ምሁራኑ ሠልጣኝ፣ ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ዩኒቨርሲቲ ሆኗል – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ


addis ababa university

መጽሔታችን የአገራችን የትምህርት ሁኔታበከፍተኛ ደረጃ ችግር ላይ የወደቀ መሆኑን በመገንዘብ፣ የችግሩን ጥልቀት ለማወቅና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማስቀመጥ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ካደረጉ ምሁራን ጋር ተከታታይ ውይይቶችንስታደርግ ቆይታለች፡፡ በዚህ ዕትማችንም ውይይቱን በመቀጠል ከዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጋር ስለትምህርት ፍልስፍና፣ ስለዩኒቨርሲቲ ተልዕኮና ስለሌሎቸ ተያያዥ ጉዳዮች ቆይታ አድርገናል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ለአብዛኛው የመገናኛ ብዙኃን ተከታታይ እንግዳ ስላልሆኑ ማስተዋወቅ ያለብን አይመስለንም፡፡ ውይይቱን እነሆ፡-

ዕንቁ፡-ውይይታችን በዩኒቨርሲቲባህሪና ትርጉም እንጀምር፡፡ ለመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ምን ማለት ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ከሁሉ አስቀድሞ ይኼ ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ መልስ የሚሰጠው ሳይሆን በተለያየ ጊዜና በተለያየ የባህልና የአመለካከት አውድ ውስጥ ተፈትሾ ለመግለጽ የሚሞከር ጉዳይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ በባህሪው የሕዝብ (‘ፐብሊክ’) እና የግል (‘ፕራይቬት’) የሆነ ልዩ ተቋም መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እንደሕዝብ ተቋምነቱ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተሰማርቶ ለማኅበረሰቡ ይውላሉ ወይም አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ነገሮች በማበርከት አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ እንደግል ተቋምነቱ ደግሞ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ የራሱ የሆነ ግብና ዕቅድ አንግቦ ለሰው ልጅ መንፈሳዊና አዕምሯዊ ብልጽግናንናበአጠቃላይ ዕውቀትን ለማጎናጸፍ የተቋቋመማዕከል ነው፡፡

አሁን የበላይነት ወደያዘው የአገራችን የትምህርት ፍልስፍና ስንገባ፣የዩኒቨርሲቲዎች ሕልውና የተመሰረተበትን የግል ጥሪና ፍላጎት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ተቋማቱን የሕዝብ አገልግሎት አቅራቢ ብቻ ለማድረግመንግሥትና የዩኒቨርሲቲዎቹ የበላይ አስተዳዳሪዎች ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ በመሆኑም ለማኅበረሰቡ “ቀጥተኛ ጥቅም” አይሰጡም ያሏቸውን እንደፍልስፍና፣ ታሪክ፣ ሥነ-ጽሁፍ፣ ቋንቋና ሌሎች የሥነ-ሰብዕ ትምህርቶች እንዲቀጭጩ መደረግ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች አልመረጡም በሚል ፈሊጥ የቅድመ-ምረቃ ፕሮግራሙ ወደመዘጋት እየደረሰ ነው፡፡

ዕንቁ፡-የዩኒቨርሲቲን ተፈጥሮና ጠባይ ከሞላ ጎደል ለመመልከት ትንሽ ወደታሪክ መመለስ ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለመሆኑዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም እንዴት ተጀመረ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ይኼ ጥያቄ ማንም ሰው እንደሚረዳው ሰፋ ያለ ትንታኔና ገለጻ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ሆኖም ግን ጥቂት ነገሮች ለመግለጽ ያህል፣ በዚህ መስክጥናት ያደረጉትምሁራንእንደሚነግሩን ዩኒቨርሲቲ አውሮፓበ13ኛው እና በ14ኛው ክፍለ ዘመን ከደረሰችበት የመንፈስ፣ የባህል፣ የፍልስፍና… ወዘተ ሥልጣኔ የመነጨ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ታሪክ ዙሪያ ከጻፉት ምሁራን መካከል እውቅናን ያገኙትና በሰፊው የሚጠቀሱት ‘ቻርልስ ሆሜር ሀስኪንስ’ (Charles Homer Haskins) ናቸው፡፡ እንደሳቸው አቀራረብ ዩኒቨርሲቲ ከጥንታዊ ግሪኮችና ከሮማውያን ሥልጣኔ ጋር ግንኙነት ቢኖረውም በይዘቱና በጠባዩ የመካከለኛው ዘመን ውጤት ነው፡፡

ከአዕምሯዊ ይዘቱ አካላዊ ወደሆነው ቅርጹናአደረጃጀቱስንመጣ፣ ‘ሀስኪንስ’ በታሪክ ድርሳናቸው ላይእንዳብራሩትለዩኒቨርሲቲ (ግቢ) መፈጠር ምክንያት ከሆኑት ውጫዊ ሁኔታዎች መካከል በወቅቱ ተማሪዎችን የገጠማቸውየቤት ኪራይ ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜብዙ ተማሪዎች ትምህርት ለመቅሰም ወደከተማ ይጎርፉ ነበር፡፡ የተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የቤት ኪራይ ዋጋም በጣም እየናረ ሄዶ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች የሚከፍሉትን የቤት ኪራይ ወጪ ለመቀነስ በአንድ ላይ መሰባሰብና በጋራ በመሆንተደራድረው የቤት ኪራይ ማስቀነስ ጀመሩ፡፡ ይሄ አንዱ ምክንያት ነው፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ ከአስተማሪዎች የሚመጣው ችግር ነበር፡፡ ይኸውም በአንድ በኩል ገንዘብ እየተቀበሉ ከማስተማር ሥራቸው የሚጠፉ መምህራን ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይኼ ነው የሚባል የትምህርት ዝግጅት ወይም የማስተማር ችሎታ ሳይኖራቸው “መምህራን ነን” የሚሉም ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ተማሪዎች ተሰብስበውና ተቋም ፈጥረው አስተማሪዎችንሕጋዊ ግዴታ ያስገቧቸው ጀመር፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸውን የሚያሳይ ሰርተፊኬት መጠየቅምተጀመረ፡፡ ይህ ሰርትፊኬት ቀስ በቀስ ለዲፕሎማና ለዲግሪ መፈጠር አስኳል ሆነ፡፡

ዕንቁ፡- አንደኛው የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ ዕውቀት ማመንጨት ነው ካልን፣ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የዕውቀት ድርሻ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-የዩኒቨርሲቲን ተልዕኮና የእውቀትን ድርሻ በሚመለከት ሁለት አበይት የሆኑ ክርክሮችና አመለካከቶችአሉ፡፡ አንደኛው፣ ከ300 ዓመት በፊት በአጠቃላይ ስለ ትምህርትና ስለዕውቀት ጠቃሚነት የጻፉት (የሳይንስ አብዮት ጀማሪዎች ከሚባሉት አንዱ)እንግሊዛዊው ሮጀር ቤከን እንዳስተማሩት ዕውቀት ከተግባር ተለይቶ ሊታይ የማይችል፣ ለሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ (በጤና፣በእርሻ …ወዘተ)አስተዋጽኦ ማድረግ ያለበት ነገር ነው፡፡በቤከን እምነት ዕውቀት የዕድገት ወይምየኑሮ ማሻሻያ መሳሪያ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የሚጠቀስላቸው አባባል እንደሚነግረን ለእርሳቸው ‹‹ዕውቀት ማለት ሀይል ነው››፡፡

ወደ ሁለተኛው አመለካከት ስንመጣ ደግሞ ከመቶ ዓመታት በፊት “The idea of the University” በሚል ርዕስ ወሳኝ ድርሳን የጻፉትን ካርዲናል ኒውማንን እናገኛለን፡፡ እንደ እርሳቸው አመለካከት ዕውቀት የራሱ ተልዕኮ አለው፡፡ እንደ መገልገያ መሳሪያ ብቻ ሊታይ አይገባውም፡፡ ዕውቀት የሰውን ልጅ አዕምሮ የሚኮተኩትና ሰውን የተሟላ ፍጡር የሚያደርግ ነው፡፡

እነኝህን ሁለት የአመለካከት ዘይቤዎች መሰረት አድርጎ አሁንም አልፎ አልፎ ክርክሩ ቢቀሰቀስም፣ ባለንበት ዘመን አንድ ዩኒቨርሲቲ የተሟላ ነው የሚባለው ቢያንስ ቢያንስ የሚከተሉትን ሦስትዕቅዶች አንግቦ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ ይኸውምየመማር ማስተማር ሂደት የሚከናወንበት፣ ዕውነት ላይ ለመድረስ ጥናትና ምርምር የሚደረግበትና በልዩ ልዩ መስክለማኅበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጥበትተቋም ነው፡፡ በመሆኑም ምርጫው የሮጀር ቤከን “ጥቅማዊ” መንገድ ብቻ ወይም የካርዲናል ኒውማን“አዕምሮን ማበልጸግ” የተናጠል አስተሳሰብ አይደለም፡፡

dagnachew assefa

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

አሁን በአገራችንመንግሥት እየተከተለ ያለውንየትምህርት ፍልስፍና ስንመለከት፣ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ችግር-ፈቺና ቁሳዊ ጥቅምን ማምጣት የሚችሉመሆን አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ይኼም ማለት፣ ትምህርት ራሱ በራሱ በጎና አስፈላጊ ነገር ሳይሆን መንግሥት ላቀደው የትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት አጋርና አካል መሆን አለበት ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲውን በሚመለከት አንድ ትልቅ እንደ ደንቀራ ሆኖ የገጠመን ችግር ይኼ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ወደፊት በሚቀጥለው ዕትም በሰፊው እንመጣበታለን፡፡ ከወዲሁ ግን ከችግሩ አኳያ አንድ ሁለት ነገሮች ብቻተናግሬ ልለፍ፡፡ በሌላ ጉዳይም ላይ ተደጋግሞ እንደሚታየው ሁልጊዜም በባህላችን መካከለኛ መንገድ ከመምረጥ ይልቅ ነገሮችን ከአንድ ወይም ከሌላ ጥግ ብቻ የማየት ግድፈት አለብን፡፡

ሁለተኛ፣ ገዥው ግንባር በሌሎች ጥያቄዎችም ላይ እንደሚያደርገውችግር ብሎ ለሚያነሳቸው ጉዳዮች በሙሉ አንድ ብቸኛ መፍትሄ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አባዜ አለበት፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ ‹‹ከቀረበው የመፍትሄ ሃሳብ ውጪ የተለየ አቀራረብ ሊኖር አይችልም›› የሚለው ወይም ደግሞ ‹‹አማራጭ የለም››የሚለው አመለካከት ምርጫ የሚያሳጣ ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ነጻነትን በእጅጉየሚጋፋም ነው፡፡ እንዲያውም በሕግ የሰው ልጆችን አስተሳሰብ ከመገደብ የበለጠ ጫና የሚፈጥረውና ነጻነት ገፋፊ የሚሆነው በተወሰነ ጥያቄ ዙሪያ አማራጮችን ዘግቶ ልክ አንድ ብቸኛ መፍትሄ እንዳለ አድርጎ የማቅረብ አካሄድ ነው፡፡ ይኼ ‹‹እኔ ካቀረብኩት የመፍትሄ አማራጭ ውጪ ሌላ መንገድ ሊኖር አይችልም›› የሚለው አካሄድ ዩኒቨርሲቲዎችን አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲከተሉ እያደረጋቸው ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲ የሰው ልጅ በረዥም ታሪኩ ያከማቻቸው የአዕምሮ ውጤቶች ተጠብቀው የሚቀመጡበት፣ ለአዲሱ ትውልድ የሚተላለፉበትና በታሪክ ውስጥ የተነሱ ጥያቄዎች የሚፈተሹበት፣ የሚመለሱበት… ወዘተ ማዕከል ነው እንጂ የፖለቲካ አስተዳደሩ ወሳኝ ናቸው የሚላቸውን ጉዳዮች ብቻ እንግቦ የሚንቀሳቀስ ተቋም አይደለም፡፡ አንድ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ተልዕኮዬ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት መስጠት ብቻ ነው›› የሚል ከሆነ ሕልውናውን እንደዩኒቨርሲቲ ያጣል፡፡ዩኒቨርሲቲ ዕውቀት ፈልገው የሚመጡት ተማሪዎች ማኅበረሰቡ ሊያቀርብላቸው ወይም ሊያስተምራቸው የማይችለውን ትምህርትና ተሞክሮ የሚቀስሙበት አምባም ነው፡፡

ዕንቁ፡-በዘመናችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ወይም የበላይነት የያዘው ትምህርት ፍልስፍና ምንድን ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ወደ አሁኑ ዘመን የትምህርት ፍልስፍና በምንገባበት ጊዜ ብዙ ጸሐፍት አራት ዋና ዋና ንድፈ-ሃሳቦችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው መሠረታዊነት ወይም ‘ፐረኒያሊዝም’ የሚባለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይኼን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚሉት የሰው ልጅ ተፈጥሮ (በየትኛውም ቦታ ቢኖር) ተመሳሳይ ነው፤ ዕውቀት የትም ቦታ አንድ አይነት ነው፡፡ ስለሆነም የሚሰጠው ትምህርትም አንደ አይነት ወይም ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ የሰው ልጅ ምክንያታዊ እንስሳት ነው፤ ይህ ምክንያታዊነቱ ግን መኮትኮት አለበት፡፡ የአስተማሪው ተቀዳሚ ሥራ ደግሞየሰውን ልጅ ምክንያታዊነት መኮትኮት ነው፡፡ ትምህርት ዘለዓለማዊ የሆነ ዕውነትን የሚያስተምር ነው፤ ለኑሮ የሚያዘጋጀ መሳሪያምነው፤የሰው ልጅ ወሳኝ ወይም መሠረታዊ የሆኑ እንደሥነ-ጽሁፍ፣ ታሪክ፣ ሒሳብ፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ጥበብ … ወዘተ ትምህርቶችን መማር አለበት፡፡ እንዲሁምተማሪዎች ያለፈውን (ሊቃውንትትተውት ያለፉትን) ዕውቀት መማርና መመርመር አለባቸው፡፡

ሁለተኛው፣ አመለካከት ደግሞ ‘ፕሮግረሲቪዝም’ የሚባለው ነው፡፡ ይኼን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ ትምህርት በየጊዜው እየጎለበተ የሚሄድ ነገር በመሆኑ መምህራን ራሳቸውን በዕውቀትና በማስተማር ዘዴ በየጊዜው ማሻሻል አለባቸው፤ትምህርት ራሱ ሕይወት ነው እንጂ ለሕይወት የሚደረግ ዝግጅት አይደለም፤ማወቅ ማለት መተንተንና የሕይወት ተሞክሯችንን መረዳት ማለት ነው፤ ትምህርት ከተማሪው ፍላጎት ጋር መዛመድ አለበት፤ ተማሪው ሌላ ሰው “ይህን ተማር” ስላለው ሳይሆን የሚፈልገውንና ለእርሱ አስፈላጊ የሆነውን ትምህርት ነው መማር ያለበት፤ዕውቀት ተፈላጊ የሚሆነውአንድ ነገር ልናደርግበት ስንችል ብቻ ነው፤ የመምህሩ ሚና ማማከር እንጂ አቅጣጫ ማስያዝ አይደለም፤ ትምህርት ቤት ውድድር ሳይሆን ትብብርና መደጋገፍ የሚፈጠርበት ቦታ ነው፤ ነጻ የሆነ የሃሳብ ልውውጥ ሊፈጠር የሚችለው በዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡

ሦስተኛው፣ አመለካከት ‘ኢሴንሻሊዝም’ የሚባለው ሲሆን፣ አመለካከቱን የሚያራምዱ ምሁራን እንደሚሉት የሰው ልጅ ተምሯል የሚባለው መሠረታዊ የሆኑ ትምህርቶችን ሲያውቅ ነው፡፡ መማር ከፍተኛ ጥንካሬ የሚጠይቅ ነገር ነው፤ መማር የማንፈልገውን የትምህርት ዓይነት መማርን ጭምር የሚያካትት ሲሆን ለመማር ደግሞ ‘ዲሲፕሊን’ በጣም አስፈላጊ ነው፤ትምህርት የሚሰጠው “ተማሪው ምን ይፈልጋል?” የሚለውን መሠረት አድርጎ ሳይሆን “ለተማሪው ምን ያስፈልገዋል?” የሚለውን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ተማሪው የሚማረው የማይፈልገውን ትምህርት እንኳን ቢሆን በሂደት እየተማረ ሲሄድ ይወደዋል ብለው ያምናሉ፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት የሚያርፈው በአስተማሪው ላይ ነው፤ ስለዚህ አስተማሪው ወሳኝ ነው፡፡ ትምህርት ሰዎች የውስጥ አቅማቸውን እንዲያወጡ የሚረዳ መሳሪያ ነው፡፡

አራተኛው፣ አመለካከት ‘ሪኮንስትራክሽኒዝም’ይሰኛል፡፡ ትምህርት አዲስ የኅብረተሰብ ሥርዓት (social order) ለመፍጠር ማገልገል አለበት፤ ትምህርት ማኅበረሰቡን ለመለወጥና ለመሻሻልመዋል አለበት፤ ትምህርት የተሻለ የኑሮ ግብ የምንመታበት መሳሪያ ነው፤… ወዘተ የሚሉትን ሃሳቦች የሚያራምድ አመለካከት ነው፡፡

ዕንቁ፡-ከላይ የተመለከትናቸው የትምህርት ንድፈ-ሃሳቦች ከጥንታዊው እና ከአሁኑ ዘመን የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና ጋር እንዴት ይዛመዳሉ?
ዶ/ር ዳኛቸው፡-ከሁሉ አስቀድሞ ይኼ ጥያቄ በጣም ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ሦስት በዚሁ ጉዳይ ላይ የተጻፉ ድርሳናትን መመልከቱ ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንደኛ የዛሬ 45 ዓመት ገደማ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ዳኜ በ“ውይይት” መጽሔት ላይ “የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና” በሚል ርዕስ የጻፉት ጽሑፍ፣ ሁለተኛ፣ የዶ/ር ሀይሉ ፉላስ “Knowledge and Its Attainment in the Ethiopian context” (The Ethiopian Journal of Education June 1974 vol.7 no.1) የሚለው ጽሑፍና ሦስተኛ፣ ዶ/ር ተሾመ ዋጋው የጻፉት “The Development of Higher Education and Social Change an Ethiopian Experience” (1990) የሚለው መጽሐፍ በጣም ጠቃሚ ድርሳናት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

addis-ababa-police

ፌዴራል ፖሊስ ኬኔዲ ቤተመጻህፍት አካባቢ (ቆየት ካሉ ፎቶዎች)

እነኝህን ሦስቱን ድርሳናት በምናይበት ጊዜ፣ጥንታዊው የኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና ከላይ ‘ፐረኒያሊዝም’ ብለን ከጠቀስነው የትምህርት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ የተዛመደ መሆኑንእንረዳለን፡፡ የጥንታዊ ኢትዮጵያ የትምህርት ፍልስፍና በመሠረታዊነት በክርስትና ወይም በእስልምና አስተምህሮት ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ስለ እግዚአብሔር ጠባይ፣ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋራ ስላለው ግንኙነት፣ ስለዓለም አፈጣጠር …. ወዘተ ያለቀለት ወይም ዳግመኛ ምርምር የማይጠይቅና በቅዱሳን መጽሐፍት ላይ ተመርኩዞ የሚጠና ነው፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ከሃይማኖት አበው ጠቅሰው እንደጻፉት ‹‹ነአምን ዘእንበለ ተኅሥሦ›› (ሳንመረምር ሚስጥራቸውን እንቀበላለን) የሚለው አባባል ይኼንን ነጥብ በሚገባ ያብራራዋል፡፡ ይኼ አንደኛው አስተምህሮት ነው፡፡

ሁለተኛው፣ አስተምህሮት ዓለም በሁለት ነገሮች እንደተከፈለችው ሁሉሰውም በሁለት ነገሮች የተከፈለ ነው የሚለው ነው፡፡ የዓለም አከፋፈል ሰማያዊና ምድራዊ ሲሆን የሰው ልጅ አከፋፈል ደግሞ ነብስና ሥጋ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ሰማያዊ ዓለሙ ምድራዊ ዓለሙን እንደሚመራ ነብስ ደግሞ ሥጋን እንድትመራ ይጠበቃል፡፡ የቀለም ትምህርት ዓላማው ቅዱሳት መጽሐፍትን እያስተማረ ለሚመጣው ዘለዓለማዊ ዓለም ማዘጋጀት ነው፡፡

ሦስተኛ፣ አስተምህሮት ደግሞ ይህች ዓለም አላፊና ጠፊ በመሆኗ ከንቱ ናት፤ ሰማያዊው ዓለም ግን ዘለዓለማዊ ደስታን ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ይኼ እንግዲህ ቁሳዊ ብልጽግናንና ዕድገትን አያበረታታም፡፡ ዶ/ር ኃይለገብርኤል ይኼን አስተሳሰብ በሚመለከትሲጽፉ ‹‹ባህላችን ቀለም ለተማረ ሰው ከእጅ ሠራተኛና ከገበሬ የበለጠ ደረጃ ሰጥቶታል›› ይላሉ፡፡

በኔ እምነት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ትልቅ ቦታ የነበራቸው በቴክኒክ፣ በግንባታ/ምህንድስና፣ በልዩ ልዩየእደ-ጥበብ ሥራዎች … ወዘተ የተሰማሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ክርስትናና እስልምና ከሙጡ በኋላ ቀደም ሲል ትልቅ ቦታ ይሰጣቸው የነበሩት ተሽረው ካህናትና ኡለማዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛውን ቦታ እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ ምናልባት የአገሪቱ የቁሳዊ ሥልጣኔና ብልጽግና ከአክሱም በኋላ ወደታች እየወረደ የመጣው ከዚህ የዕሴት ለውጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡

ለማጠቃለል፣ የአገራችንም ሆነ የምዕራቡን ዓለም የ‘ፐረኒያል’ አመለካከት ስንመለከት አንደኛ፣ ሁለቱም ማለትም የኢትዮጵያው ቁዱሳን መጽሐፍትን፣ የምዕራቡ ዓለም ደግሞጥንታዊ የግሪክና የሮማውያን ድርሳናትን አይሻሩም፣ አይለወጡም፣ አይጠየቁም የሚሉ ናቸው፡፡ሁለቱም በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይየአስተማሪው ድርሻ ትልቅ እንደሆነናአካላዊ ቅጣት ዋና የማስተማሪያ መሳሪያ እንደሆነም ይቀበላሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፣ ትምህርት ማለት መንፈሳዊና አዕምሯዊ ብቃትን ማዳበርነው፤ ከሃይማኖትና ከባህል የተረከብነውን እውቀት እናጠናዋለን እንጂ ወደፊት ሌላ የዕውቀት ግኝት እናመጣለን በሚል ተስፋ ምርምር የምናካሄድበት ዘርፍ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡

አሁን ወዳለንበት የትምህርት ፍልስፍና በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ፣ ከ‘ኮንስታረክሽኒዝም’ና ከ‘ፕሮግረሲቪዝም’ አስተሳሰቦች ጋራ የተዛመደ አመለካከት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ትምህርት በይዘቱ ማኅበራዊ የኑሮ ደረጃን የሚለውጥ መሳሪያ ነው፤ማኅበረሰብን ከመለወጥ ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም፤በተጨማሪም የትምህርት ተቀዳሚ ትኩረት መሆን ያለበት በትምህርቱ ይዘት ላይ ሳይሆን ችግር ፈቺ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጥያቄ ላይ ነው፤ በመሆኑም የሚመረጠው የትምህርት ዓይነት የሚወሰነው የማኅበረሰቡን ችግር ይፈታል ወይስ አይፈታም ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ ትምህርት ተማሪውን ያማከለና የተማሪውን አጠቃላይ ፍላጎት የሚያሟላ መሆን አለበት፤ የትምህርት ሥርዓቱ በየጊዜው እንዳስፈላጊነቱ መሻሻልና መለወጥ አለበት…ወዘተ የሚሉት አመለካከቶች ከወቅቱ የአገራችን የትምህርት ፍልስፍና ጋር በእጅጉ ይዛመዳሉ፡፡ ወደአገራችንሁኔታ በምንመጣበት ጊዜ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገ ትምህርት የልማት አጋር በመሆን መንግሥት ያቀደውን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ አስፈጻሚ መሆን አለበት የሚል አቋም ተይዟል፡፡

ዕንቁ፡-እስካሁን የተነጋገርንበትን ጉዳይ ማለትም ስለ ትምህርት ፍልስፍና ስለጥንታዊውና አሁን ስላለው የትምህርት ይዞታ በሚቀጥሉት ዕትሞቻችን ላይ በሰፊው እንቀጥላለን፡፡ ለአሁኑ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ዩኒቨርሲቲ መጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ ስለደሞዝ ጭማሪ የተናገሩት አስካሁን ድረስ በማነጋገር ላይ ያለ ጉዳይ ስለሆነየእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? የሚለውን ይግለጹልን፡፡

ዶ/ርዳኛቸው፡-ዩኒቨርሲቲ ከሕዝብም ሆነ ከፖለቲካ አመራሩ ክፍል የሚመጣ ሃሳብ የሚፈትሽበት፤ለማኅበረሰቡም ሆነ ለአስተዳደር ክፍሉ ገንቢ አስተያየቶችንና አመለካከቶችን የሚቀርቡበት ተቋም ነው፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ በተገላቢጦሹ ሃሳብና ምክር ይፈልቅበታል በሚባለው ተቋም ሹመኞች በተለያየ ምክንያት እየመጡ አስተማሪዎችን እየሰበሰቡ የሃሳብና የምክር አቅራቢነት ሚና መጫወታቸው በጣም ያስገርማል፡፡ በተለያየ ጊዜ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን እየሰበሰቡ ከኃይማኖት እስከ ልማት፣ ከዕድገት እስከ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ … ወዘተ “አሰልጣኞች” ተመድበው “ሥልጠና” ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለማብራራት በቅርቡ አቶ ብርሃኑ አስረስ ከጻፉት መጽሐፍ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከታህሳሱ ግርግር በኋላ ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ ተይዘው ፍርድቤት በቀረበቡበት ወቅት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲጠየቁ “የተናቀ መንደር ‘በምንትስ’ ይወረራል” ብለው የተረቱት ተረት ሁኔታውን በሚገባ የሚገልጸው ይመስለኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሠልጣኝ የመንግሥት ሹመኞች አሰልጣኝ የሆኑበት ግቢ ሆኗል፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን የደሞዝ አንሶናል ጥያቄውን ሲመልሱ ‹‹እናንተ እውቀትና ክህሎት ያላችሁ በመሆናችሁ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ተንቀሳቅሳችሁ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ትላላችሁ›› ብለው ነበር፡፡ መምህራንን ከተመደቡበት የማስተማር ውጪ ሌላ ተፎካካሪ ሥራ “ሥሩ” ብለው መምከራቸውና በመማር ማስተማርሂደቱ ላይ ጫና እንደሚፈጥር አለመገንዘባቸው አስገሞኛል፡፡ መቼም ይኼ “ምክር” ለአብዛኞቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች አዲስ ነገር ሆኖ እንደማይገኝ ጥርጥርየለኝም፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን “ከማስተማር ውጪ በኮንሰልታንሲም ሆነ በልዩ ልዩ መንገድ ገንዘብ ይገኛል” ብሎ መንገር ለነብር “ሚዳቋ ወይም ጥንቸል ትበላላች” ብሎ እንደመምከር ይሆናል፡፡

ደሞዝን በሚመለከት ከመምህራኑ ይበልጥ በጣም እየተጎዱ ያሉት የጥበቃ፣ የጽዳት፣ የካፍቴሪያና የአትክልተኛነት ሥራዎችን የሚሰሩት ሠራተኞች ናቸው፡፡ እነኚህ ሠራተኞች የሚሰሩት ሥራ ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ሆነ ሳለ የሚከፈላቸው ደሞዝ ግን እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይበልጥ የሚገርመው ደግሞ ሰባት እና ስምንት ዓመታት ያህል ያገለገሉ ሠራተኞች ደሞዝ ይጨመርልናል ብለው ሲጠብቁ “ቋሚ አድርገናችኋል” በሚል ፈሊጥ የደሞዝ ቅነሳ ተደርጎባቸዋል፡፡ ይኼ በእጅጉ የሚያሳዝንና ፍትሃዊነት የጎደለው እርምጃ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በበኩሌ ዩኒቨርሲቲው አንጋፋና ትልቅ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ስሙንና ክብሩን በጠበቀ መልኩ ለእነኝህ ሰዎች ደህንነት አስቦ የደሞዝ ማስተካከያ ማድረግ አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደጽዳት ሠራተኞች በምንሄድበት ጊዜ ደግሞ ያለው ችግር ተገቢ ደሞዝ ያለማግኘት ብቻ ሳይሆን ከጤንነትምጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቅርቡ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ስለማቀርብ ለጊዜው በዚሁ ይብቃን፡፡(ምንጭ: ዕንቁ መጽሄት)

Posted By Alemayehu Tibebu

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s