Archive | November 22, 2014

በሽብር የተከሰሱት የተቃዋሚ አመራሮች ዋስትና ተከለከሉ

Abrha-Desta-Yeshiwas-Assefa-Daneil-Shibeshi-Habtamu-Ayalew

በሽብር የተከሰሱት የአንድነት፣ የሰማያዊ፣ የአረና ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ተከሳሾች፣ ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ከትናንት በስቲያ በፍ/ቤት ውድቅ የተደረገ ሲሆን፤ አቃቤ ህግ የተጓደሉ ማስረጃዎችን አሟልቶ እንዲቀርብ ታዟል፡፡
ከወራት በፊት የታሰሩት ተከሳሾች፤ በዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ጥያቄያቸውን ፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የልደታ ምድብ 19ኛ ችሎት ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የሁሉም ተከሳሾች ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ በአቃቤ ህግ ክስ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል አንቀፅ የዋስትና መብትን የሚያስከለክል መሆኑን ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፣ ሁሉም ተከሳሾች ጉዳያቸውን ማረሚያ ቤት ሆነው ይከታተሉ ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡
በእለቱ ጠበቆች ከክሱ ጋር ተያይዘው አንዳንድ ማስረጃዎች ያልተሟሉ በመሆናቸው፣ ተሟልተው ከቀረቡልን በኋላ ነው የክስ መቃወሚያ ማቅረብ የምንችለው በማለታቸው ፍ/ቤቱ አቃቤ ህግ ለህዳር 17 ጎደሉ የተባሉትን የማስረጃ ዝርዝሮች አሟልቶ ያቅርብ ብሏል፡፡

habtamu-ayalew
የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ሃብታሙ አያሌው፤ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና የአረና ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታን ጨምሮ በአስር ሰዎች ላይ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስ ተማሪ ዘላለም ወርቅአገኘሁን አንደኛ ተከሳሽ በማድረግ አቃቤ ህግ ያቀረበው መዝገብ፤ ተከሳሹ የግንቦት 7 አባል ነው ብሏል፡፡ ግንቦት 7 በመንግስት አሸባሪ ነው ተብሎ እንደተፈረጀ አቃቤ ህግ ጠቅሶ፣ ተከሳሹ ለግንቦት 7 ሰዎችን በመመልመል ወደ ኤርትራ ሄደው እንዲሰለጥኑ አድርጓል፤ ህገ መንግስታዊ ስርአቱንና ማህበራዊ ተቋማትን በሽብር ለማፈራረስ ተንቀሳቅሷል የሚል ክስ አቅርቧል፡፡ አራቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ህጋዊ ፓርቲን እንደ ሽፋን ተጠቅመዋል በማለት አቃቤ ህግ ያቀረበው ክስ ደግሞ፤ ተከሳሾቹ ከግንቦት 7 አመራሮች ጋር በመገናኘትና በመመካከር የተለያዩ የሽብር ተልዕኮዎችን ተቀብለዋል የሚል ነው፡፡
በሌሎቹ ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስም የግንቦት 7 አባል በመሆን አላማውን ለማስፈፀም ተንቀሳቅሰዋል ይላል፡፡