Archive | August 2, 2014

በአሜሪካ ከጠፉት አትሌቶች ሁለቱ ከ“ናይኪ”ና ከ“አዲዳስ” ጋር ተፈራርመዋል

Atletoch          በዓለም የወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል ወደ አሜሪካ አቅንተው ከነበሩ አትሌቶች መካከል ባለፈው ቅዳሜ ድንገት ከተሰወሩትና ከቀናት ቆይታ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት አራት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል ሁለቱ ከታዋቂዎቹ ‹ናይኪ›ና ‹አዲዳስ› ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ኦሪጎን ላይን ድረገጽ ትናንት ዘገበ። አማኑኤል አበበ፣ ዱሬቲ ኢዳኦ፣ መዓዛ ከበደና ዘይቱና ሞሃመድ የተባሉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ ባለፈው ቅዳሜ ከልዑካን ቡድኑ ተለይተው መጥፋታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ የኦሪጎን ፖሊስ ትናንት በሰጠው መግለጫ ከጠፉት አትሌቶች መካከል ዘይቱና ሞሃመድ ከናይኪ፣ ዱሪቲ ኢዳኦ ደግሞ ከአዲዳስ ጋር የኮንትራት ስምምነት መፈራረማቸውን ከቡድኑ አሰልጣኞች ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ የኦሪጎን ፖሊስ አትሌቶቹ ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት ሊጠፉ አንድ ቀን ሲቀራቸው እንደነበር መግለጹን የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩን በተመለከተ ሁለቱንም ኩባንያዎች ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ጠቅሷል፡፡ 

        ፖሊስ አትሌቶቹ በአሜሪካ የመቅረት ዕቅድ ይዘው እንደጠፉ ከአሰልጣኞቹ መረጃ እንዳገኘና አትሌት ዱሪቲም የፓስፖርቷን ኮፒ ለአዲዳስ ኩባንያ የኮንትራት ስራ አስኪያጅ ለመላክ እንደምትፈልግ ለአሰልጣኞቿ ጥያቄ ማቅረቧንና አሰልጣኞቹም የቡድኑ አባላት ፓስፖርት የሚገኝበትን ክፍል ቁልፍ እንደሰጧት አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አሰልጣኞቹ፤ አትሌቶቹ ከጠፉ በኋላ ፓስፖርታቸውን ካስቀመጡበት እንዳጡት ተናግረዋል ያለው ዘገባው፤ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባከናወነው ቀናትን የፈጀ ፍለጋ አትሌት ዘይቱናን በዋሽንግተን፣ ሌሎቹን ሶስት አትሌቶች ደግሞ ቤቨርተን ውስጥ እንዳገኛቸው አስረድቷል፡፡ አትሌቶቹ በአሜሪካ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩም ሆነ ቀጣይ ዕጣ ፋንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ምንም አይነት መረጃ አለመስጠቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ማህበራዊ ግንኙነቶቻችንን እናጠንክር /Birhanu Baue/

ኢትዮጵያ ሀገራችን የጥንታዊ ገናና ስልጣኔና ሳያቋርጥ በተከታታይ የዘለቀ የብዙ አመታት የነጻ መንግስት ባለቤት መሆኗ  በወዳጅም ሆነ በጠላትም በኩል ግልጽ የሆነ ሀቅ ነው:: ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪክ የግዛት መስፋፋትና ጥበት የሀይል ብርታትና ድክመት አንጻራዊ የ ስልጣኔ ምጥቀትና ዝግመት የተፈራረቀባት ሀገር ብትሆንም በአለም ታሪክ መቼውንም ጊዜ  ቢሆን የነጻ ህዝብና የጥቁር ህዝብ የነጻነት ፋና ሆና የኖረች ሀገር ናት:: ይህም ታሪክ የኢትዮጵያ ልዩ መገለጫ አንጸባራቂ የማንነታችን ምንጭና የእኛነታችን መስታወት ነው::

ኢትዮጵያ የአንድ ማህበረሰብ ወይም ባህል መገለጫ ሳይሆን በኢትዮጵያ ምድር ለሚኖሩ ብሄረሰቦች ሁሉ ከብዝህነታቸው በላይ አብሮነታቸው ውህደታቸው ገላጭና ክብርና ሞገሳቸው ከመሆኑም በላይ የአንድነታችንና የቃል ኪዳን ማህደራችን ነበር:: ግን አንባገነን መንግስት ይሄንን ማህበራዊ አንድነታችንን ንዶ እርስ በእርስ እንዳንተማመን አድርጎን ይኅው በባእድ ሃገር እርስ በርሳችን እየተፈራራን የእነሱን ስልታን ዘመን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እያራዘምንላቸው እንገኛለን::

በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄረሰቦች የተመሰረቱት በተራዘመ ሂደት ውስጥ በተከሰቱ የህዝብ ፍልሰቶች ንግድና ጦርነቶች በፈጠሩት ግንኙነት እና መስተጋብር ባስከተሉት የባህል መወራረስና የብሄረሰቦች ጋብቻና ተዋልዶ ነው::   ኢትዮጵያ የረጅም ታሪክ ባለቤት ናት ስንል የሚያመለክተው ቁም ነገር ታሪክ የብሄረሰብ ውህደት ድምር ውጤት መሆኑን መገንዘብ አለብን:: ህዝቦች የሚመሰረቱት በአስገዳጅ ሀይል ሳይሆን በጊዜ ሂደትና በህዝቦች ባህላዊና ማህበራዊ ፍላጎት የመነጨ ሲሆን ነው::  ኢሃዴግ እንደሚለው ታሪካችን 100 አመት ነው እንደሚለው አደለም:: አንባገነኖች ሁሌም ቢሆን ታሪክን ማፍረስና አዲስ ትውልድ ፈጥረው ለእነሱ በሚመቻቸው መንገድ መግዛት ስለሚፈለጉ ነው:: ስለዚህ ኢሃዴግ የጀመረውን አፍራሽ ተግባር በምንችለው መንገድ እየገለጽን ከእነዚህ አረመኔዎች እጅ ፈልቅቀን ለአዲሱ ትውልድ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ አንድነቷ ሳይሸራረፍ የተጠበቀች ሀገር ገንብተን ማስተላለፍ አለብን::

ስለዚህ ባጠቃላይ ወያኔ ከሚያራምደው የጎሳ ፖለቲካ ሙጥኝ ብሎ ከያዘው የግትርነት አቋሙና አሁን በሃገርችን በሁሉም በኩል እየ ተወሳሰቡ ላሉ ችግሮች ተጠያቂው ገዢው መንግስት ነው:: ኢሃዴግ ለሃገራችን ችግሮች መፍትሄ ያመጣል ተብሎ አይገመትም:: በተቃራኒው ሃገርንና ህዝብን ለባእዳን ሃገር አሳልፎ ሲሰጥና ሲሸጥ የህዝብን ድምጽ በአደባባይ ሲሰርቅ ህዝቦችን ሲያስርና ሲገድለል አገ ር ሲሸጥና ሲገነጥል የምናየው ሃቅ ነው:: ስለሆነም በሀገራችን ላይ የተጣለውን የጥፋት ደመና ለመግፈፍ የተጀመረውን የውድቀት ጉዞ ለመግታት ምትክ የማይገኝለት የህዝብ ትግል በማደራጀት በማስተባበርና በመምራት ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወት የተሻለና ያለፉት ስህተቶቻችንን ሁሉ አርመን አንድነታችንን ማህበራዊ ግንኙነቶቻችንን የሚያጠናክርልን ስብስብ ስንፈጥር ብቻ ነው:: የነጻዋን ኢትዮጵያ መሰረቷን እንዲቀጥል ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ነው::

Birhanu Baue

Germany

የኢቦላ በሽታን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሁም ኢቦላ ወረርሽኝ ስላለበት ደረጃ ከተለያዩ ድረገፆች የተገኙ መረጃዎች

Stop

1. የኢቦላ በሽታ ምንድ ነው?
የኢቦላ በሽታ በቫይረስ ምክንያት የሚመጣ፣ በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡ የኢቦላ በሽታ በምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች በተደጋጋሚ በመከሰት ከፍተኛ ህመምና ሞት እያደረሰ የሚገኝ በሽታ ነዉ፡፡ በሽታው በማንኛውም ወቅት በአገራችንም በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት የሚችል በመሆኑ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የኢቦላ በሽታ ለከፍተኛ ህመምና ለሞት የሚዳርግ ቢሆንም መከላከል ግን ይቻላል፡፡
2. የኢቦላ በሽታ መተላለፊያ መንገዶች፡-
•በኢቦላ ከታመመ ሰው ቁስል፣ ደም፣ ምራቅ፣ ትውከት፣ አይነምድርና ሽንት ጋር በቀጥታ በመነካካት ወይም እነዚህ ፈሳሾች ወደ ጤነኛ ሰው አይን ከተረጩና ከገቡ፣
•ንጽህናቸው ባልተረጋገጠ ወይም ሌሎች ህሙማን የተጠቀሙበትን መርፌ ሳይቀቅሉ በመጠቀም፣
•የኢቦላ በሽታ ታማሚ የተጠቀመባቸዉን ስለታማ መሳሪያዎች በመጠቀም፣
•በኢቦላ በሽታ የሞተ ሰውን አስከሬን በቀጥታ በመነካካት፣
•በኢቦላ በሽታ የሞተውን እንሰሳ ስጋ በመመገብ ናቸው፡፡
3. በኢቦላ በሽታ የተያዘ ሰው የበሽታዉን ምልክቶች የሚያሳያው መቼ ነው?
በኢቦላ በሽታ ከተጠቃ ሰው ጋር ንኪኪ የፈጠረ ሰው ከ 2 እስከ 21 ቀናት ባለዉ ጊዜ ውስጥ የበሽታውን ምልክቶች ማሳየት ይጀምራል፡፡

4. በኢቦላ በሽታ የተያዘው ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶችና ስሜቶች፡-
•ድንገተኛና ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት ይይዘዋል፡፡ በተጨማሪም ማስመለስ/ትውከት/፣ ተቅማጥ፣ ራስ ምታት፣ የቆዳ ሽፍታ እና የአይን ቅላት ምልክቶች ይታዩበታል፡፡
•በሰውነታችን ክፍት ቦታዎች ማለትም አይን፣ አፍንጫ፣ ድድ፣ ጆሮ፣ ፊንጢጣና በብልት በኩል የመድማት ምልክት ሊታይም ላይታይም ይችላል፡፡
5. በኢቦላ በሽታ መያዙ የተጠረጠረ ወይም የተያዘ ሰው ከገጠመን ምን ማድረግ አለብን?
•ታማሚውን በምንረዳበት ጊዜ ሰውነታችንን ከበሽታው መከላከል የሚያስችለንን የእጅ ጓንት፣ የአይን መከላከያ መሳሪያ (ጎግል) እና የአፍንጫና የአፍ መሸፈኛ ማስክ መጠቀም፤
•የታመመውን ሰው ወድያውኑ ለአስፈላጊ ህክምናና እርዳታ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጤና ተቋም መወሰድ፤
•በኢቦላ በሽታ የተጠረጠረ ሰው በሚገኝበት ወቅት ወድያውኑ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጤና ተቋም ወይም ጤና ጽ/ቤት ሪፖርት ማድረግ፣
•በበሽታው መያዙ የተጠረጠረ ወይም የታመመ ሰው የተጠቀመባቸዉን አልባሳትና መኝታውን በበረኪና ማጠብ ይኖርብናል፡፡
6. ለኢቦላ በሽታ ተጋላጭ የሆኑት ማናቸው?
•በሽታዉ ከታመመ ሰው የሚወጣውን ደምና ሌሎች የሰውነት ፈሳሾች በቀጥታ በመነካካት የሚተላለፍ በመሆኑ ከታመመው ሰው ጋር የሚኖር ማንኛውም ሰው በበሽታዉ ሊያዝ ይችላል፡፡
•በሽተኛውን በሚመግቡበትና በሚንከባከቡበት ወቅት የእጅ ጓንትና ሌሎች መከላከያ መሰሪያዎች ሳያደርጉ ከሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ የሚፈፅሙ ሰዎች በቀላሉ በበሽታው ሊያዙ ይችላሉ፡፡
•በኢቦላ በሽታ የሞተውን ሰው አስከሬን ያለ እጅ ጓንትና ሌሎች የመከላከያ መሳሪያዎች የምንነካካ ከሆነ በቀላሉ በበሽታ ልንጠቃ እንችላለን፡፡
7. የኢቦላ በሽታን እንዴት ልንከላከል እንችላለን?
•የእጅ ጓንት፣ የአይን ጎግል እና ሌሎች የሰውነት መከላከያ መሳሪያዎችን በመጠቀም በበሽታው ከተጠቃ ሰው ውስጥ ከሚወጣው ማንኛውም ፈሳሽ ጋር በቀጥታ ባለመነካካት፤
•ያለ እጅ ጓንት በበሽታው የተጠቃውን ሰው ቁስል አለመንካት፤
•በኢቦላ በሽታ የተያዘው ሰው የተጠቀመውን መርፌና ሌሎች ስለት ያለቸውን መሳሪያዎች አለመጠቀም፤
•በኢቦላ በሽታ መያዙ የተጠረጠረና የሞተ እንስሳን ሥጋ አለመመገብ፤
•በኢቦላ በሽታ የሞተን ሰው አስከሬን ያለጓንትና ሌሎች የመከላከያ መሰሪያዎች ያለመንካት፣ የቀብር ሥነ ሥርኣቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈፀም ማድረግ ፤ እንዲሁም ከቀብር በኋላ ያለውን ስነስርዓት ማሳጠር፤
•የታመመውን ሰው ከረዳን ወይም በበሽታዉ ምክንያት የሞተውን ሰው አስከሬን ከነካን በኋላ እጃችንን በውሃና በሳሙና በደንብ መታጠብ፣
8. በቤት ውስጥ መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ ፡-
•በኢቦላ በሽታ የተጠቃ ወይም የተጠረጠረ ሰውን በተቻለ መጠን ለብቻው በተዘጋጀ ቦታ መለየት፣
•በበሽታው የተጠቃ ወይም የተጠረጠረን ሰው ወደ ጤና ተቋማት በምንወሰወድበት ወቅት ከታማሚው ጋር አላስፈላጊ ንክኪ አለማድረግ፣
•በበሽታው ከተጠቃ ወይም ከተጠረጠረ ሰው ወይም የሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ወዲያውኑ እጃችንን በውሃና በሳሙና መታጠብ፣
•በኢቦላ በሽታ የተጠቃውን ሰው በምንረዳበት ወይም በምንንከባከብበት ወቅት የእጅ ጓንት፣ የአይን ጎግል፣ የፊት መሸፈኛ እና ሌሎች የሰውነት መከላከያ መሳሪያዎችን መጠቀም፣
•በበሽታው የተጠቃ ወይም የተጠረጠረ ሰው የሰውነት ፈሳሽ መሬት ከበከለ በረኪና ይጨምሩበት፤ ከ15 ደቂቃ በኋላም ይፀዳ፤ በቆሻሻ የተነካኩ ቁሳቁሶችና አልባሳት መቃጠል ይኖርባቸዋል፣
•በኢቦላ በሽታ ታሞ የሞተ ሰው የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም ከአስከሬን ጋር ንክኪ አለማድረግ፣ የጋራ እጅ መታጠቢያም አለመጠቀም፣
•የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም አስከሬኑ በፕላስቲክ ከረጢት መጠቅለል፣ የቀብር ስነስርዓት ሲፈፀም በሰለጠነ የጤና ባለሙያ ምክር መታገዝ፣

9. በሽታው ወደ ሀገራችን ሊገባ የሚችልባቸዉ ሁኔታዎች፡-
በሽታው እስከ አሁን በሀገራችን ያልታየ ቢሆንም በምዕራብ አፍሪካ ሀገሮችና በሀገራችን መካከል ባለው የህዝብ እንቅስቃሴ ምክንያት በማንኛውም ጊዜ ወደ አገራችን ሊገባ ይችላል፡፡ በተለይም በኤርፖርቶችና በድንበር አከባቢ ባሉ መውጫና መግቢያ በሮች በኩል ሊገባ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ስለሚችል አስፈላገው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡
10. እየተወሰዱ ያሉ እምጃዎች
በሽታው እስከ አሁን ወደ ሀገራችን ባይገባም ከወዲሁ ለመከላከልና ከተከሰተም አፋጠኝ ምላሽ መስጠት እንዲቻል በቂ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር በአየር መንገዱ የሚጓዙ መንገደኞችን ጤንነት ሁኔታ መለየት፣ የታመመ ሰው ከተገኘም ወዲያውኑ ህክምና የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡ እንዲሁም የህክምና ግብዓቶችና ለባለሙያዎች የሚሆን የመከላከያ መሳሪያዎች ተለይተው በመሟላት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ጤና ተቋማት ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ መስጠት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ፡-
ዶ/ር ዳዲ ጅማ -በስልክ፡ +251911247092
አቶ አህመድ ኢማኖ – በስልክ፡ +251912673924 ማነጋገር ይቻላል