብለን እንተወዋለን፡፡
ስሙኝማ… የጥቅስ ነገር ካነሳን ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ በብዛት እናያለን፡፡ በእርግጥ መልካም ያልሆኑ በተለይ ሴቶች ላይ የሚጠነክሩ ጥቅሶች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሪፎች አሉ፡፡ አንድ ወዳጄ ያያት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ…“የከፋው ሲሞት፣ የደላው መች ቀረ፡፡” ይቺ ዝም ብላ የምትመስል ጥቅስ ውስጧ መአት ነገር አላት፡፡ ዘመናችንን የምታሳይ አይመስላችሁም! ‘ስለደላቸው’ ብቻ ሰማይን ለመርገጥ የሚቃጣቸው በበዙበት ዘመን…አሪፍ ጥቅስ ነች፡፡
እኔ የምለው…‘አንደርግራውንድ’ መነጣጠቅ እንዲህ ለየለት ማለት ነው! የምንሰማው እኮ አንዳንዴ…“እነ ስቴፈን ስፒልበርግ ስንት ታሪኮች አምልጧቸዋል…” ያሰኛል። ታዲያ…እንደው ተገኘ ተብሎ…አለ አይደል…ጨዋታው የፊፋንም፣ የካፍንም ሆነ የማንንም ህጎች የማያከብር ይሆንና ‘አራቱን ወር’ ሲደፍን ቁልጭ ነዋ! ይሄኔ ዕድሜ ለተረቶች ወዳጅነታችን…ህመም ማስታገሻ አናጣም…
“ለፍቅር ብተኛት ለጠብ አረገዘች”
እንላለን፡፡ ከዛ ጠብ ይመጣል፡፡ ሁለቱም “የመውደድ መድሃኒት…” ምናምን ሲሉ የቆዩትን “አንተ ነህ…” “አንቺ ነሽ…” ነገር ይመጣል፡፡ ይሄኔ ለተረትና ጥቅስ ምስጋና ይግባውና ምን ይላል መሰላችሁ…
“ያንቺን አትበይ ገንዘብ የለሽ
የሰው አትበይ ምግባር የለሽ”
እናላችሁ… እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…የሆነች እንትናዬን ‘ኪሶሎጂ ለማጦፍ’ ስትፈልጉ እንዲህ ትሏታላችሁ…“ሕይወት ምንድነች? ሕይወት ፍቅር ነች፡፡ ፍቅር ምንድነው? ፍቅር መሳሳም ነው፡፡ መሳሳም ምንድው? ጠጋ በዪኝና ምን እንደሆነ ላሳይሽ፡፡” አሪፍ አይደል! እኔም በ‘ፌስቡክ’ ያገኘሁትን ‘ሼር’ ላድርግ ብዬ ነው!
ሌላ ‘ሼር’ እንዳላደርጋችሁ ደግሞ አንድ ተረት ትዝ አለችኝ…
“ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡”
አለቀ፡፡
እናላችሁ…እንኳንም በእኛ ቤት ‘ጥቅስ’ አልጠፋ። የ‘ጥብሱ’ ያለመኖር ‘ወና ያደረገውን’ ባይሞላውም… ማስታገሻ ይሆነናላ!
መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

ዋናውን “ሌባ” ማን ይከሰዋል?

 

አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የ“ሰው” ንግድ!

ethio human trafficking

 
 

ኢህአዴግ ልዩ ምክንያት ከሌለው በስተቀር የውጪ ጠላት አያፈራም የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ምክንያት ካለው ግን ቅንድቧን አንደተላጨችው ነገረኛ ሴት ለመጋጨት ይፈጥናል። ከፊትለፊቱ ገንዘብ ካየ ደግሞ ኢህአዴግ ገደል ሜዳው ነው የሚሉም አሉ። ገንዘብ በሌለበት ቦታ ኢህአዴግ አይታይም በማለት ከበረሃው ኑሮ ጀምሮ የሚከሱት ጥቂቶች አይደሉም። በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ ምድር በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚሰቃዩትን ወገኖች አስመልክቶ የያዘው አቋምም ከዚሁ መርሁ የተቀዳ እንደሆነ የሚከራከሩ በርካታ ናቸው። “ምን ያድርግ የኖረው የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ ተቆልለው እሱ ላይ ወደቁ” በማለት ኢህአዴግን ለኢትዮጵያ የተቀመጠ “የተቀባ” መፍትሔ አድርገው የሚያወድሱ አሉ።

ኳስ ሜዳ ያደገችው ኑሪያ መሐመድ አሁን የምትኖረው ኳታር ነው። ኑሮ እንዳሰበችው የተመቻቸ ባይሆንላትም ወደ አገርዋ ለመመለስ አትፈልግም። አታስበውም። “ኢትዮጵያ ምን አለ?” ከማለቷ በቀር ለምክንያቷ ብዙ ማብራሪያ መስጠት አትፈልግም። አገሯ እሷንና መሰል ወገኖቿን ለማኖር አልቻለችም። በኳታር ባይመቻትም የታናናሽ እህቶቿንና የምትወዳቸውን እናቷን ጉሮሮ መሸፈን የሚያስችላትን አቅም አግኝታለች። ይህ ለእርሷ ታላቅ በረከት ነውና ችግሯን በበረከቷ እያዋዛች ትኖራለች። በኳታር በረሃ!!

ኑሪያ ኳታር የሄደችው አሜሪካን ግቢ በሚገኝ አንድ የጉዞ ወኪል ቢሮ ውስጥ ሰዎችን ወደ አረብ አገራት የመላክ ህጋዊ ፈቃድ አለው በተባለ ሰው አማካይነት ነው። የላካትን ሰው በአካል አታውቀውም። ቢሮውንም የረገጠችው የመጓጓዣ ቲኬትና ሰነዶቿን ለመቀበል ብቻ ነው። በወቅቱ እዛው ቢሮ ወደ ሳዑዲ ለመሔድ በዝግጅት ላይ የነበረች እህት ተዋውቃለች። ልጅቷ ከደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ የመጣች ነበረችና ቤቷ ወስዳ ጋብዛታለች። በዚያው በመሰረቱት ጓደኝነት ከያሉበት ሆነው ይጠያየቁ ነበር። እድሜ ለጊዜና ለስልጣኔ!!

ኑሪያ እንደምትለው ጓደኛዋ ወደ ጅዳ ለመሄድ እንደትችል ቤተሰቦቿ የሚያርሱባቸውን ሁለት በሬዎች ሸጠዋል። ገንዘብ በአራጣ ተበድረዋል። አሁን የተፈጠረው ትርምስ ከመከሰቱ ስድስት ወር በፊት በህጋዊ መንገድ ሳዑዲ አረቢያ ሄዳ የነበረችው ጓደኛዋ “ህገወጥ” ተብላ ተመልሳለች። ቅድሚያ እቅዷ ለቤተሰቦቿ ሁለት በሬዎች መግዛትና የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል ሲሆን፣ በየደረጃው ሌሎች እቅዶችም ነበሯት።

ሁሉም እንደታሰበው ሳይሆን ቀረና የኑሪያ ጓደኛ እዳ ተሸክማ ቤተሰቦቿ ዘንድ ገባች። በሬዎች የሉም፣ እዳ አልተከፈለም። አርሶ ለመብላትም አልተቻለም። ኑሪያ ስለ ጓደኛዋ ብዙ ተናግራለች። በኳታር ከምትኖር ሌላ ጓደኛዋ ጋር በመሆን የአቅሟን ለመርዳት ሞክራለች። ወደ ፊትም ከእህቶቿ ለይታ እንደማታያት ገልጻለች። መንገዱ ካለም “ከኢትዮጵያ የማይሻል ነገር የለምና እወስዳታለሁ” ብላለች።

የሚገርመው የኑሪያ ጓደኛ በህጋዊ መንገድ የላካት ድርጅት ዘንድ ስትሄድ የተሰጣት መልስ ነው። በስም የጠራችውና እሷን የላካት ሰው የለም። ድርጅቱ የጉዞ ወኪል ሆኖ ይሰራል። ሰውየው ግን የለም። ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄ ለተመሳሳይ ድርጅቶች ያቀርባሉ። ላኪዎቹ የውሃ ሽታ ሆነዋል። መልስ የለም … እንቆቅልሽ!!

ባለኮብራዎቹ ሰው ነጋዴዎች

ባለ ኮብራዎቹ የጉዞ ወኪል ድርጅት ባለንብረቶች ናቸው። ለጸሎት ወደ ጅዳ የሚሄዱትን መንገደኞች በኮታ እየተከፋፈሉ የጉዞ ቲኬትና ማረፊያ በማዘጋጀት ብር ሲያመርቱ ኖረዋል። ከአንድ ሰው እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ ንጹህ ትርፍ ያተርፋሉ። ስለ ስራው የሚያውቁ “ዝርፊያ” የሚሉትን ስራ ህጋዊ ለማድረግ በማህበር ተደራጅተው ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ፣ እንዲሁም የኦዲት ኮሚቴ አቋቁመው ኢህአዴግ ህጋዊ እውቅና አጎናጽፏቸዋል።

infinitiወደ ሳዑዲ ለጸሎት የሚደረገው ጉዞ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገላበጥበት በመሆኑ በማህበር የተደራጁት ነጋዴዎች ሳዑዲ ድረስ በመሄድ ለጸሎት የሚሄዱ ምዕመናን የሚያድሩበትን፣ ስለ አጠቃላይ የጉዞ ኮታና ስለ ጉዞ መስፈርቶች ከመንግሥት አካላት ጋር ይነጋገራሉ፤ ያቅዳሉ። አንዳንዴም የመጅሊሱን ስራ ይሰሩለታል። የኢህአዴግንም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስራ ያከናውኑለታል። በዚህ ያልተገደበ የስልጣንና የስራ ደረጃቸው ባከማቹት ሃብት ተብለጭልጨዋል። የሚያሽከረክሩት ኮብራ ነው። አንዳንዶቹ ፊታቸው የሚፈርጥ ይመስላል። ኑሯቸው የተቀናጣ ሲሆን ከትምህርት ጋር ብዙም የሚዋደዱ አይመስሉም። የሃብታቸውን መጠን በልጆች ብዛት፣ በዘመናዊ መኪናና በሌሊት የዝግ ቤቶች በመመንዘር ከማሳየት የዘለለ የሚስብ ነገር የላቸውም። ሰውነታቸው ግዙፍና አብዝተው ጫት የሚጠቀሙ የሺሻ ወዳጆች ናቸው። ቢሯቸው ውስጥ ለእለት ጉርስ ሳይሆን “ሱስ” የሚሆኑ ቁሳቁሶች አሉ። በዚህ መካከል በድንገት በተደረገ የመጅሊስ ሹም ሽር መሰረታቸው ቆዳ ንግድ የሆነው ሃጂ ኤሊያስ ሬድዋን ወደ መጅሊስ ተመርጠው ገቡ።

ሃጂው ንግዱን ከውጪ ሆነው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት የመጅሊሱን ወንበር እንደተቀመጡበት አፍታም ሳይቆዩ ዘመቻ “የጉዞ ወኪል” ጀመሩ። ጉዞ ወደ ጅዳ አድርገው ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር መከሩ። አዲስ መስመር ዘርግተው መጡና ከማህበራዊ ጉዳይ ጋር ስትራቴጂ ነደፉ። ጎን ለጎን በዘመዶቻቸው ስም የጉዞ ወኪል ድርጅቶችን ከፈቱ።

ዳግም ወደ ሳዑዲ በመሔድ ራሳቸው በዘመድ አዝማድ ስም ከፍተዋቸዋል ለተባሉት ስምንት የሚደርሱ የጉዞ አመቻች ድርጅቶችና ቁጥራቸው በጣም ውስን ከሆኑ ሌሎች የቀድሞ ድርጅቶች በስተቀር የተቀሩት ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በመጅሊሱ ሰም ከስምምነት ላይ ደረሱ። ሳዑዲ ድረስ በመሄድ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ባካሄዱት የፊርማ ስምምነት የቀድሞዎቹን የንግዱ ፈጣሪዎች አራገፉዋቸው። ድርጊቱና ውሳኔው ድንጋጤ ፈጠረ።

በድንገት የገንዘብ ምንጫቸው የደረቀባቸው ባለኮብራዎቹ በግልና በድርጅት ተሯራጡ። ሃጂ ኤሊያስ ሙሉ የኢህአዴግ ድጋፍ ስለነበራቸው የሚነቀንቃቸው ጠፋ። አሸነፉ። ንግዱንም አስተዳደሩንም ተቆጣጠሩት። ያለ ከልካይ ብር ያመርቱ ጀመር። አምርተው የሚያቋድሱት የማይገፋ ሃይል ስላደራጁ እሳቸውን ለማሳጣት የሚደረጉ ሙከራዎች መዝናኛዎቻቸው ሆኑላቸው። በጉዳዩ ዙሪያ ሚዲያዎች ሲጠይቁዋቸው ያረገፉዋቸውን የቀድሞ ቱጃሮች አፈር ከመሬት እያስገቡ ከመናገር ውጪ አንዳችም ስጋት አልነበረባቸውም።

ባለኮብራዎቹ ገንዘብ በማፍሰስ ከዳር እስከዳር ቢሮጡም የሃጂ ኤሊያስን ሃይል መግፋት ተሳናቸው። ስልት በመቀያየር ሞከሩ አልሳክም ሲል ሁሉም ባይሆኑም አንዳንዶቹ ከባለ ጊዜዎቹ ጋር ሽርክና መስርተው ተገን በማግኘት ንግዳቸውን ለማስፋት ወሰኑ ። በዘመኑ ቋንቋ ድርጅታቸው ቀይጠው “ዲጂታል” ሆኑ። ሃጂ ኤሊያስ በተራቸው ተገዘገዙ። በመጨረሻም ኢህአዴግ በቃውና ከሃጂ ኤሊያስ ጋር የነበረውን ፍቅር ጨረሰ። ቀን ጠብቀው ሃጂ ኤሊያስን አሰናበቱዋቸው። በየአቅጣጫው ጠላት ያበዙት ሃጂ ኤሊያስ ከፍተኛ ሃብት ስላላቸው ከዛሬ ነገ ይከሰሳሉ ሲባል ሳይሆን ቀረ። እንደውም አክሲዮን ማህበር ከፍተው እየሰሩ ነው።

ዲጂታሎቹ የሰው ነጋዴዎች

በጉዞ አመቻችነት ስም ተደራጅተው ቀስ በቀስ ሰው መነገድ የጀመሩት “ዜጎች” ካዝናቸው ማፈስ የለመደውን ጥቅም ሲያጣ ሁሉም ባይሆኑም በከፊል መልካቸውን ቀይረው “ከባለ ጊዜዎች” ጋር በየፊናቸው ተጎዳኙ። ድርጅታቸውን ለጋራ ባለቤትነት መስዋዕትነት አቅርበው “ካድሬ ተኮር” አካሄድ ጀመሩ። ለከርሳቸው ሲሉ የካድሬ ሚና መጫወት ጀመሩ። አብረዋቸው በተቀናጇቸው የጊዜው “ፊት አውራሪዎች” አማካይነት “አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ” ስብዕና የተላበሱ “የሰው ነጋዴ ሆኑ” በሌላ ቋንቋ “ዲጂታል” ሆኑ።

ድህነት ካቃጠላቸው ወገኖች ላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ እየተገለባበጡ ድፍን አረብ አገራት ሰራተኛ የማስቀጠር ህጋዊ ውክልና በአጋሮቻቸው አማካይነት ተረከቡ። ሃጂ ኤሊያስ የቆረጡትንና ወደ ራሳቸው ካዝና ያዞሩትን ንግድ መልሰው ገቡበት። ያልቻሉና በቀደመው “ያረጀ/አናሎግ” አካሄድ የዘለቁ የያዙትን ይዘው ተንጠባጠቡ። ቀደም ሲል ባከማቹት ሃብት ስራ ቀየሩ።AlAmoudi_Saudi

ስራው ከፍተኛ ገንዝብ የሚያስገኝና አንዳችም ኪሳራ ስላልነበረው የከፍተኛ ባለሃብቶችንም ቀልብ ስቦ ነበርና በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ “የሰው ንግድን” ስራ በጅምላ ለመቆጣጠር የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ስብዕና የተላበሱት በረጅሙ አቅደው ተንቀሳቀሱ። ከስራቸው ባሉት ጭፍራዎቻቸውና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አመራሮች ታግዘው ባደባባይ ከመንግሥት ጋር በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ሳዑዲ ለመላክ ተፈራረሙ። አዲሱ ጠ/ሚኒስትርም ሳዑዲ 50ሺህ ሰራተኛ ሃይል ትፈልጋለች ሲሉ ተናገሩ። አቶ መለስ የጀመሩትን ለማስቀጠል ክርስቶስን ወደ ኋላ አድርገው የሚምሉት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስራው በህጋዊ መንገድ እንደሚሰራም ወተወቱ።

ቅምጦቹን ሚዲያዎች ጨምሮ ሁሉም በየደረጃው ዜናውን አራገቡት። “የኢትዮጵያን ድህነት ታሪክ አደርጋለሁ” በማለት የሚወተውቱን ሼኽ መሐመድ አላሙዲ በስተመጨረሻ የሰው ንግድ ውስጥ መግባታቸው ታወጀ። “ዘመነ ዲጂታል”!! እርሳቸው በህግ ከገቡት ውል ጋር ተያይዞ ወደ ሳዑዲ የሄዱት ዜጎች ብዛት መረጃው ባይገለጽም ታይቶ በማታወቅ መልኩ ዜጎቻችን “ከአገር ውጡ” ተብለው ሲገደሉ፣ አስከሬናቸው አደባባይ ሲጎተት፣ ሴቶቻችን ሲደፈሩ፣ ወገኖቻችን ማጎሪያ ገብተው ሲሰቃዩ፣ ከሰብአዊነት ውጪ ሲሰቃዩ፣ የሰይፍና የካራ ስለት ሲሳልባቸው፣ የጦር መሳሪያ ሲሳብባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰማ፣ ታየ፣ ተመሰከረ። ይህንን አስደንጋጭ ድርጊት ለመቃወም ወይም በህግ ለመጠየቅ አንድም በገሃድ ወጥቶ ሃላፊነት የወሰደ የንግዱ ተዋናይ አለመኖሩ ሃዘኑን ድርብ አደረገው። ቢያንስ እርሳቸው ይህንን ድርጊት በመቃወም ወይም ሃዘናቸውን በመግለጽ ግንባር ቀደም አለመሆናቸው በርካታ ጥርጣሬዎችን አነገሰ። ከሳዑዲ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የሚነሱ ሃሜቶችን አስታወሰ። ዛሬስ ሳዑዲ ምን አዲስ ነገር አጋጠማትና ነው ወደ እንደዚህ ያለው አስከፊና አስነዋሪ ተግባር ለመሸጋገር የወደደችው?

ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት ጀምሮ

ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት ዜጎችን ለስራ ወደ ተለያዩ አረብ አገራት የሚልኩትን በማደን አከሰማቸው። በየመንደሩ በደላላ የሚሰሩትንና ቢሮ ከፍተው የሚንቀሳቀሱትን ህጋዊ ፈቃድ እንዲያወጡ በማወጅ ኢህአዴግ ንግዱን ወደ ራሱ ሰዎች በተለይም ለህወሃት ምርጦች አስተላለፈው። አዲሱን አሰራር ተከትሎ በቦሌ ቪላ ቤት ውስጥ በተከፈቱ ቢሮዎች ሰዎች አገራቸውን ጥለው ለመውጣት ለአይን የሚታክት ሰልፍ ያደርጉ ጀመር። ድሆች ተሰልፈው ተዘረፉ። ባደባባይ ህጋዊ ፈቃድ አላቸው የተባሉ ባለጊዜዎች ከድሃው ላይ በቀሙት ገንዘብ ኑሯቸውን አመቻቹ። ቀደም ሲል ቤህሩት፣ ኳታር፣ ዱባይ፣ ኩዌት፣ … ዘመድና ጓደኞች የነበራቸው በተባራሪ ጀምረውት የሰፋው የሰው ንግድ ኢህአዴግ ካስቆመውና በራሱ ሰዎች ከተካው በኋላ የተከለከሉት የቀድሞዎቹ ሰው ነጋዴዎች ለአዳዲሶቹ “ኩባንያዎች/ኤጀንሲዎች” ሰው አቅራቢ ደላላ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ደላላ መሆን ያልፈቀዱትም ለኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች የደንቡን እየከፈሉ ስራቸውን ይሰሩ ቀጠሉ።

አገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የስራ እድል መመናመንና ወገን እየለየ የሚከናወነው የስራ እድል ተስፋ ያስቆረጣቸው እየበረከቱ በመሄዳቸው ኤጀንሲ ከፍቶ መስራት ታላቅ ቢዝነስ ሆነ። በዚህም የተነሳ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ ሹመኞች ከሰው ንግድ ጀርባ ሆነው መጫወት ጀመሩ። በእንዲህ መልኩ የመንግስት ከፍተኛ ሰዎች ያሉበት ዝርፊያ ተከናወነ። ሌቦቹም፣ ህግ አስከባሪዎቹም ራሳቸው ስለሆኑ ለህዝብ በደል ጆሮ የሚሰጥ ጠፍቶ የድሆች እምባ ተደፋና ቀረ።

በመርከብ ስራ እናስቀጥራለን በማለት የድሮው አውሮፕላን ማረፊያ የተሰራውን ድራማ ለአብነት እናንሳ። ቢሮው በአደባባይ ማስታወቂያ አስነግሮ ስራ ሲጀምር የድሃ ልጆች መርከብ ላይ ስራ እናገኛለን በማለት የሚያርሱበትን በሬ በመሸጥ፣ የእርሻ መሬታቸውን በማስያዝ ተበድረው፣ የቤተሰቦቻቸውን ንብረት ሸጠው፣ የሚፈለግባቸውን ከፈለው ተመዘገቡ። አስቀድሞ የህክምና ምርመራ ማድረግ ግዴታ ነው ተብሎ አንድ የግል ክሊኒክ ብቻ በመሄድ 500 ብር እየከፈሉ ከጉበትና ከሳንባ በሽታ ነጻ የሆኑበትን ማስረጃ እንዲያመጡ ተደረገ። አራት ጉርድ ፎቶግራፍ ያስፈልጋል በሚል አሁንም አንድ ቦታ ብቻ እየሄዱ 50 ብር እየከፈሉ ፎቶ እንዲነሱ ተደረገ። በጥቅሉ አንድ ሰው ገና ሳይመዘገብ 550 ብር ይከፍላል።

ማስታወቂያው የጨበጣ መሆኑ ሲታወቅ የድርጅቱ ባለንብረት ካገር ወጡ ተባለ። ጉዳዩ ሲጣራ 11 ሺህ የሚጠጋ ሰው በሰልፍ ከመመዝገቢያ ውጪ ለፎቶና ለሜዲካል ብቻ ከ6.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ተሰብስቧል። የህክምና ክሊኒኩ ባለቤትና የፎቶ ቤቱ ባለቤት ስራ እናስቀጥራለን በሚለው የቁጭበሉ ድርጅት ውስጥ መስራች ናቸው።

ገንዘቡ ከተበላ በኋላ ድሆች የደም እንባ ሲያነቡ “ድርጅቱ ተዘግቷል። ሰውየው አገር ለቀው ወጥተዋል” ከመባሉ ውጪ የተወሰደ አንድም ርምጃ የለም። ገንዘቡን ከዘረፉት መካከል አሁንም ሹመት የሚፈራረቅላቸው አሉ። የሚገርመው ይህ ሁሉ ሲሆን ኢህአዴግ ደጅ፣ ኢህአዴግ አፍንጫ ስር፣ በራሱ አባላት፣ በራሱ ዳኞችና በራሱ የጸጥታና የፍትህ አስከባሪ ሃይሎች ፊት መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻር ይመስላል በርካታ አስተያየት ሰጪዎችና የአረብ አገራት ሰለባ ከሆኑት መካከል ከኢህአዴግ “ተቆርቋሪነት አይጠበቅም” ሲሉ የሚደመጠው።

አስካሉካ ትሬዲንግ ደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ማየት ለሚፈልጉ እንደሚያመቻች ጠቅሶ በመንግሥትና በግል ሚዲያዎች ማስታወቂያ አስነገረ። አቶ ሳምሶን ማሞና ኢቲቪ ቅስቀሳውን ተያያዙትና የሰው ጎርፍ ከደቡብ ኢትዮጵያ ጎረፈ። በተለይም የሃድያ ዞን አስተዳደር ልዩ መድረክ አዘጋጅቶ ቅስቀሳው ተካሄደ። ዜጎች የመንግስት ሰዎችንና ሚዲያዎችን አምነው በሰው 32ሺህ 582 ከ65 ሳንቲም ከፍለው ተመዘገቡ። 1200 ሰዎች ይህንን ገንዘብ ገቢ አደረጉ። በዚህም 40 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ተሰበሰበ።wegagan

አሳዛኙ ጉዳይ ገንዘቡ ገቢ የሚደረገው የህወሃት ንብረት በሆነው የወጋጋን ባንክ ሲሆን፣ ከስራው በስተጀርባ “አንቱ” የሚባሉት የህወሃት ሰዎች አንዳሉበት የአደባባይ ምስጢር መሆኑ ነው። ቀበና በተከፈተው የአስካሉካ ቢሮ ሰዎች ጉዳያቸውን ለመከታተል ሲመላለሱ ጊዜ ነጎደ። ዓለም ዋንጫ ሲቃረብ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ተጠይቆ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስታወቀ። አስካሉካም ግቢውን በፖሊስ እያስጠበቀ ገንዘባቸውን የዘረፋቸውን ለመመልከት ተጸየፋቸው። ሁከት ፈጣሪ ናቸው አስብሎ በፖሊስ አደባባይ ላይ አስደበደባቸው። ቀበናና የቀበና ጎዳና ይፍረዱት እንጂ ብዙ ግፍ ተሰራ። በተፈጠረው ሁኔታ የተደናገጡና ወፍጮ ቤት ውስጥ ተጠግተው ያድሩ ከነበሩት ዜጎች መካከል የአስካሉካ ባለቤት አገር ጥለው መጥፋታቸው ማስታወቂያውን በሰራው የመንግስት መገናኛ ይፋ ሲሆን ራሳቸውን ያጠፉ አሉ። ኢህአዴግና የፍትህ አካላቱ ከተቀሙት ንጹሃን ይልቅ ያለ አንዳች ብጣሽ የፈቃድ ወረቀት ድሆችን ሲዘርፍ የነበረ ማጅራት መቺ በልጦባቸው ድሆችን ቀጠቀጡ። ጎዳና ለጎዳና አሳደዱ። ሁሉም ነገር ታሪክ ከሆነ በኋላ ፖሊስና መንግሥት የአዞ እንባ አነቡ። የከረከሱ መኪናዎችና 5ሚሊዮን የሚሆን ገንዘብ ማገዳቸውን አበሰሩ። አቶ ግርማይ ገ/ሚካኤልንም ከተሰወሩበት ጀርመን አገር ለፍርድ አዲስ አበባ እንዳስመጣ አስታወቀ። ድሆች ግን ተዘርፈው ቀሩ። ለሞቱትም ነፍስ ይማር። ቂሙ ግን ቀን የሚቆጥር ነው።

ከድህነት በላይ ክህደት ያደቀቃቸው ዜጎች

በዱባይ፣ በኳታር፣ በኩዌት በሳዑዲ እና በተለያዩ የስደት ምድር ድህነትን ለማሸነፍና የመንግስት ሸክም ላለመሆን በሚንከራተቱ ወገኖች ላይ በተደጋጋሚ ለጆሮ የሚዘገንኑ በደሎች ተፈጽመዋል። ከፎቅ የተወረወሩ አሉ። በፈላ ውሃ የተቀቀሉ አሉ። በስለት የተወጉና የታረዱ አሉ። ማን እንዳደረገው ባይታወቅም የተሰቀሉ ጥቂት አይደሉም። በመርዝ ህይወታቸው ያለፈ … ተዘርዝሮ አያልቅም። ከሁሉም በላይeth saudi dubai ኤምባሲዋ በር ላይ ከለላ አገኛለሁ ያለች ወገናችን እንደ ውሻ እየተጎተተች ህይወቷ ሲያልፍ የሚያሳየውን ትዕይንት ለሚያስታውሱ ኢህአዴግ ድህነት በሚያሰቃያቸው ወገኖች ላይ በግልጽ ክህደት የፈጸመ ስለ መሆኑ ነው።

በሌላ በኩል ኢህአዴግ በተለይም ህወሃቶች በተመደቡበት የቆንስላ ጽ/ቤቶች፣ እንዲሁም ድንበር በማሻገር ህገወጥ ከሚሏቸው ስደተኞች ገንዘብ የሚያግበሰብሱ መሆኑ፣ በሌላ በኩል በርካታ ስራውን የሚሰሩ ኤጀንሲዎች የህወሃት ሰዎች መሆናቸው፣ በመንግስት ደረጃም ሰዎችን ወደ አረብ አገር ለመላክ በኦፊሻል የተዋዋለው ኢህአዴግ መሆኑ በየትኛውም ደረጃ በዜጎች ላይ ለሚደርሰው በድል ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጥ የሚስማሙ ይበረክታሉ።

በሳዑዲ አረቢያ መከራ እየተጋፈጡ ያሉ ዜጎች ህገወጥ ይሁኑም ህጋዊ የስራ ተቀጣሪዎች አገር አላቸው። በጠመንጃና ደም በማፍሰስ በጉልበት የሚገዛቸውም ቢሆን አገራቸውን የሚመራ ድርጀትና “ጉልቻ” ፓርላማ አላቸው። በዘር እየለየ ድጋፍ የሚሰጥና ለወደፊቱ ቂም የሚያከማች ድርጅት ቢያረክሰውም የሚኮሩበት ባህልና ወግ አላቸው። ገንዘብ ካገኘ ገደል የማይታየው ኢህአዴግ ከድህነታቸው በላይ ክህደት ቢፈጽምባቸውም እጁን ዘርግቶ የሚቀበል ቤተሰብ ከድህነቱ በላይ ተካፍሎ መብላት የሚያስጨንቀው ማህበረሰብ አካል ናቸው።

ከድሆች ገንዘብ እየሰበሰቡ የሚንደላቀቁ ሁሉ በቅድሚያ ከራሳቸው ህሊና፣ ቀጥሎም ከተጎጂዎችና በዙሪያቸው ካሉ ወገኖች እንዲሁም አገር ወዳዶች የበቀል ቋት ውስጥ ከቶውንም አይወጡም። ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት የተሸከመውን የነፍጥ ብዛትና የሰበሰበው የሃብት ክምችት ትምክህት ሆኖባቸው ወገኖቻቸው ላይ ለሚሳለቁ “ወዮልኝ” አብዛኞች እየራባቸውና ችግር እያዳፋቸው በጥጋብ ድሃው ህዝብ ላይ ለምታገሱ አሁንም “ወዮልኝ”። የበቀል ሽታው እየናኘ ነውና “ከወዮልኝ” እንድንሰወር ይሁን። አገር ውስጥ ያላችሁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አላችሁ? ኢህአዴግና ጭፍራዎቹ የደርግ ያበቃበት ዘመን ዛሬም ይመጣልና አስቡ። የመጣል ቀን ቀጠሮ የለውም። አሁን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ካለው የሃዘንና የድህነት መጠን አንጻር የሚያጨካክነውን አስተሳሰብ ወደ መደጋገፍ ለመቀየር ትጉ!!the bees

አንድ አገር ያላት ዜጋ አደባባይ ተገድላ አስከሬኗ ሲጎተት፣ አንድ ወገንና አገር ያለው ጀግና ድህነት ክብሩን አሳጥቶት አስከሬኑ በስለት ሲወጋ ከማየትና አህቶቻችን ሲደፈሩ እየሰማ ቁጣውን በትዊተርና በፌስቡክ የሚገልጽ መንግስት ለዜጎቹ ማፈሪያ ነው። ይህንን ያህል ተለሳላሳሽነትስ መነሻው ምንድ ነው? ኢህአዴግ ልዩ በጥቅሙ ካልተነካ በስተቀር፣ ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት የሚጎዳበት ነገር ከሌለ በስተቀር ሁሉም ሰላም፣ አገር አማን ነው ማለት ነውን? አገርን፣ ዜጎችንና ብሄራዊ ክብርን በጎጥ ሂሳብና በከርስ መጠን በመለካት መኖር መጨረሻ ላይ ዋጋ ያስከፍላል። ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው። ዳሩ ምን ያደርጋል ሌባ ሌባን አይከስ?