የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች በመልካም አስተዳደር እጦት ተማረናል አሉ


 press

“የደሞዝ ጭማሪው ለሌላው ሲደርስ ለጋዜጠኛው አልደረሰም” ጋዜጠኞች

“ጭማሪው ሰሞኑን በቦርዱ ተወስኗል፤ በቀጣዩ ወር ይደርሳቸዋል” አቶ ሽመልስ ከማል

“ድርጅቱ በደመነፍስ ይመራል የሚለው አጉል አሉባልታ ነው” የፕሬስ ድርጅት ሥ/አስኪያጅ

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስር የሚታተሙት አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሪሳ እና አል-አለም ጋዜጠኞች በመስሪያቤታቸው የመልካም አስተዳደር እጦት እየተማረሩ መሆኑን ገለፁ፡፡ መንግስት በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር እያወቀ ምላሽ አለመስጠቱ እንዳሳዘናቸው ጋዜጠኞቹ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ለጋዜጠኞች አለመድረሱን የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ላለፉት አራት ዓመታት የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ሽመልስ ከማል አንድም ቀን ሰብስበው አወያይተዋቸው እንደማያውቁ በምሬት ገልፀዋል፡፡

“ድርጅቱ በዚህ ዓመት ይህን እሰራለሁ ብሎ ያስቀመጠው ግብ የለም፣ ጋዜጠኛው የሚመራው ብቃት በሌለው ስራ አስኪያጅ ነው፣ ይህንንም በስብሰባ ለራሳቸው ለስራ አስኪያጁ ተናግረን ችግሩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ያጣራውን ለሚመለከተው አካል ቢያቀርብም የተሰጠ ምላሽ የለም” ብለዋል – ጋዜጠኞቹ፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው፤ አንድም ቀን አወያይቶን አያውቅም የሚለው ፍፁም ሀሰትና የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ገልጸው፣ በየጊዜው ከጋዜጠኞችና ከኤዲተሮች ጋር እንደሚወያዩና በኤዲተሮችና ዋና አዘጋጆች ፎረም ላይ የተለያዩ ሃሳቦች እየተነሱ በምክክር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

“ከሰራተኛው መካከል የራሳቸው ጥቃቅን የጥቅም ግጭት ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች የሚነዙት አሉባልታ እንደ አጠቃላይ የሰራተኛው ችግር ተደርጎ መነሳቱ መሰረተ ቢስ ነው” ብለዋል – አቶ ሽመልስ፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰብስቤ ከበደን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረናቸው በሰጡት ምላሽ “ድርጅቱ በእቅድና በፕሮግራም እንደሚመራ በቢሮ ተገኝቶ አሰራሩን ማረጋገጥ ይቻላል” ያሉ ሲሆን፣ አንዳንድ የግል ችግር ያለባቸው ግለሰቦች የድርጅቱንና የአመራሩን ስም ለማጥፋት ሆን ብለው የሚነዙት ተጨባጭ ያልሆነ ወሬ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ድርጅቱ ችግር ቢኖርበት ኖሮ ሰራተኛውን የሚያወያይበት የስብሰባ መድረክ እያዘጋጀ አያወያይም ነበር” ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በቅርቡ አጠቃላይ ስብሰባ ተጠርቶ ከሰራተኞች የተለያዩ አስተያየቶች መሰጠታቸውንና በውይይት መድረኩ ላይ የተነሱትን አንዳንድ ክፍተቶች እንደግብአት በመጠቀም የአሰራር ማስተካከያ እየተደረገ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

ጋዜጠኞቹ በበኩላቸው ለመልካም አስተዳደር እጦቱ እንደዋና ማሳያ ያቀረቡት የድርጅቱ ህንፃ በሁለት ዓመት ተገንብቶ ይጠናቀቃል ቢባልም አራት አመት ፈጅቶ እንኳን አሁንም ይቀረዋል፣ የሰራተኛ የቅጥር ሁኔታው ግልፅነት የለውም፣ ሹፌር ሳይቀር በፍሪላንስ የሚቀጠርበት ሁኔታ አለ፣ የደሞዝ ጭማሪና የእድገት ሁኔታ በአድሎአዊ አሰራር የተተበተበ ነው፤ በዚህም የተነሳ ለጋዜጦቹ አለኝታ የሚባሉ ወደ 50 ሰራተኞች ባለፈው ዓመት ለቀዋል፤ ዘንድሮም የለቀቁ አሉ በማለት ተናግረዋል፡፡ መንግስት ይህን ሁሉ ችግር ያውቃል፤ ግን ማስተካከያ አልተደረገም ብለዋል፡፡ ፕሬስ ውስጥ በሲቪል ሰርቪስና በቦርድ የሚተዳደር ሁለት ዓይነት ሰራተኛ መኖሩን ጋዜጠኞቹ ገልጸው፣ በሲቪል ሰርቪስ የሚመራው ሰራተኛ ጭማሪው ሲደርሰው የእኛ ዘግይቷል ብለዋል፡፡

“በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ጋዜጠኞች ደሞዝ የፕሬሱ ጋዜጠኞች ይበልጥ ነበር” ያለው አንድ ቅሬታ አቅራቢ ጋዜጠኛ፤ ኢዜአዎች ፕሬስ አቻ ድርጅት ሆኖ እንዴት ደሞዝ ይበልጡናል በሚል ላነሱት ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ ተሰጥቷቸው ደሞዛቸው መስተካከሉን አስታውሶ፤ የእኛ አቻ ድርጅት በሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) በቅርቡ እስከ 200 ፐርሰንት የደሞዝ ጭማሪ ቢደረግም በእኛ ድርጅት ምንም የተባለ ነገር ባለመኖሩ ጋዜጠኛው በድርጅቱ ተስፋ እየቆረጠ ነው ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ጭማሪውን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፤ በሲቪል ሰርቪስ የሚተዳደሩት የሚከፈላቸው በመንግስት በመሆኑ እንደማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ጭማሪው ቀድሞ እንደረሳቸው አምነው፣ ሆኖም በቦርድ ለሚተዳደሩት ጋዜጠኞች የሚከፈለው ድርጅቱ ከማስታወቂያና ከጋዜጣ ሽያጭ ከሚያገኘው ገቢ ላይ በመሆኑና ስኬሉ ስለሚለያይ ቦርዱ ተወያይቶ ውሳኔ እስኪሰጥበት ሲጠበቅ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ “ውይይቱ ተጠናቅቆ ቦርዱ ከትላንት በስቲያ ስለወሰነላቸው ጭማሪው በቀጣዩ ወር ይደርሳቸዋል” ብለዋል – ሥራ አስኪያጁ፡፡

በስብሰባው ላይ የአመራር ብቃት የለዎትም፤ ቦታውን ይልቀቁ በሚል ከጋዜጠኞች ቅሬታ ስለመቅረቡ አቶ ሰብስቤን ጠይቀናቸው፤ “እኔ ስብሰባ ላይ እንዲህ የሚባል ትችት አልቀረበብኝም” ያሉት አቶ ሰብስቤ፤ እርግጥ በስነ-ምግባርም ሆነ በእውቀት ብቃት የሌለው አንድ ጋዜጠኛ “ቦታውን ልቀቅ” ብሎ በግል ተናግሮኛል፤ ጋዜጠኛው አሁን ስራ ለቋል” ብለዋል፡፡ ብዙ ጋዜጠኞች ከድርጅቱ ይለቃሉ ስለሚባለው አንስተንባቸው በሰጡት ምላሽ፤ “ከጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ጋዜጠኞች ይለቃሉ፣ የተሻለ ደሞዝ ሲያገኙ የትኛውም መ/ቤት እንደሚልቁት ሁሉ እዚህም ይለቃሉ፤ በዚያው ልክ እኛም እንቀጥራለን” ብለዋል፡፡ ሰራተኞቹ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሩ በአስቸኳይ ካልተቀረፈ፣ እንደአቻ ድርጅት ማግኘት የሚገባንን የደሞዝ እድገት ካላገኘንና አድሎአዊ አሰራር ካልቀረ ድርጅቱን ለመልቀቅ እንገደዳለን ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው፤ በድርጅቱ ውስጥ መሻሻሎችን ለመፍጠርና ወደ ኮርፖሬት አደረጃጀት ለመቀየር ስራዎች ተሰርተው በመጠናቀቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s