ወያኔ/ኢሕአድግ እና ምርጫ 20072007 election
በያዝነው 2007 ዓ.ም በግንቦት ወር ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በገዢው ፓርቲ እንዲሁም በተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን ምርጫ ቦርድም ምርጫውን በበላይነት ለመምራት ቁሳዊና ቴክኒካል ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ከገዢው ፓርቲ ልሳን ከሆነው EBC በተደጋጋሚ እየተሰማ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል መከፋፈሎች እንዲሁም አለመረጋጋቶች እየተስተዋሉ ሲሆን ለዚህም ምክንያቶቹን በእርግጠኝነት መግለጽ አዳጋች ቢሆንም ካለፉት የምርጫ ተሞክሮዎች በመነሳት የገዢው ፓርቲ ረጃጅም እጆች እንዳለበት መተንበይ አዳጋች አይሆንም፡፡

በዚህ በያዝነው አመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫን ለመተንበይ በቅድሚያ ከዚህ ቀደም የተካሄዱትን አገራዊ ምርጫዎች በወፍ በረር ቅኝት ማየቱ የግምቱን ይዘት ጠንካራ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ እምነት እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያቶች ከሚወጡ ጥናታዊ ጽሁፎች ለመረዳት እንደሚቻለው በአገራችን ተስፋ ሰጪ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዷል ተብሎ የሚታሰበው በ1997ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ነው፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋነኛነት ገዢው ፓርቲ በወቅቱ ለነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበረው ዝቅተኛ አመለካከት (በወቅቱ ቅንጅት የምርጫው ምዝገባ ሊጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት በቀሩበት ወቅት ቅንጅት መፍጠሩን ልብ ይለዋል) እንዲሁም የምዕራባዊያኑን ቀልብ በመሳብ አገሪቷ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ እየተጋች መሆኗን ለማሳየትና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞም በወቅቱ በመንግስት ይዞታ ስር የነበሩትን የንግድ ተቋማት ወደ ግል ይዞታነት በማዞር (privatization) መንግስት ቀደም ሲል ይተችበት የነበረውን ሶሻሊስምን ወደ ጎን በመተው ዘመኑን መምሰሉን በማሳየት ምዕራባዊያንን ለማሳመን የሚተጋበት ወቅት ስለነበረም ጭምር ነው፡፡ ስለሆነም ያለፉትን የምርጫ ሂደቶችን ለመገምገም ምርጫ 97 እንደመነሻ (base year) በመውሰድ ገዢው ፓርቲ እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ የነበራቸውን ሚና በሚከተለው መልኩ ለመዳሰስ ወደድኩኝ፡

ምርጫ 97

ኢሕአድግ 1997ቱ ምርጫ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ለተቃዋሚዎች በነበረው ዝቅተኛ ግምት ፤ ምርጫውን በበላይነት አሸንፋለው ከሚል የተሳሳተ ግምት እንዲሁም የምዕራባዊያኑን ቀልብ ለመግዛት የዲሞክራሲ በሩን ገርበብ አድርጎ በመክፈቱና ለምርጫው ቅስቀሳ ከዛ በፊት ይሰጡ ከነበሩት የመከራከሪያ ሰዓት በአንጻራዊነት ሰፊ ጊዜ ለተቃዋሚዮች በመስጠቱ ህዝቡ የሁሉንም ፓርቲዎች ፕሮግራም የሚሰማበት እድል ፈጥሯል፡፡ በወቅቱ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንጻር ኢሕአድግ በፖለቲካ ልምድ እንዲሁም በህብረተሰቡ ተሰሚም ታዋቂም ስለነበር ገዚው ፓርቲ ምርጫውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ሙሉ ዕምነት ነበረው ሆኖም ግን ወደ ምርጫው ቅስቀሳ ሲገባ እየታየ የመጣው ፈጽሞ ያልተጠበቀና ገዚው ፓርቲ የከፈተውን የዶሞክራሲ በር ለመዝጋት አስቸጋሪ የነበረበት እንዲሁም ወደ ኋላ ማፈግፈግ የማይችልበት ወቅት ነበር፡፡

በተቃዋሚዎች በኩል በወቅቱ የምሁሮች ስብስብ ተብሎ ሲሞካሽ የነበረው ቅንጅት የገዢው ፓርቲ ጠንካራ ተፎካካሪ ነበር ለዚህም ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆኑም ድርጅቱ በውስጡ ጉምቱ የፖለቲካ አዋቂዎችን ማካተቱ ፤ ድርጅቱ በመረጃ የተደገፈ ጠንካራ ክርክር ማካሄዱ፤በምርጫ  ክርክሮች ወቅት ሚያቀርባቸው ተከራካሪዎች ኢሕአዴግ ከሚያቀርባቸው የተሻሉ መሆናቸው፤ የማህበረሰቡን የልብ ትርታን መሰረት ያደረጉ ጠንካራ ትችቶችን  በገዢው ፓርቲ ላይ በማቅረባቸው (የዘር ፓለቲካን  ፊትለፊት  በመተቸታቸው ፤ ሙስናን በመረጃ አስደግፈው በማጋለጣቸው፤ በገዢው ፓርቲ  የተንቋሸሸውን  ስራ አጥ ወጣቱን ስራ ፈጣሪ ለማድረግ ንድፈ ሃሳብ ማቅረቡ ከብዙ በጥቂቱ ሚጠቀሱ ናቸው) ፤ ዘርን መሰረት ያላደረገ  የፖለቲካ አቅጣጫ (political ideology) ይዞ መቅረቡ ፤ ድርጅቱ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ያቀናጀ መሆኑና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው የምርጫውን ግምት አፋልሰውታል፡፡

ኢሕአዴግን ለውድቀት የዳረጉ ውስጣዊ ምክንያቶች

ከላይ በጠቅላላው ለማሳየት እንደተሞከረው የምርጫ 97 ለተቃዋሚዎች የፈጠረውን እድልና ገዢው ፓርቲ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ሲሆን ከዚህ በታች የምንመለከተው በድርጅቱ ውስጥ የነበረውን ውስጣዊ ችግሮችን ይሆናል፡

1.ከመጠን ያለፈ በራስ መተማመን

ኢሕአዴግ ከ1997 በፊት በነበሩት ምርጫዎች ተቀናቃኝ የነበሩትን በቀጥታ እንዲሁም በተዘዋዋሪ ካዳከማቸው ከፊሎችንም ከበታተነ በኋላ አስጊ የፖለቲካ ተቃዋሚ ስላልነበረ በምርጫ 97 ፍጹም የበላይነትን ለመቀናጀት እምነት ነበረው ለዚህም ማሳይው ከሌሎች የምርጫ ጊዜያቶች በተለየ ሁኔታ ለተቃዋሚዎች ሰፊ የአየር ሽፋን መስጠቱ ፤ የተለያዩ በርካታ የመከራከሪያ መድረኮችን ማዘጋጀቱ ፤ ክርክሮቹ ቀጥታ የአየር ሽፋን ማግኘታቸው ሲሆኑ ባልተጠበቀ መልኩ ጠንካራ ሆኖ የቀረበው ቅንጅት እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚዎች እድሉን በሚገባ ስለመጠቀማቸው በወቅቱ የነበረው የምርጫ ውጤት አመላካች ነው፡፡

2.ጠንካራ ተከራካሪ ያለማዘጋጀት

በተለያዩ የክርክር መድረኮች ኢሕዴግን ወክለው የሚቀርቡ ተከራካሪዎች ከተቃዋሚዎች ተሸለው ባለመገኘታችው እንዲሁም የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች በመረጃ የተደገፉ አለመሆናቸውና  በተደጋጋሚ በተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎች ሲሰሙ የቆዩ በመሆናቸው አሰልቺ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በተቃዋሚዎች የሚቀርቡትን ፈታኝ ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ የሚመልስ ባለመኖሩ ኢሕአዴግ እየኮሰሰ ሌላው እየገነነ የመጣበት ሁኔታ እንደነበር የሁላችንም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤፤

3.የአባላት ታማኝ አለመሆን

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክተው ኢሕዴግ በ1997 ምርጫ ወቅት ጠቅላላ ከ6 ሚሊዬን በላይ አባላት የነበሩት ሲሆን ይህንን አባላት በማሰብ ገዢው ፓርቲ በቀላሉ እንደሚያሸንፍ መገመቱ ስህተት ላይመስል ይችል ይሆናል ነገር ግን ከምርጫው ማግስት ለመረዳት እንደተቻለው አብዛኛው አባላት የድርጅቱን የፖለቲካ ፕሮግራምን በመረዳት ሳይሆን የስራ ዕድል ለማግኘትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በመፈለግ ፓርቲውን መቀላቀላቸው ነው፡፡ በአዲስ አበባ ድርጅቱ ድምጽ አገኝባቸዋለው ብሎ ባሰበባቸው በተክለሃይማኖት ፤ ቦሌ እና ሌሎች አካባቢዎች መሸነፉ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

4.ሙስና

ኢሕአዴግ በዋነኛነት ከሚታወቅባቸው እኩይ ባህሪያቶቹ አንዱ ሙስና ሲሆን ይህም የሚከናወነው ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሳይሆን በተወሰኑ ቡድኖች ፤ ነባር ታጋዮች እንዲሁም ዘርን መአከል ያደረገ ስለነበር ሌሎች አጋር ድርጅቶች ውስጥ ውስጡን መከፋታቸው የነበረ ሲሆን ይህም መከፋት አባላቱ ሌሎች አማራጫ ፓርቲዎችን  እንዲመለከቱ ወይም ድርጅቱ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ከማነሳሳቱም በላይ ድርጅቱን የግላቸው አድርጎ ለማሰብ አዳጋች ነበር፡፡

ምርጫ 2002:- በዚህ ምርጫ ላይ ኢሕአዴግ ከ1997ቱ ምርጫ ብዙ የተማረበት እና በቂ ዝግጅት ያደረገበት ስለነበር ውጤቱን ለመቀልበት ችሎ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ ወቅት ድርጅቱ በአብዛኛ የፖለቲካ ተንታኞች ሲገለጽ እንደነበረው ብቻውን ሮጦ ብቻውን ያሸነፈበት ምርጫ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ፡-

 • በምርጫ 97 ላይ ጠንካራ የነበረውን ቅንጅትን አከርካሪውን በመስበር የበላይ አመራሮቹን በማሰር እንዲሁም ከሀገር እንዲሰደዱ በማድረግ ፤ ህዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቁ በማስገደድ በህዝቡ ውስጥ እምነት እንዳይኖራቸው በማድረግና በሌሎችም እኩይ የፖለቲካ ስራዎቹ ድርጅቱን በማዳከሙ /በማፈራረሱ
 • በራሱ በኢሕአዴግ የተፈጠሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመፍጠር እንዲሁም ሌሎች ተቃዋሚዎች በኢሕአዴግ ሴራ እንዲሁም በግላቸው ምክንያት ከምርጫ እራሳቸውን ማግለላቸው
 • አጭር የክርክር መድረኮችን በማዛጋጀት እንዲሁም ለተቃዋሚዎች አጭር ጊዜ በመስጠት በተቃራኒው ለራሱ ሰፊ የአየር ሽፋን በመስጠት የድርጅቱን ፕሮግራሞች ማስተዋወቁ
 • በ1997 በቅንጅትና በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይቀርቡ የነበሩ አማራጭ የልማት እስትራተጂዎችን በመውሰድና ከፊሎችንም በመተግበር ከተሰራው ስራ በላይ ፕሮፖጋንዳ በመስራት (ጥቃቅንና አነስተኛ ፤ ማህበራትን ማደራጀት ፤ ወጣቱን አደገኛ ቦዘኔ ከማለት ወደ ወጣት የልማት ሀይል መቀየር ፤ የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን መገንባትና የመሳሰሉት ከምርጫ 1997 በፊት በገዢው ፓርቲ ተሰምተው የማይታወቁ ሲሆን ከምርጫ 97 በኋላ ጽንሰ ሀሳቡ ከተቃዋሚዎች ስለመሰረቁ ማሳይዎች ናቸው)
 • ቀደም ሲል ገጠርን ማዕከል ያደረገውን ልማት ወደ ከተማ በማምጣት የሚታዩ ለውጦችን በማቅረብ እነሱንም በመንግስት ሚዲያዎች አግንኖ ማቅረቡ (መንገድ ፤ ውሃ ፤ ኤሌክትሪክ ወዘተ)
 • የህዝቡ ተስፋ መቁረጥ፡ – በምርጫ 97 ወቅት በህዝቡ ተስፋ የተጣለባቸው ፓርቲዎች ከነአካቴው መጥፋታቸውና እነሱን ሊተካ የሚችል ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ መጥፋቱ
 • ጠንካራ የፖለቲካ ቅስቀሳ መደረጉ ፡ – መንግስት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት የተሰሩ የልማት ስራዎችን በማቅረብ ፤ ህብረተሰቡን በማወያየት እንዲሁም ትልልቅ ካፒታል የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋቱና የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን በማቅረቡ
 • ምርጫ ቦርድ ላይ ያለውን ስውር እጅ በማስፋፋት ጠንካራ ክትትል ማድረግና የድርጅቱ የቀኝ ክንፍ መሆኑ በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ገዢው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ የምርጫው አሸናፊ ሊሆን ችሏል፡፡ ከሁለቱ ተከታታይ ምርጫዎች የምንማራቸው አበይት ጉዳዮች ቢኖሩ፡
 • ኢህአዴግ በቢሊዮን የሚቆጠር የፋይናንስ አቅም እንዳለውና ለፖለቲካ ቅስቀሳ በቂ አቅም እንዳለው በተቃራኒው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላቸው የፋይናንስ አቅም እጅግ አናሳ በመሆኑ በራካታ አባላትን ለማፍራት እንዲሁም ቅስቀሳዎችን ለማድረግ የአቅም ውሱንነት እንዳላቸው
 • ኢሕአዴግ የ1997ቱ ምርጫ ብዙ ልምዶችን የቀሰመበትና በወቅቱ አሳይቶት የነበረው የዲሞክራሲ ጭላንጭል በማጥፋት ፍፁም አምባገነን እየሆነ መምጣቱን
 • ኢሕአዴግ የተቃዋሚዎችን ደካማ ጎን በመጠቀም እንዲሁም የስለላ መረቦቹን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን የማዳከምና የማፈረካከስ ልምዱን ያካበተ መሆኑን እና ፓርቲዎች ለምርጫ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ ጫና ማሳደሩን
 • የምርጫ ቦርድ መመሪያዎችንና ደንቦችን ኢሕአዴግ በፈለገው መልኩ ማሻሻሉንና ህጉ ለሁሉም በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ የማያደርግ መሆኑንና እና ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ናቸው፡፡እነዚህን እንደ መነሻነት በመጠቀም በምርጫ 2007 ሊገጥሙ የሚችሉትን ከወዲሁ ለመገመት ያህል፡ –

ኢሕአዴግ

በገዢው ፓርቲ በኩል ለምርጫው እየተደረጉ ያሉ ቅድመ ዝግጅቶች ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ከነበሩት በእጅጉ የላቁ ናቸው፡፡ ይህም ነፃ የግል ፕሬሶችን ያለምንም በቂ ማስረጃ  በማሰር ፤ በመክሰስ ፤ በማስፈራራት ፤ እንዲሁም አገር ለቀው እንዲሰደዱ በማድረግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን  የሚያስተዋውቁበትን  መንገድ መዝጋቱ፡፡ ከዚህም  በተጨማሪ  ህዝቡ አማራጭ የመረጃ ምንጮች እንዳይኖሩት በማድረግ ህዝቡ በሚያገኘው አንድ አገራዊ የቴሌቪዝን ጣቢያ የገዢውን ልማታዊ ስራዎች ብቻ እንዲያይ ማድረጉ ነው፡፡

የተለያዩ የማህበረሰብ ድህረ ገፆች ላይ ፤ የደህንነት ሀይሎችን በማሰማራት እና ድንገተኛ ፍተሸዎችን በማድረግ ህዝቡን በማሸማቀቅ ፤ ሀይማኖትን ከሀይማት በማጋጨት ፤ የዘር ግጭቶችን በማቀነባበር ፤ ህዝቡ ላይ ሽብር በመንዛት ህዝቡ ከኢሕአዴግ ውጭ አማራጭ እንዳያስብ በማድረግ ህዝቡ እንዲመርጠው ብሎም ደግሞ የደህንነቱን ጡንቻ በማሳየት ለማስፈራራት በመሞከር ላይ ነው ለዚህም ማሳይው የተለያዩ የፖለተካ ስደተኞችን እና እንዲሁም በተለያዩ አገራት ይኖሩ የነበሩ የተቃዋሚ ድርጅት ቁልፍ ሰዎችን  አፍኖ በማምጣት ህዝቡ ላይ ፍራቻን ሲዘራ ይስተዋላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ምርጫ 2002 ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን  በመከፋፈል ፤ በመታተን እንዲሁም በተለይዩ ምክንያቶች አመራሮቻቸውን በማሰር ተሳትፏቸውን ማዳከምን ተያይዞታል እንደ ማሳይም በአንድነት ለዲሞክራሲና ለልማት ፤ በአረና ፓርቲ እንዲሁም በሰማያዊ ፓርቲ ላይ እያደረሰ ያለው የማፈራረስ ፤ የማሸማቀቅ እንዲሁም እስራቶችን ማየት በቂ ማስረጃ ነው፡፡

የፖለቲካ ቅስቀሳዎችን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት በሲቪል ሰርቫንቱ እና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲሁም በነዋሪው ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ስልጠናዎችን እያካሄደ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ  ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰብሰቢያ አዳራሾችን የመከራይት አቅም ማሳጣት  አቅም ያላቸውንም  ደግሞ የአዳራሽ፣ ቢሮ፣እንዲሁም  ኪራይ ቤቶች እንዳያገኙ ተጽዕኖ በመፍጠር  ላይ ነው፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች

በያዝነው ዓመት ማገባደጃ ላይ ለሚከናወነው አገራዊ ምርጫ ተቃሚ ፓርቲዎች እያደረጉ ያለው ቅድመ ዝግጅት በገዢው ፓርቲ ጥብቅ ክትትል ስር ሲሆን ፓርቲዎቹ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም እንዲሁም ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን እንዲያስችላቸው ውህደት ለመፈፀም በሂደት ላይ ሲሆኑ በገዢው ፓርቲ ስውር እጆች ምክንያት በሚፈለገው ፍጥነት እየተጓዘ እንዳልሆነ እያየን ነው፡፡ በዚህ ምርጫ በሃገር ውስጥ ትልቅ  ግምት ከሚሰጣቸው እንደ አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ  በገዢው ፓርቲ ተደጋጋሚ ትንኮሳ እየደረሰባቸው ሲሆን ይህም የምርጫው ዋዜማ ላይ ሊበረታ እንደሚችል ይገመታል፡፡

ህብረተሰቡ

ካለፉት የምርጫ ጊዜያቶች በተለየ ሁኔታ ማሕበረሰቡ የፓለቲካ አድማሱ የሰፋበት ሆኔታ ሲሆን ለዚህም አበይት ምክንያቶቹ በማሕበራዊ ድህረ ገፆች የሚለቀቁ የተለያዩ አክቲቪስቶችን  ንግግር ፤ ክርክሮች ፤ በግል ፕሬሱ ይታተሙ የነበሩ የፖለቲካ ትንታኔዎች ፤ ከገዢው ፓርቲ እየሾለኩ የሚወጡ የተለያዩ መረጃዎች እንዲሁም ህብረተሰቡ አማራጭ የመረጃ ምንጭ በማግኘቱ ነው፡፡ በመሆኑም ማሕበረሰቡ ምርጫው በገዢው ፓርቲ የተለመደ ማጨበርበሮች ሊጠናቀቅ እንደሚችል ግምቱ ቢኖረውም እንደ ባለፉት የምርጫ ጊዜያቶች በቸልታ ያልፈዋል ተብሎ አይታሰብም ምክንያቱም ህዝቡ መንግስት የሚያደርገውን የመብት ረገጣ ፤ አድሎአዊ አገዛዝ ፤ ሙስና ፤ እንዲሁም በእስልምና ሀይማኖት እና በኦርቶዶክስ የዕምነት ተከታዮች ላይ እጁን በማስገባት እየፈፀመ ያለውን በደል በሚገባ ስለሚያውቅ ድርጅቱ ጉልበት ያለው ቢመስልም ውስጡ ግን ባዶ ፤ ደጋፊ ያለው ቢመስልም አባላቱ በጥቅም ፤ በዘር እንዲሁም በመልካም አስተዳደር እጦት ያኮረፉ የሚበዙበት ሲሆን ገዚው ፓርቲ ከሕወሓት ውጨ ያሉ ፓርቲዎችን በአይነ ቁራኛ መመልከቱና አብዛኛውን ስልጣን ጠቅልሎ መያዙ በአጋር ድርጅቶች ጥርስ ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆነዋል፡፡

ማጠቃለያ

የምርጫውን ውጤት ከወዲሁ መተንበይ ባይቻልም በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያሉ አባላት   በወያኔ ሕወሓት ላይ በተለይዩ ምክንያቶች ውስጣቸው የሻከረ በመሆኑ (ብአዴን በግንቦት 7 ፤ ኦሕዴድ በወጣት ተተኪዎቹ የስልጣን ይገባናል ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ፤ እንዲሁም በሌሎች አጋር ፓርቲዎች) የምርጫውን ውጤት ወዳልተገመተ አቅጣጫ ሊመሩት እንደሚችል ይገመታል፡፡ የማሕበረሰቡ ንቃተ ህሊና መጨመር ፤ ገዢውን ፓርቲ በተጨባጭ መረጃዎች መወንጀል መጀመሩ ፤ መንግስት በተደጋጋሚ የሚፈፅማቸው የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ፤ የአገሪቱን ከፍተኛ ቁጥር የሚሸፍኑትን አንጋፋ የሀይማኖት ተቋማትን ማስኮረፉ ከሀይማኖቱ ተከታዮች የምርጫ ካርድ ሊነፈግ እንደሚችልም  ይገመታል ይሁንና ገዢው ፓርቲ በምርጫ ቢሸነፍም ስልጣኑን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ድምፁ የተሰረቀበት ማሕበረሰብ አልመረጥኩም ብሎ በጥያቄ  ተቃውሞ ቢነሳ  ተቃውሞውን በበቂ ሁኔታ የሚያስተባብርና ሀላፊነቱን የሚወስድ ፓርቲ ባለመኖሩ አገሪቷን ወደ አላስፈላጊ ዕልቂት እንዳይጥላት ያሰጋል፡፡ ገዢው የወያኔፓርቲ የምርጫውን ውጤት በጸጋ ተቀብሎ ለመጪዋ ኢትዮጵያ ዘላለማዊነት በቅን ልቦና ምርጫውን ለግል ጥቅም ሳይሆን የህዝቡን ድምፅ እንዲያከብር ልባዊ  ምኞቴ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ዳኛቸው ተገኝ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s