Archive | October 2016

የሜርክል ጉብኝት በኢትዮጵያ

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪቃ ሃገራት ያደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ኾኗል። በተለይ መራኂተ-መንግሥቷ ኢትዮጵያን በይፋ የጎበኙት ሀገሪቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገ በሁለተኛው ቀን መኹኑ ጠንካራ ትችት አስከትሎባቸዋል።

ሜርክል በኢትዮጵያ

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅትየኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ክፍት እንዲያደርግ ሳይጠቁሙ አላለፉም። በእርግጥ የጉዟቸው ዋነኛ ዓላማ አውሮጳን ያስጨነቀው እና ያሰጋው የአፍሪቃውያን ፍልሰት ባለበት እንዲገታ ከአፍሪቃውያኑ መሪዎች ጋር መነጋገር ቢሆንም ማለት ነው። በአፍሪቃ የጸጥታ እና የደኅንነቱ ጉዳይ እንዲጠናከር ማድረግም የመራኂተ-መንግሥቷ አብይ አጀንዳ ነበር።

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን ጨምሮ ላደረጉት የሦስት ቀናት የአፍሪቃ ጉብኝታቸው በመጀመሪያ ያቀኑት ወደ ሳህል አካባቢ ሃገራት ነበር። በማሊ የአንድ ቀን ቆይታቸው መዲና ባማኮ ውስጥ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ቦባካር ኬታ ጋር ባደረጉት ውይይት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተንሰራፋውን ጽንፈኝነት ለመታገል ጀርመን ትብብር እንደምታደርግ ገልጠዋል። በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ወደ አውሮጳ የሚደረገው ፍልሰትም ባለበት እንዲከስም ስለሚቻልበት መላ ተወያይተዋል።

Afrika Kanzlerin Merkel besucht Niger (Getty Images/AFP/B. Hama)የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከኒጀሩ ፕሬዚዳንት ማኅማዱ ኢሶፉ ጋር

በበነጋታው ወደ ኒጀር ያቀኑት ሜርክል እዛም ያነሱት ተመሳሳይ አጀንዳ ነበር። ጽንፈኝነትን መዋጋት እና ፍልሰትን መግታት። ለዚያ ዓላማ በሚል ደግሞ የዓለማችን እጅግ ድኃ ለሆነችው ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ኒጀር €27 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ እና የቁስ ርዳታ እንደሚለግሱ ቃል በመግባት ነበር ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት።

ኢትዮጵያ ሲደርሱ ተመሳሳይ ግብ ይዘው ቢሆንም፤ ሌላ ነገር ግን ይጠብቃቸው ነበር። የፖለቲካ ምስቅልቅል እና  ከ25 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይዞት የመጣው ስጋት።

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የተቃውሞ ሰልፎች በኢትዮጵያ እንዲፈቀዱ አጽንዖት ሰጥተዋል። ከአዲስ አበባ ሆነው በሰጡት መግለጫም በዴሞክራሲ ሥርዓት ፓርላማን ጨምሮ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ድምጽ ሊኖር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

«አንድ ዴሞክራሲ የተሟላ የሚሆነው በፓርላማ ውስጥም የተቃዋሚዎች ድምጽ ሲታከልበት ነው። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማንሸራሸር እና ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ገቢራዊ እንዲሆን መሠራት አለበት። አሁን የታሰበው የለውጥ እርምጃቸው ከዚህ ጋር የተያያዘ ከሆነ በምክር ቤት ውስጥም የተለያዩ ሥሜቶችን ለማንጸባረቅ ይቻል ይሆናል»  

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV (picture alliance/AP Photo/ltomlinson)

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተጨማሪም የተቃውሞ ሰልፎች በኢትዮጵያ እንዲፈቀዱ አጽንዖት ሰጥተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቃውሞ ሰልፎችን ጨምሮ በርካታ መብቶችን የሚገድብ ነው። አዋጁ፦ «ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ የመናገር ነፃነትን መገደብ፣ የመሰብሰብ መብትን ማገድ» እና የሌሎች መብቶችን ገደብንም ያካተተ እንደሆነ ተጠቅሷል።

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል አዲስ አበባ ሲገቡ የኢንተርኔት አገልግሎት በስፋት ተቋርጦ ነው የቆያቸው። የተቃዋሚ ፖለቲከኞች አባላት እና ዜጎችም በጸጥታ ኃይላት ተይዘው እስር ቤቶች ውስጥ ይጣሉ እንደነበር ተዘግቧል። እናም በዚህ ኹኔታ ውስጥ መራኂተ-መንግሥቷ ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው ተገቢ እንዳልነበር የአውሮጳ ምክር ቤት አባል የኾኑት ወ/ሮ አና ጎሜሽ ጠንከር ባለ ትችት ገልጠዋል።

«ሌላው ቢቀር ትናንት ወ/ሮ ሜርክል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎም ሀገሪቱን መጎብኘታቸው የሁላችንም የጋራ ሐፍረት ነው።»

ወ/ሮ አና ጎሜሽ በአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የልማት ኮሚቴ እና የሰብአዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ አባላት ባለፈው ረቡዕ እለት ባደረጉት ኢትዮጵያን የተመለከተ ውይይት ላይ በኢሬቻ በአል ላይ የሞቱትን ሰዎች ጨምሮ በሀገሪቱ የሚከናወነውን ጭቆና የሚከታተል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ሊኖር ይገባል ብለዋል። ኢንተርኔትን እና ሚዲያን የሚገድበው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳም ጠይቀዋል። የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ጥሪ አስተላልፈዋል። በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው የተናገሩት በቤልጂግ የኢትዮጵያ  አምባሳደር የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አማካሪ አቶ ዮሐንስ አብራኃ ናቸው። የመንግሥት ተወካዩ መንግሥታቸው ዲሞክራሲን ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለው ተናግረዋል።

«ክብርት ሊቀ መንበር፣ እንዲሁም ክቡራን  እኛ ዲሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እያደረግን ነው  ብለን እናምናለን። ይኼን የምናደርገውም ሌሎችን ለማስደሰት ሳይሆን፤ የምናደርገው ሕዝባችን እና ሀገራችን ስለሚፈልጉት ነው።»

Afrika Kanzlerin Merkel in Äthiopien Einweihung Julius-Nyerere Gebäude für Frieden und Sicherheit (picture-alliance/dpa/M. Kappeler)የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ መርቀው ያስከፈቱት የአፍሪቃ ኅብረት ጁሊየስ ኔሬሬ ሕንጻ

ወደ መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኢትዮጵያ ጉብኝት ጉዳይ ስንመለስ ሜርክል አዲስ አበባ ውስጥ የአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ በመገኘት በጀርመን መንግሥት ድጋፍ የተገነባውን የአፍሪቃ ኅብረት የሠላም እና የፀጥታ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ሕንጻ መርቀዋል። ሕንጻው ከጀርመን የ30 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተደረገበት ሲኾን፤ የተገነባውም በጀርመን ተቋም ነው። መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲ  እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ከጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተለያየ ስፍራ ተወያይተዋል።

ሜርክል ከተቃዋሚ ፓርቲ እና ሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ዐርባ ደቂቃ ግድም የፈጀ ውይነበር። በውይይቱ አንጋፋዎቹ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ተሳትፈዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የጋዜጠኛ ማኅበር ተወካይ፣ ጠበቃ እና ጦማሪም በውይይቱ ተገኝተዋል። ይኽ ውይይት በአብዛኛው ትኩረት ያደረገው በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ እና መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ እንደነበር በውይይቱ የተካፈሉ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤

በኢትዮጵያ መሠረታዊ ጉዳይ፤ «ሕዝቡ እየጠየቀ ያለው መሠረታዊ ለውጥ ነው።» ያሉት ዶር መረራ ጉዲና ነገሮችን «ቀባብቶ መንግሥት ኹኔታዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸው ነገሮች መሠረታዊ ችግሩን አይፈታም» ብለው ለሜርክል መናገራቸውን አስታውቀዋል። መራኂተ-መንግሥቷ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጥ ለማድረግ  ቃል እንደገባላቸው ክትትል እንደሚያደርጉም  መናገራቸውን ዶ/ር መረራ ጠቁመዋል።

Demonstration der Semayawi-Partei in Addis Ababa Äthiopien 22.09.2013 (DW)የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማን የሚያውለበልብ ወጣት

 

ውሎም ሳያድር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚው ሰማያዊ ፓርቲ በርካታ አባላቱ በመንግሥት ፀጥታ ኃይላት መታሰራቸዉን አስታውቋል። ወ/ት ብሌን መሥፍን፣ አቶ እያስፔድ ተስፋዬ እና አቶ አወቀ ተዘራን እንዲሁም ከዋግ ህምራ ለጠቅላላ ጉባኤ የመጡ አንድ የአመራር አባል እና ሌላ አንድ አባልን ጨምሮ ስድስት አባላቶቻቸው መታሰራቸውን የፓርቲዉ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸዉ ከበደ ለዶይቸ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።

«የታሰሩበትን ምክንያት በግልጽ ባናውቅም ግን ይኼ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በግልጽ ከቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከአባሎቻችን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ 6 የሚኾኑ አባሎቻችን ታስረውብናል።»

መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአፍሪቃውያን ስደተኞች እና የአህጉሪቱ የጸጥታ ኹናቴ በርሊን ውስጥ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችን እየተቀበሉ ሲያነጋግሩ ከተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በአውሮጳ ኅብረት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

በመንግሥት ታጣቂዎች የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ለማሰብ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሐሙስ እለት ቤልጅግ ብራስልስ ውስጥ ሠልፍ አድርገው ነበር። ኢትዮጵያውያኑ በኢሬቻ በዓል ላይ እንዲሁም ከበዓሉ በፊት  እና በኋላ ለሞቱት ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ ሻማ ማብራት ሥነስርአት አከናውነዋልም።  በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ግድያ እና  እስራትም የአውሮጳ ኅብረት እንዲያስቆም በመጠየቅ አቤት ብለዋል። በተወካዮች በኩልም የተፃፉ ደብዳቤዎችን ለአውሮጳ ኅብረት ባለሥልጣናት አድርሰዋል።  ከሰላማዊ ሰልፈኞቹ ተወካዮች መካከል አንዱ አቶ አበራ የማነአብ ከሚመለከተው የአውሮጳ ኅብረት ክፍል ባለሥልጣናት ጋር ፊት ለፊት መነጋገራቸውን ገልጠዋል።

Berlin Merkel trifft Tschads Präsident Idriss Deby Itno (picture-alliance/AP Photo/M. Schreiber)

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተውም ኾነ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች መዲናቸው በርሊን ድረስ መጥተው ቢወያዩም ዋነኛው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና የዲሞክራሲያዊ መብቶች እጦት እስካልተቀረፈ ድረስ የአፍሪቃውያን ፍልሰት እና የአካባቢው ጸጥታ ስጋት የሚረግብ አይመስልም።

የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ ባቀረበው አስተያየቱ የመራኂተ-መንግስቷ ንግግርን በማጣቀስ፦ «አዲስ አበባ ላይ አፍሪቃ ግሩም የሆኑ ጭንቅላቶችን ማጣት አይኖርባትም ብለዋል። ይህ አላዋቂነት ይመስላል፤ ምክንያቱም ምርጥ የተባለ ጭንቅላት ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን ዛሬ በሀገራቸዉ ሊያኖራቸዉ የሚችል ተስፋ በማጣታቸዉ ዋሽንግተን ላይ ታክሲ ይነዳሉ።» ሲል የመራኂተ-መንግሥቷ ግብ እና ተግባራዊነቱ ላይ አጠያይቋል። በእርግጥም የጀርመን መራኂተ-መንግሥትም ኾኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድራጊዎች እንደመኾናቸው መጠን ሀገሪቱ የገባችበትን ውስብስብ ችግር እስካላጤኑ ድረስ ነገ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪቃውያን በገፍ ወደ አውሮጳ ስላለመፍለሳቸው መቼም እርግጠኛ ሊኾኑ አይችሉም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

አንጌላ መርከል መንግስት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን በሚያቅርቡ ሰዎች ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ እንዲያቆም አሳሰቡ

ኢሳት (ጥቅምት 1 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርከል መንግስት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን በሚያቅርቡ አካላት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ እንዲያቆም ማከሰኞ አሳሰቡ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋ በመሆን የጋራ መግለጫን የሰጡት መርከል “ችግር/ጥያቄ ካላቸው ሰዎች ጋር መወያየት ይኖርባችኋል” ሲሉ ለአቶ ሃይለማሪያም በመግለጫው ስነስርዓት ወቅት መናገራቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚወስዱትን ድርጊት የኮነኑት የጀርመኗ ቻንስለር በስልጣን ላይ ያለውን ገዢው የኢህአዴግ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ክፍት እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

angela
ሃገሪቱ በአስቸኳይ የጊዜ አዋጅ ውስጥ እያለች ጉብኝታቸውን እያደረጉ ያሉት አንጌላ መርከል በዲሞክራሲ ሂደት ውስጥ ድምፅን የሚያሰሙ የተቃዋሚ አካላት በፓርላማ ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የጀርመኗ ቻንስለር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኘተው ንግግር እንዲያደርጉ በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ቢቀርብላቸውም አንገላ መርከል የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ በሌለበት ፓርላማ ንግግሩን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ዲፕሎማቶች ለሮይተርስ ተናግረዋል።
“በቻንስለሯ በኩል የተሰጠው ምላሽ ጀርመን የተለመደውን አካሄድ እየተከተለች እንዳለሆነ ማሳያ “ ሲሉ እነዚሁ ዲፕሎማት አከለው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ባለው ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ስጋት እንዳደረባቸው የሚናገሩት መርከል በነጻነት የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ከአንድ ሃገር የዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ መሆኑንም በአጽንዖት ገልጸዋል።
ቻንስለሯ ያላቸውን ስጋት ማቅረባቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ መንግስታቸው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ጥረት እያደረገ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ የጀርመን ባለሃብቶች ቅሬታን እያቀረቡ ይፋ ያደረጉት መርከል መንግስት ባለሃብቶቹ ላቀረቡት ቅሬታ በጎ ምላሽን እንዲሰጥ መጠየቃቸውም ታውቋል።
ባለፈው ሳምንት አንድ የእስራዔል የማዕድን ኩባንያ መንግስት የገባውን ቃል ተግባራዊ አላደረገም በማለት ከአፋር ክልል ከተሰማራበት የፖታሽ ማዕድን ስራ ጠቅልሎ መወጣቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በማዕከላዊ ሶማሊያ ቁልፍ ወታደራዊ ስፍራዎችን ይዘው የቆዩት የኢትዮጵያ ወታደሮች የተቃጣባቸውን ጥቃት ተከትሎ አካባቢውን ለቀው ወጡ።
ወታደሮቹ ስፍራውን በለቀቁ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ጥቃቱን አድርሷል የተባለው የሶማሊያ ታጣቂ ሃይል አልሸባብ አካባቢውን እንደተቆጣጠረው ቢቢሲ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ ብማድረግ ሰውኞ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግስት የማህበራዊ ድረ ገፆችን (በተለይ ፌስቡክን) ለመዝጋት እየሞከረ ነው

የኢትዮጵያ መንግስት የማህበራዊ ድረ ገፆችን (በተለይ ፌስቡክን) ለመዝጋት እየሞከረ ነው። ምክንያት፡ ችግር እየፈጠረብኝ ነው የሚል ነው። ችግሩ ደግሞ ህዝባዊ ተቃውሞ መሆኑ ነው። የህዝባዊ ተቃውሞው መንስኤ (Basic Cause) ጭቆና እንጂ ፌስቡክ አይደለም። social-media-banned-e1468104677454የኢትዮጵያ መንግስት ይደበድብህና አሞህ ስታለቅስ የሚያሳስበው መደብደብህን ሳይሆን ማልቀስህን ነው። የሱ ተግባር የሚሆነው ለቅሶውን ማስወገድ ሳይሆን ለቅሶውን እንዳይሰማ ማፈን ነው። ለቅሶውን ማፈን ለቅሶውን ማስወገድ አይደለም። ለቅሶው እንዳይሰማ ቢታፈን እንኳ ድብደባው እስካልቆመ ድረስ ለቅሶው ይኖራል። ስለዚህ ለቅሶ መስማት ካልፈለግን ለቅሶውን ማስወገድ እንጂ ለቅሶ የሚሰማበትን ሚድያ መዝጋት መፍትሔ አይሆንም። ለቅሶውን ለማስወገድ ድብደባውን ማስቀረት ነው። ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ማስቀረት ከተፈለገ ጭቆናና ዓፈና ማስወገድ እንጂ ጭቆናና ዓፈና የሚጋለጥባቸውን ማህበራዊ ሚድያዎችን መዝጋት መፍትሔ ሊሆን አይችልም። የችግሩ መንስኤ ዓፈና ከሆነ መፍትሔው ዓፈና ሊሆን አይችልም፡ የዓፈና መፍትሔ ዓፈናን ማስቀረት ነው። ማህበራዊ ሚድያዎች አሉባልታዎችና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመልቀቅ ህዝብን በማደናገር ከተወቀሱ … የዚህ መድሐኒት ትክክለኛና እውነተኛ መረጃ ሊያቀርቡ የሚችሉ ሕጋዊ፣ ነፃና ገለልተኛ የግል ሚድያዎች መፍቀድ እንጂ ፌስቡክን መዝጋት አይደለም። ፌስቡክ መዝጋት ዓፈናን መጨመር እንጂ መቀነስ አይደለም። ዓፈናን መጨመር ደግሞ ህዝባዊ ተቃውሞውን ማባባስ እንጂ መቀነስ አይደለም። ፌስቡክን መዝጋት መረጃን ማፈን ነው። ዓፈና የችግር መንስኤ እንጂ የችግር መፍትሔ ሆኖ አያውቅም።

 

ሰበር ዜና:- ኃይሉ ሻወል አረፉ


አቶ ኃይሉ ሻወል

አቶ ኃይሉ ሻወል

ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲና ከመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት – መኢአድ መሥራቾችና መሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ኃይሉ ሻወል አረፉ፡፡

ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲና ከመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት – መኢአድ መሥራቾችና መሪዎች አንዱ የነበሩት አቶ ኃይሉ ሻወል አረፉ፡፡

አቶ ኃይሉ ሻወል በሰማንያ ዓመት ዕድሜአቸው ዛሬ ያረፉት በሕክምና ሲረዱ በነበረባት ታይላንድ መሆኑን ለቪኦኤ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልፀዋል፡፡

አቶ ኃይሉ ሻወልን ለሕልፈት ያበቃቸው የጤና ችግር ምን እንደሆነ ለጊዜው እያጣራን ቢሆንም እራሣቸው በፃፉት መፅሐፍ ላይ እሥር ቤት ሣሉ በገጠማቸው ቅዝቃዜ ምክንያት አከርካሪያቸው ላይ ሕመም ይሰማቸው እንደነበረ ጠቁመዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታትም በብርቱ ሲታመሙ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

የአቶ ኃይሉ ሻወል (ኢንጂነር)አስከሬን ነገ፤ ዓርብ አዲስ አበባ ይገባል ተብሏል።

ተጨማሪ መረጃ ባገኘን ጊዜ ይህንን ዜና እናዳብራለን፡፡ በነገ የአየር ሥርጭታችን ላይ ሥፋት ያለው ዘገባ ለማቅረብ እንጥራለን፡፡

ምንጭ :(ቪኦኤ)