የባለሥልጣናት ሃብት ተመዝግቦ አያልቅም እንዴ?


የሃብታቸው መጠን ይፋ የሚደረገው ከስልጣን ሲወርዱ ይሆን? (ያመለጡን አሉ!)
በሃብት ምዝገባው ላይ የትዳር አጋርም ሊካተት ይገባል (መነጣጠቅ ተጀምሯላ!)
“Grand corruption” አለ የሚባለው ገንዘብ ሚኒስቴር ሲዘረፍ ነው እንዴ?
የእነቴሌ “የእንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት “ፅድቁ ቀርቶብኝ–” ያሰኛል!
ኢትዮ- ቴሌኮም በየበዓሉ የሚልከው የ “እንኳን አደረሳችሁ” መልካም ምኞት አሁን አሁን “ሙስና” እየመሰለኝ መጥቷል፡፡(ግራንድ ኮራፕሽን ሳይሆን ሚጢጢዬ ሙስና!) ለነገሩ ቢመስለኝም እኮ አይፈረድብኝም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ዓመቱን ሙሉ በብዙ የአገልግሎት አሰጣጦች ችግር ሲያማርረን ከርሞ — በዓል ሲደርስ እንደ ደህና አገልጋይ “እንኳን አደረሳችሁ” የሚለን ሊደልለን ካልሆነ በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? (“ደለለኝ — ደለለኝ” ነው ያለችው ድምፃዊቷ) ነፍሷን ይማረውና! እውነቴን እኮ ነው… ኔትዎርክ ሳይኖር፣ ኢንተርኔት ተቋርጦ፣ የቢሮና የቤት ስልክ ጠፍቶ… እንዴት ነው “እንኳን አደረሳችሁ” የሚለን? (ያውም ለእኛ አሻፈረኝ በሚለን ኔትዎርክ!) እኔ የምለው —- እኛና ቴሌ የምንተዋወቀው በስልክ አገልግሎት አይደለም እንዴ? (ከዚያ ውጭ የት ስንተዋወቅ ነው!) ከሁሉም የሚገርመኝ ደሞ ”ከመጪው ዘመን ጋር አገናኛችኋለሁ” የሚለው ፉከራው ነው፡፡ (“ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” አሉ!) እንኳንስ ከመጪው ዘመን… ከዛሬ ጋር እንኳን መች ተገናኘን! (ማን ነበር “አቅምን አውቆ ማደር ጥሩ ነው ታላቅ ችሎታ ነው” ያለው?!) አሁንማ ከምንፈልገው ሰው ጋር መገናኘት አይደለም— ሂሳብ ለመሙላትም ኔትዎርክ ማግኘት መከራ ሆኗል (ቴሌኮም በነፃም እንኳን ገንዘብ አልቀበልም እያለን እኮ ነው!) እስካሁን የውሃና የመብራት መ/ቤቶች ለገና በዓል “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት አለማለታቸውን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ምናልባት ሳልሰማቸው ብለውን ከሆነ ግን የእነሱንም ከ“ሙስና” ለይቼ አላየውም፡፡ ለምን ብትሉ… ገንዘብ የምንከፍልበትን ዋናውን አገልግሎት በቅጡ ሳናገኝ በየበዓሉ “እንኳን አደረሳችሁ” ማለት ለእኔ ተራ መደለያ ነው፡፡

(የመረረው ደንበኛ አታውቁም!?) ለነገሩ እዚህ አገር እኮ ቀድመው የሚናደዱት አገልግሎት ሰጪዎቹ እንጂ ደንበኞች አይደሉም፡፡ እኛ ደህና አገልግሎት የሚሰጠን አጣን ብለን ከመናደዳችን በፊት እነሱ ቀድመውን ይናደዱብናል (“ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ” አለች አስቱ!) እናላችሁ—የበዓላት ጊዜው ድለላ ቀርቶብን አንዴም ክፍያው ተቋርጦ የማያውቀውን የውሃና የመብራት አገልግሎት ሳይቆራረጥ፤ሳይጠፋ እናገኝ ዘንድ ለብዙ መቶኛ ጊዜ እንማጠናለን፡፡ (“Where is my beef?” አለ ፈረንጅ!) ምን እንደሚገርመኝ ታውቃላችሁ? ሦስቱም የመንግስት ተቋማት ለአገልግሎታቸው መቋረጥ የሚሰጡት ሰበብ ሁሌም ተመሳሳይ ነው – እንደሰነፍ ተማሪ እየተኮራረጁ፡፡ (አዲስ ሰበብ መፍጠር ሮኬት ሳይንስ ሆነ እንዴ?) እናላችሁ —- ውሃም መብራትም ኔትዎርክም የሚጠፉትና የሚቆራረጡት በ“ልማቱ” የተነሳ ነው፡፡ መብራት ለምን ይቋረጣል? ግድቦች እየተሰሩ ስለሆነ! ኔትዎርክ ለምን ይጠፋል? ኔትዎርክ እየተስፋፋ በመሆኑ! ውሃ ለምን ትጠፋለች? አዲስ የውሃ መስመር እየተዘረጋ ነዋ! ሰላማዊ ሰልፍ ለምን ታገደ? ልማቱን ለማፋጠን! እኔ የምለው ግን —- ነባሩ አገልግሎት ሳይቋረጥ፣ እኛም ሳንማረር — ልማቱን ማስፋፋት እንዴት አቀበት ይሆንብናል? ሳስበው ግን አቀበት ሆኖብን አይመስለኝም፡፡ በልማት ሰበብ የስንፍናን ካባ ደርበን ለሽ ስላልን ነው፡፡

(ልማትና እንቅልፍ መቼም ተስማምተው አያውቁም!) አሁን የምፈራው ግን ምን መሰላችሁ? ለምን ሙስና ያለቅጥ ዓይን አወጣ ብለን ስንጠይቅ —“የፀረ- ሙስና ዘመቻው ስለተጧጧፈ” የሚል ምላሽ እንዳንሰማ ነው፡፡ (ነገሩ ሁሉ እኮ ምፀት ሆኗል!) እኔ የምላችሁ ግን… ለምንድነው ግን ጦቢያን እንዲህ የጠላናት? ብንጠላትማ ነው… በየመንግስት መ/ቤቱ ቱባ ቱባ ሹማምንቶች የአገር ሀብት ዘርፈው የተያዙት! ብንጠላትማ ነው— ከአገርና ከህዝብ ላይ እየዘረፍን የ15 ሚ.ብር ዶዘሮች ስንገዛ ቅንጣት ታህል የማይቆረቁረን! ብንጠላትማ ነው… ከመንግስትና ከባለሀብት ላይ እየነጠቅን በሚስትና በዘመዶቻችን ስም በየባንኩ ብዙ ሚሊዮን ብሮችና ዶላሮች የምናከማቸው! ብንጠላትማ ነው… በሙስና ገንዘብ መንትፈን በየቦታው ግራውንድ ፕላስ 2 ምናምን የምንገነባው! የጠላነው ግን ጦቢያን ብቻ እንዳይመስላችሁ… ራሳችንንም ነው!! ቤተሰቦቻችንንም ነው!! ልጆቻችንንም ጭምር ነው!! በሙስና ተይዘን የመገናኛ ብዙሃን ዜና መክፈቻ ስንሆን ቀድመው የሚያፍሩብን እኮ ቤተሰቦቻችን ናቸው፡፡ ልጆቻችን ናቸው፡፡ ወዳጆቻችን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የሾመን መንግሥት ነው። የመለመለን ፓርቲ ነው፡፡

የማታ ማታም የጠላናት ጦቢያ—- በተራዋ አንቅራ ትተፋናለች፡፡ “እኒህ ከእኔ ማህፀን አልወጡም!” ብላ ትክደናለች (“ሰው የዘራውን ያጭዳል” አለ ታላቁ መፅሐፍ!) አሁን አሁንማ ወዳጆቼ… በመዲናዋ ዙሪያ እንደ እንጉዳይ የፈሉትን አማላይ ህንፃዎች ስመለከት ልቤ ድንግጥ ማለት ጀምሯል (“ከሙስና ነፃ” የሚል ታፔላ ይለጠፍባቸው!) ምን ህንፃዎቹ ብቻ… በኢቴቪ ብቅ እያሉ ስለ ኪራይ ሰብሰባቢዎች ፀረ – ልማት እንቅስቃሴ የሚደሰኩሩንን የመንግስት ሹማምንቶችም መጠራጠር ከጀመርኩ እኮ ቆየሁ! (ከቫይረሱ ነፃ የሆነውና ያልሆነው አይለይማ!) እንዴ…አንዳንዶቹ እኮ “አገሩን የሚወድ ሰው ሙስና አይፈጽምም” ብለው በነገሩን ማግስት ነው “ቫይረሱ” እንዳለባቸው በኢቴቪ የዜና እወጃ የምንሰማው! (ዕድሜ ለፀረ – ሙስና ኮሚሽን!) እኔ የምለው ግን —- የፀረ ሙስና ኮሚሽን በአገራችን Grand corruption የለም የሚል ነገር የተናገረው በግምት ነው እንዴ? በጥናት ላይ ተመስርቶ እንዳልሆነማ ራሱ እያሳየን እኮ ነው፡፡ (Grand corruption ቀላል አለ እንዴ!) የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቁንጮ ቁንጮ ሃላፊዎች ሲፈጽሙ የከረሙትን ሙስና ምን ልንለው ነው? (መቼም “ግራንድ ኮራፕሽን” ነው ለማለት የገንዘብ ሚኒስቴር ሙሉ በሙሉ መዘረፍ ያለበት አይመስለኝም!) እኔ የምለው ግን—-የመንግስት ባለስልጣናት ሃብት ተመዝግቦ አያልቅም እንዴ? ለነገሩ የአንዳንዶቹን የሃብት መጠን ለመመዝገብ እኮ አመትም የሚበቃው አይመስልም፡፡

ቦቴው፣ ዶዘሩ፣ ቪላው፣ በየባንኩ ያለው ገንዘብ፣ የጦር መሳሪያው፣ (የጦር መሳሪያም እንደ ሃብት ይቆጠራል እንዴ?) እኔማ አንዱ ወዳጄ “የባለስልጣናት ሃብት ተመዝግቦ አልቋል” ሲለኝ — እንግዲያውስ ከስልጣን ሲወርዱ ይሆናል ይፋ የሚደረግልን ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ (አንዳንዶቹ እኮ ሃብታቸው ሳይታወቅ እያመለጡን ነው!) በነገራችሁ ላይ የባለስልጣናቱን የሃብት ምዝገባ ጉዳይ ያነሳሁት ክፉ አስቤ አይደለም፡፡ ባለስልጣን ባየሁ ቁጥር “የሙስና ቫይረስ ይኖርበት ይሆን?” እያልኩ በመጠርጠር ሃጢያት እንዳልገባ ሰግቼ ነው፡፡ ከደሙ ንፁህ የሆኑ ባለስልጣናትስ ለምን ያለምግባራቸው ይጠርጠሩ? እናላችሁ —- የባለሥልጣናቱ የሃብት መጠን ቶሎ ተጠናቆ ይፋ ቢደረግ በጥርጣሬ ዓይን ከመተያየትና መረጃ ላይ ካልተመሰረተ ሃሜትና አሉባልታ እንድናለን፡፡ ሃሜት እኮ ሃጢያት ነው! መረጃ እንደ መንፈግ ግን አይሆንም!! የሃብት ምዝገባው ገና ካልተጠናቀቀ—- ይህችን ማዳበሪያ ሃሳብ ተቀበሉኝ (መዝጋቢውን አካል ማለቴ ነው!) ምን መሰላችሁ… በሃብት ምዝገባው ላይ የትዳር አጋርም መካተት አለበት የሚል ሃሳብ ስላለኝ ነው (መነጣጠቅ ተጀምሯላ!) በመጨረሻ አንድ የቤት ሥራ ጣል አድርጌ ልሰናበት፡፡ ይሄ የሥነ ዜጋ (ሲቪክ ኤጁኬሽን) ትምህርታችን እንደገና ይቀረፅ ይሆን እንዴ? (ሙስናው ቅጥ አጣ ብዬ እኮ ነው!)

Posted by- Alemayehu Tibebu

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s