Archive | August 4, 2014

ሕዝብ የት አቤት ይበል?

reporter

ከጊዜ ወደ  ጊዜ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ያለው የአገልግሎቶች አቅርቦት የሕዝቡን ምሬት እያናረው ነው፡፡ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የስልክ ኔትወርክና የትራንስፖርት አቅርቦት መስተጓጎል አጋጥሞ፣ ለተፈጠሩ ችግሮች ሰሚ ሲጠፋና

አቤት የሚባልበት አካል ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ሲል የሕዝቡ ምሬት ከሚገመተው በላይ እየሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ አገሪቱ እየታየ ያለው የአገልግሎቶች አቅርቦት መስተጓጎል መንግሥት በአገር አለ ወይ የሚል ጥያቄ በስፋት እያስነሳ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕዝብ አቤት የሚባልበት ቦታ በማጣቱ፡፡

ከዚህ በፊት ውኃ ለሰዓታት ወይም ለአንድ ቀን ጠፍቶባቸው የማያውቁ ሥፍራዎች ሳይቀሩ ያለ በቂ ምክንያት ለበርካታ ቀናት ይጠፋባቸዋል፡፡ ሕፃናት፣ አቅመ ደካማ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ባልዲና ጄሪካን ተሸክመው ረጂም ርቀት እየተጓዙ ውኃ ፍለጋ ሲንከራተቱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ የሚመለከተው መሥርያ ቤት አንዴ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ሌላ ጊዜ ደግሞ ለመረዳት የሚያዳግቱ ምክንያቶችን ሲደረድር እንሰማለን፡፡ ነገር ግን መፍትሔ የለም፡፡

በአንዳንድ ቦታዎች ውኃ ለበርካታ ቀናት ጠፍቶ ምክንያቱ ሲጠየቅ በቂ ምላሽ አለመገኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ በማን ትዕዛዝ እንደተዘጉ ያልታወቁ የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች በነዋሪዎች ተከፍተው ውኃ ሲመጣ ገረሜታ ይፈጠራል፡፡ እነዚህን መስመሮች ማን ዘግቷቸው ነበር ተብሎ ሲጠየቅ መልስ የለም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ተመልካች ያጡ የውኃ መስመሮች ፈንድተው ሐይቅ ሲፈጠር ይታያል፡፡ በወቅቱ ጥገና ስለማይደረግ የአገር ሀብት ይባክናል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ግራ የሚያጋቡ ድርጊቶች በቅጡ ለሚመለከት በሕዝብ ላይ ደባና አሻጥር የሚፈጽሙ ወገኖች አሉ ብሎ ቢደመድም አይፈረድበትም፡፡ ምክንያቱ ሕዝቡ አቤቱታ ሲያቀርብ ሰሚ የለምና፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በአሁኑ ጊዜ ለሁለት ተከፍሎ ይቅርና ድሮም ‹‹እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ›› ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የሚያሰራጨው አካል አለ ወይ እስኪባል ድረስ ሕዝቡ እየተመረረ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ድርጅቶች፣ በሕክምና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በአነስተኛና በመካከለኛ ማምረቻዎች፣ በግዙፍ ኢንዱስትሪዎች፣ ወዘተ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ጨርሶ መጥፋት አገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረጋት ነው፡፡ ሕፃናትን መመገብ፣ ሕሙማን ማስታመምና በየደረጃው አገልግሎትና ምርት ማቅረብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ እንኳን መፍትሔ መስጠት የደረሰው ችግር ምን እንደሆነ ደፍሮ የሚናገር ጠፍቷል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል ከመቆራረጥ አልፎ ለበርካታ ቀናት እየጠፋ ሲመጣ ከግለሰብ እስከ አገር ድረስ ከፍተኛ ሀብት እየወደመ ነው፡፡ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ዕምቅ ኃይል አውጥቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ርብርብ እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ይህንን ኃይል በተገቢው መንገድ ማሰራጨት ያለበት ተቋም በአሳዛኝ ሁኔታ ሥራውን መሥራት ሲያቅተው እንዴት ጠያቂ አይኖርም? ሕዝቡ አቤት የሚልበት አጥቶ በጨለማ ውስጥ ሲደናበር፣ ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን በአግባቡ ለማቅረብ ግብር ከፋይ ዜጎች ሲሰቃዩ፣ የሕክምና ተቋማት ሕሙማንን መርዳት ሲቸገሩ፣ ወዘተ ጠያቂና ተጠያቂ ከሌለ እንዴት ሊዘለቅ ነው? ሕዝብ አቤት ሲል ሰሚ ጠፍቷል፡፡

በማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥር ያለው የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ጉዳይ እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል የተባለው የአዲስ አበባ ፕሮጀክት አንድ ወር አልፎት እንኳ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል ቢባልም፣ የአገልግሎቱ ጥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ብሶበታል፡፡ በሞባይል ስልክ መገናኘትና ሒሳብ ማስገባት ካለመቻሉም በላይ፣ ምክንያቱ ሳይታወቅ ከታሪፍ በላይ ከፍተኛ ሒሳብ ከደንበኞች ላይ ይወሰዳል፡፡ ሕዝብ ሲጠይቅ ምላሽ የለም፡፡ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሁሉም ክልሎች በሞባይል ስልክ ለመገናኘት ከፍተኛ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ችግሩ መፍትሔ ሳያገኝ እየተነገረ ያለው ግን ግራ ያጋባል፡፡ ከዕለት ዕለት እየባሰበት ያለው የቴሌኮም ዘርፍ ለሕዝቡ አቤቱታ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ አይደለም፡፡ መንግሥትም ችግሩን ተረድቶ አቅጣጫ እያሳየ አይደለም፡፡ ምን ይሻላል?

የትራንስፖርት ችግርን ብንመለከት ያው ነው፡፡ በዚህ ክረምት ጠዋትና ምሽት ላይ ሠርቶ አደሩ ሕዝብ ሠልፍ ይዞ በዝናብ እየተደበደበ ነው፡፡ የቀጣና ሥምሪት ተጀምሮ በተወሰነ ደረጃ ችግሩ ይቃለላል ቢባልም ብሶበታል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ አጭርና መካከለኛ ጉዞ ላይ ተሰማርተው የነበሩ በርካታ የሕዝብ ትራንስፖርት አውቶቡሶችና ሚኒ ባሶች በስፋት እንዲገቡ ተደርጓል ቢባልም፣ በሥርዓት ሥምሪቱን መምራት ባለመቻሉ ሕዝቡ እየተንገላታ ነው፡፡ የረጂም የጉዞ መስመሮች ሁለትና ሦስት ቦታዎች እየተቆራረጡ ሕዝቡ ሲበዘበዝና ለውጣ ውረድ ሲዳረግ ጠያቂ የለም፡፡ ሕዝቡ ብሶቱን ሲገልጽ አዳማጭ የለም፡፡ በፀሐይና በዝናብ እየተደበደበ ምሬቱን ለፈጣሪው በመግለጽ ላይ ነው፡፡ ምን ያድርግ ታዲያ?

አገር በመምራት ላይ ያለው መንግሥት ነጋ ጠባ በመልካም አስተዳደር እጦትና በአገልግሎቶች መስተጓጎል አቤቱታዎች ሲቀርቡለት መፍትሔ እያፈላለገ መሆኑን ቢገልጽም፣ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት በማጣቱ የሕዝቡን ምሬት እያናረው ነው፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ጠፍተው አገር ምድሩን ምሬትና ሰቆቃ እየሞሉት ነው፡፡ አገሪቱ የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፋ የመጨረሻው ዓመት ላይ ናት ቢባልም፣ በተለይ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ የሚታየው ግድየለሽነት ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘቀጠ ያለውን የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአገልጋይነት መንፈስ ለማስተካከል ጥረት ካልተደረገ አገሪቱን ወደ ቁልቁለት ያንደረድራታል፡፡ ውጤቱም አስከፊ ይሆናል፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንኳን ኢንቨስትመንትን በተወዳዳሪነት ለመሳብ፣ ለዜጎች መጠነኛ ዕርካታ ለማስገኘት አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ ይልቁንም ምሬት እየተዘራ ነው፡፡ በአገሩ መንግሥት የለም ወይ እስኪባል ድረስ አገልግሎቶቹ በሙሉ እንከን በእንከን ሲሆኑና በየጊዜው ሲዘቅጡ እያየን ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ውኃ፣ ስልክ፣ ኤሌክትሪክና ትራንስፖርት ከደረጃቸው በታች ወርደው ሲገኙ እንዴት ዝም ይባላል? እስከ መቼስ እዚህ ግባ የማይባል ምክንያት ይደረደራል? ሕዝቡስ አቤት ሲል እንዴት ሰሚ ይጠፋል? ሌላው ቀርቶ ምርጫው ከፊት አፍጥጦ እያለ ሕዝብን አለማዳመጥ ማለት ውጤቱ ምን እንደሆነ አልታወቀም? ወይስ መንግሥትን እንደ ነቀዝ እየበላ ያለ ኃይል ውስጡ ተሰግስጓል? ግራ የገባ ነገር!