Archive | November 29, 2014

ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የከንቲባው ቢሮ በነገው የተቃውሞ ስብሰባ እየተወነጃጀሉ ነው

የመስተዳድሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ሠማያዊ ፓርቲን በጥብቅ አስጠንቅቋል

/አዲስ አድማስ/ ዘጠኝ የ9 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነገ እሁድ የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ የእውቅና ጥያቄውን የሚቀበል የመንግስት አካል ቢያጣም ስብሰባውን ከማከናወን ወደኋላ እንደማይል አስታውቋል፡፡ የከንቲባ ፅ/ቤቱ ቀደም ሲል ህዳር 7 ሊካሄድ የነበረውን የአደባባይ ስብሰባ ተከትሎ ለሰማያዊ ፓርቲ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሠጥቷል፡፡
ነገ እሁድ ህዳር 21 ቀን የአደባባይ ስብሰባ ለማካሄድ በመኢዴፓ በኩል የእውቅና መጠየቂያ ደብዳቤው ለአዲስ አበባ መስተዳድር የከንቲባ ለመስጠት በተደጋጋሚ ሞክረው አለመሣካቱን ገልፀዋል፡፡ የከንቲባ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ደብዳቤውን ሊቀበሉን ፍቃደኛ አልሆኑም ያሉት የተቃዋሚ አመራሮች “ቢሮ ውስጥ ደብዳቤውን ስናስቀምጥ ‹ወንጀል ነው› በማለት ሃላፊው ሊያስፈራሩን ሞክረዋል” ብለዋል፡፡
ደብዳቤውን ህዳር 12 ቀን በኢትዮጵያ ፖስታ ድርጅት የፈጣን መልዕክት (ኢ.ኤም.ኤስ) አገልግሎት ልኮናል ብለዋል አመራሮች ነገር ግን አንድም የመስተዳድሩ አካል ደብዳቤውን ለመቀበል ፍቃደኛ እንዳልሆነ ከፖስታ አገልግሎቱ እንደተገለፀላቸው የትብብሩ አመራሮች ሰሞኑን በሠማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በነገው እለት ሊያካሂድ ያቀደውን የአደባባይ ስብሰባ ትብብሩ እንደማይሠርዝ የገለፁት ሊቀመንበሩ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ደብዳቤውን በድጋሚ ወደ ከንቲባ ጽ/ቤት በአካል ይዘው እንደሚሄዱና የማይቀበሏቸው ከሆነም በሩ ላይ እንደሚለጥፉ ገልፀዋል፡፡ የአንድ ወር ጊዜ ተይዞለት በትብብሩ የተጀመረው የአደባባይ ስብሰባ ዘመቻ “ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል መርህ ከምርጫ በፊት “ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ” እና ብሔራዊ መግባባት እንዲሁም ምርጫው ነፃ ፍትሃዊ፣ አሣታፊ፣ ተአማኒ መሆን በሚችልበት ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በማሰብ የተጀመረ መሆኑን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል በሠማያዊ ፓርቲ አስተባባሪነት ህዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም በተመሳሳይ “የትብብሩ አባል በሆነው ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” በሚል መርህ የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ ተጠርቶ የነበረ ሲሆን ስብሰባው ጥቂት ሠዎች በተገኙበት ከተጀመረ በኋላ በፖሊስ መበተኑ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎም ስብሰባውን ሲያስተባብሩ ነበር የተባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ፍ/ቤት ቀርበው ምርመራ እየተጣራባቸው ነው መባሉ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት በቀን 11/03/07 በቁጥር አ.አ/ከፅ/03/304/43 በሠማያዊ ፓርቲ “የተደረገውን ህገወጥ ተግባር በማስመልከት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ” በሚል በተፃፈ ደብዳቤ ፓርቲው ምንም አይነት የአደባባይ ስብሰባ እውቅና እንዳላገኘ እያወቀ ህዳር 6 ቀን 2007 ዓ.ም የቅስቀሳ በራሪ ወረቀት በመበተንና ህገ – ወጥ የአደባባይ ስብሰባ ለማድረግ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር አላስፈላጊ ግብግብ በመፍጠርና ጩኸት በማሰማት የአካባቢውን ህብረተሰብ ፀጥታና ሠላም የማወክ ተግባር ተከናውኗል ብሏል፡፡ ድርጊቱም ፓርቲው ህግን ተከትሎ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በህገወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ያለ መሆኑን እንደሚያሳይ በደብዳቤው የጠቆመው ጽ/ቤቱ፤ በቀጣይ ፓርቲው ህግን አክብሮ የማይንቀሳቀስ ከሆነ ድርጊቱ ፀረ – ህገመንግስት ስለሆነና የከተማዋን ህዝብ ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ በጥብቅ አስጠንቅቋል፡፡  “የእውቅና ስጡን ጥያቄያችንን የሚቀበለን አካል አጣን” የሚለውን የተቃዋሚዎቹን አቤቱታ በተመለከተ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን የስራ ኃላፊ በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባላችን ሊሳካልን አልቻለም፡፡