Archive | October 17, 2014

ከፍቶኛል፡፡ በጣም ቅር ብሎኛል፡፡ ደስ የሚል ስሜት አይሰማኝም፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መታሰር ነው (መስፍን ጌታቸው የሰው ለሰው ድራማ ደራሲ )

መስፍን ጌታቸው (የሰው ለሰው ድራማ ደራሲ )
ተመስገን ደሳለኝ ??
ከፍቶኛል፡፡ በጣም ቅር ብሎኛል፡፡ ደስ የሚል ስሜት አይሰማኝም፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መታሰር ነው፡፡
ተሜ በጣም የማከብረው ወዳጄ ነው፡፡ ትህትናወ፤ቅንነቱ፤ሰው አክባሪነቱና አገር ወዳጅነቱ ወዘተ ተሜን በቀላሉ በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ የሚያደርጉት ባህሪያት ናቸው፡፡
ከዚህ ውጪ ተሜ ላመነበት ነገር በድፍረት እራሱን አሳልፎ ለመስጠት የማያመነታ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነው፡፡ በሀገራችን ነፃ ሚዲያ ታሪክ አንድ የህትመት ውጤት ሲዘጋበት ወይም ከገበያ ውጪ ሲሆንበት ” አከተመ ” ብሎ ባለመቀመጥ ከፍትህ እስከ ፋክት ድረስ በተለያየ መንገድ እምነቱን ዳር ለማድረስ እስከመጨረሻው በፅናት የቆመና አዲስ ታሪክ መስራት የቻለ ብርቱ ጋዜጠኛ ነው፡፡
ከሙያው ባሻገር በግል ህይወቱም ቢሆን በጣም ደግና ተግባቢ የሆነ መልካም ሰው ሲሆን ሌሎችን መርዳትና ማገዝም ልዩ መታወቂያው ነው፡፡ ሁለት መንታ ወንድማማች ህፃናትን አጠቃላይ ወጪያቸውን በመቻል እያስተማረና እሳሳደገ እንደሚገኝ አውቃለሁ፡፡
ከሱ መልካም ስብዕና አንፃር የሚረዳቸው ሰዎች ከዚህ በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የቅርብ ወዳጆቹ ሁሉ ያምናሉ፡፡ነገር ግን ይሄን በጎ ተግባሩን መናገርና ለገበያ ማቅረብ የማይፈልግ በመሆኑ ቁጥራቸውን በትክክል ማወቅ አይቻልም፡፡ሁለቱን ወንድማማቾች እያሳደገ መሆኑን እኔ የሰማሁት ከሱ አንደበት ሳይሆን ስሙን አንስተው ከማይጠግቡት የህፃናቶቹ ወላጆች ነው፡፡ እናም ወዳጆቼ ተሜ ብቻውን ሳይሆን የታሰረው ቢያንስ የነገይቷ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ መሆን ከሚችሉ ሁለት ህፃናት ጋ ጭምር ነው፡፡
የተሜን ፅሁፎች ሁሉንም አይደለም የምወዳቸው፡፡ ሰው እንደመሆኔ መጠን እዚህ ጋ ልክ አይደለም እንዲህ ባይል ኖሮ ጥሩ ነበር በማለት የምነቅፋቸውና ለራሱ የምነግራቸው የተወሰኑ ፅሁፎች ይኖራሉ፡፡በአጠቃላይ ግን የወርቃማ ብዕሩ ትልቅ አድናቂ ነኝ፡፡
እናም አኔ የማውቀው ተሜ የተሸለ ነገር ለማድረግ ከማሰብ ባለፈ በብዙ መልኩ አገር የሚያጠፋ ክፉ ተግባር ውስጥ ይገባል ብሎ ማሰብ በጣም ይከብዳል፡፡
ተሜ አንድ ቀን ሊታሰር እንደሚችል በእርግጠኝነት ደጋግሞ እየተናገረና አገር ለቆ እንዲሰደድ የሚቀርቡለትን ተደጋጋሚ ምክሮች ፊት እየነሳ ቅንጣት ሳይሸበር በልበ ሙሉነት ስራውን ለመጀመር ደፋ ቀና ሲል የቆየውስ ያለ ምክኒያት ይመስላችኋል?…..እኔ አይመስለኝም

mesfin