Archive | November 18, 2014

የአፍሪቃ ስደተኞች ህይወት በሲሲሊ

/ዶቼ ቬሌ/ ከአፍሪቃ በሜዲትራንያን ባህር አድርገው ወደ ኢጣሊያ የሚገቡት ስደተኞች ቁጥር ምንም እንኳን አሁን ቀዝቀዝ እያለ በመጣው የአየር ጠናይ ሳቢያ ረገብ ቢልም፤ ከ መቶ ሺ በላይ ስደተኞች ባለፈው ዓመት ኢጣሊያ ገብተዋል።

Flüchtlingsaufnahmelager der Caritas in Palermo, Italien

« ለ 20 ሰዓታት ባህር ላይ ነበርኩ። ጀልባዬ ውሃ ስለገባባት ሞላች። ከዛ የባህር ኃይል አባላት ጋር ደወልኩ። የባህር ኃይሎቹ በ አምስት ደቂቃ ውስጥ እንደሚመጡ ነገሩኝ። የህይወት ማዳኛ መንሳፈፊያ ጃኬት ሰጥተውኝ ከባህር አወጡኝ። ህይወቴን ስላተረፉዋት ደስተኛ ነኝ።»

Flüchtlingsaufnahmelager der Caritas in Palermo, Italienታምቦ ከወራት ጉዞ በኋላ ነው ኢጣሊያ የገባው

በማለት ነው ታምቦ በዓለም አቀፉ የሊቢያ እና የሲሲሊ የባህር ክልል ውስጥ ሳለ ህይወቱ በኢጣሊያ ግብረ ኃይል እንዴት እንደተረፈ የገለፀው። የ18 ዓመቱ የማሊ ስደተኛ ኢጣሊያ የገባው ባለፈው ሰኔ ወር ነው። አሁን ከሌሎች 37 የአፍሪቃ ስደተኞች ጋር «ካሪታስ» በተባለው የካቶሊካውያን የበጎ አድራጎት ድርጅት የስደተኞች ማቆያ ፤ ፓሌርሞ በተባለው የሲሲሊ ከተማ ውስጥ ይኖራል።

ታምቦ ከባህር ጠረፉ ወደ አሁኑ መኖርያ ሲመጣ ባዶ እጁን ነበር። አሁን ግን በርዳታ የተሰበሰቡ ልብሶች እና አንድ አሮጌ ስልክ እንዲሁም በጆሮ ማዳመጫ አግኝቷል። ሙዚቃ በስልኩ ያዳምጣል። በስደተኞቹ ማቆያ በነፃ ኢንተርኔት ይጠቀማል። ስልክ ግን ውድ ስለሆነበት ወደ አፍሪቃ አይደውልም። ነገር ግን ይላል ታምቦ « በኋትስ ዓፕ» አማካይነት ማሊ የሚያውቃቸው ሰዎች ጋር ደህና መሆኑን የሚገልፅ መልዕክት ለእናቱ ይልካል።« እናቴ በህይወት አለች። አባቴ ግን ሞቷል። ስለዚህ ከእናቴ ጋር ልገናኝ እችላለሁ። እዚህ እንደሚገኙት እኔ ባለ ትዳር አይደለሁም። እናቴን ብቻ ነው አፍሪቃ የተውኳት።»

ታምቦ በማሊ በበርሃ አቋርጦ ሊቢያ የባህር ጠረፍ እንደደረሰ ይናገራል። በወቅቱ ተሳፍሮበት የነበረው ታክሲ መዘረፉ ብቻ ሳይሆን « አብረውኝ ተሳፍረው ከነበሩት ሰዎች መካከል የተገደሉም ነበሩ» ይላል ። ወጣቱ ሊቢያ ውስጥ ስራ ይሰራ ነበር። ይሁንና አረቦች እንደደበደቡት ነው የሚያስታውሰው። በመጨረሻም የእንጨት ጀልባ የሚሸጥለት ሰው አግኝቶ ወደ አውሮፓ ለመጓዝ ቆርጦ ተነሳ።

ፓሌርሞ የሚኖሩት ስደተኞች ተመሳሳይ ታሪክ ነው የሚናገሩት። እንደ ታምቦ ከማሊ የመጣው ማማዶ 24 ዓመቱ ነው። ወጣቱ ገበሬ በኢጣልያ ባህር ኃይል «ማሬ ኖስትሩም» አማካይነት ነው ከ5 ወር በፊት ከባህር ከመስመጥ የተረፈው። እሱ በተሳፈረበት የአሳ ማጥመጃ ጀልባ ላይ 115 ሰዎች ተሳፍረው ነበር። ለሁለት ቀን ያክል ጀልባ ላይ ከቆዩ በኋላ የሚበሉት እና የሚጠጡት እንዳለቀባቸው ማማዶ ይናገራል። እሱ የተሳፈረበትም ጀልባ ውኃ ስለገባበት አደጋ ላይ ነበሩ። ኋላም ጀልባዋ ልትሰምጥ ትንሽ ሲቀራት የኢጣሊያ የባህር ኃይል አዳናቸው።« ማሬ ኖስትሩምን ሊያቆሙ እንደሆነ ሰምቼያለሁ። ካቆሙት ከፍተኛ አደጋ ነው። የነፍስ አድኑን ቡያቆሙ እንኳን ሰዎች መምጣታቸውን አያቆሙም ብዬ አምናለሁ። ሰዎቹን ካላዳኗቸው ደግሞ ጀልባዎቹ መገልበጣቸው አይቀርም። ምክንያቱም ጀልባዎቹ ጠንካራ አይደሉም። ከ አንድ እና ሁለት ቀናት በላይ እዛ ላይ መቆየት አይችሉም። ስለዚህ ካላዳንዋቸው ጀልባው ይገለበጣል። »

Palermo Flüchtlinge 5.ማማዶ ወደ ጀርመን ቢሄድ ምኞቱ ነው

ይህ ነው የማማዶ ዕምነት። ማሬ ኖስትሩም ስራውን ካቋመ 15 ቀናት አለፏ። ይህንን ግብረ ሀይል የተካው «ትሪቶን» አዲሱ የአውሮፓውያን የባህር ተልኮ ዋና ተግባር የአውሮጳ ህብረትን የባህር ድንበር ማስከበር እንጂ የነፍስ አድን ተግባር አይደለም። ብቻ ማማዶ ነፍሳቸው ተርፋ ኢጣሊያ ከገቡት ስደተኞች አንዱ ነው። እሱም በርሃ አቋርጦ ነው ሊቢያ የገባው። ወጣቱ ሊቢያ በቆየበት የአንድ ዓመት ጊዜ ስራ ሰርቷል፣ ወህኒ ቤትም ነበር። አንዱን ሌሊት ግን ማሊ ያሉ አማፂያንን እንዲቀላቀል ወደ ባህር ዳር ሲወሰድ «ለማምለጥ ተሳካልኝ » ይላል።« እኔ የጠፋሁት፤ በሀገሬ ፤ በተለይ እኔ በምኖርበት በነበረው አካባቢ አብዮት በመቀስቀሱ ነበር። አንድ ቀን አማፂያኑ የኛ መንደር ላይ ጥቃት መጣል ጀመሩ። በዚህ ተግባራቸው ወንድሞቼን፣ እኔን እና የተወሰኑ ጓደኞቼን ወደ ጫካ ወሰዱን። እነሱ የመንግሥቱን ጦር እንድንዋጋ ነበር የፈለጉት። »

ማማዶ ሁለት ወንድሞች እና አንድ እህት አሉት። እነሱን ምን እንደገጠማቸው እና በህይወት ስለመኖራቸው እንኳን አያውቅም። ፓሌርሞ የሚገኙት ስደተኞች ትዕግስት ያስፈልጋቸዋል። በተገን ጠያቂዎች ኮሚሽን ተገኝተው ቃል መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ከዛም የተገን ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ አንድ ዓመት ያክል ሊፈጅ ይችላል ይላሉ ፍራንሴስኮ ቪዛኒ ከ ካሪታስ የካቶሊክ ርዳታ ድርጅት።

በካሪታስ ስር ያሉት ወጣቶች የግድ በስደተኞቹ መኖርያ መቆየት የለባቸውም። ሲፈልጉ ወደ ከተማ መሄድ ይችላሉ። አንዳንዶች የኪስ ገንዘብ ለማግኘት የቀን ስራ ይሄዳሉ። ሌሎች ደግሞ በዛው በስደተኞቹ መኖርያ ግቢ ውስጥ በሰዓት እየተፈራረቁ ይሰራሉ።

ስደተኞቹ የሚኖሩት ቀደም ሲል የአዛውንቶች መኖርያ የነበረ ፎቅ ውስጥ ነው። የመጀመሪያው ፎቅ ላይ አሁንም ርዳታ የሚያስፈልጋቸው አዛውንቶች ይኖራሉ። እነሱንም የካቶሊክ መነኩሴዎች ይረዷቸዋል። ጎረቤቶቻቸው ስደተኞቹን ሰላም ይሏቸዋል። ነገር ግን ስደተኞቹ የጠረጴዛ ቴኒስ ሲጫወቱ ድምፃቸው ስለሚረብሽ በሚል፤ ጎረቤታቸው ለካሪታስ ወቀሳ አሰምተው ነበር። በዚህም የተነሳ ካሪታስ ምሳ ሰዓት ላይ ፀጥታ እንዲከበር አውጇል። ስደተኞቹ ጠዋት ጠዋት ጣሊያንኛ ይማራሉ። ከትምህርት ቤት መልስ ፣ በቡድን ሆነው ቴሌቪዥን ይመለከታሉ፣ ያርፋሉ፣ ይጫወታሉ። ከዚህ በተረፈ ግን ከ 3-5 አልጋዎች ባሉበት ክፍል የሚኖሩት ስደተኞች በመቀመጥ ነው ጊዜያቸውን የሚያሳልፏት። « ማስረጃ ኖሮ መስራት ቢቻል ይሻሻል። እንደዚህ ቁጭ ከማለት ይልቅ»

Italienisch-Kurs für Flüchtlinge in Palermo, Italienበየቀኑ ስደተኞቹ ጣሊያንኛ ይማራሉ

ይላል ታምቦ። ማማዶ ደግሞ ወደ ሰሜን አውሮፓ መሄድ ቢችል ይመርጣል።ሳቅ እያለ ጀርመን የምመኛት ሀገር ናት ይላል። ስደተኞቹ ምንም እንኳን ከግቢ መውጣት ቢችሉም የፓሌርሞን ከተማ ለቀው መሄድ አይፈቀድላቸውም ይላሉ ፍራንሲስኮስ ቪዢኒ። ይሁንና አንዳንድ ጥለው የሚሄዱ እንዳሉ ከሌሎች የካሪታስ ጣቢያዎች እንደሚያውቁ ቪዢኒ ይናገራሉ።

ሮም የሚገኘው የተገን ጠያቂዎች ምክር ቤት ባልደረባ ክርስቶፈር ሀይን፤ ኢጣሊያ በማሬ ኖስትሩም አማካይነት ሀገሪቱ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ብዙ ስለሆነ ፤ ሀገሪቱ ከአቅሟ በላይ እንደሆነባት ያስረዳሉ። ስለሆነም የአፍሪቃ እና የሶርያ ስደተኞች ዘመድ ወይም የሚያውቁት ሰው እያፈላለጉ ወደ ሰሜን ይጓዛሉ።« ከደቡብ ኢጣሊያ ወደ ኦስትሪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ኔደርላንድስ እና ስዊዲን ሌላ ሁለተኛ እንቅስቃሴ ይታያል። ሰዎቹ በአውሮፓ ህብረት ሀገራት አድርገው ወደ ሌሎች ሀገራት ለመግባት ይሞክራሉ። በድጋሚ በህገ ወጥ መንገድ አድርገው ለመጓዝ እና ለደላሎች ለመክፈል ዝግጁ ናቸው።»

በአውሮፓ ህብረት የደብሊን ህግ መሰረት ስደተኞች መቆየት የሚፈቀድላቸው ተገን የጠየቁበት ሀገር ነው። የካሪታስ ሥራ አስኪያጅ ቄስ ሴርጂዎ ማታሊአኖ እኢአ ህዳር 1 ቀን 2014 ዓም ማሬ ኖስትሩምን የተካው የ « ትሪቶን» ግብረ ሃይል ተግባር ብዙም አላሳመናቸውም።« የትሪቶን ዘመቻ ምናልባት የባህር ጠረፉን ለመቆጣጠር እና አውሮፓን ለመዝጋት ጥሩ ሊሆን ይችላል። አላማው ህይወት ለማትረፍ ሳይሆን አውሮፓን ለማጠር ነው።»

Palermo Flüchtlinge 6.አባቴ ብለው ነው የሚጠሩኝ ይላሉ ሴርጂዮ

ቄስ ሴርጂዮ መርዳት ነው አላማቸው። በስደተኞቹ መኖሪያ የሚገኙት 38 ወጣት አፍሪቃይናንን ቤተሰብ አድርጎዋቸዋል። ስደተኞቹም በካቶሊኩ መንፈሳዊ ይተማመናሉ።ምንም እንኳን አብዛኞቹ ስደተኞች ሙስሊም ቢሆኑም ፤ ሀይማኖት ለማንኛቸውም ሚና አይጫወትም።« እኔ ልክ እንደ አባታቸው ነኝ። ከኔ ጋር ስለ ገጠማቸው ችግር መወያየት ይችላሉ። በሲሲሊ፣ በኢጣሊያ ህልማቸውን እውን ለማድረግ ይፈልጋሉ እና ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ተስፋ አላቸው። »የማሊ ስደተኛ ታምቦ እጁን ቄሱ ትከሻ ላይ አድርጎ አቅፎዋቸዋል። የሚሉት በደንብ ባይገባውም ቄስ ሴርጂዮ በጣልያንኛ ቀስ ብለው ታምቦን ይመክሩታል።

የስደተኝነት ህይወት በሲሲሊ እንዴት እንደሚቀጥል ግን ማንም አያውቅም ። ታንቦ የመጣውን ለመቀበል ዝግጁ ነው።« ህይወት እንግዲህ እንደዚህ ነው። ከዚህ በፊት ሌላ ህይወት ነበረኝ ። አሁን ደግሞ እዚህ ህይወቴ የሚመጣውን አያለሁ። ነገ ኢጣሊያ ልቀር ወይ ወደ ጀርመን ልሄድ እችላለሁ። ህይወት እንዲህ ናት።»

በፖሌርሞ ከታንቦና ማማዶ ጋር የሚኖሩት አፍሪቃውያን ስደተኞች መጠለያ ፣ ምግብ ፣ መዝናኛ እና የቋንቋ ትምህርት የመሣሰሉትን ቢያገኙም ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለተጓዙት ጉዞ፤ ገና ከዚህ የተሻለ ህይወት እንዲጠብቃቸው ይመኛሉ።

በርት ሪገርት / ልደት አበበ

ተክሌ የኋላ