Archive | February 4, 2015

የአንድነት ፓርቲ አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በወሰኑብን ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ተነጥቀናል ያሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት› በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስታወቁ፡፡

udj-blue

በእነ በላይ ፍቃዱ አመራርነት አንድነት ፓርቲን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ዛሬ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከቀድሞ ፓርቲያቸው አንድነት ጋር የፕሮግራምም ሆነ የስትራቴጂ ተመሳሳይነት ወዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
መግለጫውን የ”ቀድሞው አንድነት ፓርቲ” አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔው አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፈረደኝ እንዲሁም የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ሌሎችን በመወከል ሰጥተዋል፡፡
“የምናምነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላማዊ ትግል ለመምራት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ብቁ ነው ብለን በማመን ፓርቲውን ተቀላቅለናል” ብለዋል በመግለጫው ላይ የተወከሉት አዲሶቹ የሰማያዊ አባላት፡፡
በዚህ መሰረትም በርከት ያሉ አመራሮችና አባላት በይፋ የሰማያዊ ፓርቲ የአባልነት ፎርም ሞልተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ወደ ሰማያዊ ቢሮ ባቀኑበት ወቅት፤ ፖሊስ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ በመግባት “በሰማያዊ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ ሰለሰማን ነው” በሚል ለፓርቲው አመራሮች ጥያቄ ማቅረባቸውን ከስፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ ሚዲያ
ዮናታን የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደግሞ በዚህ ጉዳይ የሚከተለው ብሏል።

ትላንት አንድነት አፈረሱት ሲባል ሊጨልም ነው ያልነው ተስፋ ዛሬ ደግሞ አንድነቶች ግርርርር ብለው ሰማያዊን ሲቀላቀሉ፤ ማንሰራራት ጀመሯል። (የፎቶ አስተያየት በ-አበበ ቶላ ፈይሳ)

ዛሬ ታሪካዊ ቀን ነው
በግሌ ውህደትን ሲገፉ ከነበሩት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ቀደም ባሉ ጊዜያትም ይህንኑ ሀሳቤን አብራርቻለሁ፡፡ እርግጥ የኔ ምኞትና ትልም አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲነታቸውን እንደያዙ በመተባበር ስርዓቱን የመቀየር ትግል ቢያካሂዱ ነበር፡፡ በኔ እምነት ለሀገራችን ዘመኑን የዋጀ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱት በህዝብ ተቀባይነት ያላቸው ፓርቲዎች መሆናቸው ለወደፊቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ እና ህዝብን በንቃት የሚያሳትፍ የፖሊሲ እና መሰል ክርክሮችን በፉክክር እያካሄዱ የዲሞክራሲን መርህ በሀገራችን እንዲተገበር ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋልም ብኜ አምን ነበር፡፡
የሁኔታዎች አስገዳጅነት እና የፖለቲካው ተለዋዋጭነት ግን ይህን ትልም መና አድርጎታል፡፡ አንድነት ለትግስቱ አወሉ ተላልፎ ሲሰጥ እጅግ ያዘንኩት አንዱም ምክንያቴ ይኸው በውስጤ የነበረው ምስል አብሮ በመፍረሱ ነው፡፡ ከነበሩኝ ስጋቶች ዋነኛው ደግሞ አንድነትን የመሰለ ሰፊ መዋቅርና የህዝብ ድጋፍ ያለው ፓርቲ እንደው ዝም ብሎ ‘ተበትኖ ሊቀር ነው’ የሚል ቁጭትም ይዞኝ ነበር፡፡
ግና – ነገር ሁሉ ለበጎ ነው እንዲሉ በክፋት እና ሴራ ፓርቲያቸውን የተነጠቁት የአንድነት አባላት(በክፍላተ-ሀገራትም ይሁን በአዲስ አበባ) ትግሉን ትተን ወደቤታችን አንገባም በማለት መወሰናቸው፤ ወደ ሰማያዊም መቀላቀላቸው ቁርጠኝነታቸው አረጋጧልና በይፋ ክብር ልሰጣቸው እወዳለሁ፡፡ በሰላማዊ ትግል አንዱ በር ሲዘጋ ሌላ ማስከፈት፣ እየወደቁ መነሳት ያለና የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህን አውቆ ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መንቀሳቀሱ ደግሞ በሳልነት ነው፡፡