Archive | June 15, 2016

ግብፅ ሰሞኑን በሶማሊያ ለሞቱ የኢትዮጵያ ወታደር ቤተሰቦች ሃዘኗን ገለጸች

ኢሳት (ሰኔ 8 ፥ 2008) የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን ሶማሊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ላይ በተፈጸመው ጥቃት የሞቱ ወታደሮች እንደሌሉ ቢገልፅም፣ የግብጽ መንግስት ደርሷል ባለው ጥቃት ለተጎጂ ቤተሰቦች ሃዘኑን ገለጸ። የደረሰው ጥቃት በተመለከተ ማክሰኞ ምሽት መግለጫን ያወጣው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱ ክፉኛ እንደሚያወግዝ አስታውቆ፣ የተሰማውን ሃዘን ለኢትዮጵያ መንግስትና ለተጎጂ ቤተሰቦች አስተላልፏል። የኢትዮጵያ መንግስት ከቀናት በፊት በወታደሮቹ ላይ በተደረገው ጥቃት የሞቱ ወታደሮች እንደሌሉ ሲገልጽ ቢቆይም፣ የግብጽ መንግስት ጥቃቱን በማውገዝና ለተጎጂ ቤተሰቦች ሃዘንን በማስተላለፍ የመጀመሪያው ሃገር መሆኑ ታውቋል። የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ የሆኑት አህመድ አቡ ዘይድ ሃገራቸው ጥቃቱን እንደምታወግዝና ጉዳት በደረሰባቸው ቤተሰቦች የተሰማውን ሃዘን ማስተላለፍ እንደሚወድ መግለጻቸውን የግብጽ የዜና አውታር ሜና ዘግቧል። ግብጽ በሶማሊያ ሃልጋን ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በደረሰው ጉዳት ሃዘኑን ብትገልጽም ስለደረሰው ጉዳት ግን ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥባለች። የኢትዮጵያ መንግስት በአልሻባብ ታጣቂ ሃይል በተፈጸመው ጥቃት ከ100 የሚበልጡ ታጣቂዎች መገደላቸውን ቢገልጽም፣ በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ማረጋገጫ ሳይሰጥ መቅረቱ ይታወቃል። ዘግይቶ ለኢሳት በደረሰውና ከደህንነት ምንጮች በተገኘ መረጃ፣ በሰሞኑ የአልሻባብ ጥቃት የተገሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ብዛት 89 መሆኑ ታውቋል። ጥቃቱን መፈጸሙንና በርሱ ወገን ወደ 20 ታጣቂዎች እንደተገደሉበት የገለጸው ታጣቂ ሃይሉ ከ60 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ተገድለዋል ሲል ማስታወቁን ቢቢሲ እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ዘግቧል። ይሁንና ታጣቂ ሃይሉም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ወስጀዋለሁ ስላለው እርምጃ ከነጻ ወገን ማረጋገጫ አልተሰጠም። ጥቃቱ ከተፈጸመ ከአራት ቀን በኋላ ይፋዊ መግለጫን ያወጣው የግብጽ መንግስት ግን በደረሰው ጉዳት ሃዘን እንደተሰማው ለኢትዮጵያ መንግስት በላከው መልዕክት አስተላልፏል።

amisom5-610x250