Archive | June 5, 2014

ለዕምነት የሚከፈል ዋጋ

ከእስልምና ወደ ሌላ ዕምነት መቀየር ፍፁም የተከለከለ ነው፡፡ ዕምነት የሚፀናውም በአባት ነው፡፡ ልጆች ከሙስሊም አባት ከተወለዱ የእናታቸው ዕምነት እስልምና ካልሆነ በስተቀር የፍላጎታቸውን ዕምነት መከተል አይችሉም፡፡

Kenya

ከ70 በመቶ በላይ ሕዝቧ የእስልምና ዕምነት ተከታይ በሆነባት ሱዳን የሌላ ዕምነት ተከታይም ቢሆን ትዳሩን ሲመሠርት የሚዳኘው በእስልምና ሕግ ነው፡፡ ክርስቲያን ሆኖ ሙስሊሟን ቢያገባ ልጁን የማሳደግ መብት አይኖረውም፡፡ ሚስቲቱም ሃይማኖቱ የሚያዛትን እንደጣሰችና ዕምነት እንደቀየረች ተቆጥራ በወንጀል ሕግ ትዳኛለች፡፡

በሱዳን የእስልምና ሃይማኖትን በሌላ ዕምነት የቀየረ የሚፈረድበት ሞት ነው፡፡ በአፍጋኒስታንና በሌሎችም የእስልምና መንግሥት ያላቸው አገሮች እስልምናን ከመቀየር ጋር በተያያዘ የሚወስኑት የሞት ፍርድ ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሙስሊም አስተምርሆ ውስጥ ሆነው ባህላዊ አካሄድ ነው በማለት ቅጣቱ ሞት መሆን እንደሌለበት ከሚናገሩ፣ እንዲሁም ከሌሎች ዕምነት ተቋማት ጋር ሁሌም እንዳወዛገባቸው ነው፡፡

በመንግሥት ተቋማት ደረጃ ብቻም ሳይሆን የእስልምና እምነቱን የቀየረ ወይም የቀየረች ሲገኝ ወይም ስትገኝ በመደበኛ ፍርድ ቤት ደረጃ ሳይደርሱ በአካባቢያቸው ነዋሪዎች ፍርዱ የሚፈጸምባቸውም ቀላል አይደሉም፡፡ በተለይ ደግሞ ሴቶች የብትሩ ሰለባዎች ናቸው፡፡

ሰሞኑን በሱዳን ካርቱም አከራካሪና አነጋጋሪ ሆኖ የከረመው አጀንዳም ይኼው ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊት ክርስቲያን እናትና ከሱዳናዊ ሙስሊም አባት የተወለደችው ማርያም ያህያ ኢብራሂም ክርስቲያን ማግባቷ ከስህተት ተቆጥሮባት እስር ቤት እንድትገባ፣ 100 ጅራፍ እንድትገረፍና በሞት እንድትቀጣ እንዲወሰን ምክንያት ሆኖባታል፡፡

እ.ኤ.አ በ2011 አሜሪካዊ ዜግነት ካለው ሚስተር ዳንኤል ዋኒ ጋር ጋብቻ የፈጸመችው የ27 ዓመቷ ማርያም፣ የቤተሰብ አባል ጥቆማ ባደረገው መሰረት እስር ቤት የገባችው እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2014 ነበር፡፡ የእስልምናን ሕግ ተላልፋለች ተብሎ የሞት ፍርድ የተወሰነባት ደግሞ በግንቦት አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም የስምንት ወር ነፍሰ ጡር በመሆኗ የሞት ቅጣቱ ከወለደች ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲፈጸም ነበር ውሳኔ የተላለፈው፡፡

ማርያም በአባቷ ሙስሊም በመሆኗ እንደ ሙስሊም የምትቆጠር ቢሆንም፣ ዕምነቷ ክርስትና ነው፡፡ ሆኖም ክርስቲያንነቷን የአባቷ ሙስሊም መሆን ይሽረዋል፡፡ ክርስቲያን በማግባቷ ደግሞ በወንድ አያታቸው ሙስሊም የሆኑትን ልጆች ክርስቲያን አባት ማሳደግ አይችልም፡፡ በመሆኑም አንድ ዓመት ከስምንት ወራት የሆነውን ልጇን ይዛ ነው እስር ቤት የገባችው፡፡ ማርያም እስር ቤት በገባች በአምስት ወሯ ሴት ልጅ በሰላም የተገላገለች በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ጫና የበዛበት የሱዳን መንግሥት የማርያምን የሞት ፍርድ በቅርቡ እንደሚያነሳና ከእስር እንደሚፈታት አስታውቋል፡፡

በተለይ የሴቶችን በሞት መቀጣት የማይቀበለው አብዛኛው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በማርያም ላይ የተፈረደውን ሞት ለማስቀልበስ ደፋ ቀና ሲል ከርሟል፡፡ በካርቱም ያሉ ሱዳናውያንም ነፍሰ ጡር የሆነችው ማርያም ሞት አይገባትም በማለት ለተቃውሞ ሠልፍ ወጥተዋል፡፡

ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ከአገር ውስጥ ጫና የበዛበት የሱዳን መንግሥት በሴቶች እስር ቤት ውስጥ ሴት ልጇን ባለፈው ሳምንት የተገላገለችውን ማርያም እንደሚፈታ አስታውቋል፡፡

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ፍርድ ቤቱና የፍትሕ ሚኒስቴር በሚያዘው መሠረት ትፈታለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ አብዱላህ አል አዝራቅ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማብራራት ቢቆጠቡም የሞት ፍርዱ እንደማይፀናባት ተናግረዋል፡፡

የሞት ፍርድ ከመወሰኑ በፊት ጋብቻዋ የተሰረዘባት ማርያም ወደ እስልምና ሃይማኖት እንድትመለስም የሦስት ቀናት ጊዜ በፍርድ ቤቱ ተሰጥቷት ነበር፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ክርስትናን ተከትላ ማደጓን በመግለጽ ዕምነቷን ለመቀየር ፈቃደኛ ባለመሆኗም ሞት ተፈርዶባታል፡፡ የሱዳን መንግሥት ከእስር እንደሚፈታት መግለጹን ተከትሎ ጠበቃዋ መሐመድ ሙስጠፋ ከአልጄዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይግባኝ ሲያቀርቡ አልተሟላም ተብለው የጊዜ ቀጠሮ እንደተላለፈና የመጨረሻው ውሳኔ እስካልታወቀ ድረስ የመንግሥትን ገለጻ እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡

ሚስተር ሙስጠፋ እንደሚሉት ፍርድ ቤቱ ነፍሰ ጡር በነበረችው ማርያም ላይ የሞት ፍርድ መወሰኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገሪቱ እንድትወቀስ አድርጓል፡፡ በሌላም በኩል የዕምነት መብት መከበር አለበት በማለት ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጉትጎታው አይሏል፡፡ ውሳኔው በአገር ውስጥም ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ፊርማ እያሰባሰቡ ነው፡፡ ይህንን ከግምት ያስገባው የሱዳን መንግሥት የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አመለካከት ለመቀየር ብቻ የተናገረው ነው ብለዋል፡፡

ባለቤቷ ዋኒ በበኩሉ የሞት ፍርዱ ስለመነሳቱም ሆነ ከእስር እንደምትፈታ መረጃ እንዳልደረሰው ገልጿል፡፡ ባለፈው ሳምንት ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታም መረጃ አልተሟላም ተብሎ የጊዜ ቀጠሮው ተላልፏል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የወጡ መረጃዎችም ማርያም ልትፈታ የምትችለው በይግባኙ አሳማኝነት ብቻ እንደሆነ ያሳያሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩም ማርያም የምትፈታው በሕግ ፊት ተቀባይነት ያለውና ውጤታማ ይግባኝ ሲቀርብ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኦንዱርማን የሴቶች እስር ቤት ውስጥ የምትገኘውን ማርያም ከሞት ለመታደግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤክስፐርቶች በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸም ያልተገባ ድርጊት በማለት ውሳኔውን ተቃውመውታል፡፡ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሩ ማርያም ትፈታለች ብለው ከመናገራቸው አስቀድሞም የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር፣ የሱዳን መንግሥት የተላለፈውን የሞት ፍርድ እንዲያነሳ ጠይቀው ነበር፡፡

ሚስተር ካሜሮን ‹‹በማርያም ላይ የተፈረደው ሞት አሁን ባለንበት ዓለም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ ጭካኔ ተሞልቶበታል፤›› ብለዋል፡፡ ሚስተር ብሌር በበኩላቸው፣ ‹‹እምነትን ማዛባት›› ሲሉ ድርጊቱን ኮንነውታል፡፡ ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው የእንግሊዝ መንግሥት ሱዳን የሞት ፍርዱን እንድትቀለብስ ግፊት አድርጓል፡፡

ሚስተር አል አዝራቅ ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማርያም እንድትፈታ የሚያደርገው ተፅዕኖ በውሳኔው ላይ የጎላ እንዳልሆነ፣ ሆኖም የአገራቸው መንግሥት የሃይማኖትን ነፃነትን ለማስጠበቅና ማርያምን ለመከላከል ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ውስብስብ ነው፡፡ ጎሳንና ማኅበራዊ ሕይወትን ይነካካል፡፡ በመሆኑም የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ አይሆንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ማርያም በቅርቡ ከእስር እንደምትፈታ በሱዳን መንግሥት የተነገረ ቢሆንም ለጊዜው የታየ ነገር የለም፡፡

ethiopianreporter.com