አንበሶች የራሳቸው… እስኪኖራቸው ድረስ


ከዳንኤል ክብረት
በቤኒን በጋናና በቶጎ የሚገኙ ኢወ- ሚና(Ewe-mina) የሚባሉ ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ በተረቶቻቸው፣ በአባባሎቻቸውና በምሳሌዎቻቸው እጅግ የታወቁ ናቸው፡፡ ከሚታወቁባቸው አባባሎች አንዱ አዳኝና አንበሳን አስመልክተው የተናገሩት አባባል ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ አባባል በናይጄሪያ፣ በታንዛንያና በኬንያ ማኅረሰቦችም ጭምር የሚነገር የታወቀ አፍሪካዊ ታላቅ ፍልስፍና ቢሆንም ምንጩ የኢወ ሚና ማኅረሰብ ሊሆኑ እንደሚችል ብዙዎች ገምተዋል፡፡
ኢወ- ሚናዎች የታሪክ አጻጻፍንና የታሪክ አነጋገርን ያኄሱበት፣ እንደ ቼኑዋ አቼቤ ያሉ ታላላቅ አፍሪካውያን ደራስያንም ነጮች በአፍሪካ ታሪክ ስነዳ ላይ ያደረሱትን በደል ለመግለጥ የተጠቀሙበት ታላቁ አባባላቸው ‹‹አንበሶች የራሳቸው ታሪክ ነጋሪ እስኪኖራቸው ድረስ፣ የአደን ታሪክ ምንጊዜም አዳኙን ከፍ ከፍ እንዳደረገ ይኖራል(Until Lions have their own historians, tales of the hunt shall always glorify the Hunter) የሚለው ነው፡፡
በኢወ- ሚና ማኅበረሰብ አደን እጅግ የሚያስመሰግን የጀግና ሥራ ነው፡፡ አዳኞች ለብዙ ቀናት ከአካባቢያቸው ርቀው ‹ታግለውና አሸምቀው› በማደን ታላላቅ አራዊትን ተሸክመው ወደ አካባቢያቸው ሲመጡ ሠፈርተኛው በእልልታና በሆታ ይቀበላቸዋል፡፡ እነርሱም አንበሳውን ወይም ዝሆኑን እንዴት እንደገደሉት፣ ያደረጉትን ትግልና የተጠቀሙበትን ድንቅ ዘዴ፣ ተአምራዊ በሆነ መልኩ እንዴት ከሞት እንዳመለጡና ያንን አንበሳ እንዴት ድል እንደነሡት ለሀገሬው ሕዝብ በኩራት ይተርካሉ፡፡
ከአዳኙ ትረካ፣ ከያዘውም ግዳይ የተነሣ አንዳንድ ጊዜ አዳኙ ልክ አማልክታዊ ኃይል ያለው አካል መስሎ እስከመታየት ይደርስ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አዳኞችን የተመለከቱ ዘፈኖች፣ ግጥሞችና ተረቶች ሁሉ በአዳኞቹ ድንቅና ገናና ድርጊቶች የተሞሉ፣ ታዳኙን ንቀው አዳኙን የሚያንቆለጳጵሱ፣ የአዳኙን ግርማና ሞገስ አወድሰው ታዳኙን የሚያንኳስሱ ሆነዋል፡፡
ኢወ ሚናዎች ምንም እንኳን አዳኞቹን ቢያሞግሱ፣ ቢያወድሱና በአዳኞቻቸው ገድልም ቢኮሩ፣ ምንም እንኳን አዳኞቹን ቢሸልሙና የከበሬታ ሥፍራ ቢሰጡ ነገር ግን አዳኙና ታዳኙ በጫካ ውስጥ ብቻቸውን ፊት ለፊት በተፋጠጡ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በአዳኙና በታዳኙ መካከልም የተከናወነውን ነገር ሁሉ፣ አዳኙ ያደረገውን፣ የደረሰበትንና ታዳኙ የፈጸመውን ሁሉ እንዳልሰሙት ዐውቀዋል፡፡ አንበሳው የተገደለው በተኛበት ቢሆንስ? አንበሳው የታመመ አንበሳ ቢሆንስ? አዳኙ አንበሳን የገደለው በአጋጣሚ ቢሆንስ?  አንበሳው በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከባድ ተጋድሎ አድርጎ ከሆነስ? የሚለውን ጥያቄም ጠይቀዋል፡፡
አሁን ታዳኙ አንበሳ የለም፤ ያለው አዳኙ ብቻ ነው፡፡ የአንበሳን ወገን ገድል የሚዘክርለት የለም፡፡ እርሱ ታሪኩን የሚያወራለት፣ ተጋድሎውን የሚመሰክርለት፣ አሟሟቱ የክብርና የጀግንነት ሞት ቢሆን እንኳን ያን የሚተርክለት የለም፡፡ አሁን ታሪኩን የሚተርከው፣ ስለ አንበሳውም የሚናገረው፣ ራሱን ጀግና አንበሳውንም ፈሪ አድርጎ የሚያወራው አዳኙ ብቻ ነው፡፡ አዳኙ ስለራሱም ይናገራል፣ ስለ አንበሳውም ይናገራል፡፡ምስኪኑ አንበሳ ሁለት ጊዜ ነው የሞተው፡፡ በአካልና በታሪክ፡፡ ዘፈኑም፣ ቀረርቶውም፣ ፉከራም፣ ተረቱም፣ አዳኙን እንዲያሞግስ ያደረገው ታሪክ ነጋሪው አዳኙ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ኢወ- ሚናዎች ታሪኩ የተሟላ የሚሆነው አዳኙም ታዳኙም ታሪካቸውን የመናገር እድል ሲኖራቸው መሆኑን ዐውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አንበሶች የራሳቸው ታሪክ ነጋሪ እስኪኖራቸው ድረስ፣ የአደን ታሪክ ምንጊዜም አዳኙን ከፍ ከፍ እንዳደረገ ይኖራል›› በማለት የተናገሩት፡፡
የአንድን ማኅበረሰብ ልዕልና ከሚያስጠብቁት፣ ነጻነቱን ከሚያስከብሩለት፣ ርእዮቱን ከሚቀርጹለት ነገሮች አንዱ የታሪክ ንግርቱ ነው፡፡ የታሪክ ንግርት የአንድን ማኅበረሰብ ሞራል ለመግደልም ሆነ ለማዳን፣ ተገዥ ሆኖ እንዲኖርም ሆነ ነጻ እንዲወጣ፣ ክብር ወይም ውርደት እንዲሰማው፣ ለራሱ የሚሰጠው ዋጋ እንዲወርድ ወይም እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡
ስምኦን ሜሳን የተባሉ በአሜሪካ ኒው ጀርሲ የሚኖሩ አፍሪካዊ ጸሐፊ ለዚህ አባባል በምሳሌነት የሚያነሡት በግብጽ የነበሩ እሥራኤላውያንን ታሪክ ነው፡፡ እሥራኤላውያን ግብጽ ውስጥ ለ400 ዓመታት ያህል ሲኖሩ ግብጻውያን በተደጋጋሚ የሚነግሯቸው ሦስት ዘውጎች ያሉት የታሪክ ትርክት ነበሯቸው፡፡ ‹‹እናንተ ሀገር አልባ የግብጽ ስደተኞች ናችሁ፣ እናንተ ነጻ አውጭ የሌላችሁ ባሪያዎች ናችሁ፣ እናንተ የከበሬታ ሥፍራ የማይገባችሁ ወራዶች ናችሁ››፡፡ እነዚህ ነገሮች የተፈጠሩት በግብጻውያን ነው፡፡ ግብጻውያኑ የአዳኙን ቦታ ይዘው ነበርና ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የታሪክ ትርክቱን ይቆጣጠሩት ነበር፡፡ ደጋግመው የመናገር መብትም ስለነበራቸው ራሳቸውን እሥራኤላውያኑን እንኳን አሳምነዋቸው ነበር፡፡
የሙሴ መነሣት በእሥራኤል ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጣው የራሳቸው ታሪክ ነጋሪ በማግኘታቸው ነበር፡፡ እስከዛሬ ከገዥዎቻቸው፣ ከጨቋኞቻቸውና ከአስገባሪዎቻቸው ግብጻውያን ሲሰሙት ከነበረው የማንነታቸው ትርክት የተለየ፣ ለእነርሱም ሌላ ማንነትን ሊፈጥርላቸው የሚችል፣ ስላበት ሁኔታ አዲስ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ ታሪክ ነጋሪ ተገኘ፡፡ አንድ ማኅበረሰብ እንደ ሙሴ ዓይነት ሰዎችን ሲያጣ የሚጎዳም ለዚህ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ገዥዎችና ጨቋኞች እንደ ሙሴ ዓይነት የታዳኙን ታሪክ ሊነግሩ የሚችሉ ሰዎች እንዳይነሡ፣ ከተነሡም እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉትም ይህንን ስለሚያውቁ ነው፡፡
የእሥራኤላውያን የማንነት ግንዛቤ ሙሴ ወደነርሱ ሲመጣ ተለወጠ፡፡ የሙሴ መምጣት የመጀመሪያወን ለውጥ ያመጣው በእሥራኤል የኑሮ ሁኔታ ላይ አይደለም፡፡ በታሪክ ንግርታቸው ላይ ነው፡፡ ሙሴ አዲስ ታሪክ ነጋሪ ሆኖ ብቅ አለ፡፡ አሁን የአዳኙን ብቻ ሳይሆን የአንበሳውን ገድል የሚተርክ የታሪክ ንግርት መጣ፡፡ ሙሴ መጀመሪያ የቀየረው ሦስቱን የትርክቱን ዘውጎች ነበር፡፡ ‹‹እናንተ ሀገር አልባዎች ስደተኞች ናችሁ፡፡›› ይሏቸው ነበር፡፡ ሙሴም ‹‹ስደተኞች አይደለንም፤ ነገር ግን በበደላችን ምክንያት የተቀጣን ነን፤ አሁን ፈጣሪ ይቅር ብሎናል፣ ከነዓን የምትባል ሀገርም ተዘጋጅታልናለች፣ ከዚህ ወጥተንም እንገባባታለን›› ብሎ ነገራቸው፡፡ የተስፋ ሀገርም ሰጣቸው፡፡ የሚጓጉላት፣ የሚሞቱላት፣ ሀገር፡፡ በአንድ ወቅት እስራኤላዊው ነጻ አውጭ ቴዎዶር ኸርዝል ‹‹እኔን የሚቆጨኝ የምኖርባት ሀገር ስለሌለኝ አይደለም፣ የምሞትላት ሀገር ስለሌለኝ እንጂ›› እንዳለው፡፡
‹‹እናንተ ባሪያዎች ናችሁ›› ሲሏቸው ሙሴ ግን ‹‹እናንተ የተጨቆናችሁ ጭቁኖች ናችሁ፣ ባሪያዎች አይደላችሁም፡፡ ጭቁኖች ናችሁና ከጭቆና ነጻ ትወጣላችሁ›› አላቸው፡፡ ግብጻውያኑ ‹‹እናንተ ዝቅተኛ ማኅበረሰቦች ናችሁ›› ሲሏቸው ሙሴ ግን ‹‹እናንተ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝቦች ናችሁ፣ ራሱ እግዚአብሔርም ነጻ ያወጣችኋል›› ብሎ ነገራቸው፡፡ ሙሴ እሥራኤል የነበሩበትን ሁኔታ አይደለም የቀየረው፡፡ በግብጽ ነበሩ፣ እንደ ባሪያ ይገዙ ነበር፣ ዝቅተኛ ማኅበረሰቦችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሙሴ የታሪክ ትርክቱን ነው የቀየረው፡፡ ማንነታቸውን የሚያዩበትን ዓይን ነው የቀየረው፡፡ ይህንን ለመቀየር የተቻለው ታሪክ ነጋሪው ሙሴ በመሆኑ ነበር፡፡
ለአንደ ማኅበረሰብ የራሱ ታሪኮች፣ ተረቶች፣ አባባሎች፣ አፋዊ ታሪኮችና ሌሎችም የሚያስፈልጉት በራሱ መንገድ የራሱን  የዓለም የሚያነጽርባቸው መሣሪያዎች ስለሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በጣልያን ድል ተደርገው የአምስት ዓመቱ የፋሺስት አገዛዝ ሲመጣ የፋሺስቶች የታሪክ ትርክትና የኢትዮጵያውያን የታሪክ ትርክት መለያየት ነው የአርበኝነት ትግሉን ያስጀመረው፡፡ ኢትጵያውያን ሽንፈቱን እንዴት ነበር ያዩት፣ አዝማሪዎቹ፣ ፎካሪዎቹ፣ የእምነት መምህሮቹ፣ ትንቢት ተናጋሪዎቹ፣ ምንድን ነበር ትርክታቸው? ይህ ሁሉ ለምን መጣብን? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ ምን ነበር?
ገለል በሉና ገለል አርጓቸው
ወደመጡበት ወዳገራቸው
ለነዚህ ጣልያኖች መድኃኒት ስጧቸው
የሚያስቀምጥ ሳይሆን የሚያስመልሳቸው
አርኩም ይሄድና ሶልዲውም ያልቅና
 ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና
የሚሉትና ሌሎችም የሕዝቡ ትርክቶች የጣልያንን መመለስ፣ በኢትዮጵያ ምድር ለዘለዓለም ለመቆየት እንደ ማይችል የሚገልጡ ነበሩ፡፡ ይኼ ትርክት ‹ነጭን ማሸነፍ አይቻልም፣ አሜን ብላችሁ ለጣልያን ተገዙ› እያሉ ይለፍፉ በነበሩት የጣልያን ፕሮፓጋንዲስቶች ሕዝቡ እንዳይዋጥ አድርጎታል፡፡ ምንም እንኳን የእነዚህ ታሪክ ነጋሪዎች ትርክት በወቅቲ ነባራዊውን ሁኔታ ባይቀይረውም፣ ነባራዊውን ሁኔታ ለመቀየር እንዲቻል ግን የአርበኞችን የመመልከቻ መነጽር ቀይሮታል፡፡ ታሪክ ነጋሪዎቹ ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ክፉ ዘመናት እያነሡ፣ እነዚህን ክፉ ዘመናት እንዴት እንደተሻገረች እየተረኩ፣ ይህም ሊያልፍ የሚችል እንጂ ነዋሪ አለመሆኑን ይገልጡ ነበር፡፡ ኢጣልያ በየቦታው ያደረገችውን ጦርነት በራስዋ ሚዲያና ፕሮፓጋንዲስቶች በኩል በመለፈፍ የሕዝቡን ቅስም ለመስበርና ሁሉም ነገር አልቋል ብሎ እንዲቀመጥ ለማድረግ ሞክራ ነበር፡፡ ታሪኩ የአዳኞችን ብቻ እንዲገልጥ ጥረት አድርጋም ነበር፡፡ አንዳንድ አርበኞች ሲያዙ፣ በአደባባይ ሲገደሉ፣ አንዳንድ ባንዶች እጃቸውን ሲሰጡ፣ ስለ ጣልያን ታላቅነትና ደግነትም ሲመሰክሩ ሕዝቡ የአዳኞቹን ብቻ ገድል እንዲሰማ ተሞክሮ ነበር፡፡
ነገር ግን አልሆነም፡፡ በወሬውም፣ በተረቱም፣ በዘፈኑም፣ በቀረርቶውም፣ በፉከራም፣ በባሕታውያኑም፣ በልቅሶ ሙሾም፣ በወፍጮ ፈጭውም፣ በውኃ ወራጁም ግጥም ውስጥ የጀግኖቹ ስምና ዝና፣ ገድልና ታሪክ እየተነሣ ከሀገር ሀገር ተዛመተ፡፡ የታሪክ ትርክቱ በሕዝቡ እጅ መሆን፣ የተማረኩትንና የተገደሉትንም ቢሆን እንደ ተሸናፊ፣ እንደ ድል ተነሺ ሳይሆን እንደ ሰማዕታትና እንደ ጀግና እንዲታዩ አደረጋቸው፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በእንግሊዞች ተከብበው፣ በመጨረሻ ራሳቸውን በሽጉጣቸው አጠፉ፡፡ እንግሊዞች ድል አድራጊዎችና ማራኪዎች ሆነው፣ ዐፄ ቴዎድሮሰ ድል ተነሺና ተማራኪ ሆነው ነገሩ ተጠናቀቀ፡፡ ይህንን ነገር ኢትዮጵያውያን እንዴት ነው የተረኩት? ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ታሪክ የማንጽፍ፣ የራሳችንን ታሪክም የማንተርክ ቢሆን ኖሮ አሁን የምናውቃቸውንንና የጀግና ምሳሌ ያደረግናቸውን ዐፄ ቴዎድሮስን ልናገኛቸው ባልቻልን ነበር፡፡ አንዳንድ የታሪክ ሰዎች እንዲያውም ‹‹ሕዝቡ የሚያውቃቸው ቴዎድሮስና ታሪካዊው ቴዎድሮስ ይለያያሉ››  እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ሕዝቡ የአዳኞችን ትረካ እንደማይስማማበት የገለጠው ወዲያው በጦርነቱ ጊዜ መሆኑን የምንረዳው
ገደልንም እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
ማረክንም እንዳይሉ ሰው የለም በጃቸው
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው
ለወሬ አይመቹም ተንኮለኞች ናቸው
በማለት መግጠሙን ስናይ ነው፡፡
የዐድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት በተጠናቀቀ ጊዜ በአፍሪካ በቅኝ ገዥነት የተሠማሩት አውሮፓውያን ትልቁ ሩጫቸው ዜናው በኢትዮጵያውያን መንፈስ እንዳይሰማ ማድረግ ነበር፡፡ ቢቻል ፈጽሞ ዜናው እንዳይደርስ፣ ካልሆነም ደግሞ የኢትዮጵያውያንን የአሸናፊነት መንፈስ በጠበቀ መንገድ እንዳይሰማ፣ እንዲሁ ተራና መናኛ ዜና ሆኖ እንዲቀር ማድረግ፡፡ የዐድዋ ጦርነት ቅኝ ገዥዎች ለአፍሪካውያን ሲተርኳቸው የኖሩትን ሦስት ትርክቶች ያፈረሰ ጦርነት ነበር፡፡ ‹‹ነጭን ጥቁር አያሸንፍም፣ አሸንፎም አያውቅም፡፡ ጥቁሮች እንዲገዙ፣ ነጮች እንዲገዙ የአምላክ ትእዛዝ ነው፤ አፍሪካ ታሪክ የላትም፣ ታሪኳ የቅኝ ግዛት ታሪክ ነው›› ፡፡
የዐድዋ ጦርነት እነዚህ ሦስቱን መሠረታውያን የቅኝ ግዛት ትርክቶች አፈረሰ፡፡ ነጭን ጥቁር ሕዝብ አሸነፈ፡፡ በአስደናቂ ሁኔታ በአንድ ቀን ጦርነት አሸነፈ፤ ነጮች ተማረኩ፡፡ ነጮች ጥቁሮችን እንዲገዙ ከእግዚአብሔር የተፈቀደ ነው፤ ለነጮች አለመገዛት የፈጣሪን ትእዛዝ አለማክበር ነው ይባሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን ታቦት ይዘው ወጥተው፣ ስመ እግዚአብሔር ጠርተው፣ ያውም በዕለተ ጊዮርጊስ፣ ቀሳውስቱና ደባትሩም አብረው ዘምተው ጣልያንን ድል አደረጉ፤ የኢትዮጵያ አምላክ ለነጭ ታዘዙ የሚል አምላክ አለመሆኑን አሳዩ፤ ኢትዮጵያውያን ነጭ ቅኝ ገዥዎችን ድል ሲያደርጉ የተቆጣ፣ የቀሰፈ አምላክ አልታየም፡፡እንዲያውም አብሮ ተዋጋ፡፡ የራስዋ ታሪክ ያላት፣ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ የኖረች፣ ለማንም ያልተንበረከከች አንዲት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መኖሯም ታወቀ፡፡ ጥቁርም ታሪክ አለው፡፡ ከቅኝ ገዥዎችም በፊት ታሪክ ነበር የሚለው ታወቀ፡፡
የዐድዋ ጦርነት እነዚህን ሦስት ትርክቶች ሻረ፡፡ ይህን ነው ቅኝ ገዥዎች ከአፍሪካውያን ሊሠውሩት የሞከሩት፡፡ ይህ የአድዋ ጦርነት በአፍሪካውያን ዘንድ ሲሰማ የፀረ ቅኝ ግዛት ስሜትን ቀስቅሶ ነበር፣ እኛ የምናምነው በኢትዮጵያ አምላክ ነው የሚሉ ኃይሎችን አስነሥቶ ነበር፡፡
የአንድን ሕዝብ ማንነት፣ መንገድና መዳረሻ ለመወሰን ዋነኛው መሣሪያ የዚያን ሕዝብ ትርክት መቀየር ነው፡፡ ስለራሱ፣ ስለ ማንነቱ፣ ስለ ታሪኩ፣ ስለ ጀግኖቹ፣ ስለ እሴቶቹ፣ ስለ ክብሩና ዝናው፣ ስለ ጀብዱውና የት መጣው የሚተርከውን ነገር መቀየር፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ማነነት፣ እምነት፣ አቋምና ስለ ነገሮች የሚኖረው ምላሽ ከትርክቶቹ የሚሠራ ነው፡፡ እኛ የታሪክ፣ የተረት፣ የአባባል፣ የአፈ ታሪክ፣ የእምነት ትምህርት፣ የቀረርቶ፣ የሽለላ፣ የሙሾ፣ የዘፈን ትርክቶች ውጤቶች ነን፡፡ ከምግብ ንጥረ ነገሮች በላይ በእነዚህ ንጥረ ነገሮች ተገንብተናል፡፡ እነዚህን በቀየርን ቁጥር አብሮ ሰብእናም ይቀየራል፡፡
ጣልያኖች አዲስ አበባ እንደገቡ ታዋቂ አዝማሪዎችን ካዛንቺስ መሸታ ቤት እየጠሩ፣ ራቁቷን ያለች ሴት ሥዕል አቁመው ለፀጉሯ፣ ለዓይኗ፣ ለጥርሷ፣ ለአንገቷ፣ ለደረቷ፣ ለወገቧ፣ ለሽንጧ፣ ለዳሌዋ፣ ለባቷ ፣ እንዲዘፍኑ ያደርጓቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ስለ ሴት ልጅ ውበት የሚገልጡበት የራሳቸው ነባር ትርክት ጠፍቶ አውሮፓዊ በሆነውና ውጫዊ አካልን ብቻ በሚያሞግሰው ሌላ ትርክት እንዲተካ አደረጉት፡፡ ከዚያም የዘፈኖቻችንን ባህል፣ እኛም ስለ ሴቶቻችን የሚኖረንን እሳቤ አውሮፓዊ ርእዮት ሰጡት፡፡
የዘመናችን ሚዲያዎችና የፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎች ትልቁ ሚናቸው የተራኪነቱን ሚና መውሰድ ነው፡፡ ተራኪነቱን የወሰደ ታሪኩን ይወስነዋል፡፡ ማን ጀግና እንደሆነ፣ ማን ድል እንዳደረገ፣ ማን ታሪክ እንደሠራ፣ ማን እንዳደገ፣ ማን እንደታገለ፣ ማን ታላቅ እንደሆነ፣ ማን እንደሠለጠነ፣ ማን ነጻ እንዳወጣ፣ የሚወስነው ታሪክ ነጋሪው ነው፡፡ የአደን ታሪክ ምን ጊዜም አዳኙን ይከተላልና፡፡ ማንዴላ ለአፓርታይድ ነጮች አሸባሪ፣ ወንጀለኛ፣ ሀገሩን የካደ፣ የዕድሜ ልክ እሥራት የሚገባው አረመኔ ነው፡፡ ማንዴላ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ነጻ አውጭ፣ ታጋይ፣ ጀግና፣ ለሀገሩ የሚሞት፣ የነጻት አባት፣ ቆራጥ፣ ደቡብ አፍሪካዊ ነው፡፡ የሁለቱም ሰው ግን ማንዴላ ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ለፋሺስቶች ወንበዴና ሞት የሚገባቸው ወንጀለኛ ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ቆራጥ፣ የጀግኖች ኮከብ፣ የጽናት ተምሳሌት፣ የእምነት አባቶች አርአያ የሆኑ ጀግና ናቸው፡፡ ታሪኩ የተወሰደበት – ጀግናውን ያጣል፣ አርአያውን ይነጠቃል፣ አይከኑ ይሰበርበታል፣ ኩራቱ ይወሰድበታል፤ ሌላ ማንነትም ይሰጠዋል፡፡ እርሱ ከብት ቢኖረውም አፍ ያለው ከብቱን ይወስንለታል፡፡ ታሪክም አንበሳውን ትቶ አዳኙን ብቻ እንዳገነነ ይቀጥላል፡፡ አንበሳው ነጋሪ የለውምና፡፡
ኳታር    

© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s