Archive | July 19, 2014

ኢትዮጵያዊው ገበሬ የእንግሊዝን መንግስት ከሰሱ

news

       በጋምቤላ ክልል ለሰፈራ ፕሮግራም ከቀያቸው ከተፈናቀሉት በርካታ ሺህ ዜጐች አንዱ እንደሆኑና ወደ ኬንያ እንደተሰደዱ የገለፁ ገበሬ፤ የእንግሊዝ መንግስት ለሰፈራ ፕሮግራሙ የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት በደል ፈጽሞብኛል በማለት ሰሞኑን በለንደን ፍ/ቤት ክስ መሰረቱ፡፡  ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ እርዳታ በመስጠት በአለም ቀዳሚ ስፍራ የያዘው የእንግሊዝ መንግስት በበኩሉ፤ ለሰፈራ ፕሮግራም የሚውል ገንዘብ አልሰጠሁም በማለት ምላሽ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከአስር አመት ወዲህ በየክልሉ የሰፈራ ዘመቻዎች መካሄዳቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት “ከፊል አርብቶ አደር” ተብለው በሚታወቁ እንደ ጋምቤላና ሶማሌ በመሳሰሉ ክልሎች፤ ነዋሪዎችን በመንደር የማሰባሰብና የማስፈር ፕሮግራሞች ተካሂደዋል፡፡ በርካታ ነዋሪዎች ያለፈቃዳቸው በግዳጅ እየተፈናቀሉ ለችግር ተዳርገዋል የሚል ተደጋጋሚ ትችት የሚሰነዘርባቸው እነዚህ የሰፈራ ፕሮግራሞች ላይ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተለያዩ የምርመራ ሪፖርቶች አቅርበዋል፡፡
የማህበረሰብ ልማት ፕሮግራም በሚል ስያሜ የዛሬ ሦስት ዓመት በጋምቤላ በተካሄደ የሰፈራ ፕሮግራም ከመኖሪያ መሬታቸው እንደተፈናቀሉ የገለፁት ገበሬው፤ ከመኖሪያዬ ልፈናቀል አይገባም በማለት ይዞታዬን ለመከላከል ስለጣርኩ አስከፊ ስቃይና እንግልት ደርሶብኛል ሲሉ ለለንደን ፍ/ቤት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የአራት ልጆች አባት እንደሆኑ የገለፁት እኚሁ ገበሬ፤ ቤተሰቦቼን ችግር ላይ ጥዬ ወደ ኬንያ ለመሰደድና በመጠለያ ጣቢያ ለመኖር  ተገድጃለሁ ብለዋል፡፡ የእንግሊዝ መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለተፈፀመበት የሰፈራ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ በመስጠቱ ተጠያቂ  መሆን ይኖርበታል፤ ላደረሰብኝ በደልም ካሳ መክፈል አለበት ሲሉ ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል – ኢትዮጵያዊው ገበሬ፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ባለፉት አራት አመታት ከ1.3 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ (አሁን ባለው የምንዛሬ መጠን ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ) እርዳታ መስጠቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ዘንድሮም አለማቀፍ የልማት ድርጅት በተሰኘው መስሪያ ቤት አማካኝነት 10 ቢሊዮን ብር ገደማ እርዳታ እንደሚሰጥ ከሳምንት በፊት ገልጿል፡፡
እርዳታው ለሌላ ጉዳይ ሳይሆን፤ የጤና፣ የትምህርት፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለመሳሰሉት የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች የሚውል እንደሆነ የተናገሩት የእንግሊዝ መንግስት አለማቀፍ ልማት ድርጅት ቃል አቀባይ፤ ለሰፈራ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ አልሰጠንም ብለዋል፡፡
ከሰፈራ ፕሮግራሙ ጋር የእንግሊዝ መንግስት ግንኙነት እንደሌለው በመግለጽም፤ በኢትዮጵያዊው ገበሬ የቀረበው ክስ ውድቅ ሊደረግ ይገባል ብለዋል – የእንግሊዝ መንግስት ባለስልጣናት፡፡ የለንደኑ ከፍተኛ ፍ/ቤት ግን የቀረበለትን ክስ ውድቅ አላደረገም፡፡ ከሳሹ ገበሬ፣ “የእንግሊዝ መንግስት ለሰፈራ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል” ብለው የማመን መብት እንዳላቸው ፍ/ቤቱ ገልፆ፤ የክሱ ፍሬ ነገር በአግባቡ መመርመር አለበት በማለት ክሱን ለማየት ወስኗል፡፡  የሰፈራ ፕሮግራሙ ድህነትን ለመቀነስ ታስቦ በኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ መደረጉን የገለጸው ቢቢሲ፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሁለት አመታት በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ በጋምቤላ ክልል 70 ሺህ ያህል ዜጎች ያለፈቃዳቸው ከይዞታቸው ተነስተው በቂ ምግብ፣ የእርሻ ቦታና የመሰረተ ልማት አውታር ወደሌሉባቸው መንደሮች ተዛውረዋል ማለቱን አስታውሷል፡፡
የከሳሹ ገበሬ ስም ያልተጠቀሰው “የቤተሰቦቼ ደህንነት ያሰጋኛል” በማለታቸው እንደሆነ የገለፀው ዴይሊ ሜይል በበኩሉ፣ ገበሬው በጠበቆች አማካኝነት ክስ ለማቅረብና ለመከራከር በአስር ሺዎች ፓውንድ የሚገመት ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸውና ወጪው የሚሸፈነው በእንግሊዝ መንግስት እንደሆነ ጠቁሟል፡፡ ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ አገራት በየአመቱ በሚመደበው እርዳታ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚባክንና ሸክሙ በእንግሊዛዊያን ግብር ከፋዮች ትከሻ ላይ እንደሚያርፍ በመዘገብ የሚታወቀው ዴይሊ ሜይል፤ ኬንያ ውስጥ የሚኖር የሌላ አገር ዜጋ ክስ የሚመሰርተውና ካሳ የሚከፈለው በእንግሊዝ ግብር ከፋይ ዜጐች ኪሳራ ነው የሚል ተቃውሞ እንደተፈጠረ ገልጿል፡፡ ክስ አቅራቢው ገበሬ በበኩላቸው፤ በፍ/ቤቱ ውሳኔ ካሳ ከተከፈላቸው ገንዘቡን ለበጐ አድራጐት እንደሚያውሉት ተናግረዋል፡፡

Source :- addisadmassnews

የፕሬስ አፈናው በ”ሎሚ” መጽሔት ተጀመረ

 

ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ከመንግስት በተላኩ ኃይሎች የ‹‹ሎሚ›› መጽሔት ቢሮ ‹‹ያለ ንግድ ፍቃድ›› በሚል ሠበብ ታሸገ፡፡ እነዚህ ከየትኛው ወገን እንደተላኩ ያልታወቁት ኃይሎች በቢሮ ውስጥ የነበሩትን የሂሳብ ሠነዶች ‹‹ይዘን እንሄዳለን፣ አትሄዱም›› በሚል በተፈጠረው እሰጥ አገባ ምክንያት ስልክ ደውለው ቁጥራቸው ከ20 ያላነሱ የታጠቁ የፌደራል ኃይሎችን በመጥራት እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙትን ንብረቶችና ወረቀቶችን ጨምሮ እንዳናወጣ በመከልከልና በማስፈራራት አስቀድመው ታዘው ይዘውት የመጡት ወረቀት “ያልታሰደ ንግድ ፍቃድ” የሚል ቢሆንም፣ ንግድ ፍቃዱ የታደሰበትን ማጋገጫ ሲመለከቱ ደግሞ ፊት ለፊታችን ወረቀቱን በመሠረዝ “ያለ ንግድ ፍቃድ” በሚል ጽፈው አሽገውታል፡፡ በወቅቱ ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም ለንባብ የምትበቃው ‹‹ሎሚ›› መጽሔት ወደ ማተሚያ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንዳለች ይህ ችግር መፈጠሩ በሎሚ አባላቶች ላይ ግሬታን ቢፈጥርም፣ በተወሰደው ሕገ-ወጥ እርምጃ ሳንደናገጥ ከምንገባበት አንድ ቀን ዘግይተንም ቢሆን በተከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ማተሚያ ቤት ልናስገባ ችለናል፡፡ በወቅቱም ቢሮአችን እንደሚታሸግ ለምን አስቀድማችሁ በደብዳቤም ሆነ በስልክ አላሳወቃችሁንም ቢባሉም ‹‹የእናንተ ስፔሻል ኬዝ ነው፤ እኛ ከላይ ታዘን ነው›› የሚል ምላሽ ሠጥተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሎሚ መጽሔት አጋር ሆና በሣምንት ሁለቴ ለንባብ የምትበቃው ‹‹አፍሮ ታይምስ›› ጋዜጣም ከወዲሁ ልትዘጋ እንደምትችል አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የዞን 9 አባሎች ያውቁ እንደነበር መረጃዎች እየጠቆሙ ይገኛሉ፡፡ ይኸውም እነዚሁ ኃይሎች ከመጀመሪያው ቀን በተለየ ሁኔታ በበነጋታው ተደራጅተው በመምጣት “ሠነዶችን እንፈልጋለን” በሚል ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በፌደራል ኃይሎች የታገዘ የ5 ሠዓታት ፍተሻ (ከብርበራ አይተናነስም) ከአካሄዱ በኋላ በቢሮ ውስጥ የሚገኙትን የሂሳብ ሠነዶች በሙሉ ሰብስበው ወስደዋል፡፡ ሆኖም ግን የምንፈልገው የሂሳብ ሠነዶችን ይበሉ እንጂ፣ በቢሮው ውስጥ የሚገኙትን በተለያዩ ጊዜ የታተሙ የሎሚ መጽሔቶች፣ የአፍሮ ታይምስ ጋዜጦችና በእጅ ጽሁፍ የተተየቡ ወረቀቶችን አንድ በአንድ ሲፈትሹ ተስተውሏል፡፡ ይሄ ሕገ-ወጥ እርምጃ የእኛ የፕሬስ ውጤቶች በሆኑት ሎሚ መጽሔትና አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ሆነ ተብሎ ለማጥቃት የታለመ መሆኑን የሚያመለክተው እነዚሁ ያልታወቁት ኃይሎች አስቀድመው ከመምጣታቸው በፊት ‹‹የአፍሮ ታይምስ ቢሮን ለማሸግ እየመጣን ነው›› በማለት የደወሉ ቢሆንም፣ ቢሮ ድረስ መጥተው የነበሩትን ሠነዶች ከወሰዱ በኋላም ከአለቆቻቸው ጋር በስልክ በመነጋገር ሊያሽጉበት ይዘውት መጥተው የነበረውን የማሸጊያ ወረቀት ሳያሽጉበት ተመልሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከአንድ ወር በፊት ገዢው መንግስት ነፃውን ፕሬስ ጥላሸት በመቀባትና እርምጃ እንደሚወስድ (ሎሚ መጽሔትን ጨምሮ) በፈበረካቸው የተለያዩ ዶክመንተሪዎቹ ሲዝት የቆየ ሲሆን፣ አሁን አፈናውን በሎሚ መጽሔት ‹‹አሃዱ›› ብሎ ጀምሯል፡፡ ሎሚ መጽሔትም ሆነ አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ እራሱ ገዢው መንግስት ባወጣው የፕሬስ አዋጅ መሠረት ሕግና ደንቡን ተከትለን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ድምጽ በመሆን ተገቢውን መረጃ በወቅቱ እያደረስን ቢሆንም፣ ይህንን ያልወደደው ገዢው መንግስት ነፃ ፕሬሱን ከነአካቴው ለማጥፋት የተለያዩ ወጥመዶችን እያዘጋጀ መሆኑን አንባቢያን እንድታውቁልን እንፈልጋለን፡፡ ውድ አንባቢዎቻችንም ይሄንን ተገንዝባችሁ እስከመጨረሻው ድረስ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመቀበል ከጎናችን እንድትቆሙ እናሳስባለን፡፡