Archive | April 2014

የፕሬስ እቀባና አፈና በኢትዮጵያ

 

የመናገር ነጻነት ለአንድ ሃገር እድገት መሰረታዊ ነገር ነው:: በአሁኑ ዘመን ባደጉት ሃገሮች ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሃሳባቸውን ያለ ፍርሃት መናገር እንዲችሉ ከፍተኛ ድጋፍ እና ክትትል ይደረግላቸዋል:: የዚህም ድጋፍ ዋና ጥቅሙ ካደጉም በሁዋላ በማንኛውም የስራ ዘርፍ ትክክል የሆነውን ትክክል ስህተት የሆነውን ደግሞ በመወያየት በመነጋገር ሂስ በመሰጣጣት ያርሙታል::

እንግዲህ መንግስትም ለዚህ ነው ለሃገር እድገት የሚሆነውን ነገር ብቻ እንጂ በተሳሳተና በተጭበረበረ መንገድ ህዝቡን ማስተዳደር የማይችለው:: ምክንያቱም “ለምን?” የሚለው ይበዛላ:: ስራውንም ባግባቡ ካልከወነ እንደ አንድ ደካማ ሰራተኛ ከስራ እንደሚባረረው እሱንም በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጊዜ “አንተ የተሰጠህን የስራ ድርሻ ባግባቡ አልተወጣህም እና ለሌላው እድል ስጥ” ይባላል:: ይህንን በግልጽ የግል ሚድያዎች ቢያወሩ ሃሳባቸውን ቢያስተላልፉ ማነው ሊያፍናቸው የሚችለው? የመናገር ነጻነት እንደ እህል እና ውሃ በደማቸው አለና ፣ ህዝብም በመረጠው መንግስት ላይ የበላይ ነውና እንዲሁም መንግስት ህዝብን ማገልገል እና መብቱን መጠበቅ ብቻ እንደሆነ ስራው ያውቃልና

liberdade-de-imprensa_18.02

እንደው ወደኛው ሃገር ስመልሰው ከቤተሰቦቻችን ፣ ከአካባቢያችን እና ከትምህርት ቤት ይነሳል:: “ልጅና ምን ወደጉዋዳ” ፣ “ታላቅ ሲያወራ ልጅ አይገባም” እየተባለ እንዳናወራ ፣ ፈሪ እንድንሆን ፣ በትንሽ ነገር የምንደነግጥ ሆነን እንድናድግ ሆንን::

መንግስትም እንግዲህ እንዲሁ ነው እሱ የሰራው ካልሆነ ሌላው የሞከረው የተሳሳተ እና የተረገመ ነው:: የምትሄድበት መንገድ ስህተት ነው የተባለ እንደው ለምን ተባለኩ ብሎ በማን አለብኝነት ተናጋሪውን ከነ ዘር ማንዘሩ ማሸማቀቅ ማሰር የተለመደ ሆንዋል::

መንግስት በራሱ ሚድያ ሃያ አራት ሰአት የፈለገውን እንዲናገር ሌላው ዝም ብሎ እንዲያዳምጥ የተፈረደበት ሃገር ላይ ነን ያለነው::

የግል ሚድያው ቀጭጮ መንግስት የፈረጠመበት ፣ የተማረው ሃይል የተዋረደበት ፣ የግል ሴክተሩ በጣር ያለበት ፣ ማህበራት የመንግስት አሽከር እንዲሆኑ የተፈረደበት ሃገር ሆንዋል::

እንግዲህ “ይሄንን ሁሉ ነገር እያየን ዝም አንለም ከጭቆናም ሞት ይሻላል” ያሉና የተናገሩ እንዲሁም የጻፉ በእስር የሚማቅቁበት የተወሰኑት ደግሞ እንዲሰደዱ የሚገፉበት ሃገር መሆኑ አፍጥጦ የሚታይበት ዘመን ላይ ነን::

የጋዜጠኛነት ሙያ የተከበረ መሆኑ የተዘነጋበት እና እውነትን ፍለጋ የሚደክመውን ባለሙያ ሲናገር ለምን ተናገርክ ፣ ሲጽፍ ማን ላይ ነው ፣ አስተያየት ሲሰጥ አንተ ምን ታውቅና የሚባልበት ሃገር ነው::

ታድያ እንዴት ነው ሃሳቡን መግለጽ የሚችለው? እንዴት ነው ይሄ ልክ ነው ወይም አይደለም ብሎ ሊል የሚችለው? መንግስት እኮ ልማታዊ ነኝ እንዳለው በአግባቡ ለህዝቡ የሚገባውን እኩል እድገት ለውጥ እና ከድህነት እና ከችግር አላቆ ቢሆን እኛም ደስ ባለን

የሚሰራው እየታየ ለውጥ እና እድገት ከመንግስት የፕሮፖጋንዳ ሚድያ ያልዘለለ በሆነበት ሃገር እንዲሁም የህዝቡ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በሆነበት ጥቂት ሰዎች ከብረው ሌላው በድህነት የሚማቅቁበት በሆነበት መጻፍ መሰብሰብ ወይም ሃሳብን በነጻነት መግለጽ የዛፍ ላይ እንቅልፍ በሆነበት ሃገር ይህ ሁሉ ችግር አለ ብለን እንድንናገር ጸሃዩ መንግስታችን ባይፈቅድም እኔ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ አፈናና እቀባ አለ!!! እላለሁ::

Alemayehu Tibebu

Germany

የቢዚ ሲግናል፣ የጃሉድና የናቲ ማን የአዲስ አበባው ኮንሰርት ተዘረዘ

(ዘ-ሐበሻ) የታዋቂው የሬጌ ሙዚቃ ተጫዋች ቢዚ ሲግናልን አጅበው ኢትዮጵያዊያኑ ጃሉድ እና ናቲ ማን ይሳተፉበታል የተባለው የአዲስ አበባው ኮንሰርት ተሠረዘ። የፊታችን ቅዳሜ ቴዲ አፍሮ በግዮን ሆቴል ለዳግማዊ ትንሣኤ በዓል በሚያቀርበው ኮንሰርት ቀን በተመሳሳይ በሚሊኒየም አዳራሽ ይደረጋል ተብሎ የነበረው የነዚሁ ታዋቂ አርቲስቶች ኮንሰርት መሰረዝ የከተማው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

Busy-singnal
የአዲስ አበባ የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳስታወቁት ቢዚ ሲግናልን ጨምሮ በርከት ያሉ የሬጌ ሙዚቃ ተጫዋቾጮች በተለይም ጸረ ግብረሰዶማዊ አቋም ስላላቸው በአብዛኛው በግል አውሮፕላኖች እንደሚጓዙ ጠቅሰው ወደ አዲስ አበባም በግል አውሮፕላን ለመሄድ አስበው አውሮፕላን አለመገኘቱን ጠቅሰው ለኮንሰርቱ መሠረዝም ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ ጌይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ሰጥቶ እያለ በኋላም ሰልፉ እንዲቀር ከተደረገ በኋላ የጸረ ጌይ አቋም ያለው ድምጻዊ ቢዚ ሲግናል ኮንሰርት መሰረዙ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል።

 

በሚሊኒየም አዳራሽ ለዳግማዊ ትንሳኤ የፊታችን እሁድ ይደረጋል ተብሎ የነበረው ኮንሰርት ከተሰረዘ በሁላ የተሰጠው ምክንያት ለዘፋኙና ባንዱ ማመላለሻ የአውሮፕላን ማጣት ይሁን እንጂ ከበስተጀርባው የጸረ ጌይ ጉዳይና ሌሎችም ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በሌላ በኩል ቴዲ አፍሮ የፊታችን ቅዳሜ ምሽት በጊዮን ሆቴል ለሚያደርገው ኮንሰርት በትናንትናው ዕለት የመድረክ ግንባታ ሥራ መጀምሩን ለማወቅ ችለናል።

jalud

ከሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተላለፈ ጥሪ!

blue-road-sign-on-background-clouds-and-sunburst (1)

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ምሁራን መፍለቂያ ለመሆኗ አለም ይመሰክርላታል፡፡ አንቱ የተባሉ ምሁራንን በማፍራት ለዓለም አበርክታለች፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በአለም ካሉ ታላላቅ ዩንቨርስቲዎች እና የምርምር ተቋማት እስከ አመራነት ድረስ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መገኘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ምሁራን በተሰማሩበት ስራ መስክ የሚያስመዘግቡት ውጤት እና በስራቸው ተሸላሚ መሆን ላነሳነው ሀሳብ ማጠናከሪያነት ያገለግለናል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነውና ልብ የሚሰብረው ግን ሀገራችን ከእነዚህ ውድ ልጆቿ ተገቢውን ዋጋ አለማግኘቷ ነው፡፡ ሀገራችን የወላድ መካን እየሆነች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሆነ ተብሎ የሚቀነባበር ሴራ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ምሁራን መፍለቂያ ብትሆንም ቅሉ በተከታታይ ስልጣኑን የጨበጡት ጭፍን አንባገነኖች በሚያራምዱት አግላይ ምሁር ፖሊሲ ምክንያት እውቀታችሁን እና ገንዘባችሁን በምትወዷት ሀገራችሁ ኢንቨስት አድታደርጉ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው የስደትን መራራ ጽዋ እንድትጨልጡ ተገዳችኋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለይ ባለፉት 10 አመታት በተቃዋሚዎች መዳከም የሚያታግል ኃይል አጥታችሁ እንደቆያችሁም እናምናለን፡፡

ፓርቲያችን ሰማያዊ እያንዳንዱ ዲያስፖራ ሀገር ቤት ያለውን ዜጋ ያክል የኢትዮጵያዊነት መብት አለው ብሎ ያምናል፡፡ ይህ ይረጋገጥ ዘንድም አጥብቆ ይታገላል፡፡ በተለያየ ሁኔታና ወቅት አንባገነኖችን በሀገር ውስጥ እንደታገላችሁ እናምናለን፡፡ ለዚህ ትግላችሁና ለከፈላችሁት ዋጋም እውቅና እንሰጣለን፡፡ በስርዓቶቹ ጨካኝ ዱላ እና ሰቆቃ ብዛት ውድ ሀገራችሁን ትታችሁ የሥደትን ኑሮ ትገፉ ዘንድ ቢበየንባችሁም ስለ ኢትዮጵያ ከመብሰልሰል እንዳልዳናችሁና ሀሳባችሁ ሀገር ቤት ስለ መሆኑ መስካሪ አያሻም፡፡

ውድ የሀገራችን ልጆች እናንተ የሰው ሀገር በምታለሙበት በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ኢትዮጵያ የጉልበት ሰራተኛ ሳይቀር ከቻይናና ከህንድ በከፍተኛ ክፍያ እያስመጣች ትገኛለች፡፡ ይህ ደግሞ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ስለ መሆኑ ለእናንተ መንገር ለቀባሪ እንደ ማርዳት ያለ ነው፡፡ ይህ በእውነት ለአንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ እንደ እግር እሳት ያንገበግባል፡፡ ልማታዊ መንግስት ነኝ በሚል የቃላት ጋጋታ ብቻ ከድሃው ወገናችሁ በሚሰበስበው ገንዘብ የሰከረው ጉልበታም መንግስት ዴሞክራሲና ልማት አንድ ላይ አብረው አይሄዱም በሚል ማሳሳቻ በየ ጊዜው ጉልበቱን እያፈረጠመ የሄደው በአብዛኛው እናንተ ከምትኖሩበት ከምዕራባውያን ሀገራት በሚቀበለው እርዳታ መሆኑ ሀቅ ነው፡፡
ዳያስፖራው በነጻነት መኖር ምን ማለት እንደሆነ በተግባር ያውቀዋል፡፡ ነጻ ሆኖ መስራት ለሀገር ልማት ግንባታ ያለውን ጠቀሜታም ሀገር ቤት ካለው ህዝብ በተሻለ ሁኔታ ይገነዘባል፡፡ ድህነትና አንባገነንነት ባመጣው ጦስ ኢትዮጵያዊ ክብራችን ተገፎ በየ በረሃው ዜጎቻችን እንደ እንስሳት ሲታረዱ፣ እህቶቻንን በቡድን ሲደፈሩ፣ ወገኖቻችን ልብና ኩላሊታቸው ወጥቶ ለገበያ ሲውል እንደማየት ያለ ዘግናኝ ተግባር ምን አለ?!! ይህ ህገ ወጥ ተግባር ሊፈጸምባቸው አይገባም ብላችሁ ያሳያችሁት ለወገን መቆርቆር ይበል የሚያስብልና ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለን እናምናለን፡፡
በተለይ የሳውዲ መንግስት በዜጎቻችን ላይ የወሰደባቸውን ህገ ወጥ ተግባር ለማውገዝ ያደረጋችሁትን ርብርብና ለሀገራችን በአንድ ሆ ብላችሁ መቆማችንሁን በድጋሚ እያመሰገንን አንባገነኑን ኢህአዴግ ለመታገል በሚደረገው ትግል አጋራነታችሁን ስለምንገነዘብ ከጎናችን በመሆን ለምታሳዩት ውጣ ውረድ እውቅና እንሰጣለን፡፡ ከዚህ በፊት ያሳያችሁትን የትግል ቁርጠኝነት እንደምትደግሙት በማመን ያላችሁን የገንዘብ አቅም፣ የእውቀትና የተሰሚነት ሚና በመጠቀም የአንባገነኑን ስርዓት አፈና በማጋለጥ ከጎናችን እንድትሰለፉ ስንል እንጠይቃለን፡፡ ዳያስፖራው ያለውን የኢኮኖሚ ነጻነት፣ የሚዲያ ነጻነትና፣ ሀገር ቤት ካለው ጋር ሲነጻጸር ያለው የለሻለ የትምህርት ደረጃና ልምድ፣ እንዲሁም በእርዳታ ሰጭ ሀገራት ያለው የተሰሚነት አቅም ተጠቅሞ ሀገር ቤት ያለውን ትግል በማገዝ ነጻ የምንወጣበትን ቀን ሊያፋጥን እንደሚገባ ፓርቲያችን ያምናል፡፡

ፓርቲያችን የህግ የበላይነትን ለማስፈን ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጋ ያሳተፈ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ዘርፈ ብዙ ትግል ውስጥ ደግሞ ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ‹‹የተነጠቁ መብቶቻችን እናስመልስ›› በሚል መሪ ቃል ታላቅና ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ያካሂዳል፡፡ በመሆኑም ይህን ሁሉን አቀፍ የሆነ ሰላማዊ ትግል በሞራል፣ በእውቀትና በምክር፣ እንዲሁም በገንዘብ በማገዝ የትግሉ አጋር ትሆኑ ዘንድ ጥሪያችን እናስተላልፋለን፡፡

ከአገራችሁ እርቃችሁ የምትኖሩ በመሆናችሁ አዲስ አበባ ውስጥ አብራችሁን ባትቀሰቅሱ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ባትወጡና ባትታሰሩም መረጃውን ለዓለም ህዝብ በማድረስ ከፍተኛ ሚና እየተጫወታችሁ ቆይታችኋል፡፡ በዚህ ሰልፍም አገር ቤት ለሚኖሩ ቤተሰብ፣ ጓደኛ እንዲሁም ሌላው ህዝብ በስልክ፣ በማህበራዊ ድህረ ገጽና የተለያዩ መልዕክት ማስተላለፊያዎች በመጠቀም ህዝቡን የማነቃቃት አቅምና አጋጣሚ ተጠቅማችሁ በትግል ጉዟችን ተሳታፊ እንድትሆኑ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ኑ ራሳችንን ነጻ በማውጣት የአገራችንን እጣ ፈንታ እንወስን!

ዋና ኦዲተር ለብክነት የተጋለጡ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሒሳቦችን አጋለጠ

-ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ሒሳብ አለ
-785 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ወጪ ታይቷል
-ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል
Abadula
የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ላለፉት በርካታ ዓመታት ለፓርላማ ሲያቀርበው እንደቆየው ሁሉ፣ ለብክነት የተጋለጠ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ሀብት መኖሩን ባለፈው ሚያዝያ 14 ቀን 2006 ዓ.ም.
ለፓርላማው ይፋ አድርጓል፡፡ ተመሳሳይ ሪፖርቶችን ሲሰማ የቆየው ፓርላማው ፈጣን ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የአንድ ዓመት ገደብን መስጠት መርጧል፡፡
በዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ምክንያት ሠራተኞችን ለማቆየት መቸገራቸውን የገለጹት የፌደራሉ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ራሳቸው ጭምር በቡድን መሪነት በተሳተፉበት የ130 የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ2005 ዓ.ም. በጀት ኦዲት በማድረግ፣ እንዲሁም በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን የስምንት መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በማሠራት፣ በአጠቃላይ የ138 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት በመተንተን የኦዲት ግኝቱን ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡
ከቀረበው የፋይናንስ ሕጋዊነትን የተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ውስጥ አንድ ቢሊዮን 527 ሚሊዮን ብር ተሰብሳቢ ሒሳብ መኖሩን፣ ሕጋዊ ሥርዓቱን በልተከተለ መንገድ የተለያዩ የመንግሥት ድርጅቶች 785 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን፣ የተፈቀደው በጀት በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት ደግሞ 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት መገኘቱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በወቅቱ ካልተወራረደ ወይም ካልተሰበሰበ በቆየ ቁጥር የመሰብሰብና ወደ ሀብትነት የመለወጥ ዕድሉ አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ፣ ኦዲት ከተደረጉት መሥሪያ ቤቶች 77 በሚሆኑት ላይ 877.1 ሚሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሰው ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ከያዙት መካከል በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ቴክኒክ ሙያና ትምህርት ሥልጠና ማስተባበሪያ 173.6 ሚሊዮን ብር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 149.5 ሚሊዮን ብር፣ የትምህርት ሚኒስቴር 100 ሚሊዮን ብር ይገኙበታል፡፡
ዋና ኦዲተር የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰቡን ለማጣራት ባካሄደው ኦዲት 32.2 ሚሊዮን ብር ከገቢ ግብር፣ ከቀረጥና ታክስ እንዲሁም ከሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ ደንቦች መሠረት አለመሰብሰቡን አረጋግጧል፡፡
ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጀቶች አግባብ ባለው ሕግና ደንብ መሠረት የመንግሥት ገቢ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት 326.7 ሚሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ አብዛኛው ይህ ውዝፍ ያልተሰበሰበ ገቢ የሚመለከተው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን እንደሆነ ከኦዲት ሪፖርቱ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በጊዜያዊነት ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች የጊዜ ገደባቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የጊዜ ገደቡ በሕግ አግባብ እንዲራዘም ካልተደረገ በስተቀር በዋስትና የተያዘውን ገንዘብ የመውረስ መብት በሕግ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን በጊዜያዊነት ገብተው የመቆያ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ በድምሩ 222.5 ሚሊዮን ብር የዋስትና ገንዘብ አለመሰብሰቡን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
‹‹የሚሰበሰብ ገቢ መንግሥት ለሚያከናውናቸው የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋትና ለአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ሚና የሚኖረው በመሆኑ፣ የመንግሥት ሕግና ደንብ ተከብሮ መሠራት አለበት፤›› ሲሉ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ አሳስበዋል፡፡
ሕጋዊነት የጎደላቸው ወጪዎችን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት 785 ሚሊዮን ብር አግባብነት የጎደላቸው ወጪዎች መኖራቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዋነኝነት የሚጠቀሰው በ25 መሥሪያ ቤቶች በወጪ ተመዝግቦ ነገር ግን የወጪውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ማስረጃ ሊቀርብበት ያልቻለ 202.6 ሚሊዮን ብር በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡
የግዥ አዋጁን እንዲሁም ደንብና መመርያን ያልተከተሉ ግዥዎችን በተመለከተ ደግሞ፣ 43 መሥሪያ ቤቶች 165.9 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ወጪ አድርገዋል ብለዋል፡፡ ሌሎች 41 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 76 ሚሊዮን ብር ደንብና መመርያን በመጣስ ክፍያ መፈጸማቸውን በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
ሒሳቦች በወጪነት የሚመዘገቡት የሚፈለገው አገልግሎት መገኘቱን ወይም የሚፈለገው ንብረት በአግባቡ በእጅ መግባቱ ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ 13 መሥሪያ ቤቶች አገልግሎቱን ወይም ንብረቱን ሙሉ በሙሉ ሳያገኙ የከፈሉትን የ234.8 ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ በወጪ መዝገብ ይዘው ተገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የተፈለገው አገልግሎት ወይም ንብረት ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ በተሰብሳቢ መያዝ ይኖርበታል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በ104 መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ለተለያዩ ግዥዎች አራት ሚሊዮን 471 ሺሕ ብር ያላግባብ በብልጫ መከፈሉን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም በአሥር መሥሪያ ቤቶች የንብረት ገቢ ደረሰኝ ያልቀረበለት 22.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መኖሩን፣ በሌሎች ሰባት መሥሪያ ቤቶች ደግሞ 1.6 ቢሊዮን ብር ቀረጥ የተከፈለባቸው ንብረቶች ገቢ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
ቀረጥ ተከፍሎባቸው ንብረቶቹ ገቢ ለመሆናቸው ለማረጋገጥ ካልተቻለባቸው መሥሪያ ቤቶች ትልቁን ድርሻ የያዘው፣ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ሲሆን፣ በቀጣይነት ደግሞ ጤና ጥበቃና ትምህርት ሚኒስቴር ተጠቅሰዋል፡፡
በ23 መሥሪያ ቤቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ 90.9 ሚሊዮን ብር መኖሩን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የፌደራል መንግሥት ግዥ አፈጻጸም መመርያ በግንባታ ቦታ ላይ ላሉ ዕቃዎች፣ ወይም ግንባታ ላይ ላልዋሉ ክፍያ መፈጸምን የሚከለክል ቢሆንም፣ 11 መሥሪያ ቤቶች ይህንን በመጣስ 168.6 ሚሊዮን ብር መክፍላቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ መንግሥት የግንባታ ዕቃዎችን በብድር ሲያገኝ የተገኘው ቁስ መጠን ተሰልቶ ከግንባታ ወጪ ላይ መቀነስ የሚገባው ቢሆንም፣ አራት መሥሪያ ቤቶች ግን 18.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ በብድር የተገኙ የግንባታ ዕቃዎች ወጪን ሳይቀንሱና ለመንግሥት ካዝና ሳያስገቡ በኦዲቱ ተገኝተዋል፡፡
የተፈቀደላቸውን በጀት በትክክል ለሥራ አውለዋል ወይ የሚለውን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት ደግሞ፣ በ96 መሥሪያ ቤቶች 2.3 ቢሊዮን ብር ያልተሠራበት በጀት ተገኝቷል፡፡ ይህ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት የነበረ ቢሆንም፣ የፓርላማው አባላት በቁጭትና በእልህ እንዳለፈው ዓመት ሲናገሩ አልተስተዋሉም፡፡
ብቸኛው የፓርላማ የግል ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ የኦዲት ሪፖርቱን አስመልክተው፣ ‹‹በዚህ አገር ማንም ምንም ሊያደርግ አይችልም የሚሉ ባለሥልጣናት ያሉ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ እንደዚያ ያስባሉ ወይ?›› የሚል ጥያቄ ዋና ኦዲተሩን አቶ ገመቹ ዱቢሶን ጠይቀዋል፡፡
አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ምላሽ፣ እንዲዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ፣ ነገር ግን ችግር መኖሩን እያወቁ የማያስተካክሉ ኃላፊዎች መኖራቸውን፣ አንዳንድ ጊዜ በሒሳብ ባሙያዎች የሚታለሉ ኃላፊዎች እንዳሉ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
መደረግ የሚገባውን በተመለከተ በዶ/ር አሸብር ለተነሳው ጥያቄ ዋና ኦዲተሩ የሰጡት ምላሽ በዋና ኦዲተርና በአፈ ጉባዔው መካከል በተደረገ ስምምነት በ2006 ዓ.ም. የኦዲት ሪፖርት ላይ የሚገኙ የኦዲት ግኝቶች እስካሁን በነበረው ግዝፈት የሚቀጥሉ ወይም የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ሕጋዊ ቅጣት በመሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ ለመውሰድ ስምምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፓርላማው ቋሚ ከኮሚቴዎች የሚከታተሏቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በይበልጥ መጠየቅ እንደሚገባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሚያዝያ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. የ2006 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ጥያቄ ይቀርብላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ካልገደሉ አያቆሙንም – ሃብታሙ አያሌዉ (የአንድነት አመራር) ሰልፉን በተመለከተ

Ud

ሀገር የመገንጠል ዓላማ ይዞ የተነሳው የህወሓት ጁንታ፣ በስውር እና በአደባባይ የጫካ ልማዱን መሰረት አድርጎ ሲገድል መኖሩ አዲስ ባይሆንም፣ ከሰሞኑ መረር ያለ እርምጃ ‹‹ግድያ›› ማሰቡን ከጓዳው የወጣ የወሬ ምንጭ ደረሰን፡፡
ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በአዲስ አበባ አስተዳደር ጽ/ቤት ተገኝቼ ነበር፡፡ የመገኘቴ ዓላማም የፊታችን እሁድ ሚያዚያ 26 የሚደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የዕውቅና ደብዳቤውን ለመስጠት የተያዘውን ቀጠሮ በማክበር ነበር፡፡
የሰላማዊ ሰልፍ እውቅናን በተመለከተ ኃላፊ የሆኑት አቶ ማርቆስ ፎርም እንዲሞላ አዘዙ፤ የተባለውን ፎርም ሞላን፤ ያን ጊዜ የአቶ ማርቆስ የቢሮ ስልክ አንቃጨለ፤ አነሱት ……ቀጭን ትዕዛዝ ከወዲያ ማዶ……………
‹‹የአንድነትን ሰላማዊ ሰልፍ በተመለከተ ዕውቅናው እንዳይሰጥ ይቆይ›› አቶ ማርቆስ ፊቱ ተለዋወጠ ‹‹ ይቅርታ አድርግልኝ የኔ ችግር አይደለም›› ሌላ ቃል ካፉ አልወጣም፡፡
«አልገባኝም ….ቀጠልኩ ….የአንድነት ሰላማዊ ሰልፍ ተከለከለ እያልከኝ ነው ? »
መለሰ …..«እኔ ምን ላድርግ ? …..»
«የከለከለው ማነው የበላይ ኃላፊ ነው ? »
«አዎ» አጭር መልስ፡፡
ትቼው ወደ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊው አመራሁ፤ ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡ ወደ ፓርቲ ጽ/ቤት ደውዬ ሁኔታውን አሳወኩ። የፓርቲው ፕሬዘዳንት ኢንጅነር ግዛቸውን ጨምሮ በርካታ አመራሮች ፈጥነው ደረሱ፡፡ የአስተዳደሩ ስብሰባም ለሻይ እረፍት ተቋርጦ ኃላፊው ወደ ቢሯቸው ሲገቡ ተከታትለን ገባን፡፡ ላለማናገር ጥቂት አንገራገሩ ። የቢሯቸውን በር አንቀን አናግሩን በማለት ጸናን፡፡
‹‹ምንድነው ችግሩ የሰልፉ ጉዳይ ከሆነ ጨርሰናል፤ እውቅናውን ወሰዳችሁ አይደለም ? ›› አሉ።
ባጭሩ መልስ ተሰጣቸው ፤ «አልወሰድንም ። የአቶ ማርቆስ መልስ ተከልክሏል የሚል ነው፡፡ »
ጥያቄ አስከተልን ……«እርሰዎ መረጃ የለዎትም ? መንግስታዊ ኃላፊነቱ የርስዎ ነው፤ ማነው ከልካዩና ፈቃጁ ? »
መልስ የለም ። ጥቂት ዝም ብለው ‹‹የጠየቃችሁን ሚያዚያ 19 ለማድረግ ነበር፡፡ በዚያ ቀን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የጥበቃ እጥረት አለብኝ በማለት ስላመለከተ የእናንተ ሰልፍ ለሚያዚያ 26 እንዲደረግ ጠየቅናችሁ ። ተስማማን ከዚህ ውጪ የተደረገ ነገር ካለ በኔ በኩል መረጃ የለኝም። ማን እንደከለከለ አናውቅም››
« ስለዚህ ይህንን ከተማ ከንቲባው ካልሆነ ማን ነው የሚመራው? »
ከወዲያ ማዶ መልስ የለም……….ስልክ አነሱ እና አቶ ማርቆስን ወደ ቢሯቸው ጠሩ ። ሰውዬው መጡ ። ማጣሪያ ተጠየቁ። «መመሪያ ደርሶኛል» ሲሉ ለከንቲባው ጽ/ቤት ኃላፊ በኛው ፊት ተናገሩ፡፡ «መመሪያ ሰጪው ማነው?» ወደ አንዱ ቢሮ ዘው ብለን አንድ ሰው አናገርን ………..
‹‹እባካችሁ ይቅርባችሁ ደህንነቶቹ የሚውሉት እዚህ ግቢ ነው፡፡ አንድነቶች ከወጡ እርምጃ ይወሰድ ሲሉ ሰምቻለሁ›› አለን በማንሾካሾክ ድምጽ ………….
ጎበዝ ይሙት ሰነፍ ይኑር ቢሻው
አተላ መሸከም ይችላል ትከሻው………..
ፍርሃት ማነው ቢሉኝ ስሙን አላውቀውም
ሞትን በቁሜ እንጂ ሞቼ አልጠብቀውም፡፡
………………..ህወሓት ሊተኩስ ተዘጋጅቷል እኛም የነሱን ጥይት የሚሸከም ደረት …….እመነኝ ካልገደሉ አያቆሙንም፡፡፡

በዩኒቨርሲቲው መቆየት ካልቻልኩ የፖለቲካ ፓርቲ እቀላቀላለሁ፡፡ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

 •  

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮች በሚሰነዝሯቸው ጠንካራ ትችቶች ይታወቃሉ፡፡ ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት የነፃውን ፕሬስ ሁኔታ አስመልክቶ በሬድዮ ፋና በተዘጋጀው ውይይት ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ጋዜጠኛ ናፍቆት ተስፋዬ ከዶ/ር ዳኛቸው ጋር ባደረገችው ቃለምልልስ የገባበት ስለጠፋው የዩኒቨርሲቲ የኮንትራት ውል፣ ስለፍርድ ቤት ነፃነት፣“በኢትዮጵያ ውስጥ የመናገር ነፃነት የለም”— ስለማለታቸውና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡

  1622800_645309315518047_251774734_n

  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስተማር የተዋዋሉባቸው ሰነዶች በሙሉ መጥፋታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው?

  ከዚህ ቀደም ባልሳሳት—ከአንድ ዓመት ከሁለት ወይም ከሶስት ወር በፊት ይመስለኛል “60 ዓመት ስለሞላህ ኮንትራት ያስፈልግሀል” ተብዬ የሁለት ዓመት ኮንትራት ፈርሜ ነበር፡፡ የዚህ ኮንትራት ግልባጭም ለእኔ የተሰጠኝ ሲሆን በተጨማሪም ለፍልስፍና ዲፓርትመንቱ፣ ለዲኑ ቢሮና ለምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዲሁም ለፐርሶኔል ቢሮ በአጠቃላይ አምስት ቦታ ተላከ፡፡ ሆኖም አምስቱም ደብዳቤዎች ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ሌላው ቀርቶ እኔም ቢሮ የነበረው ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንዲያውም የዲፓርትመንት ኃላፊው፣ የኮሌጁ ዲኑና፣ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ቢሮም “ሲጀመርም ደብዳቤውን ስለማየታችን ትዝ አይለንም” የሚል መልስ ነው የሰጡት፡፡

  ከዚያስ?

  ከዚያማ ይሄ ሰውዬ ኮንትራት ሳይኖረው ከአንድ ዓመት በላይ አስተማረ እስከ ማለት ደረሱ፡
  ፡ እኔም በበኩሌ፣“ኮንትራትህ እድሳት ያስፈልገዋል ተብዬ ሂደቱ አራት ወር ስለወሰደ፣ ለአራት ወራት ደሞዜ ታግዶ ነበር፣እድሳቱ ሲያልቅ ደሞዜ መለቀቁ ምልክት አይሆናችሁም ወይ?” ብላቸው ያመነኝ ሰው አልነበረም፡፡ ፐርሶኔል ክፍሎች ግን ፍቃዱ ባይራዘምለት ከአራት ወር በኋላ ደመወዙን አንለቅም ነበር ብለው ተከራከሩ፡፡ ሆኖም የነሱንም ሀሳብ የሚያዳምጣቸው አላገኙም፡፡ አሁን ለጊዜው በዝርዝር ለማስረዳት ባልዘጋጅም፤በጥቅሉ ሰነዱ ባንዳንድ ሰዎች እርዳታ ፐርሶኔል ቢሮ ከሳምንት በላይ ተፈልጎ ተገኝቷል፡፡ይህ ኮንትራት ባይገኝ ኖሮ ምናልባት ከሥራ ለመሰናበት እደርስ ነበር፡፡ አሁን ግን የኮንትራቱ ውል በመገኘቱ ምክንያት እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ማስተማር እችላለሁ ማለት ነው፡፡ የኮንትራቱ ውል ከመገኘቱ በፊት ግን ደብዳቤ ፅፈውልኝ ነበር፡፡

  ምን ዓይነት ደብዳቤ?

  “በአንተ እጅ ያለውም ሆነ ሌላው ክፍል የነበረው የኮንትራት ውል ስለጠፋ፣ የተሰጠህን የዓመት ፈቃድ ለጊዜው ይዘነዋል” የሚል፡፡ የእኔ ክርክር ጭብጥ ሁለት መንገድ የተከተለ ነው፡፡ አንዱ የኮንትራት ውሉ ሲሆን ሁለተኛው የዓመት ፈቃዱ ነው፡፡ የኮንትራት ውሉ ተገኘ፡፡ በመጀመሪያ የዓመት ቃዱን የያዙት የኮንትራት ውሉ ስለጠፋ ነበር፡፡ ወረቀቱ ሲገኝ ደግሞ የዓመት ፈቃዱ መለቀቅ ሲገባው አሁን ሌላ ሰበብ አመጡ፡፡ እድሜህ ስልሳ ዓመት ስለሞላና የጡረታ ሂደቱ በደንብ ተካትቶ ፋይልህ ውስጥ ስለሌለ፣ የዓመት ፈቃድህን ሰርዘነዋል አሉኝ፡፡ አሁን “ከሰስፔንሽን” ወደ “ካንስሌሽን” ሄደዋል ማለት ነው፡፡ የዓመት ፈቃዴን ባለፈው ሳምንት ነበር የምጀምረው፣ እሱን ተነጥቄያለሁ እልሻለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ማለት አልፈልግም፡፡

  ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በሬዲዮ ፋና ላይ በነፃው ፕሬስ ዙሪያ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ እርስዎም በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ የውይይቱ ፋይዳ ምንድን ነው ይላሉ?

  እንግዲህ አንድ የሬድዮ ጣቢያ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ ፋይዳውን የሚያውቀው ሬዲዮ ጣቢያው ራሱ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከሰጡን ርዕስ ተነስቼ አንዳንድ ነገሮችን ለመገመት አያዳግተኝም፡፡ ርዕሱ እንግዲህ በኢትዮጵያ ያሉ የነፃው ፕሬስ ጋዜጦችና መፅሄቶች ምን ይመስላሉ? እንዴትስ ሊሻሻሉ ይችላሉ? የሚል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ስመለከተው የግሉን (ነፃውን) ፕሬስ በተጠናከረ ሁኔታ መተቸት ይፈልጋሉ፡፡ ሁለተኛ ከመንግስት ጋር ያልተያያዝን ሰዎች በውይይቱ ብንሳተፍ፣ ትችቱ ይሰምራል የሚል አስተሳሰብም ነበራቸው፡፡ ሌላው እኔን በግሌ ብትጠይቂኝ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጆርናሊዝም እና ኮሚዩኒኬሽን ዲፓርትመንት በቅርቡ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ “በኢትዮጵያ ውስጥ የመናገር ነፃነት (Freedom of Speech) የለም” ብዬ ሽንጤን ገትሬ ተከራክሬ ነበር፡፡ ይህም በዩቲዩብ እና በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች ስለተሰራጨ፣ ለዚህ ምላሽ በመስጠት ያንን የተሰራጨ ሃሳብ ለማምከን እቅድ የነበራቸው ይመስለኛል፡፡ እኔ በሁለት ፕሮግራሞች ላይ ነው የተሳተፍኩት፣ እነሱ ግን ቀደም ብለው የጀመሩት ይመስለኛል፡፡

  ውይይቱ ላይ ተጋብዘው ነው ወይስ በራስዎ ተነሳሽነት?

  የሬድዮ ፋናው አቶ ብሩክ ከበደ ጋብዘውኝ ነው የተገኘሁት፡፡

  በውይይቱ ላይ“ዶ/ር ዳኛቸው ስሜታዊ ሆነው ነበር”የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚል ትችትም ተሰንዝሮቦታል፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

  የስሜታዊነቱን ነገር ያመጡት እንኳን እነሱ ናቸው፡፡ ስድብና ዘለፋውን በመጀመር እነሱ ይቀድማሉ፡፡ “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ለሚለው በእውነቱ በናፍቆት ደረጃ ፍትህ ናፋቂ ነኝ፡፡ዴሞክራሲና የህዝባችንን ነፃነት ናፋቂ ነኝ፡፡ የዱሮ ሥርዓት ናፋቂ የሚሉኝ “አሁን ያለንበት ወርቃማው ጊዜ ነው” የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡ “ያለፈው ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አባባል ሆን ብሎ ሰዎችን ለማሸማቀቅ የተፈጠረ ቃል ነው፡፡ በሌላ መልኩ የአሁኑ ስርዓት እኮ በጣም የተሻለ ነው ለማለት ነው፡፡ እኔ የዛሬ 40 ዓመት ወደ ኋላ ሄጄ ለማወዳደር የፈለግሁት አጠቃላይ ሥርኣቱን ሳይሆን የመናገር ነጻነትን በተመለከተ ርዕስ ብቻ ነበር፡፡ ይህንንም ለመናገር የዕድሜ ባለጸጋም ነኝ፡፡ “ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” በሚባልበት ጊዜ አንድ ዓመት ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለሁ፡፡ ያኔ የተሻለ የመናገር ነፃነት ነበር ብያለሁ፡፡ ይህንን አባባሌን አሁንም እደግመዋለሁ፡፡ “በአፄው ጊዜ የፈለግነውን ለመተቸት የዩኒቨርሲቲው ህግ ይፈቅድልናል፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ መዲና ነበር፡፡ ዛሬ ግን ተነስተሸ አንድ ፖለቲካዊ የሆነ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ አስተያየት ብትሰነዝሪ ከጸጥታ ኃይሉ የሚጠብቅሽ ችግር ይኖራል፡፡” ስላልኩኝ ነው “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የተባልኩት፡፡ ይሄ አይነተኛ የሆነ የካድሬዎች ማስፈራሪያና በነፃነት የሚናገሩ ሰዎችን ማሸማቀቂያ መንገድ ነው፡፡ እኔ እኮ የድሮ ትዝታ አለኝ፣ ልናፍቅም እችላለሁ፡፡

  ለምሳሌ ከድሮው ስርዓት ምን ምን ይናፍቅዎታል?

  ለምሳሌ የእንግሊዝ ፈላስፋ ኤድመን በርክ “Familiarity” የሚል ስለ ትዝታ ያነሳው ሀሳብ አለ፡፡ “ፋሚሊያሪቲ” ምንድነው? መተዋወቅ፣ ያሳለፍነው ትዝታ፣ትውስታ ማለት ሲሆን፤እንደ አርሱ አቀራረብ በአንድ ጉዳይ ላይ ስለተዋወቅን ብቻ መናፈቅ፣ የሰው ልጅ ባህሪና ፀጋ ነው ይላል፡፡ ገባሽ? እኔ የጥንቱን የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ እናፍቃለሁ፣ የፖሊስ ኦርኬስትራንም እንዲሁ፡፡ ዛሬ አንድ ኪቦርድ አስቀምጠው የሚዘፍኑትን ከምሰማ የእነዚያን ኦርኬስትራዎች ሥራ ብሰማ እናፍቃለሁ፡፡ የፈረሱትን የድሮ ሲኒማ ቤቶች— እነ ሲኒማ አድዋን እናፍቃለሁ፡፡ የድሮውን የመድረክ ተውኔት እናፍቃለሁ፡፡ የድሮው የክብር ዘበኛ አለባበስ ከፈረሳቸውና ከነማዕረግ ልብሳቸው ትዝ ሲለኝ እናፍቃለሁ፡፡ እንዴ ብዙ ብዙ የምናፍቀው ነገር አለኝ— እሱን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ በሰፈሬ ሳልፍ አሁን የደረቀው ቀበና ወንዝ ከነሙላቱ ይናፍቀኛል፣ ድሮ ለምሳሌ ሆቴል ገብተን ክትፎ በ75 ሳንቲም “ቅቤ ይጨመር?” እየተባለ የምንበላው ይናፍቀኛ…..እንዴት ያለ ነገር ነው! ድንች በሥጋ ወጥ 15 ሳንቲም የነበረበት ጊዜ ይናፍቀኛል፡፡ የድሮዎቹ አስተማሪዎቼ ይናፍቁኛል፡፡ ታዲያ የድሮውን መናፈቅ ምን ነውር አለው? ምንስ አድርግ ነው የምባለው?

  እርስዎም “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” የሚለው አነጋገር የካድሬ ቋንቋ ነው ብለዋል፡፡ ምን ማለት ነው?

  ካድሬዎች ሁልጊዜ ያለንበት ስርዓት ነው ወርቃማው ይላሉ፡፡ ያለፈው በጠቅላላው አይረባም ባይ ናቸው፡፡ ሲያስተምሯቸውም እንዲህ እንዲያስቡ ነው፡፡ እኔን “የድሮ ስርዓት ናፋቂ” ያለኝም ወጣት በዚያ ስለወጣ ነው፡፡ በጣም ልጅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም በሌላ ፕሮግራም ላይ አግኝቼዋለሁ፡፡ ያን ጊዜ አቦይ ስብሀት ባሉበት በጣም ሀሳባዊ የሆነ፣ የአሁኑን ሥርዓት “ፍየልና ነብር የሚሳሳሙበት” ወርቃማ ጊዜ እንደሆነ አድርጎ ሲያወራ፣ “አንተ ልጅ እስኪ አቦይ ስብሀት ጋር ዝም ብለህ አንድ ሁለት ዓመት አሳልፍ፣ ያኔ ፖለቲካህ መሬት የረገጠ ይሆናል” በማለት መክሬው ነበር፡፡

  በእርሶ እይታ አሁን ያሉት በጣት የሚቆጠሩ የግሉ ፕሬስ ውጤቶች ምን ይመስላሉ?

  እኔ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ማስቀመጥ የፈለግሁት ጉዳይ ምን መሰለሽ? አንደኛ የአንድን አገር የፕሬስ ሁኔታ ለማየት ከፈለግሽ ወደ አወቃቀሩ ነው የምትሄጂው፡፡ አወቃቀሩ አሀዳዊ ነው ወይስ ብዝሀነትን ያስተናገደ ነው የሚለውንም ታያለሽ፡፡ በእኔ እይታ ከአፄ ኃይለሥላሴ እስከ ኮሎኔል መንግስቱና በአሁኑም ስርዓት ስትመጪ አወቃቀሩ አሀዳዊ ነው፣ አንድ ወጥና በአንድ አካል የሚታዘዝ ነው፡፡ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ የሚሰማው ዜና ከአንድ ምንጭ የሚቀዳ ነው፡፡ ሁሉንም በሞኖፖል የያዘ ነው፡፡ ይሄ “Univocal” ይባላል፡፡ “Multivocal” የሚባለው ደግሞ ብዙ ውድድር ያለበት፣ በአማራጭ የተሞላ ዜና እና የዜና ምንጭ ያለበት ነው፡፡ አሜሪካ ስትሄጂ CNN አለ፣ ABC አለ፣ ሌሎችም መዓት የዜና አውታሮች አሉ፡፡ እዚህ ይህ አይነት አማራጭ የለም፣ ይመጋገባሉ እንጂ፡፡

  ይመጋገባሉ ሲሉ እንዴት ነው?

  ለምሳሌ የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያለው ወሬ ነው የሚያወራው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት አወቃቀሩ ተመሳሳይና የሚታዘዘው በአንድ አካል ስለሆነ ነው፡፡ ማንም ሰው ቴሌቪዥን ጣቢያ በግሉ የመክፈት መብትም የለውም፡፡ እንዲህም ሆኖ አሁን ትንሽ ለቀቅ ተደርጎ በጥቂቱም ቢሆን ትችትም እየተፃፈ ነው፣ ይህን አልካድኩም፡፡ “Freedom of speech” እና “Freedom of expression” ይለያል ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡

  እስቲ የሁለቱን ልዩነት ያብራሩልኝ?

  ይኸውልሽ “Freedom of speech” ብዙ ነገርን ያካትታል፡፡ ለምሳሌ የመሰብሰብን፣ ማህበራት የማቋቋም፣ ለተለያየ የመረጃ ነፃነት እድል የማግኘትን (“exposure” የሚለው ይገልፀዋል) —– ያካትታል፡፡ በተለያየ አይነት መንገድ መረጃ ክፍት ሆኖና ተፈቅዶለት እንዲያገኝ እድል የሚሰጥ ነው – “Freedom of speech” ማህበራትን ማቋቋምና የመሰብሰብ ነፃነትም በጣም ጠቃሚ ነገሮች ናቸው፡፡ “Freedom of expression” ደግሞ መናገርን (የአንደበትን) ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ ይሄ ኢትዮጵያ ውስጥ ይፈቀዳል ግን ህዝቡ መረጃ ለማግኘት አማራጮቹ አልሰፉለትም ወይም ህዝቡ ለተለያየ መረጃ “exposed” አይደለም፡፡ ይሄ ነው ልዩነታቸው፡፡ ዋናው ልዩነቱ “Freedom of speech” የሚባለው ነገር ካለ፣ የመረጃ ስብጥሩ ነፃ ነው፡፡ ዜጎች የፈለጉትን መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡

  እስቲ ለ “Freedom of speech” ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ይስጡኝ?

  በጣም ጥሩ! ለምሳሌ የአባይ ግድብን ሁኔታ ውሰጂ ፡፡ መንግስት የግድቡ 30 በመቶ ተሰርቷል አለ፡፡ በቃ! እኛ ይህንን ይዘን ነው ቁጭ ያልነው፡፡ አንቺም ስትፅፊ የሚመለከተው አካል የነገረሽን ነው። አማራጭ የመረጃ ምንጭ ቢኖር እኮ 40 በመቶም 45 በመቶም ሊሆን ይችላል የተሰራው፡፡ አሊያም 15 በመቶም 10 በመቶም ሊሆን ይችላል፡፡ ዜጋው የመንግስት አካል የነገረውን እንጂ ሌላ አያውቅም፡፡ አንድ ግብፃዊ ግን እጅግ በርካታ የሬድዮ፣ የጋዜጣና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስላሉት፣ ስለ አባይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ በብዙ እጥፍ የበለጠና የተሻለ መረጃ የማግኘት እድል አለው፡፡ ይሄ እንግዲህ ነፃ የመረጃ ምንጭ (Freedom of speech) ምን ማለት እንደሆነ ያሳያል፡፡ የፖለቲካ ፈላስፋዎች እንደሚሉት፣ የዜና አውታሩ የመረጃ ምንጩ በሞኖፖል ከተያዘ፣የህዝቡ አንደበት መናገሩ (Freedom of expression) ጥቅም የለውም፣ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውም ይሄው ነው፡፡

  አሁን ያለው ስርዓት (መንግሥት) ራሱ ህግ አውጭ ራሱ ህግ ተርጓሚ ነው፣ ይህ ትክክል አይደለም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው? ህግ አውጭና ተርጓሚው መሆን ያለበትስ ማን ነው?

  ዋነው የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ይሄ ነው። “Separation of Power” የሚለው አስተሳሰብ የመጣው ለአንድ መቶ ዓመት ህግንና ነጻነትን በሚመለከት በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ ነው፡፡ ይህንንም ለመረዳት መካከለኛው ዘመን ወደ ነበረው የሕግና የሥነ-መለኮት ፍልስፍና እንሂድ፡፡ በዚያን ጊዜ “ህግ የሚገኝ እንጂ የሚረቀቅ አይደለም” የሚለው አስተሳሰብ በሰፊው ተንሰራፍቶ ነበር፡፡

  ማነው የሚፅፈው? ማነው የሚያረቅቀው?

  በዚያን ወቅት ከላይ በጥቂቱ እንዳልኩት፣ መንግስት ህግ የሚያገኝ አካል እንጂ አርቃቂ አይደለም ብለው ያምኑ ነበር፡፡

  እኮ ከየት ነው መንግስት ህግ የሚያገኘው?

  ጥሩ ጥያቄ ነው! ከተፈጥሮ ነው ህግ የሚገኘው። ህገ-ተፈጥሮ (Natural Law) ይባላል፡፡ ከዚያ ነው የሚገኘው፡፡ በ15ኛውና በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መንግስት ትልቅ እየሆነ እየተስፋፋ ሲመጣ ህግ ማውጣት ግድ ሆነ፡፡ ሆኖም ግን የተወሰነው የአውሮፓ የማኅበረሰብ ክፍል “በፍፁም ህግ ልታወጡ አትችሉም፡፡ ራሳችሁ ህግ አውጥታችሁ ራሳችሁ ልትዳኙን አትችሉም፣ ነጻነታችን አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ክርክር ተነሳ፡፡

  ከተፈጥሮ በግልፅ ይገኛሉ የሚባሉት ህጎች ምንድናቸው?

  ጥሩ! ሰው መግደል አይፈቀድም – ይሄ ተፈጥሯዊ ህግ ነው፡፡ ሰው የመናገር መብት አለው፡፡ ያጠፋ ሰው ይቀጣል፡፡ የእኛም ፍትሀ-ነገስት ላይ ያሉት እኮ ከተፈጥሮ ህግ የተገኙት ናቸው፡፡ ህገ-ተፈጥሮ ለምሳሌ ወላጅ ልጁን ማሳደግ አለበት፡፡ ልጅ አባቱን አይመታም፡፡ በሰው ልቦና ላይ የተቀረፁ የተፈጥሮ ህጎች እኮ አሉ፡፡ በኋላ የግድ ህግ ማውጣቱ ሲመጣ፣ ህግ አውጭውና ህግ ተርጓሚው ይለያይ ተባለ፡፡ የእነዚህ አካላት መለያየት ግድ የሆነው ከመቶ አመት ጭቅጭቅ በኋላ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳልኩሽ የሴፓሬሽን ኦፍ ፓወር የመጣው ህግ አውጪውንና ህግ ተርጓሚውን በመለየት ለተቃውሞው ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት ማለት ለምሳሌ አበራሽ በአበራሽ ጉዳይ ላይ ራሷ ወሳኝ ናት አይደለችም? ነው ጥያቄው፡፡ መልሱ መሆን የለበትም ነው፡፡ የህግ የበላይነት ማለት ሌላ ሶስተኛ አካል በተነሳው ጉዳይ ላይ ነፃ ሆኖ ይዳኝ ማለት ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው ይዳኙ ነበር። ደርግ በራሱ ጉዳይ ላይ ይዳኝ ነበር፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፣አሁን ኢህአዴግ በራሱ ጉዳይ ላይ ይዳኛል ወይንስ አይዳኝም ብለሽ ብትጠይቂ፤ በእኔ እምነት ይዳኛል፣ ይህ ደግሞ ትክክል አይደለም። ህጉን ተመርኩዞ ነፃ ሆኖ የሚዳኝ ዳኛ የለንም እያልኩሽ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጋዜጦችንና ሚዲያውን እንደያዘ ሁሉ፣ፍርድ ቤቶችንም ወጥሮ ይዟል፡፡

  ፍርድ ቤቶቹ ነፃ አይደሉም እያሉኝ ነው?

  ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነፃ ሆነው እየሰሩ አይደለም፡፡ ትቀልጃለሽ እንዴ? ከብርቱካን ሚዴቅሳ ወዲህ በዚህች አገር ፍ/ቤት ላይ ማን ነፃ ሆኖ ትክክለኛ ፍትህ ሰጠና ነው፡፡

  እስቲ ለዚህ ስጋት እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት ካለ ይግለፁልኝ?

  ለዚህ ማሳያ ላቅርብልሽ —- የፀረ – ሽብር ህጉን 90 በመቶውን ያመጣነው ከውጭ ቀድተን ነው ይላሉ፡፡

  ከውጭ መቀዳቱ ምን ክፋት አለው ይላሉ?

  ክፋት አለው ያልኩት እኮ እኔ አይደለሁም! እነሱው የቀዱባቸው አሜሪካኖችና እንግሊዞች ልክ አይደላችሁም በሚል ወጥረው ይዘዋቸዋል፡፡ ለምን ይመስልሻል? ዋናው ነገር ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ የእነሱ ህግ በጣም ስለሚያምር ለጥቁር አይገባውም ብለው ይመስልሻል? አይደለም! “በአገራችሁ ነፃ የሆነ ዳኝነት ስለሌለ ሰው ይጎዳል፣ መጠበቂያ የሌለው ጠብመንጃ ነው” ነው ያሏቸው፡፡ “እኛ እኮ ይህን ህግ ያወጣነው መጠበቂያ ስላለን ነው፡፡ ነፃ ዳኝነት በሌለበት ይህን ህግ እንዴት ሥራ ላይ ታውላላችሁ” ነው ያሏቸው፡፡ ማሳያዬ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ማሳያ ትፈልጊያለሽ እንዴ?

  ዶ/ር ዳኛቸው “መንግስትና ዩኒቨርሲቲውን ይዘልፋሉ፡፡ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው እያስተማሩ ደሞዝ ያገኛሉ”የሚል ትችት የሚሰነዝሩ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

  ይሄ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው! ይገርምሻል እዚህ አስተሳሰብ ላይም ችግር አለ፡፡ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በሚል ርዕስ የዛሬ መቶ ዓመት በገ/ ህይወት ባይከዳኝ የተፃፈ መፅሀፍ አለ፡፡ ፀሐፊው ለአፄ ምኒልክ ምክር ያቀረቡበት አለ፡፡ በመንግስት ላይ አንድ ግድፈት ያየሁት የመንግስት እና የንጉሱ ንብረት ያልተለየ መሆኑ ላይ ነው ብለዋል – ገ/ህይወት ባይከዳኝ፡፡ የደጃዝማቾቹ ንብረትና የአገሬው ህዝብ ንብረት በትክክል መለየት አለበት ነው ያሉት፡፡ እነዚህ ደጃዝማቾችና ሌሎች ሹማምንት በደሞዝ መተዳደር አለባቸው ብለዋል፡፡ የመንግስት ንብረትና የንጉሡ ንብረት መለየት አለበት እኔ አሁንም የምፈራው፣ የፓርቲ ንብረትና የህዝቡ ንብረት አልተለየም ብዬ ነው፡፡ ኢህአዴጎቹ እኛ ቀጥረነው እኛው ስራ ሰጥተነው ይላሉ፡፡

  አንድ ነገር ልንገርሽ – አፄ ኃይለ ሥላሴና ራስ ካሳ ከዝምድናቸው ባሻገር የቅርብ ወዳጆች ናቸው፡፡ ቀልድ ይቀላለዳሉ፡፡ ሁለት ታሪክ ነው የማወራሽ። በጅሮንድ ተክለ ሐዋሪያት ተክለማሪያም ከተፈሪ ጋር ተጣልተው ራስ ካሳ ጋር ይሄዱና “ስራ ስጡኝ” ይሏቸዋል፡፡ ራስ ካሳ ግን “አንተ የተፈሪ አሽከር ስለሆንክ ስራ አልሰጥህም” ይሏቸዋል፡፡ ራስ ካሳ “እርሶ ምን ነካዎት? እኔ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰራተኛ እንጂ የተፈሪ አሽከር አይደለሁም” ይላሉ ተ/ሐዋሪያት፡፡ “እኔ አሁን ስራ ለቅቄያለሁ– ለምንስ አሽከር ይሉኛል” ሲሉ ራስ ካሳን ይሞግታሉ፡፡ አየሽ መንግሥትና ንጉሥን ራስ ካሣ መለየት አልቻሉም። ኢህአዴጎችም ከዚህ አስተሳሰብ ስላልተላቀቁ ነው “እኛ ስራ ሰጥተነው፣ እኛ ቤት ሰጥተነው፣ እኛ ደሞዝ እየከፈልነው እኛኑ ይሳደባል ይዘልፋል” የሚሉት፡፡ እኔ ግን ስራ የሰጠችኝ አገሬ ኢትዮጵያ እንጂ እነሱ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ “እስከዛሬ በክፉና በደግ ጊዜ ሳናይህ እንዴት መጣህ አላለችም፣ እንኳን ደህና መጣህልኝ ልጄ” ብላ ነው ስራ የሰጠችኝ፤ይህንን አስረግጬ እነግርሻለሁ፡፡ ስለዚህ ስራ የሰጠኝና ደሞዝ የሚከፍለኝ ማን እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

  ከዚህ ቀደም ዶ/ር ዳኛቸው የብአዴን አባል ናቸው የሚል ነገር ተወርቶ በነበረበት ጊዜ ስጠይቅዎት “እንኳን የብአዴን የምወደው የኢህአፓ አባልም አልሆንኩም የየትኛውም ፓርቲ አባል የማልሆነው በአካዳሚክ ስራዬ ላይ ነፃነት እንዳላጣ ነው” ብለውኝ ነበር፡፡ ያስታውሳሉ?

  በደንብ አስታውሳለሁ እንጂ!

  ታዲያ በአሁኑ ወቅት በየፖለቲካ መድረኮቹ ላይ ፅሁፍ ያቀርባሉ፣ ትችቶችን ይሰነዝራሉ፡፡ ይሄ ነገር በስራዎ ላይስ ተፅዕኖ የለውም?

  በጣም ጥሩ! ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ጋር በፍፁም ግንኙነት የለውም፡፡ በአካዳሚክ ስራዬም ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም፡፡ እንዴት የሚል ጥያቄ ካነሳሽ ደግሞ፤ እኔ እንደ አንድ ሲቪል ግለሰብ ነው እየተቸሁ ያለሁት፡፡ ሁለት አይነት ምክንያታዊነት አለ- አንደኛው ግለሰባዊ ምክንያታዊነት ይባላል፤ ሁለተኛው ደግሞ ማኅበረሰባዊ ምክንያታዊነት (public reason) ይባላል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማህበረሰባዊ ምክንያታዊነቴን ተጠቅሜም እየተቸሁ ነው፡፡ ሁለቱ አብረው ይሄዳሉ፡፡ እንደግለሰብ ደግሞ እያስተማርኩ ነው፡፡ በሙያዬም እያገለገልኩ ነው ማለት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በፍፁም አይጋጩም፡፡ ምናልባት ሊጋጭ የሚችለው የፓርቲ አባል የሆንኩ እንደሆነ ነው፡፡

  የፓርቲ አባል ቢሆኑ የአካዳሚክ ስራውና የፓርቲ አባልነቱ የሚጋጩበትን መንገድ ሊገልፁልኝ ይችላሉ?

  ማስተማርም ሆነ የፖለቲካ ስራ የሙሉ ሰዓት ስራ እንጂ የትርፍ ጊዜ ስራ ስላልሆኑ ሁለቱም ራሳቸውን ችለው መሰራት ያለባቸው ነገሮች ናቸው፤ ይጋጫሉ የምልሽ፡፡

  ግን እኮ እንደ እርሶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲ የሚስተምሩ ሌሎች ምሁራን በአንድ በኩል እያስተማሩ ወዲህ ደግሞ ፓርቲ እየመሩ ነው፡፡ እንዴት ያዩታል?

  እኔ በዚህ በፍፁም አልስማማም! ይሄ የራሴ አቋም ነው፡፡ በእኔ እምነት እነዚህን ስራዎች በአንዴ ስትሰሪ ከሁለቱ አንዱ ይጎዳል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ከበደችና ዘነበችን በአንዴ እወዳለሁ የሚለው ጉዳይ የማያስኬድ ፍልስፍና ነው፡፡ ከከበደችና ከዘነበች በጣም የምወደውን መምረጥ አለብኝ፡፡ አለበለዚያ አንዷን መጉዳቴ ግልፅ ነው፡፡ ይሄ ማለት ወይ ትምህርቱ አሊያም ፖለቲካው ጉዳት ይደርስበታል ማለት ነው፡፡ ይህ የእኔ እምነት ነው። በበኩሌ በዩኒቨርሲቲው ለመቆየት ካልቻልኩ ወደ አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ እቀላቀላለሁ፡፡ እያስተማርኩ ግን የየትኛውም ፓርቲ አባል መሆን አልፈልግም፡፡

  በአንድ ወቅት ለሰማያዊ ፓርቲ ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት ከአንድ የጋዜጣ አዘጋጅ ጋር ተጋጭተው ስለነበር የዛ ጋዜጣ መቅረፀ ድምፅ ካልተነሳ ንግግር አላደርግም ማለትዎን ብዙዎች አልወደዱትም፡፡ ዶ/ሩ ምሁር ሆነው ቂምን ለትውልድ ያስተምራሉ በሚል ተተችተዋልና ምን ይላሉ?

  አንድና አንድ ነገር ልንገርሽ፡፡ አንድ ሰው ድምፄን አልቀዳም የማለት መብት አለው፡፡ ምሳሌ ልጥቀስልሽ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል በቅርቡ 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር፤ ፕሮፌሰር ባህሩ ድምጽ መቅረጽ አትችሉም ብለው መቅረፀ-ድምፅ አስነስተዋል፡፡
  እንደዚህ ኣይነት በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ የእኔ ምን አዲስ ነገር አለውና ነው? እኔ በጎን እኮ አይደለም ይሄ ጋዜጣ እየሰደበኝ ስለሆነ መቀዳት አልፈልግም ያልኩት፡፡ ማንስ ቢሆን መሰደብ ይፈልጋል እንዴ፡፡ አሁን ያልኩሽ ጋዜጣ ወደፊትም ሊቀዳኝ አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች በዚህ ነገር ደስተኛ አይደሉም ላልሽው፤ እኔ እንዳንቺ እርግጠኛ ሆኜ ባልናገርም፤ ጓደኞቼ እንደነገሩኝ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አስተያየት ሰጪዎች በማህበረሰብ ሚዲያው በሰጡት አስተያየት፤ በዚህ ጋዜጣ ያለመቀዳት መብት እንዳለኝ ብቻ ሳይሆን ዘለፋቸው ከመስመር የወጣ መሆኑንም መስክረዋል፡፡ ቂም ለምትይው ቂመኛ አይደለሁም፡፡

  እኔ እስከምረዳው ድረስ አንድ ሰው፤ በማስታወስና በቂም መካከል ያለውን ልዩነት በቅጡ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ በመሆኑም ማስታወስ ማለት ማቄም ማለት አይደለም፡፡ ስድስት ወርና አንድ ዓመት ያልሞላውን ጉዳይ ማስታወስህ ቂመኛ ያደርግሀል የሚለው አገላለጽ አግባብ አይደለም። አልቀበለውምም፡፡ ከዚህ በፊትም እንዳልኩት ሰዎች እንደዚህ ነህ፤ እንደዚያ ነህ ባሉኝ ቁጥር ራሴን ለመከላከል ምላሽ መስጠቱ ተገቢነቱን አላምንበትም፡፡

  አዲስ አድማስ ሚያዚያ 11 ቀን 2006 ዓ.ም

ከውጭ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ለመሥራት መቸገራቸውን ገለጹ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአገር ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የሙያ ዘርፎች ከተሰማሩ ተመላሽ የዳያስፖራ አባላት ጋር ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ፣ ከ500 በላይ የዳያስፖራ አባላት ተገኝተው ችግሮቻቸውንና ምሬታቸውን ለመንግሥት አሰምተዋል፡፡

ethiopian-diaspora

በሆቴልና ቱሪዝም፣ በንግድ፣ በማዕድን ፍለጋ ሥራና በትራንስፖርትና ማሽነሪዎች ኪራይ ላይ የተሰማሩ ከውጭ ተመላሽ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተሳተፉበት በዚህ ውይይት መድረክ ላይ፣ በተለይ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር ሊያሠራቸው አለመቻሉን አስታውቀው፣ ፈቃድ ለማግኘት እስከ ሁለት ዓመትና አንዳንዶቹም ከዚያ በላይ እንደወሰደባቸው ተናግረዋል፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት በጐንደር ከተማ መሬት መውሰዳቸውን፣ የሆቴሉ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የአፈርና የዲዛይን ጥናት በውጭ ባለሙያዎች ለማሠራት ውጭ አገር ደርሰው ሲመለሱ መሬታቸው በአካባቢው አስተዳደር መወረሱን፣ አንድ ከአሜሪካ የተመለሱ ኢትዮጵያዊ ተናግረዋል፡፡

‹‹መሬቱን የወሰድከው በተጭበረበረ ዶክመንት ነው፡፡ ፎርጅድ ነው፡፡ አንተ ዳያስፖራ አይደለህም፡፡ እንዲያውም የሠራኸው ወንጀል በመሆኑ በሕግ ከመጠየቅህ በፊት ውጣ፤›› ብለው የአካባቢው የሥራ ኃላፊዎች ከቢሮ እንዳስወጧቸው እኚሁ ግለሰብ በምሬት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሰላሳ ዓመት ከኖርኩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተመለስኩት ፎርጅድ ልሠራ ነው?›› በማለት መንግሥት እንዲፈርዳቸው ግለሰቡ ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ ያልሄዱበት እንደሌለና በፍርድ ቤት ፍትሕ ለማግኘት ያደረጉት ጥረትም አለመሳካቱን የተናገሩት እኚህ ግለሰብ፣ ‹‹ወደነበርኩበት የሰው አገር ለመመለስ እየተሰናዳሁ ባለሁበት ወቅት ይህ ውይይት ተዘጋጅቷልና መፍትሔ ካገኘሁ ብዬ ነው የተገኘሁት፤›› በማለት የመንግሥትን ምላሽ ጠይቀዋል፡፡

ይህ መሰሉ አጋጣሚ ወይም መልኩን የቀየረ ሌላ ችግር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ተመልሰው ከመሥራት ይልቅ፣ አገራቸውን እየወቀሱ በሰው አገር መቅረትን እንዲመረጡ እያስገደዳቸው መሆኑ በተለያየ አጋጣሚ የተገለጸ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በተጠራው የውይይት መድረክ ላይ የተነሳውም ተመሳሳይ ከመሆኑም በላይ፣ ሁሉንም ችግሮች ችለው በአገራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙትን ጭምር እየነካ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የገለጹ ሌላ አንድ በአውሮፓ ይኖሩ የነበሩ የሕክምና ባለሙያ፣ አገራቸው ከገቡ በኋላ በምግብ ይዘት የበለፀጉ እንክብሎችን በኔትወርክ ማርኬቲንግ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሺሕ በላይ ሠራተኞች በሥራቸው እንደሚገኙና ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መመርያዎች ከንግድ ሥራቸው እንዳስተጓጐላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንግሥት መመርያ የሚያወጣው ለማስተዳደር እንጂ ማነቆ ለመፍጠር ለምን ይሆናል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹መንግሥት ያሉትን ችግሮች ለይቶ ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ ውይይቶች ዋጋ የላቸውም፡፡ ዳያስፖራውም የኢትዮጵያ አንድ አካል በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ይሰጠው፤›› ሲሉ ተወያዮቹ ጠይቀዋል፡፡

በተለያዩ የዓለም አገሮች ከ2.5 እስከ ሦስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል፡፡

አሁን በሥልጣን ያለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከተቋቋመ ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን 2,947 ብቻ ነው፡፡ በውጭ ይኖራሉ ተብሎ ከሚገመተው አንፃር በአገሪቱ ላለፉት 20 ዓመታት 2,947 የዳያስፖራ አባላት ብቻ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸው፣ መንግሥት ለዚህ ዕምቅ ሀብት የሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ለመረዳት እንደሚችል የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ወደ ሥራ የገቡ የዳያስፖራ አባላት ሦስት ሺሕ አይሙሉ እንጂ፣ 22.3 ቢሊዮን ብር ኢንቨስት በማድረግ 125,600 ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ቢሰጥ ሊፈጠር የሚችለውን ለውጥ የሚያሳይ ነው ይባላል፡፡