Archive | March 23, 2014

“ርእዮት ዓለሙ ምን ትሠራልናለች?”

 

“ኑ እንዋቀስ! ይላል ነፋሱ የአገልግሎት ዋጋቸውን በልተን በዕዳችን ያስጠየቅናቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ ጡጫና እርግጫ የጠገቡት እነርሱ እያሉ እኛ       ግልምጫ የሚሸሽ ውርደታም ሕዝብ ኾነናል፡፡ ልጆቻችንን ሰብስበን የእነርሱን በትነናል፡፡ ቤተሰቦቻችንን ሸክፈን የእነርሱን አንከራትተናል፡፡ ቤታችንን አሙቀን የእነርሱን ጎጆ አቀዝቅዘናል፡፡” (ዓለማየኹ ገላጋይ) 
 
 Reeyot Alemu
 
ቀኑ እሑድ ነው፡፡ በየሳምንቱ እንዲያልፉኝ የማልፈልጋቸውን ኹለት መጽሔቶች ከቢጢቆ የደምናወዜ ጭማቂ ላይ አንጀቴን አሥሬ ቦጨቅኹና ገዛኹ፡፡ በረንዳ ላይ ጥቂት ቆይቼ ወደ ቤት ገባኹና አንደኛውን መጽሔት ማገላበጥ ጀመርኹ፡፡ እበረንዳው ላይ ትቼው የገባኹት ሌላኛው መጽሔት “ስኬታማ ሴቶች” በሚል ርእስ አጅቦ የብርቱ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ፎቶግራፍ የሽፋን ገጹ ላይ ደርድሯል፤ ከሴቶቹ ውስጥም አንዷ ርእዮት ዓለሙ ነበረች፡፡ አንድ አብሬ አደጌ የኾነ የሠፈራችን ልጅ እንደ ልማዱ እቤታችን መጣ፡፡ ይኽ የዕድሜ አቻዬ ስምንተኛ ክፍልን እንኳ በቅጡ አላጠናቀቀም፡፡ ነገር ግን በልጅነታችን የክረምት ሥራ ለመሥራት ጎራ እንልባቸው ከነበሩ የመንደራችን ጫማ “ፋብሪካዎች” ጫማ መወጠር ተምሯል፡፡ አኹንም ኑሮውን በዚኹ ሥራ ይገፋል፡፡ ትምህርት እንዲቀጥል ለማድረግ እኔና ሌሎች ኹለት ሦስት ሰዎች ውትወታ ለማድረግ ሞክረን ነበር- ሰሚ ጆሮ አላገኘንም፡፡ አብሮ አደጌ በመደበኛው ትምህርት አይግፋ እንጂ ታዲያ ዘወትር ዐዲስ ነገር ለመማር ካለው ጉጉት የተነሣ ብርቱ ሬድዮ አድማጭ ነው፡፡ ከአማርኛ ውጪ የሚያውቀው ቋንቋ ስለሌለም የኢትዮጵያ ቴሌፍጀን ቋሚ ተሰላፊም ነው፡፡ 1993 ዓ.ም. ዐዲስ ዐበባ ውስጥ ተነሥቶ በነበረው ብጥብጥ እንዲኹ ከመንገድ ላይ ታፍሶ፣ በአቅራቢያችን በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ታሥሮ እንደነበር ኹላችንም እናውቃለን፡፡ ከፖሊስ ጣቢያው ጥቂት ቀናት ቆቶ ሲወጣም ፊቱና ጭንቅላቱ ቆሳስሎ እንደነበር አይተናል፡፡ ምን እንደኾነ ስንጠይቀውም “በሰባራ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ያለአንዳች ጥያቄ ደበደቡን፡፡” የሚል መልስ ነበር የሰጠን፡፡ እኛም በልጅነት ልቡና “መቼም መንግሥት ባለበት ሀገር በገዛ እጁ ራሱን እንዲኽ ሊያቆስል አይችልም” አምነነዋል፡፡
 
እነሆ ይኽ አብሮ አደጌ አኹን መጽሔቱን እየመለካከተ ነው፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ “ርእዮት ዓለሙ እንኳን ታሠረች! ምን ትሠራልናለች?!” ሲል ሲናገር ሰማኹት፡፡ ከእግር ጥፍሬ እስከራስ ፀጉሬ ነዘረኝ፡፡ ብልጭ አለብኝ፡፡ መጀመሪያ ጭንቅላቴ ውስጥ የመጣልኝ መልስ “አንተ ደነዝ! እንኳን ርእዮት አንተም ትሠራለኽ፡፡” የሚል ዓይነት መልስ ነበር፡፡ ወዲያው ግን “እንዴ! ያሻውን መናገር መብቱ አይደለምን?” ስል ራሴን ጠየቅኹት፡፡ “ማንም ሰው አስተያየቱን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዳለውስ አታምንምን?” ስል ጥያቄዬን ለራሴ አስከተልኹ፡፡ ወዲያውም “አምናለኹ፤ ስለዚኽም መብቱን በመጠቀሙ ልወቅሰው አይገባኝም” የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኹ፡፡ ይኹን እንጂ ይኽ ሰው እንዴት እንዲኽ ዐይነት አመለካከት ሊያዳብር እንደቻለ ማስተንተን ጀመርኹ፡፡ 
 Reeiot_cover1

ፈረንሳዊው ሊቅ ዣክ ኤሉል “Propaganda: formation of men’s attitude” በተሰኘው መጽሐፉ ላይ የምንከታተላቸው ብዙኃን መገናኛዎች እንዴት አእምሯችንን፣ አመለካከታችንን እንደሚቀርጹት የተናገረውን፣ ሌላ አንድ ፈላስፋ ደግሞ ሰዎች በግለሰብነት ሳይኾን በጅምላ፣ በመንጋ እንዲያስቡ ስለሚያደርገው ልዩ ልዩ አመለካከቶችን ደምጥጦ አንድ የማድረግ (leveling) የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከመቶ ምናምን ዓመት በፊት መናገሩን አስታወስኹ፡፡ በማሳረጊያነትም የሒትለር ፕሮፓጋንዳ ክፍል ኃላፊ የነበረው ጆሴፍ ጎብልስ “If you tell a lie big enough and keep repeating it, people will eventually believe it.” ሲል የተናገረውን አሰብኹ፡፡
ከዚያም ወትሮ የማውቀው አምባገነኖች መገናኛ ብዙኃንን መቆጣጠር የሚፈልጉበትን ምክንያት እንዲኽ ግዘፍ ነሥቶ፣ በሥጋ ስለተገለጠ ነፍሴ ተሳቀቀች፡፡ 
 
አምባገነኖችና ብርቄ ሬድዮ
 radio
 
ከጥቂት አመታት በፊት አልጀዚራ ላይ ስለቤላሩስ ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የቀረበ ዘጋቢ ፊልም ነበር፡፡ በዚያ ዘጋቢ ፊልም ላይ የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ የየዕለቱ ዘገባው ፕሬዚደንቱ የተናገሩት ንግግር ስለት፣ የበሉት ኬክ ዓይነት፣ የጠጡት ቡና ውፍረት፣ የተጫወቱት የበረዶ ሸርታቴ አዝናኝነት ነው፡፡ በሀገሪቱ ላይ ሌላ ሰው የተፈጠረ አይመስልም፡፡ የአሌክሳንደር ሉካሼንኮ መንግሥት “ከቸርነቱ” የተነሣ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ለሚኖሩ ሰዎች የኾነ በስብስቴ ነጋሢ ዘመን የተሠራ የሚመስል ሬድዮ አድሏቸዋል፡፡ ታዲያ ይኽ ሬድዮ ከአንድ ጣቢያ ውጪ እንደሌለው ስነግርዎት ሳቄን ለመቆጣጠር እየታገልኹ ነው፡፡ ይኽ ጣቢያ ደግሞ አዎን፣ እርስዎ አንባቢዬም አኹን እንደገመቱት የአሌክሳንደር ሉካሼንኮን አተነፋፈስ ከመቁጠር የዘለለ ሥራ የማይሠራ ጣቢያ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ይቺን ቴክኒክ ደርግም እነ ቪኦኤን ለማፈን ተጠቅሞባት ነበር ብለው በዘመኑ የኖሩ ሰዎች አጫውተውኛል፡፡ የዚኽችን ሬድዮ አንድ ጣብያ ብቻ ማስተላለፍ የተመለከተው ሰውም “ብርቄ ሬድዮ” እያለ ያሽሟጥጣት ነበር አሉ፡፡)
 
ይኽ ምናልባት ፈገግ ሊያሰኝ ቢችልም በሀገሪቱ የተማረ ከተሜና በትምህርት ብዙም ያልገፋው የገጠር ነዋሪ መካከል የፈጠረውን የአስተሳሰብ ክፍተት ላስተዋለ ግን ሕዝብንም፣ ልብንም ከኹለት የሚሰነጥቅ አእምሯዊ ዘር ማጥፋት (intellectual genocide) ሊባል የሚችል ይመስለኛል፡፡ ይኽ ክፍተት ደግሞ በእነዚኽ የሀገሪቱ ዜጎች ነዋሪ መካከል ለማስታረቅ እጅግ በጣም ብዙ የሚያደክም አለመናበብ ይፈጥራል፡፡ ከተሜዎቹ መንግሥቱን ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲወጡ የሉካሼንኮ መንግሥት ገጠሬዎቹን ሰብሰብ ያደርግና በተቃርኖ ያሰልፋል፡፡ ገጠሬዎቹም ከተሜዎቹን ሰልፍ አድራጊዎች ከሬድዮ ጣቢያቸው በተማሩት የቃላት ካራቴ “እነዚኽ የምዕራብ አውሮፓውያን ቅጥረኞች፣ ፀረ ሰላሞች፣ ፀረ ልማቶች” ምናምን እያሉ ይቀጠቅጧቸዋል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያሉ ሰዎችንም እንደነገሥታቱ ዘመን “ልማታዊው መሪያችንና ፓርቲያቸው ለዘለዓለም ይኑሩ፡፡” እያሉ እንዲሰግዱ የማድረግ ዐቅም አለው- ሚዲያ፡፡ 
 
 
 
በሥልጡኖቹ ዘንድ ሚዲያ ያነቃል፤ ያስተምራል፤ ሐሳብ ይቆሰቁሳል፡፡ በሰው ልጅ የሐሳብ ነጻነት በሚያምኑት ዘንድ ሚዲያ የማስተማሪያ፣ የማንቂያ፣ ሐሳቦች ተፋጭተው የተሻለ፣ የነጠረ ሐሳብ የሚቀርብበት የማኅበረሰብ ንቃተ ኅሊና ማዳበሪያ ነው፡፡ በአምባገነኖች ዘንድ ደግሞ እንዲኹ እንደሉካሼንኮዋ ቤላሩስ ሕዝብን ማደደቢያ፣ ማደንዘዣ መሣሪያ ኾኖ ያገለግላል፡፡ የዚኽ ምክንያቱም አምባገነኖች በሥልጣን ላይ ሊኖሩ የሚችሉት ላቅልጥኽ ቢሉት ሰም፣ ልቀጥቅጥኽ ቢሉት ገል ኾኖ የሚታዘዛቸው የደነዘዘ ማኅበረሰብ ሲኖር ብቻ እንደኾነ አበጥረው ስለሚያውቁ ነው፡፡  
          
እነሆ በአብሮ አደጌና በእኔ መካከል በአልዓዛርና በነዌ ነፍሶች መካከል ያለውን ገደል ያኽል የአስተሳሰብ ልዩነት አለ፡፡ ለዚኽ አብሮ አደጌ ርእዮት አሸባሪ ባትኾን እንኳ መታሠር የሚገባት፣ ምንም የማጠቅም ለፍላፊት ናት፡፡ ለእኔ ግን ዛሬ አሸባሪ ተብላ የታሠረችው ርእዮት ጽሑፎቿን በስስት የማነብላት፣ እንባዬን አነባሽልኝ የምላት፣ ፈገግታውን ስለተነጠቀው ትውልዴ ሳስብ እፊቴ ድቅን የምትል ደፋር ብዕር ናት፡፡ ጭንጫ ላይ ተዘርቶ ሳለ ስንዴ ለማፍራት ለሚጥረው፣ ደጋግሞ ቀናሊል ወድዶ አንገቱን ለተዘለሰው የእኔ ትውልድ ብዙ በጎ ዕሴቶችም ወኪል ትኾንልኛለች፤ የሐሳብ ልዩነቶችን ታግሦ በማስተናገድ አበቦች ፍሬ እንዲያፈሩ በማድረግ ረገድ ምን ያኽል ኋላ ቀር የዓለም ጥግ ውስጥ እንደኾንኹ ታስታውሰኛለች፡፡ ለዚኽ አብሮ አደጌ ግን የርእዮት ጉዳይ ዐዲስ የወጣ ዘፈን ወይም የማንችስተር ሲቲና የአርሰናልን ጨዋታ ያኽል እንኳ አይመስጥም፡፡  
   

         ቀስ እያልኹ አኹን አጠገቤ ያለው ይኽ አብሮ አደጌ፣ እርሱ የሚከታተለውን ቴሌፍጀንና ሬድዮ ያለአማራጭ የሚከታተሉ ሰዎችን በሙሉ ወክሎ እንደቆመ ተሰማኝ፡፡ እናም ራሴን በርእዮት ቦታ አድርጌ ማሰብ ጀመርኹ፡፡ ርእዮት አኹን ይኽ ሰው ያለውን ብትሰማ ምን ይሰማታል ብዬ አሰብኹ፡፡ ጭንቅላቴም ሕይወት ተፈራ “Tower in the Sky” በተሰኘው መጽሐፏ ውስጥ በኢሕአፓነት ተይዛ ሻሸመኔ ወደሚገኝ የጦር ማሠልጠኛ በተወሰደች ጊዜ በዚያ ይሠለጥኑ የነበሩት (እርሷ ነጻ ልታወጣቸው በሕይወቷ ስትወራረድላቸው የነበሩት) ገበሬ ሚሊሻዎች “ስጡንና እዚኹ እርምጃ እንውሰድባቸው! እንግደላቸው!” እያሉ ሲያቅራሩ ስትመለከት የተሰማት ስሜት ተሰማኝ፡፡ 

          ኒኮሎ ማኪያቬሊ “ተራው ሕዝብ ደደብ ነው፡፡” ይላል፡፡ እኔ ግን “አምባገነኖች የሚገዙት ተራ ሕዝብ ደደብ ይኾናል፡፡” ብዬ ላርመው ወደድኹ፣ አምባገነን መሪዎች የሕዝባቸውን አእምሮ እንደሰም አቅልጠው፣ እንደገል ቀጥቅጠው በፕሮፓጋንዳና በዱላ ይፈጥሩታልና፡፡

 
ጦማሪው at 8:39 AM

በአዲስ አበባ አንድ አንበሳ አውቶቡስ 15 ሜትር ጥልቀት ካለው ድልድይ ገባ፤ 8 ሰዎች ሞቱ

 

ዘነበወርቅ ድልድልይ የገባው አውቶቡስ ሲወጣ

anbesa-bus
(ዘ-ሐበሻ) በአዲስ አበባ ከተማ ከካራ ቆሬ ወደ ለገሃር ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ዘነበወርቅ አለርት ሆስፒታል ፊትለፊት ረዥም ድልድይ ውስጥ ገባ፤ በዚህ አሰቃቂ አደጋ ስምንት ሰዎች መሞታቸው ይፋ ሆነ። 

አውቶቡሱ ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቁ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ሲያስታውቅ የአውቶቡሱ ቁጥር 66 እንደሆነ ታውቋል።

ካራ ቆሬ ወደ ለገሃር ሲጓዝ ዘነበወርቅ አለርት ሆስፒታል ፊት ለፊት ባለው ረዥም ድልድይ ውስጥ በገባው አውቶቡስ የተነሳ በአደጋው እስካሁን አንድ እግረኛን ጨምሮ አራት ወንድ እና አራት ሴት ተሳፋሪዎች ህይወታቸው እንዳለፈ ሲገለጽ 46 የሚሆኑት ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ዘ-ሐበሻ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። የአውቶቡሱ ሹፌር እና ትኬት ቆራጭ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት ተርፈዋል።

የአውቶቡሱ አደጋው መንስኤ ላይ መሆኑ ሲታወቅ በአውቶቡሱ ድልድይ ውስጥ መግባት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑ ዘ-ሐበሻ ጨምሮ የደረሳት ዜና ያስረዳል።