20ኛውን የዓለም ዋንጫ ምን ልዩ ያደርገዋል?


world cop 2

ደቡብ አሜሪካ እና አውሮፓ ይፋጠጡበታል፤ 9.6 ቢሊዮን ዶላር  የሚያወጡ ተጨዋቾች ይሳተፉበታል፤ ከ5 በላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አራቅቀውታል፤  በኢንተርኔት ማህበረሰብ ድረገፆች ተሟሙቋል
20ኛው ዓለም ዋንጫ ባለፈው ሐሙስ ብራዚል እና ክሮሽያ በሳኦ ፓውሎ በሚገኘው ኮረንቲያስ ስታድዬም ባደረጉት የመክፈቻ ጨዋታ ተጀምሯል፡፡ 30 ደቂቃ የፈጀው የዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ስነስርዓት በ7.6 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተዘጋጅቷል፡፡ ትናንት ምሽት ሜክሲኮና ካሜሮን ሲገናኙ፤ ሌሎቹ  ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የ19ኛው የዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ስፔን እና ሆላንድ የተገናኙበትና ቺሊ ከአውስትራሊያ የተጋጠሙባቸው ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መታየት ያለባቸውን ለመጠቆም ያህል፤ ዛሬ  እንግሊዝ ከጣሊያን፤ ነገ አይቬሪኮስት ከጃፓን፤ ሰኞ ጋና ከአሜሪካ፤ ማክሰኞ  ጀርመን ከፖርቱጋል፤ ረቡዕ ብራዚል ከሜክሲኮ፤ ሐሙስ ኡራጋይ ከእንግሊዝ ይገናኛሉ፡፡

በቴክኖሎጂ ድጋፍ ዳኞች ይራቀቃሉ፤  ማህበረሰብ ድረገፆች በመረጃ ያሟሙቃሉ
20ኛው ዓለም ዋንጫ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ በመራቀቅ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ለውጥ እየታየበት ነው፡፡ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች ለስፖርት አፍቃሪው በርካታ መረጃዎችን በማቅረብ በአስደናቂ ሁኔታ ተሟሙቋል፡፡
የመጫወቻዋ ኳስ “ብራዙካ” ባላት የቴክኖሎጂ ጥራት የምንግዜም ምርጥ የዓለም ዋንጫ ኳስ ተብላለች። “ብራዙካ”ኳስ ያቀረበው ከእግር ኳስን ጋር በአጋርነት በመስራት ከ60 ዓመት በላይ የቆየው የጀርመኑ አዲዳስ ነው፡፡ አዲዳስ ለዓለም ዋንጫ አዲስ የኳስ ምርት ሲያቀርብ የዘንድሮዋ “ብራዙካ” 12ኛዋ ናት፡፡
በብራዙኳ ኳስ አመራረት ላይ ከተጨዋቾች ሊዮኔል ሜሲና ሴባስትያን ሸዋንስታይገር፤ ከክለቦች የአውሮፓዎቹ ባየርሙኒክና ኤሲሚላን እንዲሁም የብራዚሎቹ ክለቦች ፖልሚራስና ፍልሎሚንሴ በተግባር ሙከራዎች ተሳትፈዋል፡፡ በአጠቃላይ የብራዙካን ብቃት አስተማማኝ ለማድረግ አዲዳስ 287 የዓለማችን ምርጥ ተጨዋቾችን አስተያየት በመጠየቅ ሰርቷታል፡፡ በፓኪስታን ሲየልኮት በተባለች ስፍራ በሚገኘው የፎርዋርድ ስፖርት ፋብሪካ ተመርታለች፡፡
በሌላ በኩል  በአዲዳስ እና ናይኪ ኩባንያዎች ለተጨዋቾች የቀረቡ ታኬታዎች ለኳስ ቁጥጥር እና ምት የሚመቹ ሆነው ተዘጋጅተዋል፡፡ ከሞቃታማው የብራዚል አየር የሚታደጉ እና በልዩ ቴክኖሎጂ ሰውነት የማቀዝቀዝ ብቃት ያላቸው ማልያዎችና ሙሉ የስፖርት ትጥቆችም ቀርበዋል፡፡ ከሁሉም ግን የውድድር ዳኞች በተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በመታገዝ በአስተማማኝ ሁኔታ ግጥሚያዎችን እንዲመሩ በማስቻል ዓለም ዋንጫውን ልዩ ገፅታ አላብሰዋል፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂ አፈፃፀምም የሚያጓጓ ነው፡፡ የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂው በ12 ስታድዬሞች በሚገኙ 24 የግብ መረቦች ላይ ይገጠማል። በእያንዳንዱ መረብ ላይ 7 ካሜራዎች የሚገጠሙ ሲሆን እነዚህ ካሜራዎች በሰከንድ አምስት መቶ ምስሎችን በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመቱ ኳሶችን ተከታትለው ይቀርፃሉ፡፡ የመሃል ዳኞች አንዳንዴ ለውሳኔ የሚቸገሩበትን ሁኔታ ለማስቀረት፤ የግብ መስመር ያለፉ ወይም ያላለፉ ኳሶችን ለማፅደቅ እና ለመሻር ፤ የሰው ልጅ አይኖች በሰከንድ 19 ምስሎች መመልከታቸውን በማሻሻል የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይገለፃል፡፡ ወደ ጎል የተመታች ኳስ የግብ መስመሩን ስታልፍ የመሃል ዳኛው ያሰረው ሰዓት ላይ ከንዝረት ጋር ጎል የሚለው መልክት ይበራለታል፡፡ የጎል ማረጋገጫ ቴክኖሎጂውን የሰራው የጀርመን ኩባንያ ጎልኮንትሮል የመሳርያዎቹን ብቃት ለመለካት በብራዚል ብቻ 2400 ሙከራዎች ያለአንዳች ስህተት ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በዓለም ዋንጫው 33 የመሃል ዳኞች ጨዋታዎችን የሚመሩ ሲሆን በእያንዳንዱ 40 ሰከንድ ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ የስራ ጫና አለባቸው፡፡
የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂው ይህን የዳኞች ከባድ ሃላፊነት በማገዝ እንደሚጠቅም ተጠብቋል፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአንድ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜ የሚሸፍነው ከ7 እስከ 12 ማይሎች ርቀት ከምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋች 7 ማይሎች ርቀት ይልቃል፡፡ ምርጥ ዳኞች ከፍተኛው ፍጥነታቸው 20.7 ማይል በሰዓት ሲሆን የልብ ምታቸው በደቂቃ እስከ 160 ምቶች ነው፡፡ የግብ ማረጋገጫ ቴክኖሎጂ በአንድ የዓለም ዋንጫ ስታድዬም ለመግጠም 260ሺ ዶላር የሚጠይቅ ሲሆን በአንድ ጨዋታ ተግባራቱን ለማከናወን 3800 ዶላር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የተነሳም ቴክኖሎጂው ከዓለም ዋንጫ ውድድር ውጭ ተግባራዊ ለማድረግ ይከብዳል፡፡
ሌላውም የዓለም ዋንጫው ቴክኖሎጂ ለዳኞች ስራ መቀላጠፍ የተሰራ ነው፡፡ ቅጣት ምትን የሚመታበት ቦታ ምልክት የሚደረግበትና ግድግዳ በመስራት ለመከላከል የሚቆሙ ተጨዋቾችን ለመገደብ የሚሰመርበት “ቫኒሺንግ ስፕሬይ” ነው፡፡ ከተሰመረበት በኋላ በንኖ ለመጥፋት ከ45 እስከ 2 ደቂቃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በአርጀንቲናዊ ጋዜጠኛ የተፈለሰፈ ሲሆን በመላው ዓለም ተሞክሯል፡፡
ዓለም ዋንጫው በታዋቂዎቹ የኢንተርኔት ማህበረሰብ ድረገፆች ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ዩቲውብ፤ ኢንስታግራም እና ሌሎችም ላይ በሚኖረው ሽፋን ዲጂታል ዓለም ዋንጫ ሆኗልም እየተባለ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ሰሞን 8.8 ቢሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በሚያደርጉት የመረጃ ክትትል የሚፈጠረው መጨናነቅ በሪከርድ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡ ከዓለም ህዝብ 90 በመቶው ዓለም ዋንጫውን በማህበረሰብ ድረገፆች እየተከታተለ ሲሆን በ203 አገራት የስርጭት  ሽፋን ያላቸው የማህበረሰብ ድረገፆኙ በዓለም ዋንጫው ደንበኞቻቸውን ለማብዛት የተለያዩ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ፕሮግራሞችን በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
የማህበረሰብ ድረገፆቹ በዓለም ዋንጫው በቲቪ ከሚሰሯቸው ማስታወቂያዎች በተሻለ ስኬታማ መሆናቸውንም እየገለፁ ናቸው፡፡ የትዊተር ሃላፊዎች እንደገለፁት ገና ዓለም ዋንጫው ሳይጀመር ስለውድድሩ በሰፈሩ መልዕክቶች ከ4 ዓመት ደቡብ አፍሪካ ካስተናገደችው 19ኛው ዓለም ዋንጫ የላቀ ተከታታይ አፍርተዋል፡፡ፊፋ ለ23ኛው ዓለም ዋንጫ የከፈተው ኦፊሴላዊው የፌስቡክ ድረገፅ እስካሁን ከ20 ሚሊዮን በላይ ወዳጆች ያፈራ ሲሆን  ኦፊሴላዊ የትዊተር ድረገፁ ደግሞ  እስከ 5 ሚሊዮን ተከታዮች አፍርቷል፡፡ የማህበረሰብ ድረገፆችን ከሚጠቀሙ 1.2 ቢሊዮን የዓለም ህዝቦች 40 በመቶው ያህሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s