Archive | September 7, 2014

ያለፈቃድ ፎቶን መጠቀምና መዘዙ

 

በአገራችን ልማድ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ መብት ሲጣስ አለመጠየቅ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡

በዕለት ተዕለት ኑሮአችን መብታችን እየተጣሰ ዝም የምንል ብዙ ነን፡፡ ታክሲ ያለአግባብ ሲያስከፍለን፣ ጎረቤት ሁከት ሲፈጥርብን፣ መብራት ኃይል ያለአግባብ ኃይል በመልቀቁ ምክንያት ኤሌክትሮኒክስ ሲጎዳብን፣ መንገድ ላይ የተቆፈረ ጉድጓድ እግራችንን ሲሰብርብን፣ መንገደኛ ያለአግባብ ሲተነኩሰን፣ ተከራይ ከውል ውጭ ያለአግባብ ዋጋ ሲጨምርብን፣ ነጋዴ ሚዛን ሲያጓድልብን ወዘተ መብታችን እየተጣሰ የማንጠይቅ ብዙዎች ነን፡፡ መብት እየተጣሰ ላለመጠየቁ ብዙ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል፡፡ አንዳንዱ መብቱን፣ የመብቱን ወሰን፣ ገደቡንና የመጠየቂያ መንገዱን አያውቀውም፡፡ አንዳንዱ መብቱንም ቢያውቅ ለመፈጸም፣ ለመጠየቅ ችላ ይላል፡፡ ጊዜ የለኝም፣ መፍትሔ አይኖረውም፣ ማን የተሻለ መፍትሔ ይሰጠኛል /ይሰማኛል ወዘተ በቸልታ ውስጥ የሚቀርቡ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከብዙኃኑ ውስጥ ግን አንዳንድ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች አይጠፉም፡፡ የመብት ትርጉሙ የሚገባቸው፣ ሰዎች እንዲማሩ/ እንዲቀጡ ቁርጠኝነት ያላቸው፣ መብትን ላለመጠየቅ ምክንያት የለም ብለው የሚያስቡ አሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን አንድ ጉዳይ በዚህ ጽሑፍ እናነሳለን፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አሥራ አምስተኛ ቮልዩም ያወጣው ባለፈው የነሐሴ ወር ነበር፡፡ በቮልዩሙ ከተካተቱት አስገዳጅ ፍርዶች ውስጥ የተወሰኑት ቀልብ የሚገዙ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የአንድ ሕፃን ሞግዚት በችሎቱ አቅርበው ያስወሰኑት ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ አንድ ሰው ያለፈቃዱ በተነሳው ሥዕል ወይም ፎቶ ላይ ያለውን ካሣ የማግኘት መብት የሚመለከት ሲሆን፣ ጉዳዩ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተነስቶ በመጨረሻ በሰበር ችሎቱ የመጨረሻ እልባት አግኝቷል፡፡ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ሰፊ የሕግ ትንተና ሊሰጥበት የሚችል አከራካሪ ፍርድ ባይሆንም መብታቸው ተጥሶ ባለመጠየቅ መብታቸው ላይ ለተኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተማሪ ስለሚሆን በዚህ ጽሑፍ እንመለከተዋለን፡፡ 

የጉዳዩ አመጣጥ

ኤል ሲውዲ ኬብልስ የተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ምርቶቹን ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ዘዴ በአንድ ሕፃን (ሪያን ሚፍታህን) ምስል ነው፡፡ ድርጅቱ የሕፃኑን ፎቶ በማንሳት በግዙፍ የማስታወቂያ ሰሌዳ በማሠራት ድርጅቱንና ምርቱን በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች አስቀመጠ፡፡ በተጨማሪም ኢንተርኔትን በመጠቀም በግብፅና በሌሎች 25 አገሮች ምርቶቹን አስተዋወቀ፡፡ ድርጅቱ ይህን ሁሉ ያደረገው ያለ ሕፃኑም ሆነ አሳዳጊው ዕውቅናና ፈቃድ ነው፡፡ አሳዳጊው ጉዳዩን ባወቁ ጊዜ የድርጅቱ ሥራ ሕገወጥ እንደሆነ በመግለጽ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል ይጠይቁታል፡፡ ድርጅቱ ለመክፈል ፈቃደኛ ባይሆንም ከተወሰኑ ጊዜያት ድርድር በኋላ ግን ብር 15,000 ለመክፈል ይስማማል፡፡ የሕፃኑ አሳዳሪ ድርጅቱ በማስታወቂያ ሥራው ካገኘው ጥቅም አንፃር ክፍያው ተመጣጣኝና አነስተኛ መሆኑን ገልጸው ሳይስማሙ ቀሩ፡፡ ቀጥለውም ድርጅቱ በማስታወቂያ ሥራው የሕፃኑን ፎቶ ለተጠቀመበት ጊዜያት (ከሰኔ ወር 2000 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ የካቲት ወር 2004 ዓ.ም.) ብር 400,000 በካሣ መልክ እንዲከፍላቸው ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ አቀረቡ፡፡

የሥር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ

ሕፃኑ በሞግዚቱ አማካኝነት ላቀረበው ክስ ተከሳሹ ድርጅት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያና የመከላከያ መልስ ቢያቀርብም ፍርድ ቤቱን አላሳመነም፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱም የተከሳሽ ድርጊት የከሳሽን መብት መጣሱን በማረጋገጥ፣ ካሣውን በተመለከተ በርትዕ ብር 200,000 ሊሆን እንደሚገባ መጠኑን በመወሰን ተከሳሽ እንዲከፍል ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ ከሳሽም ተከሳሽም አልተደሰቱም፡፡ ተከሳሹ ኃላፊነቱን ለማውረድ፣ ከሳሽ ደግሞ የተወሰነልኝ ካሣ አነስተኛ ስለሆነ እንዲስተካከልልን ሲሉ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርበዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የከሳሽን የካሣ ይጨመርልኝ ጥያቄ ሰርዞ፣ ተከሳሽ ሊከፍለው የሚገባውን የካሣ መጠን በመቀነስ ብር 150,000 ተከሳሽ እንዲከፍል ወስኗል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህንኑ የይግባኝ ሰሚውን ፍርድ በማጽናቱ ጉዳዩ ለሰበር ደርሷል፡፡

የሰበር ችሎቱ ፍርድ

ሰበር ችሎቱ ተጠሪ የሕፃኑን ፎቶ ለኤሌክትሪክ ኬብል ምርቶች ለማስተዋወቅ ያለሕፃኑ ሞግዚት ፈቃድ መጠቀሙ የተረጋገጠ መሆኑን አስምሮበታል፡፡ ይህ ድርጊት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 27 ድንጋጌ መሠረት ያለፈቃድ ፎቶውን መለጠፍም ሆነ ማባዛት እንደማይቻል ገልጾ ካሣ መክፈሉ ተገቢ መሆኑን ተንትኗል፡፡ የካሣ መጠኑን በተመለከተ ግን የሰበር ችሎቱ ዳኞች ልዩነትን አሳይተዋል፡፡ የዳኞቹ አብዛኛው ድምፅ ተከሳሽ ብር 150,000 ካሣ እንዲከፍል መወሰኑ ተገቢ ነው ሲሉ አቋም ወስደዋል፡፡ ለአቋማቸው የወሰዱት ምክንያት የሚከተለው ነው፡፡

‹‹በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 29(2) መሠረት በርትዕ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ስዕሉን በአደባባይ በመለጠፍና በመሸጥ የተጠቀመው ሰው በዚሁ ምክንያት ያገኘው ሀብት ተመዛዛኝ በሚሆንበት መጠን ዳኞች ካሣ እንዲከፍሉ ሊወስኑበት እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው የሥር ፍርድ ቤት ተጠሪ የካሣውን መጠን ክዶ በመከራከሩና አመልካችም በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2141 በተመለከተው አግባብ ትክክለኛውን የካሣ መጠን በማስረጃ ያለማስረዳታቸው ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 29(2) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የካሣውን መጠን ብር 200,000 እንዲሆን የወሰነ ሲሆን፣ አመልካች በዚህ ውሳኔ ቅር በመሰኘትም በሥርዓቱ መሠረት የመስቀለኛ ይግባኝ አቅርበው ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የካሣ መጠኑን የሕፃኑ ፎቶ በማስታወቂያው ከገለጹት የምርት ዓይነቶች ጋር የሚኖረውና ሊያስገኝ ከሚችለው ጥቅም አንፃር፣ ከነባራዊው ሁኔታ በመነሳት በመመርመር በሥር ፍርድ ቤት የተወሰነው የካሣ መጠን የበዛ ሆኖ ማግኘቱን ጠቅሶ ብር 150,000 የካሣ መጠን ሊሆን እንደሚገባ ወስኗል፡፡ ይህ የካሣ ውሳኔ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 29(2) መሠረት ያደረገ በመሆኑ የሚነቀፉበት አግባብ የለም፤›› በማለት የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቷል፡፡

የልዩነት ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ዳኛ ግን ለሕፃኑ ሊከፈለው ይገባው የነበረው የካሣ መጠን ብር 200,000 እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እንደ ዳኛው አመለካከት የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የተከሳሽን ጥፋተኝነት በማፅናት የካሣ መጠኑን መቀነሱ ተገቢ አይደለም፡፡ ዳኛው በሰጡት ምክንያት ‹‹በመርህ ደረጃ የካሣ መጠንን አስመልክቶ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች በተወሰነ ፍርድ ላይ ለበላይ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ለማለት አይቻልም በማለት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2152 ሥር ከተደነገገው አኳያ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም፡፡ የካሣ መጠንን በተመለከተ ይግባኝ የሚፈቀደው በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2153 ሥር በተመለከቱት ሁኔታዎች ሲሆን ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤቶች ሁኔታዎቹ መኖራቸውን በፍርዱ ላይ አላሰፈሩም፤›› በማለት ሕፃኑ ሊካስ የሚገባው የካሣ መጠን ብር 200,000 ነበር ሲሉ አቋማቸውን አስፍረዋል፡፡

በአጠቃላይ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ገዥ ፍርድ ማንም ሰው ያለባለቤቱ ዕውቅናና ፈቃድ የሰውን ፎቶ ለማስታወቂያነት ከተጠቀመ በርትዕ ለሚወሰን ካሣ መጠን ኃላፊ እንደሚሆን ነው፡፡ ካሣ በርትዕ የሚወሰንበት መርህ፣ ካሣው ሲወሰን ግንዛቤ ሊወሰዱባቸው ስለሚገቡ ነጥቦችና የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ወዘተ. በሌላ ጽሑፍ የምንመለስበት ሆኖ የጉዳዩን አስተማሪነት ግንዛቤ በማስገባት የአገራችንን ሕግ ይዘት ዓላማውንና የሚሰጠውን ጥበቃ እንመልከት፡፡ 

የአገራችን ሕግ ስለ ሰው ሥዕል

የሰው ሥዕል ወይም ፎቶግራፍን በተመለከተ ስናነሳ ግንዛቤ ውስጥ የሚገቡት ሕጋዊ መብቶች የሥዕሉ ጥበቃ፣ ሥዕሉን የማሳተም ሥነ ምግባር፣ የፎቶግራፈሩና የፎቶው ባለቤት መብቶች ናቸው፡፡ የፎቶው ባለቤት ፈቃድ ሁልጊዜም ቢሆን አስፈላጊ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ በተለይ ግለሰቡ ፎቶውን በግል ሁኔታው የተነሳ፣ የተለየበትና በሕዝብ ቦታ ከሌሎች ጋር በጅምላ ያልተነሳው በሆነ ጊዜ የፈቃዱ አስፈላጊነት የታመነበት ነው፡፡ ፎቶውን ለንግድ ዓላማ ለማዋል ደግሞ በማንኛውም ሁኔታ የግለሰቡ ፈቃድ መረሳት የለበትም፡፡ የፈቃዱ ዓይነትና ደረጃው እንደነገሩ ቢለያይም የፈቃድ መኖር በሁሉም የሕግ ሥርዓት ተመሳሳይ ነው፡፡ 

ሰው በምሥሉ ወይም ሥዕሉ ላይ ያለው መብቱ የሰውነት መብቶች (Personality Rights) አንዱ ክፍል ነው፡፡ ምሥሉን የማንሳት፣ የመለጠፍና የመጠቀም መብት ራስን ከመግለጽና ከግላዊነት መብት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በአንድ በኩል አንድ ሰው የራሱ ሥዕል ወይም ምሥል ለንግድ ዓላማ የመዋሉን ነገር የመቆጣጠር መብት አለው፡፡ የዚህ መብት መገለጫው ፎቶውን ለማስታወቂያነት በማዋል የሚፈጠረውን ሁኔታ መቆጣጠር ነው፡፡ ማስታወቂያው ለንግድ ዓላማም ይዋል ለሌላ ከፎቶ ግራፈሩ የኮፒ ራይት መብት ይልቅ የፎቶው ባለቤት ያለው መብት ቀዳሚ ነው፡፡ ባለቤቱ ለመነሳት ሊፈቅድ፣ ከተነሳም በኋላ ለምንም አገልግሎት ሲውል ፈቃዱን የመግለጽ መብት አለው፡፡ ከፎቶው ጋር የተያያዘው የግላዊነት መብት ደግሞ የፎቶው ባለቤት ካልፈቀደ ፎቶው ለራሱ ብቻ እንጂ ለሕዝብ ዕይታ፣ ግምገማና ትችት የማይቀርብ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ከፎቶ ጥበቃ አንፃር ከአገር አገር ቢለያይም የግላዊነት መብት በብዙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ዕውቅና የተሰጠው መብት ነው፡፡ ሥዕል ያለአግባብ የባለቤቱን የግል ወይም የቤተሰብ ሕይወት ሊገረስስ ወይም ሊጥስ አይገባም፡፡ ፎቶግራፉን የተመለከቱ የግላዊነት የሕግ ጭብጦች ፎቶው የተነሳው በግል ቦታ ነው ወይስ በአደባባይ በሚለው የሚወሰኑ ናቸው፡፡ በመዝናኛ ቦታ ድንኳኑ ውስጥ የተነሳው ሰው ፎቶ ግላዊ ሲሆን በሕዝብ ስብሰባ የተነሳው ደግሞ የአደባባይ መሆኑን በምሳሌ መረዳት ይቻላል፡፡

የሰው ሥዕል ወይም ፎቶግራፍን የተመለከተ የሕግ ጥበቃዎች በአገራችን ሕግጋት የተቀረፁት ከ60 ዓመታት በፊት በፍትሐ ብሔር ሕጋችን የመጀመሪያ መጽሐፍ ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 26 እስከ 30 የተደነገጉት ድንጋጌዎች የመብቱን ምንነት፣ ወሰንና ልዩ ሁኔታዎችን የሚዘረዝር ነው፡፡ በመርህ ደረጃ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 26 እንደተደነገገው ‹‹ባለ ፎቶግራፉ ወይም ባለሥዕሉ ካልፈቀደ በቀር የማንም ሰው ፎቶግራፍ ወይም ሥዕል በሕዝብ አደባባይ ሊለጠፍም ሆነ ሊባዛ ሊሸጥ አይችልም፡፡›› ይህ ድንጋጌ መሠረታዊ ሲሆን ያለፈቃዱ ፎቶው ለተለጠፈበት ወይም ለተባዛበት ወይም ለተሸጠበት ግለሰብ መብት ይሰጣል፡፡  የፎቶግራፉ ባለቤት በሞተ ጊዜ መብቱ ለቤተ ዘመዱ የሚተላለፍ ሲሆን ቤተ ዘመዶቹ በባለ ፎቶግራፉ ቦታ ተተክተው ሰውዬው ሊኖረው የሚችለውን መብት መጠቀም እንደሚችሉ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 30 በግልጽ ይደነግጋል፡፡

የዚህ መብት መጣስ ሦስት ውጤቶች እንደሚኖሩት በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 29 ተደንግጓል፡፡ የመጀመሪያው መብቱ የተጣሰበት ሰው አድራጎቱ እንዲወገድለት ለመጠየቅ (ለማስገደድ) መብት ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ ያለፈቃዴ ፎቶዬ በአደባባይ ስለተለጠፈ፣ ስለተሸጠ ወይም ስለተባዛ እንዲቆምልኝ በሚል ፍርድ ቤቱ እንዲያግድለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ሁለተኛው ሥዕሉን በመለጠፍ ወይም በመሸጥ የተጠቀመው ሰው በዚህ ምክንያት ካገኘው ሀብት ተመዛዛኝ በሆነ መጠን ከዳኞች ካሣ የማግኘት መብቱ ነው፡፡ ይህ ካሣ ዳኞች በርትዕ የሚወሰኑት ሲሆን የግራ ቀኙን ድርጊት፣ የበደሉን ከባድነት፣ የተገኘውን ጥቅም፣ የሥርጭት አድማሱን፣ የጊዜውን ቆይታ ወዘተ. ከባቢ ሁኔታዎችን በማገናዘብ የሚወሰኑት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የተመለከትነው የፍርድ ቤት ጉዳይ ይህንን መሠረት አድርጎ መወሰኑን ልብ ይሏል፡፡ ሦስተኛው የሥዕሉ መታገድ ካልቆመ ባለመብቱ በስም ማጥፋት በመክሰስ የሞራል ጉዳት ካሣ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የሞራል ካሣ ለመጠየቅ ባለመብቱ መብቱን የጣሰው ሰው በፍርድ ቤት እንዲታገድ የተሰጠውን ትዕዛዝ አለማክበሩን ማስረዳት የሚጠበቅበት ሲሆን፣ ካሣው ከሁለተኛው በርትዕ ከሚገኘው ካሣ በተጨማሪ የሚጠየቅ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ 

ከላይ የገለጸውን ሕግ ለተገነዘበ ሰው ተግባራዊ ጥያቄ ማቅረቡ አይቀርም፡፡ በኅብረተሰባችን በየአደባባዩ ፎቶአቸው ተባዝቶ እንድንገዛቸው የምንጠየቃቸው ታዋቂ ሰዎች፣ አርቲስቶች፣ የፖለቲካ ሰዎችና ምሁራን ፈቀዳቸውን ሰጥተው ስለመሆኑ  መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡ ሕጉ ሁሉም ሰው በፎቶግራፉ ላይ እንዲፈቅድ ወይም ፈቃዱን እንዲገልጽ አያስገድድም፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 28  በግልጽ እንደሚደነግገው በሕጉ በተገለጹ አራት ምክንያቶች ባለፎቶግራፉ ባይፈቅድም በአደባባይ ቢለጠፍ፣ ቢባዛና ቢሸጥ ለመቃወም አይችልም፡፡ እነዚህም ባለፎቶግራፉ የታወቀ ሰው በመሆኑ ወይም በሚያከናውነው ሕዝባዊ ሥራ ምክንያት ወይም በፍርድና በፖሊስ መሥሪያ ቤቶች በኩል አስፈላጊነቱ የተረጋገጠ ምክንያት ያለው በመሆኑ ወይም ለኪነጥበብ (ለሳይንስ) ለሥልጣኔ አስተዳደግ ወይም ለትምህርት መስጫ ጥቅም በመሆኑ ወይም ደግሞ የፎቶግራፉ መባዛት የተፈጸመው በክብረ በዓል ወይም በሕዝብ ስብሰባ ላይ ከተፈጸመ ሥርዓት ጋር ግንኙነት ባለው ምክንያት ቢሆን የባለፎቶግራፉ ፈቃድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ 

ከሕጉ ለመረዳት የምንችለው አንዳንድ ሰዎች ለተወሰነ ዓላማ በፎቶግራፋቸው መለጠፍና መሸጥ ላይ ላይፈቅድ እንደሚችሉ ነው፡፡ የሕጉ አመክንዮ የተለያዩ ጥቅሞችን ለማስታረቅ በማሰብ ይመስላል፡፡ ታዋቂ ሰው የሕዝብ የመሆኑ ጉዳይ፣ ሕዝባዊ ሥራም የሚሠራው ለሕዝብ በመሆኑ፣ የፎቶግራፎቹም ዓላማ ለአጠቃላይ የሕዝብ ጥቅም በሆነ ጊዜ ከግለሰቡ ጥቅም ይልቅ ሕጉ የሕዝቡን ጥቅም ያስቀድማል፡፡

እንደ ማጠቃለያ

በአገራችን በልማድ ወይም በቸልተኝነት የመብት ጥሰቶች በማይጠየቁበት ሁኔታ በዚህ ጽሑፍ የተመለከትነው የሰበር ፍርድ አስተማሪ ነው፡፡ ሰዎች በድፍረት የግለሰቦችን መብት ከጣሱ በፍርድ ኃላፊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ ጽሑፍ እንደተመለከትነው ተከሳሽ የሆነው ድርጅት የሕፃኑን አመልካች ፎቶ ያለፈቃዱ ለማስታወቂያ በማዋሉ ብር 150,000 በካሣ መልክ እንዲከፍል ተወስኖበታል፡፡ ድርጅቱና መሰል ተቋማት ከዚህ ፍርድ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ማንኛውንም በሕግ ፊት ዋጋ ያለው ግብይት ከመፈጸም በፊት ሕጉ ምን ይላል? በሕጉ ምን መብት አለ? ምንስ ግዴታ ተጥሎብኛል? ብሎ ከውሳኔ በፊት መመርመሩ ወይም የሕግ ምክር መጠየቁ ተገቢ ነው፡፡ በየቤቱ የተቀመጡ፣ የተዳፈኑ የመብት ጥሰቶች ወደ ሕግ ፊት በቀረቡ መጠን ኅብረተሰባችን መብትና ግዴታውን አውቆና አክብሮ የሚኖርበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተመሳሳይ የሆኑትን ብናነሳ ያለ ዘፋኙ ፈቃድ፣ ያለ አቀናባሪውና ያለ አሳታሚው ፈቃድ ሙዚቃውን በሬዲዮና በቴሌቪዥን፣ በፊልምና በድራማ በዘፈቀደ የሚለቁት ሰዎች ጉዳይ ቀጣዩ የፍርድ ቤት ተረኛ ቢሆንስ ማን ያውቃል?

ተጻፈ በ 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው getukow@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡