Archive | January 11, 2014

እስክንደር ነጋ አሸባሪ ከተባለ ጆን ኬሪና አል ባራዴየም አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው – ግርማ ካሳ

ኢቲቪ በቅርቡ አንድ በአንድ በኩል አሳዛኝ በሌላ በኩል አስቂኝ ዶኪሚንተሪ ለተመልካቾቹ አቅርቧል። በርካታ ጉዳዮች ተነስተዋል። ለዛሬ፣ የፌዴራል ከፍተኛ አቃቤ ሕግ የሆኑት፣ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ አንጋፋዉ ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋን በተመለለተ፣ በተናገሩት ላይ ጥቂት ሃሳቦችን ለመገልጽ እወዳለሁ። ሰዉዬ ስለ ሕግ፣ ስለ ሕገ መንግስቱ እየደጋገሙ አውርተዋል። ማንም ሕገ መንግስቱን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት የገለጹት፣ አቃቤ ሕጉ፣ የአገሪቷ ሕግ ሲናድ ወንጀለኞችን ይዞ ለሕግ ከማቅረብ ወደኋላ እንደማይሉ አሳስበዋል። ማለፊያ ነዉ። ወንጀለኛ መያዝና መቀጣት አለበት። ሕግ መከበር አለበት። ይሄ ብዙ አያከራክረንም።

ነገር ግን «ሕግ፣ ሕግ» እየተባለን፣ ፍጹም ሕገ ወጥ የሆነ ተግባራት፣ ሕግ አስከባሪ ነን በሚሉ እየተፈጸመ መሆኑ ነዉ ብዙ እያከራከረን ያለው። ሕግ ሁላችንንም በእኩልነት የሚዳኝ መሆኑ ቀርቶ፣ ጥቂቶች እንደፈለጉ የሚገለባብጡት፣ የመጨቆኛ መሳሪያን በርት መሆኑ ነዉ እያሳሰብን ያለው። አቶ ብርሃኑ ስለ እስክንደር ነጋ ሲናገሩ የሚከተለዉን አሉ፡

«የእስክንድርንም ኬዝ ቢሆን፣ የ2004 አረብ ስፕሪንግ አይነት፣ ኢትዮያ ዉስጥ የአመጽ ጥሪ በማድረግ ከተንቀሳቀሱ ኃይሎች አንዱ እራሱ ነዉ። እርሱ በተለይም በየተኛዉ እርስ ላይ፣ በመጻፉ ምክንያት፣ አንድም ክስ አልቀረበበትም።የእስክንድር ጉዳይ ከፍሬደም ኦፍ ኤክስፕረሽን፣ ከመናገር ነጻነት ጋር፣ ከመናገር መብት ጋር የተያይዘ በፍጹም አይደለም። ቅድም እንዳልኩት፣ የአመጽ ጥሪ ማስተላለፉ ነዉ። የአምጽ ጥሪው ደግሞ የግንቦት ሰባት ተልእኮን ለማሳካት ነዉ። ከዚህ ጋር እስከ ፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ በጣም ሰፋ ይሉ ክርክሮችን በተደጋጋሚ አድርገናል።የአገሪቱ የመጨረሻ የሆነው ፌደራል ጠቅላ ፍርድ ቤት ፤ የጠፋተኝነት ዉሳኔ ሰጧል።»

በግብጽ የታየው፣ በኢትዮጵያም እንዲደገም እስክንደር ነጋ የሚፈልግ እንደነበረ ብዙም አያክራክረንም። በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት በተደረገ ስብሰባ ላይ «እንችላለን! በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች እንደሚቻል አይተናል። ኢትዮጵያ ከእነሱ ቢያንስ ቢያንስ አታንስም። ታሪክ እንስራ!» ያለዉና ኢቲቪ ቀንጥቦ ያወጣዉ አባባል ትክክለኛ አባባል ነው። እስክንደር ነጋ፣ ይሄን አልክዳእም። ሊክድም አይችልም።

«እስክንደር፣ በግብጽ የተከሰተዉ በኢትዮጵያ እንዲከሰት መፈለጉና በዚያ ዙሪያ መንቀሳቀሱ በምን መስፈርትና ሚዛን ነዉ ሽብርተኘንት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ? » በሚለው ላይ ነዉ የመጀመሪያ ክርክራችን። በግብጽ የነበረው እንቅስቃሴ ፍጹም ሰላማዊ የነበረ እንቅስቃሴ ነዉ። ከዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች መካከል የነበሩ አንዱ ዶክርተር ሞሃመድ አል ባራዴ ይባላሉ። በተባበሩት መንግስታት የአለም አቀፍ ኑክሊያር ኤጀንሲ ሰብሳቢ ሆነው ለበርካታ አመት ያገለገሉ የተከበሩ ሰው ናቸው። እንደ ሳዳም ሁሴን የመሳሰሉ ሽብርተኛ መንግስታት ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች በማከማቸት ለአለም ስጋት እንዳይፈጥሩ የታገሉ የሰላም ሰዉ ናቸው። እኝህ ሰውና የሚመሪት ድርጅታቸው እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2005 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ታዲያ ሰላማዊ በሆነ መልኩ፣ አምባገነኑ የሙባረክ መንግስት ለሕዝብ ፍቃድ ተጠያቂ እንዲሆን፣ የስርዓት ለዉጥ እንዲመጣ፣ መታገላቸው እኝህ የሰላም የኖቤል ተሸላምዊ ሽብተኛ ያደርጋቸዋልን ?

ከሰባት ወራት በፊት ጆን ኬሪ፣ ሃርድ ቶክ ቢቢሲ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተው ነበር። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቴዎድሮስ አዳኖም በዚያ ነበሩ። ጆን ኬሪ ንግግራቸውን ሲጀመሩ የተናገሩትን ማንሳት እፈልጋለሁ። በግብጽ ስለነበረው ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ሽብርተኘንት ብሎ ስለሚጠራዉ፣ እንቅስቃሴ ሲናገሩ የሚከተለዉን ነበር ያሉት፡

«…the greatest concern has to be the lack of the fulfillment by governments in many countries, of the aspirations of people. Particularly the creation of jobs, and tሀ educational opportunities that are needed, for this modern world….In Egyopt, that was not a revolution that was moved by Islamism, or any ideology ….It was young people.. ..it was you ..people who came to the square , and twitted each other , texted each other , e-mail each other and brought people»

ጆን ኬሪ፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ንደ ሽብርተኝነት የሚቆጥረዉን በግብጽ የታየውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደ ትልቅ ምሳሌ አጉልተው ሲናገሩ፣ እስክንደር ነጋና ሌሎች ከተናገሩት አባባሎች ጋር የሚስማማ ንግግር ሲናገሩ፣ የሕወሃት/ኢሕአዴጉ ዶር ቴዎዶርስ ቁጭ ብለው ያዳምጡ ነበር። ታዲያ ጆን ኬሪ፣ የግብጽን እንቅስቃሰ እበነደገፋቸው፣ ወጣቶች ከግብጽ ወጣቶች እንዲማሩ በማባረታታቸው ችብርተኛ ሆኖን ? ሌላ ሌላም ምሳሌዎች ማቅረብ ይቻላል።

በግብጽ የታየዉ «አምባገነኖች» እምቢ የማለት ሰላማዊ እንቅስቃሴ የአለም አቀፍ ሕግን ያከበረ፣ በሰለጠነው አለም አድናቆትን ያተረፈ፣ የሕዝብ ጉልበት ታፎኖ እንጂ ከተነሳ ተአምር ሊያደርግ እንደሚቻል ያስተማረ ፣ ለአምባገነኖች ፍርሃትን የለቀቀ እንቅስቃሴ ነዉ። ሽብርተኝነት በፍጹም አይደለም።

እንግዲህ ሕወሃት/ኢሕአዴግ እስክንደርን ሽብርተኛ እያለ መጠራቱን ከቀጠለ ጂን ኬሪ፣ የስላም የኖቤል ተሸላሚ የሆኑትን ዶር መሃመድ አልባራዴን የመሳሰሉትን ሽብርተኛ እያለ እንደሆነ መቆጠር ይኖርበታል።

ሌላዉ ማንሳት የምፈልገው አቶ ብርሃኑ ከየት ዘለዉ እስክንደር ነጋን ከግንቦት ስባት ጋር እንዳገናኙት ነዉ። በግብጽ የነበረዉ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ነዉ። ግንቦት ሰባት «የሰላም እንቅስቃሴ አይሰራም» ብሎ ነፍጥ ጨብጫለሁ ያለ ደርጅት ነዉ። እንዴት ተደረጎ ነዉ በግብጽ የታየዉን መደገፍ፣ የግንቦት ሰባት አባል የሚያሰኘው ? እዚህ ላይ ሕወሃት/ኢሕአዴጎች እራሳቸው ያስገመቱ ይመስለኛል። ምን አለ ባይቀልዱብን ?

በመጨረሻ በትክክለኛ መንገድ ክርክሮች ተደረገዉ በርካታ መረጃዎች ቀርበው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የጥፋተኛ ዉሳኔ እንደሰጠ በመግለጽ አቶ ብርሃኑ፣ የሕግ ስርዓት እንዳለ፣ ለማሳየት ሞክረዋል። እስክንደር ነጋ ቦምብ አላፈነዳም። ቤቱ ተበርብሮ አንድም ጥፋተኝነቱን የሚገልጽ መረጃ አልተገኘም። ወንጀሉ እንደ ጆን ኬሪ፣ ሞሃመድ አልባራዴ የግብጽ ሕዝባዊ እንቅስቃሴን መደገፉ ፣ በሕዝብ ጉልበት ኃይል መተማመኑ ነዉ። ወንጀሉ አገሩን መዉደዱ ነዉ።

«እክንድር ሽብርተኛ መሆኑን የሚያመለከት መረጃ አላየሁምና ልፈታው ነው» ባሉ ጊዜ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አማረ አሞኜ ፣ የሚኒስተሮች ምክር ቤት ተጠርተዉ መመሪያ እንደተሰጣቸው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አንድ ወቅት ዘግቦልን ነበር። ዳኛ አማረ፣ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ምንም እንኳን ጉዳዩን ሲያዳምጡ የነበሩ እርሳቸው ቢሆንም፣ ጉዳዪን ያላዳመጣ ሌላ ዳኛ (ወይንም ካድሬ) ተመድቦ ነዉ፣ የፖለቲካ ዉሳኔዉን በፍርድ ቤት ያነበበዉ። ሐቁ እንግዲህ ይሄ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሕግ ስርዓት የለም። የግብጽ አይነቱን እንቅስቃሴ፣ የሕዝቡ መነሳት ምን ጊዜም አምባገነኖችን የሚያስጨንቅ ስለሆነ፣ ክህደት፣ ሽብር፣ ወዘተረፈ እያሉ ማሰርና መግደል ልማዳቸው ነዉ። ነገር ግን ለጊዜ ያሸነፉ ሊመስላቸው ይችላል እንጂ ወዳቂዎች ናቸው። ይህ በነ እስክንደር ላይ የምናየው ድራማ አገዛዙ በራሱ የማይተማመን፣ የደነበረ መሆኑን ያሳየ ነው፡ በሚቆጣጠሩት ሜዲያ ጠዋትና ማታ መለፈፋቸውም የዉሸታቸውና የግፋቸውን መጠን አይቀንሰውም። ሕዝቡንም ማታለል አይችሉም። ሕዝቡ ያውቃል። ሕዝቡ እስክንደር ነጋ ማን እንደሆነ ያወቃል። እስክንደር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግና ነው። እርሱ ቃሊቲ የሚቆዩባቸው ቀናት በጨመሩ ቁጥር፣ እርሱ የበለጠ እየሸነፈ፣ እነርሱ ደግሞ እየመነመኑ ፣ ምናምንቴ እየሆኑ ነዉ። እርሱ በአለም አቀፍ መድረክ እየተከበረ፣ እነርሱ ደግሞ ሃፍረት እየተከናነቡ ነዉ።

posted by Kidanewold, Alemayehu

ጃዋር መሐመድ In My Mind!

1074891_501448586602754_1044490877_o

Abraha Desta
ጎበዝ ሰው አያስፈራኝም (ጉረኝነቴ)። ምክንያቱም ጎበዝ ሰው ብቃት አለው። ብቃት ያለው ሰው በሐሳብ (በምክንያታዊነት) ያምናል። በምክንያት የሚያምን ሰው ደግሞ አያስፈራም። ምክንያቱም በሐሳብ (በምክንያት) ከሚያምን ሰው ጋር ስትገናኝ ምክንያታዊነት እንደ መስፈርት በመጠቀም በሐሳብ ትከራከራለህ እንጂ ወደ ሌላ የሐይል መንገድ አትሯራጥም። በሐሳብ መከራከር ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም። ምክንያቱም በምክንያት ስትከራከር አንድም ሰውየው ያሳምነሃል አልያም ደግሞ አንተ ታሳምነዋለህ። አንዳቹ ካሳመናቹ ሁለታችሁ ትስማማላቹ። ካልተስማማችሁ ደግሞ በሐሳብ ትለያያላቹ። በሐሳብ መለያየት በራሱ ችግር የለውም።

ጃዋር መሐመድ በፖለቲካ ብቃታቸው ከማደንቃቸው ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች አንዱ ነው። እስከ ቅርብ ግዜ ጃዋር በሚሰጣቸው ትንታኔዎች እደነቅ ነበር። አንድ ግዜ ዕድል አግኝቼም አድናቆቴን ገልጨለታለሁ።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የሐሳብ ልዩነት እየፈጠርን ነን (እኔና ጃዋር)። አሁንም ቢሆን የሐሳብ ልዩነት ስለተፈጠረ ብቻ ጃዋርን አልጠላዉም። የራሱ ሐሳብ የመያዝና የማራመድ ሙሉ መብት አለው። በሱ ምርጫ ጣልቃ አልገባም። ግን የፖለቲካ ብቃቱ ግምት ዉስጥ በማስገባት ጃዋርን በአካል አግኝቼ በፖለቲካ ጉዳዮች ዙርያ መነጋገር (መከራከር) አማረኝ።

የጃዋር የፖለቲካ ብቃት ለኢትዮጵያ ሀገራችን የወደፊት እጣፈንታ እሴት ነው (ነበር) ብዬ አስባለሁ። ጃዋር ከሌሎች ቆራጥ ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች ጋር በመሆን መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት ይችል ነበር። አሁንም ተስፋ አልቆርጥም።

ከጃዋር ጋር መከራከር (መነጋገር) የምፈልገው ነጥብ ምንድነው? የተለያየንበት ነጥብ ላይ ነው። ከጃዋር ጋር የተለያየንበት ነጥብ ‘የኢትዮጵያዊነት ደፍኒሽን’ ላይ ነው። የድሮ ስርዓቶች (የአሁንም ጭምር) በህዝቦች ላይ በደል ፈፅመዋል። የበደሉ መጠን ይለያይ እንጂ በሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ደርሷል። በደሉ (ጭቆናው) በህዝቦች ላይ መድረሱ አልደግፍም። በዚህ ነጥብ ከጃዋር ጋር እስማማለሁ።

አዎ! በህዝቦች ላይ የደረሰው (እየደረሰ ያለው) ጭቆና መቃወም አለብን። ግን የምንቃወመው ጭቆናው እንጂ ህዝብን አይደለም። ጭቆናው ማነው ያመጣው? ገዥዎች ናቸው። ህዝብ አይደለም ህዝብን የበደለ (የጨቆነ)። ነገስታት (መንግስታት) ናቸው ህዝቦችን የጨቆኑ (የሚጨቁኑ)። ስለዚህ መቃወም ያለብን ጭቋኞችን (ገዥዎችን) እንጂ ህዝብን (ተገዥዎችን) አይደለም።

አጤ ምኒሊክ በህዝቦች ላይ ግፍ ከፈፀሙ በደሉ የደረሰው በንጉሰ ነገስቱ እንጂ በሀገረ ኢትዮጵያ አይደለም። አጤ ምኒሊክን መውደድ እንደሚቻል ሁሉ መጥላትም ይቻላል። ጃዋር አጤ ምንሊክን መጥላት ይችላል። አጤ ምኒሊክ ስለ ጠላ ኢትዮጵያነቱን መጥላት ያለበት ግን አይመስለኝም። ምክንያቱም አጤ ምኒሊክ የኢትዮጵያ ንጉስ እንጂ ኢትዮጵያ አይደሉም። ይሄው አጤ ምኒሊክ ካረፉ መቶኛ ዓመታቸው ያዙ። ኢትዮጵያ ግን አለች፤ ለዘላለምም ትኖራለች። ስለዚህ ንጉስና ሀገር ማገናኘት አልታየኝም። ኢትይጵያና ምኒሊክ አንድ ያደረጋቸው ማነው?

የሀገር መሪዎችን እንደየተግባራቸው መጥላት ወይ መውደድ እንችላለን። እናት ሀገር ኢትዮጵያ ግን መውደድ ብቻ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሀገራችን የምትጠላበት ምንም ምክንያት የለም። ኢትዮጵያችን በማህፀኗ ይዛ፣ ወልዳ፣ አሳድጋ ይሄው ለዚህ በቃን። ኢትዮጵያ በደል (ጭቆና) አላደረሰችብንም። ህዝቦች የተጨቆኑ በኢትዮጵያ ንጉሶች እንጂ በኢትዮጵያ ሀገር አይደለም። በንጉስ ተግባር ምክንያት ሀገር ከጠላን ተሳስተናል። ጨቋኞች ካሉ እዋጋቸዋለሁ፤ እቃወማቸዋለሁ። ኢትዮጵያዬን ከጨቋኞች ነፃ አወጣታለሁ እንጂ ጨቋኝ መሪዎች ስላሏት (ስለነበሯት) አልጠላትም። ስለዚህ ሀገርና ገዢ ብንለያይ።

ጃዋር ሐሳብህ በስህተት ተረድቼህ ከሆነ አርመኝ። በዚህ ጉዳይ ተገናኝተን ብንነጋገር ግን ደስ ይለኛል (አጋጣሚ ሲፈጠር ማለቴ ነው)።

ሁላችን ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ለሌሎች አሳልፈን አንስጥ። ኢትዮጵያዊነታችን በራሳችን ለራሳችን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

It is so!!!

የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያን ሻሮን አረፉ

safe_image (1)

የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያን ሻሮን በ85 አመታችው አረፉ።

ከ1948 የእስራኤል የነጻነት ጦርነት ጀምሮ እስከ አመራር ዘመናችው በበሳል ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራራችው በእስራኤል ህዝብ ዘንድ ተወዳጅ ነበሩ።

ከ1967 እና በ1973 እስራኤል ከአረቦች ጋር ባደረገችው ጦርነት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ሻሮን ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 አመታት በጠቅላይ ሚኒስተርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል።

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ለ8 አመታት በስትሮክ በሽታ በጽኑ በመታመማቸው ቴላቪቭ በሚገኘው ሼባ የህክምና ማእከል ህክምናቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸው ይታወሳል ።

ምንጭ ፦ ቢቢሲ

የግል መጽሔት አዘጋጆች፤ “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሳናት ሆነዋል” መባላቸውን አጣጣሉ

2b19039892926da39539af655fbfaff8_M

  • Written by  አበባየሁ ገበያው

ሪፖርቱ የአደጋ ምልክት ነው ብለዋል

“በኢትዮጵያ የሚታተሙ ሰባት የግል መጽሔቶች የጽንፈኛ ፖለቲካ ልሳናት ሆነዋል፤ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ህዝቡ በስርአቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ ያደርጋሉ” ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋራ ያሠሩት የጥናት ሰነድ አመለከተ። የመጽሔቶቹ አዘጋጆች በበኩላቸው፤ ሪፖርቱን ያጣጣሉ ሲሆን ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡ ተቋማቱ ያስጠኗቸው አዲስ ጉዳይ፣ ፋክት፣ ሎሚ፣ ቆንጆ፣ ጃኖ፣ ዕንቁና ሊያ መጽሔቶች ሲሆኑ ከመስከረም 1 ቀን እስከ ህዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም ባወጧቸው ህትመቶች ላይ በተደረገ የአዝማሚያ ትንተና መሠረት፤ መጽሔቶቹ የግል መገናኛ ብዙሃን ሳይሆኑ የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት ሆነዋል ተብሏል፡፡ መጽሔቶቹ በሚያቀርቧቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ይዘት፣ ህዝቡ በስርአቱ ላይ እምነት አጥቶ ለአመጽ እንዲነሳሳ የሚያደርጉና የቀለም አብዮት ባስተናገዱ አገሮች የታየውን ቅኝት የሚከተሉ ሆነው ይታያሉ ብሏል – የጥናት ሰነዱ፡፡ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ በረቡዕ እትሙ የጥናት ሰነዱን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ “የሁሉም ጽሑፎች ይዘት ያተኮረው አሉታዊ ጉዳዮችን በማራገብ፣ መረጃዎችን አዛብቶ በማቅረብ፣ መንግስት በልማት፣ በሰላምና በዲሞክራሲ መስኮች ያመጣቸው ለውጦች የሌሉ በማስመሰል እንዲሁም ህዝቡ ከችግር ለመውጣት የሚያደርገው ጥረት ላይ በማሾፍና በማንኳሰስ ነው” ብሏል፡፡

ሁሉም መጽሔቶች የጋራ የመረጃ ምንጮችን ይጠቀማሉ ያለው ሰነዱ፤ የኒዮሊበራል አክራሪ ሃይሎች ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች፤ ለህገመንግስታዊ ስርአቱ እጅግ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው የድሮ ስርአት ናፋቂዎችና በሽብር ወንጀል የተፈረደባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ሲል ዘርዝሯቸዋል፡፡ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ላይ የወጣውን የጥናት ሪፖርት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የግል መጽሔቶች አዘጋጆች፤ “የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት ሆነዋል” በሚል የወጣውን ትንተና ያጣጣሉት ሲሆን ጥናቱ ከዚህ ቀደም በታየው ልምድ መሠረት ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በሪፖርቱ ከተካተቱት መጽሔቶች መካከል የእንቁ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ኤልያስ ገብሩ፤ “ጥናቱ የግሉን ፕሬስ ሆን ብሎ ለማሸማቀቅ እና ለመወንጀል የወጣ ነው” ሲል ተችቶታል፡፡

የጥናቱ ምንጭ የሆኑት ሁለቱ ተቋማት የመንግስት እንደመሆናቸው ገለልተኛ ናቸው ለማለት እቸገራለሁ ብሏል አዘጋጁ። “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት” የሚለው አገላለጽ በየአስራ አምስት ቀኑ የምትወጣውን “ዕንቁ” መጽሔትን አይወክልም፤ እኛ ከጋዜጠኝነት መርህ አኳያ እንሠራለን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን አይደለንም፤ ልንሆንም አንችልም ብሏል – ዋና አዘጋጁ፡፡ “ነገር ግን መንግስት አካሄዱን እንዲያስተካክል በመረጃ ተደግፈን እንተቻለን፣ የምንሠራው ህግና ስርአቱን አክብረን ነው” ሲል ገልጿል፡፡ ሪፖርቱ ለመጽሔቶቹ የአደጋ ምልክት መሆኑን የጠቀሰው ዋና አዘጋጁ፤ በተለይ መጽሔታቸውን ከሽብርተኝነት ጋር ማያያዙና የአመጽ ጥሪ አቅራቢ እያለ መወንጀሉ በስራቸው ላይ ከባድ ስጋት እንደሚፈጥርባቸው ገልጿል፡፡ ከዚህ በፊት በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት ያቀርቡ የነበሩ ጋዜጦችም የዚህ መሰሉ ውንጀላ ሠለባ ከሆኑ በኋላ ነው የተዘጉት ያለው ኤልያስ፤ የአሁኑ ሪፖርትም በመጽሔቶቹ ላይ ትልቅ አደጋ እንደተደቀነ የሚያመላክት ነው ብሏል፡፡

ከሰላሳ በላይ ገፆች ያሉትን የጥናት ሪፖርት እንዳነበበ የገለፀው የ “ቆንጆ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ካሣ በበኩሉ፤ መንግስት በቀጣዩ ምርጫ መጽሔቶች ስጋት ይሆኑብኛል ብሎ በመፍራቱ ነው እንዲህ ያለ ሪፖርት ያወጣው ሲል ተናግሯል፡፡ መጽሔታችን ሚዛናዊነትን ጠብቆ የጋዜጠኝነት ሚናውን እየተወጣ እንጂ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ልሣን አይደለም ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ መንግስት የግሉ ፕሬስ ስላልተመቸው በርግገው ከሃገር ይሰደዳሉ በሚል እምነት ነው ይሄን ያደረገው ብሏል፡፡ በተለይም የአጥኝዎችን ማንነት ስንመለከት ዋና ስራቸው ዜናዎችን መቀበልና ማሠራጨት እንጂ ጥናት እያጠኑና እያስጠኑ፣ ደረጃ እንዲመድቡ ወይም እገሌ መጽሔት ይሄን ያህል በመቶ ሽብርተኝነትን ቀስቅሷል፣ ይሄን ያህል በመቶ ደግሞ የኢኮኖሚ እድገቱን ክዷል በሚል መፈረጅ አይደለም ሲል ተችቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ጋዜጦች የከሰሙበትን መንገድ ሲያስታውስም፤ “ብዙውን ጊዜ በአዲስ ዘመን ላይ ትችቶች በተከታታይ ይቀርባሉ፣ በቴሌቪዥን ዶክመንተሪ ይሰራበታል፤ ከዚያም የህዝብ አስተያየት ተብሎ ይሰበስብና ይወገዛል፤ በሂደትም መጽሔቶቹንና ጋዜጦቹን በተለያዩ ክሶች በማዳከም እንዲከስሙ ይደረጋል” ያለው ቴዎድሮስ፤ ይህ መሰሉ ልምድ ባለበት ሁኔታ የዚህ ሪፖርት መውጣት ከፍተኛ ስጋት ይፈጥርብናል ብሏል፡፡

“ጥናቱን ያደረጉት የመንግስት ተቋማት ምን ለማለት እንደፈለጉ ይገባናል፤ እዚህች ሃገር ላይ የፕሬስ ነፃነት እንዲኖር አይፈልግም” ያለው የሳምንታዊው ሎሚ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር፤ የጥናቱ ሪፖርት በግል መጽሔቶቹ ላይ እርምጃ ሊወሰድ መታሰቡን የሚጠቁም ነው ብሏል። “መጽሔቶች የጽንፈኛ ፖለቲካ ልሣናት ናቸው የተባለው እንደልብ የምናገኛቸውን የመረጃ ምንጮች ስለምንጠቀም ነው” ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ የመንግስት ባለስልጣናትን ቃለ መጠይቅ ለመስራት ስንሞክር አናገኛቸውም ብሏል፡፡ ጥናቱን የሠሩት ተቋማት እኛን ከመፈረጅ ይልቅ በማተሚያ ቤቶች ያለብንን ችግርና ወረቀት ከውጭ ሀገር ለማስመጣት ያለውን ፈተና ለምን አያጠኑም ሲልም ጠይቋል – ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፡፡ የሊያ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር መላኩ አማረ በበኩሉ፤ በጥናቱ የተገለፀው ፍረጃ የመጽሔታቸውን ባህሪ እንደማያንፀባርቅ ገልፆ፤ ከሪፖርቱ በተቃራኒው የህብረተሰቡ ልሣን በመሆን እየሠሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ጥናቱ ሚዛናዊነት የጐደለው ነው ያለው መላኩ፤ ጥናቱ ተደረገ የተባለባቸውን ያለፉትን ሶስት ወራት የመጽሔቶች ህትመት እንዳየና ከተወነጀሉበት “የፅንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣናት” አስተሳሰብ የራቁ ጉዳዮችን ሲያነሱ እንደነበር ማረጋገጡን ገልጿል። የፕሬስ ትልቁ አላማው የፖለቲካ አስተሳሰብና የህዝቡን ሃሳብ በነፃነት ማንሸራሸርና ማስተላለፍ ነው ያለው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ ሪፖርቱ ምናልባትም የመጽሔቶቹ ቀጣይ ህልውና ላይ ቀይ ምልክት የሚያበራ በመሆኑ አዘጋጆችን የበለጠ የሚያሸማቅቅና ሥጋት ላይ የሚጥል ነው ብሏል። “መንግስት ፕሬሶችን ለማጥፋት ሲፈልግ ቀይ መብራት የሚያሳየው አዲስ ዘመን ላይ በሚወጡ ትችቶች ነው” ያለው መላኩ፤ የረቡዕ እለቱን የጋዜጣውን እትም ለየት የሚያደርገው ርዕሰ አንቀፁም ጭምር የኛ ጉዳይ ላይ ማተኮሩ ነው ብሏል፡፡ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ዮሐንስ ካሣሁን ስለጉዳዩ በሰጠው አስተያየት፤ “የጽንፈኛ ፖለቲካ ፓርቲ ልሣን” የሚለው ፍረጃ ለእኛም አዲስና ያልጠበቅነው ስለሆነ ተገርመናል፤ እኛ የምንሠራው የጋዜጠኝነትን ሙያ እንጂ ሌላ አይደለም ብሏል። “ቀደም ባሉት የአዲስ ዘመን እትሞች ላይ ‘አዲስ ጉዳይ’ን የሚያብጠለጥሉ ጽሑፎች ሲስተናገዱ ተመልክተናል፡፡ እኛም ለትችቶቹ መልስ ስንሰጥ ከርመናል፡፡ ይሄኛውም ከዚያ የተለየ አይሆንም” ሲል አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡ በመጽሔቶቹ ላይ የተደረገው ጥናት ያተኮረው “የመንግስት ኀላፊዎችን የግል ስብዕና የሚነኩ፣ የአመጽ ጥሪዎችን የሚያስተላልፉ፣ ሽብርተኝነትን የሚያበረታቱ፣ የፖለቲካ ስርአቱን የሚያጨልሙ፣ የኢኮኖሚ እድገቱን የሚክዱና ህገመንግስቱን የሚያጣጥሉ” በሚሉ ነጥቦች ላይ ሲሆን በተከታታይ ህትመቶች የተነሳበት ድግግሞሽም ሆነ በአንድ ህትመት የተለያዩ አምዶች የተነሳበት ብዛት በቁጥር መተንተኑ ተገልጿል፡፡

ለቴዲ አፍሮ 4.5ሚ. ብር ይከፈለዋል

images

በደሌ ለኮንሰርቶቹ 25 ሚ.ብር መድቦ ነበር ኮንሰርቶቹ ቢሰረዙም ውዝግቡ አልተቋጨም የቴዲ ደጋፊዎች የአፀፋ ዘመቻ ጀምረዋል

አለማቀፉ የኔዘርላንድ ኩባንያ ሄኒከን ከሚያስተዳድረው በደሌ ቢራ ጋር በመሆን በበርካታ ከተሞች ሊካሄዱ የነበሩ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርቶች ቢሰረዙም፣ ቴዲ አፍሮ በውላቸው መሰረት 4.5 ሚ. ብር እንደሚከፈለው ምንጮች ገለፁ፡፡ እስካሁን በአገር ውስጥ ከተካሄዱ ኮንሰርቶች በላቀና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በድሬዳዋ ተጀምሮ በርካታ ከተሞችን እንዲያዳርስ ታስቦ የተፈረመው የቴዲ አፍሮና የበደሌ ቢራ ስምምነት፤ በኢንተርኔት በተካሄደ የተቃውሞ ዘመቻ ታውኮ ነው ሳምንት ሳይሞላው የፈረሰው፡፡ ከ20ሺ በላይ ሰዎች በኢንተርኔት በተሰባሰበ ድምጽ ለተካሄደው የተቃውሞ ዘመቻና ውዝግብ እንደመነሻ ሆኖ የሚጠቀሰው ዐረፍተ ነገር “የአፄ ምኒልክ ጦርነቶች ቅዱስ ናቸው” የሚል አባባል ሲሆን፤ ቴዲ አፍሮ የኔ አባባል አይደለም በማለት ማስተባበሉ ይታወሳል፡፡ በምኒልክ ጦርነት ብዙ ሰው አልቋል በሚል የገፋው ተቃውሞ፤ በደሌ ከቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ጋር እንዳይተባበር ለሄኒከን ኩባንያ ጥያቄውን በማቅረብ እንዲሰረዝ አድርጓል፡፡

የቀድሞ የአገሪቱ ነገሥታትን በተመለከተ፣ በተለይም በአፄ ምኒልክ ዙሪያ ከየአቅጣጫው “መልካም ወይም መጥፎ ናቸው” የሚባሉ የንጉሱ ድርጊቶች እየተጠቀሱ በተደጋጋሚ የፖለቲካ ጭቅጭቆች፤ መነሳታቸው አዲስ አይደለም፤ በአንድ በኩል ምኒልክ ለአገሪቱ ነፃነት፣ አንድነትና ሥልጣኔ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ስልጣናቸውን ለማስፋፋት ባካሄዱት ጦርነት ግፍ ተፈጽሟል፤ ብዙ ህዝብ አልቋል ብለው የሚያወግዙም ጥቂት አይደሉም፡፡ በመሃል ደግሞ፣ በታሪክ የተከሰቱ ነገሮችን ወደኋላ ተመልሶ መለወጥ እንደማይቻል የሚገልፁ ወገኖች፤ መጥፎ ነገሮችን እያስተካከልን መልካም ነገሮች ላይ አተኩረን እየወረስን ማሳደግ አለብን በማለት ለማስታረቅ የሚሞክሩ አሉ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎችና ብሔረሰቦች የፈለቁ ጀግኖች ከአፄ ምኒልክ ጋር ለአገራቸው ነፃነትና ስልጣኔ ተጣጥረዋል በማለት ከአስታራቂዎቹ ወገን የተሰለፈው ቴዲ አፍሮ፤ የምኒልክን መቶኛ ሙት ዓመት በማስመልከት ለ“እንቁ” መጽሔት በሰጠው ቃለ ምልልስ፣ ካለፈው ዘመን የሚወረሱ መልካም ታሪኮችን ጠቅሶ፣ የስህተቶችና የጥፋቶች መድሃኒት ፍቅር ነው በማለት የዘረዘራቸው ሃሳቦች ታትመው ወጥተዋል፡፡

“የአፄ ምኒልክ ጦርነቶች ቅዱስ ናቸው” የሚል ሃሳብ ግን እንዳልተናገረና በመጽሔቱ እንዳልታተመ በመጥቀስ ያስተባበለው ቴዲ አፍሮ፤ በኢንተርኔት የተሰራጨው አባባል እኔን አይወክልም ማለቱ ይታወሳል፡፡ የበደሌ ቢራ ባለቤት የሆነው የአለማችን ታዋቂ ቢራ አምራች ኩባንያ ሄኒከን፤ የበደሌ ቢራ ፋብሪካ እና የቴዲ አፍሮ ስምምነት እንዲሰረዝ የወሰነው፤ እንደብዙዎች ኩባንያዎች ሁሉ አደባባይ በወጣ ውስብስብ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ መዘፈቅ ባለመፈለጉ እንደሆነ ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ እነዚሁ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለፁት፤ በደሌ ቢራ “የፍቅር ጉዞ” በሚል ስያሜ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ በበርካታ ከተሞች በተከታታይ ለሚካሄዱ ኮንሰርቶች 25ሚ. ብር ገደማ መድቦ ነበር፡፡ በደሌ 4.5 ሚ. ብር ለቴዲ አፍሮ ለመክፈል ተስማምቶ ውል ሲፈራረም 1.5 ሚ ብር የመጀመሪያ ክፍያ እንደፈፀመ የገለፁት እነዚሁ ምንጮች፤ በተለያዩ ከተሞች የሚቀርቡት ኮንሰርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ድምቀትን የተላበሱ ለማድረግ ከ20 ሚ. ብር በላይ ወጪ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ነበር ብለዋል፡፡ በደሌ ቢራ በራሱ መሪነት በሚያዘጋጃቸው ኮንሰርቶች ላይ፣ ከትኬት ሽያጭ የሚሰበሰበውን ገቢ ለበጐ አድራጐት ድርጅቶች ለመለገስ ሃሳብ እንደነበረውም ምንጮቹ ጠቅሰዋል፡፡

በደሌ ከኮንሰርቶቹ ዝግጅት ራሱን ለማግለል ሲወስን፣ ቀደም ሲል የተፈራረመውን ውል በሚመለከት ከቴዲ አፍሮ ጋር ተደራድሮ የውል ማፍረሻ ስምምነት መፈራረሙንም ምንጮቹ ገልፀዋል፡፡ የስምምነት ማፍረሻ ስምምነቱንና የክፍያውን መጠን በተመለከተ በደሌ እና ቴዲ አፍሮ ዝርዝር መግለጫ ካለመስጠታቸውም ባሻገር፣ ከሁሉም ወገኖች መረጃ ለማግኘት የተደረጉ ሙከራዎች አልተሳኩም። በድርድር የተቋጩ ጉዳዮች ላይ ተዋዋይ ወገኖች ጉዳዩን በተናጠል በይፋ ላለመግለጽ መስማማታቸው የተለመደ እንደሆነ ምንጮቹ ጠቅሰው፤ በደሌ የመጀመሪያ ክፍያውን ጨምሮ ለቴዲ አፍሮ 4.5 ሚ. ብር የሚከፍል መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ብለዋል፡፡ በኢንተርኔት ሲካሄድ የነበረው ዘመቻ፣ የበደሌ እና የቴዲ አፍሮ የስምምነት ውል ከፈረሰ በኋላ ቢረግብም፤ ያንን ተከትለው የመጡ ሌሎች ዘመቻዎች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ የቴዲ አፍሮን ኮንሰርት ለመቃወም የተጀመረው ዘመቻ፣ በተቃራኒ ኮንሰርቱን በመደገፍ ከተፈጠረው ሌላ ዘመቻ ጋር እንካ ሰላንቲያው ቀጥሏል፡፡ በቅርብ ጊዜ የሚካሄድ ኮንሰርት ባለመኖሩ ጭቅጭቁና ዘመቻው ምን ያህል የፌስቡክ ዕድምተኞችን ሳያሰለች ሊቀጥል እንደሚችል ገና አልታወቀም፡፡

ሻምበል ጉታ ዲንቃ፤ ጊዜውን ጠብቆ ይነጋል (ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም )

Prof. Mesfin Woldemariam

Prof. Mesfin Woldemariam

በአሁኑ ጊዜ ወያኔ ሰውን እያፈረሰ፣ ማህበረሰብን እያፈረሰ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻዎችን በሚሠራበት ጊዜ፣ ከትናንት ወዲያ የሰዎችን ቤቶች አፍርሶ ትናንት የመኪና መንገድ ከሠራ በኋላ ዛሬ መንገዱን አፍርሶ የባቡር መንገድ እየተሠራ አዲስ አበባ በትራፊክ መጨናነቅ መኪና መንዳት አደገኛ በሆነበት ጊዜ፣ ዛሬ ባለሥልጣኖች የሚሠሩት ጠፍቶአቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የሚባለውን በአማካሪዎች ከሞሉት በኋላ ለሚኒስትሮችም አማካሪ መሾም በተጀመረበት ጊዜ፣ ዛሬ በሳኡዲ አረብያ ኢትዮጵያውያን እንደአደገኛ አውሬ እየታደኑ በሚደበደቡበት፣ በሚታሰሩበት፣ በሚደፈሩበትና በሚገደሉበት ጊዜ፣ ዛሬ በኬንያና በዩጋንዳ እንዲሁም በእሥራኤል ኢትዮጵያውያንን የማንገላታት ዝንባሌዎች በሚታዩበት ጊዜ፣ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ከስዊድን እስከአውስትራልያ እየተሰበሰቡ በመጮህ ለማይሰሟቸው ሁሉ አቤቱታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ፣ ዛሬ በተለያዩ አገሮች በኢትዮጵያውያን ላይ በሚፈጸመው ጥቃትና በደል፣ አለሁላችሁ የሚል መንግሥት በሌለበት ጊዜ —- ዛሬ ታሪካዊትዋ ኢትዮጵያ፣ ራሳቸውን የሚያከብሩና ኩራት ራታችን የሚሉት ኢትዮጵያውያን አልቀው ለሆድ በየሰው አገር መሰደድ ባህል በሆነበት ጊዜ፣ ዛሬ ዶር. በድሉ ዋቅጅራ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን ውርደት ደጋግሞ የነፍሱን ኡኡታ ባሰማበት ጊዜ በድንገት አንገታችንን ቀና አድርጎ ኩራታችንን ሊያስጎነጨን የሞከረ ሰው ተገኘ! ኢትዮጵያ ሁሌም የተአምር አገር ነች።

በታላቁ ሰው በኔልሰን ማንዴላ እረፍት ምክንያት አንድ ተደብቆ የኖረ ክቡር ኢትዮጵያዊ ብቅ አለ፤ ማንዴላ ለሥልጠና በኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜ ምናልባትም እንግሊዞች ማንዴላን ሊያስገድሉ ከጠባቂዎቹ አንዱ የነበረውን ወታደር በገንዘብ ገዝተው ዓላማቸውን ለመፈጸም አቅደው ነበር፤ ወታደሩ ገንዘቡን ከተቀበለ በኋላ ሀሳቡን ለውጦ ገንዘቡን ለአለቃው ሰጠ፤ ማንዴላ ከሞት ተረፈ፤ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ራሱንና አገሩን የሚያስከብር ሥራ ሲሠራ የሚኮሰኩሳቸው ባለሥልጣኖች ለእነሱ የማይተላለፍ ክብር በመሆኑ ተዳፍኖ እንዲኖር አደረጉት፤ እነሱ ሞተው ወይም ተሰድደው ሲያልቁ የተዳፈነው ምሥጢር ብቅ አለ፤ ባለሥልጣኖቹ ሸልመውት ይሆናል፤ ግን አላከበሩትም፤ ሻምበል ጉታን ያከበረው የማንዴላ ሞት ነው፤ የሚያሳዝነው ማንዴላ ይህንን የሱን ሕይወት ለማትረፍ ሁለት ሺህ ፓውንድ ያጣውን ኢትዮጵያዊ ወታደር ሳያውቀው መሞቱ ነው።

የኢትዮጵያ አርበኞች ታሪካቸው ተቀብሮ የቀረው እንዲህ እየሆነ ነው፤ ታዴዎስ ታንቱ ሥራዬ ብሎ የተረሱ አርበኞችን ከመቃብር እያወጣ ያስተዋውቀናል፤ በሌሎች አገሮች እንደዚህ ለአገር ትልቅ ፋይዳ ያለው ሥራ በአንድ ሰው በበጎ ፈቃድ የሚሠራ ሳይሆን ዋና የመንግሥት ተግባር ነው።

ሻምበል ጉታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባይሆንም ራሱን ችሎ ለኔልሰን ማንዴላ መቃብር ደርሶአል፤ በአገር ደረጃ በሥልጣን ወንበሮቹ ላይ ለአገር የሚያስቡ ሰዎች አለመኖራቸውን ለማወቅ ግሩም ማስረጃ ነው፤ ለቀብር የሄደው ባለሥልጣን ሻምበል ጉታን ይዞ ቢሄድ ኖሮ ለራሱም ሆነ ለአገሩ ክብርና ጌጥ ይሆንለት ነበር፤ ለደቡብ አፍሪካ ሕዝብም ሆነ ለዓለም በመላ አንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር አልሸጥም-አልለወጥም ብሎ የኔልሰን ማንዴላን ሕይወት ማትረፉን በማስታወቅ አገሪቱን ያስከብር ነበር፤ የታፈነው ታሪክ አፈትልኮ ሲወጣ ከስደተኞች ጋር ተያይዞ መሆኑ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን የአደባባይ መክሸፍ የሚያሳይ ነው፤ ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ ተቀበለው፤ መንግሥት ያፈነውን ክብር ስደተኞች አጌጡበት!

ለእኔ አሁን አንድ ጥያቄ ይቀራል፤ ሻምበል ጉታ የአገሩን ክብር ከራሱ ጥቅም በላይ በማድረጉ፣ የተቀበለውን አደራ በመጠበቁ ቢያንስ ሁለት ሺህ ፓውንድ አጥቷል፤ እንዳጣ ሊቀር ነው? ቢያንስ የከፈለውን ሁለት ሺህ ፓውንድ ወይስ ያንን አሥር እጥፍ አድርገን እንከፍለዋለን? ሻምበል ጉታን የምናመሰግነው በርጥቡ ነው በደረቁ? እኛ ያለጥርጥር ኮርተንበታል፤ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን የሱን ክብር በመጋራት ራሳችንን አክብረናል፤ ሻምበል ጉታም በእኛ እንዲኮራና በእኛ እንዲከበር ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፤ ስለዚህ ምን እናድርግ? ለራሱ ክብር፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ክብር ሲል የከፈለውን እስቲ ከወሬ ያለፈ ነገር እናስብና ለዚህ ጀግና የምንችለውን አድርገንለት እግዚአብሔር ዕድሜ ይስጥህ እንበለው።