Archive | May 21, 2014

‹‹የሚገሥጹንን ሁሉ መቅጣት የለብንም››

ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ በሊቅነታቸው፣ በቆራጥነታቸው፣ ለየት ባለ አስተሳሰባቸውና ለነገሮች በሚሰጡት አስደናቂ ምላሽ የሚታወቁ የትግራይ ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ እስካሁንም እርሳቸውን በተመለከተ የሚተረኩ እጅግ አስገራሚ ታሪኮች አሏቸው፡፡ አንዱ እንዲህ ይላል፡፡ አቡነ ዮሐንስ በዓላትን በተመለከተ የነበራቸው አስተሳሰብ ከብዙው ሰው ለየት ያለ ነበር፡፡ ‹‹በዓል መከበር ያለበት በሥራ ነው›› ብለው ያምኑ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት እንዲያውም በቀዳሚት ሰንበት ሥራ ሲሠሩ ያያቸው ሰው ‹‹እንዴት ጌታ ባረፈበት ቀን ይሠራሉ›› ቢላቸው ‹‹እርሱኮ ያረፈው ሥራውን ጨርሶ ነው፡፡ እኔ መች ሥራዬን ጨረስኩ ብለህ ነው›› ብለው መመለሳቸው ይነገራል፡፡

daniel-kibret

 ‹‹የበዓላትን ቀናት ለበዓሉ የሚስማማ ሥራ በመሥራት እንጂ እጅና እግርን አጣጥፎ በመቀመጥ፣ መጠጥ ቤትና ጭፈራ ቤት በመዋል ማክበር ከማክበር አይቆጠርም፡፡ ሰው ምንጊዜም መቦዘን የለበትም፡፡ በየዕለቱ ለዕለቱ ተስማሚ የሆነ ሥራ መሥራት አለበት›› ብለው ያም ይህንንም ያስተምሩ ነበር፡፡

 ታድያ በአንድ ወቅት በበዓል ቀን ቤተ ክርስቲያን ሲያሠሩ ውለው ለጉዳይ ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ ለአቤቱታ ወደ እርሳቸው ዘንድ ከገጠር የመጣ አንድ ካህን እርሳቸውን ፍለጋ ወደሚያሠሩት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይመጣል፡፡ ሲመጣ እርሳቸው የሉም ነገር ግን ሠራተኞቹ በሥራ ተጠምደዋል፡፡ ተገረመም፣ ተናደደም፡፡ ‹‹እንዴት በበዓሉ ቀን ትሠራላችሁ›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ያዘዟቸው አቡነ ዮሐንስ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ እርሱ ግን አልተቀበለውም፡፡ ከኖረበትና ከተማረው ውጭ የሆነ ነገር ሲፈጸም እያየ ዝም ማለቱን ኅሊናው አልተቀበለውም፡፡ በርግጥ ያዘዙት ሊቀ ጳጳሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሊቀ ጳጳሱም ቢሆኑ ሊሳሳቱ ይችላሉ አለና አሰበ፡፡

 አስቦም አልቀረ ወደ ሠራተኞቹ ሄደና ‹‹በሉ ሥራችሁን አቁሙ›› አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ሊቀ ጳጳሱ ያዘዙትን እንደማያቆሙ ነገሩት፡፡ በዚህ ጊዜ መስቀሉን አወጣና አወገዛቸው፡፡ ያን ጊዜም ሠራተኞቹ ሥራቸውን አቆሙና ቁጭ አሉ፡፡ እርሱም ሊቀ ጳጳሱን ፍለጋ ሄደ፡፡

 አቡነ ዮሐንስ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲመጡ ሠራተኞቹ ሁሉ ቁጭ ብለዋል፡፡ ‹‹ለምን ሥራ ፈትታችሁ ተቀመጣችሁ?›› አሏቸው፡፡ ‹‹አንድ ካህን መጥቶ አወገዘን›› አሉና መለሱላቸው፡፡ ካህኑ ይጠራ ተባለና ተፈልጎ መጣ፡፡ ‹‹አንተ ነህ ወይ ያወገዝካቸው›› አሉት፡፡ ‹‹አዎ›› አለ፡፡ ‹‹ለምን?›› ሲሉ መልሰው ጠየቁት፡፡ ‹‹አባቶቻችን ያቆዩትን ሥርዓት ጥሰው ለምን በዓል ይሽራሉ ብዬ‹‹ አላቸው፡፡ ‹‹ያዘዝኳቸውኮ እኔ ነኝ›› አሉት፡፡ ‹‹ቢሆኑም ስሕተት ነው፡፡ ስሕተቱን እያየሁ ዝም ማለትም ሌላ ስሕተት ነው›› አላቸው፡፡

 አቡነ ዮሐንስ ተገረሙ፡፡ ካህኑን በመኪናቸው አሳፈሩና ወደ ቤታቸው ወሰዱት፡፡ ‹‹በል ያንተን ጉዳይ በጉባኤ ነው የማየው፤ እስከዚያ እዚሁ እኔ ቤት እየበላህ እየጠጣህ ተቀመጥ›› አሉት፡፡ አቡነ ዮሐንስ ለጉዳይ የሚመጣ የገጠር ሰው ከገጠማቸው ከተቻለ ጉዳዩን ዕለቱኑ ይፈጽሙለታል፡፡ ካልተቻለ ደግሞ እዚያው ራሳቸው ቤት አስቀምጠው ጉዳዩ እስኪያልቅ ያስተናግዱታል፡፡ ክሱ የሚቀርበው በእርሳቸው ላይ ቢሆንም ሰውዬው በቤታቸው መስተናገዱ ግን አይቀርም፡፡

ቀን ተቀጠረና በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ ጉዳዩ ታየ፡፡ የመቀሌ ከተማ ሕዝብ፣ ካህናትና ሊቃውንት ተሰበሰቡ፡፡ አቡነ ዮሐንስ በሚሰጡት ለየት ያለ ፍርድ፣ በሚናገሩት ዘመን ተሻጋሪ ንግግር ይታወቃሉ፡፡ በአንድ ወቅት ወደ እርሳቸው የመጣ ሰው ‹‹ተማር›› ቢሉት ‹‹ምን እየበላሁ ልማር›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹ታድያ የደነቆርከው ምን እየበላህ ነው›› ብለው ጠይቀውታል ይባላል፡፡

 ያ ካህን ቀረበ፡፡ ‹‹ለምንድን ነው ሠራተኞቹን የገዘትካቸው?›› ተብሎ ተጠየቀ፡፡ ‹‹አባቶቻችን ባቆዩን ሥርዓት በበዓል እንዲህ ያለ ሥራ መሠራት የለበትም ብዬ ነው›› አላቸው፡፡ ‹‹ያዘዝኩት እኔ ነኝ፣ አንተ ይህንን ስታደርግ ሊቀ ጳጳሱ ይቀጡኛል፣ ከሥራ ያባርሩኛል፣ ክህነቴን ይይዙብኛል ብለህ አላሰብክም›› አሉት፡፡ ‹‹ቢያባርሩኝም፣ ክህነቴን ቢይዙብኝም መቀበል ነው እንጂ ምን ይደረጋል፡፡ ስሕተት እያየሁ ግን እንዴት አልፈዋለሁ፡፡›› አላቸው፡፡ ‹‹እና የሚመጣብህን ሁሉ ለመቀበል ተዘጋጅተሃል›› አሉት ‹‹ከመጣ ምን ይደረጋል›› አለ ካህኑ፡፡ ‹‹ከምቀጣህ ለምን ግዝትህን አታነሣም›› አሉት፡፡ ‹‹እርሱማ አቋም ነው፡፡ እምነቴ ነው፡፡ ቃሌ ነው፡፡ ይኼማ ከእርስዎ የባሰ ስሕተት መሥራት ነው›› አላቸው፡፡

 ያን ጊዜ አቡነ ዮሐንስ ተነሡ፡፡ ሕዝቡም ምን ሊፈርዱበት ይሆን? እያለ በጉጉት ጠበቀ፡፡ ግማሹ እንዲያ ግማሹም እንዲህ አሰበ፡፡ አቡነ ዮሐንስም የመጣበትን አውራጃ ጠየቁት፡፡ ነገራቸው፡፡ አሁን ሕዝቡ የቅጣቱ ደብዳቤ ለአውራጃው እንደሚጻፍ አረጋገጠ፡፡ አቡነ ዮሐንስም አውራጃውን ከሰሙ በኋላ ‹‹እገሌ የተባለው የዚህ አውራጃ ሊቀ ካህናት እንዲህ ወደተባለ አውራጃ ተዛውሯል›› አሉ፡፡ ያን ጊዜ ሕዝቡ ‹‹የኃጥኡ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ›› ብሎ ተረተ፡፡ በዚህ ካህን ዕዳ ሊቀ ካህናቱ በመቀጣቱ አዘነ፡፡ አቡነ ዮሐንስም ቀጠሉ፡፡ ‹‹የዚህ አውራጃ ሊቀ ካህናት ግን ይህ ቄስ ይሆናል›› ሲሉ ሕዝቡ በአግራሞት አጨበጨበ፡፡ካህኑም ግራ ገባው፡፡ የጠበቀውና ያገኘውም ተለያየበት፡፡ ሕዝቡም በጥያቄ ተወጠረ፡፡ ለምን?

‹‹አያችሁ ወገኖቼ›› አሉ አቡነ ዮሐንስ፡፡ ይህ ሰው ሊቀ ጳጳሱን አወገዘ፡፡ እንደ ሥርዓታችን ልክ አልነበረም፡፡ ቢያንስ ለምን እንደዚያ እንዳደረግን እንኳን መጠየቅ ነበረበት፡፡ ነገር ግን በአቋሙ ትክክል ነው፡፡ ሰው ማለት፤ ጀግና ማለት፣ ጎበዝ ማለት አቋም ያለው ሰው ነው፡፡ የበላዩን የማይፈራ፤ ፈጣሪውን ብቻ የሚፈራ፡፡ ላመነበት እውነት የሚቆም፡፡ በአቋሙ ምክንያት የሚመጣበትን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ የሆነ፡፡ አሁን እኔ ሥልጣኑን ልይዝበት፣ ከሥራ ላግደው፣ ጨርሶም ላወግዘው እንደምችል ያውቃል፡፡ ይህንን ሁሉ እያወቀ ግን ላመነበት እውነት መጽናቱ ጀግና ያደርገዋል፡፡ ማክበር ያለብን የሚፈሩንን፣ ቅዱስ ቅዱስ የሚሉንን፣ የሠራነውንም ያልሠራነውም የሚያደንቁልንን፣ የሚያወድሱንን ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይህማ የማንም ሰው ጠባይ ነው፡፤ አክባሪውን የማይወድ ማን አለ፡፡ እኛም ጀግና የምንሆነው የሚገሥፁንን፣ የሚቆጡንን፣ ስሕተታችንን በድፍረት የሚናገሩንን፣ ሥልጣናችንን ሳይፈሩ ያመኑበትን እውነት የሚመሰክሩልንን ጭምር መውደድና ማክበር አለብን፡፡
እናንተ እንደምቀጣው ነው የጠበቃችሁት፡፡ የሚገሥጹንን ሁሉ ግን መቅጣት የለብንም፡፡ ያመኑበትን ስሕተታችንን የሚነግሩንን፣ በአቋም የሚሞግቱንን ሁሉ መቅጣት የለብንም፡፡ እንዲያውም መሸለም አለብን፡፡ ለዚህ ካህን ክህነቱን የሰጠሁት እኔ ነኝ፡፡ ስሰጠውም ‹ደኻ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ በል› ያልኩት እኔ ነኝ፡፡ ያን የሰጠሁትን እኔ ላይ ሲፈጽመው መናደድ የለብኝም፡፡ ፍርደ ገምድል መሆንም የለብኝም፡፡ እንዲያውም እንዲህ ያለ ልጅ በማድረሴ ልኮራ ይገባል፡፡ ሞኞች የሚገሥጽዋቸውን አይወዱም፡፡ ግን ቢሆንም እየመረረን እንኳን መቀበል አለብን፡፡ አሠራሩ ስሕተት ቢሆንም አቋሙ ግን ልክ ነው፡፡ ቆራጥነቱ ግን ልክ ነው፡፡ ማንንም አለመፍራቱ፣ ላመነው እውነት ብቻ መቆሙ፣ የሚመጣበትን ለመቀበል መዘጋጀቱ ግን ልክ ነው፡፡ ስለዚህ ሸልሜዋለሁ፡፡
አዳራሹ በጭብጨባ ተሞላ፡፡ ካህኑም መሬት ወድቆ እጅ ነሣ፡፡ ታሪክም ለእኛ እንዲህ ሲል አቆየን፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው

Source: Danielkibret