Archive | November 10, 2014

የበርሊን ግንብ መናድና የዓለም ፖለቲካ

ጎርቫቾቭን ታቸር ከለንደን ሬገን ከዋሽግተን እየተቀባበሉ ሲያንቆለጳጵሷቸዉ፤ መራሔ መንግሥት ሔልሙት ኮል የቀዳሚዎቻቸዉንም፤ የራሳቸዉንም የሕዝባቸዉንም ሕልም ምኞት እዉን ለማድረግ ሞስኮዎችን እንደ ጥሩ ወዳጅ ቀረቧቸዉ።አግባባቡ አባበሉ።

መሽቷል።በርሊኖች ግን የነጋ ያክል ከምሥራቅም-ከምዕራብም ወደዚያ ግዙፍ ግንብ ይተማሉ።ካጠገቡ ሲደርሱግንቡን ከምሥራቅም፤ ከምዕራብም፤ ካናቱም ይወቅሩ-ይቀጠቅጡ፤ይሸራርፉ-ይቦዳድሱት ያዙ።ግንቡ ይጥፋ እያሉ፤-

በርግጥም ለበርሊኖች ሊነጋ ነዉ።ዙድዶቸ ሳይቱንግ የተሰኘዉ ጋዜጣ እንደዘገበዉ ግን የሚነጋዉ ለበርሊኖች ብቻ አይደለም ለመላዉ ጀርምን እንጂ።«በዚሕ ምሽት፤ የጀርመን ሕዝብ ከመላዉ ዓለም ሕዝብ ሁሉ እጅግ ደስተኛ ነዉ።»የምዕራብ በርሊን ከንቲባ ቫልተር ሞምፐር የጋዜጣዉን አባባል ደገሙት

«የጀርመን ሕዝብ ከዓለም እጅግ ደስተኛዉ ሕዝብ ነዉ።» ሕዳር 9 1989።ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።የተቀረዉ ዓለም እንደ ጀርመኖች ይደሰት፤ ወይም በተቃራኒዉ ያዝን ይሆናል።ጀርመንን ለዘመናትለሁለት የገመሰዉ ግንብ- መደርመስ ግን ግንቡን ያሳጠረዉ ኮሚንስታዊ ሥርዓት መገርሰስም መሆኑ እዉነት ነዉ።የዓለም የአርባ-አምስት ዘመን ፍጥጫፍፃሜነቱም ሐቅ።ዘንድሮ ትናንት ሃያ-አምስት ዓመቱ።ላፍታ እንዘክረዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ጀምሮ ሶቬት ሕብረት ከምትቆጣጠረዉ ወይም ከጦርነቱ ፍፃሜ በሕዋላ «የሶቬት ዞን» ተብሎ ከሚጠራዉ ምሥራቃዊ ጀርመን፤ ምዕራባዉያኑ መንግሥታት ወደ ሚቆጣጠሩት ምዕራብ ጀርመን የሚፈልሰዉ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ ለሞስኮ ኮሚኒስቶች አሳሳቢ፤ ለምሥራቅ በርሊን ተከታዮቻቸዉ ደግሞ አስጊ ነበር።

ጀርመን በይፋ ለሁለት ተገምሳ-ቦን እና ገሚስ በርሊን ላይ-ካፒታሊስታዊ እና ኮሚኒስታዊ መንግሥታት ከቆመላት ከ1949 እስከ 1952 በተቆጠሩት ሰወስት ዓመታት ብቻ 2 ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ ከምሥራቅ ጀርመን ወደ ምዕራብ ፈልሷል።

ከምስራቅ ወደ ምዕራብ የሚየፈልሰዉ ጀርመናዊ ቁጥር መጨመር፤ ሶቭየት ሕብረት በምትቆጣጠራቸዉ በሌሎች የምሥራቅ አዉሮጳ ሐገራት ብልጭ-ድርግም የሚለዉ ፀረ-ኮሚኒስታዊ እንቅስቃሴ መደጋጋም ያሳሰባቸዉ የሶቭየት ሕብረቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን «የስታሊን ማስታወሻ» የተባለዉን «የእርቅ» ሐሳብ ፃፉ።መጋቢት 1952።

«በዚሕ ሐሳብ መሠረት የሶሻሊስት ሶቪየት ሕብረት ሪፐብሊክ መንግሥት የሠላም ሥምምነት ለመፈራረምና የጀርመንን አንድነት ዳግም ለመመሥረት በፅናት መቆሙን ያረጋግጣል።የሶቪየት መንግሥት በመጋቢት 10ሩ ማስታወሻዉ፤ምዕራባዉያኑ ሐያላንም ሆኑ ቦን ተቃራኒ መልስ ለመስጠት በማያሻማ ሁኔታ አቋሙን ግልፅ አድርጓል።»

የያኔዉ የምሥራቅ ጀርመን ሶሻሊስት አንድነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ኦቶ ግሮተቮል።በግልፅ ከቀረበዉ ጥያቄ ይልቅ ከጥያቄዉ ጀርባ ያለዉን አላማ መስተንተኑን የመረጡት የዋሽግተን፤ ለንደን-ፓሪስ ተሻራኪዎች ጥያቄዉን ዉድቅ አደረጉት።

ሰዉዬዉ ተናደዱ።እድሜም፤ የጤና እጦትም ተጫችኗቸዋል። ምዕራባዉያኑን ለመበቀል ግን አልሰነፉም።የምዕራባዉያኑን ስስ ብልት እንዲጠቁሟቸዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ቫየስላቭ ሚኻኢሎቪች ሞሎቶቭን አዘዙ።ሞሎቶቭ ጊዜ አላጠፉም የምሥራቅ ጀርመን መሪዎች ወደ ምዕራብ ለመጓዝ በሚፈልገዉ ሕዝብ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ያድርጉ የሚል ሐሳብ ጠቆሙ።

ስታሊን ተቀበሉት።የምሥራቅ ጀርመን መሪዎችን ወደ ሞስኮ አስጠሩ።«ሁኔታዉ ሊታገሱት የማይገባ ነዉ» አሉ ጠንካራዉ ሰዉዬ።ምሥራቅና ምዕራብን የሚለያየዉ መስመር-እንደ ድንበር መቆጠር አለበት።እንደ ማንኛዉም ድንበር አይደለም-እንደ አደገኛ ድንበር እንጂ።ጀርመኖች ድንበሩን በሕይወታቸዉ ጭምር ማስከበር አለባቸዉ።»

ትዕዛዙ አይጣስም።የምሥራቅ ጀርመን መሪዎች መስመሩን በሽቦ አሳጠሩት።ሚያዚያ 1952።የሞስኮ-ምሥራቅ ን እርምጃ ምዕራቦች አወገዙት።ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚደረገዉ ጉዞ ግን በእጅጉ ቀነሰ።እየተሽሎከለከ-ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚሰርገዉን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ማስቆም ግን አልተቻለም።

ስታሊንን የተኩት ግዮርጊ ማሌንኮቭ-ብዙም ሳይሉ፤ ምንም ሳያደርጉ በኒኪታ ኽሩስቾቭ ተፈነገሉ።ክሩስቾቭ ስታሊን በሽቦ-ያሳጠሩትን ወሰን በግምብ በማስለሰን የስታሊን ተገቢና ጠንካራ ወራሽነታቸዉን አረጋገጡ።ነሐሴ 1961።እንደተለመደዉ ምዕራቦች ተቃወሙት።በ1963 በርሊንን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ ፓሬዝዳንት ጆን አፍ ኬኔዲ ዝነኛ ንግግር የዉግዘቱ ንረት መገለጫ ነበር።«በርሊናዊ ነኝ።»«ነፃ ሰዎች በሙሉ የትም ቢኖሩ የበርሊን ዜጎች ናቸዉ።ሥለዚሕ እንደነፃ ሰዉ እኔ በርሊናዊ ነኝ የሚሉትን ቃላት እስጠቀም ኩራት ይሰማኛል።»

የኬኔዲ ንግግር የምዕብ በርሊንን ሕዝብ ስሜት መነቅነቅ ብቻ ሳይሆን ምዕራባዉያን መንግሥታት ግንቡን ለማፈረስ መቁረጣቸዉንም ጠቋሚ ነበር።በዲፕሎማሲዉም፤ በስለላ፤ በገንዘብ-ማስፈራራቱም ያን ግዙፍ ግንብ ከነ-ኮሚንስታዊዉ ሥርዓት ለመናድ ይወዘዉዙት ገቡ።የሞስኮዎች አፀፋም ቀላል የሚባል አይደለም።

ምሥራቅ ጀርመኖች «የፀረ-ፋሽት ትግል መከላከያግንብ« Anti-Faschistischer Schutzwall»የሚሉትን ግንብ የሚዳፈርን እንደሚያጠፉት ዛቱ።«ድንበራችንን የማያከብር ዋጋዉ-ጥይት ነዉ።»አሉ አንዱ ጄኔራል።ዛቻዉ በዛቻ አልቀረም።ከወላጅ-ወዳጅ ዘመዱ ለመቀየጥ፤ ከጎመራዉ ምጣኔ ሐብት ለመቋደስ፤ አለያም ከኮሚስታዊ ሥርዓት ለማምለጥ እስከዚያች ቀን ድረስ ከሞከሩ ቢያንስ አንድ መቶ ያሕል ሰዎች ተገድለዋል።ቁጥሩ አወዛጋቢ ነዉ።ሰዉ ግን ተገድሏል።

የምሥራቅ-ምዕራቦች ጉልበት መፈታተሻ የሆነዉን ያን ግንብ ለማስፈረስ ምዕራባዉያን መንግሥታት ያላወገዙ፤ ያልዛቱ፤ያላስጠነቀቁበት ዘመን የለም።የግንቡ መናድ በዉጤም የኮሚኒዝም ሥርዓት ፍፃሜ ብቅ ያለዉ ግን ከራሷ ከኮሚንስታዊ ሥርዓት መስራችና አራማጅ ከሶቭየት ሕብረት እንጂ ከሌላ አልነበረም።ሚኻኤል ሰርግየቪች ጎርባቾቭ።

ጎርቫቾቭ በ1985 በዉርስ ያገኙትን ሥልጣን በተደላደሉ ማግሥት ያን ከ1917 ጀምሮ ሞስኮ ላይ የፀናዉን ኮሚንስታዊ ሥርዓት ቀስበቀስ ይመነጋግሉት ገቡ።የዋሽግተን-ለንድን፤ የፓሪስ-ቦን ፖለቲከኞችን የጎርቫቾቭ እርምጃን እርምጃ ለማፋጣን፤ ጎሮቫቾቭን ለማጃገን-እንዳዴም ለመጫን ይረባረቡ ያዙ የብሪታንያዋ ጠቅላይ ሚንስትር ማርጋሬት ታዘር ከዚሕ ሰዉዬ ጋር ተግባብቶ መሥራት አይከብድም እያሉ ሲያሞጋግሷቸዉ፤ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን ደግሞ እባክዎ ይሕን ግንብ ይናዱ እያሉ ይጎተጉቷቸዉ ነበር።

«ሶቭየት ሳትሳሳት ልትወስደዉ የምትችለዉ አንድ እርምጃ አለ።ይሕ እርምጃ የሰላምና የነፃነትን መሠረት ያጠናክረዋል።ዋና ፀሐፊ ጎርቫቾቭ ሠላም ከፈለጉ፤ ለሶቭየትና ለምሥራቅ አዉሮጳ ብልፅግናን ከተመኙ፤ ነፃነትን ከፈለጉ ወደዚሕ በር ይምጡ።ሚስተር ጎርቫቾቭ ይሕን በር ይክፈቱ።ሚስተር ጎርቫቾቭ ይሕን ግንብ ያፍርሱ።»

ጎርቫቾቭን ታቸር ከለንደን ሬገን ከዋሽግተን እየተቀባበሉ ሲያንቆለጳጵሷቸዉ፤ መራሔ መንግሥት ሔልሙት ኮል የቀዳሚዎቻቸዉንም፤ የራሳቸዉንም የሕዝባቸዉንም ሕልም ምኞት እዉን ለማድረግ ሞስኮዎችን እንደ ጥሩ ወዳጅ ቀረቧቸዉ።አግባባቡ አባበሉ።እና ጎርቫቾቭ «አንድ ሕዝብ በግንብ ለሁለት ተገምሶ መኖር የለበትም አሉ።»ትክክለኛዉ ትዕዛዝ ከሞስኮ ምሥራቅ በርሊን ደረሰ።

ሕዳር 9 1989።ከምሽቱ አንድ ሰዓት።ዜና።«ከዚሕ ጊዜ ጀምሮ የጀርምን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዜጎች በሁሉም አቅጣጫ ወደ ፌደራል ጀርመን መጓዝ ይችላሉ።»

ሕዝበ-በርሊን ከምሥራቅም ወደ ምዕራብ፤ ከምዕራብም ወደ ምሥራቅ ይግተለተል ያዘ።መሐል ተገናኙ።ግንቡ ጋ።ግንቡን ይቀጠቅጡት ያዙ።ግንቡም፤ኮሚንስታዊዉ ሥርዓትም ይቀረደድ ያዘ።ትናትን ሐያ አምስት ዓመቱ።

ግንቡ የተናደበት፤ እንደ ግንቡ ሁሉ የዓለም ልዕለ ሐያል የነበረችዉ ሶቮየት ሕብረት ምሥራቅ አዉሮጳን ጨምድዳ የያዘችበት ጥርስ-ጥፍሯ መርገፍ የጀመረበት፤ ሪፐብሊኮችዋ እያፈተለኩ ታላቅ ግዛትዋ መሸራረፍ የጀመረበት ሃያ አምስተኛ ዓመት ትንት በርሊን ላይ ተከበረ።

በዓሉ «ቀዝቃዛ ጦርነት» ይባል የነበረዉ የኮሚንስት ካፒታሊስቶች የጦር ፍጥጫ ያበቃበት፤ ከኢትዮጵያ እስከ አንጎላ፤ ከአልባኒያ እስከ ካምቦዲያ፤ ከደቡብ የመን እስከ ደቡብ አሜሪካ ተዘርግቶ የነበረዉ ኮሚንስታዊ ሥርዓት መንኮታኮት የጀመረበት ዝክርም ነበር።ለጀርመኖች በያኔዉ የበርሊን ከንቲባ ቋንቋ ከዓለም ሕዝብ ሁሉ እጅግ የተደሰቱበት ዕለት መታሰቢያ።

ከሚኒዝም ከተገረሰ ወይም መገርሰስ ከጀመረ እነሆ-ሃያ አምስተኛ ዐመቱ።ከአይዘናወር እስከ ከኬኔዲ፤ ከችርችል እስከ ታቸር የተፈራረቁት የምዕራብ ሐያላን መሪዎች አሸናፊነታቸዉ በርግጥ ተመስክሯል።በኮሚስቱ ጨቋኝ ሥርዓት መወገድ ያኔ-የቦረቀ፤የፈነደቀ፤ የነ ማርክስ-ኤንግሊስ፤ ሌኒን ሐዉልት ለመገርሰስ የተጣደፈዉ ሕዝብ ዛሬ ከጭቆና ግፍ መላቀቁ ግን ዛሬም በየሐገሩ እንዳጠያየቀ ነዉ።ዓለምስ ሰላም ነች።አይደለችም ይላሉ—ጎርቫቾቭ።

«የአዉሮጳ እና የአለም አቀፍ ፖለቲካ ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በሕዋላ የገጠመዉን ፈተና መቋቋም አልቻለም።ምዕተ-ዓመቱ መባቻ ላይ አዲሱ (የዓለም) ስራዓት ከተቀረፀ ወዲሕ አሁን ያለንበትን ዓይነት ዉጥረትና አደገኛ አጋጥሞን እንደማያዉቅ መቀበል አለብን።ሐያላኑ መነጋገር ባለመቻላቸዉ አዉሮጳና መካከለኛዉ ምሥራቅ የሚፈሰዉ ደም በጣም አሳሳቢ ነዉ።ዓለም ከአዲስ «ቀዝቃዛ ጦርነት አፋፍ ላይ ናት።አንዳዶች እንዲያዉም ቀዝቃዛዉ ጦርነት ተጀምሯል እያሉ ነዉ።»

ሚኻኤል ጎርቫቾቭ።በትናንቱ የበርሊን በዓል የክብር እንግዳ ነበሩ።ለጉድ ያስቀመጣቸዉ።ነጋሽ መሐነድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ግልጽ ደብዳቤ ”ለጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ

ከታሳሪ ዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስታችንን ያክብሩ!

ሠላም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!? እንዴት ነዎት? ያስታውሱ ከሆነ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢከፊሉ የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች  ‘ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ’

“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎትን የተለያዩ የመንግስት አካላት የሕገ መንግስታችንን ድንጋጌዎች እየጣሱ ነውና እርስዎም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 74/13/ መሠረት ሕገ መንስቱን የማስከበርና የማክበር ግዴታ ስላለብዎት ሕገ መንግስቱን ያክብሩ” በማለት አንዲት አጭር ደብዳቤ ፅፈንልዎት ነበር፡፡

ድንገት በተለያዩ ምክንያቶች የጻፍንልዎትን ደብዳቤ ካላነበቡት ወይም ማስታወስ ካልቻሉ ዛሬ ይሄን ማስታወሻ ስለምንፅፍልዎት ግለሰቦች አንድ ሌላ ማስታወሻ እንስጥዎ፡ ከ6ወራት በፊት /በሚያዚያ 2006 ዓ.ም/ ሶስት  ጋዜጠኞችንና ስድስት ጦማሪያንን ‘ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ጠርጥሬያችኋለሁ’ በማለት መንግስትዎ ልማታዊ ርምጃ (አብዮታዊ ርምጃ እንደሚባለው) ወስዶ ነበር፡፡

እኛም የዚህ ማስታወሻ ፀሃፊዎች የዚህ ‘ልማታዊ ርምጃ’ ሰለባ የሆንን ግለሰቦች ነን፡፡በርግጥ ከሁለት ዓመታት በፊት ‘ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሕገ መንግስቱን’ ያስከብሩልን በማለት ጥያቄ ያቀረብንልዎት ግለሰቦች ‘ከ6 ወራትበፊት ሕገ መንግስቱን ለመናድ  ሞክራችኋል’ በማለት መንግስትዎ ሲያስረን ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ጠይቀን ሕገ መንግስቱን ለመናድ በመሞከር ወንጀል ተጠርጥረን ስንታሰር እስሩ በጣም ግራ አጋብቶን ነበር፡፡በዚህ ያልቆመው መንግስትዎ ክሱን ‘ሕብረተሰቡንና ሀገሪቱን ለማሸበር አቅዳችኋል ሞክራችኋል አሲራችኋል…’ በማለት ወደ ‘ሽብርተኝነት’ያሳደገው ሲሆን እርስዎም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳብዎትን ሲሰጡ ስለተመለከትንዎ ትንሽ ቅሬታ ይዘን መጣን፡፡

በቅድሚያ አሁን ያለንበትን ሁኔታ በትንሹ ብናስረዳዎት ቅሬታችንን ለመረዳት ያስችልዎታልና አንዳንድ ጉዳዮችን እንንገርዎት፡፡

ይሄን ማስታወሻ በምንፅፍልዎት ወቅት ከታሰርን ከ 200 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፣ነገር ግንጉዳያችን ገና በቅድመ ክስ (Pre Trial) የክርክር ሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ይሄ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም መንግስትዎ እንኳን ለእኛ ለተከሳሾች ለከሳሽ አካልም ግልፅ ያልሆነ ክስ በማቅረቡ ነው፡፡ ይሄንንም ስንል ልትፈፅሙት ነበር የተባለው ‘የሽብርተኝነት ድርጊት’ ሳይጠቀስ ‘በቃ የሽብርተኝነት ድርጊት ልትፈፅሙ ነበር’ በማለት በጨበጣ ስለመጣብን ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንግዲህ የብዙ ድብደባ፣ ዛቻ እና ስድብ ሰለባዎች ከሆንን በኋላምየቀረበው ይሄ  ክስ ነው ከ6 ወራት በኋላም ተከሳሾች ከሳሾቻችንምሳንረዳው በየቀጠሮው እየታሸ ነው የሚገኘው፡፡ ‘የተፋጠነ ፍትህ’ ሕገ መንግስትዊ መብት ነውና የተፋጠነ ፍትህ ይሰጠን፣ እርስዎምይሄን ሕገ መንግስታዊ መብት ያክብሩ እያልንዎት አይደለም ‘ሕገ መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ’በማለት ‘ጥፋት የሚያሳምን’ ( አንዱ የዚህ ደብዳቤ ጸሃፌ ጦማሪ ጥፋት ብሎ አንዲፈርም የተገደደው ህገ መንግስቱ ተከብሮ እያለህገመንግስቱ ይከበር ማለቴ ጥፋት ነው ብሎ መሆኑ መንግስትዎን መልክ ግልጽ አድርጎ ያሳያል) መንግስት አለዎትና ይህ ጥያቄ አንደሚበዛብዎትእናውቃለን፡፡

ይልቁንም ቀላልና ግልፅ ቅሬታን ነው ይዘን የመጣነው፡፡ ይሄውም የኢፌድሪ ሕገ መንግስትበአንቀፅ 20/3/ ላይ

‘የተከሠሡ ሰዎች[…]  በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር[…]መብት አላቸው::’

በማለት የደነገገ ሲሆን፣ ይሄንን ሕገ መንግስታዊ መብትም ማንኛውም የመንግስት አካል እንዲሁም ግለሰብ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እርስዎና መንግስትዎም በተደጋጋሚ ‘ሕገ መንግስቱ ሳይሸራረፍ እናስከብራለን’ ይላሉና ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ የምታውቁት ይመስለናል፡፡ ነገር ግን ከታሰርን ወዲህ ስለእኛ የእስር ጉዳይ በተጠየቁባቸውጊዜያት ይሄን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስ ‘ፍርድዎትን’ በተደጋጋሚ ሲሰጡ ታዝበናል፡፡ እናስረዳዎ፡- ሐምሌ 12/2006 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣሚ መግለጫ ላይ ስለእኛ እስር ጉዳይ ለቀረበልዎት ጥያቄ ሲመልሱ፡-

‘ከአስመራ እስከ ሞቃዲሾ የተዘረጋው የሽብር ሰንሰለት ውስጥ አንዴከገቡ በኋላ ብሎገር ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ ማለት ዋጋ የለውም’

በማለት ብዙ ነገሮችን ተናገሩ፡፡ ይሔውልዎት ስህተትዎ፡-

1.     የክሳችን ዋነኛ ጭብጥ በሃገርውስጥ ‘የሽብርተኛ ድርጅት በማቋቋም ‘የሽብርተኝነት’ ተግባራትን ለመፈጸም አሲረዋል፡ አቅደዋል… የሚል እንጂ፣ እርስዎም እንደሚሉት ‘ሰንሰለት’ ምናምን አይደለም፣

2.    እሺ አሸባሪዎችም ይበሉን፣ነገር ግን ሕገ መንግስቱ እንደሚደነግገው በፍርድ ቤት ‘ጥፋተኝነታችን’ እስሚረጋገጥ ቢጠብቁስ ምናለበት? ይህ የሚያመለክተው እርስዎም እንደ ማእከላዊ መርማሪዎች ነፃ ሆኖ የመገመት (presumption of innocence) መብታችንን እያከበሩልን እንዳይደለ ነው፡፡

ይሄ ነገር የሆነው በድንገት ሊሆን ይችላል ብለንዝም ብንልም እርስዎ ግን በድጋሚ ጥቅምት 6/2007 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባል ለቀረበልዎ ጥያቄሲመልሱ፡-

“የብሎገር ጭምብልአጥልቆና በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ተሸሽጎ ከተከሳሽነት ማምለጥ አይቻልም፡፡ ሽብርተኝነትን መዋጋታችን ይቀጥላል…” እያሉ እርስዎ ያሉትን የብሎገር ጭምብል አውልቀውና ተሸሸጉበት ያሉትን የጋዜጠኝነት ሙያመሸሸጊያ አፍርሰው ባንዴ ‘የአሸባሪነት’ ካባ ደረቡልን፡፡

ክቡር ጥቅላይ ሚኒስቴር፣ እያልን ያለነው የአንድ ሰው ‘አሸባሪነት/ወንጀለኝነት’ የሚረጋገጠው በፍርድ ቤት እንደሆነ ሕገ መንግስቱ ደንግጎ እያለ፣ እርስዎ ግን ነፃ ሆኖ የመገመት መብታችን ወደ ጎን ብለው እንደ ከሳሽም እንደፈራጅም በመሆን ‘አሸባሪዎች’… እያሉን ይገኛሉ ነው፡፡

ምናልባት ‘ስራ አስፈጻሚው ከሳሽ ነውና እኔም የስራ አስፈጻሚው አካል መሪ ስለሆንኩ የፈለኩትን አስተያየት የመስጠት መብት አለኝ’ ብለው ከሆነ፣ ሕገ መንግስቱን የማክበር ጉዳይ ‘ርስዎን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች ላይ የተጣለ ግዴታነው፡፡ እርስዎ ‘L’e’tat, c’est moi’ ይሉት አይነት የራስ ግምት ውስጥዎ ከሌለ በስተቀር እንዲህ በግልፅ እየጠየቅንዎት ‘ሕገ መንግስትቱን  አላከብርም’ በማለት ገና ዋነኛ ክርክሩ እንኳንያ ልተጀመረ ክስን (ዋነኛ ክርክር ካለው) መሠረት በማድረግ ከዚህ በኋላ እኛን ‘አሸባሪዎች’ አይሉንም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ይህን ተመሳሳይ ምላሽ “በእርግጠኝነት አሸባሪ ናቸው” በሚል ቃና ለቢቢሲ ለኢንቢሲ ለመሳሰሉት አለም አቀፍ ሚዲያ  ተቋማትም መስጠትዎን ሰምተናል፡፡

ሌላው ልናስታውስዎ የምንፈልገው ጉዳይ እንደኛ አይነት የተራገበ( በሰፊው በታወቀ የአደባባይ)የፍርድ ጉዳይ ([un] popular case) ላይ የመንግስት አካላት አስተያየት (say) ያለውን ተፅእኖ እንዲያስቡት ነው፡፡እርስዎ በምክር ቤት ቀርበው የአሸባሪነት ፍርድ ከበየኑብን (አሁን እያደረጉት እንዳሉት) ፍርድ ቤትም ሆነ ሌሎች የመንግስትዎ አካላትምን ሊያስቡ እንደሚችሉ አስተውለውታልን?!

ይሄን ሁሉ ስንልዎ እንዲያው ሕጉን ያክብሩልን ለማለት ያክል ነው እንጅ፣ ከሽብርተኝነትጋር የሚያገናኘን ቅንጣት ያክል እውነት /A segment of fact/ እንደሌለና የሰው ልጆች መልካምና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸውከመመኘትና ለአገራችን ያገባናል ከማለት ያለፈ ሕይወትም ፍላጎትም እንደሌለን እኛም እናውቀዋለን እርስዎና መንግስትዎም ያውቁታል፡፡ነገር ግን ካለፉት ስድስት ወራት አንስቶ ጨዋታውን በግድ ካልተጫወታችሁ ተብለናልና እየተጫወትን ነው፡፡ የአሁኑ ጥያቄያችን ግን በጣም ቀላል ነው፣ ጨዋታው ገና በደንብ እንኳን ሳይጀመር ውጤቱን እይወስኑት ነው፡፡

እርስዎ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የስልጣን ደረጃ በወጡ ሰሞን አብዛኞች የዚህ ማስታወሻፀሃፊዎች መጠነኛ ለውጥና ማሻሻዎች ያደርጋሉ የሚል ተስፋ ሰንቀን “The First 100 Days” ወዘተ እያልን ብዙ ጠብቀንዎት ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት በሚበልጥ ግዜ እንደተመለከትንዎ ግን ተስፋችን ፍሬ ሊያፈራልን አልቻለም፡፡ አሁንም አዲስ ተስፋ ሰንቀን ግን ፡- “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር እባክዎትን ሕገ መንግስቱን ያክብሩ! የእኛንም መብት ያክብሩልን” እንላለን፡፡

‘’የብሎገር ካልሲ አድርጎ፣ የጋዜጠኝነት ጫማ ተጫምቶ የሽብረተኝነት ሰንሰለት ውስጥ ከገቡ በኋላ ሕገ መንግስቱን ያክብሩልኝ ማለት ዋጋ የለውም!’’በማለት ተስፋችን ዋጋ እንደማያሳጡት ተስፋ አለን፡፡

ከአክብሮት ጋር

 ጦማርያን                    ጋዜጠኞች

ዘላለም ክብረት                 ኤዶም ካሳዬ

ናትናኤል ፈለቀ                ተስፋለው ወ/የስ

በፍቃዱ ሃይሉ                አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ

አጥናፍ ብርሃኔ

አቤል ዋበላ

ማህሌት ፋንታሁን 

የዞን ፱ ጦማርያንና የጋዜጠኞችን የ200 ቀናት እስር አስመልክቶ በማኅሌት ሰለሞን የተዘጋጀ

የዞን ፱ ጦማርያንና የጋዜጠኞችን የ200 ቀናት እስር አስመልክቶ በማኅሌት ሰለሞን የተዘጋጀ