የስልክና የኢንተርኔት ስለላ እሰጥ አገባ


‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቃወሙትን ዜጎች ለማፈን የስልክና የኢንተርኔት ስለላ ያካሂዳል›› ሒዩማን ራይትስ ዎች

‹‹ቅርፁን ቀየረ እንጂ የተለመደ ውንጀላ ነው›› የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት

Redwan

የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮሙዩኒኬሽንና የኢንተርኔት አገልግሎት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም

ዜጎቹን እየሰለለ ነው በማለት፣ መቀመጫውን በኒውዮርክ አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሒዩማን ራይትስ ዎች ወቀሳ አቀረበ፡፡

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎች ባለሙያዎችን በማነጋገር አዘጋጀሁት ባለውና በተጠናቀቀው ሳምንት ይፋ ባደረገው ባለ 100 ገጽ ሪፖርት ነው የኢትዮጵያ መንግሥትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ ነው በማለት የኮነነው፡፡ ‹‹የምናደርገውን በሙሉ ያውቁታል›› በሚል ርዕስ ይፋ የሆነው ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስለላ ተግባሩ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ከተለያዩ አገሮች እንዳገኘ፣ የስለላ ተግባሩን የሚፈጽመውም በአብዛኛው በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ላይ ነው ሲል ወንጅሏል፡፡

ከ100 በላይ በመንግሥት የቴሌኮምና ኢንተርኔት ስለላ የተያዙና ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያንን፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የደኅንነት ሠራተኞችንና የሌሎች አሥር አገሮች የደኅንነት ባለሙያዎችን አነጋግሮ ሪፖርቱን ማውጣቱን ድርጅቱ ገልጿል፡፡

በተለይ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም አገር ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ ከታገደ የፖለቲካ ድርጅት ጋር በማንኛውም መንገድ ቅርበት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ይሰለላሉ፣ የሚያደርጉት የስልክ ንግግር በተለይ ደግሞ ከውጭ አገር የተደወለ ከሆነ ያለ ግለሰቦቹ ፈቃድ ወይም ዕውቅና ተጠልፎ እንደሚቀዳ የሒዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ሰላማዊ ሠልፎች በሚኖሩበት ጊዜ በተለይ ሠልፍ በሚደረግበት አካባቢ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ የሚቋረጥ መሆኑን፣ አንዳንዴ ደግሞ ዋነኛ የሠልፉ አዘጋጆች ባሉበት ቦታ የስልክ ልውውጣቸውን መሠረት በማድረግ እንዲያዙ የሚደረግ መሆኑን ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

‹‹አንድ ቀን የደኅንነት ሰዎች መጡና አሠሩኝ፡፡ ከዚያም እኔን የሚመለከቱ ነገሮች አሳዩኝ፡፡ የተደዋወልኳቸውን ስልኮች ዝርዝር በሙሉ አሳዩኝ፡፡ ከዚያም አልፈው በስልክ ከወንድሜ ጋር የተለዋወጥኩትን መልዕክት አስደመጡኝ፡፡ ይዘው ያሠሩኝ ከወንድሜ ጋር ስለፖለቲካ በስልክ ስላወራን ነው፡፡ ይህ የሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ የሞባይል ስልክ ባለቤት በሆንኩበት ወቅት ነው፡፡ አሁን ግን በነፃነት ማውራት እችላለሁ፤›› ሲል አንድ ስሙ ያልተገለጸ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆነ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ደረሰብኝ ያለው እንግልት በሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ተካቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ስለላውን በስኬታማ መንገድ እንዲያካሄድ የሚያስችሉ መሣሪያዎችን በማቅረብ ረገድ ዜድቲኢ የተባለው የቻይና የቴሌኮም ኩባንያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ዜድቲኢ ከተባለው የቻይና ኩባንያ በተጨማሪ በርካታ የአውሮፓ ኩባንያዎች የተለያዩ የስለላ ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ መንግሥት አቅርበዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ ከእነዚህም መካከል መቀመጫውን በእንግሊዝና በጀመርመን ያደረገው ጋማ ኢንተርናሽናል የተባለ ኩባንያ የሚያመርተው “Finfisher” (ፊንፊሸር) የተባለ ዘመናዊ የስለላ ሶፍተዌር፣ እንዲሁም ሃኪንግ ቲም የተባለ በጣሊያን የሚገኝ ኩባንያ የሚያመርታቸው ‹‹ሪሞት ኮንትሮል ሲስተም›› የተባሉ የስለላ ቴክኖሎጂዎችን የኢትዮጵያ መንግሥት በእጁ አስገብቶ እየተጠቀመበት ነው ሲል ሪፖርቱ ያብራራል፡፡

እነዚህ ከላይ የተገለጹት ሶፍትዌሮች ለደኅንነት ተቋማትና ለስለላ ሠራተኞች የሚፈለጉ ሰዎችን መረጃዎች ለማግኘት የሚያስችሉ እንደሆነ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

የተጠቀሱት ሶፍትዌሮችን በመልቀቅ የሚፈለጉ ሰዎች ኮምፒዩተሮችንና ስልኮችን እንዲያጠቁ፣ በተጨማሪም ያለ ኮምፒዩተሮቹ ወይም ስልኮቹ ባለቤቶች ዕውቅና መረጃውን ማየት፣ የኮምፒዩተሮቹን ካሜራ በመጠቀም ምን እየተከናወነ መሆኑን ከርቀት መመልከት የሚያስችሉ ናቸው ሲል የሒዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱት ዜድቲኢ እና ጋማ ኢንተርናሽናል የቴክኖሎጂ ምርቶቻቸውን ለኢትዮጵያ መንግሥት ከማቅረባቸው በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸምባቸው የሚያስችሉ ገደቦችን አካተው እንደሆነ ለማነጋገር ቢሞክርም፣ ምላሽ ሊሰጡት እንዳልቻለ የሒዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ይገልጻል፡፡

በአሁኑ ወቅት በ800 ሚሊዮን ዶላር የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ዜድቲኢ የአዲስ አበባ ቢሮ ሪፖርቱን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጥያቄ የቀረበለት ቢሆንም፣ ጉዳዩ ‹‹መንግሥትን የሚመለከት ነው›› በማለት ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አመራሮች በጽሑፍና በስልክ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

ይሁን እንጂ የመንግሥትን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት ምላሽ፣ የሒዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት የተለመደ የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሒውማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የማበላሽት የተለመደ ዘመቻው በመሆኑ የተለየ የምለው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም አገልግሎትን ከከተሞች አልፎ በገጠር አካባቢዎች እያስፋፋ የሚገኘው አንዱ የልማቱ አካል በመሆኑ እንጂ ስለላን ለማስፋፋት አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ይህ የሒዩማን ራይትስ ዎች የተለመደ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ አሁን በቴሌኮም ኢንዱስትሪው አማካይነት የሰብዓዊ ጥሰት ይፈጸማል በማለት ያወጣው ሪፖርት የሄደበት መንገድ መቀየሩን ያሳይ እንጂ ግቡ አንድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s