Archive | April 16, 2015

የምሥራች! የአንድ ደሮ ዋጋ የዐርባ አምስት በሬ ዋጋ ሆነ!

ክርስቲያን አንባቢዎቼ እንኳን ለ2007ዓ.ም የጌታችን የመድሓኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፡፡ ሙስሊሞችና ሌሎችም እንኳን ለኛ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ ለእናንተም በዓል(ላት) በሰላም እንዲያደርሰን የጋራ የሆነውን ፈጣሪን በጋራ እንለምነው፡፡
ይቺ የዘንድሮ የትንሣኤ በዓል ከቀደሙት ትንሽ ለዬት ሳትል አትቀርም፡፡ ይሄ ግፋፎ ብር እዬለየለት መጥቷል፡፡ የሰሞኑ ገበያ በጣሙን ተበሻቅጧል፡፡ መንግሥቶቻችን ሲያቀብጣቸው ብሩ ላይ የወፍ ስዕል አኑረውበት ብሩ በዓለማችን የመጨረሻው ፈጣን ወፍ ሆነ፡፡ ሲበር ፍጥነቱ ልዩ ነው፤ በሣይንሳዊ መሣሪያ እገዛ ካልሆነ በዐይን ብቻ አይታይም፡፡ አቶ ብሩ ጉድ አፍልቷል፡፡ በአብዛኛው ከሆዱ ባለፈ የማይጨነቅ የልምድ ነጋዴ በሞላባት ሀገራችን ውስጥ በአቋራጭ ለመክበር የሚስገበገበው ሰው በዛና አቅልን የሳተ የገንዘብ ግንኙነት ነግሦ ሁላችንንም አቅል እያሳጣን ከሰውነት ተራ እያስወጣን ይገኛል፡፡ የዛሬው አዋዋሌ ራሱ ከወትሮው የተለዬ ሆኖብኝ በጣም ሲገርመኝ ውሎ አመሸ፡፡ ከማን ጋር እንደማወጋው ጨንቆኝ ሳለ እናንተ ትዝ አላችሁኝ፡፡ እስኪ ተንፈስ ልበል፡፡
chiken
ትዳር ያደረገ ልጄ(በትግርኛ አማርኛየ ቅር አትሰኙም መቼም) – ለአቅመ-በግ ያልደረሰ በቅርብ ትዳር ያደረገ ልጄ ደሮ አጋዛኝ ብሎ ዛሬ እኩለ ቀን ላይ ይደውልልኛል፡፡ ወዲያውኑ እንገናኝና የካ ሚካኤል አካባቢ ወዳለው ሾላ የደሮ ገበያ እንሄዳለን፡፡ ትርምሱ ሌላ ነው፡፡ ከቤት የቀረ ሰው ያለም አይመስልም፤ በዚያም ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እዳር ተመካክሮ ሰው ከማፍራት ውጪ ተኝቶ የሚያድር አይመስልም፤ የሰው ፋብሪካ በየቤታችን የተከልን እንመስላለን – ብዛታችን ሲታይ፡፡ ለማንኛውም ከልጄን ጋር የተለያዩ ሸቀጦችንና ዕቃዎችን ዋጋ በእግረ መንገድ እየጠያየቅን ወደደሮ ተራ አመራን፡፡ የሁሉም ነገር ዋጋ ሰማይ ነው፤ ከምናውቀው ሰማይ በላይ ሌላ ሰማይ ካለም ከዚያም በላይ፡፡ የሁሉም ሸቀጥና ዕቃ ዋጋ ያስደነግጣል፡፡ ሁሉም ነጋዴ ቁጥር የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ቁጥሩ ቀላል የማይባለው ሸማችም እንዲሁ ቁጥር የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ነጋዴው ስምንት መቶ የሚለውን የቻይና አቃጣይ ጫማ – ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ከሁለት መቶ በዘለለ የማይሸጠውን ጫማ ማለት ነው – ብዙም ሳይከራከር በሰባት መቶ ሃምሳ የሚሸምት ገዢ አለ፡፡ ተራዋ የላስቲክ ነጠላ ጫማ እንኳ ነፍስ አውቃ መቶና መቶ ሃምሳ ብር ስታወጣ ማየት ብርቅ ከመሆን አልፏል፡፡ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ደሞዝ ባለበት እየረገጠ የዕቃዎች ዋጋ በየሴከንዱ ሽቅብ እየተወነጨፈ እንዲህ ያለ ተናግዶት ማየት ገንዘቡ ከየት መጣ ያስብላል፤ አንዳንዱ ሰውማ ከቤቱ ውስጥ ገንዘብ ማተሚያ ማሽን ያለው ይመስላል፡፡

ኑሯችን ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ተቆጣጣሪ ብሎ ነገር የለም፡፡ ያለውና የሌለው በምን ምክንያት እንዳለውና እንደሌለው ሊታወቅበት የሚያስችል አንድም ሕጋዊ መንገድ የለም፡፡ በሀገራችን መንግሥት አለ ማለት የሚያስችል ምንም ዓይነት ምልክት ደግሞ አይታይም፡፡ በኪነ ጥበቡ ውለን ከመግባታችን በስተቀር የመንግሥትን ቀርቶ የሕዝብን ኅልውና የሚያስረግጥ አንድም ነገር ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ዛሬ ሃያ ብር የሚሸጥ ነገር ነገ በትንሹ መቶ ብር ሲሸጥ ማየት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት የሚከብደው ሰው አይኖርም፡፡ የሀብት ክምችት እሽቅድምድሙ እንደመቶ ሜትር ሩጫ ፍጥነቱ ንፋሳዊና ብርሃናዊ ሆኗል፡፡ በዚህ ላይ ዳኛ የለ፤ ታዛቢ የለ፤ ሕግ የለ፤ አዳሜን እየረጋገጥህና እየረመረምክ ባዋጣህ መንገድ መሮጥና የምትፈልገው የሀብት ደረጃ ላይ ወጥተህ ፊጥ ማለት ነው፡፡ የመንግሥት አካላት ደግሞ አሯሯጮች ብቻ ሣይሆኑ ሯጮችም ናቸው፡፡ ስለዚህም በሩጫው ተረገጥኩ ብለህ የምታመለክትበት ቅሬታ ሰሚ ቢሮ የለም፡፡ ተጋግጠህ ከሩጫው ሜዳ ትወጣለህ ወይም እንደምንም ብለህ እዚያው ትንከላወሳለህ፡፡ እንዳሁኑ የጠበቀ ሕግ ሳይወጣለት በዱሮ ዘመን የእግር ኳስ ጨዋታም እንዲህ ነበር አሉ – ማንም ጉልበተኛ ኳሷን በጥበብ ሣይሆን በጉልበት ነጥቆ በመውሰድ እግብ የሚከትበት፡፡ በሀገራችን የአሁን ሁኔታ በገቢህ ላይ ምንም የተጨመረ ነገር ሳይኖር ዋጋዎች እንዲህ ሲንሩ ስታይ ሕይወትህ በነሲብ የሚነዳ እንጂ በህግና በሥርዓት የሚመራ አይመስልህም፡፡ ደናቁርት ደናቁርትን እየጎተቱ ወደ ገደል እየጨመሩ ናቸው፡፡

ዝኮነ ኮይኑ ልጄና እኔ ዶሮ ተራ ገባን፡፡ ከድስት የማይወጣ ጫጩት ዶሮ ዋጋው 250 ብር ይሉናል፡፡ እዚያም እዚህም ስንጠይቅ የተማከሩ ይመስል – ተማክረውም ሊሆን ይችላል – የሚጠሩትም ሆነ የሚሸጡበት ዋጋ አንድና አንድ ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ – ብዙ ሰዎች ጫጩት ዶሮ በ200 ብርና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ ሲገዙ አየን፡፡ አንዳንዱ ገዢማ ስለለመደው ይመስላል በዋጋው መናር ሲያቅማማ አይስተዋልም፡፡ እኛ ግን ደነገጥን፡፡ ሥጋ ቢኖረው ግዴለም፡፡ ግን ለወግና ባህል ሲባል ብቻ አንዲት ስትታረድ ከአየር ወርዶ መሬት የሚደርስ ደም እንኳን የሌላት ጫጩት ዶሮ በ200 ብር መግዛት ግፍ የሚሆንብን መሰለን፡፡ ልጄ ግን ሚስቱ አንደምትቆጣው አስረዳኝና እንደምንም ተከራክሮ በ190 ብር አንዱን ወንድ ጫጩት ገዝቶ በፌስታል ቋጠረው፡፡ ይህ እንግዲህ የድሆችን ዶሮዎች በሚመለከት የታዘብኩት ነው፡፡ የኮርማ ዶሮ ታሪክማ ሌላ ነው፡፡
ወደ ሀብታም ሰዎች የደሮ ግዢ ደግሞ ልውሰዳችሁ፡፡ አንዱ ሀብታም ሁለት ወፋፍራም ዶሮዎችን አነሳና ዋጋቸውን ጠየቀ፡፡ ለያንዳንዳቸው 375 ብር ተባለ፡፡ ብዙም አልተከራከረም፡፡ 700 ብር ውልቅ አድርጎ ከፈለና ሁለቱንም ገዝቶ እመኪናው ጀርባ ሸጉሮባቸው ሸመጠጠ፡፡ ያለው ማማሩ አልኩ – በልቤ፡፡ ወደሌላ የዶሮ መሸጫ ቦታ አመራሁ፡፡ የኔ ቤት ድስት የማይችለውን አንድ ዶሮ አንዷ ሴት ሀብታም ብድግ አደረገችና ዋጋውን ጠየቀች፡፡ አምስት መቶ ብር ተባለች፡፡ እንደነገሩ ተከራከረችና በአራት መቶ ሃምሳ ተስማምታ ይዛው እብስ አለች፡፡ አንድ ዶሮ አራት መቶ ሃምሳ ብር! ይህን ትክክለኛ መረጃ ከሌላ ቦታ የምታገኙት አይመስለኝም፡፡ አንድ ዶሮ አራት መቶ ሃምሳ የኢትዮጵያ ብር ሲሸጥ እቦታው ነበርኩ፡፡ ጉድ ነው፡፡ ዶሮው ግን እንዳልኳችሁ ፍሪዳን ያስነቃል፡፡ ቢሆንም ግን ዶሮ ነው፡፡ በሬ ወይም በግና ፍየል አይደለም፡፡ እናም ዶሮ 450 ብር ሲያወጣ አየሁ፡፡ በዱሮው ዘመን አሥር ብር ፍሪዳ ይገዛ ነበር፤ እናም ዘንድሮ አንድ ዶሮ የተገዛበት ብር በዱሮው ዘመን ዐርባ አምስት ፍሪዳ ይገዛበት ነበር ማለት ነው፡፡ የሒሣብ ዕውቀቴ ወንዝ ባያሻግርም ከዚች የዶሮ ግዢ ነጥብ አንጻር የገንዘባችን ግሽበት 4500% ይመስለኛል፡፡ ዱሮ በግራም ሁለትና ሦስት ብር ይሸጥ የነበረውን የ18 ካራት ወርቅ ከአሁኑ ሰባት መቶና ስምንት መቶ ብር ዋጋው ጋር ስታነጻጽሩትም ግሽበታዊ ሥሌቱ በድንጋጤ ደም ቀጥ ያደርጋል፡፡ በ“ሰው በላው ሥርዓት” በኪሎ አንድ ብር ይሸጥ የነበረው ቅቤ ዛሬ 210 ብር ሲሸጥ ዕድገታችንን ለመለካት ምን መሣሪያ መጠቀም እንዳለብን ለማወቅ ወያኔን መጠየቅ ነው፡፡ ዱሮ በ120 ብር የሚሸመተውና ማንም ተራ ዜጋ የሚለብሰው የእንግሊዝ እውነተኛ ከሱፍ የተሰፋ ሙሉ ልብስ ዛሬ ሌላ ነገር ተቀያይጦበት በአሥራዎቹና ሃያዎቹ ሺዎች ሲገዛና የደረጃ መለያ ሲሆን ዕድገታችን የደረሰበትን ጫፍ ማሰብ እንችላለን፡፡ በቅርብ በደርግ ዘመን እንኳን በሦስት ሺህ ይገዛ የነበረ ያማሃ ሞተር ሣይክል ዛሬ ከመቶ ሺ ብር በላይ ሲገዛ የገንዘባችንን “ጥንካሬ” ያሳያል – ሊያውም እኮ በወረፋ ለወራት ጠብቀህ፤ መኪናውም እንዲሁ ነው፡፡ አሁን ለጥገና ብቻ የምታወጣው ገንዘብ ዱሮ ብዙ መኪናዎችን ሊገዛልህ የሚችል ገንዘብ ነው፡፡ አሁን አንድ ቤት ለመሥራት አስበህ ለምስማር ብቻ የምታወጣውን ወደዱሮው ብትመነዝረው ያኔ አንድ ቪላ ቤት ሊሠራልህ ይችላል፡፡ ዱሮ አሥር ብር መንዝረህ ለመጨረስ “የጓደኛ ያለህ” እንዳላልክ ዛሬ አሥር ብር አንዲት ቡትሌ ቢራ እንኳን የማይገዛ ከንቱ ወረቀት መሆኑን ስትረዳ ሀገርህ ከየት ወዴት እያመራች እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታይሃል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ሚስቱ ልጅ ስለወለደችለት ፈረስ በሚያስጋልብ አዳራሽ ቅልጥ ያለ ድግስ ደግሶ ከአልማዝና ዕንቁ ውድ ስጦታዎች በተጨማሪ የ2.5 (ሁለት ነጥብ አምስት!) ሚሊዮን ብር መኪና ቁልፍ ለሚስቱ በስጦታ መልክ የሚያበረክት የትናንት ሙልጭ ድሃ የዛሬ ወፍዘራሽ ከበርቴ በቀየህ ትታዘብና የት እንዳለህ ታውቅ ዘንድ ዐይንህን ብታሽ ከድቅድቅ ጨለማ ውጭ የሚታይህ ሌላ ነገር የለም፡፡ ጥሬ እውነት ነው እየነገርኩህ ያለሁት – ለሥነ ጽሑፍ ውበት ብዬ ያጋነንኩ እንዳይመስልህ፡፡ …

በዕድሜየ ቆዳ መልስ ሁለትና ሦስት ብር በግና ፍየል ሲሸጥ አይቻለሁ፡፡ በዚያን ዘመን አንድ አነስተኛ ከብት(በሬ/መሲና) በግልም ሆነ በቡድን ለማረድ በትንሹ አሥር ብር ያስፈልግ እንደነበር ቀድሜ እንደጠቆምኩት እኔ ራሴ ኅያው ምሥክር ነኝ፡፡ ያኔ ከአሥር ብር እስከ ሃምሳ ብር ይሸጥ የነበረው በሬ ዛሬ እስከ ሃያ ሺህ ብርና ከዚያም ባለፈ እስከ ስልሣ ሺህ ብር ድረስ መቸብቸቡን፣ ያኔ ከ12 ዕንቁላሎች ጋር 10 ወይም 15 ሣንቲም ይሸጥ የነበረው ዶሮ ዛሬ ያለ አንዲትም ዕን