Archive | December 29, 2014

“ኢትዮጵያን እናድን”

ወ/ዮሐንስ  ቢክሰኝ  ሀ/ልዑል – ከ ጀርመን

ኢትዮጵያ ሀገራችን  ከማን ፣ ከምን ነው የምናድናት ? በርግጥ ችግር ውስጥ ናት ? እነዚህ ጥያቄዎች ለተለያዩ የሀገራችን ዜጎች  ቢቀርብ መልሱ ሁለት ዓይነት ነው የሚሆነው ። በጣት ለሚቆጠሩ የስርዓቱ ተጠቃሚዎች እና ባለስልጣናት እንደዚህ  አይነት ጥያቄዎችን የሚያነሳ ሰው ወይም ድርጅት አሸባሪ ፣ ፀረ  ሰላም ፣ ፀረ ዲሞክራሲ ፣ ፀረ ልማት እና ወዘተ በማለት  ያስፈራራሉ  ።  ለተቀረው የህብረተሰብ ክፍል እኔን ጨምሮ አዎ ርግጥ ነው  ሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ ናት ። ከየትኛውም ጊዜ በከፋ መልኩ ሀገራችን እና ዜጎቿ በወያኔ አገዛዝ ስር ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ የሆነ የሰባዓዊ መብት ረገጣዎች ፣ስደት ፣እስር ፣የኑሮ ውድነት ፣ ግርፍት እናወዘተየተባባሰባት ሀገር ሆናለች ።

በዚህ ጽሁፌ በወያኔ አገዛዝ በ ሀያ ሶስት ዓመታት  ውስጥ  የተደረጉቱን  የሰባዓዊ መብት ረገጣዎች ፣ስደት ፣እስር ፣የኑሮ ውድነት ፣ ግርፍት እናወዘተ መዘርዘር  አላማዬ አይደለም ፤ ምክንያቱም  የወያኔ በደል እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ ተፅፎ የሚያልቅ አይደለም ።

በወያኔ አገዛዝ  ሁሌም ምርጫ በመጣ ቁጥር ሽብር አለ ዜጎችን ማሰቃየት አይቀሬ ነገር ነው ፤ በስራቸው የማይተማመኑ የስርአቱ ባለስልጣናት  የህብረተሰብ ተቀባይነት ስለሌላቸው  እና ስልጣንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማስረከብ  ስለማያውቁ እና ስለማየፈልጉ  በትግል ሜዳ ላይ ያሉ ዜጎችን የስቃይ በትር ያሳርፉባቸዋል ። በቅርቡ እየሆኑ ያሉትን ግድያዎች፣የጅምላ እስሮች ፣የሰባዓዊ መብትረገጣዎች መጥቀሱ ማሳያ ነው  ። መሳሪያ ያልታጠቀን ዜጋ በሰላማዊ መንገድ ልታገል ስላለ መግደል ፣   ማሰቃየት መልስ ይሆናል ትላላቹ ?

በርግጥ ይኼ የወያኔ መንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ አይደለም ። የሚገርመው ሁሌም ከስልጣናቸው እና ሀገርን ከመዝረፍ የሚያደናቅፋቸውን ግለሰብ እንዲሁም ድርጅት የሚሰጡት ተለጣፊ ስሞች አለማለቃቸው ነው።አሸባሪ ፣ ፀረ  ሰላም ፣ ፀረ ዲሞክራሲ ፣ ፀረ ልማት እና ወዘተ።ስለሆነም እኔም በዚህ ጽሁፍ ምክንያት የነዚህ ስሞች ባለቤት ነኝ ፤ በሰላማዊ መንገድ መታገልም የተለጣፊ ስሞች ባለቤት ያደርጋል ፤ ያስቀጣል ያስገድላል በወያኔ ስርአት  ።

በግልፅ ቋንቋ ሳልናገር የማላልፈው ነገር ቢኖር ሰላማዊ ታጋይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መታግሉ ዋናው ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሀገሩ ሲፈልግ የነበረው ፣ዛሬም ነገም የሚፈልገው እና የሚመኘው ሰላም የሰፈነባት ፣ ልማትዋ የተረጋገጠባት፣በዲሞክራሲያዊ አካሔድ የምትምራ እና ከአሸባሪ መንግስት የጸዳች ሀገርን ነው ።

ethiopian_terrorists-300x225

በቅርቡ ታስሮ ከነበረ ሰላማዊ ታጋይ የፍርድ ቤት ልምድ ካነበብኩት ውስጥ መጥቀስ ወደድኩ ፤ በጅምላ ከታሰሩ ሰላማዊ ታጋዮች መካከል ለዳኛዋ ባሰሙት አቤቱታ የታሰሩበት ሁኔታ ጤናቸውን ስላዛባው ህክምና ያገኙ ዘንድ አቤት ይላሉ ። ዳኛዋም በመልሳቸው ወደ ፖሊሶቹ ዘወር በማለት “ታሳሪዎቹ የጠየቁትን ህክምና እንዲያገኙ አድርጉ ለእናንተም ለመቅጣት እንድትችሉ በህይወት ይቆይላቹ” በማለት ነበር የተናገሩት ።ልብ በሉ እስረኛ በህይወት መቆየት ያለበት ቅጣት ለመቀበል ብቻ ነው  ። በርግጥ እኚህ ዳኛ የስርአቱ ነጸብራቅ ናቸው ፤ ከዝንብ ማር አይጠበቅም ።ስርአቱ የፈጠራቸው ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው ፤ መሪ ነን የሚሉ ተመሪዎች ንግግራቸው ፣ድርጊታቸው ወርዷል ከመሪ አይጠበቅም ፤ እንኳን ለመምራት ለመመራትም አይሆኑም አይችሉም ። በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስተሩ ወራቤ ከተማ የተመሰረተችበትን አስርኛ አመት ለማክበር ባገኙት መድርክ በመጠቀም የተለመደ አሉባልታቸውን አውርተዋል ። በዚህ አሉባልታም ስደተኛ ኢትዮጵያውያውንን ገረድ ፣ዱቄት ለማኝ ፣ ኮንቴነር ውስጥ የሚኖሩ እና የሰው መኪና እየተደገፉ ፎቶ የሚነሱ  ብለዋል የሚገርመው አለማፈራቸው ነው፤ እንዴ ? ሀገሩ ላይ ስራአቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት መኖር ያልቻለ ዜጋ በስደት በሰው ሀገር ገረድ ቢሆን ቢለምን ውጪ ቢያድር ብሎም ኮንቴነር ውስጥ ቢኖር ምን ይገርማል ? ለዚህ ሁሉ ችግር ተጠያቂው ማን ነው ? በኔ ምልከታ በስደት የሚገኘው ዜጋ ለወያኔ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ከነበረው በበለጠ ሁኔታ ፈተና እንደሆነባቸው ያሳያል።

በመጨረሻም ፦

የወያኔአገዛዝማብቃት እንዳለበት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማለቴ ከጥቂት የስርአቱ ተጠቃሚዎቹ በቀር የሚስማሙበት ነው ።ኢትዮጵያ ሀገራችንእናድን !አንድ ሁነን በአንድነት ሰርአቱን በቃህ እንበለው ፤ ከኛ ውጪ ሌላ ሰው ሌላ ዜጋ ይኼን ስርአት በቃህ ሊለው አይችልም ።በቃህ እንበለው በአንድ እጅ አይጨበጨብም ።

ሰላም!