Archive | July 2014

ሦስት የኢቴቪ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራቸው ለቀቁ Three ETV senior officials Resigned

ashber2

በ ፍሬው አበበ (ሰንደቅ ጋዜጣ)
በርካታ ጋዜጠኞች በለውጡ ደስተኞች ሆነዋል
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት) ሦስት ከፍተኛ ኃላፊዎች በቅርቡ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር የነበረው ጋዜጠኛ አሸብር ጌትነት፣ የትምህርታዊ ፕሮግራሞች ክፍል ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ተመስገን ገ/ህይወት፣ የመዝናኛ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበረው አቶ ፍቅር ይልቃል በወራት ልዩነት ድርጅቱን መልቀቃቸው ታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ከጥር ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ከኃላፊነታቸው ተነስተው በኢቴቪ ከተሾሙ በኋላ የድርጅቱን የአሠራር ሥርዓት ለማስተካከል የወሰዱት ጠንካራ እርምጃዎች በኃላፊዎቹ እንዳልተወደደ ምንጮች ተናግረዋል።
በኢቴቪ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሚደረጉ የውጪ አገር ጉዞዎች በጥቂት ግለሰቦች ሞኖፖሊ ብቻ ተይዞ የቆየ ሲሆን፤ አዲሱ ዳይሬክተር ይህን አሰራር በመሰረዝ የሚመለከታቸው ሪፖርተሮች በየተራ ተመድበው እንዲሰሩበት ማድረጋቸው፣ አንዳንድ ኃላፊዎች የጥቅም ግጭት በሚያስከትል መልኩ ኢቴቪ ውስጥ እየሰሩ በግል ድርጅታቸው አማካይነት ሥራዎችን ለመወዳደር ማመልከታቸውና ይህም ተቀባይነት ማጣቱ፣ እንዲሁም ለሙስናና ብልሹ አሰራር ክፍት የነበሩ አሰራሮች እየተዘጉ መምጣታቸው ኃላፊዎቹን ሳያበሳጭ እንዳልቀረ ምንጮቹ ጠቁመዋል።
አንድ የድርጅቱ ባልደረባ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገረው፤ አዲሱ ማኔጅመንት ሥር ነቀል ለውጥ እያደረገ መምጣቱ በአብዛኛዎቹ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ዘንድ ድጋፍ ማግኘቱን ተናግረዋል። አንዳንድ ኃላፊዎች ያለ ችሎታቸው ጭምር ተመድበው የሚሰሩበት ሁኔታ እንደነበርና ይህም በሰራተኛው ዘንድ ቅሬታ ሲቀርብበት ነበር ያሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ ይህ ሁኔታ አሁን እንዲስተካከል መደረጉ አስደስቶናል ብለዋል። በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ የሚካሄደው ለውጥ በዚሁ ከቀጠለ በቀጣይ ሕዝባዊ ሚዲያ ለመፍጠር የሚያስችል ይሆናል ብለው እንደሚገምቱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የዋና ዳይሬክተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝን በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ደረጃ እንዲያድግ የሚደነግገውን አዋጅ ተቀብሎ ማጽደቁ ይታወሳል።

የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሕወሓት መንግስት ከ3 ቀን በፊት በቲቪ በማሳየት ላቀረበው ቪድዮ ምላሽ ሰጡ

የግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሕወሓት መንግስት ከ3 ቀን በፊት በቲቪ በማሳየት ላቀረበው ቪድዮ ምላሽ ሰጡ። ቪድዮው የተዘጋጀው የሰውን አንገት ለማስደፋትና ለፕሮፓጋንዳ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ብርሃኑ በአቶ አንዳርጋቸው እጅ ምንም ዓይነት ምስጢሮች እንደሌሎ ተናግረዋል። አቶ አንዳርጋቸው ሰጥተውታል ለተባለው ፓስወርድም “የኦፕሬሽናል ጉዳዮችን የያዘ ፓስወርድ አይደለም፤” ያሉት ዶ/ር አንዳርጋቸው የሰጠው ፓስወርድ የተለያዩ ጥናቶችን የያዘ እንጂ ወያኔ ቢያገኘውም ባያገኘውም ምንም የሚጎዳ ነገር አይደለም ብለዋል። ዶ/ሩ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር በኢሳት ቲቪ የተነጋገሩበት ቪድዮ ይኸው።

ፖሊቲካና የግለሰብ ጠባይ

Download

መስፍን ወልደ ማርያም

ለእኔ ፖሊቲካና የግለሰብ ጠባይ እንደውሃና ዘይት የማይደባለቁ ነገሮች ይመስሉኛል፤ አጼ ምኒልክ ‹‹አመልህን በጉያህ›› ያሉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ ዘይትና ውሀ በባሕርያቸው የሚለዩትን ያህል ፖሊቲካና ግለሰብም የባሕርይ ልዩነት አላቸው ማለት ነው፤ የወያኔ መሪዎች ምንም ነገር የማይሰምርላቸው፣ ከመጀመሪያውኑ እነዚህን ሁለት የማይደባለቁ ባሕርዮች አደባልቀው በመንሣታቸው ነው፤ ፖሊቲካ ለማኅበረሰቡ መቆርቆር ነው፤ ለሕዝቡ መቆርቆር ነው፤ ለአገር መቆርቆር ነው፤ የፖሊቲካ መነሻም ይኸው መሆን አለበት፤ ዓላማውም የማኅበረሰቡ፣ የሕዝቡ ልማት እንጂ ጥፋት አይደለም፤ የነበረውንና ያለውን ማጥፋት የፖሊቲካ ዓላማ ሊሆን አይችልም።

የደርግ መንደር ምሥረታ የሕዝብ ዓላማ ነበረው፤ የዓላማው መሣሪያ ግን የሕዝብ ሳይሆን ወታደራዊ ጉልበት ነበር፤ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ዓላማ ያለው ሥራ የሕዝብን ህልውና በሚፈታተን የጉልበት መንገድ መከተሉ ዓላማው እንዳይሳካ፣ ሕዝብና አገዛዙ ባላንጣዎች ሆኑ፤ ጥሩው ዓላማ በከሸፈ ጉልበተኛነት ሳይሳካ ቀረ፤  በመንደር ምሥረታው ዓላማ ደርግ ክፋት ወይም ቂም ቋጥሮ አልተነሣም፤ ስሕተቱ ከውትድርና ባሕርይ የመጣ ይመስለኛል፤

ማጥፋት ዓላማ ሲሆንና ጉልበት የማጥፋት መሣሪያ ሲሆን ፍጹም የተለየ ነው፤ማጥፋት የሚመጣው ከግል ጠብና ከግል ቂም ነው፤ የራሱን ወይም የአባቱን፣ ወይም የእናቱን ቂም በልቡ ቋጥሮ ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባ ሰው ለጥፋት የተዘጋጀ ነው፤ ለጥፋት የተዘጋጀ ሰው ፖሊቲካ ውስጥ ሲገባ እሳት አደጋ መኪና ላይ ቆሞ ቤት እንደሚያቃጥል ሰው ነው፤ አታላይ ነው፤ ዓላማውንም የዓላማውንም መሣሪያ አያውቅም፤ የሚንቀሳቀሰው በጥላቻና በቂም ነው፤ ወይ የሕጻን ልጅ ወይም የተስፋ-ቢስ ደደብ ጠባይ ነው፤ እንዲህ ያለ ሰው ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባውም በዚሁ በደደብነቱ ምክንያት ነው፤ የደደቡ ፖሊቲከኛ ሥራ የማያስወቅሰው ፖሊቲከኛውን ብቻ አይደለም፤ በዚያ ፖሊቲከኛ የሚመራው ሰው ሁሉ አብሮ የሚወቀስ ነው፤ እንዲያውም በፖሊቲከኛው እውቀትና ችሎታ ማጣት የተነሣ የሚደርሰው ስቃዩና መከራው፣ ችግሩና አበሳው በዚህ ዓይነቱ ፖሊቲከኛ ላይ አይደርስም፤ ሰቃዩንና መከራውን፣ ችጋሩንና አበሳውን የሚጋፈጠው በዚህ ዓይነቱ ፖሊቲከኛ የሚመራው ሕዝብ ነው፤ ሕዝብ መሪውን በትክክል መምረጥ ያለበትም ለዚህ ነው፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ የሚባለው ይደርሳል።

ዛሬ እያጎረሰ ምረጠኝ የሚለው ነገ ቆዳህን ልግፈፍ ይላል፤ እንደምንሰማው ወደቦሌ አካባቢ ‹መቀሌ› የሚባል የሰማይ-ጠቀስ ፎቆች መንደር አለ ይባላል፤ የዚህ መንደር ባለቤቶች የወያኔ ባለሥልጣኖች ለመጦሪያቸው የሠሩአቸው ናቸው ይባላል! በአንጻሩ እኔ የማውቀው አንድ ወያኔ አለ፤ በውጊያ ላይ በደረሰበት ጉዳት ይመስለኛል አንድ ዓይኑን ክፉኛ የታመመ ነው፤ ስለሚሸፍነው የጉዳቱን መጠን ባላውቅም ጉዳቱ ይሰማኛል፤ ሚስትና ሁለት ልጆች አሉት፤ ሚስቱ ጠዋት በጀርባዋ ከባድ ነገር አዝላ ልጆቿን ወደተማሪ ቤት ታደርሳለች፤ እንደምገምተው አንድ ቦታ ገበያ ዘርግታ የምትሸጠውን ትሸጣለች፤ ወደማታም እንደጠዋቱ ተጭና ወደቤትዋ ከልጆችዋ ጋር ትመለሳለች፤ የዚህ አንድ ጉዳተኛ ወያኔ ቤተሰብና የባለሰማይ-ጠቀስ ሕንጻ ባለቤቶች የሆኑት ወያኔዎች ኑሮ የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቀ ነው፤ ለአንድ ዓላማ አብረው የተነሡ ሰዎች በሃያ ዓመታት ውስጥ ይህንን ያህል መራራቃቸው በጣም ያሳዝናል ብሎ ማለፉ አይበቃም፤ ደሀው ወያኔ ሕመሙንና ስቃዩን የምገነዘብበት መንገድ ባይኖረኝም አንድ ዓይኑን ማጣቱ ብቻ ጉዳቱን ያሳየኛል፤ እንግዲህ ባለሰማይ-ጠቀስ ወያኔዎችና ይህ ደሀ ወያኔ በጦርነት ላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ በጉዳታቸው ቢመዘን የዚህ ደሀ ወያኔ እንደሚበልጥ አልጠራጠርም፤ ቢያንስ እንደአንዳንድ መሪዎቹ አልሸሸም፤ ታዲያ በምን ተበላልጠው እነሱ እዚያ ላይ እሱ እዚያ ታች ሆኑ? ይህንን አሳዛኝና አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ሁነት የሚያመጣው እሳት አደጋ መኪና ላይ ቆሞ ቤት እንደሚያቃጥለው ሰው ያሉ ፖሊቲከኞች-ነን-ባዮች የተዛባ ሚዛን ነው፤ በዚህ የተዛባ ሚዛን በየጦር ሜዳው አሞራ የበላቸው የታደሉ ናቸው፤ ተስፋቸው ትርጉም አጥቶ ሳያዩ፣ ውርደት ሳይሰማቸው፣ ችግርንና ግፍን ሳይቀምሱ ቀርተዋል፤ ለነገሩ ነው አንጂ እንኳን ወያኔ በሥልጣን ምኞት ከወገኑ ጋር የተዋጋውና ከኢጣልያ ወራሪ ጦር ጋርም የተዋጉት አርበኞችም ተመሳሳይ ዕድል ገጥሟቸው ነበር፤ ዛሬ ኢትዮጵያን ለክፉ ነገር የዳረጋት የእነዚህ ሰዎች ጡር ይመስለኛል።

የፖሊቲካ ተግባሮቻቸውን ከግል ጠባዮቻቸው እየለዩ የሚኖሩ ፖሊቲከኞች በአንዳንድ አገር አሉ ለማለት ይቻላል፤ ከአውሮፓ ስዊድንና ኖርዌይ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ከእስያ ዛሬን እንጃ እንጂ በነኔህሩ ዘመን ህንድ የሚጠቀስ ነበር፤ በአብዛኞቹ አገሮች ግን ፖሊቲከኞቹ እንደየደረጃቸው ለሀምሳ፣ ለሠላሳ፣ ለሀያ፣ ለአሥር ሰዎች የሚበቃ የተሟላ ቤት ውስጥ አምስት መቶ ሰዎችን የሚያስተዳድር ደመወዝ እያገኙ የሚኖሩ ሲሆኑ ምግባቸው ግን አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ሰው ይመስለኛል፤ የዚህ ትርጉሙ ምንድን ነው? ለፖሊቲከኞቹ መቀማጠል በላባቸው የሚከፍሉት ደሀዎች ናቸው፤ ከተፎካካሪዎቻቸው ተንኮል የሚጠብቋቸው ደሀዎች ወታደሮች ናቸው፤ ምርጫ ሲደርስ በነቂስ ወጥተው ፖሊቲከኞቹን የሚመርጧቸው ጦማቸውን የሚያድሩት ደሀዎች ናቸው፤ እነዚህም ጊዜያዊና ትንሽ የግል ጥቅምን ከዘላቂው የአገርና የሕዝብ ጥቅም መለየት ያልቻሉ የሕዝብ ክፍሎች ከተበላሹት ግለኛ ፖሊቲከኞች የማይለዩ ናቸው።

ወደፍሬ ነገሩ ልምጣና፤- በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖሊቲከኞች የሚወጡትና የሚወርዱት ለየትኛው ዓላማ ነው?

  1. የበትረ መንግሥቱን ሥልጣን ከወያኔ ፈልቅቆ ለማውጣትና ለመያዝ?
  2. በምክር ቤት ገብቶ የወያኔ አጫፋሪ በመሆን ደህና ደመወዝና ነጻ ቤት ለማግኘት?
  3. ከውስጥ ሆኖ ወያኔን ለማጋለጥ?

የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖሊቲካ ቡድኖችን ሲደግፍ የፖሊቲካ ቡድኖቹን ዓላማዎች አጣርቶ በማወቅ መሆን አለበት፤ አለዚያ በሎሌነት እየኖሩ ጌታ መለወጥ ነው።

 

ሱዳናዊቷ የሞት ፍርድ ፍርደኛ ማርያም ኢብራሂም ከአውሮፕላን ስትወርድ የግብረ ሶዶማውያን ዋና መለያና ሰንደቅ አላማ የሆነው የሬንቦን ቲሸርት በመልበስ ቫቲካን ያደረገችላትን ውለታ አስታወሰች::

ሱዳናዊቷ የሞት ፍርድ ፍርደኛ ማርያም ኢብራሂም ከአውሮፕላን ስትወርድ የግብረ ሶዶማውያን ዋና መለያና ሰንደቅ አላማ የሆነው የሬንቦን ቲሸርት በመልበስ ቫቲካን ያደረገችላትን ውለታ አስታወሰች::

Meriam_2985211k

meriam_yahia_and_pope
በሼርያ ህግ የሞት ፍርድ የተፈረደባት የ 27 አመቷ የሁለት ልጆች እናት ሱዳናዊቷ ማርያም ኢብራሂም ትናንት ሮም ቫቲካን በካሳ ሳንታ ማርታ የቫቲካን እንግዳ ማረፍያ ከሮማው ሊቀነ ጳጳስ ፍራንሲስ ጋር ተገናኘች::

በቢንያም መንገሻ 

ሱዳናዊቷ ማርያም ኢብራሂም በግንቦት ወር የአገሪቱ ሼሪያ ፍርድ ቤት ሙስሊም የነበረውን የልጆቿን አባት ቧሏን ወደ ክርስትና ሀይማኖት ለውጠሻል በማለት 100 የጅራፍ ግርፋትና የሞት ቅጣት ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን:: የሞት ቅጣት ውሳኔውን ተከትሎ አለም የተጫጫበትና የወቅቱ ጥሩ ዜና ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል:: ስለሆነም ብርቱ የሆነ ሀይማኖታዊና ፓለቲካዊ ዲፕሎማሲ አማካኝነት የማርያም ኢብራሂም ከግርፋትና ከሞት ቅጣ ነጻ ወጥታለች :: ነገር ግን ማርያም ኢብራሂምና ቤተሰቧ ከተፈረደባት የሞት ፍርድ ነጻ እንደወጣች ወድያውኑ ከመላው ቤተሰቧ ጋር ከሀገር በመውጣት ላይ እንዳለች ከኤርፓርት በሱዳን መንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተመለሰች ሲሆን ለአንድ ወር ያህልም በካርቱም የአሜርካ ኤንባሲ ከነቤተሰቧ ተጠልላለች:: ስለሆነም ከሱዳን መንግስት ጋር የነበረው የሀይማኖታዊ ዲፕሎማሲ የማርያም ጉዳይ ስላለቀ ትናንት ረፋዱ ላይ ማርያምና ቤተሰቧ በጣሊያኑ አየር መንገድ አውሮፕላን በሆነው አሊኢታሊያ ወደ ሮማ አቅንተዋል:: በትልቁ የጣሊያን አለም አቀፍ ኤርፓርት በሻምፒዮን እንደደረሰች የጣሊያን ትላላቅ የመንግስት ባለስልጣናትና የቫቲካን ካቶሊክ አቀባበል አድርገውላታል::
ማርያም ኢብራሂም ከአውሮፕላን ስትወርድ የግብረ ሶዶማውያን ዋና መለያና ሰንደቅ አላማ የሆነው የሬንቦን ቲሸርት መልበሷ ደግሞ እኔን አሰደምሞኛል የተፈጠረውንም የሀይማኖታዊ ዲፕሎማሲ በጥልቀት እንዳየው አድርጎኛል::
Meriam_2985211k
ሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ከሀይማኖቶች ሁሉ ግብረሰዶምን በአንደኛ ደረጃ የምትደግፍ ሲሆን ብዙዎች የካቶሊክ ቄሶች የዚህ ጸያፍ ክፉ መንፈስ ዋናዎቹ ተሸካሚዎችና አስተላላፊዎች ናቸው::
Homo (3)
የሮማው ሊቀነ ጳጳስ ፍራንሲስ የግብረ ሶዶማውያን ዋና መለያና ሰንደቅ አላማ የሆነው የሬንቦን ያለበትን የእጅ አንባር ብዙግዜ በይፋ የሚያደርጉ ሲሆን እሳቸውም ይህንን እርኩሰት በይፋ ይደግፋሉ::
464338699

10271199_319594294860925_7157337756490590646_o

Francesco-May-31-2014-02

media-621439-7
ማርያም ኢብራሂም ከተፈረደባት የሞት ቅጣት ነጻ የወጣችው እንደ እኔ እምነት የካቶሊክ እምነት ሀይማኖት ተከታይ ስለሆነች ነው:: ምክንያቱም ካቶሊክና ኢስልምና በጣም የተቆራኘ የእምነት አንድነት ስላላቸው ነው:: ለዚህም ደግሞ “ ሮማ ካቶሊክ የእስልምና እምነትን ብቸኛ ፈጣሪ ነች” የሚለውን ጥናታዊ መረጃ እውነት ያደርገዋል:: ስለዚህ አባባል ከዚህ ቀደም በሁለቱ በካቶሊክና በኢስላም ሀይማኖቶች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ማቅረቤ ይታወሳል ለማየት ከወደዱ በእዚሁ መጦመሪያ ውስጥ ያገኙታል::

https://binjaminia.wordpress.com/2014/07/07/6-2/

ማርያም ኢብራሂም የትክክለኛውን መንገድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ብትሆን ቅጣቷ ምን የሚሆን ይመስላችኋል?
ማራናታ !

“መኖር ወይስ አለመኖር፣ To be or not to be” በውቀቱ ስዩም

Shakespeare_ToBeOrNotToBe

ሐምሌት በተባለው የሸክስፒር ተውኔት ውስጥ፣to be or not to beብሎ የሚጀምር ዝነኛ ያንድ ሰው ንግግር አለ፡፡ሐምሌት የሚያነሣውን ጥያቄ ከእለታት አንድ ቀን ርስዎም ያነሡታል፡፡እናም ይሄን ሳስብ ፣የጸጋየ ገብረመድህንን አሪፍ ትርጉም ልጋብዝዎት ፈልጌ ነበር፡፡እንዳለመታደል ሆኖ የጸጋየ ትርጉም ከመደርደርያ ላይ አልተገኘም፡፡እንደመታደል ሆኖ ግን ራሴ ለምን አልተረጉመውም የሚል ሐሳብ መጣልኝ፡፡የሸክስፒርን እንደ ቅርስ ቤተመዘክር ውስጥ የተቀመጠ የድሮ እንግሊዝኛ፣ ቃል በቃል ወደ አማርኛ ለመመለስ አልቃጣም፡፡ፍሬ ነገሩን ወስጄ፣እንደሚከተለው ሞክሬዋለሁ፡፡
To be or not to be
የኑሮን ትርጉም የምትሹ
መኖር ወይስ አለመኖር፣
ይህ ነው እንቆቅልሹ
መድከም፣
የኑሮን ቀንበር መሸከም
ወይስ ፣
ህይወት ሚሉትን ደዌ፣በሞት ወጌሻ ማከም?
የርጅናን ንቀት ልግጫ
የጌቶችን ርግጫ
የከሸፈ ፍቅርን ጡጫ
የጉልቤውን እብሪት ናዳ
በቀልደኛ ዳኞች ችሎት
ውሀ መልስ፣ ውሀ ቅዳ
ይህን ሁሉ ፣የኑሮ እዳ

ችሎ፣
አሜን ብሎ
መቀጠል
ወይስ ራስን በራስ ማንጠልጠል
መሞት ፣ማንቀላፋቱ
ማራገፍ፣ሥጋን ከነክፋቱ
ቢቻልማ፣መልካም ነበር
ግና በሰው
ያልታሰሰው
የመቃብር ፣ስውር አገር
የሄዱትን ውጦ ሚያስቀር፣ዜናው እንዳይነገር
ግርማው ወኔ ያሳጣል
ከማታውቀው ወለላ ሞት፣ሬት ኑሮን ያስመርጣል፡፡

ሰውና ልማት

Download

መስፍን ወልደ ማርያም

ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነው፤ ሕይወቱ ክቡር ነው፤ ክቡር ሕይወቱን ለመጠበቅ ብዙ ፍላጎቶቹን ማሟላት አለበት፤ አንዳንዶቹ ፍላጎቶች በየዕለቱ የሚከሰቱና የሚጎተጉቱ ናቸው፤ ስለዚህም ወዲያው ካልተስተናገዱ በጤንነት ላይ መጥፎ ውጤትን ያስከትላሉ፤ምግብና መጠጥ ግዴታዎች ናቸው፤ ልብስና መጠለያም ግዴታዎች ናቸው፤ ሰው ሁሉም ነገር ከተሟላበት ከገነት ከተባረረ በኋላ በግንባርህ ላብ ብላ ተብሎ ተረግሟል፤ በሰላም በሕግ ጥላ ስር የመተዳደር ፍላጎትም አለ፤ በአለው አቅምና ችሎታ አነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት ይጥራል፤ ይህ ቀላል አይደለም፤ ቀላል የማያደርጉት ብዙ ምክንያቶች አሉ።

አንደኛ፣ የሰውም፣ የእንስሳም፣ የእጸዋትም ሁሉ መኖሪያና መመገቢያ ምድር አንድ ነች፤ ስለዚህ ውድድሩ ከባድ ነው፤ በዚች ምድር ላይ እየኖሩ፣ ምድር የምታፈራውን እየተመገቡ፣ ውሀዋን እየጠጡ በሰላም መኖር አይቻልም፤ የሰው ልጅ ከቢምቢ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰው ቢምቢ ጋርም መታገል አለበት፣ ከዱር አንበሳ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰው አንበሳ ጋርም ነው።

ሁለተኛ፣ ፍላጎቶች የሥራ ሁሉ ምንጭ ስለሆኑ በጣም ይራባሉ፤ የመራባት አቅማቸው ከሰው ልጅ መራባትና የመፍጠር ችሎታ ጋር የተያያዘ ነው፤ በተጨማሪም ለተመቸው ሁሉ አምሮቶች ፍላጎቶች ይሆናሉ፤ ደሀዎችንና ሀብታሞችን የሚለየው አንዱ ዋና ነገር የፍላጎቶች ብዛት ነው፤ የደሀ ፍላጎቶች ከመሠረታዊ ፍላጎቶች አይርቁም፤ የሀብታሙ ፍላጎቶች ከትልቅ ቤት ወጥተው በትልቅ መኪና አድርገው በአውሮጵላን ሰማይ ይወጣሉ፤ ከዚያም አልፈው ይቧጭራሉ።

ሦስተኛ፣ በፍላጎቶች መራባት ላይ አምሮት ታክሎበት፣ እነዚህን ፍላጎቶችና አምሮቶች ማስተናገድና ማርካት ከባድ ፉክክርን ይፈጥራል፤ አብዛኛውን ጊዜ በፉክክር ላይ የሚታየው የተሠራው ቤት ትልቅነትና ውበት፣ የታረደው ሙክት ትልቅነትና ስብነት፣  የሚለብሰው ልብስ ስፌትና ውበት፣ የሚነዳው መኪና ዓይነት የሰዎቹን የኑሮ ደረጃ ያሳያል፤ በግለሰብ ደረጃ ይህ ከፍተኛ የልማት ደረጃን ያመለክታል፤ የግለሰቦችን እድገት የሚጠላ የለም፤ ጥያቄው የግለሰቦች አድገት በምን ዓይነት መንገድ ተገኘ ነው፤ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ ደሀውን እያሠሩና እያፈናቀሉ መሬቱን በዝርፊያና በቅሚያ ሌሎቹን እያደኸዩ ራሳቸውን የሚያበለጽጉ ነገን የማያስቡ ዕለትዋን ዘለዓለም አድርገው የሚቀበሉ ግዴለሾች፣ ወይም ጅሎች ናቸው።

በግፍ የበለጸጉ በግፍ ይደኸያሉ፤ ትናንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በአንድ ቀን ስንቱን ሀብታም ባዶ እንዳደረገውና እንዳኮማተረው ይህ ትውልድ አላየም፤ ግን ሰምቷል፤ በደርግ ዘመን የመሬት አዋጁንና የትርፍ ቤቶች አዋጆች ያስከተሉትን ሐዘንና ድንጋጤ ያዩ ሰዎች እንዴት እንደገና ሊመጣ ይችላል ብለው ማሰብ ያቅታቸዋል? አንዱ የመክሸፍ ዝንባሌ እንዲህ በቅርቡ የሆነውን መርሳትና ምንም ትምህርት ሳያገኙበት ኑሮን እንደዱሮው መቀጠል ነው፤ ታሪክ የሚከሽፈው እንዲህ ትምህርት መሆን ሲያቅተው ነው፤ በየመንገዱ፣ በየቀበሌው በየስብሰባው ጥርሱን እየነከሰ የውስጥ ቁስሉን የሚያሽ ሰው ሞልቷል፤ የሚራገም ሰው ሞልቷል፤ ከተወለዱበት፣ከአደጉበትና ለስድሳ ዓመት ከኖሩበት፣ ሠርግና ተዝካር ከደገሱበት ሰፈር ተገድዶ መልቀቅ፣ በልጅነት አብረው እየተጫወቱ፣ በኋላም በትምህርት ቤት አብረው በጓደኝነት ከዘለቁ፣ በሥራ ዓለም ከገቡ በኋላ በቅርብ ወዳጅነት አብረው ከቆዩ፣ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት በዓላት በደስታም በሐዘንም ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያልተለያዩ ሰዎች ጉልበተኛ መጥቶ በግድ ሲበትናቸውና ሲለያዩ፣ መድኃኔ ዓለም ይበትናችሁ! ሳይሉ ይቀራሉ? በግፍ የበለጸጉ በዚህ እርግማን እየተበተኑ ይደኸያሉ፤ እግዚአብሔር በቀዳዳው ያያል፤ አትጠራጠሩ!

ሰውን ገድሎ በሬሣው ላይ ቤት ሠርቶ ሀብታም መሆን ልበ-ደንዳኖች ለአጭር ሕይወታቸው የሚጠቀሙበት ከንቱ ድሎት ነው፤ ሕገ-ወጥነት ነው፤ ግዴለሽነት ነው፤ በቅርቡ ኤርምያስ እንደነገረን የአዲስ አበባን የመሬት ዘረፋ የአዘዘው መለስ ዜናዊ ዛሬ ለአሻንጉሊት የተሠራች በምትመስል ቪላ ውስጥ በሥላሴ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገባው በላይ ድርሻውን ይዞአል፤ የሁሉም መጨረሻ ይኸው ነው፤ ኤርምያስ እንደሚነግረን የአዲስ አበባ የመሬት ዝርፊያ ከልማት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከዓመታት በፊት የነፍጠኞችን አከርካሪት ለመስበርና የወያኔን ትንሽ ልብ አፍኖ የያዘውን ጥላቻ ለማስተናገድ የታቀደ የሕመም መግለጫ ነው፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አምስት ከመቶው ዓለም-አቀፍነት ሀበታምነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆነው ደግሞ ወደለማኝነት ደረጃ ሲወርደ ምንም አይሆንም ብሎ ማሰብ — አይ ማሰብ የት አለ — መመኘት ሳያስቡት በድንገት የሚመጣውን የሕዝብንም፣የእግዚአብሔርንም ኃይል፤ አሜሪካ ተማሪ በነበርሁበት ዘመን (በድንጋይ ዳቦ ዘመን!) አንድ ተወዳጅ ዘፈን ነበር፡– ከቀኜ ብታመልጥ ከግራዬ አታመልጥም! የሚል።

ልማት ምንድን ነው? ከመጀመሪያውኑ መጠየቅ የነበረብን ጥያቄ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ኑሮውን ለማሻሻል፣ ከዛሬው ኑሮ ተምሮ ነገን የተሻለ ለማድረግ ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር በመተባበር የሚያደርገው ጥረት ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መክሸፍ ጎልቶ የሚታይበት የቁሞ መቅረት ጉዳይ ነው፤ እውነቱ ግን ቁሞ መቅረት አይደለም በአንጻራዊ መለኪያ ቁልቁለት መውረደረ ነው፤ እዚህ ላይ ቆም ብለን የሩቁን መክሸፍ ከቅርቡ መክሸፍ ለይተን እንመልከተው።

ዱሮ ከአክሱም ሐውልቶችና ከላሊበላ ሕንጻዎች ብንጀምር የመክሸፍ ተዳፋቱ ከባድ ነው፤ ከአክሱምና ላሊበላ የሕንጻ ሥራዎች ወደጭቃ ጎጆ ያለው ቁልቁለት ነው፤ ወደቅርብ ዘመን መጥተን በእኔ ዕድሜ የሆነውን ብናይ ወደ1950 አካባቢ ኢትዮጵያ በማናቸውም ነገር የአፍሪካ መሪ ሆና ነበር፤ ዛሬ ያለችበትን ሁሉም ያውቀዋልና አልናገርም፤ ልማት የሚባለውን ነገር ገና አልጀመርንም፤ ልማት በዝርፊያ፣ ልማት በትእዛዝ አይመጣም፤ ልማት የምንለው የማኅበረሰቡን እድገት እንጂ የጥቂት ሰዎችን መንደላቀቅ አይደለም፤ ልማት የምንለው ከእያንዳንዱ ዜጋ ነጻነትና ፈቃድ ጋር የተያያዘውን የጋራ እድገት እንጂ በጥቂት ጉልበተኞች የአገሩን ዜጎች በአገራቸው ስደተኞች የሚያደርገውን አፍርሶ መሥራት አይደለም።