Archive | July 6, 2014

የዓለም ዋንጫና እያስተናገደ ያለው ክስተት

article-0-1E5E71FD00000578-487_634x381

ብራዚልን በሁለት መልክ ሲያስወቅሳት የቆየው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ፍጻሜውን ሊያገኝ እነሆ ከ32 ቡድኖች አራት ቡድኖችን ለግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ የሚያፋልመው መርሐ ግብር ብቻ ቀርቶታል፡፡

የዓለም ዋንጫው ሊጀመር የወራት ዕድሜ ቀርቶት በነበረበት ሰዓት ሳይቀር ብራዚል የዜጎቿን መሠረተ ልማት ሳታሟላ ለዚህ ለ20ኛው የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ወደ 14 ቢሊዮን ዶላር ማውጣቷ መላውን ሕዝቧን አስቆጥቶ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱ ይህ ሊጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰው ዝግጅቷ በታቀደው መልክ ይፈጸም ዘንድ ሥጋት መሆኑ አልቀረም ነበር፡፡ እግር ኳስን ከየትኛውም ዓለም በተለየ ለሚወዱት ብራዚላውያን ለተቃውሞ አደባባይ መውጣት መነሻ የሆናቸው፣ አገሪቱ ያወጣችው በቢሊዮን የሚቆጠረው ዶላር የወጣባቸው ስታዲየሞቿ በሌላ በኩል ብራዚል የአስተናጋጅነቱን ኃላፊነት ስትቀበል በገባችው ቃል መሠረት አለማጠናቀቋ እንዲሁ የዓለም ዋንጫን ለሚናፍቁ ሁሉ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

እግር ኳስን በተለየ ዓይን የሚመለከቱት ብራዚላውያን በአገራቸውና በክሮሽያ ብሔራዊ ቡድኖች የተከፈተው 20ኛው የዓለም ዋንጫ መክፈቻ እውን እስከሚሆን ድረስ ተቃውሞዋቸው ቢዘልቅም፣ የዓለም ዋንጫው መጀመር ከተበሰረ በኋላ ግን ከ50 ዓመት በፊት የዓለም ዋንጫን አስተናግደው በሜዳቸው የገጠማቸው ዓይነት ዕጣ ፈንታ ቡድናቸው እንዳይገጥመው መማፀን መጀመራቸው፣ ብራዚላውያን ለእግር ኳስ ያላቸው ፍቅር ምን ያህል እንደሆነ ምስክር ሆኗል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በአፍሪካ አህጉር ለመጀመርያ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ንግሥናዋን ያረጋገጠችው ስፔን ገና በምድብ ማጣሪያው በወቅቱ በፍጻሜው ጨዋታ ተፋላሚዎቹ ሆላንዳውያን በደረሰባት የጎል ናዳ ለስንብት መብቃቷ፣ የአዘጋጇ አገር የዝግጅት መጓተትን ያህል መነጋገሪያ ባይሆንም በዚህ ዓለም ዋንጫ በውድቀት ደረጃ ክስተት መሆኑ አልቀረም፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ለግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ የሚበቁት ቡድኖች ማንነት ባይታወቅም የአስተናጋጇ ብራዚል ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ፊሊፔ ስኮላሬ የብሔራዊ ቡድናቸውን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለሚናፍቁት ብራዚላውያን መፅናኛ ይሆን ዘንድ የዓለም ዋንጫን አንዱን እጀታ መያዛቸውን አብስረው ነበር፡፡

20ኛው የዓለም ዋንጫ ከደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ በሚለይባቸው ነጥቦች ውስጥ በ201ሩ የዓለም ዋንጫ አራት ውስጥ የገቡት ቡድኖች፣ ከአራት ዓመት በፊት የወርቅ አክሊሉን የደፋችው ስፔንና ለዋንጫው የተፋለመቻት ሆላንድ ነበሩ፡፡ ለደረጃ የተጫወቱት ደግሞ ጀርመንና በንክሻ ጥፋት ከማንኛውም የእግር ኳስ እንቅስቃሴ የአራት ወር ዕገዳ የተጣለባት የስዋሬዝዋ ዑራጓይ ነበሩ፡፡ የዓለም ዋንጫ ንግሥናዋን ብቻ ሳይሆን፣ በፊፋ የአገሮች ደረጃ ቁጥር አንድ አገር ሆና ላለፉ አራት ዓመት የዘለቀችው ስፔን፣ ከብራዚል የዓለም ዋንጫ በምድብ ማጣሪያው የወጣች ሲሆን፣ ዑራጓይ ደግሞ ከምድብ ማጣሪያው ቀጥሎ በተከናወነው ጥሎ ማለፍ በኮሎምቢያ ተሸንፋ ለመሰናበት በቅታለች፡፡

በሕትመት ምክንያት የሁሉንም ውጤቱን መያዝ ባንችልም ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት በተደረገው ጨዋታ ጀርመን ፈረንሳይን 1 ለ0 በመርታት ከአራቱ ቡድኖች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡ የተቀሩት አስተናጋጇ ብራዚል ከኮሎምቢያ እንዲሁም በሊዮኔል ሜሲ እግር ላይ የተንጠለጠለችው አርጀንቲና ከቤልጄምና  ሆላንድ ከኮስታሪካ ተጫውተዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ የወርቅ ኳስ ተሸላሚ የነበረው ዲያጎ ፎርላን ከዑራጓይ ሲሆን፣ የወርቅ ጫማው የወሰደው ደግሞ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር ነበር፡፡ ሙለር ወጣት ተስፈኛ ተብሎ ተሸላሚም ነበር፡፡ ኮከብ በረኛ ደግሞ የስፔኑ ኤካር ካስያስ ሲሆን፣ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ የነበረውም ቡድን ስፔን ነበር፣ ዘንድሮስ?

ከ ሪፖርተር ጋዜጣ