Archive | April 25, 2014

የፕሬስ እቀባና አፈና በኢትዮጵያ

 

የመናገር ነጻነት ለአንድ ሃገር እድገት መሰረታዊ ነገር ነው:: በአሁኑ ዘመን ባደጉት ሃገሮች ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሃሳባቸውን ያለ ፍርሃት መናገር እንዲችሉ ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል ይደረግላቸዋል:: የዚህም ድጋፍ ዋና ጥቅሙ ካደጉም በሁዋላ በማንኛውም የስራ ዘርፍ ትክክል የሆነውን ትክክል ስህተት የሆነውን ደግሞ በመወያየት በመነጋገር ሂስ በመሰጣጣት ያርሙታል::

እንግዲህ መንግስትም ለዚህ ነው ለሃገር እድገት የሚሆነውን ነገር ብቻ እንጂ በተሳሳተና በተጭበረበረ መንገድ ህዝቡን ማስተዳደር የማይችለው:: ምክንያቱም “ለምን?” የሚለው ይበዛላ:: ስራውንም ባግባቡ ካልከወነ እንደ አንድ ደካማ ሰራተኛ ከስራ እንደሚባረረው እሱንም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጊዜ “አንተ የተሰጠህን የስራ ድርሻ ባግባቡ አልተወጣህም እና ለሌላው እድል ስጥ” ይባላል:: ይህንን በግልጽ የግል ሚድያዎች ቢያወሩ ሃሳባቸውን ቢያስተላልፉ ማነው ሊያፍናቸው የሚችለው? የመናገር ነጻነት እንደ እህል እና ውሃ በደማቸው አለና ፣ ህዝብም በመረጠው መንግስት ላይ የበላይ ነውና እንዲሁም መንግስት ህዝብን ማገልገል እና መብቱን መጠበቅ ብቻ እንደሆነ ስራው ያውቃልና

liberdade-de-imprensa_18.02

እንደው ወደኛው ሃገር ስመልሰው ከቤተሰቦቻችን ፣ ከአካባቢያችን እና ከትምህርት ቤት ይነሳል:: “ልጅና ምን ወደጉዋዳ” ፣ “ታላቅ ሲያወራ ልጅ አይገባም” እየተባለ እንዳናወራ ፣ ፈሪ እንድንሆን ፣ በትንሽ ነገር የምንደነግጥ ሆነን እንድናድግ ሆንን::

መንግስትም እንግዲህ እንዲሁ ነው እሱ የሰራው ካልሆነ ሌላው የሞከረው የተሳሳተ እና የተረገመ ነው:: የምትሄድበት መንገድ ስህተት ነው የተባለ እንደው ለምን ተባለኩ ብሎ በማን አለብኝነት ተናጋሪውን ከነ ዘር ማንዘሩ ማሸማቀቅ ማሰር የተለመደ ሆንዋል::

መንግስት በራሱ ሚድያ ሃያ አራት ሰአት የፈለገውን እንዲናገር ሌላው ዝም ብሎ እንዲያዳምጥ የተፈረደበት ሃገር ላይ ነን ያለነው::

የግል ሚድያው ቀጭጮ መንግስት የፈረጠመበት ፣ የተማረው ሃይል የተዋረደበት ፣ የግል ሴክተሩ በጣር ያለበት ፣ ማህበራት የመንግስት አሽከር እንዲሆኑ የተፈረደበት ሃገር ሆንዋል::

እንግዲህ “ይሄንን ሁሉ ነገር እያየን ዝም አንለም ከጭቆናም ሞት ይሻላል” ያሉና የተናገሩ እንዲሁም የጻፉ በእስር የሚማቅቁበት የተወሰኑት ደግሞ እንዲሰደዱ የሚገፉበት ሃገር መሆኑ አፍጥጦ የሚታይበት ዘመን ላይ ነን::

የጋዜጠኛነት ሙያ የተከበረ መሆኑ የተዘነጋበት እና እውነትን ፍለጋ የሚደክመውን ባለሙያ ሲናገር ለምን ተናገርክ ፣ ሲጽፍ ማን ላይ ነው ፣ አስተያየት ሲሰጥ አንተ ምን ታውቅና የሚባልበት ሃገር ነው::

ታድያ እንዴት ነው ሃሳቡን መግለጽ የሚችለው? እንዴት ነው ይሄ ልክ ነው ወይም አይደለም ብሎ ሊል የሚችለው? መንግስት እኮ ልማታዊ ነኝ እንዳለው በአግባቡ ለህዝቡ የሚገባውን እኩል እድገት ለውጥ እና ከድህነት እና ከችግር አላቆ ቢሆን እኛም ደስ ባለን

የሚሰራው እየታየ ለውጥ እና እድገት ከመንግስት የፕሮፖጋንዳ ሚድያ ያልዘለለ በሆነበት ሃገር እንዲሁም የህዝቡ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ጥቂት ሰዎች ከብረው ሌላው በድህነት የሚማቅቁበት በሆነበት መጻፍ መሰብሰብ ወይም ሃሳብን በነጻነት መግለጽ የዛፍ ላይ እንቅልፍ በሆነበት ሃገር ይህ ሁሉ ችግር አለ ብለን እንድንናገር ጸሃዩ መንግስታችን ባይፈቅድም እኔ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ አፈናና እቀባ አለ!!! እላለሁ::

Alemayehu Tibebu

Germany