Archive | May 3, 2014

ግብፅ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ የሚከታተል ሳተላይት ማምጠቋን ገለፀች

ግብጽ 43 ሚሊዮን ዶላር ያወጣችበትንና የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የግንባታ ሂደት በአየር ላይ ሆኖ እየተከታተለ መረጃ የሚሰጣትን ወታደራዊ ሳተላይት ከሁለት ሳምንት በፊት ማምጠቋን በይፋ እንደገለፀች   አህራም ኦንላይን ዘገበ፡፡

Gibets

ኢጂሳት የሚል ስያሜ የተሰጠው ሳተላይቱ፤ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቁመት፣ ውሃ የመያዝ አቅምና የሚለቀውን የውሃ መጠን የተመለከቱ መረጃዎችን እየተከታተለ የሚያቀርብ እንደሆነ የገለጹት የግብጽ ብሄራዊ የሪሞት ሴንሲንግና ስፔስ ሳይንስስ ባለስልጣን ምክትል ፕሬዚደንት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ሳተላይቱ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከሚከናወንበት አካባቢ በተጨማሪ፣ የአባይ ወንዝ በሚፈስባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በማተኮር፣ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ጠቃሚ ፎቶግራፎችን እያነሳ እንደሚልክ  ሰሞኑን በካይሮ በተካሄደ ሴሚናር ላይ ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ወራት ከሚቆይ የሙከራ ጊዜ በኋላ፣ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ላይ መደበኛ ስራውን ይጀምራል የተባለው  ሳተላይቱ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከታተለ ለግብጽ ባለስልጣናት መረጃ ከማቀበል ባለፈ፤ የኮንጎ ወንዝን ተፋሰስ በመከተል በሚያነሳቸው ፎቶግራፎች፣ ወንዙን ከአባይ ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተረቀቀውን የፕሮጀክት ሃሳብ ውጤታማነት በተመለከተ የራሱን ፍተሻ ያደርጋል ተብሏል፡፡ የግብጽ መንግስት ሳተላይቱ ከሚያቀርባቸው መረጃዎች የሚያገኘው ውጤት፣ ከኢትዮጵያ ጋር በግድቡ ዙሪያ የጀመረው ክርክር ተጠናክሮ እንዲገፋ እንደሚያደርገው ያምናል ያሉት አላ ኤልዲን ኤል ናህሪ፣ ግድቡን ከታለመለት የሃይል ማመንጨት ስራ ውጭ ለማዋል በኢትዮጵያ በኩል ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ቢደረጉና ጉዳዩ ወደ አለማቀፍ ግልግል የሚያመራ ከሆነም፣ የግብጽ መንግስት ይሄንኑ የሳተላይት መረጃ ለክርክሩ የህግ ድጋፍ ለማግኘት እንደሚጠቀምበት አል አህራም ለተባለው  ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

አል አረቢያ ድረ-ገጽ በበኩሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ግብጽ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የምታነሳቸውን ቅሬታዎች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለማቅረብ ከወሰነች፣ ኢትዮጵያ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗን ባለፈው ሳምንት መናገራቸውን ዘግቧል፡፡
የግድቡ መገንባት የአባይን ወንዝ የውሃ መጠን በመቀነስ ተጎጂ ያደርገናል በሚል ተቃውሞአቸውን በተደጋጋሚ የገለፁት የግብጽ ባለስልጣናት፣ ሳተላይቱ የሚሰጣቸውን መረጃ መሰረት በማድረግ የሚደርሱበት ውጤት፣ በግድቡ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርጉት ክርክር ይዘውት የቆዩትን አቋም እንደሚያጠናክርላቸው ተስፋ ማድረጋቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡ የግብጽን ሳተላይት ማምጠቅ በተመለከተ፣ አንዳንድ ድረገጾች ቀደም ብለው መረጃ ያወጡ ቢሆንም፣ የአገሪቱ መንግስት ስለጉዳዩ ይፋዊ መግለጫ ሲሰጥና ድርጊቱን ሲያምን የአሁኑ የመጀመሪያው  ነው፡፡

Source/www.addisadmas.com

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አንድነት የጠራውን የሰላማዊ ሰልፍ እንደሚቀላቀሉ አስታወቁ

በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው የሰነበቱትና ቀሪዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶች ዛሬ ባደረጉት ሳምንታዊ የወጣቶች የውይይት ፕሮግራም አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) የ‹‹እሪታ ቀን›› በሚል የጠራውን ሰልፍ በግንባር ቀደምነት በመቀላቀል ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ አስታውቀዋል፡፡

Udj

ወጣቶቹ ሰልፉን እንደሚቀላቀሉ ያስታወቁት ‹‹ሰላማዊ ሰልፉ ውጤታማ እንዲሆን በምን መልኩ ልናግዝ እንችላለን?›› በሚል አጀንዳ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከውህደት በዘለለ በሰላማዊ ሰልፍም ሆነ በሌሎች የትግል ስልቶች መተባበርና አብሮ መስራት እደግፋለሁ የሚል አቋም እንደሚያራምድ በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን ወጣቶቹ በሰላማዊ ሰልፉ የሚያደርጉት ተሳትፎ ፓርቲው ለትብብር ያለውን አቋም ያሳያል ብለዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለሰላማዊ ፓርቲው ድምቀት የሚያገለግሉ ሜጋ ፎኖች፣ ጥሩምባዎችና ሌሎችም ሰልፉን ለማድመቅ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ይዘው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

‪#‎UDJ‬ ‪#‎BlueParty‬ ‪#‎AddisAbeba‬

ህመሙ የጋራ ሀመም ነው ጩኸቱም የሁላችንም ጩኸት ነው (የአቋም መግለጫ እና ምክር ብጤ!)

(Abe Tokichawበአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ እያሰማ ነው። መንግስትም በበኩሉ የፈሪ ዱላውን እያወረደው ይገኛል። እውነቱን ለመናገር መፍራት ተቃወሞ የሚያመጣ ተግባር ሲፈጽሙ ነበር እንጂ ተቃውሞውን አለነበረም።

ኢህአዴግዬ በክላሿ ተማምና ያላስቀየመችው የህብረተሰብ ክፍል ካለ እርሱ ኢህአዴግን እንደ ግል አዳኙ የተቀበለ ብቻ ነው። ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላየ እየተወሰደ ያለው ርምጃ በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል ጎንደርም እየተወሰደ ይገኛል ይሄው አይነት ከዚህ በፊት በጋምቤላ፣ በአዲሳባ፣ በደቡብ ብሄር በሄረሰቦች ክልል ሀዋሳ እና ተረጫ ወረዳ ላይ እንዲሁም በቅርብ ጊዜ በሀረሪ ከልል ሀረር ላይ ሲወሰድ ነበር። (እነዚህ በቀላሉ ያስታወስኳቸው ናቸው ማስታወሻ ብናገላብጥ ደግሞ ሌላም ሌላም ይገኛል)

dire 2

በጥቅሉ እነደ ኢህአዴግ ያሉ ”ፋራ” አምባገነኖች ለሰላማዊ ተቃወሞ ሰላማዊ ምላሽ ሲሰጡ ታይቶም አይታወቅ። እኛ የምንጸለይ የነበረው ኢህአዴግ ገደላውን ትታ የምትጠየቀውን እንደ ዘመናዊ ገዢ ፓርቲ፤ በቅጡ ብትመልስ ነበር። ግን አልሆነም። በዚህም የተነሳ እስከ አሁንም ድረስ በኦሮሚያ ክልል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ዜጎች በአልሞ ተኳሾች እና ሳያልሙ ተኳሾች ተገድለዋል ቆስለዋልም።

ይህ ህመም የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች እና ዘመዶቻቸው ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን ነው። ሰለዚህም ሁሉም በያለበት እና በየ አቀሙ ጩኸቱን ሊቀባበል ይገባል የምለው።

“አንተ ውጪ ቁጭ ብለህ….”

ወጪ ሀገር የሚገኝ ሰው የሚገጠመው ትልቁ ፈተና ይሄኔ ነው። ጩኸቱ የጋራ ነው ብዬ ስናገር አንዳንድ ወዳጆች ገና አንብበው ሳይጨረሱት ሁላ “አንተ ውጪ ቁጭ ብለህ እኛን ልታስጭርስ” የሚል አስተያየት ለመጻፍ ሲያቆበቁቡ ይታየኛል። በተወሰነ ደረጃ እወነትም ውጪ ሃገር የሚገኝ ሰው “አይዟችሁ አትፍሩ በረቱ…” ብሎ ለማለት የሞራል የበላይነት እንደሌለው አምናለሁ።

ስለዚህም አትፍሩ ብዬ አልመክርም። ነገር ግን እየፈራንም ቢሆን፤ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ጩኸቱ የጋራችን እንደሆእነ ልናሳይ ይገባል፤ ይሄ ማለት የግድ አደባባይ ውጡ ብሎ ማደፋፍር አይደለም። ቢያንስ ግን ከገዳዮቹ ጋር ባለመተባበር ጩኸቱ እና ኡኡታው የእኛም መሆኑን ማሳየት እንችላለን ለማለት ነው።

በተጨማሪም በተለያዩ ሰለፎቻችን ላይ፤ ለምሳሌ ነገ በሚካሄደው የአንደነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ የእሪታ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ከሚያሰማቸው እሪታዎች አንዱ በኦሮሚያ እንዲሁም በአማራ ክልል ጎንደር ላይ እየተደረገ ያለውን የሰላማዊ ዜጎች ጭፈጨፋ የሚያወግዝ ሊሆን ይገባዋል የሚል እምነቴን ለማካፈልም ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በጎንደርም ሆነ በኦሮሚያ አካባቢዎች እየተደረገ ያለውን ግድያ በሶሻል ሚዲያዎቻችን እና ባገኘነው አጋታሚ በማሰራጨት ጩኸቱ የጋራችን መሆኑን እናሳይ ለማለትም ነው። ምክንያቱም አንድም ዛሬ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየደረሰ ያለው ትላንት ብብዙዎች ላይ ደርሷል፤ ነገም በእያንዳንዳችን እንደማይደርስ ዋስትና የለንምና ነው!

በመጨረሻም

ህይወታችውን ላጡ ነፍስ ይማርልን!
ለቆሰሉት ምሀረትን ይስጥልን!
የሚገድሉትንም ክላሻቸውን ያክሽፍልን!

አሜን!

ኦሮሚያ ካለቀሰች በኋላ – ህዝብ ሃሳቡን ሊጠየቅ ነው

የኢህአዴግ ቴሌቪዥን የቅስቀሳ ዘመቻ ጀመረ

በአምቦ ህዝብ አዝኗል። የሟቾች ቁጥር ከ22 በላይ እንደሆነ ይገመታል። በድፍን ኦሮሚያ ከ36 ሰዎች በላይ ተገድለዋል የሚሉ መረጃዎች አሉ። ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ 11 ሰዎች መሞታቸውን አምኗል። ታዛቢዎች እንደሚሉት ኦሮሚያ እያነባች ነው። ህዝብ ለቅሶ ከተቀመጠ በኋላ ኢህአዴግ በቴሌቪዥን ቅስቀሳ ጀመረ።

አርብ ሚያዚያ 24፤2006 (2/05/2014) ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በትዊተር ባሰራጩት መረጃ በጉዳዩ ዙሪያ ህዝብ ሃሳቡን እንደሚጠየቅ አመላክተዋል። የዚሁ መነሻ እንደሆነ የተነገረለት የቅስቀሳ ዘመቻ ዛሬ በቴሌቪዥን ተላልፏል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ኩማ የድንበር ጉዳይ እንደማይነሳ በመጥቀስ ተቃዋሚዎችን ወቅሰዋል።

ኦሮሚያን ልዩ ዞን ከአዲስ አበባ ጋር ያዋሀደው አዲሱ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንዲሆን እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ በክልሉ ከተካሄዱት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች የአምቦው በጉልህነቱ ይጠቀሳል። አምቦ ነዋሪው ግልብጥ ብሎ በመውጣት ተማሪዎችን ተቀላቅሏል። ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ “… በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ሁከት ወደ ከተማ በመዝለቁ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በአምቦና ቶኬኩታዮ ከተሞች የሰባት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ባንኩን ጨምሮ በበርካታ የመንግስትና የሀዝብንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል” በማለት ግድያውን ከንብረት ውድመት ጋር ለማያያዝ ሞክሯል። በመደ ወላቡ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን፣ በሌላም በኩል “በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሰላም የእግርኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ ወደ70 ያህል ተማሪዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል” ሲል በህይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት አስታውቋል።

Ambo 4

ኢህአዴግ የሟችና የቁስለኞችን ቁጥር ዝቅ ቢያደርግም የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ኦ.ፌ.ኮን በመጥቀስ እንደዘገበው በአምቦ ለተገደሉት 17 ሰዎች ኢህአዴግን ተጠያቂ አደርጓል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ባወጣው መግለጫ ደግሞ አመጹን ከኋላ ሆነው የመሩትን የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል። ክልሉ በመግለጫው ህይወታቸው ስላለፈ ዜጎች ያለው ነገር ስለመኖሩ የኢህአዴግ ቴሌቪዥን ያለው ነገር የለም። ግድያው ስለተፈጸመበት አግባብ የማጣራት ስራ እንደሚከናወን እንኳን አልጠቆመም።

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትና የጎልጉል የኦሮሚያ ምንጮች እንዳሉት በሰሞኑ ተቃውሞ ከ36 ሰዎች በላይ ተገድለዋል። የሲኤንኤን አይ ሪፖረተር በአምቦ ብቻ 30 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን አመልክቷል። ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ታስረዋል። የቁስለኞች ቁጥርም ቀላል አይደለም። በዚሁ ሳቢያ የህዝብ ስሜት በቁጭት የተሞላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የክልሉ ምክር ቤት ግን ህዝብ ከጎኑ መቆሙን በመጥቀስ ምስጋናውን አቅርቧል።

በአምቦ ከደረሰው ሰብአዊ ጉዳት በመቀጠል በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ወረወረው በተባለ ቦንብ አንድ ሰው መሞቱና 70 መቁሰላቸው አስደንጋጭ ዜና ሆኗል። ቦንቡን ማን ጣለው፣ ከየት መጣ? ማን፣ ለምን ዓላማ ተማሪዎች ላይ ቦንብ መወርወር ፈለገ? ተማሪዎችን መጨረስ ከፈለገ ከተጠቀሰው በላይ ጉዳት እንዳያደርስ ማን ከለከለው? የሚሉትና ተመሳሳይ ጥያቄዎች እየተሰነዘሩ ነው። ምን አልባትም የተቀነባበረ ድራማ ሊሆን አንደሚችልና ጉዳዩን ከብሄር ጋር የማገናኘት ዓላማ ያለው እንደሚሆን እየተሰማ ነው።

ኢህአዴግ በቴሌቪዥን ባሰራጨው የቅስቀሳ ፕሮግራም “ኦሮሚያ መሬት ተቆርሶ ለአዲስ አበባ እንደማይሰጥ፣ ክልሉ ካልፈቀደ የሚሆን ነገር እንደሌለ፣ ክልሉ ቢፈቅድ እንኳን እንደ ቀድሞው ልዩ ዞኑ ውስጥ ያሉት ወረዳዎች በኦሮሚያ ስር እንደሚተዳደሩ፣ የመሬት ቆረሳው ተራ የጠላት ወሬና ፕሮፓጋንዳ” እንደሆነ አቶ ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ የተለያዩ ሃላፊዎች ሲናገሩ አሰምቷል።

በዚሁ የፕሮፓጋንዳ ስርጭት “የክልሎች ማንዴት በህገመንግሰት የታሰረ ዋስትና አለው” በማለት የኦህዴድ ሰዎች ሲናገሩ ታይተዋል። ስርጭቱ አዲስ አበባና የልዩ ዞኑ ከተሞች በተቀናጀ ልማት ተሳስረው “ሲያብቡ” የሚያሳይ ዲዛይን በተደጋጋሚ በማቅረብ “ለዚህ ልማት እንረባረብ” የሚል ጥሪ አሰምቷል።

ቪኦኤና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ እንደዘገቡት የኦሮሚያ ፌዴራል ኮንግረንስ ድርጊቱን ክፉኛ መቃወሙንና ለደረሰው የህይወት ኪሳራ ኢህአዴግ ተጠያቂ አድርጓል። በልማት ስም ከድሃ አርሶ አደሮች ላይ የሚወሰደው መሬት “የመሬት ቅርምት” ስለሆነ ባስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል። ክልሎች ህገ መንግስታዊ መብትም ሳይሸራረፍ እንዲከበር አሳስበዋል።

በተያያዘ ዜና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ በሚወጡ ሰልፈኞች ላይ ፍጹም የሃይል ርምጃ እንዲወስዱ የታዘዙ የጸጥታ ሃይሎች ርምጃቸውን እንዲያለዝቡ መታዘዙ ታውቃል። በተወሰደው የሃይል ርምጃ ህዝብ ክፉኛ በመቆጣቱ የሚወሰዱ ርምጃዎች እንዲላዘቡ መታዘዙን ተከትሎ በዛሬው እለት አንዳንድ ከተሞች ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸው በሰላም መበተናቸውቸው ሰምቷል። ቪኦኤ እንዳሰማው የድምጽ መረጃ “የነፍጠኞች ሃውልት ይፍረስ” የሚለው ጥያቄ አሁንም እየተስተጋባ ነው።

የኦፌኮው አቶ ገብሩ ገ/ማርያም እንዳሉት አማራውንና ኦሮሞውን ለማጫረስ እየተከናወነ ያለ ሴራ አለ። ለረዥም ዓመታት አብሮ የኖረን ህዝብ ለማናከስ የሚደረገውን ሴራ ድርጅታቸው እንደማይቀበለውም አመላክተዋል። ከዚሁ ነፍጠኛን ከማውገዝ ጋር በተያያዘ “የአዲስ አበባን መስፋፋትና ነፍጠኛነትን ምን አገናኛቸው?” በማለት የሚጠይቁ፣ “ያረጀውን የነፍጥ ታሪክ ከማውራት አሁን ነፍጥ አንስቶ ጥቃት እየፈጸመ ስላለው ህወሃት የሚባለው የአንጋች ቡድን መነጋገር አይሻልም ወይ” ሲሉ ይደመጣሉ። (ፎቶዎቹ ከፌስቡክ የተወሰዱ ናቸው – የየትኛውም ኢትዮጵያዊት እናት ለቅሶ የሁሉም መሆኑን እንዲያሳይ የተጠቀምንበት ነው)

http://www.goolgule.com/after-sheding-blood-eprdf-is-requesting-public-opinion/