ልማትና ነጻነት


በመስፍን ወልደ ማርያም

 ከሰው ልጅ፣ ከአዳምና ከሔዋን ልጆች ውጭ ልማት የሚባል ነገር የለም፤ ከነጻነት ውጭ የልማት ምንጭና መሠረት የለም፤ የሰው ልጅና ነጻነት ዝምድና ከአዳምና ከሔዋን ይጀምራል፤ ሁላችንም እንደምናውቀው ልብስ መልበስ የጀመሩት፣ ምግብ ማምረት የጀመሩት በነጻነት ነው፤ ለሰው ልጅ ትልቁ ቁም-ነገር እርግማን የነጻነት ልጅ መሆኑ ነው፤ ያለእርግማን ነጻነትን ማሰብ አይቻልም፤ የሰው ልጅ ነጻነቱን አውጆ ከተመቻቸበት ከገነት ሲወጣ የገጠመው ነጻነትና እርግማን በአንድ ላይ ነው፤ ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው፤ ለነጻነት የተደረገ የትግል ምዕራፍ ነው።

Download

ሁለተኛው ምዕራፍ የሚጀምረው የሰው ልጅ ነጻነት ሲያጋልጠውና ሲያሳፍረው ልብስ ለመልበስ ቅጠል ቆርጦ ልብስ ሲሰፋ ነው፤ የሰው ልጅ ለነጻነት የከፈለው ዋጋ ራቁቱን መሆኑን ማወቁ ነው፤ ከዚያ በፊት ራቁቱን መሆኑንም አያውቅም ነበር፤ ሥራ የሚጀምረው የሰው ልጅ ይህንን እውቀት ካገኘ በኋላ ነው፤ ነጻነት ማለት ራስን መቻል መሆኑን የተገነዘበበት ምዕራፍ ነው።

ሦስተኛው ምዕራፍ የሰው ልጅ ነጻነቱ ያመጣበትን ጣጣ፣ ራስን መቻልና የተፈጥሮ ፍላጎቶቹን ሁሉ ለማሙዋላት መሥራትና ማምረት በስፋት የጀመረበት ነው፤ መሥራትና ማምረት ብዙ ነገሮችን ማወቅ፣ በእውቀት መራቀቅንና መመራመርን፣ የሥራ ዘዴዎችንና ጥበብን መፍጠርና አዳዲስ ሙያዎችን ማፍለቅ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

አራተኛው ምዕራፍ የሰው ልጅ በትግሉ ያገኘውን ነጻነት ይዞ የአእምሮውን ሙሉ ኃይል በሥራ ላይ በማዋል የዓለምን ምሥጢር ሁሉ የሚያጠናበትና በእውቀትና በጥበብ የሚራቀቅበት፣ መጨረሻው ወደማይታይበት የእውቀት ተራራ የሚጓዝበትን መንገድ ይዞ ሳይቆም የሚቀጥልበት ዓላማ ነው፤በማናቸውም አቅጣጫ የእውቀትና የእድገት ጉዞ ነው።

አምስተኛው ምዕራፍ ልክ እንደመጀመሪያው ምዕራፍ የትግል ምዕራፍ ነው፤ በዚህ ጉዞ ላይ ብዙ ፈተናዎችና ብዙ ትግሎች ያጋጥማሉ፤ ሰዎች በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚተባበሩ ቢሆኑም በብዙ ጉዳዮች ላይም ይፎካከራሉ፤ ሰዎች ከፍ ወደአለ የእውቀትና የእምነት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ በነጻነት ጉዳይ ላይ በጣም ይፎካከራሉ፤ ለምን? ነጻነት ኃይል በመሆኑ ነው።

እውቀት የሚፈልቀው፣ የሚዋለደውና የሚዳቀለው በአእምሮ ውስጥ ነው፤ ስለዚህም ለሰው ልጅ አእምሮው ዋናው ሀብቱ ነው፤ ይህንን የሀብት ማኅደር ሲጨምቁት፣ ሲኮተኩቱትና ሲያዳብሩት የእውቀትና የጥበብ ፍሬዎች ይበረክታሉ።

የእውቀትና የጥበብ ፍሬዎች የሚራቡትና የሚፈልቁት ከነጻ አእምሮ ውስጥ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ነጻ በሆነበት ማኅበረሰብ ከእያንዳንዱ ሰው የሚፈልቀው እውቀትና ጥበብ ከዚያ ማኅበረሰብ አልፎ ተርፎ ለሰው ልጅ በአጠቃላይ የሚያገለግል ይሆናል።

ከአገዛዞች ሁሉ የከፋው የማይታፈነውን የሰው ልጅን አእምሮ ለማፈን የሚሞክረው ነው፤ የአካል መታሰር የአእምሮ መታፈንን እንደማያስከትል በደርግ የአገዛዝ ዘመን በወህኒ ቤቱ ውስጥ የተቋቋመው ትምህርት ቤት ማስረጃ ነበር፤ በያመቱ በሚደረገው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አንደኛ ሲወጣ እንደነበረ እናውቃለን፤ ከዚያም በላይ ብዙ ሰዎች የተለያዩ ቋንቋዎችን — ግእዝ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ፣እንግሊዝኛ፣– ኢኮኖሚክስም፣ ታሪክም … ሌላም እየተማሩ እንደወጡ አውቃለሁ፤ በአንጻሩ በወያኔ ወህኒ ቤት ሕግ ለመማር፣ ሁለተኛም ኦሮምኛ ለመማር ጀምረን ተከልክለናል፤ ብዙዎቻችን የወያኔን ጸረ-እውቀት አመራር በተጨባጭ የተረዳነው ያን ጊዜ ነበር፤ አልተረዳነውም እንጂ ቀደም ብሎ የታወቁ አርባ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን ‹‹የችሎታ ማነስ›› ተብሎ ሲያባርር ጸረ- እውቀት እንደሆነ አመልክቶአል።

ቀደም ሲል ለማረጋገጥ የተሞከረው ነጻነት የእውቀትን በር በመክፈት ልማትን እንደሚያመጣ ነበር፤ ግን እውቀት መሰራጨት አለበት፤ እውቀት ወደተግባር ተለውጦ የሥራ ጥበብ ወይም የእውቀት ጥበብ (ቴክኖሎጂ) መሆን አለበት፤ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና ለመበልጸግ ነጻነት ግዴታ ነው፤ አምባ-ገነኖች ልማት ከነጻነት ይቀድማል እያሉ የሚሰብኩት ምንም እውነት የሌለበት ፈጠራ ነው፤ ይህንን አመለካከታቸውን ለማስፋፋት ምዕራባውያንን በገንዘብ እየደለሉ እንዲጽፉላቸው ያደርጋሉ፤ የሩቅ-ምሥራቅ አገሮችን ይጠቅሳሉ፤ በነዚህ አገሮች የቆዩ ባህላዊ አገዛዞችን ሥርዓቶች በደንብ ማጥናት ያስፈልጋል፤ መንፈሳዊ እሴቶቻቸውን ከክርስትናና ከእስልምና ጋር ማስተያየት ያስፈልጋል፤ በአንድ አምላክ የሚያምኑ ሕዝቦች በአሉባቸው አገሮች ሹሞችን አንደአምላክ የመመልከት ባሀል የለም።

ደርግና ወያኔ በሀብት ድልድል በኩል በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫኑት ቢለያይም ነጻነትን በማፈን ተመሳሳይ ነው፤ ደርግ ጥቂቱን ሀብታም አራቁቶ ብዙውን ደሀ ለመጥቀም ሞከረ፤ ደሀው በዛና አልሆነለትም፤ በተጨማሪም ደሀውም ሀብታሙም በአፈና ስቃይ አንድ ሆነ፤ ወያኔ በበኩሉ ጥቂቱን መናጢ ደሀ ሀብታም አደርጋለሁ ብሎ ብዙውን ደሀ አጥንቱ ድረስ ፋቀው፤ የሀብታሙ ደስታ በጭለማ ሆነ፤ የደሀውም ኡኡታ በጭለማ ሆነና አንድ ሆኑ፤ ሀብታሙ ሀብታም የሆነው በጭለማ፣ ደሀው ደሀ የሆነው በጭለማ፤ ደሀው ብርሃን እንዲመጣ ይፈልጋል፤ ሀብታሙ ጭለማውን ለማደንደን እየታገለ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s