Archive | May 13, 2014

ተቃውሞ እና ጭፍጨፋ በኦሮሚያ

(ተመስገን ደሳለኝ)

Ambo

ዕለተ-ሐሙስ፤ ሚያዚያ 23 ቀን 2006 ዓ.ም የታሪካዊቷ አምቦ ከተማ ጀንበር አዘቅዝቃ ሰማዩ መቅላት ሲጀምር፣ ከወትሮው ለየት ያለ ጉዳይ በሰደድ እሳት ፍጥነት ጠቅላላ የዩንቨርስቲ ግቢውን አዳርሶ ተማሪውን ከባድ ሃሳብ ላይ ጣለው፡፡ ሌሊቱ ዕኩሌታ ላይ የግቢው ኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪ በሙሉ ስለጉዳዩ መረጃው እንደደረሰው ያረጋገጡ ጥቂት አስተባባሪዎች በተረፈችዋ ሰዓት ቢያንስ ጎናቸውን ለማሳረፍ ወደየመኝታቸው ሲያዘግሙ ተስተዋሉ፡፡ …ነገስ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን? አንዳቸውም ይህን አስቀድመው የማወቅ መለኮታዊ ፀጋ አልነበራቸውም፤ የሚያውቁት በግቢው ስታዲዮም ለመሰብሰብ ቀጠሮ መያዛቸውን ብቻ ነው፡፡ ከዚያስ? አንድ ስሙን መናገር ያልፈለገ የዩኒቨርስቲው ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እና የተቃውሞው አስተባባሪ ክስተቱን በእኔ ብዕር እንዲህ ይተርክልናል፡-
አርብ

የንጋት ፀሐይ ዓይኗን ከመግለጧ በፊት ተማሪው አንድ፣ ሁለት… እያለ በቀጠሮው ቦታ መሰባሰብ ጀመረ፡፡ ረፋዱ ላይም ምልአተ ጉባኤው የተሟላ መሰለ፤ ኦሮሞ ያልሆኑ ተማሪዎችም አብረውን ነበሩ፡፡ ከዚያም ‹በፊንፊኔ ዙሪያ የሚገኙት ሱሉልታ፣ ቡራዩ፣ መናጋሻ፣ ለገጣፎ፣ ለገዳዲ፣ ገላን፣ ዱከም እና ሰበታ ከኦሮሚያ ክልል ተወስደው ከአዲስ አበባ ጋር ሊቀላቀሉ ነው› ስለሚባለው ጉዳይ፣ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በቦታው የተገኙት የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ምትኩ ቴሶ ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠየቅን፡፡ ፕሬዚዳንቱም በቂ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ ግና፣ እንቅስቃሴያችን እምብዛም ጠንካራ አልነበረምና ተከታዮቹ ሶስት ቀናት ያለፉት የጎላ ድምጽ ሳይሰማ በተለመደው ፀጥታ ውስጥ ነበር፡፡
ማክሰኞ
ከምሳ በኋላ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ አድፍጦ የነበረው የተቃውሞ ድምጽ ድንገት ፈንድቶ በዩኒቨርስቲው ሰማይ ስር ናኘ፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት በሰላማዊ መንገድ ላቀረብነው ህጋዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ የሚሰጠን አካል በማጣታችን ቁጣችን ከመቅፅበት ሰማይ ጥግ ደረሰ፡፡ በሰከንዶች ሽርፍራፊም ግቢው ከዳር እስከዳር በመሬት አርድ ጩኸት ተናወጠ፡፡ መፈክር እያሰማን፣ በታላቅ ሆታ እየዘመርን፣ ከአሁን አሁን የሚያነጋግረን ባለሥልጣን ይመጣል ብለን ስንጠብቅ ባልገመትነው አኳኋን ከአንገት በላይ እና ከጉልበት በታች ድንጋይ መከላከያ ያጠለቁ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት ግቢውን ከብበው ውጥረቱን ይበልጥ አባባሱት፡፡ በዚህ አስፈሪ ድባብ ውስጥ በሚከት የከበባ ቀለበት አስገብተውን ለደቂቃዎች ያህል ሁኔታውን ሲያጤኑ ከቆዩ በኋላ ድንገት ወደ ግቢው በመዝለቅ መብቱን በሰላማዊ መንገድ እየጠየቀ የነበረውን ተማሪ እያሳደዱ ፍፁም በሆነ ጭካኔ በቆመጥ አናት አናቱን እየቀጠቀጡ በወደቀበት ይረጋገጡት ጀመር፡፡ እግሬ አውጭኝ ብለን አጥር እየዘለልን ሽሽት ከጀመርን መሀል ዕድለቢሶቹ በአይን ፍጥነት እየተወረወሩ በቆመጥ ወገብን ከሚሰብሩና በወታደራዊ ስፖርት በዳበረ ክንዳቸው ጨምድደው ይዘው መሬት ላይ ከሚደፍቁ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ማምለጥ አልተቻላቸውም፡፡ ብዙዎቻችን ግን ባለ በሌለ አቅማችን ሮጠን ባቅራቢያው ወደሚገኝ ጫካ ገብተን ተደበቅን፡፡ ዕለቱም ምንም እንኳ ህይወት ባይከፈልበትም፣ በድብደባ፣ ሽብር፣ ዋይታ ተጥለቅልቆ ሲተራመስ አለፈ፡፡
ረቡዕ
የትላንቱ የፌደራል ፖሊስ ተገቢ ያልሆነ አረመኔያዊ የኃይል እርምጃ ያስቆጣቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በብዛት ከእኛ ጎን ከመቆማቸውም በላይ ጥያቄውም በአራት ተባዝቶ አደገ፡፡ እነሱም ‹ኦሮሚኛ የፌዴራል ቋንቋ ሊሆን ይገባል፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ መሆን አለበት፣ አማራና ትግሬ ከክልላችን ይውጡልን፣ የጨፍጫፊው ምኒልክ ኃውልት ይፍረስ› የሚሉ ነበሩ፡፡ ይሁንና ቅንጣት ታህል ርህራሄ ያልፈጠረባቸው ፖሊሶች ህፃን-አወቂ፣ ሴት-ወንድ ሳይመርጡ መደብደብ መጀመራቸው፣ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን እያቀረበ የነበረውን ሕዝብ ስሜታዊ አድርጎት ጎማ ማቃጠል እና መንግስታዊ ቢሮዎች ላይ ድንጋይ እስከ መወርወር ደረጃ አደረሰው፡፡ ይህን ጊዜም በእንዲህ አይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት አነጣጥሮ ተኩሶ በመግደል የተካነው ‹‹አግአዚ›› ተብሎ የሚጠራው ክፍለ ጦር ድንገት ደርሶ ከተማዋን የቀለጠ የውጊያ ቀጠና አስመሰላት፡፡ ከዚህ በኋላማ ምኑ ይወራል! ምህረት የለሾቹ አነጣጥሮ ተኳሽ የአግአዚ አባላት ቀጥታ ወደ ሕዝቡ ጥይት በማርከፍከፍ አምቦን ከመቅጽበት በደም-አበላ አጠቧት፡፡ በዩኒቨርስቲያችን ግቢ በር እና አበበች መታፈሪያ ሆቴል አካባቢ ብዛት ያላቸው ሰዎች በጥይት ወድቀው ተመልክቻለሁ፡፡ ከተማሪዎችም መካከል ቢያንስ አስር የሚሆኑት መገደላቸውን በዓይኔ በብረቱ ያየሁት እና ከጓደኞቼም ያገኘሁት መረጃ ይጠቁማል፡፡ ዛሬም ድረስ (28/8/06) የት እንዳሉ የማይታወቅ ተማሪዎች መኖራቸውን ሰምቻለሁ፡፡
…በዚህ ጽሑፍ የማነሳውን አጀንዳ በደንብ ግልፅ ለማድረግ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ከተካሄዱት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች መካከል አንድ ማሳያ ልጨምር፤ ወለጋ፡፡ ደህና! ይህንንም ክስተት እንደ አምቦው ተማሪ ስሙን መግልፅ ላልፈለገው የወለጋ ዩንቨርስቲ መምህር ብዕሬን ላውሰውና እንዲህ ያውጋን፡-
በወለጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሔርን መሰረት ያደረገ ውጥረት እንደ አዲስ ለማገርሸቱ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ወቅት በባሕር ዳር የተከሰተው ቋንቋን መሰረት ያደረገ የጥላቻ ዘለፋ እና የአኖሌ ሐውልት ምርቃት ዋነኛዎቹ ሲሆኑ፤

ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማሁት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከደንቢዶሎ ቡና ጭኖ የተነሳ አንድ ኤፍ.ኤስ.አር መኪና ‹ጎጃም ላይ ተዘረፈ› ተብሎ በከተማዋ የተናፈሰው ወሬም ተጨማሪ ቤንዝን የሆነ ይመስለኛል፡፡ ወደ ተቃውሞው ትዕይንት ደግሞ እንለፍ፡፡

ማክሰኞ

እንደሚታወቀው የወለጋ ዩኒቨርስቲ በነቀምት፣ ግምቢ እና ሆሩ ግድሩ ካምፓሶች የተከፈለ ሲሆን፤ ሰሞነኛው ተቃውሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳው በዕለተ ዓርብ በዋናው የነቀምት ካምፓስ ውስጥ ነው፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪዎች አዲሱን ማስተር ፕላን በተመለከተ ላቀረቡት ጥያቄ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ፍቃዱ በየነ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡ ሀገር ውስጥ እንደሌሉና ወደ ቻይና ማቅናታቸው ይነገራቸዋል፡፡ በዚህም ተበሳጭተው በተቃውሞ ጩኸት ታጅበው ግቢውን ለቀው ለመውጣት የሞከሩ ቢሆንም፣ ከአጥር ውጪ ባደፈጡ የከተማዋ ፖሊሶች ትዕዛዝና ማስፈራሪያ ወዲያውኑ ተበታተኑ፡፡ በመጪው ሰኞም የሶሻል ሳይንስ ትምህርት ብቻ በሚሰጥበት የግምቢው ካምፓስ ለመገናኘት ውስጥ ለውስጥ ይነጋገሩና ቀጠሮ ይይዛሉ፡፡ በዚህ መልኩ በተጠቀሰው ዕለት በግምቢው አዳራሽ የተሰበሰበው የሁለቱ ካምፓስ ተማሪ የነቀምቱን ጥያቄ ለዲኑ ያቀርባል፡፡ ነገር ግን ተማሪውና ዲኑ መግባባት ላይ ካለመድረሳቸውም በተጨማሪ ጥቂት ተማሪዎች ለድብደብ በመጋበዛቸው ስብሰባው ያለምንም ውጤት ይበተናል፡፡ ዕለቱም ፍሬ አልባ ሆኖ ያልፋል፡፡

ረቡዕ

በዚህ ቀን ከሰዓት በኋላ ተማሪው ግቢውን እየዞረ በከፍተኛ ድምፅ ‹‹ቡራዩ ኬኛ፣ ሰበታ ኬኛ፣ ለገዳዲ ኬኛ….›› እያለ ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ ሲገልፅ ዋለ፤ ምሽት ላይ ግን ድንገት መንፈሱ ተቀይሮ ያልተጠበቀ መልክ በመያዙ፣ አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሆኖ የዋለውን ሂደት ከማደፍረሳቸውም በላይ፣ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆኑ ጥቂት የማይባሉ የንግድ እና መኖሪያ ቤቶችን ወደ መዝረፍ ተሸጋገሩ፡፡ በማግስቱ ወደ ዩኒቨርስቲው ግቢ ሄጄ ስለሌሊቱ ክስተት የኦሮሞ ተወላጅ ከሆኑ ባልደረቦቼ ጋር ስንወያይ፣ ቢያንስ ዘረፋውን ይኮንናሉ ብዬ ስጠብቅ፤ በተቃራኒው ‹‹ንብረታቸውን ነው ያስመለሱት፤ ሀጢአት አልፈፀሙም!›› በማለት ድርጊቱን ሲደግፉ በመስማቴ በእጅጉ ተገረምኩ፡፡ ከተማዋም ቀኑን ሙሉ ለተቃውሞ በወጡ ነዋሪዎቿ መናጧን ቀጠለች፡፡ አልፎ ተርፎም በግምቢ አቅራቢያ ባለችው የጉትን ወረዳም የአንድ ብሔር ተወላጆች በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው ወደ ክልላቸው እንዲሄዱ በሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ተጨናንቃ እንደዋለች ስሰማ፣ ያ ሀገሪቱን አንድ ቀን ሊያፈራርሳት እንደሚችል ሲነገርለት የነበረው ብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም ዕውን መሆኛው ጊዜ በጣም እንደቀረበ ስለተሰማኝ የቀኑ ግርምቴ በከባድ ፍርሃት ተተካ፡፡ ምክንያቱም የዚህች ወረዳ አብላጫው ነዋሪ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው አይደለምና ሊፈጠር የሚችለው ትርምስና ዕልቂትን መገመት የሚከብድ አይመስለኝም፡፡

ሐሙስ

በግምቢ ከተማ ኦሮሞ ያልሆኑ ነዋሪዎችን ንብረት መዝረፉ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከፍተኛ ፍርሃት በመንገሱ የብሔሩ ተወላጅ ያልሆንን ሰዎች ከቤታችን መውጣት አልቻልንም፡፡ እቤት ውስጥ ምግብ የማሰናዳት ልምዱ ስለሌለኝ ቁርስም ምሳም ምንም ሳልቀምስ በመዋሌ ረሀብ ክፉኛ እየሞረሞረኝ ነው፤ እንደዚያም ሆኖ ወደ ምግብ ቤቶች ለመሄድ ድፍረቱ አልነበረኝም፡፡ ተከታታይ የጥይትና የዋይታ ድምፅ ያለማቋረጥ በቅርብ ዕርቀት ይሰማኛል፡፡ በርግጥ ዘግይቶ እንደተረዳሁት በነቀምት ፖሊሶች ተገድሎ፣ በማግስቱ ወደመኖሪያው ግምቢ ማርያም ሠፈር አካባቢ አስከሬኑ ከመጣ አንድ ተማሪ በቀር ስለተገደሉ ሌሎች ሰዎች የሰማሁት ምንም ነገር የለም፡፡ የሆነው ሆኖ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት አከራዬ ከራሳቸው ቤት ምግብ አምጥተውልኝ ረሀቤን ማስታገስ ቻልኩ፡፡ እኚህ ከዘር ሐረግ መዘዛ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሰጡ ደግ ኢትዮጵያዊት እናት ወደውጪ እንዳልወጣ መክረውና አፅናንተውኝ ቢሄዱም፣ ሌሊቱስ እንዴት ያልፍ ይሆን? እያልኩ በጭንቀት ተጠፍንጌ ስገላበጥ አደርኩ፡፡ ልክ ጎህ ሲቀድም ጨርቅ-ማቄን ሳልል ቀጥታ ወደ ትውልድ ቦታዬ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡
ኦሮምያ-የጦር ቀጠና?

ባለፉት ሁለት አስርታት ሊካዱ ከማይችሉ ሀገራዊ እውነታዎች አንዱ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪው ከሌላው አካባቢ ኢትዮጵያውያን በተለየና በከፋ መልኩ ለሞት፣ ለስቃይ፣ ለእስር፣ ለስደት… ተጋላጭ ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡ ሰሞኑን በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙ ዜጎች ላይ የደረሰው ርህራሄ አልባ ጭፍጨፋም የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ የተቃውሞው መነሾ ‹በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ሰባት የኦሮሚያ አነስተኛ ከተሞች በአዲስ ማስተር ፕላን ወደ ፌደራል መንግስቱ መቀመጫ ሊቀላቀሉ ነው› መባሉን ተከትሎ ስለጉዳዩ ግልፅ የሆነ ማብራሪያ አለመሰጠቱ ያስነሳው ቁጣ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የአዲስ አበባውን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የስምንት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም በእንቅስቃሴው ቀጥተኛ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በአምቦ፣ ወለጋ፣ መደወላቡ እና ሐሮማያ ደግሞ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ተቃውሞው ጠንከር ያለ ነበር፤ ከተማሪዎቹ በተጨማሪ የከተሞቹ ነዋሪዎችም መቀላቀላቸው ተስተውሏል፡፡ አገዛዙም ይህንን አስታክኮ ‹‹ንብረት ማውደም››፣ ‹‹ባንክ መዝረፍ›› ገለመሌ በሚሉ ውሃ በማይቋጥሩ ምክንያቶች የበርካታ ዜጎችን ህይወት ቀጥፏል፡፡ ይሁንና ይህንን መሰሉ ሕዝባዊ ተቃውሞን የእነ አባይ ፀሀዬ እና በረከት ስምኦን መቀለጃ የሆነው ሕገ-መንግስት እንኳ ሊከለክል እንደማይችል ይታወቃል፡፡ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳም በሳምንቱ መግቢያ ላይ ለ‹‹ቪኦኤ›› ራዲዮ ‹‹በሁሉም አካባቢ ተማሪዎች ያነሱት ጥያቄ ፍትሓዊና ሕጋዊ ነው›› ሲል የተናገረበት መግፍኤ ይኸው ነው፡፡ ሆኖም ሀገሪቱ ለዘመናት ተፈራራቂ አምባገነን ገዥዎቿን አቀማጥላ መሸከም የማይታክታት ኢትዮጵያ ናትና፣ የጭፍጨፋው መሪዎችም ሆኑ አስፈፃሚዎቹ በሕግ እንደማይጠየቁ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እዚህ ሀገር ከሥርዓቱ የተለየ የፖለቲካ አቋም የሚያራምደውንም ሆነ ሰላማዊ ተቃውሞ አድራጊዎችን መግደል አያስኮንንም፡፡ ግፋ ቢል አባዱላ ገመዳ ለጠቀስኩት ራዲዮ ጣቢያ ‹‹መንግስትም ሐዘኑን ገልጿል፤ እኔም በቦታው ደርሼ አይቻለሁ፤ አዝኛለሁ!›› ሲል ከገለፀው የለበጣ ንግግር አይዘልም፡፡ ግና፣ እስከ መቼ ወገኖቻችን እየታሰሩ፣ እየተሰቃዩ እና እየተገደሉ ዝምታው እንደሚቀጥል ግራ አጋቢ ነው፡፡ …ይህ አይነቱ ነውረኛ ድርጊት በኦሮሚያ እንግዳ ባይሆንም፣ አጀንዳችን የተቃውሞውን ገፊ-ምክንያት መፈተሽ በመሆኑ፣ ከሁለት የቢሆን መላምቶች (Sinarios) አኳያ በአዲስ መስመር ለማየት እሞክራለሁ፡፡

አዲሱ መንፈስ

የክልሉ አስተዳዳሪ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ከተቃውሞው ጀርባ ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ መፈተሹ ቀዳሚው ነው፡፡ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የመረጃ ምንጮች የውዝግቡ መነሾ ዕቅድ በአቶ መለስ ዜናዊ የመጨረሻ ዘመን የተዘጋጀ እና የኦህዴድ መሪዎችም ያለአንዳች ጥያቄ ለማስፈፀም አምነው የተቀበሉት እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡ በርግጥም መለስ የቱንም ያህል ከሕገ- መንግስቱ እና ከፌዴራል ስርዓቱ የሚቃረን ነገር ማድረግ ቢፈልግ፣ ለሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች አመኑበትም አላመኑበትም በፀጋ ከመቀበል ውጪ ተቃውሞ ቀርቶ፣ ጥያቄ ለማቅረብ መሞከሩ የሚያስቀስፍ ሀጢያት እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይህንንም ዕቅድ ያለ ኦህዴድ ስምምነት አዘጋጅቶ ሲያበቃ፣ ለከፍተኛ አመራሮቹ በተለመደው ያሰራር ትዕዛዝ ተላልፎ ተግባራዊ የሚሆንበትን ወቅት ሲጠብቅ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ዛሬ እርሱ ከሕይወት አፀድ በመለየቱ ጊዜው ተቀይሮአል፤ አገዛዙም ከግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ወደ ቡድናዊ አምባገነንነት ተሸጋግሯል፤ በዚህም የዕዝ ክፍተት በመፈጠሩ፣ ያያኔው ኦህዴድ ‹‹አሜን›› ብሎ የተቀበለውን ዕቅድ፣ ዛሬ ወደታች ለማውረድ ሲሞክር ጠንካራ ተቃውሞ ቢያጋጥመው ያልተጠበቀ ክስተት አይሆንም፡፡
በአናቱም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ወዲህ የኦነግ መዳከም ተስፋ ያስቆረጣቸው በርካታ ወጣቶች፣ ክልላዊ ጥያቄያቸው በኦህዴድ በኩል መልስ እንዲያገኝ ለመሞከር ድርጅቱን የተቀላቀሉ ስለመሆኑ ተደጋግሞ በፖለቲካ ተንታኞች መነገሩ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ልባቸው ከኦህዴድ ይልቅ ለኦነግ የቀረበ አባላት በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ በትምህርታቸው ገፍተው፣ በድርጅቱ መካከለኛ የሥልጣን እርከን ላይ የመገኘታቸው አጋጣሚ፣ ‹ከኦሮምኛ ተናጋሪውም ሆነ ከኦህዴድ እውቅና ውጪ የተዘጋጀ ኢ-ሕገ መንግስት› ሲሉ የኮነኑትን ዕቅድ በመቃወም ተማሪውን ከጀርባ የሚያነሳሱበት ዕድል መኖሩን ሌላው ዓብይ መላምት አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ በርግጥ በዚህ መስመር በርትተው ቢሄዱ፣ ሥርዓቱ ካነበረው ፌዴራሊዝም አኳያ መብት እንጂ ሕገ-ወጥነትም ዘውገኝነትም አለመሆኑ አያከራክርም፡፡ እንዲያውም የአንድ ወቅት ጠርዘኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች የተሰበጣጠረ ተቋማዊ አቅማቸውን በዚህ መልኩ ለመፈተሽ ከሞከሩ፤ ለልባቸው ከአባዱላ ይልቅ ሌንጮ ይቀርባልና፣ ለቀጣዩ ምርጫ ኦቦ ሌንጮ ሸገር ከደረሰ የሚሆነውን ለመገመት ከባድ አይመስለኝም፡፡ …እነዚህ ሁለት ትንተናዎችም የሚያስማሙን ከሆነ፣ ኩነቱ ኦህዴድን ወደሚከፋፈልበት ጠርዝ መግፋቱ አይቀሬ ነው ብለን ልናምን እንችላለን፡፡

የሆነው ሆኖ እንደ ኦህዴድ ምንጮቼ፣ መካከለኛ ካድሬዎቹ ከጉዳዩ ጀርባ መኖራቸውን የሚጠቁመው፣ እንዲህ በሰላይና በአንድ ግዙፍ ፓርቲ መዳፍ ስር ባደረች ሀገር ንቅናቄው ያለእንከን ከአምቦ እስከ ሐረር፤ ከወለጋ እስከ ባሌ፤ ከቡራዩ እስከ አዳማ… መስፋፋት የመቻሉ ምስጢር አንዱ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በርካታ የከተማ ሰዎች በተሳተፉበት የአምቦውና የወለጋው ሕዝባዊ ንቅናቄ በላኤ-ሰቡ ‹‹የወገን›› ጦር በወቅቱ ለቅሞ ካሰራቸው ሰላማዊ ዜጎች በቀር፣ እንቅስቃሴውን ማን አስተባበረው? እንዴትና በምን መልኩ? የሚለው ጥያቄ በደፈናው የፈረደባቸው ተቃዋሚ ድርጅቶችን እና የውጭ ኃይሎች ላይ ከመደፍደፍ ያለፈ ምንም የታወቀ ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ የኦህዴድ የበታች ካድሬዎችም ይህንን መሰል ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ እንደተለመደው ከመኖሪያ ቤታቸው የሚታፈሱትን ዜጎች ቁጥር ለመቀነስ የሄዱበት ርቀት በጎ ጅምር ይመስለኛል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ደግሞ ቢያንስ ኦሮምኛ ተናጋሪ መኮንኖችና ወታደሮች ‹ከአብራኩ በተገኘን ሕብረተሰብ ላይ አንተኩሰም› የሚሉበት ታሪካዊ ቀን ይቃረባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከዚህ በግልባጩ አባዱላ ገመዳ ለሶስት ቀናት ያህል የሕዝባዊ ንቅናቄው ማዕከል በሆነችው አምቦ ከተማ ተገኝቶ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች እና በአካባቢው ዙሪያ ካሉ 18 ወረዳዎች የተሰባሰቡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያይቶ ‹መግባባት ላይ ደርሷል› መባሉ በመንግስት ሚዲያ ተነግሯል፡፡ ይህ ግን የልጆች ዕቃ-ዕቃ ጨዋታ መሆኑ ከራሱ ከአባዱላም የተሰወረ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ይህን መሰል ተቃውሞ በገጠመው ቁጥር ‹ተግባብተናል› የሚለው በካድሬ መዋቅር ከሚሰበስባቸው አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ተወያይቶ እንጂ ከጥያቄ አቅራቢዎቹ ጋር አለመሆኑ የተለመደ ነውና፡፡ እንዲህ አይነቱ ‹‹ውይይት›› ሲጠናቀቅም ‹‹የእገሌ ከተማ ነዋሪዎች ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴውን አወገዙ››፣ ‹‹አጥፊዎቹ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠየቁ››፣ ‹‹የፀረ-ሰላም ኃይሎች እጅ አለበት አሉ›› እና መሰል ዜናዎች እስኪቸኩ ድረስ መተላለፋቸው ነባር ስልቱ ነው፡፡ ሰሞኑንም የታዘብነው ይህንኑ ነው፡፡

ስውሩን እጅ ፍለጋ

ከመጀመሪያው መላምታችን በተቃራኒው ሊጠቀስ የሚችለው ተማሪዎቹን ለተቃውሞ ቀስቅሶ ለዘግናኙ ጭፍጨፋ የዳረጋቸው የአገዛዙ ስውር እጅ ሊኖር ይችላል የሚለው ጥርጣሬ ነው፡፡ ይኸውም አብዮታዊው ግንባር ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ እና የሊቢያው ሞሀመር ጋዳፊን የመሳሰሉ ጉልበታም መሪዎችን ሥልጣን ያሳጣው የአረቡ የፀደይ አብዮት ያነቃቃቸው ኢትዮጵያውያን በምርጫ ፖለቲካው ረገድ ካላቸው ጥቁር ታሪክ አንፃር በተመሳሳይ መንገድ መንግስት እንዲለወጥ ይሞክሩ ይሆናል የሚል ስጋት ላይ ከመውደቁ ጋር ይያያዛል፡፡ ለዚህም ከእነ እስክንድር ነጋ እስከ ሶስቱ ጋዜጠኞችና ‹‹ዞን ዘጠኝ›› ጦማሪዎች ድረስ በአርምሞ የተመለከትነው የጅምላ እስር አይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በዚህ ስሌትም የኢህአዴግ የቀድሞ አመራር ‹‹ጦርነትን እንሰራለን!›› እንዲል፤ ከቀጣዩ ምርጫ አስቀድሞ ታማኝ በሆኑ የኦህዴድ ካድሬዎች አማካይነት ተቃውሞውን ቀስቅሶታል ወደሚል ጠርዝ እንገፋለን፡፡ ይህ አይነቱ ስልት በ97ትም መተግበሩን የሚያሳየን፣ ለብጥብጡ ተጠያቂ የተደረገው የቀድሞው ቅንጅት የሰኔውም ሆነ የጥቅምቱ የአደባባይ ተቃውሞን እንዳልጠራ በማስረጃ አስደግፎ ማቅረቡ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ተማሪዎቹንና የከተማ ነዋሪውን ስሜታዊ እንዲሆኑ ገፋፍቶ፣ ጥቂት የመንግስትና የግል ንብረቶች እንዲወድሙ ካደረገ በኋላ ጭፍጨፋውን አካሄዷል ብለን መገመታችን አይቀሬ ነው፡፡ በሰሞኑ ዘግናኝ እልቂትም የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ በአምቦ እና አጎራባቿ ተኪ ብቻ ከአርባ በላይ ንፁሃን በአደባባይ የጥይት እራት መሆናቸውን ዘግበዋል፡፡ በበኩሌ ገዥው ግንባር በእንዲህ ያለ ዲያብሎሳዊ ሥራ በመላ አገሪቱ ፍርሃት በማንበር፣ ውስጣዊ መፈረካከሱን ሸፍኖ ምርጫውን እንደ መለስ ዜናዊ ዘመን ያለጎላ መንገራገጭ በአሸናፊነት ማለፍን አላማው አድርጎ እየሰራ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሌላው ቀርቶ በድህረ-ምርጫ 97 በዕድሜ ከገፉ አዛውንት እስከ የአስር ዓመቱ ህፃን ነብዩ ድረስ ለፈፀመው ግድያ ምክንያት ያደረገውን ‹ባንክ ለመዝረፍ መሞከር›፤ ከአስር ዓመት በኋላም በአምቦና ጉደር አካባቢ ከልጆች እናት እስከ አስር ዓመት ህፃን ድረስ ያሉ ንፁሀንን

ረሽኖ ሲያበቃ ምክንያቱ ይኸው መሆኑ ግጥምጥሞሽ አይመስለኝም-አንዳች ስውር መልዕክት ለማስተላለፍ አስቦ ያዘጋጀው እንጂ፡፡ በርግጥም ጉዳዩን ለጥጠን ካየነው የ97ቱን ጭፍጨፋ በቀጥተኛ ተሳታፊነት ለመገንዘብ ያልደረሱ (አሁን ዕድሜያቸው 18/19 ዓመት ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል) ሰሞኑን በዘጠኙ ዩንቨርስቲዎች ለተቃውሞ የወጡ ወጣቶች እና ከአንድነት እስከ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፎች የተሳተፉ በዚሁ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ለውጥ ፈላጊዎች (በብዛት ሥራ-አጥ ወጣቶች) የመኖራቸውን ሀቅ ህወሓት መረዳቱ ሌላ ቀጣይ አስር የሥልጣን ዓመት ዕውን እስኪሆን ድረስ ለመቅጣት መፈለጉ ነው፣ በኦሮምያ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን ሳይቀር ያለምህረት በጥይት እስከመጨፍጨፍ ያደረሰው ልንል እንችላለን፡፡

ኦሮሞ ብቻውን?

ሰሞነኛው የኢህአዴግ ወታደራዊ ጭፍለቃ እና ተያያዥ ጉዳዮች የኦሮሞ ጥያቄን መልሶ ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት ገፊ መራራ ፅዋ ሊሆን ችሏል፡፡ ብዙ የኦሮሞ እናቶችን ደም እንባ ያስለቀሰውን ይህንን አሳዛኝ ክስተት ተከትሎ ድምፃቸውን ካሰሙ የብሄሩ ልሂቃን መካከል ኦቦ ሌንጮ ለታ ያስቀመጣቸው ነጥቦች፣ ወቅቱን ተንተርሰን ልንነጋገርባቸው የሚገቡ እንደሆኑ አምናለሁ፡፡ ‹‹ኦሮሞ ሲጨፈጨፍ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ዝም ሊል አይገባውም፡፡ ዛሬ ኦሮሞ ላይ የደረሰው ነገ በሌላውም ላይ ይደርሳልና›› የሚለው የመጀመሪያው ጭብጥ ነው፡፡ በህወሓት የብረት ክንድ ስር ያሳለፍናቸው ሃያ ሶስት አመታት፤ ኦሮምኛ ተናጋሪውን ዋነኛው ግፉዕ ቢያደርጉትም፣ ሌሎቻችንም የአገዛዙን ግፍ እንደየድርሻችን ተጋርተናል፡፡ ከኦጋዴን እስከ ትግራይ፣ ከጋምቤላ እስከ አፋር፣ ከደቡብ እስከ አማራ. የሥርዓቱ ምህረት አልባ ክንድ ህልውናውን ያላደቀቀውን የትኛውንም ቋንቋ ተናጋሪ ማግኘት ዘበት ነው፡፡ ይህም ሆኖ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ምስረታን ተከትሎ፣ በብዙዎቹ አካባቢዎች የተስተዋለው የየዘውጎቹ የማንነት መለዮ መናድ፣ አንድም በየቋንቋው ተናጋሪ ልሂቃን ስልጣንን ያሰላ ትንታኔ እና የገዢው ስብስብ ተቋማዊ መልክ መስጠት፤ የአንዳችንን መከራ ሌላኛችንን እንዳይሰማን (እንዳያመን) ሳያደርገን አልቀረም፡ ፡ ያሳለፍናቸው ሩብ ክፍለ-ዘመን ሁለት ቀሪ ዓመታት ግን፣ ህመሞቻችን ልንጋራ፣ ስለጋራ ህልውናችን እንድናሰላስል፣ አልፎም አንዱ ላይ የሚርከፈከፈው የደመ ቀዝቃዞቹ ጥይት የእኛንም ቁስል እንዳመረቀዘ እንድናምን የሚያደርጉ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም አሁን ያየነው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ስቃይ የሁላችንም መከራና ቁስል ነውና በደምና በዜግነት ስለቆመው ጠንካራው አሀዳዊ ማንነታችን ስንል፤ በሕብረት ድምፃችንን ከፍ አድርገን ልናሰማ፣ አብረናቸውም ልንጮኽ ግድ ይለናል፡፡

ሌላው ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪው ብቻውን ይህን ስርዓት ሊጥልም ሆነ የተሻለች ሀገር ሊገነባ እንደማይጠበቅበት ማመን ነው፡፡ ‹‹ስለቀጣይቱ ኢትዮጵያ ሁሉን ያሳተፈ ውይይት እናካሂድ›› የሚለውን የሌንጮን ሰሞነኛ ጥሪ “እህ” ብለን በንቃት ልናደምጠው ይገባል፡፡ እርሱና ጓዶቹ ያመጧቸውን የፖለቲካውን ክስረት የሚያሻግሩ ሀሳቦችን እየገሩ መሄድ፣ ወቅቱን ተንተርሰን በጽሞና ልናስብበት እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ የኦሮሞ ጥያቄ ከሌሎቹ ዘውጎች ጩኸት ተለይቶ ለብቻው እልባት ሊያገኝ አይችልም፤ ‹ኦሮሞ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ በማድረጉ ረዥም ጉዞ ላይ ዋነኛው አዋጪ መሆን አለበት› የመሰሉትን አቋሞች ለተሻለች ኢትዮጵያ ልናውለው የምንችለው፣ እንደሰሞኑ ባለ የብቻ የዘውጉ መከራ ፊት ዝምታችንን ሰብረን ስናብር ነው፡፡ ይህ ሂደትም፣ ቅጥ-ያጣውን ወታደራዊ ስርዓት ለማስቆም ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ቀድሞስ ነገር ታንጎ ለብቻ የሚደነሰው እንዴት ተሆኖ ነው?
ኢትዮሚድያ