Archive | March 8, 2014

ፓትርያርኩ ‹‹ቤተ ክርስቲያን በዩኒቨርስቲ ምሩቃን አትመራም” ማለታቸው ቅሬታ ፈጠረ

ስለማኅበራት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት ተጠየቀ

‹‹ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከል ይገባል›› – መንግሥት

c202cea0c2c3f4fe8e4357a6180470ed_M
(addisadmass) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ‹‹ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ቤተ ክርስቲያንን እንምራ እያሉ ነው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊትና ሥርዓት አላት፤እንዲህ ማለት አይችሉም›› በማለት የሰጡትን አስተያየት መልሰው እንዲያጤኑት በንግግራቸው ቅር የተሰኙ የመንፈሳውያን ማኅበራት አገልጋዮች ጠየቁ፡፡
አገልጋዮቹ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ አቡነ ማትያስ ይሄን አስተያየት የሰነዘሩት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ከኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጋር በመተባበር የካቲት 21 እና 22 ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል የምክክር ጉባኤ በተካሔደበት ወቅት ነው፡፡
በምክክር ጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹በባዮሎጂና ኬምስትሪ እንቀድስ እያሉ ነው፤›› ያሉት አቡነ ማትያስ፤ ‹‹ምን እያልኹ እንደኾን ይገባችኋል›› በማለት ማንን እንደሆነ የማሳየት ያህል የጠቆሙበት አስተያየት ያልተለመደና ጥቂት የማይባሉ የጉባኤውን ተሳታፊዎች ያሳዘነ እንደነበር የጉባኤው  ምንጮች አመልክተዋል፡፡
በምክክር ጉባኤው ላይ ለውይይት በቀረቡ ጽሑፎች፣ እስከ ሰማንያ ሺሕ የሚገመቱ መንፈሳውያን ማኅበራት በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በአዲስ አበባ እንደሚንቀሳቀሱ የተጠቀሰ ሲሆን  ቤተ ክርስቲያኒቱ ማህበራቱ በሕግና በሥርዐት የሚመሩበት ደንብ አውጥታ እስካልተቆጣጠረቻቸው ድረስ እየተከሠቱና ሊከሠቱ የሚችሉ ችግሮች በቀላሉ እንደማይታዩ ተመልክቷል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፤በማኅበር ሽፋን ለግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው የሚሯሯጡ፣ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ሕጸጽ የሚታይባቸው ማኅበራት የመኖራቸውን ያህል ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው፣ ምእመናንን በማትጋት ለበለጠ ሀብተ ጸጋ የሚያበቁ ጠንካራ ማኅበራትም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምክክር መድረክና በቤተ ክህነቱ ጉባኤያት እየታየ ያለው “ማኅበራት አላሰራ አሉን” በሚል በጅምላ የመፈረጅና የመኰነን ዝንባሌ፣ አብዛኞቹ ማኅበራት ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን እያበረከቱ ያለውንና  በቤተ ክህነቱ ቀጥተኛ አቅም ሊሸፈን የማይችለውን ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት ያላመዛዘነ ነው ብለዋል -የማህበራት አገልጋዮች፡፡
“በአሁኑ ጊዜ ማኅበራት የአባሎቻቸውንና የበጎ አድራጊ ምእመናንን የገንዘብ፣ የዕውቀትና ሞያዊ አቅም በማስተባበር የገጠር አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ት/ቤቶች በተቀናጀ መንገድ እንዲረዱ ያደርጋሉ፤ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ዕድገት የሚጠቅሙ ልዩ ልዩ ጥናቶችን ያካሒዳሉ፤ በጠረፍ የሀገሪቱ ክፍል በሚያከናውኑት የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ምእመኑ በቋንቋው የሚገለገልበትን ኹኔታ ያመቻቻሉ፤ የቅዱሳት መካናት ተሳላሚዎችን ጉዞ በማስተባበር ሕዝቡ ቅርሱንና ባህሉን አውቆ እንዲጠብቀውና እንዲከባከበው ከማስቻላቸው ባሻገር ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መስፋፋትና መጠናከርም ያላቸው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡” ሲሉ የማህበራትን ጥቅም አብራርተዋል፡፡
ማኅበራቱ አብዛኞቹን ተግባራት የሚያከናውኑት በየደረጃው ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሓላፊዎች ፈቃድ እያገኙና መመሪያ እየተቀበሉ መኾኑን የሚገልጹት አገልጋዮቹ፣ በግንቦት 2004 ዓ.ም. የማኅበራትን ቁጥር ስለመቆጣጠር ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ በነበረው ጥናት መነሻነት ምልዓተ ጉባኤው ራሱን የቻለና ማኅበራቱን የሚያሠራ ሕግ እንዲዘጋጅ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሕግ ባለሞያዎች ያሉበት ደንብ አዘጋጅ ኮሚቴ ሠይሞ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ የማኅበራት አደረጃጀትና የፋይናንስ ቁጥጥር መርሕን ጠብቆ እንደሚወጣ ሲጠበቅ የቆየው ደንብ ከሚገባው በላይ መዘግየቱ ችግሩ ከቤተ ክህነቱ እንጂ ከማኅበራቱ አገልግሎትና ብዛት አለመኾኑን እንደሚያመለክት ይከራከራሉ፡፡
ፓትርያርኩ አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማስተዳደር በዕለተ ሢመታቸው ቃለ መሐላ መፈጸማቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በምክክር ጉባኤው ላይ በተጠቀሰው አኳኋን የመናገራቸው ግፊት የተለያየ መነሻ ሊኖረው እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመጀመሪያው መንሥኤ፣ የሙስናንና ብልሹ አሠራርን ችግር ለመቅረፍና ለማድረቅ በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተሠራው የመዋቅር፣የአደረጃጀትና የአሠራር ጥናት ተቃዋሚዎች የጥናቱ ባለቤት ነው በማለት በሚከሡት ማኅበረ ቅዱሳን ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር አማካይነት እንዲፈጠር የሚሹት ጫና ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ በመንግሥት በኩል፣ ‹‹በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚታየው ህልውናቸውና ዓላማቸው ሃይማኖታዊና በሃይማኖቱ የበላይ ጠባቂዎች ይኹንታ በተቋቋሙ የወጣት ማኅበራት አደረጃጀቶች ውስጥ በመሸጉ አካላት ነው፤ ስለዚህም ማኅበራት በትኩረት ሊመሩና ጉዟቸውም እየተፈተሸ ሊስተካከሉ  ይገባል፤›› የሚለው ክሥ በመሪዎቹ ላይ ያሳደረው ማኅበራቱን የመቆጣጠር ጫና ነው፡፡
የአክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ምንነትና መፍትሔዎችን በሚተነትኑት የመንግሥት ሰነዶች፣ የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ከሚባሉት ኹኔታዎች ውስጥ÷ የሃይማኖት ተቋማቱ የሰው ኃይል አስተዳደርና የፋይናንስ ሥርዐት ለተከታዩ ሕዝብ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌላቸው መኾናቸው፣ በሙስናና በአስተዳደር በደል ሳቢያ የሚፈጠር ግጭት፣ የሰው ኃይል አስተዳደር በዘመድ አዝማድና በጉቦ እየኾነ የሥራ ብቃት በሌላቸው ሰዎች የሚሠራበት፣ የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ የሚተችበትና አስተያየት የሚሰጥበት ሥርዐት አለመዳበሩ፣ ተከታዮችን አክራሪነትን የሚቋቋም በሃይማኖት ዕውቀት የማስታጠቅ ክፍተት ይገኙበታል፡፡
በመንግሥት ትንታኔ መሠረት፣አክራሪነትን የመዋጊያው ቁልፍ መሣሪያ ልማትንና ዕድገትን በማፋጠን የመልካም አስተዳደር ችግርን መቅረፍ፣ሕዝቡን በሃይማኖታዊ ዕውቀት ማስታጠቅ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማትን ለአክራሪነትና ጽንፈኝነት ተጋላጭ ያደርጓቸዋል የተባሉት የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሠራር ችግሮች÷ ማኅበረ ቅዱሳን በተቃዋሚዎች አላግባብ በሚከሠሥበት የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ትግበራ በማፋጠን እንዲኹም ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ በርካታ ማኅበራት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የገዳማትና የአብነት ት/ቤት ማኅበረሰብን በልማትና ተራድኦ ከመደገፍ ጀምሮ በሚያከናውኑት ሐዋርያዊ ተልእኮ ንቃት ሊወገድ እንደሚችል ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያምናሉ፡፡ ከዚኽም አንጻር ፓትርያርኩ ንግግራቸውን መልሰው በማጤን ማኅበራት አገልግሎታቸውን አጠናክረው ለመቀጠል የሚያስችላቸው ኹኔታ እንዲያመቻቹ ጠይቀዋል፡፡

“ለስድስት ወር ያልጋ ቁራኛ የዳረገኝ የግድያ ሙከራ” የኢየሩሳሌም አርአያ እውነተኛ ታሪክ

የሞት “ድግስ”

መስከረም 4 ቀን 1996ዓ.ም ለኢትኦጵ ጋዜጠኛ የስልክ ጥሪ ይደርሰዋል። “ በነገው እለት ከቀኑ 6ሰአት መስቀል አደባባይ በሚገኘው የትግራይ ልማት ዋና ቢሮ 4ኛፎቅ እንድትገኝ” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪ ነበር የደረሰው። ከዛ በፊት ለስድስት ወር የአየር መንገድ የደህንነት ሃላፊ ሃይሌ ጋዜጠኛውን ሲያስጨንቀው፣ የተለያዩ የማግባቢያ ወይም መደለያ ሃሳቦችን ሲያቀርብለት ቆይቷል። መስከረም 2 ቀን ደግሞ በቀበሌ 06/07 መ/ር ቢሮ እንዲገኝ የሚገልፅ መጥሪያ ቢደርሰውም በአጋጣሚ ጋዜጠኛው ስላልተመቸው አልሄደም። በማግስቱ የቀበሌውን ሊ/መ አቶ ቢሻው አበጋዝን ያገኘውና « ትላንት ፈልጋችሁኝ ነበር፤ ለምን ነበር?» ሲል ይጠይቀዋል፤ ቢሻውም « እኛ አይደለንም የፈለግንህ፤ ከደህንነት ቢሮ የመጡ ሰዎች ናቸው የፈለጉህ፤ ባለመምጣትህ ተናደው ነው የሄዱት፤ ለምን እንደፈለጉህ አልነገሩንም፤» በማለት መለሰ። …ከዛ በኋላ ነው – የመስከረም 4 ጥሪ የደረሰው፤ በማግስቱ በተባለው ቢሮ ተገኘ። ከ30 ደቂቃ ቆይታ በኋላ የማህበሩ ዳይሬክተር « ከሚፈልጉህ የበላይ አካላት ጋር አገናኝሃለሁ» በማለት ለጋዜጠኛው ተናግሮ በሚያሽከረክራት ኒሳን መኪና ተያይዘው ቦሌ በሚገኘው የደህንነት ቢሮ አመሩ።..ከአንድ ግዙፍና አስፈሪ ገፅታ ካለው ሰው ጋር ጋዜጠኛውን አገኛኝቶት ወጥቶ ሄደ። ..« እሺ ኢየሩሳሌም አርአያ..» አለ ንቀት በተሞላበት ሁኔታ፤ አስከተለና፥ « ወ/ስላሴ እባላለሁ፤ ….ከእኛ ባልደረባ ጋር ስትገኛኝ ነበር፤ መንግስት ብዙ አማራጮችን አቅርቦልህ..አንተ ግን አሻፈረኝ ብለሃል። ለመሆኑ የምታወጣቸው መረጃዎች ተፅፈው ነው የሚሰጡህ?…ለምንድነው መረጃ የሚሰጡህን የሕወሐት ሰዎች የማትነግረን?..የምናስራቸው፣ የምንጠይቃቸው መስሎህ ነው?…» ሲል ሹሙ ሲናገር፣ ጋዜጠኛው ግን የቀረቡትን መደራደሪያዎች እንደማይቀበል ተናገረ። ለሁለት ሰአት ተኩል ከደህንነት ሃላፊው ጋር ውዝግብ የተቀላቀለበት ቃላት ተለዋወጡ። በተለይ የደህንነት ሹሙ « ..የትግራይ ተወላጅ ያውም ቤተሰብህ አድዋ ሆነው..እንዴት ፀረ-ሕወሐት ትሆናለህ?..ከጠላቶቻችን አንዱ ከሆነው ኢትኦጵ ጋዜጣ ጋር እንዴት ትሰራለህ?..» እያለ ከመናገሩ በተጨማሪ « እንዳንተ የተለማመጥነውና የታገስነው የለም። ብንገድልህስ?..» ሲል በንቀት ሲጠይቅ፣ ጋዜጠኛውም « ምንም ጥያቄና መልስ አያስፈልገውም፤ አሁኑኑ ሽጉጥህን መዘህ ልታደርገው ትችላለህ። እኔ ብእር እንጂ የያዝኩት – ከጀርባዬ ያሰለፍኩት ሰራዊትና መሳሪያ የለም። ..ደግሞም ለስልጣን ያበቋችሁን 36ሺህ ታጋዮች ላይ ምን እንደፈፀማችሁ ስለማውቅ..» አላስጨረሰውም፤ ..« እሱ አይመለከትህም፤ ከማን ጋር ምን እያወራህ እንዳለህ እወቅ!?..ከዚህ በኋላ እንድታስብበት የ15 ቀን ጊዜ ብቻ ሰጥተንሃል። በነዚህ ቀናት አቋምህን አስተካክለህ፣ የተባልከውን ካልፈፀምክ ግን…እንገድልሃለን!! ማንም አያድንህም!! ጨርሻለሁ።» በማለት አምባረቀበትና አሰናበተው። ..ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ረቡዕ መስከረም 20 ቀን 1996ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 ሰአት ገደማ በመኖሪያ ቤቱ አቅራቢያ ወ/ስላሴ ያሰማራቸው ሰባት የፌደራል ፖሊስ አባላት “አቦ ድልድይ” አቅራቢያ ጋዜጠኛውን ጠብቀው በያዙት ዱላ የቻሉትን ያክል ቀጥቅጠውና ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው ወደ ድልድዩ ወረወሩት። ሶስት ጥርሱ ተሰበረ፣ ጭንቅላቱ 5 ቦታ ተፈነካከተ፤ ሁለቱ እጆቹ፣ ግራ እግሩ፣ ወገቡ፣..አጠቃላይ አካሉ ተጎዳ። …እነ ወ/ስላሴ ከድርጊቱ በኋላ ለጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና 5 ጊዜ ስልክ ደውለው « የኢየሩሳሌምን ሬሳ ሂድና ከምኒሊክ ሆስፒታል ውሰድ..» ሲሉ ተሳለቁ።…ከጨካኞች፣ ገዳዮችና አምባገነኖች ..የሚጠብቅ ፈጣሪ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን የጋዜጠኛውን ነፍስ በኪነ-ጥበቡ ታደጋት። እነሆ ከአስር አመት በኋላ የቀድሞ የደህንነት ሹም ወ/ስላሴ ወ/ሚካኤል እስር ቤት ሲወረወር፥ በእርሱ “ሞት የተደገሰላት” የጋዜጠኛው ነፍስ በህይወት ቆይታ ለማየት በቃች። ሁሉም የዘራውን ሊያጭድ ግድ ነው!! …ይህ ታሪክ የእኔ ነው።
(በምስሉ የሚታየው ለስድስት ወር ያልጋ ቁራኛ የዳረገኝ የግድያ ሙከራ ከተፈፀመብኝ በኋላ፣ )

posted by Alemayehu Tibebu