Archive | December 12, 2014

አንዳርጋቸው ፅጌ እንዴት ተያዘ?

ከተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)

አንዳርጋቸው ፅጌን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሁት የ2014 የፋሲካ በአል በዋለ ማግስት ነበር። ወደ ለንደን መንገድ ስለነበረው ከተከዜ በረሃ ወደ አስመራ መጥቶ ሳለ ደወለልኝና ተገናኘን። ሳገኘው ታሞ ነበር። ከምግብ ወይም ከውሃ ጋር የተያያዘ ቀላል ህመም እንደሆነ ነገረኝና ወደ ፋርማሲ ሄደን መድሃኒት ገዛን። እየደወልኩ ስለ ጤንነቱ ስጠይቀው ቆየሁ። በሶስተኛው ቀን ተሲያት ላይ ይመስለኛል ወደ ቤቱ ብቅ አልኩ። የግቢውን በር ገፍቼ ስገባ አንዳርጋቸው በሁለት እጆቹ ልሙጥ የባህር ድንጋዮችን ተሸክሞ ቁጭ ብድግ እያለ ስፖርት ሲሰራ አገኘሁት። ማጅር ግንዱ በላብ ርሶአል። ግቢው ውስጥ ካለችው የብርቱካን ዛፍ ላይ ያንጠለጠለውን ፎጣ አንስቶ ላቦቱን ማደራረቅ ያዘ።
በረንዳው ላይ ቁጭ ብለን ጥቂት ካወጋን በሁዋላ ለመሄድ ተነሳሁ። በዚህ ጊዜ ከሶስት ቀናት በሁዋላ ወደ ለንደን ለመሄድ ትኬቱን እንደቆረጠ ገልፆልኝ በነጋታው ምሽት የራት ቆይታ እንድናደርግ ጠየቀኝ። ሁለታችንም በጋራ የምናውቀውን ሰው ስም ጠቅሶም በራት ቆይታው ላይ እንደሚገኝ ጠቆመኝ። ተስማማሁና ቀጠሮ ያዝን።
በነጋታው በቀጠሮአችን መሰረት ተገናኘን። ምንም ልዩ ርእሰ ጉዳይ አልነበረንም። ስለ አካባቢያችን ፖለቲካ ተጨዋወትን። ስለ ግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል አንስቶም ጥቂት ነገረን። በሰው ሃይልና በአንዳንድ አስፈላጊ ተሽከርካሪዎች በመጠናከር ላይ መሆናቸውን፣ ወያኔ ያዳከመውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለመመለስ የሚሰራው የፖለቲካ ስራ ራሱን የቻለ ጊዜ የሚወስድ ስራ እንደሆነ፣ በጥቅሉ ግን ትግሉ ተስፋ እንዳለው ነበር ያጫወተን። ሞራሉ ጥሩ ነበር። ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ አላየሁበትም።
ራት እስኪቀርብ፣ “የጀሚላ እናት” በሚል ርእስ ካዘጋጀሁት (በወቅቱ ካልታተመ) መፅሃፍ አንድ ትረካ አነበብኩላቸው። “የአዲሳባ ቀብር” የሚል ነበር። ትረካው ኮሜዲ አይነት ስለነበር እየሳቁ ነበር ያዳመጡኝ። ከእኩለ ሌሊት በፊት መለያየታችን ትዝ ይለኛል። አንዳርጋቸው መኪና ስላልያዘ ቤቱ አድርሼው፣ “መልካም መንገድ” ተመኝቼ ተሰናበትኩት።
ያቺ ምሽት ከአንዳርጋቸው ጋር የመጨረሻ የምተያይባት እለት ትሆናለች ብዬ ግን እንዴት ማሰብ ይቻላል?
አሁንም ቢሆን ለዘልአለሙ አንተያይም ብዬ አልደመደምኩም። ሌላው ቀርቶ ይህች መጣጥፍ እንኳ ካለበት ጉረኖ
ደርሳ ሊያነባት እንደሚችል ተስፋ አደርጋለሁ።
ስለነገ ማንም አያውቅም። መለስ ዜናዊ ከግርማ ወልደጊዮርጊስ ቀድሞ ይሞታል ብሎ ሊያስብና ሊገምት
የሚችል ማንም አልነበረም። ደካማና በቀላሉ ተሰባሪ የሆነች ነፍሳችን ከአስር ደቂቃ በሁዋላ ምን ሊገጥማት
እንደሚችል እንኳ አናውቅም። ተስፋ ግን በልባችን ሞልቶ ተርፎአል። ስለዚህም ሰዎች በተስፋ ይኖራሉ። ሰዎች
በተስፋ አሻግረው ያልማሉ። ሰዎች በተስፋ እርቀው ይጓዛሉ…
ደጋግሜ እንደገለፅኩት አንዳርጋቸው ከነሙሉ ችግሮቹ ብርቱ ሰው ነበር። አንዳርጋቸው አደጋ ላይ
በመውደቁ ኢትዮጵያውያን “የአንድነት ሃይል” ፖለቲከኞች ትልቅ ሰው ጎድሎባቸዋል። ርግጥ ነው፣ ከአንዳርጋቸውጋር ስናወጋ የኦሮሞ ጉዳይ ከተነሳ ተግባብተን አናውቅም። አንዳርጋቸው በያዘው የፖለቲካ አቋም ከሰፊው የኦሮሞ
ህዝብ ደጋፊ ሊያገኝ እንደማይችል መናገሬም አልቀረ። በተለያዩ ፅሁፎች የማንፀባርቀውን አቋም አነሳ ነበር። አንድ
ጊዜ በወግ መሃል፣
“የታሪክ እስረኛ ላለመሆን ምኒልክ የኦሮሞ ህዝብ ላይ ለፈፀመው ግፍ ይቅርታ ጠይቃችሁ አጀንዳውን
ለመዝጋት ለምን አትሞክሩም?” ብዬ ጠይቄው በአነጋገሬ በጣም መቆጣቱን አስታውሳለሁ።
አንዳርጋቸው ለአማራ ብቻ ሳይሆን፣ ለትግራዩም፣ ለኦሮሞውም በአጠቃላይ ለመላ ኢትዮጵያውያን
የሚጠቅም የፖለቲካ መስመር ተከትያለሁ ብሎ በጥብቅ ያምናል። ለነገሩ ወያኔም እንዲሁ ይላል። ኢህአፓም
ይህንኑ ይላል። ሞአ-አንበሳ እንኳ በአቅሟ የዘውድ መመለስ ለኢትዮጵያ አንድነት ፍቱን መፍትሄ መሆኑን
ትሰብካለች። ፈላስፋው ዘርአያእቆብ እንደጠየቀን ‘ሁሉም የኔ መስመር ትክክል ነው’ የሚል ከሆነ ‘በዚህ መካከል
ማነው ፈራጅ?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ምላሹ ቀላል ነበር። ፈራጅ ሊሆን የሚችለው ህዝብ ነው። የምንመፃደቅበት
ህዝብ ግን የሚሻለውን የመምረጥ እድል አላገኘም…
ሌላ ቀን ደግሞ እንዲሁ ከአንዳርጋቸው ጋር ስንጨዋወት እንዲህ አለኝ፣
“የወያኔ መውደቅ የማይቀር ነው። ከወያኔ መውደቅ በሁዋላ በአገሪቱ ሊፈጠር የሚችለው ክፍተትና
መለያየት ግን በጣም ያሳስበኛል። ከባድ ፈተና ከፊታችን ተደቅኖአል። ለብሄርና ለቋንቋ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ
መስጠት ይጠበቃል። ከፊታችን የተደቀኑትን ቋጥኝ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያበቃ በቂ ዝግጅት አለን ለማለት ግን
እቸገራለሁ። ችግሩ ምን መሰለህ? መሬት ላይ የሚሰራው ስራ ከፕሮፓጋንዳው ጋር አልተመጣጠነም።
ፕሮፓጋንዳው መቅደሙ አደገኛ ነው።”
አንዳርጋቸው ይህን መሰረታዊ ችግር የሚዳስስና መፍትሄ የሚያስቀምጥ አዲስ መፅሃፍ በመፃፍ ላይ ነበር።
የመፅሃፉን ርእስ “ነፃነትን የማያውቅ ነፃአውጪ – ክፍል ሁለት” እንዳለውም ነግሮኝ ነበር። የመጀመሪያው “ክፍል
አንድ” መፅሃፍ፣ የአርትኦት ስራ ያስፈልገው ስለነበር፣ በአጫጭር አረፍተነገሮችና በቀላል አማርኛ እንድነካካው
ጠይቆኝ በትርፍ ጊዜዬ እያገዝኩት ነበር። ሁለቱንም መፃህፍት አንድ ላይ የማሳተም አሳብ ነበረው።
ወያኔ አንዳርጋቸውን የመን ላይ አሸምቀው እንደያዙት የሰማሁ ቀን በድንጋጤ ደንዝዤ ነበር። ማመን
አቃተኝ። አንዳርጋቸው ከአራት አመታት በላይ ወደ ኤርትራ ሲመላለስ የሱዳንና የየመንን አየር መንገዶች ተጠቅሞ
እንደማያውቅ አውቃለሁ። እኔ አልፎ አልፎ የየመንን መንገድ እንደምጠቀም ስለሚያውቅ፣ “ተው፣ አትመናቸው”
ብሎ ጭምር መክሮኛል። የመን ላይ ‘መንግስት አለ’ ለማለት እንደማይቻል አንዳርጋቸው እያወቀ ምን ሊሆን የመን
ሄደ? ያልተመለሰ ጥያቄ ሆነብኝ።
ዜናውን ስሰማ የተደበላለቀ አሳብ ወደ አእምሮዬ መጣ። ሊሆን የማይችል ጥርጣሬ ነገሮች ጭምር
ረበሹኝ። ዜናውን በሰማሁበት ደቂቃ ስንቱን አወጣሁ፤ ስንቱን አወረድኩ። ማን ዘንድ ደውዬ ማንን እንደምጠይቅ
ግራ ገባኝ። በመጨረሻ ወደ አንዳርጋቸው ዘመዶች እየበረርኩ ሄድኩ።
አስመራ ላይ አንዳርጋቸው “ዘመዶች” አሉት። የስጋ ዘመዶቹ አይደሉም። አዲስአበባ ጎረቤቶቹ የነበሩ
ናቸው። ነገሩ እንኳ ከጉርብትና በላይ ነው። አንዳርጋቸው ወጣት የኢህአፓ አባል ሆኖ ሲንቀሳቀስ የደርግ አፋኞች
ሊገድሉት ያሳድዱት ነበር። ወንድሙንና አንድ ኤርትራዊ ጓደኛውን ጎዳና ላይ ሲረሽኑበት አንዳርጋቸው የሚገባበት
ቀዳዳ አልነበረውም። በዚህ ችግር መሃል፣ የእናቱ ጓደኛ የነበረች አንዲት ኤርትራዊት ሴት አንዳርጋቸውን ወደ
አስመራ በመውሰድ ከመኖሪያ ቤቷ ሸሸገችው። ስድስት ወራት ከቤት ሳይወጣ ከቆየ በሁዋላ ያቺ ሴት የሃሰት
መታወቂያ አውጥታለት፣ ትንሹን አንዳርጋቸው እንደ ገበሬ አልብሳ ወደ ገጠር በመውሰድ ለሻእቢያ አስረከበችው።
ሻእቢያ አንዳርጋቸውን በሱዳን በኩል ሸኘው። ከዚያም አንዳርጋቸው ወደ ለንደን አቀና። አንዳርጋቸው መፅሃፉን
ሲፅፍ የመፅሃፉን መታሰቢያ ከሰጣቸው መካከል ጓደኛው የነበረ የእነዚሁ የኤርትራውያኑ ልጅ የነበረ ነው። ይህን
የተከበረ ቤተሰብ አንዳርጋቸው ወስዶ አስተዋውቆኝ ነበር። ስድስት ወራት የተደበቀባትን ክፍል ጭምር
አይቻለሁ። አንዳርጋቸው ይህን ቤተሰብ እንደ ስጋ ዘመዱ ያያል። እነርሱም አንዳርጋቸውን ሲያዩ በደርግ የተረሸነ
ሟች ወንድማቸውን ያስታውሳሉ።
እንግዲህ አንዳርጋቸው የመን ላይ መያዙን ስሰማ ወደ እነዚህ ሰዎች ነበር የበረርኩት። እንደደረስኩ
የግቢውን በር ደበደብኩ። አንዲት ሴት ብቅ አለች። አላውቃትም። እንግዳ ሳትሆን አትቀርም። ማንን እንደምፈልግ
ነገርኳት። የፈለግሁዋት ሴት እንደሌለች ነገረችኝ። እና የእጅ ስልኳን ሰጠችኝ። ደወልኩ። የምፈልጋት ሴት ስልኩን
አነሳች። ማን እንደሆንኩ ከነገርኳት በሁዋላ፣
“ስለ አንዳርጋቸው ሰማሽ?” ስል ጮህኩ።
“አልሰማሁም። ምን ሆነ?” ስትል እሷም ጮኸች።
“አሁኑኑ ነይ። እነግርሻለሁ…”
ከአስር ደቂቃ በሁዋላ እዚያው ከቤታቸው በራፍ ላይ ቁጭ ብለን የሰማሁትን ሁሉ ነገርኳት። ቃል
መተንፈስ እንኳ ተቸገረች። ትንፋሿ ቆሞ ድርቅ ብላ ቆየች። በመጨረሻ ግን ጥቂት ጥያቄ አዘል ቃላት ተናገረች፣
“በየመን በኩል ለምን እንደመጣ አልገባኝም? በየመንያ እንደማይጠቀም ከዚህ በፊት ነግሮኝ ነበር?”
በመቀጠል ከአንዳርጋቸው “ዘመዶች” ወደሌላው ደወልኩ። ተገናኝተን ስናወጋ ዜናውን ሰምቶ ነበር
የጠበቀኝ። ግራ ተጋብቶ ነበር። ግራ በተጋባ ስሜትም፣
“አንዳርጋቸው ከለንደን ሲነሳ ደውሎልኝ ነበር።” አለኝ። አያያዘና አከለበት፣ “…ትኬቱ በኤርትራ አየር
መንገድ ከዱባይ በቀጥታ ወደ አስመራ የተቆረጠ ነበር። ለምን በየመን በኩል እንደቀየረው አልገባኝም?”
አንዳርጋቸው ከየመን ወደ አዲሳባ መዛወሩን እስከሰማሁባት እለት የነበሩት ቀናት ለኔ እጅግ አስጨናቂ
ነበሩ። ወሬው አስመራን አዳርሶ ነበር። ፖለቲካ የማይከታተሉ ሰዎች ሳይቀሩ የአንዳርጋቸውን ስም እያነሱ ሲነጋገሩ
ሰማሁ። የኔና የአንዳርጋቸውን መቀራረብ የሚያውቁ እየደወሉ ይጠይቁኝ ነበር። አንዳርጋቸውን በፖለቲካ አቋሙ
የሚቃወሙት የኦነግ ከፍተኛ አመራር አባላት ጭምር በየመን ድርጊት ክፉኛ ተቆጥተው ነበር። የኦነግ አመራር
ከመቆጣት አልፎ የመን ላይ ዛቻ የቀላለቀለ መግለጫ አወጣ። ዳሩ ግን ማንም ምንም ማድረግ በማይችልበት
ፍጥነት አንዳርጋቸው ተላልፎ ለወያኔ ተሰጥቶ ኖሮአል። ኦሮማይ!
አንዳርጋቸው እንዴት ከወያኔ እጅ ሊገባ እንደቻለ ዛሬም ድረስ ግልፅ መረጃ የለም። የተለያዩ መላ
ምቶችን እየሰማን፣ እያነበብን ቆይተናል። አንዳርጋቸውን በቅርብ ከሚያውቁት አንዱ እንደመሆኔ እኔም ካለኝ
መረጃ በመነሳት የራሴን ግምት መውሰዴ አልቀረም። የኔን ግምት ይፋ ከማድረጌ በፊት ሌሎች የሚሉትን
ለመስማት በሚል እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ሳልፅፍ ቆይቼ ነበር። አሳማኝ መረጃ ሳይፃፍ ወይም ሳይገለፅ ጊዜው
ስለረዘመ እነሆ! እኔም የግል አስተያየቴን ለማኖር ወሰንኩ…
ኤልያስ ክፍሌ ethiopianreview ላይ የፃፈውን አንብቤያለሁ። ግንቦት 7 የኤልያስን መረጃና ትንታኔ
በደፈናው፣ “ውሸት” ሲል ማስተባበሉንም ተከታትያለሁ። ግንቦት 7 ከማስተባበል አልፎ አንዳርጋቸው እንዴት
ሊያዝ እንደበቃ መግለፅ አለመቻሉ ግን ማስተባበሉን ጎደሎ ያደርገዋል። ያም ሆኖ የኤልያስ ክፍሌ ዘገባ ለኔ
አሳማኝ አልነበረም። በተመሳሳይ ከአንዳርጋቸው መያዝ ጋር በተያያዘ ጥቂት ወሬዎችን ተከታትያለሁ።
ከሰማሁዋቸው መካከል፣
“አንዳርጋቸው ከዱባይ አስመራ በቀጥታ የሚወስደው የኤርትራ አየር መንገድ ትኬት ነበረው። ዱባይ
ላይ የኤርትራ አይሮፕላን ስላመለጠችው የየመንን ትኬት ገዛ።” የሚለው አንዱ ነው።
ለዚህ መረጃ ክብደት ልሰጠው አልቻልኩም። አንዳርጋቸው ተጨማሪ አንድ ቀን ዱባይ በማደር
የሚቀጥለውን የኤርትራ አይሮፕላን መጠቀም እየቻለ፣ እንዴት አስተማማኝ እንዳልሆነ በሚያውቀው የመኒያ
ለመጓዝ ይወስናል? አንዳርጋቸው በየመን አየር መንገድ የተጓዘው በግማሽ ቀን ውስጥ በራሱ ውሳኔ ብቻ ከሆነ፣
የወያኔና የየመን የፀጥታ ሰዎች በዚያችው ቅፅበት አንዳርጋቸውን ለማፈን መቀናጀት ችለዋል ብሎ ማመን
ይቸግራል። የመሆን እድሉ በጣም አናሳ ነው። ለንደንም ሆነ አስመራ የሚገኙ የአንዳርጋቸው ዘመዶች የማያውቁት
አንድ ጉዳይ ያለ ይመስላል። በርግጥም አንድ ምስጢር ሊኖር እንደሚችል እጠረጥራለሁ።
ነገሩ ወዲህ ነው…
በአንድ ወቅት ግንቦት 7 ከነ ነአምን ዘለቀ እና ከአንድ የሆነ የአፋር ድርጅት ጋር ውህደት ነገር
መፈፀማቸውን በዜና ነግረውን ነበር። ከውህደቱ በሁዋላ ብዙም የተወራ ነገር ሳይኖር ነገሩ ተድበሰበሰ። ነአምን
ዘለቀ ከግንቦት 7 ጋር አብሮ ሲሰራ ስመለከት ግን አፋሮቹም ሆነ እነ ነአምን ጠቅልለው ግንቦት 7 ውስጥ ገብተዋል
የሚል ግምት ወስጄ ነበር። የአንዳርጋቸው የመያዝ ሂደት ከዚያ ሳይጀምር አልቀረም።
አንዳርጋቸው ከአፋሮቹ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነቱን አጥብቆ ቀጥሎ እንደነበር አውቃለሁ። ምን
እንደሚሰራ ግን ፈፅሞ ነግሮኝ አያውቅም። በመካከሉ ሆላንድ ሳለሁ ከግንቦት 7 ሰዎች በኩል የሾለከ የሚመስል
ወሬ ሰማሁ። ይህም ወሬ ለስራ ተብሎ 30 ሺህ ዶላር ተሰጥቶት ወደ የመን የተላከ አንድ አፋር የመሰወሩ ወሬ
ነበር። ወሬው በሰፊው የተሰራጨ አልነበረም። እጅግ በጣም ጠባብ በሆነ ቀዳዳ ነበር የሰማሁት። ይህ ወሬ
ሲመዘን ተራ ወሬ ሊመስል ይችላል። አፋሩ ገንዘብ መያዙ በርግጥ መረጃውን ከፍ አድርጎታል። ከገንዘቡ በላይ ግን
“የመን” የሚለው መረጃ ክብደት ነበረው። ግንቦት 7 የመን ላይ ትኩረት ማድረጉ ትልቅ መረጃ ነበር። አፋሩ
የመን-ሰንአ ሲደርስ ተሰወረ። ከዳ ወይስ ተያዘ? አይታወቅም። ከድቶም ሆነ ተይዞ ወያኔ እጅ ገብቶ ሊሆን
እንደሚችል ግን መገመት ይቻል ነበር። ይህ ከሆነ የግንቦት 7ን የተደበቀ ፍላጎት ወያኔ አውቆአል ማለት ነው።
ግንቦት 7 ምን እንደሚፈልግ ወያኔ ካወቀ፤ የግንቦት 7ን ፍላጎት ለማጥመጃ ሊጠቀምበት ይችላል። ቀላል
ጉዳይ አይደለም። ግንቦት 7 የመን ላይ ምንድነው የፈለገው? ከስደተኞች መካከል ታጋዮችን መመልመል?
የተመለመሉትን ደግሞ ወደ ተከዜ በረሃ ማሻገር? ይህን ስራ ለማከናወን ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። ውድ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን ይህን ስራ ለመስራት የሚችል፣ አላማ ያለው ብቁ ሰው የመን ላይ ማግኘትን ይጠይቃል።
አፋሩ ገንዘብ ይዞ የመን ላይ ከተሰወረ በሁዋላ አንዳርጋቸው ተስፋ ቆርጦ ጉዳዩን ይተወዋል ተብሎ
አይገመትም። እንደገና ይሞክራል። ወያኔዎች በዚህ በአንዳርጋቸው ዳግማዊ ሙከራ ጊዜ የራሳቸውን ሰው የመን
ላይ አስቀምጠው አንዳርጋቸውን እንዲገናኘው አድርገው ይሆን? አንዳርጋቸው በረጅም ሂደት ወያኔዎች
ያዘጋጁለትን ሰው እንደራሱ ሰው በማመን ለግንቦት 7 አባልነት በምስጢር መልምሎት ይሆን? እና በረጅም ጊዜ
ሂደት አንዳርጋቸው ወያኔዎች ባዘጋጁለት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቶላቸው ይሆን? ማለትም አንዳርጋቸው
እነዚያ አባላቱን ለማነጋገር፣ አሊያም ታጋዮቹን ወደ ተከዜ ለማሸጋገር እንዲቻል አንዳንድ ጉዳዮችን ለመፈፀም
በምስጢር የመን ገብቶ ለመውጣት ሞክሮ ይሆን?
ጥያቄዎቹ “አንዳርጋቸው እንዴት ተያዘ?” ለሚለው ጥያቄ ፍንጭ ሰጪ ሊሆኑ ይችላሉ። ቀጥተኛ መረጃ
ያለው አካል የተፈፀመውን በዝርዝር እስካልነገረን ድረስ ከምናውቀው በመነሳት ለመገመት እንገደዳለን።
ከዚህ ሁሉ በሁዋላ፣ “ወያኔዎች አንዳርጋቸውን ይዘው በማሰራቸው አተረፉ ወይስ ከሰሩ?” የሚል ጥያቄ
ይነሳል። የወያኔ ሰዎች “አተረፍን” እያሉ ነው። ማትረፍና መክሰራቸውን ለማየት በርግጥ ጥቂት ጊዜ መጠበቅ
ያስፈልግ ይሆናል። “አትርፈናል” ባዮች ከበሮ ሲደልቁ ሰምተናል። በአንዳርጋቸው መያዝ ቆሽቱ የደበነ ወገን፣ ነገ
በቁጣ ምን ሊፈፅም እንደሚችል አለመገመት የፖለቲካ የዋህነት ነው። እነ በቀለ ገርባ፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ
ኦልባና ሌሊሳ፣ እነ ኢንጂነር መስፍን አበበ (ራሶ)፣ እነ ጫልቱ ታከለ፣ እነ ኢብራሂም ሱልጣን፣ እነ ሰይድ አሊ፣ እነ
ፊፈን ጫላ፣ እነ ኮሎኔል ኦላኒ ጃሉ፣ እነ ውብሸት ታዬ፣ ዛሬም ድረስ እስርቤት ናቸው። አንዳርጋቸው ፅጌ
ተጨምሮአል። ይህን ፅሁፍ እየጻፍኩ ሳለም በርካታ ነፃነት ጠያቂዎች እየታፈኑ ወደ እስር ቤት በመጓዝ ላይ ነበሩ።
እስርቤት የተወረወሩትን ዜጎች በቀን 24 ሰአት የሚያስታውስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዜጋ በመላ ኢትዮጵያ አለ።
በደል ሲበዛ ወደ በቀል ይለወጣል። ብዙውን ጊዜ ተበዳዮች ጉልበት ሲያገኙ የማመዛዘን ችሎታቸውን
ያጣሉ። በቀል ከመጣ ከደሙ ንፁህ የሆነውን ከተጠቃሚው መለየት ሳይቻል ጊሎቲኑ ከፊቱ ያገኘውን ሊበላ
እንደሚችል ከታሪክ በተደጋጋሚ አይተናል። ወያኔ አንዳርጋቸውና መስፍን አበበን በመሳሰሉ ታጋዮች ላይ
እየፈፀመ ባለው የማፈን ድርጊት ከህዝቡ መራር ቂም በማትረፍ ላይ ነው። ጭፍን ደጋፊዎቹ አደጋ ላይ
እንዲወድቁም አጋልጦ እየሰጣቸው ነው። በመሆኑም ወያኔ አትራፊ ስለመሆኑ ማረጋገጥ አይችልም።
የፅጌ ልጅ – አንዳርጋቸው ከጠላቶቹ እጅ ላይ ወድቆአል። በወያኔ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦም ጥቂት ቃላትን
ተናግሮአል። አንዳርጋቸው በጨካኝ ጠላቶቹ እጅ ላይ ወድቆ ሳለ የተናገራቸውን ቃላት በቀጥታ መውሰድ ወይም
ንግግሩን እንደ መረጃ ተጠቅሞ በዚያ ላይ አስተያየት መስጠት ተገቢ አለመሆኑን እረዳለሁ። ያም ሆኖ
አንዳርጋቸው በንግግሩ፣ “እኔን ተክቶ በረሃ የሚወርድ ሰው ማግኘት ይቸግር ይሆናል” አይነት አባባል መጠቀሙ
በተዘዋዋሪ የትግል ጥሪ ይመስለኛል። መስማት የሚፈልግ ካለ ይህን ሊሰማ ይችላል…
ርግጥ ነው አንዳርጋቸው ከተያዘ በሁዋላ በመላ አለም የሚገኙ “የአንድነት ሃይሎች” በቁጣ የተቃውሞ
ሰልፎችን አካሂደዋል። “አንዳርጋቸው ነኝ!” የሚል መፈክር ይዘውም ታይተዋል። “ሁላችንም አንዳርጋቸው ነን!”
የሚለው መፈክር ለአንዳርጋቸው ተገልብጦ ስድብ እንዳይሆንበት ግን እሰጋለሁ። “አንዳርጋቸው ነኝ!” ለማለት
ቢያንስ አንዳርጋቸው የሞከረውን ለመሞከር ቁርጠኛነትን ማሳየት ይጠይቃል። “ሁላችንም አንዳርጋቸው ነን!”
የሚለው አባባል በአፍ ብቻ ተንጠልጥሎ ከቀረ፣ እንደተለመደው የአንድ ሰሞን የዳያስፖራ ጫጫታ ሆኖ እንደ
ቀዳሚዎቹ መፈክሮች ይህም ከተረሳ ለአንዳርጋቸው ስድብ እንጂ ክብር ሊሆነው አይችልም።

የሀገራችን ፖለቲካና ስሉጣን (Activists) በቅሊንጦ!

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

prison

አስቀድሜ ጽሑፉ ትንሽ በመርዘሙ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ከያዘው አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳይ አንጻር ነውና ተረዱኝ ያውም ብዙ ነገር ትቸ ነው፡፡ ባይሆን ከሦስት እከፍለዋለሁ ቀጣዮችን ጽሑፎች ተከታትለው ይቀርቡላቹሀል፡፡ ጽሑፉ ብዙ ብዥታ ያጠራላቹሀልና አንብቡት፡፡ ለነገሩ የኔን ጽሑፎች ባሕርያት ለምዳቹህታልና በመርዘሙ እጅግም የምትማረሩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ረዘመ ብላቹህ ሳታነቡት የምትቀሩ ብትኖሩ አመለጣቹህ!

ማሳሰቢያ ጽሑፉን ስታነቡ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ወዘተ. እያልኩ ስል አሉ ብለው ከሚያምኑ ሰዎች ጋር ነውና እያወራሁ ያለሁት ከነሱ ጋር በነሱ ቋንቋ ተናግሬ ለመግባባት ያህል እንጅ በዚህ ዘመን የብሔረሰቦች እሴቶች ቢኖሩም ብሔረሰቦቹ ግን አሉ ማለቴ አይደለምና በዚህ ግንዛቤ አንብቡልኝ፡፡

የተከሰስኩበትን ጉዳይ ታውቁታላቹህ ብየ አስባለሁ እሱም አምና መጋቢት ወር ላይ በዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 113 ላይ “የተገነቡትና በመገንባት ላይ ያሉት የመታሠቢያ ሐውልቶች የማንና ለነማንስ ናቸው” በሚል ርእስ በአኖሌ የጥፋት ሐውልትና በጥፋት ኃይሎች ፀረ ኢትዮጵያ ሸርና ሴራ ዙሪያ በጻፍኩት ጽሑፍ ሳቢያ ጅማ ዩኒቨርስቲ ነበር በዩኒቨርስቲ (በመካነ ትምህርቱ) ብጥብጥ ተነሥቶ ከባድ ጉዳት ደርሶብኛል ብሎ ባቀረበብኝ ክስ መሠረት ፖሊስ በማዕከላዊ በእኔና በመጽሔቱ ኤዲተር (አርታኢ) በኤልያስ ገብሩ ጎዳና ላይ ምርመራ አድርጎ ክሱን ወደ ዐቃቤ ሕግ በመምራቱ ዐቃቤ ሕጉ ክስ መሥርቶብን ለኅዳር 2-2007ዓ.ም. በከፍተኛ ፍርድ ቤት እንድንገኝ በተነገረን መሠረት ነበር በዕለቱ ፍርድ ቤት የተገኘነው፡፡ ችሎቱ ሲቻል ጠበቃችን ተማም አባቡልቱም እኛም ጽሑፉ ሊያስከስሰን እንደማይገባ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን እንደሆነ በተቻለን መጠን አስረዳን፡፡

ዳኛውም የዐቃቤ ሕጉን መልስ ከሰሙ በኋላ “ይህ ጽሑፍ በእርግጥ ያስከስሳል ወይስ አያስከስስም” በሚለው ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለታሕሳስ 6 ቀጠሮ ሰጥቶን እያንዳንዳችን ሃያ ሃያ ሽህ ብር ዋስትና አስይዘን እንድንወጣ አዘው ችሎቱ ተዘጋ፡፡ እኛም ይሄንን የዋስትና ገንዘብ ለማስያዝ አቅሙ የሌለን በመሆኑ የሞያ አጋሮቻችን አስተባብረው ከሕዝብ መዋጮ ሰብስበው ከፍለው እስኪያስፈቱን ድረስ ወደ እስር ለመወርወር ተገደድን፡፡ በዚህም ምክንያት በዚያው ዕለት እጃችን በካቴና ተጠርንፎ ከፍርድ ቤቱ አቅራቢያ በሚገኘው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እዚያው አቆይተው ከእኩለ ሌሊት በኋላ ደግሞ ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ ወስደው እዚያ አሳደሩንና ጠዋት ረፋዱ ላይ ወደ ቅሊንጦ ጭነው ወሰዱን እስክንፈታም ድረስ እዚያው ታሰርን፡፡

ቅሊንጦ እስር ቤት በ3 ዞኖች የተከፈለ 3 ሽህ እስረኛ ያለበት ትልቅ እስር ቤት ነው፡፡ ከእነኝህ እስረኞች ከሁለት ሦስተኛው በላይ ከውንብድና እስከ የትራፊክ አደጋ ፈጻሚነት ድረስ በተለያዩ ወንጀል በተባሉ ድርጊቶች ተጠርጥረው የታሰሩ ናቸው፡፡ የአእምሮ ሕሙማንም አሉ ወደ አእምሮ ሕሙማን ማዕከላት መቀላቀል ሲገባቸው ለምን እዚህ እንዳመጧቸው በደንብ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡ እኔ በነበርኩበት ግቢ ብቻ ከ30 በላይ የአእምሮ ሕሙማን ነበሩ፡፡ ሲያሻቸው ድንጋይ ወይም አንዳችነገር እያነሡ ግንባር ይፈነክታሉና ምናልባት ይሄንን በማድረግ ታሳሪውን እንዲቀጡ ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ የተቀረውን ቁጥር የምንይዘው ግን ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ መብት ነጻነት እኩልነት ፍትሕ ስንታገል ወይም ትችላላቹህ ተብለው በሕግ ከተፈቀደላቸው በኋላ ብሔሬ ለሚሉት መብት ነጻነት እኩልነት ሲሉ አገዛዙን ሲታገሉ ትግላችን ወንጀል ተደርጎብን የታሰርን ነን፡፡

በየ መደቡን ዞን ከመግባታችን በፊት በንባብና በቃል መብትና ግዴታቹህ ነው ያሉትን ከማስጠንቀቂያ ጋር በተለያዩ ኃላፊዎች ተነገረን ይህ ግዴታ የተባለው የእስር ቤቱ ሕግ ወይም ደንብ ግን በቀጥታ ከሕገ መንግሥታቸው ጋር የሚቃረን ነው፡፡  ወደ የዞናችን አስገቡን ከዚያም ክፍል እስክንመደብ ድረስ አንድ ጥግ ላይ አቆዩን፡፡ እኔ የታሰርኩት ዞን 2 በሚባለው የቅሊንጦ እስር ቤት ነበር፡፡ ዞን ሁለት ውስጥ ብዙዎቹና ዋና ዋናዎቹ የነጻነት የእኩልነት የመብት ታጋዮች የሚገኙበት እስር ቤት ነው፡፡ ይሄም በመሆኑ ልሠራው ለፈለኩት ሥራ በመመቸቱ ዞን 2 በመግባቴ እራሴን እንደ ዕድለኛ ቆጠርኩ፡፡ ዐሥር ሰዓት ላይ ዞን 2 ውስጥ ካሉት ከስምንቱ አዳራሾች ውስጥ ከአንዱ አስገቡኝና ባዶ ሲሚንቶ ወለል ላይ ጣሉኝ፡፡ አልጋ የምታገኘው ታሳሪ ሲለቀቅ ተራህን ጠብቀህ ነው አሉኝ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ሰዓቱ ደረሰ መሰል ቆጠራ እያደረጉ ታሳሪው በየ አዳራሹ ገባና እላያችን ላይ ተዘጋብን፡፡ በማግስቱ ጠዋት 12 ሰዓት ላይ ተከፈተ ከ30 ደቂቃ በኋላ ቆጠራ ተደረገ ከቀትር በኋላ 1 ለ 10 የሚባል ውይይት አድርጉ ተባለና ለዐሥራ አምስት ደቂቃ ያህል በየክፍላችን ተዘጋብንና ተወያዩ ተባለ፡፡ ይሄ እንግዲህ የዘወትር አሠራራቸው ነው፡፡

በዚሁ ቀን ብዙዎችን የመብትና የፍትሕ ታጋዮች አገኘሁ የማላውቃቸውንም በአሸባሪነት ተወንጅለው ከታሰሩት የዞን ዘጠኙ በፈቃዱ ኃይሉ ካሉበት ድረስ እየወሰደ አስተዋወቀኝ በዚሁ አጋጣሚ ምስጋናዬ ይድረሰው፡፡ በፈቃዱ ካስተዋወቀኝ ወገኖች ውስጥ ሦስቱ በተከሰስኩበት ጽሑፍ ሳቢያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ብጥብጥ አንሥተዋል፣ ቦምብ አፈንድተዋል፣ በር መስኮት ሰባብረዋል፣ የመማር የማስተማር ሒደቱን ለቀናት አስተጓጉለዋል ወዘተ. ተብለው የታሠሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ላናግራቸው እንደምፈልግ ነገርኳቸው እሽታቸውን ገለጹልኝ፡፡ ጥግ ከያዝን በኋላም መቅድም እንዲሆነኝ በማሰብ የኦሮሞ ሕዝብ በሀገራችን ታሪክ ከዐፄ ሠርፀ ድንግል 1571ዓ.ም. ላይ በባሕረ ምድር (ባዕዳን ኤርትራ ባሏት) ወራሪውን የቱርክ ጦርና ሀገሩን ከድቶ ከቱርክ ጋራ አብሮ የነበረውን የባሕረ ምድር ገዥ ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅን ከመደምሰስ ጀምሮ በየዘመኑ የኦሮሞ ብሔረሰብ ለሀገሩ ነጻነትና ሉዓላዊነት ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ሆኖ የከፈለውን መሥዋዕትነት የነበረውን ጉልህና ጠቃሚ ሚና እየጠቃቀስኩ ለማስረዳት ሞከርኩ ይሄንን ማንሣት ግድ የሆነብኝ የጥፋት ኃይሎች ልጆቹን ኦሮሚያ የኢትዮጵያ ግዛት አይደለችም ዐፄ ምኒልክ ናቸው የቀላቀሉት እያሉ የደንቆሮ ስብከታቸውን እንደሚሰብኳቸው ስለማውቅ ነው፡፡ አያይዠም የኢትዮጵያ ሕዝብ (ብሔረሰቦች) በረጅሙ የሀገሪቱ ታሪክ በፖለቲካዊ (እምነተ-አስተዳደራዊ) እና ማኅበራዊ መስተጋብር እንዴት ሆኖ እንደተቀያየጠ እንደተዋሐደ ይሄንንም እያንዳንዳችን የእናት አባታችንን የዘር ኃረግ ስንቆጥር የምንረዳው መሆኑን የመረጃ እጥረት ካላጋጠመን በስተቀር ከዚህ የወጣ ዜጋ እንደማይኖርና አሁን በዛሬ ዘመን ላይ እኔ አማራ ነኝ እኔ ኦሮሞ ነኝ እኔ ትግሬ ነኝ ወዘተ. ማለት ከተጨባጩ እና መሬት ላይ ካለው ሐቅ የራቀ መሆኑን እውነቱን አለመገንዘብ እንደሆነ ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በዝርዝር የተጻፈውን እዚህ ላይ ያንብቡ፡፡

ልጆቹ ግን ያው በዚህ እኩይ አገዛዝና በሌሎቹም የጥፋት ኃይሎች ተውልዱ ሆን ተብሎ ኢትዮጵያዊነቱን ማንነቱን እንዲጠላ እንዲክድ እንዳያውቅ አማራን በጠላትነት እንዲመለከት የተጠመዘዘ የጥፋት ኃይሎች አጣመው የቃኙት ያሳደጉት አተያዩ የተዛባና ጠባብ እንዲሆን በጠላትነት ስሜት የተሞላ እንዲሆን ስለተደረገ ለእነዚህ ለጠቀስኳቸው የሀገራችንና የሕዝቧ ታሪክ እንግዳና አዲስ በመሆናቸው ባልኩት ነገር ላይ ግርምትና ጥርጣሬ የተቀላቀለበት ስሜት ጎልቶ ይነበብባቸው ነበር፡፡ ከሞላ ጎደል ብንግባባም በብዙው ጉዳይ ግን ልንስማማ አልቻልንም ነበር፡፡ ወያኔ እንኳንና የሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነን የአማራን ተወላጆች እራሱ አማራነታቸውን ማንነታቸውን እንዲጠሉ እንዲክዱ ማድረግ የቻለበት ዘመን ስለሆነ ብዙም አልገረመኝም፡፡ በዚህ አንድ ጥግ ይዘን ባደረግነው ውይይት አብርሃ ደስታ፣ በፈቃዱ ኃይሉና ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ነበሩ፡፡ ይሄንን ውይይት ቅዳሜና እሑድ ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ሌሎች ወንድሞችን ማለትም ከሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ጅብሪልን፣ በግንቦት ሰባት አባልነት ተጠርጥረው ከተያዙት ሁለቱን ጨምረን ስብስቡ ከብሔረሰብ ተዋጽኦ አማራ ኦሮሞ ትግሬ ጉራጌ ከፍቾና ስልጤ የተወከሉበት ከፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ መኢአድ አረናና ሌሎችም የተወከሉበትን የዐሥሮሽ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ያዝን፡፡

ቅዳሜ ለት የቀጠሯችን ሰዓት ከመድረሱ በፊት አንድ ወንድም መጥቶ አስደንጋጭ ነገር ሹክ አለኝ፡፡ የነገረኝ ነገር ከዚህ ቀን በፊት ጥግ ይዘን በተወያየንባቸው ጊዜያት አብሮን ሲወያይ የነበረው አንዱ ልጅ የወያኔ ሰላይ መሆኑን ነበር የነገረኝ፡፡ ቀጥ ብየ ወደ ዞን ዘጠኙ በፈቃዱ ሔድኩ፡፡ ከአጥናፉ ብርሃኔ (ከዞን ዘጠኝ ተከሳሾች አንዱ) ጋራ ምሳ እየበሉ ነበር፡፡ የልጁን ስም ጠራሁለትና ስለሱ የሚያውቀውን እንዲነግረኝ ጠየኩት “የመኢአድ አባል መሆኑን ነግሮኛል የተከሰሰው በግንቦት 7 አባልነት ነው ከማዕከላዊ ጀምሮ አብሮን ነበር፡፡ በተረፈ ያውቀው ሰላይ ነውም ይባላል አለኝ” ታዲያ ይሄንን ልትነግረኝ የሚገባው አሁን ነበር? ስል ጠየኩት “አይ! እኔ በበኩሌ ከዚህ ከተከሰስኩበት ክስ የተለየ ክስ ሊያመጡ ስለማይችሉ ይሄ አላሳሰበኝም እንደራሴ አይቸው ይሆናል፡፡ ምን የሚያሳስብ የነገርከው ነገር አለ?” ብሎ ጠየቀኝ በአጋጣሚ አለመኖሩ እንጅ ኖሮኝ ቢሆን ኖሮ ግን ልጁን ባለማወቄ ምክንያት ክፍተቱ ሊፈጠር ይችል የነበረበት ዕድል ሰፊ እንደነበር ገልጨ ለሕዝብ “ወያኔ የሀገርና የሕዝብ ጠላት ነው በሁሉም አማራጮች ማጥፋት አለብን” ብየ በግልጽ ከጻፍኩትና በግልጽ ከሚታወቀው አቋሜ የተለየና የከበደ ነገር እንደሌለኝ ገለጽኩለትና አሁን ግን ጉዳዩ ይሄ እንዳልሆነ ሲጀመርም ሰውየውን ሊያስተዋውቀኝ ይገባ እንዳልነበረ ነገርኩት፡፡ እሱም “ግን እሱን ሰው እኔ ነኝ ያስተዋወኩህ?” አለኝ እንደሆነ ገለጽኩለት ያስተዋወቀኝ እንደማይመስለው ነገረኝና “አይ እኔም ሲባል ሰማሁ እንጂ እውነት ላይሆን ይችላል” ሲል ጓደኛው አጥናፉ ብርሃኔ ቀበል አደረገና ልጁ ሦስት ወራት የሆቴል እየከፈሉ ስለላ እንዳሰለሉት በኋላ ግን የደበከን ነገር አለ ብለው አሁንም አልተለወጥክም የግንቦት 7 ታጋይ ነህ ብለው መልሰው እንዳሰሩት እንደነገረው ገለጸልን “አሁን አጥናፉ በምናገርገው ውይይቶች ለምን እንደማይሳተፍና መገለልን እንደሚመርጥ ገባኝ፡፡ በምወጣበት ቀን ጠይቄው ሲመልስልኝ “እኔ ነፍጠኛ ምናምን የሚለው እውጭ በፌስቡክ የሰለቸኝ ነገር ስለሆነ ነው ብሎኝ መሰልቸት እንደሌለበት ይሄ ለነሱ ድል መሆኑን በመሆኑም መጋፈጥ እንደሚገባ የሚያወሩት ነገር በእውነት ላይ ያልተመሠረተና የወያኔ መርዘኛ ፈጠራ የታከለበት በመሆኑ ዝም ቢባል በቆይታ እንደ እውነት ተቆጥሮ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል በዚህም ምክንያት መሰልቸትና በዝምታ መመልከት እንደማይገባ እውነታው የዚህ ግልባጭ መሆኑ እየነገርኩት ሳልቋጭለት ነበር ተጠርቸ የወጣሁት” እናም እኔ በፈቃዱና አጥናፉ ሰላይ በተባለው ሰው ጉዳይ እያወራን እንዳለ እራሱ ልጁ መጣና አብሮን ተቀመጠ፡፡

እኔ ንዴት አጡፎኛል አልቻልኩምና ተነሥቸ እየወጣሁ እንዳለ ልጁ “የውይይቱ ሰዓት እኮ ደርሷል” አለ ወደእነ በፈቃዱ እየተመለከትኩ እንደማልካፈልና እነሱ እንዲወያዩ ገልጨ ትቻቸው ወጣሁና ወደ እኛው ክፍል ገባሁ፡፡ ወዲያው ልጁ በተደናገጠ ስሜት እንደተወረረ መጣና ምን እንደሆንኩ ለምን እንደማልሳተፍ ጠየቀኝ እኔም ቆጣ ብየ አልፈልግም አልኩ እኮ! እናንተ ተወያዩ አልኩት፡፡ ወጥቶ ሄደ እንደገና ተመልሶ መጣ ያኔ እኔ ከአንድ ወንድም ጋር ቆሜ ነበር በር አካባቢ ቆሞ እየጠበቅንህ ነው አለኝ፡፡ አሁንም እንደማልመጣ ነገርኩት ተመልሶ ሄደ፡፡ ወዲያውም በፈቃዱ መጣ አሁንም ደግሜ ስሕተት እንደሠራ ነገርኩት እሱም “እኔ ግን ልጁን እኔ ያስተዋወኩህ አይመስለኝም እኔ ያስተዋወኩህ” ብሎ ያስተዋወቀኝን ሰዎች ሲቆጥር ይሄንን ልጅ ማን እንዳስተዋወቀኝ ታወሰኝ ይሄንን ልጅ ያስተዋወቀኝ በፈቃዱ ያስተዋወቀኝ ጅብሪል የሚባል ልጅ ነበር፡፡ ኦው በጣም ይቅርታ! በፈቃዱ አሁን ልጁን ማን እንዳስተዋወቀኝ አስታወስኩ ጅብሪል ነበር ያስተዋወቀኝ ቢሆንም ግን አንተ ይሄ መረጃ ካለህ ልትነግረኝ ይገባህ ነበር እያልኩ ስወቅሰው አብሮን ያለው ወንድም “ልጁ አሁን መጥቶ ከኔጋር ስላየህ እኔ የነገርኩህ ነው የሚመስለው እኔ ግን ልጁንም ምንነቱንም አላውቀውም ባውቀው ኖሮ ምንም አልነበረም አንዳንዴ ወያኔ ሆን ብሎ ማጥቃት የፈለጋቸውን ሰዎችም ሳይሆኑ እንዲህ እያለ ስለሚያስወራ በእርግጠኝነት የምታውቁት ነገር ከሌለ ውሸትም ሊሆን ይችላል” ሲል አይ በቃ! እሽ እሔዳለሁ ብየ ወደ ውይይቱ ሔድን ሁሉም ነበሩ እየጠበቁን ነበር ምንም ነገር እንዳላወቀ እያስመሰልኩ በቀድሞው ግንኙነታችን ለመወያየት ወሰንኩ፡፡

የመወያያ ነጥቦችን አውጥተውት ነበር ያገኘኋቸው በፈቃዱ አነበበልን፡፡ ውይይታችን በሁለቱም ቀናት ባለመቋጨቱ ከውይይቱ ስንወጣም ጥግ እየያዝን ወይም በእስር ቤቱቶቹ ተከቦ መሀል ላይ ያለውን አነስተኛ ሜዳ እየዞርን ሁላችንም ብንሆን ሊያስነቃብን ስለሚችል አራትም አምስትም እየሆንን መወያየት መከራከሩን እንቀጥል ነበር፡፡

የእነዚህን ውይይትና ክርክር ዋና ዋና ነገር ብቻ የሐሳብ ቅደም ተከተሉን እንጅ የመቸቱን ቅደም ተከተል እንብዛም ሳልጠብቅ እንዲህ አቅርቤላቹሀለሁ፡፡

የሚገርማቹህ የገዛ ሕገ መንግሥታቸውን በሚጻረር መልኩ ቅሊንጦ ውስጥ ፖለቲካዊ (እምነተ-አሥተዳደራዊ) ውይይት ማድረግ፣ ፖለቲካዊ መጽሐፍ ጋዜጣ መጽሔት ማስገባትና  ማንበብ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ለከባድና ኢሰብአዊ ቅጣት ይዳርጋል፡፡ የተዳረጉም አሉ ዐይን ጥርስ ሳይባል እንደ እባብ ያስቀጠቅጣል ለጨለማ ቤት እስር ይዳርጋል፡፡

ቅዳሜና እሑድ ከዚያም ውጭ ባደረግነው ውይይት የመወያያ ርእሶቻችን የነበሩት፡-

  1. በኢትዮጵያ ጭቆና ነበረ ወይስ አልነበረም?
  2. ጭቆና ከነበረስ ጭቆናው የብሔር፣ የመደብ ወይስ የሌላ?
  3. ለኢትዮጵያ አዋጪ የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት የትኛው ነው አሐዳዊ? ፌደራላዊ? ወይስ ሌላ?
  4. ፌደራላዊው የመንግሥት ሥርዓት ነው ካልንስ አወቃቀሩ ምንን መሠረት ያድርግ? ብሔረሰብን? መልክአምድራዊ አቀማመጥንና ታሪክን? ወይስ ሌላ?
  5. የሐገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ካልሆነም የፌደራላዊው መንግሥት የሥራ ቋንቋ ምን ይሁን? አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሱማሊኛ፣ ከንባትኛ፣ ካሉን ብሔረሰቦች ያንዱ ወይስ ሌላ? በሚሉ ነጥቦች ጉዳይ ላይ ነበር ያደረግነው፡፡

እናም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ነጥቦች ላይ አብዛኞቻችን የመሰለንንና የምናምንበትን ተናገርን፡፡ ለመናገር ከፈቀድነው ውስጥ ሦስቱ የኦሮሞ ተወላጆች የዩኒቨርስቲ 4ኛ ዓመት ተማሪዎች ጭቆናው በጣም ነበረ ጭቆናውም የብሔር ነበረ በማለት በጥፋት ኃይሎች ተዛብቶና ፈጠራ ታክሎበት የሚወራውን በዐፄ ምኒልክ ዳግማዊ እንደ መንግሥት የሀገርንና የሕዝቧን ህልውና ደኅንነትና ጥቅም ከሀገር ውስጥና ውጭ የጥፋት ኃይሎች የመጠበቅ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲሉ ሰላማዊ አማራጮችን ለመጠቀም ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገው ውድቅ ስላደረጉባቸው አማራጭ አጥተው በወቅቱ እንቢ ባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች የወሰዱትን የኃይል እርምጃ እና በሌሎች ገዥዎች የተፈጸመውን በታሪካችን የምናውቃቸውን በአንዳንድ የኦሮሞ ተወላጆች ልኂቃን የተፈጸመውን በደል እየጠቀሱ እነኝህ ሰዎች ያ ግፍ የተፈጸመባቸው ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ነው ብለው ደመደሙ፡፡ በደል ጭቆና አድራሾችም አማሮች በመሆናቸው ጭቆናው የብሔር ነበር አሉ፡፡ ዛሬም ቢሆን በሀገራችን ተቀምጠው ለዚህ መንግሥት እያስጨረሱን ያሉት አማሮች ናቸው አሉ፡፡

ቋንቋንም በተመለከተ ሲናገሩ ኦሮሞ ከብሔረሰቦች አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ስለሚይዝ እስከአሁንም ብሔራዊ ቋንቋ መሆን የነበረበት አፋን ኦሮሞ ነበር በብሔር ጭቆናው ምክንያት ይሄ ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለሆነም ብዙ ተበድለናል እኛ የምንፈልገው ነጻ የሆነች ኦሮሚያን ነው እንገነጠላለን አሉ፡፡

እኔም ድምዳሜያቸውና ብዙ ነገራቸው ግራ አጋብቶኝ ነበርና እንደጨረሱ እንዲህ ስል ጥያቄና ማረሚያ አቀረብኩ፡-

ዐፄ ምንሊክ የዘመቱት እንደ መንግሥት ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሀገርንና የሕዝብን አንድነትና ህልውና ለማስጠበቅ ለመንግሥቷም አልገብርም ያለውን ሀገሪቱንም ለመክፈል የሚሻውን ለማስገበርና ሀገሪቱንም ከመከፈል ለመታደግ ለማዳን እንጂ ኦሮሞን ላጥፋ በኦሮሞ ላይ ልዝመት ብለው እንዳልነበረ የሚያሳየው የዛ ጦር አበጋዝ (ዋና ኃላፊ) ራስ ጎበና ዳጬና ሌሎችም የኦሮሞ ተወላጆች ያሉበት መሆኑ ከሠራዊቱም ከፊሉ የኦሮሞ ተወላጅ መሆኑ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ከእናንተ መሀል አንዱ በዐፄምኒልክ ቦታ ቢሆን ከዚህ የተለየ ሥራ ሊሠራ ይችል ነበረ ወይ? እንቢ ባለ ባመፀ ወገን ላይ ሲዘምቱም እሳቸው የመጀመሪያ አይደሉም፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስን የወሰድን እንደሆነ ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ አንድነትና ሕልውና እናንተ በዐፄ ምኒልክ ተፈጸመብን ከምትሉት ፈጠራ በላይ እንቢ ብለው ባስቸገራቸው ሕልማቸውን ሊያሰናክሉ ሊያጨናጉሉ እጅግ የተፈታተኗቸውን ሕዝብ እያሳሳቱ ያስቸገሯቸውን ደብተራዎችና ሌሎችንም መቀጣጫ እንዲሆኑ በማሰብ በእልፍኝ በአዳራሽ ጠቅጥቀው ሞልተው ድኝ አርከፍክፈው እንዳሉ በእሳት ከማቃጠል አንሥቶ እጅ እጃቸውን እስከመቁረጥ ድረስ በተለያዩ መሳፍንት ተከፋፍሎ የሀገሪቱን ህልውና ወይም የግዛት አንድነት አደጋ ላይ ጥሎ በነበረው የአማራ ሕዝብ ላይ ፈጽመዋል ለሀገር ጠቃሚ ርእያቸውን ተረድቶ ሰላማዊ ጥያቄውን የሚቀበል ገዥ ባላባት ወይም መሳፍንት ስላልነበሩ ርእያቸውን ለማስፈጸም ይሄንን ከማድረግ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውምና፡፡ እናንተ የምትሉት ከዚህ ያነሰ እንጅ የከፋ አይደለም፡፡ እንደ የሰው ልጅ እንደ ዜጋም በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ ሰቆቃ የሚያሳስባቹህ ከሆነ ይሄኛው እንዴት አልተሰማቹህም? ሩቅ ሳንሔድ አሁን በኛ ዘመን ላይ የኦነግ ታጣቂዎች በወለጋ በአርባጉጉ በአቦምሳ በበደኖና በሌሎችም አካባቢዎች ነፍስ የማያውቁ ሕፃናትን ጭምር ምንም በደል ሳይኖርባቸው አማራ በመሆናቸው ብቻ እንደ በግ እያረዱ እንደ ጎመን እየቀረደዱ ገደል እየወረወሩ ሲጥሉ ምነው አልተሰማቹህ? እናንተ ተፈጽሟል ከምትሉትና ከዚህ የትኛው ይከፋል? ከዘር ማጥፋት ውጭስ ምን ዓላማና አሳማኝ ምክንያት ነበረው?

እንዲህ አደረጉ የምትሏቸው ዐፄ ምኒልክ ግን አማራጭ ታጥቶ በተገባበት ጦርነት ምክንያት በዘመቱባቸው የጠቀሳቹሀቸውና ሌሎች አካባቢዎች ወላጆቻቸውን በጦርነቱ ያጡትን ሕፃናት የጦር ኃላፊዎቹ አምጥተው እንደየልጆቻቸው አድርገው የወቅቱን ትምህርት እያስተማሩ እንዲያሳድጓቸውና ለቁም ነገር እንዲያበቋቸው ነበር ያደረጉት፡፡ አባ መላ ወይም ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ባልቻ አባ ነብሶና ሌሎችም የኦሮሞና የሌሎች ብሔሮች የወቅቱ ባለሥልጣናት በዚህ መንገድ የተገኙ እንደነበሩ በሚገባ ታውቁታላቹህ፡፡ በወቅቱ የነበረው እውነት ይሄ ነው፡፡ እናንተ የምታወሩት የፈጠራ ወሬ አይደለም አንድም ዓይነት የጽሑፍም ይሁን ሌላ መረጃ እንደሌለውም ታውቃላቹህ፡፡ የጥፋት ኃይሎች ለምን የሌለ ነገር ፈጥረው እውነት ለማስመሰል እንደሚጥሩ ታውቃላቹህ? በ21ኛው በቶ ክፍለዘመን ያለ ሰው ይፈጽመዋል ተብሎ ፈጽሞ የማይታሰብ ኢሰብአዊ የሆነ የአውሬ የአረመኔ ሥራ ስለፈጸሙ ያንን ለመሸፋፈን፣ ወደፊትም የአውሬነት ተፈጥሯቸው እንዲያደርጉት የሚያስገድዳቸውን ኢሰብአዊ ድርጊት ለመፈጸም ሰበብ መፍጠራቸውና ሕዝብን አስቆጥተው ከጎናቸው እንዲሰለፍ ለማድረግ ነው፡፡

እኛ እንደነሱ አይደለንም የምትሉ ከሆነ በግልጽ ተቃወሟቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ወንጀል የፈጸሙ የጥፋት ኃይሎች ተዋንያንን ለፍርድ ለማቅረብ እየተንቀሳቀሳቹህ ላላቹህ ወገኖች የማሳስበው ነገር ቢኖር በአውሮፓና በአሜሪካ ሀገራት እንደዚህ ዓይነቱን የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን የፈጸሙ አሸባሪዎች ድርጊቱ አንዲፈጸም አመራር የሰጡትን የኦነግ አመራሮችንና እንደነ ታምራት ላይኔ ያሉ ተባባሪ የወያኔ ባለሥልጣናትን አሁንም ያንን አረመኔያዊ ድርጊት ለመፈጸም ሕዝብን እየቀሰቀሱ ያሉ እንደነ ጁሀር ያሉ የጥፋት ኃይሎች ተዋንያንን በእነሱ ዙሪያ ከበቂ በላይ ማስረጃ ያለ በመሆኑ ይሄንን ማስረጃ በማጠናቀር በያሉበት የአውሮፓና አሜሪካ ሀገራት ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ ከጥፋት ተልእኳቸው እንዲገቱ በማድረግ የዜግነት ግዴታቹህንና የታሪክ ኃላፊነታቹህን እንድትወጡ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ይሔ ጉዳይ ነገ ዛሬ የሚባልበት ጉዳይ አይደለም፡፡

ሌሎች የጠቀሳቹሀቸው እናንተ የኦሮሞ ልጆች ያላቹሀቸው ኢትዮጵያዊያንም ያ በደልና ግፍ የተፈጸመባቸው ኦሮሞ በመሆናቸው ነው ማለታቹህ በጣም የተሳሳተና አደገኛም ድምዳሜ ነው፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ ሲጀመርም ለዚያ ሥልጣንና ኃላፊነት ባልበቁም ነበር፡፡ እነሱ ኦሮሞ በመሆናቸው ያ በደልና ግፍ የተፈጸመባቸው ከሆነ “እኔም የአማራ ተወላጆች ሆነው የበለጠ ግፍና በደል የተፈጸመባቸውን ግፍና በደል እየጠቀስኩ” እነዚህስ ምን ስለሆኑ ነበር ያ ግፍና በደል የተፈጸመባቸው? ስል ጠየኩ፡፡ ይህ ግፍና በደል ያላቹህት በአማራ ተወላጆችም ላይ ሳይደርስ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ብቻ ደርሶ ቢሆን ኖሮ ይሄንን ብትሉ ያስኬዳቹህ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲያውም ግፍና በደል ከደረሰባቸው የሚበዙቱ አማሮች ናቸው፡፡ ሀቁ ይሄ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ተብሎ ነው ግፍና በደል ጨቋኙ አማራ በኦሮሞላይ የፈጸመው ነው ልትሉ የምትችሉት? አሁንም በሀገራችን ተቀምጠው በወያኔ እያስጨረሱን ያሉት አማሮች ናቸው የምትሉትስ የወያኔ ቅጥረኛ ሆነው የኦሮሞ ተወላጆችን እየገደሉ እያሰሩ እያሳደዱ ያሉት የኦሕዲድ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች አማሮች ስለሆኑ ነው ወይ ይሄንን ግፍ እየፈጸሙት ያለው? በጣም የሚያሳዝንና ማስተዋል የጎደለው ድምዳሜ ነው፡፡

ከድሮ ጀምሮ ያለውን ብናይ ምንም እንኳን የተናገረው ነገር እጅግ የተሳሳተ ቢሆንም “የብሔር ጭቆና አለ! የኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠራው ይሄ ይሄ ባሕል የማን ነው? የአማራና የትግሬ አይደለምን? የብሔር እኩልነት ይስፈን!” እያለ ጥያቄውን ያነሣውና ያራገበው ለወያኔና ለሌሎችም የጥፋት ኃይሎች መሠረት የሆነው የአማራ ተወላጁ ዋለልኝ መኮንን አይደለም ወይ? እኔ ይሄንን የዋለልኝ አስተሳሰብ የምኮንንበት ምክንያት ዋለልኝ ትግሬን ከጨመረ ለምን ሌሎቹህ እንደተወ ሊገባኝ ስላልቻለ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ታሪክ ከትግሬ ይልቅ የአገው ብሔረሰብ ጉልህ አሻራ አለውና የማስተዋል ችሎታው ደካማ ከመሆኑ የተነሣ ካልሆነ በስተቀር የሌሎቹም አሻራ እንዲሁ በኢትዮጵያ ባሕል ሥልጣኔ ማንነት ነጻነት እሴት ላይ ጉልህ ነው፡፡ እንዲያውም ካለስ ትግርኛ የመንግሥት ቋንቋ ሆኖ አያውቅም ትግሬ በነበሩት ንጉሥ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመንም እንኳ ንጉሡ ሲሠሩ የነበሩት በአማርኛ ነበር፡፡ ለምን? ተብለው ተጠይቀውም ሲመልሱ “አማርኛ የአክሱም ነገሥታት ቋንቋ ነው ቤተመንግሥት ቤቱ ነው እኔ ላስወጣው አልችልም” ነበር ያሉት ኦሮምኛን የወሰድን እንደሆነ ግን ያውም በጎንደር ዘመን ለአጭር ጊዜም ቢሆን የመንግሥት ቋንቋ ለመሆን በቅቶ እንደነበር የታሪክ ምሁራን ይናገራሉና የተሻለ ተሳትፎ የነበራቸው እያሉ ትግሬ ብሎ ትግሬን ብቻ ጨምሮ ማቆሙ አግባብ አልነበረም፡፡ ከጨመረ ቢያንስ እነኝህን መጨመር ነበረበትና፡፡

ይህ እጅግ ብስለት የጎደለውና በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ የዋለልኝ አስተሳሰብ የተማሪዎችን ዐመፅ ቀስቅሶ ዐፄውን ለውድቀት ዳርጎ ገና ከጅምሩ የሀገሪቱን ውድና አንጋፋ መሪዎች ቅርጥፍ አድርጎ የበላውን ደርግን ለሚያህል ጭራቅና በተመሳሳይ ሰዓትም የበፊቱን የበረሀ አውሬ የዛሬውን አንባገነን ጭራቅ የወያኔን አገዛዝ ሌሎችንም የጥፋት ኃይሎች ፈጥሮብናልና ነው፡፡

ዋለልኝና ተከታዮቹ ሐሳባቸው ያልበሰለና እንጭጭ መሆኑን ሳይረዱ ይሄው አሁን ድረስ ላለንበት ውጥንቅጥ እየተወሳሰበ ለሚሄድ ችግር ዳርገውናል፡፡ በእኔ እምነት በእኔ እምነት ብቻም ሳይሆን መሬት ላይ ያለው እውነታ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀው ባሕል፣ ተጨባጭና ተጨባጭ ያልሆኑ ቅርሶች (tangible and intangible Heritages) ፣ እሴቶች ሁሉ የአማራ ብቻ አይደሉም፡፡ እነ ዋለልኝ ሊረዱት ያልቻሉት ይሄንን ሀቅ ነው፡፡ ከአማራ የወጡ ገዥዎች መንግሥትን የመምራት ሚና እንደመጫወታቸው መጠን የኢትዮጵያ ባሕል ቅርስ እሴቶች ተብሎ የሚታወቀውን የማንነት መገለጫዎቻችንን አቀናብረው አቀናጅተው አሰናድተው ይሆናል፡፡ ይሄም ማለት የተሻለ አስተሳሰብ ባሕል እሴት ካለው ብሔረሰብ እየወሰዱ የሀገሪቱ አድርገዋል፡፡ የከፋውንና ኋላ ቀር የሆነውን የማይጠቅመውን ልማድ እያስቀሩ በተሻለው አስተሳሰብ ባሕል እሴት ለመተካት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ የአንድ መንግሥት ወይም አስተዳደር ኃላፊነትና ግዴታም ነው ለምሳሌ ያህል አንዱን ልጥቀስ ዕቁብ ወይም ቁቤ ዛሬ ላይ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለመደና ያለ ባሕላችን ነው፡፡ የሁላችንም ከመሆኑ በፊት ግን ዕቁብ የጉራጌ ባሕል ነበር፡፡ ልማዱ ባሕሉ አስተሳሰቡ የሠለጠነ የበሰለ ጠቃሚም ስለሆነ ከጉራጌ ተወስዶ የኢትዮጵያ ሆነ፡፡ በዚሁ መልኩ ጠቃሚና የላቁ ባሕላዊ አስተሳሰቦችና ልማዶች ከየብሔረሰቡ እየተለቀሙ ተውጣተው ነው የኢትዮጵያ ተብሎ የሚታወቀውን ባሕል አስተሳሰብና እሴቶችን ሊቀርጹ ሊገነቡ የቻሉት፡፡ አሁን ላይ ሲታዩ የአንድ ብሔረሰብ ሊመስሉ ይችላሉ ነገር ግን በፍጹም የአንድ ብሔረሰብ ባሕል ማንነት እሴት ብቻ አይደሉም፡፡ በዚህች ሀገር ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ በዚህች ሀገር እንደመኖራቸው ለነጻነቷ መሥዋዕትነት ከመክፈል ጀምሮ ለዚህች ሀገር ማንነት እስከ ሥልጣኔዋ ድረስ አስተዋጽኦ ላያደርጉ የሚችሉበት ምንም ምክንያት አልነበረም፡፡

ከዚህ ውጭ ግን የሁሉም ብሔረሰቦች ሁሉም እሴቶች እኩል የእውቅና ዕድል መሰጠት ነበረበት ከሆነ ጥያቄያቸው ይሄ ጥያቄ የመብትና የፍትሕ ሳይሆን የሥነ-ሥርዓትና የፍላጎት ነው የሚሆነው ይሄ ደግሞ የሚገናኘው በቀጥታ ከአቅም ጋራ ነው እንጅ ከፍትሕና ከእኩልነት ጋር አይደለም ጥያቄውም አመክንዮአዊ አይደለም ነገሮች እራሳቸውን የሚያስተናግዱበትን ተለምዷዊና ተፈጥሯዊ አሠራርም ያገናዘበ አይደለም፡፡ ይሄንንም ጥያቄ እንኳን እኛ ከሀብታሞቹ አንዳቸውም አልመለሱም፡፡ በሁሉም ሀገሮች በተለያዩ ምክንያቶች ጎልተው የሚወጡ የተወሰኑ ብሔረሰቦች እሴቶች መኖራቸው ግድ ሆኖ ኖሯል፡፡ ይሄንን ስል የዋለልኝና የተከታዮቹ አስተሳሰብ ምን ያህል ብላሽ እንደሆነ ለመግለጽ እንጅ ፈጽሞ በደል አልነበረም ለማለት ግን አይደለም፡፡ ሀገራችን ያለችው በዚህቺው ዓለም ላይ እንጅ በገነት አይደለምና እኛም ሰዎች እንጅ መላእክት አይደለንምና የዚህች ዓለም አካል እንደመሆናችን የዚህችን ኢፍትሐዊ ዓለም ትኩሳት ሳንጋራ አላቀረንም፡፡ ልንቀር የምንችልበት ዕድልም የለም፡፡ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ የሚታዩትና መታየት ያለባቸው ከዚሁ አንጻር ነው፡፡ እስከማውቀው ድረስ ጎልተው የተዋወቁ እሴቶች ይኖሩ ይሆናል እንጅ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የማንም ብሔረሰብ እሴት የኢትዮጵያ አይደለም ተብሎ አያውቅም፡፡ የቀረው የአቅም ጉዳይ ነው የተሻለና ጠቃሚ የሆነው ግን አስቀድሜ እንዳልኩት አናውቀውም እንጅ በራሱ ጊዜና ባለው የተሸለ አቅም እየተመረጠ የሐገሪቱ ሆኗል፡፡ በተረፈ እንዲህ ብለው ማሰባቸው ራሱ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ እንዲህ ብለን እንድናስብ የሚያደርገን አለመብሰላችን ነው እንጭጭነታችን ነው ጠልቀን አስፍተን ማሰብ አለመቻላችን ነው ድንቁርናችን ነው፡፡ የበሰለ የላቀ የተሸለ ሆኖ እስከተገኘ ጊዜ ድረስ ከአማራ አይደለም ባሕር ተሻግረንም ከባዕዳን እናመጣለን አምጥተናል ሰጥተናልም፡፡ ይሄንን የሚኮንን ስር የሰደደ ድንቁርና ያለበት ብቻ ነው፡፡

በመሆኑም ዋለልኝና ተከታዮቹ እንዲህ ብለው ጥልቀት በጎደለው አተያይ መንቀፋቸው እጅግ ስሕተት ነበር፡፡ እኔ ለነገሩ እንኳን የነ ዋለልኝ ይቅርና የሁለቱ ጄኔራሎች የመንግሥቱ ንዋይና የገርማሜ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንኳን እንዴት ያቃጥለኛል መሰላቹህ፡፡ የርሸናን የደም መፋሰስ ምዕራፍ የከፈቱት እነሱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ያ ድርጊታቸው ብስለት ትዕግሥት አርቆ ማሰብ የጎደለው ነበርና፡፡ ልዑሉ በአቋማቸው ተስማምቶ አጋራቸው መሆኑን ካረጋገጡ ያንን ድርጊት ከማድረግ ተቆጥበው ጥቂት ቢታገሱ የሸመገሉት ንጉሡ ይሞቱና የተመኙትን ሁሉ ከልዑሉ ጋር ማድረግ የሚችሉበት ዕድል ክፍት ሆኖ እያለ ትዕግሥት በማጣት ያንን ስሕተት በመፈጸማቸው ለደርግ 62ቱን የሀገር ሀብት አንገፋ ባለሥልጣናት ለመረሸኑ ጥሩ ትምህርት ትተውለት በማለፋቸው፡፡

ጥቂት ቢታገሱ ኖሮ ግን ዛሬ ድረስ ምናልባትም ወደፊትም ለተወሳሰበ ችግር ላይ የጣለንን የፖለቲካ (የእምነተ-አሥተዳደር) ቀውስ ባልተከሰተም ነበር፡፡ በብዙ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት በነበራቸው የአውሮፓ ሀገራት እንደሆነው ሁሉ ዘመኑ የጠየቀው የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት ለውጥ ሰላማዊ ሽግግር በሀገራችንም ማየት በቻልንና ዛሬ የት በደረስን ነበር፡፡

ስለሆነም ያላቹህት ሁሉ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው አንድ የቤት ሥራ ልስጣቹህ ካላቹህበት የጠበበና አንድ አቅጣጫ ብቻ ከሚመለከተው አስተሳሰባቹህ ውጡና ሰፋ ባለ አተያይ ነገሮችን ለመመልከት ሞክሩ፡፡ እንዳየኋቹህ ከሆነ ብስለት (maturity) እና አመክንዮ (logic) በጣም ያንሳቹሀል፡፡ በማንበብና አመለካከትን አስፍታቹህ ከተለያዩ አቅጣጫዎችን ነገሮችን በማየት ይሄንን ክፍተት ለመሙላት ሞክሩ፡፡ ነገሮችን እንዲህ በጣም በጠበበና በተሳሳተ አተያይ እንድታዩ የሚያደርጋቹህ ሁሉንም ነገር በዘር መነጽር ስለምታዩ ነው፡፡ ይሄንን መነጽር ከአይናቹህ አውልቃቹህ ጣሉ፡፡ ከጠባቡ ከብሔር ወይም ዘር ተኮር አስተሳሰብ ወጥታቹህ እንደ ኢትዮጵያዊ እንደ ሀገር ዜጋ ማሰብ ካልቻላቹህ እናንተም እድሉን ብታገኙ ከወያኔ የተለየ ነገር ልታደርጉ አትችሉም፡፡ ምናልባትም የከፋቹህ ልትሆኑ ትችላላቹህ የኦነግን አቋም አመለካከት ትልምና ምኞት በግልጽ ዐይተነዋል፡፡

የብሔረሰብን ጉዳይ የፖለቲካው ጅማሬና ፍጻሜ ያደረገ የትኛውም ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ ጉዳዩ ዓላማው ሁሉ ብሔሬ የሚለውን ብሔረሰብ ለመጥቀም ተጎድቷል ከሚለው ለመካስ እሱም በተራው በሌሎቹ ላይ ለመፈናጠጥ ለመፋነን ከመጣር የተለየ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው እኔ በብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲ ለሚመሠርቱ ግለሰቦች ንቀት የሚሰማኝ፡፡ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ደረጃ ያልበሰሉ ናቸው እንጭጮች ናቸው ጠባቦች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብና ለሀገር ትርጉም ያለው ሥራ ሊሠሩ የሚችሉትና ፋይዳ የሚኖራቸው ሥልጣን በያዙ ጊዜም ፍትሕና እኩልነትን ለማስፈን የታመኑ የተጉ ሊሆኑ የሚችሉት ጠባብ ከሆነው የብሔር ተኮር አስተሳሰብ ወጥተው እንደ ሰው አስፍተው ማሰብ ሲችሉና እንደ ዜጋም ሀገር የምትባልን ሥዕል በጭንቅላታቸው ውስጥ ማስፈር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ አስካልቻልን ጊዜ ድረስ የደም መፋሰስ በዚህች ሀገር ውስጥ ይቆማል ብላቹህ ተስፋ አታድርጉ፡፡

ቋንቋ ስላላቹህት ነገር እኔ በመርህ ደረጃ ኦሮምኛ ከአማርኛ በተጨማሪ ብሔራዊ ቋንቋ ቢሆን ችግር የለብኝም፡፡ ኦሮምኛ ብቻም ሳይሆን ሌላም ቢጨመር እንደዛው፡፡ ጥያቄውን ግን ልብ በሉት ያላቹህት በቋንቋችን እንተዳደር አይደለም ይሄንን አሁንም እያደረጋቹህ ነው አሁን እያላቹህ ያላቹህት ኦሮምኛን ሌሎች ብሔረሰቦችም የሚናገሩት የሚሠሩበትም ቋንቋ ይሁንልን ነው እያላቹህ ያላቹህት፡፡ እንዲህ ሲባል ደግሞ ብዙ የሚታዩ ነገሮች እንዳሉ ልብ በሉ፡፡ እርግጥ ነው አንድን ቋንቋ በብሔራዊ ቋንቋነት እንዲመረጥ ከሚያስችሉት መስፈርቶች አንዱ ያ ቋንቋ በአብዝኃው ሕዝብ የሚነገር መሆኑ አንዱ ቢሆንም ከዚህ በተጨማሪም የሚታዩ ሌሎች መስፈርቶችም አሉ፡፡

በነገራችን ላይ የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ተብሎ እየተጠቀሰ ካለው ቁጥር ከ7-10 ሚሊዮን (አእላፋት) የሚሆኑት በኦሮሚያ ያሉ አማሮች ናቸው፡፡ ይህ የአገዛዝ ሥርዓትና ኦነግ ከጅምሩ ከጋረጠባቸውና ካደረሰባቸው የዘር ማጥፋት አደጋ ለመዳን ሲሉ ብቻ እራሳቸውን ወደ ኦሮሞነት የለወጡ አማሮች ናቸው ይሄንን የወያኔና የኦሕዴድ ባለሥልጣናት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ይህ መሆኑ ስለተመቻቸው ነው ዝም ያሉት፡፡ አማሮች አማራነታቸውን የቀየሩት ኦሮሚያ ተብሎ በሚጠራው ብቻ አይደለም በሌሎችም ክልሎች ጭምር እንጅ፡፡ በመሆኑም አሁን የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር እየተባለ በሚጠቀሰው ቁጥር መታበይ አይገባም፡፡ እነዚህ ወገኖች ከሥጋት ነጻ ሆነው ማንነታቸውን መናገር የሚችሉበትን ዕድል ቢያገኙ የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር የሚሆነው ከእነሱ የሚቀረው መሆኑ እርግጥ ነውና፡፡ በመሆኑም “ኦሮምኛ በሀገሪቱ አብዛኛውን ቁጥር የያዘው ብሔር ቋንቋ በመሆኑ ከአማርኛ በበለጠ መልኩ በሀገሪቱ ይነገራል” የተባለው አባባል የተሳሳተ ነው ማለት ነው፡፡ አማርኛ በሀገራችን ከሚነገሩ ቋንቋዎች ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ቋንቋ ነው፡፡ ምክንያቱም አማርኛ ተናጋሪዎች አማሮች ብቻ ሳይሆኑ አማርኛ መናገር የሚችሉትን ኦሮሞዎችን ጨምሮ ከሁሉም ብሔረሰቦች አማርኛ መናገር የሚችሉትንም ይጨምራልና፡፡ ከዚህም የተነሣ የአማርኛና የኦሮምኛ ተናጋሪ ቁጥር በጣም የተራራቀና ሊወዳደር የሚችልም አይደለም፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ አንድ ቋንቋ ከሌሎቹ የሀገሪቱ ቋንቋዎች ተሽሎ ተመርጦ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ለመመረጥ የሀገሪቱን ታሪክ ሥልጣኔ ሊያሳይ ሊመሰክር የሚችል እንደ ፊደል ያሉ የራሱ መገለጫዎችና እሴቶች ያሉት መሆኑ ግድ ነው፡፡ በሌሎች የሀገሪቱ ዜጎችም ለመለመድ ነባራዊ ምቹ ሁኔታዎችና ቅለትስ አለው ወይ? የሚሉትና የመሳሰሉት ነጥቦች ይነሣሉ፡፡ እነኝህ ነገሮችን ሁሉ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ተገቢ ነው፡፡ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች ያላቸው ብሔረሰቦች አሉ ተብሎ 80 ዓይነት ብሔራዊ ቋንቋ ይኑረን ማለትም የበሰለ አስተሳሰብ አይመስለኝም፡፡ ለየራሳቸው በየቋንቋቸው ከተማሩና ከተዳደሩ በቂና አስፈላጊውም ይሄው ይመስለኛል፡፡ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ዜጎች ደግሞ እርስ በእርስ የምንግባባበት ከራሳችን ቋንቋዎች አንድ መምረጥ ያስፈልገናል፡፡ ያንን ከብዙ መስፈርቶች አንጻር ተመዝኖ ብቁ ወይም የተሻለ ሆኖ የተገኘውን ቋንቋ ሁላችንም አውቀን መሥራቱ ግድ ይለናል ማለት ነው፡፡ ሊያግባቡን የማይችሉና የሚያፈራቅቁንን ነገሮች ሆን ብለን እንፈልፍል ካልን ብዙ ነገሮችን ልናወጣ እንችላለን ይህ ግን የሚጠቅመን ወደ ፊት የሚያራምደን አንድነት ኅብረት የሚያመጣ አይደለም፡፡ የኔስ የኔስ እያልን መወዛገቡ የትም አያደርሰንም አመክንዮአዊም አይደለም፡፡

ክፍል 2

ዓላማችን ፍላጎታችን መገንጠል ነው ስላላቹህት ጉዳይ የምለው ነገር ቢኖር ይሄንን በማለታቹህ ከታሪካዊ ዳራ አንጻር ላነሣ የሚገባኝን የሞራልና የመብት ጥያቄ ለጊዜው ልተወውና መገንጠልን እንደ አማራጭ ስትወስዱ ልታዩ የሚገባቹህን ሁለት ዐበይት ነጥቦች ዐይታቹሀል ወይ? አንደኛው መገንጠላቹህ ሰላም ለማግኘት መፍትሔ ይሆናል ወይ? ሁለተኛው የምትገነጥሉትን ሀገርና ሕዝብ እንደ ሀገርና ሕዝብ ለማስቀጠል የሚያስችል ሪሶርስ (ሀብት) አላቹህ ወይ? ብየ ለጠየኳቸው ጥያቄ ሲመልሱ የመጀመሪያውን ዘለሉና ለሁለተኛው “በቂ ሀብት አለን አሁን ኢትዮጵያን ቀጥ አድርጎ የያዛት ከኦሮሚያ የሚወጣው ሀብት ነው” ብለው መለሱ፡፡ እኔ የፈለኩት ልማዳዊውን አባባል ሳይሆን ሳይንሳዊ የሆነውን ነበር አቅም ገደባቸውና በዚያ መልኩ ሊመልሱልኝ አልቻሉም፡፡

የመገንጠልን ሐሳብ የሚያስቡ ወገኖች ሁሉ ሐሳባቸውን የሚመራው ስሜት እንጅ ዕውቀት አይደለም፡፡ ይሄ ችግር በወያኔና በሻቢያ ላይም ተከስቷል፡፡ ተገንጥለው የራሳችን የብቻችን የሚሉትን ሀገር ማግኘታቸውን ነው እንጅ አርቆና ጠልቆ ማሰብ ካለመቻላቸው ስሜት እንጅ ዕውቀት አይመራቸውምና የመገንጠል ሐሳባቸውን በእነኝህ ሁለት ጥያቄዎች አይፈትሹም አይመዝኑም አይመረምሩም፡፡ ያም በመሆኑ ነው ይህ አቅም ስለሌላቸውም ነው የአፍሪካ ሲንጋፖር የመሆን ምኞት የነበራት ኤርትራ እንኳን ሲንጋፖር እራሷን መሆን እንኳን አቅቷት ከመከኑ መንግሥታት (failed state) ጎራ ለመቀላቀል እየተንደረደረች ያለችው፡፡ ኤርትራ የአፍሪካ ሲንጋፖር መሆን እየቻለች ስላልፈለገች ድሀ መሆንን ስለመረጠች አይደለም ደሀ የሆነችው፡፡ ምኞቱ ምኞት ብቻ እንጅ አቅምን ያገናዘበ አልነበረምና ነው፡፡

ወያኔም እንደዛው ነው ትግራይን ነጻ አወጣለሁ እገነጥላለሁ ሲል እነዚህን ሁለት ጥያቄዎች ጨርሶ አልመረመረም አላሰበም፡፡ አሁንም በዚህ ዘመን ላይ የትኛውም የኢትዮጵያ ክልል ከሀገሪቱ ተገንጥሎ እንደሀገር እድገትና ብልጽግናን የማረጋገጥ የአቅም ዋስትና ኖሮት መቆም የሚችል ክልል የለም፡፡ ልጆቹ የገለጹት የቡናና የስንዴ ሌላም የግብርና ምርት ካለ ታክሎ እነኝህ አንድን ሀገር እንደ ሀገር ሊያስቀጥሉ የሚችሉ ቋሚ ሀብቶች አይደሉም፡፡ የእለት ጉርስ የማያሳጣን መሬት አለ ተብሎ የአዲስ ሀገር ምሥረታ አይታሰብም፡፡ ተገንጣይ ወገኖች ሊገባቸው ያልቻለው ይሄ ነው፡፡

ሀገርን እንደ ሀገር አቁሞ ለማስቀጠል ከቡናና ስንዴ በላይ ብዙ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ሀገር እንደ ሀገር ለመቆም ብዙ የተቀናጀ የተወሳሰበ ግብአት የሚፈልግ ጎጆ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ሀብት ባሻገር ሊታዩ ግድ የሚሉ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ ልባም ልጆችና ሰላም ቢኖራት በጣም ከበቂ በላይ ሀብት አላት፡፡ አሁን አሁን አንድ የሚባል ነገር አለ በዚህ ዘመን ያለውን ወደፊትም የሚኖረውን ዓለማቀፋዊ ፈተናና የሉላዊነት (የግሎባላይዜሽን) ጫና ተቋቁሞ እንደ ሀገር ለመቀጠልና እድገት ብልጽግናን ለማምጣት የቀጠናው ሀገሮች ማለትም ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ሀገራችንም ውሕደት ግድ ይላቸዋል የሚባለው፡፡ ልብ ብለን ካጤነው ብልጽግናን ሕልሙ ያደረገው የዚህ የውሕደት ሐሳብ አስኳሉ መሠረቱ በዋናነት የኢትዮጵያን ሀብት (resource) ታሳቢ ያደረገ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ኢትዮጵያ ብቻዋን ልትበለጽግበት የሚያስችላት አቅም ካላት ለምን ታዲያ እነኝህ የቀጠናውን ፖለቲካ የሚያጠኑ ባዕዳን ተንታኞች ኢትዮጵያንም ቀላቀሏት? ቢባል ሀገራችን እነኝህን ሀገራት ካላካተተች እነኝህ ሀገራት መሣሪያ ለሚያነሱ የተቃውሞ ኃይሎች መጠጊያ በመሆን አቅሟን ተጠቅማ እድገቷን እውን እንዳታደርግ እንቅፋት ስለሚሆኗትና ይሄንን ተቋቁማ ስኬት ላይ ለመድረስ ይቸግራታል ከሚል እምነት እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ እንግዲህ እንደሀገር ለመቀጠል በቀጠና ደረጃ ውሕደት በሚታሰብበት ዘመን ጭራሽ ከኢትዮጵያ ተገንጥየ ብሎ ማሰቡ ያለውንና የሚመጣውን ዓለማቀፋዊና ክልላዊ ሁኔታ ያለማየትና ቀድሞ ያለመገንዘብ ችግር ነው፡፡ እነሱ ያሉት ገና ከድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ነው፡፡

ሌላኛው “መገንጠላቹህ ሰላም ለማግኘት መፍትሔ ይሆናል ወይ? አሁን ላሉብን ችግሮች ሁሉ መፍትሔ ይሆናል ብላቹህ ታስባላቹህ ወይ? አይሆንም ብሎ የሚዋጋ የሚዋደቅ እንደማይኖር እርግጠኞች ናቹህ ወይ? ይሄስ ከሆነ ሰላምን ካላመጣ ካላረጋገጠ እንደ አማራጭ የመውሰዱ ፋይዳ ምንድን ነው? መገንጠል ሰላምን ፍትሕን እኩልነትን እንደማያመጣ ከኤርትራ መማር አንችልም ወይ?” የሚለው ልጆቹ ሳይመልሱ የዘለሉት ጥያቄም ጉዳይ እንዲሁ አሳሳቢ ነው፡፡ መገነጣጠልን እንደ አማራጭ ስንወስድ ያጣነውን ሰላም ፍትሕና እኩልነት እንደሚያመጣልን እርግጠኞች መሆን መቻል አለብን፡፡ ይሄንን ማረጋገጥ ሳንችል ከሆነ እንደ አማራጭ ልንወስድ የምንቋምጠው አሁንም ይሄ ሐሳባችን የመነጨው በአለማወቅና ድንቁርና ከታጀለ ስሜት እንጅ ከዕውቀትና አርቆ ከማሰብ አይደለም ማለት ነው፡፡

እኔ እኮ የሚገርመኝ የፖለቲካ መሪዎቻችን እንግዲህ የዚህን ያህል እንጭጮች አርቀው ጠልቀውና ግራቀኙን ተመልክተው ማሰብ የማይችሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ እኔ የሚያሳዝነኝና የሚያንገበግበኝ የዚህ ሕዝብና የዚህች ሀገር እጣ ፋንታ በእነዚህ ከንቱዎች መወሰኑ ነው፡፡ በፍጹም እኮ ይሄንን ሕዝብ የሚመጥኑ አይደሉም በጣም የሚገርመኝ ርካሽና ውዳቂ የግልና የቡድን ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ሕዝብን አሳምኖ ከጎናቸው እንዲሰለፍ ለማድረግ ነገሮችን እያጋነኑ ብሎም የሌለ ያልነበረ ነገር ሁሉ ፈጥረው የሚያወሩ ሕዝቡ ዝምድናውን አንድነቱን እንዲያፈርና እርስ በእርሱ እንዲፋጅ ያለ የሌለ አቅማቸውን ተጠቅመው የሚገፋፉ ሥራዬ ብለው ጥፋትን የሚሸርቡ ርካሾች እኮ ናቸው፡፡

አንድ የሚገርመኝ ነገር አለ የጥፋት ኃይሎች እንዴት አድርገው ይሄንን ማድረግ እንደቻሉ ይደንቀኛል፡፡ እራሳቸውን የጥፋት ኃይል ተዋንያንንም ይጨምራል፡፡ በቀለም ትምህርት የገፉ እስከ ማስተርስ ፒ.ኤች.ዲ. ደረጃ ያሉ ሰዎች ያጋጥሙኛል በሩቅ የምናውቃቸው “ፕሮፌሰሮችም” አሉ፡፡ የሚገርመው በቀለም ትምህርታቸው የዚህን ያህል የተሳካላቸው ሆነው እያለ ይሄንን ያህል እንደመማራቸው ትምህርታቸው ረድቷቸው ሊለወጥ ሊቀየር ሊበስል የሚገባው ሌላው ነገር ግን ቅንጣትም ያልተለወጠ ያልበሰለ ያላደገ ትምህርታቸው በዚህ ረገድ ምንም ያልጠቀማቸው ባክኖ የቀረባቸው “ምን ዓይነት የማያስብ ሰብአዊነት የሚባል የሌለው ጭንቅላቱ የማይሠራ ፍጥረት ነው?” ብላቹህ ከምትሉት ሰው ያልተለዩ ሰዎችን በቅርብም በሩቅም አውቃለሁ፡፡ እኔ ዘርዝሬ የማልጨርሳቸውን ነገር እነ እከሌ እነ እከሌ አልልም፡፡ እነማን እንደሆኑ አሳምራቹህ ታውቋቸዋላቹህ በጥፋት ኃይል ጎራ የተሰለፉ ወይም የነሱ አባሪ ናቸው፡፡ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ልዕልና ያለው ሐሳብና እውነት ካላቸው በሐሳብ ተሟግተው መርታት ማሸነፍ እየቻሉ “በሜንጫ በጎራዴ አንገት አንገቱን በሉት” እያሉ አጋንንት ይመስል የሰው ደም ለመጠጣት የሚቋምጡትም ናቸው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው እነዚህ ለዚህ ሕዝብ የሚመጥኑት? እኔ መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ እውነትና ሞግቶ መርታት የሚያስችል ልዕልና ያለው ሐሳብ እንደሌላቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው እያጋነኑ ወይም ውሸትና ፈጠራን እየተጠቀሙ ጉዳዮቻቸውን በኃይል እርምጃ ለመፍታት ፍላጎታቸውን ለማሳካት የሚጣጣሩት፡፡ ከጭንቅላት ይልቅ ጡንቻ ማስቀደም የሚቀናው ጭንቅላት የሌለውና ተሸናፊ ለምንም የማይጠቅም የባከነ ዜጋ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወኔው የሞራል ብቃቱና ፍላጎቱ የላቸውም እንጅ ለአፍታ ከራሳቸው ወጥተው ልክ እንደሌላ ሰው እራሳቸውን ቢመለከቱ ከነውረኛነታቸው የተነሣ በራሳቸው እጅግ የሚያፍሩ የሚሸማቀቁ በሆኑ ነበር፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን ስመለስ ከዚህም አንጻር መገንጠል መፍትሔ እንዳልሆነ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ አብርሃ ደስታም ቀጠል አደረገና “ጭቆናና በደል የሚያደርሰውን አካል አስወግዶ ሰላምን እኩልነትን ፍትሕን ማስፈን ከተቻለ ጨቋኝ አካል ከሌለ ችግሮቻችን ተፈቱ ማለት አይደለም ወይ? ችግሮቻችን ከተፈቱ መገንጠሉ ለምን ያስፈልጋል? ለምን በዚህ ላይ አታተኩሩም?” ብሎ አከለ፡፡

ተቀራርቦ መነጋገር ከተቻለ ወያኔና ሌሎችም የጥፋት ኃይሎች የፈለጋቸውን ያህል ትውልዱን ቢመርዙ ቢጠመዝዙም የማይስተካከል ነገር እንደማይኖር በልጆቹ ተረድቻለሁ፡፡ በማግስቱ ከሦስታቸው አንደኛው ከረር ያለ አቋም የነበረው ሳይመቸው ቀርቶ ቢቀርም ሁለቱ ግን በሚያስደስት መልኩ አቋማቸው ተስተካክሎ ነበር፡፡ ይሄም አበረታትቶኝ ሁላችንንም በሰላም ካወጣን ሁላችንም አዎንታዊ አስተሳሰብ እስካለን ጊዜ ድረስ ከፖለቲካዊ አስከ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ድረስ ያሉብን ችግሮቻችን ሁሉ በውይይት መፈታት የሚችሉ ናቸውና ከፖለቲከኞቻችን እስከ የሃይማኖት መሪዎቻችን ድረስ የሚወያዩበት የሚከራከሩበት የሚሟገቱበት የውይይት መድረክ (panel discussion forum) እናቋቁማለን ብያቸው በዚህ ሐሳብ ተስማምተው ነበር እግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁንና፡፡

በመጀመሪያዎቹ ሁለት የመወያያ ነጥቦች ላይ ሐሳቡን የሰጠው ቀጣዩ ሰው አብርሃ ደስታ ነበር እሱም ጥንቃቄ ባልተለየው አገላለጽ “ጭቆና ነበረ ይሄንን ምንም ልናስተባብለው የምንችለው ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን ጭቆናው የብሔር ሳይሆን የመደብ ነበር፡፡ በሀገሪቱ የሕዝብን ስም መጠቀሚያ ያገረጉ እንጅ ሥልጣን የነበረውና ሌሎቹንም ብሔሮች የጨቆነ ብሔረሰብ አልነበረም፡፡ ገዥዎች ግን ጭቆናውን አድርሰዋል እነሱም የሚወክሉት እራሳቸውን ብቻ ነው” አለ፡፡

ቀጣዩ ተናጋሪ ጅብሪል ነበር (የ4ኛ ዓመት የምህንድስና ተማሪ ከሙስሊሞች ጉዳይ) ጅብሪል የተናገረው በቀጥታ ከያዝነው ነጥብ ጋር የሚገናኝ አልነበረም፡፡ ስለተናገረው ነገር መፍትሔውን አብሮ እንዲጠቁም ጠይቄውም ይሄንን ባያደርግም እንዲህ ነበር ያለው፡፡ በዚህ ዘመን ያለንበት የመከፋፈል ጣጣ ከብሔርና ከሃይማኖትም እልፎ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እስከ ታች ወርዶ ሰው ሊከፋፈል ይችልበታል ተብሎ በማይታሰበው ጉዳይ ሁሉ የአንድ ሀገር ሰዎች በማንመስልበት ሁኔታ ላይ እንዳለን ገለጸና እኔ ስለ ነጻነት ሳስብ አለ ጅብሪል የብዙኃኑ ነጻነት የግለሰቦችን ነጻነት እንዳይጥሥ ማድረግ እስከሚኖርበት ድረስ ማክበር እንደሚኖርብን ይሰማኛል፡፡ እኔ ስልጤ ነኝ ስልጤ መቶ በመቶ ሙስሊም ነው፡፡ አንዴ ሀገር ቤት እያለሁ ምን ተመለከትኩ መሰላቹህ? ልጆች ናቸው ተደብቀው በአንዲት ልጅ ላይ ጠጠር ይወረውራሉ፡፡ ለምን እንዲህ እንዳደረጉ ለመረዳት ወጣ ብየ ስመለከት ልጅቱ የአካባቢው ሰው አይደለችም እንግዳ ነች እና ሱሪ አድርጋ ነበር፡፡ ሕፃናቶቹም የሚወረውሩት ከእምነታቸው የወጣ አለባበስ ስለተመለከቱ በአለባበሷ ምክንያት ነበር የሚወረውሩባት፡፡

አንድ አካባቢ በሃይማኖቱ ምክንያት የአለባበሱ ሥርዓት ሊከበርለት የሚገባ ሚሆንም የግለሰቦች ነጻነት ደግሞ መከበር ይኖርበታል ብየ አምናለሁ አለ፡፡ ጨመር አደረገና የሚለው ነገር ከልቡ እንደሆነ ለመግለጽ በፈለገ ስሜት “ከዚህ ጋር በተያያዘም የንጉሣዊያን ቤተሰብም ልዩ ተደርገው የመታየት መብታቸው ሥልጣናቸው መከበር የሚኖርበት ይመስለኛል” ሲል ቀበል አድርጌ አየ አንተ! በጣም ቅን ነህ ጥሩ ነው ነገር ግን አሁን ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ እንደገና ተመልሰን ወደ ዘውዳዊው ሥርዓት መመለስ የምንችልበት ሁኔታ ያለ ይመስልሀል? የንጉሣዊያን ቤተሰቦች ቀድሞ የወቅቱ ሰው ያስበው እንደነበረው ልዩ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ እኮ ልክ አይደለም፡፡ እነሱ እንደሁላችንም ሰዎች ናቸው ከሰው የተለዩ የሚያደርጋቸው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ በእርግጥ ከእኛ ጋራ ተመሳሳይ የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት በነበረባቸው ሀገራት በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት አሁንም ድረስ አለ፡፡ ለምሳሌ በእንግሊዝና በሳውዲ ዓረቢያ፡፡ እንግሊዞች አሁንም ድረስ ዘውዳዊውም ሥርዓት እየተንከባከቡ ጠብቀው ይዘውታል፡፡ ንግሥቲቱን መጨበጥ ወይም መንካት አይደለም ማየት እንኳን ልዩ ዕድል የተለየ መብት እንደሆነ ያደረገ ሥርዓት አላቸው፡፡ የሆነ ሆኖ ግን ይህ ዘውዳዊ ሥርዓታው በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ምንም የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡ መሪያቸውንም የሚመርጡት በሕዝብ ከሕዝብ ነው እንጅ ከንጉሣዊያን ቤተሰቦች አይደለም፡፡ እንደሚመስለኝ ይህ ለዘውዳዊው ሥርዓት ሥልጣን አልባ አድርገው ነገር ግን እብክብካቤ እያደረጉለት የያዙበት አሠራር ለዘውዳዊው ሥርዓት ስድብ ቢሆንም የንጉሣዊያን ቤተሰቦች ከሰው የተለዩ ናቸው ከሚል እምነት ሳይሆን ሀገራቸው ለረጅም ዘመናት የተዳደረችበት የመንግሥት ሥርዓት በመሆኑ የሀገር ቅርስ ነውና መጥፋት የለበትም ከሚል ግንዛቤ ይመስለኛል አልኩ፡፡

ጅብሪል ቀጠል አድርጎም ከዓመታት በፊት አንድ መጽሔት ሳነብ ያገኘሁት ነው ምን ይላል መሰላቹህ? በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምሁራኑን ቁጥር በብሔር ተዋጽኦ ምን እንደሚመስል ነው የሚያብራራው፡፡ እና በዚያ ጥናት መሠረት ከሀገሪቱ ምሁራን ውስጥ 61% የአማራ ተወላጆች ናቸው ይላል ሲል አጥኝው ማን እንደሆነና መጽሔቱንም እንዲነግረኝ ጠየኩት፡፡ ካነበበው ቆየት ስላለ እንደማያስታውሰው ተናግሮ ቀጠለና በመሆኑም አማራ በተለየ መልኩ ተጠቃሚ ነበረ አለ፡፡

የዞን ዘጠኙ በፈቃዱም ቀበል አደረገና ይሄ ምንም አያጠራጥርም የሚታወቅ ነገር ነው በመሆኑም በፊት በዚህ ትክክለኛ ባለሆነ አሠራር ተጎድተው ለነበሩት ብሔረሰቦች ከአማራው የተሻለ የትምህርት ዕድል በመስጠት መካስ ይኖርባቸዋል የሚል በጣም የገረመኝን አስተያየት አከለ፡፡

ዘለዓለምም (እነ ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁ በሚለው 10 ወገኖች በአሸባሪነት በተከሰሱበት እነ አብርሃ ደስታ እነ ሀብታሙ አያሌው እነ ዳንኤል ሽበሽ ባሉበት የክስ መዝገብ አንደኛ ተከሳሽ) ቀጠለና አይ ይሄ ውጤት ሊገኝ የቻለው ሀገሪቱ ላይ በነበረው በቀደመው የቤተክህነት ትምህርት አማራው መቀራረብ ምክንያት ለትምህርት ያለው አመለካከት ቀና መሆን አስተዋጽኦ ስላበረከተለት ለትምህርት ባለው የተሻለ ፍላጎት የተነሣ እንጅ በተለየ መንገድ ስለተስተናገደ ወይም በተለየ ተጠቃሚ እንዲሆን ስለተደረገ አይመስለኝም ብሎ ገለጸ፡፡

እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ የበኩሌን ማለት ስለነበረብኝ የሚከተለውን አልኩ ይህ የተጠቀሰው ጥናት በእርግጠኝነት የወያኔና ፈጽሞ እውነትነትም የሌለው ነው፡፡ ዓላማውም በአማራ ላይ ቂምና ጥላቻ መፍጠር ነው እውነታው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው ይሄንንም ማሳየት ይቻላል፡፡ እንደምታውቁት ዘመናዊውን ትምህርት ወደ ሀገራችን ያስገቡት ዐፄ ምኒልክ ናቸው፡፡ በወቅቱ ይሄንን ትምህርት ለሕዝባቸው እንዲያስተምሩ ለአውሮፓ ሀገራት ጥሪ ሲያቀርቡ የመጡላቸው ሚሲዮኖች ነበሩ፡፡ የገቡትን ሚሲዮኖች የሚበዙትን ወደ አማራው ላኳቸው አማሮች ግን እነዚህ የመጡት ትምህርት ሊያስተምሩ ሳይሆን ሃይማኖታችን ሊለውጡብን ነው በሚል አባረሯቸው፡፡ ዐፄ ምኒልክም እነኝህን አማራው ያባረራቸውን ሚሲዮኖች ወደ ኦሮሞና ደቡቦች ላኳቸው ኦሮሞዎቹና ደቡቦቹ ግን በሚገባ ተቀበሏቸው፡፡ ዘመናዊውን ትምህርትም ቀድመው ለመማር ዕድሉን አገኙ ሚሲዮኖችም በምላሹ ያኔ የጣሉት መሠረት አሁን ባለው ምጣኔአዊ ስሌት(የሬሾ ስሌት) ዛሬ ላይ በሀገራችን የሚበዙቱ ደቡብና ኦሮምያ ሆነው 38 ሚሊዮን (አእላፋት) ዜጎቻችንን ፕሮቴስታንትና ካቶሊክ ማድረግ ቻሉ፡፡ የአማራው ሥጋትም ተጨባጭ ነበር ማለት ነው፡፡ ዘመናዊውን ትምህርት ለኦሮሞና ደቡብ ያስተማሩት ሚሲዮኖች ከትምህርቱ ባሻገር ለተማሪዎቹ እምነታቸውን ይሰብኳቸው ስለነበረ ነው እንዲህ ሊሆን የቻለው፡፡

ወደ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ስንመጣ ሁኔታው ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ከራስነታቸው ጊዜ ጀምረው ለትምህርት በሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ትምህርት ቤቶችን ከፍተው ባላባቶች ልጆቻቸውን ልከው እንዲያስተምሩ ቢያዙም የሚሰማቸው ግን አልተገኘም ነበር አሁንም “ልጆቻችን ሃይማኖታቸውን ይቀይሩብናል” በሚል ከፍተኛ ሥጋት ነበር አንልክም ያሉት፡፡ መላካቸው ግዴታ እንዲሆን ሲደነገግባቸው ደግሞ ምን አደረጉ አሽከሮቻቸውን ላኩ፡፡ በዚህ ምክንያት ራስ ተፈሪ በትምህርት ቤቶቹ ከመንገድም ከምንም ያገኙትን የድሀ ልጆች ሰብስበው እየመከሩና እያበረታቱ እንዲማሩ አደረጉ፡፡ በዚህም ምክንያት አሁንም አማራ ዘመናዊውን ትምህርት ለማግኘት ሳይችል ቀረ፡፡

በነገራችን ላይ ይሄ አመለካከት እንዲቀር ደርግም የተቻለውን ያህል ቢጥርም ዛሬም ድረስ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ያለና ያልጠፋ አስተሳሰብ ነው፡፡ የቀድሞውን ይዘው “ሃይማኖታቸውን ይቀይሩብናል” እያሉ ልጆቻቸውን ወደ ዘመናዊው ትምህርት ቤት የማይልኩ አሉ፡፡ በአማራው ዘንድ ለዘመናዊ ትምህርት ያለው አመለካከት እንዲህ በሆነበት ሁኔታና በዚህም ምክንያት ከዐፄ ምኒልክ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ተሸግሮም እስከ ደርግ የዘመናዊ ትምህርት ተቋዳሾች ኮምኳሚዎች ኦሮሞዎችና ደቡቦች በሆኑበት ሁኔታ ይህ የጠቀስከው ዳታ (አኃዛዊ መረጃ) በፍጹም ሊገኝ አይችልም ትክክልም ሊሆን አይችልም፡፡ አይ ጥናቱ ትክክለኛ ጥናት ነው ከተባለም ይህ ውጤት ሊገኝ የሚችለው ውጪ ያሉ የአማራ ተወላጆችም ተካተው ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ እነሱም ደግሞ የተማሩት መንግሥታቱ ልዩ ድጋፍ አድርገውላቸው ልከው ስላስተማሯቸው ሳይሆን በደርግ ዘመን በነበረው የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ ነፍሳቸውን ለማዳን በስደት ሸሽተው ወደ አውሮፓና አሜሪካ ወተው በዚያ የመማር ዕድል አግኝተው ስለተማሩ ነው፡፡

እኔ በሀገር ቤት ጎንደር የማውቀው ይሄንን ነው፡፡ በወቅቱ ደርሸ ሁኔታን ለመታዘብ ዕድሜየ ባይፈቅድም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ አንድ ታሪክ አለ የጎንደር ወጣት በወቅቱ ከሻለቃ መላኩና ከመሰሎቹ ቅስፈት (ቀይ ሽብር) ለመትረፍ በገፍ ወደ ሱዳን እየተሰደደ ይወጣ ነበር፡፡ ይህ አጋጣሚ ለበጎ ሆኖለት እየተሳሳበ እየወጣ ዛሬ ላይ ጎንደር ውስጥ አውሮፓና አሜሪካ ዘመድ የሌለው ሰው የለም እየተሳሳበም በገፍ ወጥታል ከነዚህ ውስጥ ከሞላ ጎደል ተምሮ ከፍ ላለ ደረጃ የበቃ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ጥናት ትክክለኛ ነው ከተባለ ሊሆን የሚችለው እነዚህን ውጪ ያሉ የአማራ ተወላጆችንም አካቶ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እንጅ አማራ ልዩ ድጋፍ አግኝቶ የዛም ተጠቃሚ ስለነበረ ባለመሆኑ መካስ ካለበት ተካሹ አማራ እንጅ የዘመናዊውን ትምህርት እፍታ ያገኙት በዚህም ምክንያት በሚሲዮኖች የውጭ የትምህርት ዕድል እየተሰጣቸው ብዙ ምሁራንን ያፈሩት ኦሮሞዎችና ደቡቦች አይደሉም ብየ ገለጽኩ፡፡

እስከአሁን በአንደኛውና በሁለተኛው የመወያያ ነጥባችን ላይ የእኔ ሐሳብ አልተሰማም፡፡ ከዚህ በላይ የገለጽኳቸው ሐሳቦች ተወያዮቹ በሚያነሡዋቸው ላይ ተንተርሸ ያልኳቸው ነበሩ፡፡ በሁለቱም ነጥቦች ላይ የኔ ሐሳብ የሚከተለው ነበር፡-

አዎ በእርግጥ ጭቆና ነበረ የነበረው ጭቆና ግን ፈጽሞ የብሔር ሳይሆን የመደብ ነበር ይሄም ቢሆን ግን የጥፋት ኃይሎች ለርካሽ ጥቅማቸው ሲሉ ጭቆናው ነበር ተብሎ እጅግ ተለጥጦና ተጋንኖ እንደሚወራው አይደለም አልነበረምም ሥልጣኑ ይያዝ ይገኝ የነበረው አማራ በመሆን ከማንኛውም የአማራ ተወላጅ ተመርጦ ሳይሆን ከሰሎሞናዊው የዘር ኃረግ ጋር የተሳሰረው ቤተሰብ ተወላጅ በመሆን ብቻ የነበረ በመሆኑ ስል እየተሻሙ ጥያቄዎችን ወደኔ ሰነዘሩ፡፡ ባጋጣሚ በፈቃዱ ያነሣው ጥያቄ የሌሎቹም ነበረ ጥያቄውም “ገዥ መደብ” ማለት ምን ማለት ነው? የሚል ነበር፡፡ ሌላኛው ጥያቄም የአብርሃ ደስታ ሲሆን ጥያቄውም “አንተ የሀገር መሪ ብትሆን አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ችግር እንዴት አድርገህ ትፈታዋለህ?” የሚል ነበር እንደሚከተለው አድርጌ መለስኩ፡፡

“ገዥ መደብ” ማለት በአንዳንድ ሀገሮች በልማዳዊ አስተሳሰብም ሊሆን ይችላል ወይም  በሚከተሉት እምነት ለምሳሌ በህንድ በሩቅ ምሥራቅ በመካከለኛው ምሥራቅ በአፍሪካ ገዥ መደብ ማለት በሌሎቹ ላይ ተጭኖ ዝንተ ዓለም የመግዛት መብት ያለው ብሔረሰብ ማለት ነው፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመጣ ደግሞ ገዥ መደብ ማለት ከሰሎሞናዊው የዘር ኃረግ ጋር የተሳሰረ የአንድ ቤተሰብ ዛጉዌዎችን ስንጨምር የሁለት ቤተሰብ ትውልድ ማለት ነው፡፡ ይህ ሥልጣን በአንድ ቤተሰብ ትውልድ የመያዙ ዘውዳዊ ሥርዓት ከሰሎሞናዊው የዘር ኃረግ ጋር አይተሳሰር እንጅ በአውሮፓም ነበረ፡፡ አልኩና ወደ አቋረጡኝ ነጥቤ ተመለስኩ፡፡

እናም በሀገራችን የነበረው ገዥና የሚወራውን ያህል ባይሆንም ግፍ ፈጸመ የሚባለው ማን እንደሆነ በሚገባ የሚታወቅ ሆኖ እያለ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ ብዙዎች አማራን ሲጨቁን ሲረግጥ የኖረ አድርገው ያስባሉ፡፡ እውነታው ግን ይሄ አይደለም፡፡ ለአማራ ያለው የጥላቻ መንፈስ መሠረቱ ማየት ማሰብ ካለመቻል የሚመነጭ ድንቁርናና ጠባብነት ነው፡፡ በሀገራችን የመደብ እንጅ የብሔር ጭቆና እንዳልነበረ ለማንም ግልጽነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዥዎች የተጨቆኑ የጠረገጡ ብሔረሰቦች አሉ ከተባለ እጅግ በከፋ ሁኔታ የተጨቆነ የተረገጠ የተበዘበዘና የግፍ ገፈት ተጋቹ አማራ እንደነበረ ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡ እንደምታውቁት በዘውዳዊው ሥርዓት የሀገሪቱ ጦር ወይም ተዋጊዎች ደሞዝ አልነበራቸውም ጦሩን የመመገብ የማሥተዳደር ግዴታና ኃላፊነቱ የተጫነው በገበሬው ላይ ነበር፡፡ ገበሬው ለሀገር ጠባቂ ጦር ልጆቹን ከመስጠቱ በተጨማሪ የሀገሪቱን ሠራዊት ተከፋፍሎ የመቀለብ ግዴታ ነበረበት፡፡ ዘውዳዊው ሥርዓት ከአማራው እንደመውጣቱና ሕዝቡ መሀል እንደመኖሩ የአማራ ሕዝብ ከሌሎቹ ብሔረሰቦች በተለየ መልኩ ይሄንን ግዴታ የመሸከም ኃላፊነት ነበረበት፡፡ በመሆኑም እነኝህ የሠራዊቱ አባላት ሦስትም ሆነ አምስት በመሆን በአንድ ገበሬ ጎጆ ይመሩ ነበር፡፡

ይህ አሠራር “ተሠሪ” ይባላል በጎጃም “እሬና” ይባላል፡፡ እነኝህ ሀገር ጠባቂ ፋኖዎች በተሠሩበት ገበሬ ቤት ይበላሉ ይጠጣሉ አባወራና ልጆች የሚያገኙት ከነሱ የተረፈውን ነው፡፡ ሲያሰኛቸውም ያለ ባለቤቶቹ ፈቃድ ጠቦቱን አርደው ይበላሉ ገበሬው ምንም ማለት አይችልም፡፡ ተሠሪዎቹ እንዲህ እንዲህ እያሉ ያች ጎጆ ስትደኸይባቸው ስታጣ ስትነጣባቸው ደሞ ወደ ሌላዋ ይሄዳሉ ደሞ ያችንም በተራዋ ያደኸያሉ፡፡ ዝርዝሩን ቢናገሩት ትንሽ አስቸጋሪ ነው እንዲሁ ልለፈው ባጠቃላይ ግን ለዚህች ሀገር ህልውናና ነጻነት መጠበቅ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ገበሬው ነው፡፡ አማራ ይሄንን ከባድ መራር ዋጋ ለገዥዎቹ ሳይሆን ለሀገሩ ነጻነትና ህልውና ሲል የውዴታ ግጌታው አድርጎ ለሽዎች ዓመታት ሲከፍል የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው የአማራ ገበሬ ጥሪት መቋጠር የተሳነው ለልጁ ማውረስ የሚችለው ነገር የሌለውና ኑሮው ከእጅ ለወደ አፍ እንኳን የሚበቃ ያጣ ሊሆን የቻለውና ዛሬም ድረስ ሥር በሰደደ ድህነት ታስሮ የቀረው፡፡

ዛሬ በወያኔ ደናቁርት አንደበት “ለእግሩ ጫማ የማያውቅ” ተብሎ እስከመዘለፍ ላበቃው ድህነት የተዳረገው ለሀገሩ ሲል ሁለንተናውን ሲከፍል በመኖሩ ነው፡፡ የአማራ ገበሬ ጫማ ብቻ አይደለም እንደምንም አንዲት ጨርቅ ከገዛ እሷኑ እየደራረተ ከገላው ላይ ተበጣጥቃ እስክታልቅ ድረስ ሌላ መቀየሪያ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያን ገጠሮች እየተዘዋወራጩህ ስትጎበኙ አንድ የምትታዘቡት ነገር አለ የደቡቦችና የኦሮሞዎች የገበሬዎች ቤቶች አቋም ጠንከር ደርጀት ያሉ ናቸው ወደ አማራው ዞር ስትሉ ደግሞ የገበሬው ጎጆ ደሳሳ ሆኖ ታገኙታላቹህ፡፡ በሌሎች ነገሮች ላይ ያለው የኑሮ ልዩነትም የዚህን ያህል ነው፡፡ አማራ የገዥዎች ጭሰኛ ሆኖ ነው የኖረው ኑሮውን ቀረብ ብለው ላዩት አንጀት ይበላል፡፡ ይሄንን መሥዋዕትነት ለማንና ለምን ሲከፍል እንደኖረ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ብቻ ነው ምንም እንዳልሆነ በችጋር እየተጠበሰ ምንም እንዳልጎደለበት ሆኖ የኖረው፡፡ ከዚህች ሀገር የሚበልጥበት ምንም ነገር የለምና ሉለንተናውን ለእናት ሀገሩ ከፍሎታል አውሎታል ሠውቶታል፡፡ የሚያሳዝነው እጁ አመድ አፋሽ መሆኑ ውለታው ሁሉ ገደል ገብቶ ያለስሙ ስም መሰጠቱ ነው፡፡ ጭንቅላት ቢኖረን ወደ ኋላም ወደ ፊትም ደወ ግራም ወደ ቀኝም መመልከት ብንችል አርቀን አስፍተን ጠልቀን ማሰብ ብንችል፣ ኢትዮጵያዊነቱ ቢሰማን የሀገራችንንና የሕዝቧንም ህልውና የምንፈልግ የምንመኝ የምንወድ ብንሆን በምንም ተአምር ለአማራ ጥላቻ ሊያድርብን አይችልም፡፡ ለዚህች ሀገርና ሕዝብ ህልውናና ነጻነት አማራ ለከፈለው ገደብ የለሽ መራራ ዋጋ እናመስግነው ብንል ለምስጋናችን ተስተካካይ ቃል ፈጽሞ ልናገኝለት አለመቻላችንን በሚገባ በተረዳን ነበር፡፡ አማራን ልንጸየፍ ልንጠላ አይደለም ወደነውም ለፍቅራችን የልባችን ባልደረሰ፡፡ ውግዘትና ጥላቻውን ትተን ክብር በሰጠነው በኮራንበትም ነበር፡፡ ለዚህ ነው ለአማራ ያለው የጥላቻ መንፈስ መሠረቱ ድንቁርና ጠባብነት የሀገር ጣላትነትም ነው ያልኩት፡፡

ቀርበው ያዩት ይሄንን ያውቁለታል ሩቅ ሆነው በወያኔ ሰይጣናዊ እኩይ የስም ማጥፋት የተመረዘ ግን ይሄንን አያውቅም፡፡ ከዓመታት በፊት ጎንደር አጠቃላይ ሆስፒታል ይሠራ የነበረ አንድ የህክምና ዶክተር የደቡብ ሰው አውቅ ነበር በአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ግብዣ ተጠርቶ ወደ አንደኛው ከመሔዱ በፊት በዚህ ሆስፒታል ለዓመታት ሠርቷል ወደ መጨረሻም ሆስፒታሉን በኃላፊነት መርቷል፡፡ እሱ ሲያጫውተኝ ጎንደር መጥቶ ሥራው በሰጠው ዕድል ሕዝቡን እንዲያ በቅርበት ከማየቱ በፊት ለአማራ በተለይም ለጎንደር ሰው የነበረው ግምትና አመለካከት እንዲህ አልነበረም፡፡ ሆስፒታሉን ለቆ ከሔደ በኋላ የነገረኝን ነገር መቸም አልረሳውም፡፡ እንዲህ ነበር ያለኝ “ፈጣሪ ቢረዳኝ ለትልቅ ደረጃ ቢያበቃኝ ልረዳው አንድ ነገር ላደርግለት የምመኘው ለጎንደር ሕዝብ ነበር” ነበር ያለው እራሱ ለወጣበት አካባቢ እንኳን አላለም፡፡ እንግዲህ በቅርብ የሚያውቁት የዚህን ያህል ይሳሱለታል፡፡

እኔ ግን የምፈራው የሌለ ያልነበረ ነገር እያወራን አማራን ያለስሙ ስም እየሰጠን እያከፋፋን ፊት እየነሳን እያሸማቀቅን የሌለ አውሬ ፈጥረን እያወራን በገዛ እጃችን አውሬውን ፈጥረነው ቁጭ እንዳንል ነው፡፡ አማራን በየሔደበት በዚህ አቀባበል እየተቀበልን በጎሪጥና በጥላቻ ዐይን ዕያየን ሳይወድ በግድ ጥላቻ እንዲቋጥር እያደረግን መልካም ምላሽ የምንጠብቅ ካለን እጅግ ተሳስተናልና እንታረም ማለትን እወዳለሁ፡፡ እንደዛ ተሰብሬ ደቅቄ ባልዋልኩበት ከዋልኩ ባልሠራሁት ከታማሁ ስም ከወጣልኝ አይቀር ብሎ የተነሣ እንደሆነ ኋላ ይቸግራልና መታረሙ ሳይሻል አይቀርም፡፡

አንድ የውጭ ጋዜጠኛ ነው አሉ የጃንሆይን ልጅ ልዕልት ተናኘወርቅን “የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንት ይሆናል” ብሎ ቢጠይቃት “ከአምስት መቶ አንበልጥም” ብላ ቁጭ አለች፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ ልዕልቲቱ በዘር አማራ እንደሆነች ብታስብም ለእሷ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት የንጉሣዊያን ቤተሰብ ብቻ እንጅ አማራውም እንኳን አይደለም፡፡ የነበረው ሐቅና እውነታ ይሄ ነው፡፡ የንጉሣዊያን ቤተሰብ ያልሆነው የአማራ ሕዝብ በገዥዎቹ ይናቅ ይገፋ ይዋረድ ይጣጣል ነበር እንጅ አማራ በመሆኑ አልተከበረም፡፡ ወያኔ እንደሆን ጥላቻን ለመፍጠር የሕዝብ አንድነትና ዝምድና እንዲፈርስ ለማድረግ ነው ሆን ብሎ እውነትን እያዛባ ገዥዎችንና አማራን አንድ አድርጎ የተሳሳተ ድምዳሜ እንዲያዝ እየደከመ ያለው፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ የገዥዎቻችን ግፍና በደል ተጋኖ የሚወራውን ያህል እንኳን ቢሆን በሀገራችን የነበረው አገዛዝ ከጥንት ጀምሮ ሃይማኖተኛ በመሆናችን ምክንያት ተመሳሳይ ዘውዳዊ የመንግሥት ሥርዓት ከነበራቸው ሀገራት እጅግ የተሻለው ነበር፡፡ አውሮፓ የተፈጸመው የሰው ልጆችን ለመዝናኛነት ከአውሬ ጋር እያታገሉና እያስበሉ መዝናናት ነገሥታቶቻቸው ሲሞቱ ጠባቂ እንዲኗቸው ተብሎ የሰው ልጆችን ከነ ሕይወታቸው አብሮ መቅበር የመሳሰለው ግፍ በሀገራችን አልተፈጸመም፡፡ የሩቁን ብንተወው በናዚ ዘመን በሰው ልጆች የተፈጸመውን ግፍ ማሰብ ይቻላል፡፡ ወደ ሀገራችን ስንመጣ ግን በተለያዩ የጥንት ፈላስፎች መጻሕፍትና የሃይማኖት መጻሕፍት ተጽፎ ያለው ሀገራችን የፍትሕ ሀገር መሆኗን ነው፡፡

ዛሬ ላይ ግን የሚገርመው እነዚያ ከእኛ እጅግ የከፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የነበረባቸው የአሥተዳደር ሥርዓት የነበራቸው የአውሮፓ ሀገራት ኮሽታ እንኳን የነበረባቸው ሳይመስሉ ተግባብተውና ተስማምተው በመሥራት ለማደግ ለመበልጸግ ሲችሉ ያሳለፉት ዘግናኝና የእርስ በእርስ እልቂት ተስማምተው ተባብረው ከመሥራት ቅንጣት ታክል እንቅፋት እንዲፈጥርባቸው ሳይፈቅዱለት ሲጓዙ እኛ ግን ጭራሽም ያልነበረ የሌለ እየፈጠርን በመናቆር ቁልቁል መሔዳችን ነው፡፡  እንደ ወያኔ ዓይነት ያለ የሌለ እያወራ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በማፋጀት ሴራ ላይ የተጠመደ ደንቆሮ ደደብ የማይገባው የማይረዳ አህያ አመራር ሳይሆን ልባም አርቆ አሳቢ በመግባባት በመስማማት በአንድነት በፍቅር መሠረትነት ሕዝብን የሚመራ ኃላፊነት የሚሰማው አመራር ስላላቸውና በዚህ ላይ ተግተው ስለሠሩ ነው፡፡ እኛ ግን እውነቱንም ውሸቱንም እየዋጥን ያን ፈጸሙ የሚባሉት ሰዎች ዛሬ ያሉና እነሱን መፋረድ ይቻል ይመስል ያለፈ የጥንት ነገርን እየጎተትን መናቆር መፋጀትን ሥራየ ብለን ይዘነው በየት በኩል አልፈን መቸስ ሠርተን ይለፍልን?

በዚህ አጋጣሚ ጥፋትን መተላለቅን መለያየትን ለምትሰብኩ የጥፋት ልጆች የምለው መልእክት ቢኖረኝ እስኪ ልብ በሉና ቆም በሉና እየሠራቹህት ያላቹህትን ነገር አስቡት፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከዚህ እንደማናተርፍ ታውቃላቹህ ወይም ማወቅ ይኖርባቹሀል የምታውቁ ከሆነም ታዲያ ምን ነው? ምን ነው? ምን አለ ይሄንን ምስኪን ሕዝብ ያሳለፈው መከራ ችጋር ቢበቃውና ፍቅርን አንድነትን ሰላምን ሰብካቹህለት ተባብሮ ሠርቶ አንገቱን ቀና ቢያደርግ? ችጋሩን ቢያራግፍ ምን አለበት? ይሄንን ብታደርጉ ምን ትሆናላቹህ? ተጠቃሚ ትሆናላቹህ እንጅ ምናቹህ ይጎዳል? እንግዲህ ምሁርነት ማለት ሕዝብን መውደድ ማለት አርቆ አሳቢነት ማለት ዐዋቂነት ማለት ይሄ ነው ሌላ ምን አለ ብላቹህ ታስባላቹህ?

ወደ አብርሃ ደስታ ጥያቄ መልስ ልለፍ፡-

እኔ የሀገር መሪ ብሆን አሁን ያለውን የመለያየትን የመከፋፈል እርስ በእርስ የመጠራጠር ችግርን ፈትቸ ሕዝብን በአንድ ልብ ለሀገሩ እንዲሰለፍ የማደርገው ይሄንን ችግር የፈጠረው ጠባብነትን ያመጣው የጎሳ ፖለቲካ በመሆኑ የብሔር ማንነትን ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳይውል በሕግ እከለክላለሁ፡፡ ስል በፈቃዱ “መከልከል መፍትሔ አይሆንም የሰው ልጅ እንዲያውም በባሕርይው የተከለከለውን ነገር ነው ለማየት ለማወቅ የሚፈልገው” ብሎ የተለመደ አባባል ተናገረ፡፡ እኔም “እስከማውቀው ድረስ በዚህች ምድር ሕግ ሳያወጣ ሳይቀርጽ ሳይከለክል የሚያሥተዳድር መንግሥት የለም፡፡ ይህ እኔ እከለክለዋለሁ የምላቹህን ነገር አሜሪካም ሩሲያም ከአፍሪካም ከፈለጋቹህ ሩዋንዳ በብዙ ሀገሮች የተከለከለ ነው፡፡ በርካታ ብሔረሰቦች በሀገሮቻቸው ያሉ ሆነው እያለ በሕግ ሳይደነግጉም በጋራ መግባባት ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ያደረጉ ሀገራትም በርካታ ናቸው፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሀገራት ለምን የከለከሉ ይመስላቹሀል? ጥቅም ስላለው ተመቅኝተው ሕዝባቸው እንዳይጠቀም ፈልገው ነው? እንደዚህ ነው የሚመስላቹህ? በመሆኑም ይሄንን አደርጋለሁ ሀብቶች ናቸውና ለብሔረሰቦች እሴቶች ጥበቃና እንክብካቤ አደርጋለሁ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ፓርቲ ግን አይኖርም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሐሳብ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማዕከል ባደረገ ዓላማ ላይ ብቻ ተመሥርተው እንዲቋቋሙና እንዲወዳደሩ አደርጋለሁ ይሄ ሲሆን ብቻ ነው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠባብነት ሊወጡ የሚችሉት ሥልጣንም ሲይዙ ለፍትሕና ለእኩልነት ትኩረት ሰጥተው ሊንቀሳቀሱ ሊተጉ የሚችሉት፡፡ አለዛ ግን ከላይ አስቀድሜ እንደገለጽኩት ሥልጣን በያዙ ጊዜ እንደወያኔ ሁሉ የሌሎቹን ብሔረሰቦች መብቶችና ጥቅሞች እየረገጡ ተጎዳ ተበደለ ተጨቆነ ተጋደልንለት ሞትንለት የሚሉትን ብሔረሰባቸውን ለመካስ ለመጥቀም ለማስደሰት ብቻ ነው የሚጥሩት እንጂ ሁሉንም ዜጎች በእኩል ተመልክተው የፍትሕንና የእኩልነትን ጥያቄ የሚፈቱ አይሆኑም ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውም ፍትሕና እኩልነትን በማስፈን ላይ አተኩረው ቢሠሩና ፍትሕና እኩልነት ከሰፈነ ግን የብሔረሰቦችን ችግር ጨምሮ የማይፈታ ችግር አይኖርም በብሔር ተመሥርቶ የሚመጣው ግን እያየነው እንዳለነው ባለን ችግር ላይ ሌላ ችግር መጨመር ብቻ ነው ትርፉ ብየ መለስኩ፡፡ ይሄንን ጥያቄ የመለስኩት ግን መሪ የመሆን ፍላጎት አለኝ ብየ ሳይሆን ለሀገሬ ይጠቅማል የምለውን ለማጋራት በሚል ነው፡፡ ለመሪነት የሚያበቃ ምንም ነገር እንደሌለኝ አውቀዋለሁና፡፡ ነገር ግን ከአቶ መለስ የማይሻል ማን አለና? ካላላቹህ በስተቀር ከአቶ መለስና ከመሰሎቹ ግን አንድ ሽ ጊዜ እንደምሻል ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ነጥቦች ዙሪያ ያደረግነው ውይይት በዚህ ተቋጨ ወደ ሚቀጥሉት ነጥቦች ስንሔድ፡-

ክፍል 3

ቀጣዩ የመወያያ ርእስ የነበረው “ለሀገራችን አዋጭ የሆነው የመንግሥት አወቃቀር የትኛው ነው? አሐዳዊ ወይስ ፌደራላዊ? ፌደራላዊ ከሆነስ የአወቃቀሩ መሠረት ምን ይሁን? የብሔረሰቦችን አሠፋፈር ወይስ መልክአ ምድርንና ታሪክን?” የሚለው ነበር፡፡

በፈቃዱ ጀመረ እንዲህም አለ፡- በእኔ እምነት ፌደራላዊ መሆን አለበት፡፡ ፌዴራላዊው የመንግሥት ሥርዓትም መሠረት ሊያደርግ የሚገባው ብሔርን መሆን አለበት፡፡ ብሔር መሆኑ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያትም ብሔሮች ያላቸውን ልዩ ፍላጎት እንደሚመቻቸው እንደፍላጎታቸው በነጻነት ለመተግበር ለማስተናገድ እንዲችሉ ያደርጋልና ነው፡፡ ለምሳሌ አለና ሶማሌዎች መቶ በመቶ ሙስሊሞች ናቸው ክልላቸውን በሸሪአ ሕግ ማስተዳደር ቢፈልጉ የፌደራላዊው የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት በብሔር መሆኑ ይሄንን እንዲያደርጉ መብት ስለሚሰጣቸው ልዩ ፍላጎትን ለማስፈጸም ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥር የፌዴራላዊው የመንግሥት ሥርዓት አወቃቀር ብሔርን መሠረት ያደረገ ቢሆን ጥሩ ነው ብየ አምናለሁ አለ፡፡ በፈቃዱ ይሄንን ሲል ስለ ሸሪአ ሕግና አፈጻጸሙ በዚህ ሕግ በሚመሩ ሙስሊም ሀገራትም ምን ምን ዓይነት ችግሮችን እንደተጋፈጡ አንዳንዶችም እንደተውትና ዓለማዊ (secular) የሆነውን የመንግሥት አስተዳደርን ሥርዓት መምረጣቸውን፤ ይሄንን ሕግ ሥራ ላይ የሚያውሉ ሙስሊም ሀገራት ቢሆኑም ቅሉ በሕጉ መመራት የሚፈልጉ እንዳሉ ሁሉ የማይፈልጉም በመኖራቸው ምክንያትና ሕጉን ሙስሊም ባልሆኑ ዜጎች ሁሉ ለመተግበር ስለሚሞከር ሕጉን ተፈጻሚ ማድረግ ከሰብአዊ መብቶች አንጻር አጠያያቂና አወዛጋቢ በመሆኑ አስቸጋሪ መሆኑን በእነዚህ ምክንያቶች በፈቃዱ ለእነዚህ ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ ሳይኖረው ይሄንን እንዳለ ገመትኩ፡፡

በግንቦት 7 አባልነት ተጠርጥረው ከታሰሩት ወንድሞች አንዱ የሆነውም በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- አሐዳዊው የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት አሁን ጊዜው ያለፈበት ይመስለኛ፡፡ ከዚህ አንጻር የሚያዋጣን ፌዴራላዊው የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ነው፡፡ ይህ አወቃቀር ምንን መሠረት ያድርግ ለሚለው ግን በእኔ እምነት መልክአምድራዊና ታሪካዊ ሁሌታዎችን መሠረት ቢያደርግ የሚሻለን ይመስለኛል፡፡ ብሔርን መሠረት ማድረጉ ግን ችግር ይኖረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላትንም ማለትም የአርበኞች ግንባርንና ደሕሚትን እንዳይዋሐዱና አብረው እንዳይሠሩ ያደረገ ጉዳይ ነው፡፡ የአርበኞች ጉዳይ “ደሕሚት ከጎንደር ተወስደው በሕወሀት ወደ ትግራይ የተከለሉትን ሑመራና ወልቃይት የጎንደር እንደሆኑ በይፋ አምኖ ያስታውቅ” የሚል አቋም በመያዙና ደሕሚትም “በጉዳዩ አቋም ለመያዝ ችግር የለብኝም ነገር ግን ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያቀያይመኛልና ድጋፉን እንዳይሰጠኝ ያደርጋልና አሁን ላይ ይሄንን ላደርግ አልችልም ጊዜ እንስጠው” አሉ ሲል አብርሃ ደስታም ድንገት መስሜት ተገፍቶ “አዎ! እንዴት አድርገው? በጣም አስቸጋሪ እኮ ነው ሕዝቡ እሽ አይልም” ብሎ ተናገረ፡፡ ልጁም ቀጠለና እንደነዚህ ዓይነት ነገሮችን መፍትሔ መስጠት ከቻልን አዋጭው ይሄኛው ነው የሚመስለኝ አለ፡፡

አብርሃ ደስታም ቀጠለና በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲያችን አረና ትግራይ ተወያይተንበት ነበር፡፡ እንደ አቋም የያዝነውም የፌዴራላዊው የመንግሥት ሥርዓት አወቃቀር መሠረት ማድረግ አለበት ብሎ ያመነበት የብሔር አሰፋፈርን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ነው፡፡ እኔ እንደ ሐሳብ መልክአ ምድራዊም ቢሆን ችግር ያለው አይመስለኝም አሁን ባለው ሁኔታ ግን አወቃቀሩ ብሔረሰብን መሠረት አድርጎ ቢዋቀርና በሒደት መልክአ ምድራዊ ቢሆን ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሲል እኔ “ያ ማለት አሁን ሥራ ላይ ያለውን ካርታ ማለትህ ነው?” ብየ ጠየኩት “የግድ እሱን ማለቴ አይደለም” አለ አብርሃ ደስታ፡፡ አሁንም ግልጽ እንዲያደርግልኝ የፈለኩት ጉዳይ ግልጽ አልሆነምና ደግሜ ለመጠየቅ ተገደድኩ “ሑመራን ወልቃይትንና ራያን በተመለከተ ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?” ስል፡፡ እሱም “እኔ ይሄ መሠረታዊ ችግር ነው ብየ አላስብም አጠቃላዩ ሀገራዊ ሁኔታ መፍትሔ ሲያገኝ አብሮ የሚፈታ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ ወልቃይቶችም ሆኑ ራያዎች ወልቃይት ነን ራያ ነን ይላሉ እንጅ አማራ ነን ወይም ትግሬ ነን አይሉም፡፡

ፓርቲያችን ውስጥ በዚህ ጉዳይ ስንወያይ ከመሀላችን አንዱ ምን አለ መሰለህ “አንድነትና መኢአድ የፌዴራል አወቃቀሩ መልክአ ምድራዊና ታሪካዊ ይሁን የሚሉት ከጎንደርና ከወሎ ተወስዷል የሚሉትን መሬት ለማስመለስ ነው እንጅ ይሄ አወቃቀር ሌላ ጥቅም አለው ከሚል እምነት አይደለም” አለ፡፡ እኔ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ከተመሠረተ ይሄ ጉዳይ የሚቸግር አይመስለኝም ሲል እንዴት? አልኩት “ሕዝቡን ወደ የት መከለል እንደሚፈልግ እንዲመርጥ በማድረግ ችግሩን መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል” አለ እኔም የትኛውን ሕዝብ ነው የምታስወስነው? አሁን እዚያ ሰፍሮ ያለው ሕዝብ እኮ በነባሩ ላይ ግፍ የተሞላበት ማጽዳት ከተደረገበትና የተቀረው ደግሞ ተፈናቅሎ እንዲሰደድ ከተደረገ በኋላ ከሌላ ቦታ መጥቶ የሰፈረ ነው፡፡ ያለው ነገር እንዲህ በሆነበት ሁኔታ “ሕዝቡ ይወስን” የሚባለው ነገር ፍትሐዊ ይሆናል? ስለው “በአንድ ሀገር የምናምን ከሆነ እኮ ወደ አማራ መጣ ወደ ትግራይ ሔደ ማለትም የሚያስፈልግ አይመስለኝም” አለ፡፡ በትክክል! አልኩት በአንድ ሀገር የሚያምን ታሪካዊንና መልክአምድራዊን ድንበርን ዘሎ የኔ ድንበር እዚህ ነው ማለት አይኖርበትም ማለት ነው፡፡ ጉዳዩ ግን እሱ ብቻ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የፍትሕ ጥያቄም አለበት አላግባብ ኢሰብአዊ ግፍ ማለትም የዘር ማጽዳት ተፈጽሞባቸው የተፈጁ ቤት ንብረታቸውን ተነጥቀው የተሰደዱ የተፈናቀሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ አንገብጋቢ የዜጎች የፍትሕ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ስለ ፍትሕ እየጮህን ይሄንን ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ ብንል እራሳችንን ውሸተኞችና አስመሳዮች እናደርጋለን፡፡

እንዲህ ስል እዛ የሰፈሩ ወገኖች ወደ መጣቹህበት ሒዱ ይባላሉ ማለቴ አይደለም በእርግጥ ከኗሪው እጅ በግፍ የወሰዱና በግፍ የተነጠቀ ንብረት እንደሆነ እያወቁ ያንን ንብረት የወሰዱት የግፈኞች ተባባሪ ናቸውና በተባባሪነታቸው የሚጠየቁ ይሆናሉ፡፡ የተቀሩት ግን በኢትዮጵያዊነታቸው ሀገራቸው ነውና ውጡ አይባሉም ንብረቱን ግን ለባለንብረቱ የመመለስ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ ለእነሱ ደግሞ ባለቤት የሌለው መሬት ይሰጣቸዋል፡፡ እስከ ሚገባኝ ድረስ ፍትሕ ማለት ይሄ ነው፡፡ መሬቱን ወደ አማራ መጣ ወደ ትግሬ ሔደ አንልም፡፡ ወደ ጎንደርና ወደ ወሎ ተመለሰ ነው የምንለው ይሄንን ማድረግ የግድ ይሆናል፡፡ እንዳልከው በአንዲት ሀገር የምናምን ከሆነ ይሄንን ማድረግ ይቸግረናል ብየ አላምንም፡፡ ለምሳሌ በደርግ ጊዜ የነበረው ካርታ ለሚኖረን የፌደራል አሥተዳደር የክልል መንግሥታት አወቃቀር አድርገን ብንወስደው የሚያመጣው ችግር ምንድን ነው? ስል ጠየኩት “ይሄማ እንዴት ይሆናል? ሕዝቡ አይቀበለውም የደርግ ሥርዓት እንደገና ተመልሶ የመጣበት ነው የሚመስለው አለ” እኔም በደርግ ጊዜ የነበረው ካርታ እኮ አሁንም ይሠራበታል አልቀረም፡፡ በግልጽ ካርታው ባይታይም መንግሥታዊ ተቋማትን ጨምሮ ሕዝቡም አሁንም ድረስ ይገለገሉበታል፡፡ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ፣ አሩሲ፣ ባሌ፣ ከፋ፣ ሲዳሞ ሐረር ወዘተ. እኮ ዛሬም አሉ ይሠራባቸዋል፡፡ ስለዚህ የሌለን ያልነበረን ክለላ ሳይሆን ያለን የሚያውቀውን የሚኖርበትን ነው የምንሰጠው ስለሆነም አንዳችም የሚፈጥረው ችግር አይኖርም፡፡ ስለው አብርሃ ይሄኔ ከመሰላቸት ይሁን ወይም እንዳለውም ተስማምቶት “በቃ ይሄ ተስማምቶኛል” በማለት ስምምነቱን እንደማረጋገጥ እጁን ጨብጦ “ግጭ” በማለት እጁን ወደኔ ሰደደ እጆቻችንን በስምምነት አጋጨን፡፡

ዘለዓለምም የአምሳሉ ሐሳብ እኮ ምንም እንከን አይወጣለትም ጠቃሚነቱም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ነገር ግን ፖለቲካ ማለት ይህ አይደለም አለ፡፡ እኔም አዎ በእርግጥም ፖለቲካ ማለት እንደዚህ አይደለም፡፡ ፖለቲካ ማለት ማጭበርበር ማወናበድ ማምታታት እንደሆነ ተደርጎ ተቆጥሮ ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል በሀገርና በሕዝብ ላይ መቆመር ማለት እንደሆነ አድርገን ከተገነዘብነው ቆይተናል፡፡ ይሄንን በተሳሳተ አቅጣጫ እየነጎደ ያለውን የሀገራችንን ፖለቲካ የመታደግ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የመመለስ ኃላፊነት በዚህ ትውልድ ላይ አለበት፡፡ አስተሳሰቡ መሰበር ይኖርበታል፡፡ በግል መሪዎቻችን ምን ዓይነት ሰዎች ይሁኑ ብለህ ብትጠይቀኝ፡፡ ደግ ቅን ብሩክ ምስኪን ሰው ቢሆኑልን አልልህም፡፡ ታዲያ ምን? ብትለኝ በቢሮክራሲ የተካኑ ሀገር ወዳዶች ሸረኞች ሴረኞች ቆራጦች ቢሆኑ ነው ለሀገር ሊጠቅሙ የሚችሉት ብየ አምናለሁ፡፡ ሸረኛ ሴረኛ ቢሮክራት እንዲሆኑ የምፈልገው እንደ አቶ መለስ የገዛ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያሰቃዩበት እንዲጎዱበት እንዲያጠቁበት ሳይሆን ከውጭና ከውስጥ ከሚመጡ ከሸረኞችና ሴረኞች የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች ጥቃት ሀገርን ሕዝብንና እራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ሴራቸውን ሸራቸውን ማክሸፍ እንዲችሉና የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ እንዲያስችላቸው ነው አልኳቸው፡፡

እኔም መናገር ከፈለጉት ውስጥ ካቀረብኳቸው ጥያቄዎችና ክርክሮች ባሻገር ተራዬ ደረሰና ስለዚህ ሀገራችንን ስለሚያዋጣት የመንግሥት አሥተዳደርና አወቃቀር ስናገር እንዲህ አልኩ፡- እኔ አሐዳዊው የመንግሥት ሥርዓት ጊዜው አልፎበታል ብየ አላምንም የሆነ ሆኖ ፌዴራላዊው የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት የሥልጣን ጥም ያለባቸውን ግለሰቦች በርከት አድርጎ ስለሚያስተናግድና የሀገራችን ፖለቲካም ችግር ላይ የወደቀውና እየተዘወረ ያለው የሥልጣን ጥም ባናወዛቸው ግለሰቦች ስለሆነ ከዚህ አንጻር በርከት ያሉ የርእሰ መሥተዳደሮች ሥልጣን ያለው የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት በመሆኑ እነሱ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ ከመከላከል አንጻር ይጠቅማል ብየ ስለማምን፣ የየ አካባቢው ሕዝብ እምነት የሚጥልበትን ዜጋ እራሱ መርጦ በእሱ የመተዳደር መብትን ስለሚሰጥ፣ ሥልጣን በማዕከል ተጠቅልሎ ተይዞ ለየአካባቢው ከማዕከል የሚሾምበትን አሠራር ስለሚከላከል እኔም የፌደራል አሥተዳደር ሥርዓትን እመርጣለሁ፡፡

አወቃቀሩ መሠረት እንዲያደርግ የምፈልገው የክልል የመንግሥታት አከላለል ግን የብሔረሰቦችን አሰፋፈር ሳይሆን መልክአምድራዊ አቀማመጥንና ታሪክን ነው፡፡ ምክንያቱም የብሔረሰቦችን አሰፋፈር መሠረት አደረኩ የሚለው የወያኔ የክልል አወቃቀር ሀገራችንን ዐይታው በማታውቀው መልኩ በድንበር ጉዳይ ላይ ምን ያህል ብሔረሰብ ከብሔረሰብ እያጋጨ እያፋጀ እንደሆነ የሚታይና የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ያውም ብዙ ድንበሮች ውሳኔ እልባት ባልተሰጠባቸው ሁሌታ ነው ይሄ ሁሉ ችግር የተፈጠረው፡፡ ውሳኔና እልባት ያልተሰጠባቸው ድንበሮች ቢሰጥባቸው ደግሞ የእርስ በእርስ ፍጅቱ ምን ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የብሔረሰብን አሰፋፈር መሠረት ያደረገው የሀገር ግዛት አወቃቀር ሀገራችንን ባለቤት አሳጥቶ ሁሉንም በክልል ድንበር ጉዳይ በመጥመድ ሲቆራቆስ እንዲኖር የሚያደርግና ሀገሪቱን የግጭት የቁርቁስ አውድማ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሁሉም ብሔረሰብ አንዱ የኔ ነው የሚለውን አጎራባቹም መተመሳሳይ የኔ ነው የሚልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይሄንን ችግር በምንም ዓይነት መንገድ መፍታት አይቻልም፡፡ ይሄንን የብሔረሰቦች የእርስ በእርስ የድንበር ግጭቶች ማስወገድ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ አወቃቀሩን ከብሔረሰብ አወቃቀር አውጥተን በመልክአምድራዊና ታሪካዊ ያደረገን የደርግ ጊዜውን ዓይነት አወቃቀር ስንጠቀም ብቻ ነው፡፡ ያኔ ክልሌ የሚለው ጠባብ የአመለካከት አጥር ይጠፋና ሀገሬ የሚለው በቦታው ይተካል፡፡ ሀገር ባለቤት ይኖራታል፡፡ የአንድነት ስሜት ይነግሣል፡፡ የኢትዮጵያዊያን እንጅ የእከሌ ብሔረሰብ የሚባል የሀገር ክልል አይኖርምና የድንበር ግጭት የሚባል ችግር ይጠፋል ይወገዳል፡፡

እዚህ ላይ ሊተኮርበት የሚገባው ነጥብ ሀገሪቱ በመልክአ ምድራዊና ታሪካዊ አወቃቀር ቢትከለልም ብሔረሰቦች እራሳቸውን በራሳቸው የማሥተዳደር መብትንና በቋንቋቸው የመገልገል መብት አይኖራቸውም ማለት አይደለም፡፡ ይሄንን ከማድረግ የሚከለክላቸው ምንም ነገር አይኖርም፡፡ አሁንም እየተደረገ እንዳለው ሁሉ የአንድ ብሔረሰብ አባላት በሌላ ክልል በርከት ብለው ሲገኙ በቋንቋቸው ከመስተናገድ ከመገልገል እንዳልተከለከሉ ሁሉ ማለት ነው፡፡

እናም የሀገራችን የፌደራል ሥርዓት የክልል አወቃቀር እንዲህ ቢሆን ምኞቴ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን በዚህ አጋጣሚ ለአረና ትግራይና ለደሕሚት ላስተላልፈው የምፈልገው መልእክት ቢኖር “የትግራይን ሕዝብ ድጋፍ ያሳጣናል” በሚል በመሬትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮችን ላይ የተሳሳተ አቋም መያዙ ኃላፊነት የጎደለውና ሕዝብን ከስሕተቱ እንዲታረም ዕድል የማይሰጥ ሕዝብን ለመምራት የተዘጋጀ ፓርቲ ሊወስደው ከሚገባው ኃላፊነትና ተጋፍጦ (risk) አንጻር የማይጠበቅ በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት ወይም አቋም ነው የሚባሉ ነገሮችን በርግጥም የትግራይ ሕዝብ እንደነዚህ ዓይነቶችን ከአንድ ሕዝብ የማይጠበቁና አሳፋሪም የሆኑ አቋሞችን ይዞ ከሆነ ሕዝቡ የያዘው አቋም ትክክል እንዳልሆነ ከወዲሁ ካልተጋፈጡትና አቋም ካልያዙበት ወያኔ ከወደቀ በኋላ “አሁን ለጊዜው ከትግራ ሕዝብ ጋር ላለመቀያየም” በሚል ትክክል እንዳለመሆኑ የያዙትን አቋም ሊለውጡ የሚችሉበትን ዕድል እንደማያገኙ ሊያውቁት ይገባል፡፡

ምክንያቱም እነኝህ ፓርቲዎች ሥልጣን ይዘው ማሥተዳደር እንደመፈለጋቸው ወደፊት የሚፈልጉት ሥልጣን ሊያገኙት የሚችሉት በሕዝብ ምርጫ በመሆኑ ትክክል የሆነውን ጉዳይ ሁሉ “የትግራይ ሕዝብ ይህ እንዲሆን ስለማይፈልግ” እየተባለ “ድጋፉን ላለማጣት በዚህ ወቅት አቋም ልንይዝበት አንችልም ከድል በኋላ ግን አይቸግረንም” ብለው በትግል ወቅት ቀጠሮ ይዘውለት የነበረውን ጉዳይ ከድል በኋላ አሁን ጊዜው ነውና ለሕዝቡ እናውጅ ቢሉ በሕዝብ ተመርጠው ሥልጣን ይዘው ለማሥተዳደር ያላቸውን ምኞት ይሄንን ትክክለኛ አቋም በመውሰዳቸው ምክንያት ሕዝቡ ስለሚከፋባቸው በዚህ ምክንያት በሕዝቡ ተመርጠው ሥልጣን መያዝ የሚችሉበትን ዕድል ሊያገኙ ስለማይችሉ ሥልጣኑን ደግሞ ማጣት ስለማይፈልጉ ያኔም ቢሆን “የትግራይን ሕዝብ ያስከፋብናል” በሚል ምክንያት አቋምና ውሳኔ የመውሰድ ዕድሉን አቅሙን ቁርጠኝነቱን ልታገኙ ከቶውንም አትችሉምና መወሰን አቋም መያዝና ሕዝቡንም ማረም ካለባቹህ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነውና አሁኑኑ ወስኑ አቋም ውሰዱ ሕዝቡን አሳምኑ አስተምሩ፡፡ እውነትን ሸሽተን ልናመልጥ የምንችልበት ዕድል ባለመኖሩና አሁን ያለብንን ችግር ዛሬ መፈታት ዛሬ መቋጨት ሲኖርበት ወደ ነገ ከማሻገር ውጪ ጥቅም ስለሌለው ይሄንን ብንረዳና ዛሬ መውሰድ ያለብንን እርምጃ ዛሬ መውሰዱ አማራጭ የሌለው መሆኑን እንዲያውቁ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ በሀገራችን ሊወገድ የሚገባው ክፉ የፖለቲካ ልማድና አስተሳሰብ ቢኖር ይሄ ነው፡፡ ከወዲሁ አክሞ ማዳን ማስተካከል ሲቻል እያደር ሌላ ጠንቅ የሚፈጥርን ጉዳይ በሆድ አሳድሮ ማስታመምና የማመርቀዝ ልማድ መቅረት አለበት፡፡ የማይቀርን ነገር በጊዜ መገላገሉ አይሻልም?

ወደ ውይይታችን ልመለስና ሳጠቃልል ይሄንን አልኩ፡- አሁን እየታየ ያለው የሀገርን እሴቶችና ኢትዮጵያን የአማራ ብቻ አድርጎ መቁጠርና የተቀሩትም እንደማያገባቸው የመቁጠር ስሜት ስር እየሰደደ መጥቷል፡፡ ይሄ ወያኔ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎ እያስፈራራ ለመኖር እንዲያስችለው የፈጠረው “የእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ሰይጣናዊ ሴራ ነው “ኢትዮጵያን ካልክ በአማራ ስር ነህ የራስህ ክልልህ ነው የራስህና ነጻ መሆን ከፈለክ ኢትዮጵያን ሳይሆን ክልሌን በል” እያለ በሕዝቡ ያለውን ወይም የነበረውን የኢትዮጵያዊነትና የባለቤትነትን ስሜት አጥፍቶታል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ነው ጠባብነትን እንዲሰፍን ያደረገው፡፡ ነገር ግን ትክክል እንዳልሆነ ሁሉም ሊያውቅ ይገባል ይህች ሀገር በዚህች ሀገር ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ ናት፡፡ እርግጥ ነው ከአማራ የወጡ ገዥዎች የአሥተዳደሩን ቦታ ይዘው በመቆየታቸው ሀገሪቱ የአማራ እንደሆነች ተደርጎ እንዲቆጠር የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቶ ይሆናል፡፡ ልክ ሩሲያ ከመቶ በላይ ብሔረሰቦች ያሉባት ሀገር ሆና እያለ ሀገሪቱን ከቀድሞ ጀምሮ ሲያሥተዳድር የነበረው የሩስ ብሔረሰብ እንደሆነች ተደርጎ እንደሚቆጠረው ሁሉ ማለት ነው፡፡ በአውሮፓ ሀገራትም እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አለ፡፡ በየ ሀገሩ ያ ሀገር በዚያ ሀገር ላይ ጎልቶ የወጣው ብሔረሰብ እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠር ልማዳዊ አስተሳሰብ አለ፡፡ ነገር ግን በአንድ ሀገር ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ በዚያች ሀገር እንደመኖራቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለዚያች ሀገር ህልውና አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ ሊቀሩ አይችሉምና ሀገሪቱ በዚያች ሀገር ያሉ ብሔረሰቦች ሁሉ ናት፡፡ ይሄንን ማሰብ ነው የሚኖርብን በመሆኑም እራስን ማግለሉ አግባብ አይደለም፡፡

ከዚህ ይልቅስ የሚጠቅመን ሀገሪቱ ያላትን ሀብትና እሴቶች ሁሉ የሁላችንም እንደሆነ አምነን መጠበቅ መንከባከብ ለወደፊቱ ደግሞ የሀገርን ጉዳይ ሁሉ የአማራ ጉዳይ እንደሆነ ቆጥሮ ለአማራ ከመተው እንደ አማራ ሁሉ ለኢትዮጵያ በመቆርቆር፣ የኃላፊነትን ስሜት በመጋራት፣ በባለአደራነት ስሜት መበቃጠል አማራን መፎካከርና ፉክክራችንን እንዲህ በመልካም ነገር ብናደርገው የት በደረስን ነበር! የምናተርፍበት የምንጠቀምበት እንጅ በምንም ተአምር የምንጎዳበት አይሆንምና እንዲህ ማድረጉ ላይ ብናተኩር መልካም ነበር፡፡ ብየ ስል አብርሃ ደስታ ተቀበለና በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ ይገርምሀል በእኛም ፓርቲ ውስጥ ያለ ችግር ነው ያነሣኸው፡፡ ምንም ነገር ሰው ሲናገር “ኢትዮጵያ” የምትል ቃል ጋስገባበት “አይ ወደዛ! ይሄ የአማራ አስተሳሰብ ነው” እየተባለ ሀገር አቀፍ የሆነ ሐሳብ ማንጸባረቅና ማስተናገድ የማይቻል የማይታሰብ ነበር፡፡ አንዴ ግን ስብሰባ ላይ አንድ አባል ተነሥተው “እንደዚህ እንደዚህ ዓይነት ሐሳቦች ሲንጸባረቁ ለምንድን ነው እሱ የአማራ ነው ተው! የምንለው? ኢትዮጵያን ለአማራ ለብቻው ማን ሰጠው? ኢትዮጵያ የኛም ናት!” ብሎ ሲናገር ሁሉም ነበር ያጨበጨበለት፡፡ ከዚያ በኋላ ሰዉ ስለ ኢትዮጵያ በተሻለ ነጻነት ለመናገር ቻለ አለ አብርሃ፡፡

የዞን ዘጠኙ በፈቃዱ የጠየቀኝንና የመለስኩለትን ነግሬያቹህ ልቋጭ፡፡ በፈቃዱ ስለ ክሴ አነሣና ክስ ሲመጣባቹህ ኤልያስ (የዕንቁ መጽሔት ኤዲተር) ምን አለ? እኔ እኮ ዕንቁ ላይ ለአንድ ለሦስት ወር ያህል ኤዲተር ሆኘ ሠርቻለሁ አለኝ፡፡ እኔም ኤልያስ በጣም ነበር የከፋው በተለይ ደግሞ ጽሑፎቸን እንዳይቆርጥ እጫነው ስለነበር ልክ ክሱ እንደመጣ “ተው እያልኩህ አትቁረጥ እያልክ አየኸው አይደል?” ነበር ያለኝ ያው አሁንም ስንገናኝ “አንተ እኮ ነህ ለዚህ የዳረከኝ” ይለኛል በዚህ ምክንያት ጸጸት ተሰምቶኛል፡፡ እንዲያው ፈጣሪን የምለምነው ለሱ ሲል ከዚህ ክስ ቢገላግለን ነው ለኔ ለራሴ አይደለም ስጽፈውም አውቄው ነውና የጻፍኩት፡፡ ስል በፈቃዱ ምን አለኝ “እኔ ብሆን ግን ይሄንን ጽሑፍ አላስተናግደውም ነበር” አለ ለምን? አልኩት “በጽሑፉ ታሪካዊ መረጃዎች ላይ ስለማላምንበት” አለኝ፡፡ በፈቃዱ ኤዲተር ማለት የማያምንበትን ጽሑፍ የሚያስቀር እንዳይወጣ የሚያደርግ ማለት መስሎታል፡፡ እንግዲህ ይሄንን የሚለኝ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ይከበር ብሎ የሚታገል ስሉጥ (አክቲቪስት) ነው ተብሎ ነው እንዲህ እያለኝ ያለው፡፡ ኤልያስም ጽሑፉን ስላመነበት አልነበረም ያሳለፈው ነገር ግን ባያምንበትም ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ ሕገመንግሥታዊ መብት ስለሚያምንና እንደ ጋዜጠኛ ለዚህም ስለሚታገል እንጅ፡፡

የትኛውን ታሪካዊ መረጃ ነው የማታምንበት? ጽሑፉ ያተኮረውና የሚያትተው የጥፋት ኃይሎችን (ወያኔ ኦነግና ሌሎች ተገንጣይ አካላትን) ፀረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጫረስ የሚያሴሩትን የጥፋት ሴራ ነው፡፡ ማለትም በሔጦሳና በጨለንቆ ያስገነቡትን የፈጠራ ወሬያቸው ሐውልትን ማለቴ ነው፡፡ በእርግጥ የጥፋት ኃይሎች የኦሮሞን ሕዝብ ስም ነውና እየተጠቀሙ ያሉት በቀጭኑም ቢሆን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ይገናኛል፡፡ ነገር ግን ጽሑፉ የሚመለከተው በኦሮሞ ሕዝብ ስም የሚነግዱትን የጥፋት ኃይሎች እንጅ የኦሮሞን ሕዝብ ስም እንደማይመለከት አበክሬ አሳስቤአለሁ፡፡ ዐፄ ምንሊክ አደረጉ እያሉ የሚያወሩት ወሬ ፈጠራ መሆኑን ከዚያ ውጭ ግን የወሰዱት እርምጃ ትክክል እንደነበር ገልጫለሁ፡፡ ስል እሱ ግን ያግፍ ተፈጽሟል ብሎ እንደሚያምን ነገረኝ በጣም ገረመኝና መረጃህ ምንድን ነው ስል ጠየኩት በዝምታ ተውጦ ቆየና በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ አንድ አባባል አለ “በጡት ቆረጣው ጊዜ” የሚባል አባባል አለ አለኝ እኔም ይሄ አባባል የጥፋት ኃይሎች ነገሩን ትውፊታዊ መረጃ ያለው ለማስመሰል የሚጠቀሙባት አባባል ነች፡፡ ይህን ድርጊት ፋሺስት ጣሊያን ለነበረው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የማፋጀት ፋሺስታዊ ሴራ ከፋሺስት ጣሊያን ተውሰው ድርጊቱ በዐፄ ምኒልክ ዘመን ተፈጽሟል የሚሉት የጥፋት ኃይሎች ቢያንስ እንኳን ፈጠራው ወይም ተረቱ እውነት እንዲመስልላቸው ቃላቸውን አንድ ማድረግ እንደነበረባቸው ዘንግተውታል አንደኛው “የአካባቢው ሕዝብ በዓል ለማክበር በተሰበሰበበት ወቅት ነው ይህ ግፍ የተፈጸመባቸው ሲል ሌላኛው በጦርነቱ ወቅት ይላል ሌላኛው ደግሞ ጦርነቱ ከተፈጸመ በኋላ ለእርቅ ብለው ጠርተው ሰብስበው ነው ይላል” ይህ ድርጊት እውነት ቢሆን ኖሮ ዘመኑ ቅርብ ከመሆኑ የተነሣና ታሪክ ጸሐፍትም የዚያን ዘመን ኩነት በዝርዝር እንደመጻፋቸው መጠን ቢያንስ ጦርነቱን ከጻፉት ከውጪ ታሪክ ጸሐፊያን ዕይታ ባላመለጠም ነበር፡፡ እነዚህ የውጭ ጸሐፍት ግን ጦርነቱ የነበረውን ገጽታ ግነት ባልተለየው ቅኝትም ቢጽፉም ቅሉ በሔጦሳም ሆነ በጨለንቆ የጥፋት ኃይሎች ተፈጸመ ብለው የሚያወሩት ተረት ተፈጸመ ብለው አልጻፉም አልተናገሩም፡፡ በጦርነቱ የነበረውን ሁኔታ ግን ጽፈዋል፡፡

እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሌላው ልብ ያላሉት ጉዳይ ቢኖር ይሄንን ጥፋት ፈጸመ የሚሉት የዐፄ ምኒልክ ጦር ዋና አበጋዝ ራስ ጎበና ዳጬ እንደነበሩና ሌሎችም የኦሮሞ ተወላጆች የጦሩን ከፍ ከፍ ያለ ሥልጣን በያዙበት ሁኔታ ከተራው ተዋጊ ጦር ከፊሉም የኦሮሞ ተወላጅ በነበረበት ሁኔታ ነው እንግዲህ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ከጠላት ፋሽስት ተቀብለው እውነት ይመስልልናል ለዓላማችን ይጠቅመናል ብለው ይሄንን ተረት የሚያወሩልንና የጥፋት ሐውልት ገንብተው ሕዝብን ለማሳሳት የሚጥሩት፡፡ የጥፋት ኃይሎች የክፋት ልክ እንግዲህ እዚህ ድረስ ነው፡፡

ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በቀጭኑም ቢሆን ይገናኛል ያልኩህ “የኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵጵያ ውስጥ የገባው በ16ኛው መቶ ክ/ዘ ከግራኝ አሕመድ ወረራ በኋላ ነው የማንን ሀገር ነው የምትገነጥሉት? የቅርብ ጊዜ እንግዶች መሆናቹህን የግድ ማስታወስ ይኖርብናል እንዴ! ከዐፄ ገላውዴዎስ ጋር ያደረጋቹህትን ውል አስቡ እንጅ” የሚል ቃል አለ እሱ ይመስለኛል ብዙ ሰዎችን ያስቆጣው የጥፋት ኃይሎችም ሕዝብን ለማስቆጣት የተጠቀሙበት ይሄንን ጠቅሰው ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ ታሪካዊ መረጃ እኔ የፈጠርኩት ሳይሆን በትውፊታዊ መረጃና የተሟላ የሀገሪቱ ታሪክ በየቅጽ በተጻፈባቸው መጻሕፍት ሁሉ ተጽፎ ያለ ታሪክ ነው፡፡ ከነሱም ውስጥ መጥቀስ ቢያስፈልግ የአቶ ይልማ ደሬሳ “የኢትዮጵያ ታሪክ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን” የአቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ልብነድንግል እስከ ዐፄ ቴዎድሮስ እና የግራኝ አሕመድ ወረራ” የአለቃ ታየ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ” የአቶ በላይ ግደይ “አክሱም” ከነዚህ ሁሉ ደግሞ የሚልቀው የአባ ባሕርይ “የኦሮሞዎችን ታሪክና አገባብ” የጻፉበት መጽሐፋቸው ናቸው ስል በፈቃዱ የአባ ባሕርይ የሚባለው መጽሐፍ ፈጠራ ነው የተጻፈውም በዐፄ ምኒልክ ዘመን ነው፡፡ አለኝ በፈቃዱ በጣም እየገረመኝ መጣ ከወያኔ የጥፋት ስብከት ሰለባዎች አንዱ እንደሆነም ተገነዘብኩ፡፡

እነዚህ ሰለባዎች ከፊሎቹ ከመረጃ እጥረት የተነሣ የወያኔ የፈጠራና የጥፋት ስብከቶች እውነት መስሏቸው የሳቱ ናቸው፡፡ እንደበፈቃዱ ያሉት ደግሞ እያወቁ ነገር ግን በወያኔ የፀረ ኢትዮጵያና የጥላቻ መርዘኛ መርፌ ተወግተው መርዙ የመረዛቸው ደግሞ አሉ፡፡ በፈቃዱ ቀጠለ ኦሮሚያ ከዐፄ ምኒልክ በፊት የኢትዮጵያ ግዛት አልነበረችም አለ፡፡ ዐፄ ምኒልክ ናቸው የቀላቀሏት ይሄም አግባብ አይደለም እኔ ኦሮሚያን ወደ ኢትዮጵያ የመቀላቀሉን ጉዳይ የማየው ልክ ኬንያ ኢትዮጵያን ወደ ራሷ ልቀላቅል ብትል እንደሚሰማኝ አግባብ ያለመሆን ያህል ነው አለ፡፡ ይሄ አባባሉ እጅግ ነበር የገረመኝ ስሉጥ (አክቲቪስት) ነው ብየ አስበው ከነበረ ሰው በዚህ ደረጃ የፀረ ኢትዮጵያና የጥፋት ኃይሎችን ሐሳብ ይጋራል ብየ እንዴት ልጠብቅ እችላለሁ? በፍጹም እኮ ከነሱ አልተለየም፡፡ በኋላማ ከእስር እንደወጣሁ ስሰማ የእሱ የቅርብ ጓደኛው የሆነችው የዞን ዘጠኟ ሶሊያና ገ/ሚካኤልም የጁሀር አድናቂና ደጋፊ እንደሆነች ገልጻ “Because I’m Oromo” የሚል ዘመቻ ቀስቅሳ እንደነበረ ስሰማ ልጆቹን አናውቃቸው እንደነበረ ተረዳሁ፡፡ የሌሎቹን አባሎቻቸውን አስተሳሰብ ግን አላውቅም፡፡

ለማንኛውም ለበፈቃዱ የኦሮሞ ሕዝብ ከዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በየዘመኑ ለዚህጭ ሀገር ነጻነት መሥዋዕትነት ሲከፍሉ የኖሩ መሆናቸውን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል ሳይሆኑ ይሄንን እንዳላደረጉ በኋላ ላይ ግን በመንግሥት ላይ እየፈጠሩት የነበረው ጫናና ጥቃት እየበዛ ሲመጣ ሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት መቀመጫውን ከሸዋ ወደ ጎንደር ማዛወሩን ተከትሎ በኋላም በዘመነ መሳፍንት ተፈጥሮ በነበረው ክፍተት አካባቢው ተዘንግቶ መቆየቱን ዐፄ ምኒልክም የዘመቱት ይሄንን የተዘነጋ የአባቶቻቸውን አካባቢ መልሶ ለማቅናት እንደነበር ኢትዮጵያ ግን ግዛቷ በዚህ በጓሯችን ብቻ የተወሰነ እንዳልነበር እስከ የቻይና የባሕር ጠረፍ ድረስ እንደነበር፡፡ በምዕራብ ደግሞ እስከ አትላንቲክ ውቅያኖስ እንደነበር የቀድሞ የአውሮፓ ሀገራትን የዓለም ካርታ ቢያይ አትላንቲክ ውቅያኖስን ከሁለት ቆርጦ ደቡቡን ክፍል የኢትዮጵያ ውቅያኖስ ብሎ እንደሚጠራው፡፡ የሳባን ታሪክ ናይጄሪያ ሔዶ ቢጠይቅ ናይጄሪያ ግዛቷ እንደነበረ እንደሚነግሩት፡፡ እንዲህ ኃያልና ግዛቷም ሰፊ የነበረች ሀገር እየተከፈለች እየተከፈለች መጥታ አሁን ያላትን የቆዳ ስፋት ብቻ ለመያዝ እንደተገደደች ይሄንንም አሁን በእኛ ዘመን እንኳ ኤርትራ ተገንጥላ ያየውና ከሱም ማረጋገጥ እንደሚችል፡፡ በመሆኑም ጭራሽ ኦሮሞዎች የሰፈሩበት አካባቢማ የኢትዮጵያ ለመሆኑ ሊጠራጠር እንደማይገባው ኦሮሚያ የሚባለው አይደለም አልፎ ገሙጎፋ ድረስ ቢሔድ 2500ዓመት ያህል ዕድሜ ያላቸው ደብሮች እንዳሉ፡፡

አባ ባሕርይም የፈጠራ ገጸ ባሕርይ ሳይሆኑ የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሊቅ እንደነበሩ እኒህ ሰው አሁን በጠቀስኩልህ ገሙጎፋ ብርብር ማርያም ከሚባል ደብር የነበሩና በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው ወደ ሸዋ መተው የነበሩ መሆናቸውን፡፡ ከጻፏቸው የታሪክ መጻሕፍት በተጨማሪ ከአራት በላይ የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን እንደጻፉ ስለ ኦሮሞዎች አመጣጥ በእጃቸው የጻፉት የብራና መጽሐፍ በሎንደንና በቪዬና እንደሚገኝ ኢኖ ሊትማን በጀርመንኛ ኢኛሲዬ ጉዪዲ ወደ ጣሊያንኛ እንደተረጎሙት በኋላ ላይም ኮንቲ ሮሲኒ አባ ባሕርይ ከጻፉት የዐፄ ሠርፀ ድንግን ዜና መዋዕል ጋር አድርጎ ወደ ፈረንሳይኛ መተርጎሙን፤ ዐፄ ልብነ ድንግል ባቀረቡላቸው የእርዳታ ጥሪ መሠረት በዚያ ወቅት ከፖርቱጋል ጦር ጋር መጥቶ እዚህ የነበረውና ከዐፄ ልብነ ድንግል ጋር በተዋዋልኩት መሠረት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ካቶሊካዊት ትሁን እኔም ጳጳስ ካልሆንኩ በማለቱ ከዐፄ ገላውዴዎስ ጋር የተጣላው ቤርሙዴዝ በሀገሩ በጻፈው በመጽሐፉ “የኦሮሞዎች ሀገራቸው ሞጋዶክሶ (ሞቃዲሾ) ጎን ነው” በማለት መናገሩን፡፡ በመግለጽ አባ ባሕርይን ፈጠራ ናቸው ሌሎቹህ ታሪክ ጸሐፍትንም ደብተራ ማለት ምን ማለት እንደሆነና ያለውን የእውቀት ስፋት ምላትና ጥልቀት ባለማወቅ በድንቁርና ድፍረት ደብተራ ምንትስ እያሉ በአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለተለያዩ የጥናት ዘርፎች (Disciplines) ዋነኛ ግብአት የሆኑትን መጻሕፍቶቻቸውን ተቀባይነት ለማሳጣት በማናናቅ የሚዋትቱ ገልቱ የጥፋት ኃይሎች ተዋንያን መሆናቸውን ነግሬዋለሁ ከገባው፡፡ ነገር ግን ወገኖቸ ከዚህ እስሬ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ወያኔ ከባድ ሥራ እንደሠራና ምን ያህል ትውልዱን እንደመረዘው በጣም ከባድ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀን ነው የተረዳሁት፡፡ ነገር ግን ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይመስለኝም ወያኔ ውሸት ይዞ ይሄንን ያህል የተደመጠና የተሳካለት ዕድሉን ካገኘ እውነት ለያዘው ደግሞ ቀላል እንደሚሆን አያጠራጥርምና፡፡

ያለው የጎሳ ፖለቲካ ሁሉም ታሪክን በታሪክነቱ እንዲያውቀው አለመፍቀዱ ከታሪክ እውነታ ልናገኝ የምንችለውን መግባባት አሳጥቶናል፡፡ ይህም በሀገርና በሕዝቧ ህልውና ላይ ከባድ አደጋን ጋርጦ ይገኛል፡፡ ታሪክ እውነታ ነው፣ ታሪክ ዳኛ ነው፣ ታሪክ ሽማግሌ ነው፣ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ለመሸፈጥና መርዝ ለመዝራት ስለማይመች በተለያዩ አግባብነት በሌላቸው ምክንያቶች ዳኛ ሽማግሌ እውነት ምስክር የሆነውን ታሪክ ካስወገድን በምን እንድንግባባ ይጠበቃል?

በነገራችን ላይ ይሄንን ታሪክ በብዙኃን መገናኛ ስገልጽ እኔ የመጀመሪያው ሰው አይደለሁም፡፡ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በፊት የሕወሀቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ለሕዝብ በብዙኃን መገናኛዎች ተናግረውታል፡፡ እሳቸው ሲናገሩት ትክክል እኔ ስናገረው ስሕተት እሳቸው ሲናገሩት መብት እኔ ስናገረው ወንጀል ሊሆን የሚችልበት ምንም ሕጋዊ አግባብ የለም፡፡ ይሄንን መናገሩ ወንጀል ከሆነ አቶ መለስ ኦሮሞዎችን “በ16ኛው መቶ ክ/ዘ ከማዳጋስካር ነው የመጣቹህት አርፋቹህ ተቀመጡ” በማለታቸው በዚህች ሀገር ለሕግ የበላይነትና ለፍትሕ የቆሙ ዐቃቢያነ ሕግ ካሉ አቶ መለስም መከሰስ ነበረባቸው፡፡ ይህ የሚያረጋግጠው ሥርዓቱ ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ በሚለው ብሂል የባለገ መሆኑን ያለበትንም የአሥተዳደር ብልሹነትና አንባገነንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በምርመራ ሰዓት ከፖሊስ እንደተገለጸልኝ “መጀመሪያ በጅማ ዩኒቨርስቲ የተጀመረው የተማሪዎች ረብሻ በኦሮሚያ ክልል ባሉ ዩኒቨርስቲዎችም ተማሪዎቹ በመደዋወል ረብሻው እንዲቀሰቀስ ያደረጉት ይሄ ያንተ ጽሑፍ በቀሰቀሰው ቁጣ ምክንያት ነው” ተብሎ ከተገለጸልኝ ቀን ጀምሮ ነገሩ እንደዜጋ በእጅጉ አሳስቦኛል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ መቶ በመቶ እርግጠኛ ሆኘ ልናገረው የምችለው ይህ ጽሑፍ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንን፣ ለሀገራችንና ለሕዝባችን ተቆርቋሪ የሆነን፣ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሸፍጥ የሌለበትን፣ ለሀገርና ሕዝቧ ጥፋት የማይመኝን ማንንም ዜጋ ቅንጣት ታክል የሚያስቆጣ፣ የሚያበሳጭ፣ የሚያናድድ፣ የሚያስከፋ አንድም ነገር የለበትም፡፡ የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ህልውናና ደህንነት የማይሹ የማይመኙ ለጥፋቷ ተግተው የሚሠሩ የሚያሴሩና የሚሸርቡ በጥፋት ኃይሎች የተማረኩ ቅጥረኞችን ግብረአበሮችንና ደጋፊዎችን ግን ጽሑፉ በእርግጥም ያስቆጣል ያበሳጫል ያናድዳል ያስከፋል፡፡

ተፈጸመ!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እጅግ ደማቅ በመሆነ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት አረንጓዴ ፤የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቢጫ፤ የክልል ዞን ተወካዮች ቀይ ቲሸርቶችን በመልበስ ለጉባኤው ድምቀት ሰጥተውታል፡፡

የአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ እጅግ ደማቅ በመሆነ ሁኔታ እየተካሄደ ነው። የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት አረንጓዴ ፤የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቢጫ፤ የክልል ዞን ተወካዮች ቀይ ቲሸርቶችን በመልበስ ለጉባኤው ድምቀት ሰጥተውታል፡፡
ዛሬና ነገ በሚደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ምርጫ ቦርድ በድርጅቱ ደንብ ላይ የኮረም ቁጠር ይጠቀስ የሚል ጥያቄ በመቅረቡ፣ የቀረበው ጥያቄ ከሕግ ውጭ ቢሆንም ( ደርጅቶች የሚተዳደሩበትን ደንብ ምን መልክ መኖር እንዳለበት የሚወስኑት፣ እነርሱ እንጂ ምርጫ ቦርድ ባለመሆኑ) ፣ የደንብ ማሻሻያ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዋናነት ግን በምርጫ ዘመቻው ዙሪያ ሰፊ ስልጠና እንደሚደረግም ታወቋል።
ከትግራይ፣ ከአፋር፣ ከቤኔሻንጉል፣ ከወላይታ፣ ከሲዳማ ፣ ከጉራጌ እያለ በደቡብ ካሉ በርካታ ዞኖች፣ከጎንደር፣ ከጎጃም ፣ ከወሎ፣ ከወለጋ፣ ከአርሲ፣ ከሐረርጌ.. ከመላው የአገሪቷ ክፍሎች ኢትዮጵያዉያን ለለዉጥ፣ ለነጻነት ተሰባስበዋል። ጉራጌው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ ወላያታው፣ አፋሩ ፣ ቅልቅሉ በስብእናዉና በኢትዮጵያዊነቱ፣ በአንድ ድንኳን ሥር ስለሃገሩ ሁኔታ ተሰባስቦ እየተመካከረ ነው።

Millions of voices for freedom – UDJ

የአንድነት ብሄራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አበበ አካሉ ንግግር እያደረጉ .....ለታሰሩት ጀግኖቻችን ህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የጠራው ጠቅላላ ጉባኤ የተጀመረ ሲሆን ተሳታፊዎች የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት አረንጓዴ ፤የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቢጫ፤ የክልል ዞን ተወካዮች ቀይ ቲሸርቶችን በመልበስ ለጉባኤው ድምቀት ሰጥተውታል፡፡

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አርብ (03/04/07) ጠቅላላ ጉባኤውን ያደርጋል፡፡ ፓርቲው ከዚህ ቀደም በታህሳስ 19/20/2007 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን አመት ሳይሞላ ሌላ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ለምን እንዳስፈለገ የጉባኤ ጠሪ ኮሚቴ የሆኑትን አቶ አስራት ጣሴን አነጋግረን ነበር፡፡ አቶ አስራት እንዳብራሩት በታህሳስ 2006 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ ቦርድ ማብራሪያ ጠይቆ ነበር፡፡ አቶ አስራት በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ማቋቋሚያ አዋጅ 573/2000 መሰረት ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ማብራሪያ መጠየቅ እንደሚችል ገልፀው በሀምሌ 25 ቀን 2006 ዓ.ም በፃፈው ባለ ሶስት ገፅ ደብዳቤ ዘጠኝ ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን አቅርቦ ነበር፡፡ by MINILIK SALSAWI

10698475_829409667117784_3680643737158512454_n

አንድነት ፓርቲ በበኩሉ ሀምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ለተጠየቁት ጥያቄዎች ማብራሪያ ላከ፡፡ ከተላከው ማብራሪያ በመነሳት ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ጥያቄዎቹን ወደ 6 ዝቅ አደረገ፡፡ ፓርቲው በበኩሉ ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም ለተጠየቁት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጠ፡፡ ከዚያ በመቀጠል ምርጫ ቦርድ ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ሶስት ማብራሪያ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ጥያቄዎች ያቀረበ ሲሆን ፓርቲውም ህዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም ማብራሪያ ሰጥቶባቸዋል፡፡

5

ለአሁኑ ጠቅላላ ጉባኤ መጠራት ምክንያት የሆነው ህዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም ወደ አንድ ወርዶ በምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ ነው፤ ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ ቁጥሩን እንዲገልፅ የተጠየቀበት፤ ፓርቲው የጠቅላላ ጉባኤ ቁጥሩ 320 መሆኑን ገለፀለት፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ይህ ቁጥር ታህሳስ 19 እና 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው ጉባኤ በተሻሻለው በደንብ ባለመካተቱ ተካቶ ይቅረብልኝ ሲል ጠየቀ፡፡ በዚህ ሁኔታ በፓርቲው ደንብ መሰረት የጠቅላላ ጉባኤ ቁጥር መወሰን የሚችለው ራሱ ጉባኤው በመሆኑ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንዳስፈለገ አቶ አስራት ጣሴ ገልፀውልናል፡፡
አቶ አስራት በመጨረሻ ባስቀመጡት ሀሳብ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ሲደርስ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ መጠየቁ እኛን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ቢሆንም ህጋዊ መሰረት ግን አልነበረውም ብሏል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በደንቡ ላይ የጠቅላላ ጉባኤውን ተሳታፊ ቁጥር የወሰነው ብቸኛው ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡

UDJ general meeting 1

– See more at: http://satenaw.com/amharic/archives/2928#sthash.lZ40ReUG.dpuf