Archive | March 10, 2014

ኢህአዴግ ዳግም በክፍፍል ጎዳና…? (ተመስገን ደሳለኝ)

ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ በተዘጋጁ ሁለት ፅሁፎች፣ የድህረ መለስን ኢህአዴግ የኃይል አሰላለፍ ለማመልከት መሞከሬ የሚታወስ ቢሆንም፤ ዛሬም ያልተጠበቁ ክስተቶችን ማስተዋላችን አልቀረም፡፡ በርግጥ «አዲሱ የኢህአዴግ አሰላለፍ ፪» በሚል ርዕስ ቀርቦ በነበረው ተጠየቅ ከሞላ ጎደል ሀገሪቷን እንደንጉስ ሚካኤል ከጀርባ ሆነው የሚያሽከረክሯት ህወሓት እና ብአዴን መሆናቸው የተጠቀሰበት አውድ ብዙም አልተቀየረም፡፡ ይሁንና በኦህዴድ እና ደኢህዴን ውስጥ እየታየ ያለው የእርስ በእርስ መተጋገል መደምደሚያ ምናልባት ወቅታዊውን መልከአ ኢህአዴግ ሊለውጠው የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ እገምታለሁ፤ ማን ያውቃል? …እነዚህን ኩነቶች ታሳቢ አድርገን የገዢው ፓርቲ አክራሞትን በአዲስ መስመር ጨርፎ ወደመመልከቱ እንለፍ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ «ብላቴኖች»

ክልሉን የሚያስተዳድረው የደኢህዴን የአመራር አባላት በስርዓቱ ልሂቃን የፖለቲካ ግምገማ ገና «ብላቴና» ተደርገው የሚወሰዱበት የትምክህት ዘመን አላከተመም፡፡ በርግጥ ድርጅቱ ደርግን ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ላይ የተሳተፈ ባለመሆኑ፣ ዛሬም ፖለቲካን (ሀገር ማስተዳደርን) በበረሃው ትግል ተፈትኖ ከማለፍ ጋር ከሚያጋምዱት የግንባሩ ጉምቱ መሪዎች ዘንድ፣ ይህን መሰል ማጣጣያ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለደኢህዴን ደካማነት በምክንያትነት የሚነሳው ጉዳይ ከአወቃቀሩ ጋር የሚያያዝ ነው፤ ይኸውም በክልሉ የሚገኙ 56 የተለያዩ ዘውጎችን ማቀፉ ለመከፋፈል አደጋ በቀላሉ የሚጋለጥበትን ዕድል የማስፋቱ እውነታ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ከክልሉ ነዋሪዎች በቁጥር የሚልቁት የወላይታና የሲዳማ ተወላጆች፣ በደኢህዴን ውስጥ ያላቸው ተሰሚነት (ተፅዕኖ) የገዘፈ መሆኑን ለመረዳት፣ ሕገ-መንግስቱ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ የፓርቲውን ሊቀ-መንበርነትም ሆነ የክልሉ ፕሬዚዳንትነት ከሁለቱ ብሔሮች በቀር፣ ለሌሎቹ የሰማይ ያህል የራቀ ያደረገውን «ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት» መጥቀሱ በቂ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የፓርቲው ሊቀ-መንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ የያዘውን መንግስታዊ ስልጣን የሚመጥን ተሰሚነት ለማግኘት ድርጅታዊ ድጋፍ ማሰባሰብ ላይ ያተኮሩ የሚመስሉ ክስተቶችን ሲከውን ታዘብናል፡፡ ኩነቱን በስነ-አመክንዮ ለማጠናከር ጥቂት ማሳያዎችን ላቅርብ፡- በጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበር ላይ ከተቀመጠ በኋላ፣ በደኢህዴን ውስጥ ያሉ የተወሰኑ ተገዳዳሪዎቹን ከኃላፊነታቸው ከማንሳትም አልፎ፣ ደጋፊዎቹ (ታማኞቹ) እንደሆኑ የሚነገርላቸውን በከፍተኛ ሥልጣን ላይ አስቀምጧል የሚያስብለው፣ ከወራት በፊት በፓርቲውም ሆነ በደቡብ ክልል ከእርሱም የበለጠ ተሰሚነት የነበረውን ሽፈራው ሽጉጤን አንስቶ፤ ትጉህ አገልጋዩ እንደሆነ የሚነገርለትን ደሴ ዳልጌን ተክቶታል፤ በቅርቡ ደግሞ ሌላኛው ‹የደኢህዴን ቁልፍ ሰው› የሚባለው የፖለቲካ (የድርጅት) ጉዳይ ኃላፊ እና የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አለማየሁ አሰፋን ያለአንዳች ኮሽታ «በትምህርት ስም» ከቦታው አንስቶታል (ይህ ጉዳይ እስከአሁን ድረስ መንግስታዊው ሚዲያ የዜና ሽፋን አላገኘም)፡፡ በግልባጩ ታማኝነታቸውን ያስመሰከሩ፣ ከሲዳማ ብሔር ውጪ ያሉ ጓዶቹን በፌደራል መንግስቱ ወሳኝ የስልጣን እርከኖች ላይ አስቀምጧል፡፡ ለማሳያ ያህልም አሰፋ አብዩ /ሀድያ/፣ ወርቅነህ ገበየውን ተክቶ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር፤ ደበበ አበራ /ከፋ/፣ የኢህአዴግ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ውዱ ሀቶ /ሸካ/፣ የፀረ ሙስና ምክትል ኮሚሽነር፤ አማኒኤል አብርሃም /ወላይታ/፣ በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ፤ ሰለሞን ተስፋዬ /ጉራጌ/፣ በተመሳሳይ ማዕረግ የፕሬስ አማካሪ፤ ካይዛ ኬ (ጂንካ) በገቢዎች ባለስልጣን የገብረሀዋድን ቦታ ተክቶ የገባ እና የፌደራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ ተደርጋ የተሾመችውን የወላይታዋ ተወላጅን መጥቀስ ይቻላል (ከደኢህዴን የሥራ-አስፈፃሚ አባላት መካከል የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትሩ ሬድዋን ሁሴን እና መከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳም የሲዳማ ተወላጅ አለመሆናቸውን ልብ ይሏል) ይህንን ጉዳይ እንዲህ በብሔር ደረጃ ቁልቁል አውርደን እንድንመለከተው የሚያስገድደን ስርዓቱ ከሚያራምደው የፖለቲካ ፍልስፍና እና በክልሉ እየተነሱ ካሉ የማንነት ጥያቄዎች ጋር የመቆራኘቱ አንድምታ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲዳማዎች ራሳቸውን ችለው
በክልል ደረጃ ለመዋቀር ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው አያሌ መስዋዕትነትን መክፈላቸው ይታወሳል (በኢህአዴጋዊ የክልል አሰያየም ቀመር ሕገ-መንግስታዊ ድጋፍ ያላቸው መሆኑ ሳይዘነጋ)፡፡ ይሁንና ጥያቄው ተቀባይነት ቢያገኝ የክልሉ አስተዳደር መቀመጫ የሆነችውን አዋሳን ከመውሰዳቸውም በላይ፣ ሊያስከትል የሚችለው አለመረጋጋት ሲታከልበት፣ ህዳጣን ልሂቃኑን የኢኮኖሚ ጥቅመኝነት ያሳጣቸዋል፡፡ ይህ ስጋትም በደኢህዴን ውስጥ ከሲዳማ ተወላጆች ውጪ ካሉ የአመራር አባላት ድርጅታዊ ድጋፍ ለማግኘት ብርቱ ትግል ከሚያደርገው ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር በወሳኝ ሰዓት፣ መሀል መንገድ ላይ ቢያስተቃቅፋቸው የማይታመን አይሆንም፡፡

የእነዚህ አዳዲስ ኩነቶች (ሹም ሽሮች) መግፍኤ፣ በሁለት የቢሆን ሃሳቦች ተነጣጥለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ የመጀመሪያው ኃይለማሪያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚንስትርነት ሹመቱን ተከትሎ ‹በዚህ ላይ ፈርም›፣ ‹ይህንን ተናገር›፣ ‹እንዲህ አይነት አስተያየት ስጥ!!› ወዘተ የሚሉ ከጀርባ ሆነው የሚሾፍሩት የአለቆቹ ቀጭን ትዕዛዛትን የሚገዳደርበት ፖለቲካዊ ጉልበት ለማሰባሰብ እና በቁርጥራጭ ጨርቅ በተጣጣፈው እናት ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ስልታዊ በሆነ መልኩ አስወግዶ ቅቡልነቱን ለማጠናከር እንቅስቃሴ ጀምሯል የሚል ሊሆን ይችላል፡፡
ሌላኛው ደግሞ ከኢትዮጵያውያንም አልፎ በውጪ ዜጎች ሳይቀር ‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሻንጉሊት ነው› የሚለውን እምነት ለማስቀየር በህወሓትና ብአዴን እየተደረገ ያለ ፖለቲካዊ ጨዋታ ሊሆን የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡

ኦህዴድ

ባለፉት የህወሓትም ሆነ የአቶ መለስ ዜናዊ የበላይነት በገነኑባቸው ዘመናት፣ ኦህዴድ ምንም እንኳን ስርዓቱን ካነበሩ የግንባሩ አባል ድርጅቶች አንዱ መሆኑ ባይካድም፣ በስጋት መታየቱ የአደባባይ እውነታ ነው፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት አቶ መለስ ራሱ «ኦህዴድ ሲፋቅ ኦነግ ነው» ማለቱ አይዘነጋም፡፡ ከሶስት ያላነሱ የስራ አስፈጻሚ አባላቱ፣ ድርጅቱን ከድተው ኦነግን መቀላቀላቸውም የውንጀላው ማሳያ ተደርጎ እስከመወሰድ ደርሶ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታም ኦህዴድን የተረጋጋ አመራር እንዳይኖረው ከማደናቀፉም ባሻገር፣ በተቀነባበረ ማኪያቬሊያዊ ሴራ እርስ በርስ በማይተማመኑና በተከፋፈሉ ሰዎች ስር እንዲቆይ አስገድዶታል፡፡ ግና፣ ኩነቱን ምፀት የሚያደርገው ህወሓት በረሃ እያለ ያሳትመው በነበረው ልሳኑ «የኦሮሞ ጥያቄና የኢትዮጵያ አብዮት» በሚል ርዕስ ባሰራጨው ፅሁፍ ኢህአፓን «የኦሮሞ ሕዝብ በነፍጠኛው ላይ የነበረውን ተገቢ ጥላቻ በማራገብ ፋንታ ለማብረድ በተጨባጭ ተንቀሳቅሷል» («የትግል ጥሪ» 3ኛ ዓመት ቁጥር 10፣ 1979 ዓ.ም) ሲል ይከስሰው እንደነበረ ማስተዋላችን ነው፡፡

በአናቱም አቶ መለስ እስከ ህልፈቱ ድረስ በኦህዴድ ደስተኛ እንዳልነበረ ይነገራል፡፡ ይህ ግን ‹የኦሮሞን ሕዝብ በአግባቡ አላገለገለም› ከሚል ቁርቆራ የተነሳ አይደለም፤ እንዲህ አይነቱ ስሜት ሌላውን ክልል ቀርቶ ትግራይንም የሚመለከት ቢሆን አሳስቦት አያውቅምና፡፡ የእርሱ ቅሬታ ‹ህዝቡን አሳምነውም ሆነ ጠርንፈው ከድርጅቱ ጎን አላሰለፉትም›፣ ‹ሁላችንንም በሚያሳጣ መልኩ ዘረፋ ውስጥ ገብተዋል›፣ ‹ዲሲፕሊን የላቸውም…› የሚሉና ሌሎች መሰል መነሾዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ የድርጅቱ «እንዝህላልነት» ደግሞ የህዝቡ ልብ ይበልጥ ኦነግን እንዲናፍቅ ማስገደዱን መለስ ዜናዊ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የክልሉን ባለስልጣናት ሁሉ ወደ ጎን ብሎ እታች ድረስ በመውረድ የወረዳ አመራሮችን ቀጥታ ያለ ሥልጣን ተዋረድ በስልክ እስከማናገር የተገደደባቸው ቀናት የበዙት፡፡ በርግጥ በድርጅቱ ስብሰባዎች ላይ መተላለፍ ያለባቸውን ውሳኔዎች በፅሁፍ መስጠት እና ለአመራርነት የሚመረጡ ሰዎችን መመደብ ድረስ ባሉ ጉዳዮች ጣልቃ የመግባቱ ነገር ማንም አሌ የማይለው በግልፅ ይታይ የነበረ ክስተት ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ከምንጮቼ እንዳረጋገጥኩት አባዱላ ገመዳ ዕድሜውን ሙሉ ሲፈራ የኖረው መለስ ዜናዊን ብቻ ነበር፤ መለስ ደግሞ ይህችን ምድር ለመጨረሻ ጊዜ ከተሰናበታት አንስቶ የተቆጠሩት በርካታ ወራት ፍርሃቱን ጥሎ ነፃነቱን እንዲጎናፀፍ ለመርዳት ያስችሉታል ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም በዚህ መልኩ ተፈጥሮ ያመቻቸለትን ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅሞ ይደቆስ የነበረውን ኦህዴድ ከወደቀበት ለማንሳት ሙከራዎችን እያደረገ ይመስለኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኦህዴድ በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ አንዳንድ አጀንዳዎችና አቋሞችን የአባዱላ ግፊት እንዳለባቸው ስናስተውል፣ «ጄነራሉ» ወሳኝ ሰው ለመሆን እያደረገ ያለው የጥንጣን ጉዞ ምን ያህል እየሰመረለት እንደሆነ ለመረዳት ያስችላል፡፡ ይህንን መከራከሪያ ከለጠጥነው ደግሞ፣ ከህወሓት/ብአዴን ጋር ትከሻ መገፋፋት ጀምሯል ወደሚል ጠርዝ ይገፋናል፡፡ ይህም ባይሆን እንኳ ከኃይለማርያም ደሳለኝ የተሻለ ተሰሚነት እንዳለው ለመናገር የሚያስደፍሩ ማስረገጫዎች አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀን የከዳ ዕለት በተናጠል በኃላፊነት ሊያስጠይቁት የሚችሉ ጉዳዮችን ሳይቀር፣ በያዘው ሕገ-መንግስታዊ ሥልጣን ከመወሰን ይልቅ በቡድን እንዲያልቅ ሲስማማ፤ በግልባጩ አፈ-ጉባኤው ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ ውስጥ ተነስተው ለአቶ መለስ ይቀርቡ የነበሩ ጉዳዮችን ወዲያውኑ መፍትሔ እንዲያገኙ በማድረግ ሲቋጫቸው ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡ ኦህዴድንም በሚመለከት ‹በድርጅታዊ መደጋገፍ› ስም ማንም ጣልቃ መግባት እንደማይችል በይፋ እስከ መናገር መድረሱን ምንጮች ጠቅሰውልኛል፡፡ በቀጣይ አመት የሚደረገውን አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫን አስመልክቶም እየተደረገ ባለው ዝግጅት በሃሳብ አመንጭነት እየተሳተፈ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ለምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤት ለተወከሉ እና ምርጫ ቦርድ ሀላፊዎች /ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እና ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር በተገኙበት/ «የአውራ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያት» በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ማቅረቡ አስረጅ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል (በነገራችን ላይ ስርዓቱ በምርጫ ስም የሚፈፅመውን ደባ ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው፣ ሁለቱ የቦርዱ ኃላፊዎች የዚህ አይነቱ ውይይት ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ነው)፡፡ እንዲሁም ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በአዳማ ለክልል አፈ-ጉባኤዎች ሰፊ ትንተና ሰጥቷል፡፡

የአባዱላ ገመዳንና የበረከት ስምኦንን መገፋፋት በጨረፍታም ቢሆን ሊያሳይ የሚችለው ሌላኛው ሁነት ደግሞ ወ/ሮ አና ጎሜዝን አስመልክቶ ሊነሳ የሚችለው ነው፡፡ በረከት «የሁለት ምርጫዎች ወግ» በሚለው መጽሐፉ «የቅኝ-ገዥነት መንፈስ ያልለቀቃት» ብሎ የገለፃትን አና ጎሜዝ (የመለስ በስድብ የተሞላ የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ መጣጥፍ ሳይዘነጋ)፣ ከሁለት ወራት በፊት አዲስ አበባ በመጣችበት ወቅት አባዱላ በጓዳዊ ስሜት እንዳስተናገዳት ራሷ ከመመስከሯም በዘለለ፣ እነርሱም በአዲስ ዘመን ጋዜጣቸው «እየተመካከርን ነው» የሚል የወዳጅነት መንፈስ የረበበበት የፎቶ ዘገባ ማቅረባቸውን እናስታውሳለን፡፡ ይህች ተራ የምትመስል ሁነት ለበረከት የምታስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ‹እናንተ እንደሰይጣን የረገማችሁትን ሁሉ እየተከተልን አንረግምም» የምትል እኩዮች ነን አይነት ትከሻ መጋፋት ትመስለኛለች፡፡

በአናቱም አባዱላ አብዛኛው የኦህዴድ አመራርን በዙሪያው ማሰባሰብ ስለመቻሉ ይነገራል፡፡ ከዚህ ቀደም በአደባባይ እስከመዘላለፍ የተደራረሱትን አቶ ሙክታር ከድርንም ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል፡፡ በአንድ ወቅት የግል ጠባቂው የነበረውና አሁን የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆነው አብይ አህመድ በእንዲህ አይነቱ ጊዜ ውለታ ለመመለስ የሚያደርገው ተጋድሎ የማይናቅ ጠቀሜታ አስገኝቶለታል፡፡ የሰሞኑ ሹም ሽርም የራሱ የሆነ አንድምታ አለው፡፡ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በማዕከላዊ ኮሚቴ ድምጽ ከስልጣኑ የተሻረው የክልሉ ፕሬዚዳንት አለማየሁ አቱምሳ (እርሱን ማንሳት የሚችለው ጠቅላላ ጉባኤው ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በርግጥ ሰውየው አሁን አልፏልና በባህላዊ ልማዳችን መሰረት ነፍስ ይማር ብለን እናልፋለን) በ2002ቱ ምርጫ ማግስት አቶ መለስ ከካድሬዎቹ ይሁንታ ውጪ አባዱላን ለመተካት ያመጣው እንደነበር ይታወሳል፡፡ (በነገራችን ላይ በወራት እድሜ ውስጥ በመለስ የተሾሙ የክልል ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ከሽፈራው ሽጉጤ እና አያሌው ጎበዜ ቀጥሎ አለማየሁ አቱምሳ ሶስተኛው ሰው መሆኑ ነው) የድርጅቱ ሊቀ-መንበር እና ምክትል ሆነው የተመረጡት ሙክታር ከድርና አስቴር ማሞም የአባዱላን የበላይነት ለመቀበል ግለ- ሂሳቸውን ውጠዋል፡፡ ይህም ሆኖ የክልሉ አስተዳዳሪ ማን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም፡፡

ምናልባት (ከስራ አስፈፃሚዎችም መካከል መምረጥ እንደሚቻል ታሳቢ ተደርጎ) በሌሎች አካባቢዎች እንደታየው ከድርጅቱ ሊቀ-መናብርት (ሙክታርና አስቴር) አንዳቸውን መሾም ቢፈልጉ እንኳ ዕውን የሚሆንበት ዕድል የለም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የህዝብ ተወካዮች እንጂ የጨፌ ኦሮሚያ ም/ቤት አባል አይደሉምና፡፡ በእኔ ግምት እስከሚቀጥለው የምርጫ ዘመን ድረስ ቦታው አዲስ ሰው ሳይሰየምበት በምክትል ፕሬዚዳንቱ አብዱል አዚዝ ስር እንዳለ የሚቆይ ይመስለኛል፡፡

ከምርጫው በኋላስ? ….አፈ-ጉባኤው በኦህዴድ ውስጥ ለማስፈን እየሞከረ ካለው «አምልኮ አባዱላ» ተነስተን «ተገፈተርኩበት!» የሚለውን ያደረ ቁጭቱን ስንደምርበት ወንበሩን ራሱ ይይዘው ይሆናል ከሚል ጠርዝ ያደርሰናል፤ አሊያም ከሽርኮቹ ሙክታር ከድር እና ወርቅነህ ገበየው አንዳቸውን አሾሞበት በጨፌ ኦሮሚያም የሚካኤል ስሁልን መንፈስ ማንበሩ አይቀርም ብሎ ቅድመ ግምት ማስቀመጥ ይቻላል (ይህ መላምት የህወሓት-ብአዴን ጥንካሬ በዚሁ ከቀጠለ እና የእነርሱ ፍላጎት ደግሞ የተለየ ከሆነ ከህልም ሊዘል አለመቻሉን በማመን ላይ የተመሰረተ ነው)

ኦህዴድን ካነሳን የሌንጮ ለታን ኦዴግን መፃኢ እድልም መመልከት ግድ ይለናል፤ ምክንያቱም ኦዴግ አገር ውስጥ ገብቶ በሰላማዊ መንገድ መታገል ወስኖ ጨርሷልና፤ ሂደቱንም ለማመቻቸት ከግንባሩ መሪዎች አቦ ሌንጮ ለታ፣ ዶ/ር ሌንጮ ባቲ፣ ዶ/ር ዲማ ነጎዎ፣ ዶ/ር ታደሰ ኤባ እና ዶ/ር በየነ አሰቦ ጋር ከስምምነት ለመድረስ፣ ኢህአዴግ በውጪ ሀገር ከሚገኙት የጄኔራል ታደሰ ብሩ ልጆች በተጨማሪ፣ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ፣ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሃቅ፣ ፓስተር ዳንኤል፣ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ፣ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ፣ አባቢያ አባጆቢር፣ አቶ በቀለ ነዲ (የአዋሽ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩ)፣ ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞንን የመሳሰሉ አደራዳሪዎችን ማሳተፉ ይነገራል፡፡

ይህም ሆኖ ድርድሩ በስኬት ተቋጭቶ ኦዴግ ሀገር ቤት መግባት ቢችል እንኳ፣ ኦህዴዶች ‹አያሰጋንም› የሚል እምነት እንዳላቸው ሰምቻለሁ፡፡ ግና፣ ያለፉት ሁለት አስርታት ዘግናኝ ክስተቶች አሻራ ዛሬም በረዣዥሞቹ የባሌ ተራሮች በጉልህ ተቸክችኮ የመታየቱ እውነታ፣ በስርዓቱ ላኮረፈው የኦሮሚያ ህዝብ፣ ኦዴግን አማራጭ የሚያደርግበት «አኪር» ሸሽጎ ይዞ እንደሆነ ማን ያውቃል? ይህ እንግዲህ እነ ሌንጮ «ካዳሚ» ለመሆን አይመጡም በሚል ስሌት ከተቃኘ ነው፡፡ ይሁንና ከድርድሩ ጀርባ ያለውን እንቆቅልሽ ለመፍታት ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ጉዳዩን ውስብስብ የሚያደርጉ ክስተቶችን ግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይኸውም በአፈ-ጉባኤ አባዱላ ፊት አውራሪነት ስር ለመጠናከር እየሞከረ ያለው ኦህዴድ፣ ከሰዎቹ ሀገር ቤት መግባት ምን ያተርፋል? ምንስ ያጣል? ከሚለው ጋር ይያያዛል፡፡

መቼም የኦዴግን መምጣት፣ ኦቦ ሌንጮ «እንጮቴ» (ተወዳጅ ባሕላዊ ምግብ ነው) በአይኑ ላይ እየተመላለሰ እንደሆነ ከሰነዘረው ቀልድም ሆነ «ከሌሎች የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘመናዊ ፌደራሊዝምን እመሰርታለሁ» ብሎ በደምሳሳው ከገለፀው ዓላማው ጋር አያይዞ ማለፍ አይቻልም፡፡ አሊያም ያኔ እርሱ ሸገርን ተሰናብቶ ሲወጣ ገና ያልፀደቀውን አንቀፅ 39ን «አስፈፅማለሁ» በሚል ቀቢፀ-ተስፋ ተገፍቶ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ በግልባጩ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ‹የኦዴግ መሪዎች በኦነግ ዘመን ለእስር የዳረጓቸውን በሺ የሚቆጠሩ የኦሮሚያ ተወላጆችን ለማስፈታት ሲሉ፣ በታማኝ ተቃዋሚነት ለመታገል ወስነው ነው የሚመጡት› የሚለውን መከራከሪያቸውን ለመቀበል የሚቸግረው ደግሞ፣ እስረኞቹን መፍታት ለሃያ አመታት ያህል በክልሉ ላይ ሰላማዊ ዜጎችን በማሰር የሚታወቀውን ኦህዴድን ሊያሳጣ የመቻሉ ነገር ነው፡፡ ያም ተባለ ያ፣ «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንዲል ጠቢቡ

ሰለሞን ሁሉም ቋጠሮ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡ አሁን ላይ እርግጠኛ መሆን የሚቻለው በኦህዴድ ውስጥ አባዱላ ገመዳ ወሳኝ እየሆነ የመምጣቱ እውነታ ብቻ ነው፡፡

ህወሓት-ብአዴን

በዋናነት ሀገሪቷን እንደሚያሽከረክሯት የሚነገርላቸው ህወሓት እና ብአዴን፣ በመጪዎቹ ጊዜያት ‹ኢህአዴግ ለዳግም ክፍፍል ሊዳረግ ይችላል› በሚል ፍርሃት ድርና ማግ ሆነው እየሰሩ ስለመሆኑ እየሰማን ነው፡፡ በርግጥ ‹መለስ ህወሓትን አዳክሞ ነው ያለፈው› የሚል የትግርኛ ተናጋሪዎች ድምፅ መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል (በነገራችን ላይ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ የህወሓትን የምስረታ በዓል የካቲት 11ን በብሔራዊ ደረጃ ማክበር መቅረቱን በይፋ ከማወጃቸውም በላይ፣ መለስ ራሱ ለመጨረሻ ጊዜ በመቀሌው የሰማዕታት አዳራሽ የተገኘው 35ኛው ዓመት በተከበረበት ወቅት ነበር፡፡ ይሁንና ከህልፈቱ በኋላ ድርጅቱ የደረሰበትን ድክመት ለመሸፋፈን በደመቀ መልኩ እያከበረው ይገኛል፤ ለዚህም ይመስለኛል በአምናውም ሆነ በዘንድሮው በዓል ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መቀሌ የሞቀ ተገኝቶ ንግግር ከማድረግም አልፎ ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኡመር ሀሰን አልበሽር ጋር በትግሉ ዘመን በተቀነቀኑ ዜማዎች ሲደንስ በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክተን ሦስተኛው ሚሊንየም ገባ እንዴ? ብለን ግራ የተጋባነው፡፡ አልበሽርስ አንድ ቻርተር አውሮፕላን ለክልሉ በስጦታ ያበረከተው ዕውን በዓሉን አስመልክቶ ነው? ወይስ በምትኩ የተሰጠው ነገር ኖሮ? መቼም የህወሓት የምስረታ በዓል እንዲህ ሊያስፈነጥዘው እይችልም)

‹ህወሓት ተዳክሟል› የሚለውን ቅሬታ የሚያሰሙ የቅርብ ሰዎች፣ ድርጅቱ አቅምና ልምድ በሌላቸው መሪዎች ስር ማደሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ተስፋ የጣሉበት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልም ቢሆን ከአምባገነንነቱም በላይ ሀሳቡን አፍታቶ የማስረዳት ችሎታው ደካማ መሆን መፍትሄውን አርቆ ሰቅሎታል፡፡ እንደ ድርጅቱ የቅርብ ሰዎች አገላለፅ የ«ጠንካራ ተተኪ» አልቦነትን ለመረዳት፣ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኃላፊነቱ በተነሳው አቶ ዘርዓይ አስገዶም ቦታ ላይ የዋልታ ስራ አስኪያጅ መመደቡ እና ራሱ ዘርዓይም በጓሮ በር የብሮድካስት ባለስልጣን ሆኖ መሾሙን (አዲስ ፊት አለመታየቱን) መመልከቱ በቂ ነው፡፡ በቅርቡ የዶክትሬት ዲግሪውን ያገኘው አርከበ እቁባይም ለአመራርነት ለቀረበለት ጥያቄ እያንገራገረ እንደሆነ ተሰምቷል፤ አቦይ ስብሃት ነጋም ኢ-መደበኛ በሆነ የጠረጴዛ ወግ ህወሓት «በግብር በላ» መሪዎች እጅ መውደቁን በቁጭት መናገራቸው ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና በዚህ ቀውጢ ወቅት ሁለት ተቋማት ድርጅቱን ለጊዜውም ቢሆን ፖለቲካዊ ጉልበቱን እንዳይነጠቅ ታድገውታል፡፡

ደህንነቱ እና ሰራዊቱ፡፡

የሆነው ሆኖ ህወሓት ዛሬም ከብአዴን ጋር በማበር (በአባይ ፀሐዬ እና በበረከት ስምኦን የፊት መሪነት) የፖለቲካው አሽከርካሪነቱን እንዳስከበረ ይገኛል፡፡ ሁለቱ ሰዎች የስርዓቱን ርዕዮተ-ዓለምንም (በተለይም አብዮታዊ ዲሞክራሲን) ከሌሎች ጓዶቻቸው በበለጠ ማብራራት እንደሚችሉ ይነገራል፡፡ በጅጅጋ ከተማ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በተከበረበት ወቅትም ሆነ ከሳምንታት በፊት በመቀሌ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ አባይ ፀሐዬ የርዕዮተ-አለሙ «ተንታኝ» ሆኖ የቀረበው ከዚህ አኳያ ነበር፡፡ በአናቱም አባይ እና በረከትን ጨምሮ ከኦህዴድ ኩማ ደመቅሳ፤ ከደኢህዴን ዶ/ር ካሱ ኢላላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡ በዋናነት ለኢህአዴግ የስልጣኑ መሰረት (ከታጠቀው ኃይል እና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬው በተጨማሪ) ‹በልማታዊ መንግስት፣ በጥርነፋ፣ ሳር-ቅጠሉን በማደራጀት፣ የብሔር ጉዳይን በማጎን እና መሰል ጭብጦችን በማስጮኽ የሚያምታታበት ርዕዮተ-ዓለሙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የእነ በረከት የተሰሚነት ምስጢርም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በርግጥም የካቲት 14 ቀን 2006 ዓ.ም. የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልን ለማቋቋም የሚያስችል ደንብ ማፅደቁን እና የአራቱም ድርጅት የአመራር አባላት የተወከሉበት ከመሆኑ አኳያ፣ ቦታው ከማማከር የዘለለ የስራ ድርሻ እንዳለው መገመት አያዳግትም (በነገራችን ላይ የመለስ ፖለቲካ ሰለባ የሆነው የብአዴኑ ተፈራ ዋልዋ ድምፁን አጥፍቶና ከውጥንቅጡ አርባ ክንድ እርቆ በእንጦጦ ተራራ እና በረዣዥም ህንፃዎች አናት በመፈናጠጥ ቴሌስኮፑን ግራና ቀኝ እያዟዟረ ከዋክብት ሲመለከት መዋልን አይነት ፀጥተኛ ህይወት፣ አንዳንድ የቀድሞ ጓዶቹም ለተረፈቻቸው እድሜ የሚመኙት ይመስለኛል)
ለውጥ ይኖር ይሆን?

የስርዓቱ ልሂቃን ብሔሮቻቸውን ማዕከል ባደረገ መልኩም ይሁን፣ በሥልጣን ከፍታ ከሚያገኙት ግላዊ ጥቅማ-ጥቅም በመነሳት፣ ከላይ ለመተንተን እንደሞከርኩት ባለ የመከፋፈል መሰል ሂደት ውስጥ እንኳን ቢያልፉ በቀጣይ ጊዜያት ‹የፖለቲካ ማሻሻያ ያደርጋሉ› ብሎ ለማመን ነገሮች በእጅጉ አስቸጋሪ ናቸው፡፡ ለዚህም ሶስት ነጥቦችን እናንሳ፡- የመጀመሪያው የሀገሪቱ የደህንነት መዋቅር አደረጃጀት ባህሪ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በእነ ጌታቸው አሰፋ የሚመራው የደህንነት ተቋም በሚታዩና በማይታዩ ድርጊቶች ለህወሓት የተገዛ ነው፡፡

ከዚህች ሀገር ጀርባ ለተፈፀሙም ሆነ ገና ለሚፈፀሙ ድርጅታዊ እና ግለሰባዊ (ባለሥልጣናዊ) ወንጀሎች አስፈፃሚና በደል አንፂ ነው፡፡

የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች በዶ/ር ደብረጽዮን ፍቃድ ካልሆነ ምንም ዓይነት ውሳኔ መስጠት እንደማይችሉ ተገለጸ

የደህንነት ሹሙ አቶ ጌታቸው አሰፋና ባለስልጣኖቻቸው በሙስና እና በዘረፋ ላይ ተሰማርተዋል

የፍርድ ቤቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ማኮላሸት ለአለቃ ጸጋዬ በርሄ ተሰቷቸዋል
የጦር ሰራዊቱን በተጠንቀቅ የሚከታተሉ ወታደራዊ ደህንነቶች ተደራጅተው በየእዙ ተበትነዋል

Image

ምኒልክ ሳልሳዊ

በመከላከያ ሰራዊት የሕወሓት መኮንኖች ስር የሰደደው የሙስና እና የዘረፋ አድራጎት በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥም ከሹሙ ከአቶ ጌታቸው እና ከባለስልጣኖቻቸው ጀምሮ እስከ ገራፊዎች ድረስ መንሰራፋቱን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገልጸዋል:: እንደውስጥ አዋቂ ምንጮቹ መረጃ ከሆነ የደህንነት ባለስልጣኖቹ የተዘፈቁበት የሙስና ተግባር በተጨማሪ ዘረፋን እና ሴት መድፈርን እንዲሁም የቡድን ወንጀሎችን ያካተተ መሆኑ ተጠቁሟል::በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ባለሃብቶችን በማስፈራራት ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ በማሰር እንዲሁም የሙስና ወንጀል ተገኝቶብሃል ይህን ያህል ገንዘብ አምጣ ካላመጣህ እንገድልሃለን እስከማለት በከመድረሳቸውም በተጨማሪ ይህንን ጉዳይ ለፖሊስ የጠቆመ ባለሃብት በማፈን ንብረቱ ባማገድ እና በተለያዩ ስልቶች የተጠየቀውን ገንዘብ እንዲሰጥ በማስገደድ ላይ መሆናቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል::

ከዚህ ቀደም በሙስና የተከሰሱ የስርኣቱ ባለስልጣናትን ተገን በማደርግ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ባለሃብቶችን በመከታተል እና ደህንነት ቢሮ ድረስ በመውሰድ በሙስና ከታሰረው ስም እየተጠቀሰ … ከሚባል ባለስልጣን ጋር ግንኙነት አለህ ማስረጃ ተገኝቶብሃል በማለት በፈጠራ ወንጀል ባለሃብቱን በመዝረፍ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበረ እና እንዲሁም የአዲስ አበባን ቆነጃጅት ቢሯቸው ድረስ በግብረአበሮቻቸው አፋኝነት እና አስገዳጅነት በመውሰድ ካለፍላጎታቸው አስገድደው በመድፈር ላይ ናቸው ያሉት ምንጮቹ ተራ የደህንነት አባላት ለዚሁ ተልእኮ ተሰማርተው የሚሰሩት ምንም አይነት ወንጀል በቡድን ሲፈጽሙ የሚጠይቃቸው አለመኖሩን የሕዝቡን በደል የከፋ አድርጎታል::

ኢትዮጵያውያን በሕወሓቱ የደህንነት መዋቅር የሚመራ የሽብር ተግባራትን አጥብቆ ስለሚፈራ እና በየጊዜው በሕወሓት ደህንነቶች መሪነት የሚወሰዱ እርምጃዎች በሃገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ስጋትን በመፍጠራቸው በየእስር ቤቱ የሚካሄዱ ሕገወጥ ጸረ ፍትህ ተግባራት እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የኢትዮጵያውያን የቀን ተቀን አጀንዳ ሆነው መምጣታቸው ገዢው ፓርቲ ሕዝቡን ምን ያህል እንዳሸበረ ይጠቁማል ሲሉ ምንጮሹ አክለው ገልጸዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕወሓትን ሳይጨምር ብኣዴን ኦሕዴድ ደኢሕዴግ እና አጋል የክልል ጎሳ ፓርቲዎች ከአቶ ደብረጽዮን በሚወርድ ትእዛዝ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይነት እርምጃ በፍቃዳቸው መፈጸም እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል:: በቅርቡ የአቶ አለማየሁ አቶምሳን ሞት ተከትሎ አፈጻጸሙ በዶ/ር ደብረጽሆን መልካም ፍቃድ እንደሆነ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የተባለው የኦሕዴድ ሙክታር ከድር አቶ አለማየሁ ደክመው እያየ እና እያወቀ ሆስፒታል እንዲሄዱ አስቸኳይ ትብብር እንዲደረግ ወይዘሮ አስቴር ማሞ ስትጠይቀው ለዶ/ር ደብረጽሆን ነግረሽ አስፈቅጂ በማለት ሕወሓት በኦሕዴድ አናት ላይ ምን ያህል እየሸና እንዳለ እንዲሁም በሞራላቸው አመራሮቹ እንዳይራመዱ እያደረገ እንዳለ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው:: ማንኛውም የኢሕኣዴግ አባል እና አጋር ድርጅት በድርጅቱ ሊቀመንበር ወይንም ምክትል አማካኝነት በቅድሚያ ለዶ/ር ደብረጺሆን ሪፖርት ማድረግ እና ሁኔታው ታይቶ ፈቃድ እና ውሳነ ካልተሰጠው በስተቀር መፈጸም እንደማይችል ትእዛ መተላለፉ ሲታወቅ በአዲስ አበባ እና በክልል ያለው የፍርድ ቤቶች እና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በአለቃ ጸጋይ በርኸ ስር ክትትል እየተደረገ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ ሲታውቅ የጦር ሰራዊቱን በተመለከት በተዋረድ የሚያስተዳድሩ የወታደራዊ ደህንነት የሕወሓት መኮንኖች ተደራጅተው በየእዙ መመደባቸው ታውቋል:

http://www.zehabesha.com