Archive | June 2, 2015

ናትናኤል የዓለም ዘውድ የ3 አመት ከ3 ወር እስራት ተፈረደበት

የኢትዮጵያ መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስ ኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመውን የጭካኔ እርምጃ ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ›› ፈጥረሃል በሚል ተይዞ የታሰረው ናትናኤል የዓለም ዘውድ የ3 አመት ከ3 ወር እስራት ተፈረደበት፡፡ ዛሬ 25/2007 ዓ.ም የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ችሎት የቀረበው ወጣት ናትናኤል የዓለም ዘውድ ላይ የቀረበው ክስ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር›› የሚል ሲሆን አቃቤ ህግ ‹‹ሁከትና ብጥብጡን የፈጠረው ኢትዮጵያውያን ላይ ግድያ የፈፀመውን አይ ኤስ አይ ኤስ ለማውገዝ የተጠራው ሰልፍ ላይ በመሆኑ፣ በተፈጠረው ረብሻ በርካታ ሰዎች የተጎዱ በመሆኑ እና ረብሻውን የፈፀመው አምስተኛው አገራዊ ምርጫ እየተቃረበ ባለበት ወቅት በመሆኑና ይህም አደጋውንያባብስ የነበር መሆኑን በማገናዘብ›› የሚል የቅጣት ማክበጃ መጨመሩን ገልጾአል፡፡

natinael

በሌላ በኩል በተመሳሳይ ክስ ተከሰው በዚሁ ፍርድ ቤት የቀረቡት ማቲያስ መኩሪያ፣ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤና መሳይ የተባለ ሌላ ወጣት መከላከያ ምስክር ለማቅረብ ለሰኔ 4 ተቀጥረዋል፡፡ እነ ማቲያስ ‹‹ሰልፉ ላይ ሀሰተኛ ወሬ በማውራት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩ በነበረበት ወቅት ወደ ፖሊስ ድንጋይ በመወርወር፣ ህዝቡን አትነሳም ወይ በማለት…›› የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በጉዳዩ ላይ ዛሬ ይቀርባል ተብሎ የነበረው የቪዲዮ ማስረጃ ባለመቅረቡ በሚቀጥለው ቀጠሮ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩ በነበረበት ወቅት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንጋይ በመወርወር ሰልፉን አውካችኋል›› የተባሉ ሌሎች አምስት ወጣቶች ለሰኔ 4 የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ ተቀጥረዋል፡፡ በሰልፉ ሰበብ ተይዘው የታሰሩት ወጣቶች በቤተሰብ እንዳይጠየቁ መከልከላቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡