Archive | February 22, 2017

አድዋ…. አድዋ…. አድዋ…. የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም

በቅዱስ ዬሃንስ

የካቲት ወር የአፍሪካውያን ወር ይባላል፡፡ ይህን ወር የአፍሪካውያን ወር ያሰኘው ብቸኛ ምክንያት የዓድዋ ድል ነው፡፡ ነጮች አፍሪካውያንን በግፍ በሚረግጡበት፣ በባርነት በሚገዙበት፣ ያሻቸውን ያለከልካይ በሚፈፅሙበት በዚያን ወቅት ” እምቢኝ! ሀገሬን በቅኝ አላስገዛም ” ብሎ በጀግንነት የተነሳ፣ ተነስቶም የቅኝ ገዢዎችን በትር በሀይል መስበር የተቻለበት ወር ይህ የካቲት ወር ነው፡፡

የአውሮፓ ሀገራት አፍሪካን በተቀራመቱበት ዘመን ኢጣሊያም ኢትዮጲያን በቅኝ ግዛቷ ለማድረግ መንገድ የሚከፍትላትን የውጫሌ ውል ከአፄ ምኒልክ ጋር ውጫሌ ከተማ ላይ በተወካይዋ አንቶሌኒ መሰረት ተዋዋለች፡፡ ከተደረገው ውል አንቀፅ 17 ግን የአማርኛ እና የኢጣልያንኛ ትርጓሜው የተለያየ ነው፡፡ በአማርኛ የተፃፈው ‹‹ ግርማዊ የኢትዮጲያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታ ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋገር ሲፈልጉ በግርማዊ የኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡›› የሚል ሲሆን የኢጣሊያንኛው ትርጉም ግን እንዲህ የሚል ነበር….‹‹ ግርማዊ የኢትዮጲያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ መንግስታት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋር ሲፈልጉ በግርማዊ የኢጣሊያ ንጉሥ አማካይነት ያደርጋሉ፡፡›› የዚህ ፍቺው ኢትዮጲያ በኢጣሊያ ሞግዚት አስተዳደር ስር መሆኗን የሚገልፅ ነው፡፡ ይህንንም የኢጣሊያ መንግስት ለአውሮፓ መንግስታት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡
ይህም በታወቀ ግዜ አንቀፅ 17 ይቅር በሚል አፄ ምኒልክ ከባለሟሎቻቸው ጋር ወሰኑ በዚህም ሌላ ውል ተፈረመ፡፡ ኮንት አንቶሌኒ ‹ይቅር› የሚለውን ቃል የተረዳው እንዳለ ይቀመጥ አይለወጥ በሚል ነበርና አለመሆኑን ሲረዳ ምኒልክ እልፍኝ ገብቶ ደነፋ፡፡ የኢጣሊያ መንግስት ይህን እንደውርደት ይቆጥራል፡፡ ክብሩን ለማስጠበቅ ጦርነት ያደርጋል፡፡ ክብሩን በጉልበት ያስጠብቃል ብሎ ፎከረ፡፡

እቴጌ ጣይቱ እንዲህ አሉት… ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬን እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ! እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር አስጥቶ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ ለአፈሩ ክብር ለብሶ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ! ሂድ! የኢትዮጲያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ግዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ግዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡››

በዚህም የኢትዮጲያና የኢጣሊያ ወዳጅነት ጥያቄው፡ የጦርነቱ አይቀሬነትም ተረጋገጠ።

የኢጣሊያ መንግስት በተወካዩ አማካይነት ኢትዮጲያ ላይ ጦርነት ሲያውጁ አፄ ምኒልክ የኢጣሊያ በጦር መሳሪያም ሆነ በስልጣኔ ከፍ ማለቱ ሳያሸብራቸው ‹‹ቴዎድሮስ በመቅደላ ዮሐንስ በመተማ የሞቱላትን ሀገር እኔም ደሜን አፍስሼ ነፃነቷን አስጠብቃለሁ፡፡ እሞትላታለሁ›› ብለው አዋጅ አወጁ…

‹‹….የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም አላስቀየምኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም..ዘመቻዬ በጥቅምት ነው እና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››

አዋጁን ተከትሎ ህዝብ ከዳር አስከ ዳር ተመመ፡፡ እቴጌይቱ እንዳሉት ደረቱን ለጥይት እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ ሀገሩን ከጠላት ሊታደግ የኢትዮጲያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ነቅሎ ተነሳ፡፡

የሩቁንም ሀገር የጎጃሙንም፣ የደንቢያውንም፣ የቋራውንም፣ የበጌምድሩንም ከጨጨሆ በላይ ያለውን አገር ሁሉ አሸንጌ ድረስ ክተት ብለው አዘዙ፡፡ የሰሜንና የወልቃይት ጠገዴንም ሰው መቀሌ ድረስ ክተት ብለው አዘዙ፡፡ ከዚህ በኋላ ራስ መኮንን የሐረርጌን ጦር ይዘው በመስከረም እኩሌታ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ከጊቤ በታች ያለው አገር ጦር የወለጋው ሹም ፊታውራሪ ተክሌ ጦራቸውን ይዘው ገቡ፡፡ አፄ ምኒልክ አዋጃቸውን በመስከረም ወር ካስነገሩ በኋላ ለአገር ጥበቃ አጎታቸውን ራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴን ሾመው እርሳቸው በጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስተው በጊዳ በኩል አድርገው ጥቅምት 18 ቀን ወረይሉ ከተማ ገቡ፡፡
ከዚያም ራስ ሚካኤልን፣ ራስ ወሌን፣ ራስ መኮንንን፣ ራስ መንገሻ አቲከምን፣ ራስ አሉላን፣ ዋግሹም ጓንጉልን፣ ደጃች ወልዴን፣ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ ፊታውራሪ ተክሌን፣ ሊቀ መኳስ አድነውን፣ ቀኛዝማች ታፈሰን ‹‹ቀድማችሁ ወደ አላጌ ዝመቱ የሚቀላችሁ ከሆነ ወጉት፡፡ የሚከብዳችሁ ከሆነ ላኩብኝ ›› ብለው አስቀድመው መላካቸውን ይነገራል፡፡

ምን አልባትም ይህ አዋጅ ታውጆ የኢትዮጲያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ተሞ አድዋ ላይ ጣሊያንን ድባቅ ባይመታ ኖሮ የኛ ዕጣ እንደሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በባርነት ቀንበር ወድቀን በኛ ማምነት ላይ የኢጣሊያ ማንነት ተለጥፎብን እንቀር ነበር፡፡ ለዛም አይደል ‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፡ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ግዜ ሐበሻ›› የተባለው፡፡

የአድዋ ጦርነት የተጀመረው የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ከማለዳው 11 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ ላይ ነበር፡፡ የጄኔራል አልቤርቶኔ ክፍለ ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ፣ በዋግሹም ጓንጉል፣ በራስ ሚካኤል እና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ፡፡ የንጉሰ ነገስቱ ሠራዊት የመሐል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ከጣሊያኖች ጋር በተደረገው ጦርነት የተመሰከረለት ጀግና ነበር፡፡ ጎራዴውን መዞ በዋናው የትግል አውድማ ላይ ተወርውሮ ገባ፡፡ በዚህም ጊዜ በጠመንጃ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ አለፈ፡፡

በገበየሁ መሞት ተሸብሮ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር ወድያው መልሶ ተረጋጋ፡፡ በታላቅ ቆራጥነት አልቤርቶኔን እንደገና ገጠመው፡፡ በ4 ሰዓት አከባቢ ላይ አልቤርቶኔ ከመኮንኖቹ አብዛኞቹን አጥቷል፡፡ በጦርነቱ እንደተሸነፈ ግልፅ ነበር፡፡ የኢጣሊያ ወታደሮች በድንጋጤ ተውጠው ፈረጠጡ፡፡ ከፊሉ ተማረከ፡ የቀረውም ወደ ሌሎቹ ክፍላተ ጦር በመሸሽ ራሱን አተረፈ፡፡ በዚህ ጊዜ ያልተነካው ክፍል የሚይዘውን አጥቶ ይተራመስ ገባ፡፡ በዚህ ሰዓት ቀጥታ በአጼ ምኒሊክ የሚታዘዘው ጦር ከውጊያው ገባ፡፡ በጦርነቱ ወቅት አጼ ምንሊክ በትክክል ወዴት እንደሚገኙ ጣልያኖች አያውቁም ነበር፡፡ ሁልጊዜ ሳይለዩት አብረውት ከሚገኙት ሁለት ሊቀመኳሶች አንዱ በአለባበሱ ንጉሱን መስሎ በስፍራው ይገኛል፡፡ ከሊቀመኳስ ተግባሮች ውስጥ አንዱ የጠላትን ትኩረት ወደ እሱ በመሳብ ንጉሰ ነገስቱን መጠበቅ ነው፡፡ በጦርነቱ ስፍራ አጼምኒሊክ እንደ አንድ ተራ ወታደር ለብሶ በጦርነቱ መሃከል ተገኝቶ ያዋጋም ይዋጋም ነበር፡፡

ቀኑን ሙሉ ውጊያ ሆኖ ከምሽቱ ዐስራ ሁለት ሰዓት ላይ ድሉ የኢትዮጲያ መሆኑ ታወቀ፡፡

በአድዋው ጦርነት እቴጌ ጣይቱ ብጡል የኢትዮጵያን ጦር በሞራል በማነቃቃትና በማበረታት እንዲሁም ሠራዊቱን እግር በእግር እየተከተሉ በፉከራ ያበረታቱ ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ ጥቁር ጥላ አስይዘው ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ ወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮቻቸው ታጅበው ከወታደሩ ጎን ተሰልፈው ነበር፡፡ የኋላው ወታደር ሲያመነታ ‹ በርታ ምን ሆነሃል ድሉ የእኛ ነውና በለው › ብለው ይናገራሉ፡፡ ወንድ ሴት ሲያበረታው መሸሽ አይሆንለትምና ሁሉም በወኔና በጀግንነት ወደፊት ገፋ፡፡ እቴጌይቱም በዚህ ቀን የሴትነት ባሕሪያቸውን ትተው እንደ ወንድ ወታደሮቻቸውን በቀኝና በግራ አሰልፈው ወደ ጦርነቱ ገቡ፡፡ መድፈኞቻቸውንም በቀኛቸው በኩል ጠምደው እየተኮሱ በመካከል የሚዋጋውን የጠላት ጦር ይቆሉት ጀመር፡፡
በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም መላው የኢትዮጲያ ህዝብ በአፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ አጋፋሪነት በባዶ እግሩ አድዋ ዘምቶ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር ድል አደረገ፡፡ይህም ኢትዮጲያን አንድ የማድረጉን ዘመቻ ቋጨው፡፡ ወደ ማዕከላዊ መንግስት ለመጠቃለል እምቢተኛ የነበሩት ገዥች ለሀገራቸው ክብር ከሚቃወሟቸው አፄ ምኒልክ ጎን ተሰልፈው ጠላትን ድባቅ መቱት፡፡ ይህም ያ ትውልድ በተሻለ መልኩ በጎሳና በሃይማኖት ሳይለያይ ስለ ሀገር ፍቅር ስለ ክብርና ስለ ነፃነት ስለ መብት ያወቀና የተረዳ መሆኑን አስረግጦ ያስረዳናል፡፡

ዛሬስ?

አፍሪካዉያን በቅኝ ገዥዎች ሥር በነበሩት ጊዜ ነፃነትን አሻግረዉ እያዩ ነበር፡፡  ኢትዮጵያ ከቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ነፃ ሃገር በመሆን ህዝቦቿ የነፃነትን አየር እንዳሻቸው የሚምጉ የአፍሪካ ብሎም የአለም ተምሳሌት ነበረች፡፡  አሁን ግን በወያኔ መራሹ ፀረ ኢትዮጵያ ቡድን ነፃነትን ተነፍጋ ነፃነት አይታ የማታዉቅ ይመስል ነፃነትን አማትራ እያየች የምትገኝ ምስኪን አገር ሁና ትታያለች፡፡ ህዝባችን አገር በቀል በሁኑ አሳማ መሪዎች ሥር ወድቀዉ ተነግሮ ለማያልቅ መከራ ተዳርገዋል፡፡ እነዚህን ሃገር በቀል ፋሽስቶች በአድዋ የታየውን የአንድነትና የድል አድራጊነት መንፈስ ተላብሰን ድባቅ በመምታት ህዝባችን ዳግም ታሪክ ፅፎ በመጭው ትውልድ የሚወደስበትን አሻራ ጥሎ እንደሚያልፍ ጥርጥር የለውም፡ የክተቱ ነጋሪትም የሚጐሰምበት ጊዜ ሩቅ አደለም።

ልዩነቶቻችሁን ሁሉ ወደጎን ገፍታችሁ… ስለሰውነት ክብር፣ ስለሀገር ነፃነትና ሉዓላዊነት፥ ሕይወታችሁን አሳልፋችሁ የሰጣችሁ አባቶቻችንና እናቶቻችን፥ ክብር ለናንተ ይሁን!!!

ምዝበራ በየፈርጁ

Alemayehu Kidanewold

ይህ የፍዳና የሰቆቃ ዘመን እስኪያልፍና የማይቀረው ወርቃማ የነፃነት ዘመን እስኪመጣ በሰመመን የምቆይበትን ብልኃት ባገኝ ወደድኩ፡፡ እንዲያ ዓይነት ጥበብ ተገኝቶ እንደእሥራኤሉ ፕሬዝደንት (ኤርየል ሻሮል) በሞትና በሕይወት መካከል አሸልቦ ሳይሰሙ ሳይለሙ ብዙ ጊዜ መቆየት ለእንደኔ ያለው ሰው ተፈልጎ አይገኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የምንኖር ጥቂት የማንባል ዜጎች አብዛኛው የምንሰማውና የምናየው ነገር ግራ እያጋባን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከመኖር ይልቅ አለመኖርን እንመርጣለን፡፡ አስደንጋጭ ወቅታዊ ሁኔታ ውስጥ ተዘፍቀናል፡፡ ራሳችንን እየታመምን የምንኖር አለን – በበኩሌ በጣም እያመመኝ እንደምኖር ብደብቅ ዋሸሁ፡፡ ዛሬ ጧት ነው፡፡ ከአንድ ወዳጄ ጋር እንጫወታለን – ስለወያኔዎች ሁለንተናዊ የምዝበራ ሥልትና የሙስናው ቅጥአልባነት ነበር በንዴት እየተንጨረጨርን የምናወጋው፡፡ የቀራቸው እኮ የለም፤ ሁሉንም እነሱ ተቆጣጥረውታል፡፡ በአንዲት ቀን አዳር መክበር የሚቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑን ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ አስመስክረዋል፡፡ በአንዲት ቀን አዳር መክበር ብቻም ሳይሆን በአንዲት ቀን አዳር ማደኽየትም ሆነ አላንዳች በቂ ምክንያትና ፍትሃዊ ፍርድ አንድን ዜጋ መቅ ማውረድም እንደሚችሉ አስተዋይ ልቦና ላለው የዓለማችን ዜጋ አሳይተዋል፡፡ ላኪዎቻቸው ግን በወያኔዎች ዕኩይ ድርጊት ቢደሰቱ እንጂ አይገረሙም፡፡ እነዚህ የስቃያችን አበጋዞች ውጤቱን አስቀድመው የማያውቁትና ሲቻላቸው ደግሞ በርቀትም በቅርበትም የማይቆጣጠሩት አንድም ድርጊት በዓለም እንደሌለ የሚገነዘቡ የፕላኔታችን ገዢዎች ናቸው፡፡ ሜቴክ የሚባለው የወያኔ ድርጅት ሀገሪቱን ራቁቷን እያስቀራት ነው፤ በላም አለኝ በሰማዩ የስኳር ፋብሪካ የውሸት ግንባታ ሂደት የሚያግበሰብሰው ገንዘብ አልበቃ ብሎ በሌሎች የመንግሥት ተብዬ ተቋማትም እጁን እየላከ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት እያሟጠጠው ነው – ኢትዮጵያን ማን ይድረስላት! እኛስ ምን እንሁን? ለማንስ ነው እግዚኦ የሚባለው – ለማን ነው የሚጮኸው? በዚህ ድርጅት የተሰገሰጉት ጡረታ የወጡ የወያኔ ኮሎኔሎችና ጄኔራሎች ዐይናቸውን በጨው አጥበው የምሥኪኑን ሕዝብ ሀብትና ንብረት ካላንዳች ይሉኝታ እየቦጠቦጡ ለግላቸው እያዋሉት ነው፡፡ ሥራ ላይ እያሉ ጎደልብን የሚሉትን አሁን እያካካሱ ናቸው፡፡ ልብ አድርጉ ለምሣሌ፡፡ ኤልፓ ውስጥ ነበረ የተባለውን ሙስና ለማስቀረት በሚል የማስመሰያ ሥልት የኤልፓን ዕቃዎች ሜቴክ እንዲያስገባ ይደረጋል፡፡ የሚገባው ዕቃ ግን ከበፊቱ የባሰ መናኛና እንደተቀየረ የሚቃጠል ወይ የሚፈነዳ ነው – ይህን የአደባባይ ምሥጢር ሁሉም የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ያውቃል፡፡ ሙስናው ግን ከዱሮው በዕጥፍ ድርብ በልጧል፡፡ ለአብነት ሜቴክ ለኤልፓ አንድ ትራንስፎርመር በ180 ሺ የኢትዮጵያ ብር ገቢ ያደርጋል – ያለምንም ጨረታ ለርሱ ብቻ በተፈቀደ ችሮታ (በየቦታው እንዲህ ነው የሚደረገው፤ አንተ በነፃ እሰጣለሁ የምትለውን ዕቃ ሳይቀር “ምን አገባህ?” ተብለህ በሚሊዮኖች እንዲገዛ ሊደረግ ይችላል፤ ወያኔና ገንዘብ እስከለተሞታቸው ላይፋቱ ተማምለው የትዝብትን ጫፍ አልፈዋል!)፡፡ ከዚህ ትራንስፎርመር በጥራትም በደረጃም እጅግ የሚበልጥ ትራንስፎርመር በ65 ሺህ ብር ከግል አቅራቢዎች ማግኘት እየተቻለ ባለቤት የሌላትን ሀገር ተረባርበው ለማለብ ሲሉ ሦስትና አራት ትራንስፎርመር በሚገዛበት ገንዘብ አንድ አልባሌ ምናልባትም ያገለገለና ያረጀ ያፈጀ ትራንስፎርመር ይገዛሉ፡፡ ለዚያውም በአነስተኛ ዋጋ የሚገኘው ጥሩ ዕቃ በድርጅቶቹ መኪና ተጭኖ የተፈለገው የኤልፓ ግቢ መግባት ሲችል የሜቴክ ውዳቂ ዕቃ ግን በኤልፓ ወጪ ከሥጋ ሜዳ (ታጠቅ አካባቢ) እንዲመጣ ይደረጋል፡፡ በአንድ ስብሰባ ይህ ዓይነት ግፍ በሀገር ላይ ለምን እንደሚፈጸም ቢጠየቅ ደብረ ጽዮን የተባለው የወያኔ ጭራቅ “እናንተን ምን አገባችሁ?” በሚል የጥጋብ አነጋገር ጠያቂዎቹን አሣፍሮና ከሥራ ደረጃም አወርዶ ከኃላፊነት አንስቷቸዋል፡፡ ዛሬ ስለሀገር ማሰብና መጨነቅ ጥያቄና አወንታዊ አስተያየትም ማቅረብ የሞትና የእሥራት ቀለል ሲል ደግሞ ከኃላፊነት ቦታ ወርዶ ተራ ሠራተኛ የመሆንና ከናካቴው ከሥራ በመባረር የበረንዳ አዳሪነትን ክፉ ዕጣ ያሰጣል፤ ዘመነ ግርምቢጥ፡፡ አፍህን ዘግተህ እነሱ እንደሚሉትና እንደሚያደርጉት እንደሚሆኑትም ካልሆንክ ጠንቁ ከባድ ነው፡፡ የነዚህ ወያኔዎች ልጆች በነገይቷ ኢትዮጵያ የሚገጥማቸውን የአንገትና የኅሊና ስብራት ከአሁኑ ሳስበው የልጆቼን ያህል እጨነቅላቸዋለሁ፡፡ በአንድ ሜትር ርቀት ውስጥ ከሚገኝ ፉርሽካ ባለፈ ሌላ ምንም ነገር እንደማይታያት አህያ የሚመሰሉት አባቶቻቸው ግን ኅሊናቸው የታወረ በመሆኑ አሁንም ሆነ ትናንት ምናልባትም የመትረፍ ዕድሉን ካገኙት ነገም ቢሆን በአሁኑ ሰይጣናዊ ድርጊቶቻቸው የሚያፍሩ አይመስሉም፡፡ እነሱም ያሳዝናሉ እኮ፡፡ ኤልፓ ውስጥ የሚሠራ አንድ ትግሬ ኢትዮጵያዊ ከትልቅ ኃላፊነት ወደ ተራ ሠራተኝነት መውረዱን ሰማሁ፡፡ ምክንያት – በየስብሰባዎች እውነቱን እያጋለጠ ሀገሪቱን ከብዝበዛና ከሙስና እናድናት ብሎ በመጮሁ፡፡ ይህ ሰው ትግሬ በመሆኑ – ምናባልት – ሊገድሉት አንጀታቸው አልጨክን ብሎ ሊሆን ይችላል – “የኛ” የሚሏቸውን ግን የሁላችንም የሆኑትን ወገኖችም ላለማስኮረፍ ጭምር፡፡ ሌላ ቢሆን ኖሮ ግን በመኪና ተድጦ ወይም በአንዳች ሌላ ሰበብ (ሰበብም ሳያስፈልግ ኧረ!) እስካሁን ደብዛው ይጠፋ ነበር፡፡ ለማንኛውም ይህ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ለሆዱ ሳያድር እየታገላቸውና ቢገድሉትም ግድ እንደሌለው በግልጽ እየነገራቸው ይገኛል – በነገራችን ላይ ቁጥራቸው ለመኩራሪያነት ባይደርስም እንዲህ ያሉ ለሆዳቸው ሳይሆን ለኅሊናቸው ያደሩ ቆራጥ ትግሬዎች እንዳሉ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን መሰል ዕንቁ ዜጋ፣ እንዲህም ያሉ ያልተዘመረላቸው ጀግኖች አሉና ሕጻኑን ከነታጠበበት ውኃ ላለመድፋት እንጠንቀቅ – የእግረ መንገድ ማሳሰቢያ ነው፡፡ በተረፈ ወያኔ ያሳለፈላቸው ትግሬዎች ብዛታቸው ቀላል ነው ባይባልም – ማይምነት በሚበዛባቸው የኛን መሰል ሀገራት እንዲህ ያለ ዘውጋዊ ጭፍን ጭፍራነት የማይጠበቅ ባለመሆኑ – በተለይ በአሁኑ ወቅት ብዙ ተጋሩ ወደ ልመና እየተሠማሩ መሆናቸውን አዲስ አበባን በማየት መረዳት ይቻላል፤ ሕጻን ዐዋቂው ከማንም ወገኑ ባልተናነሰ እየለመነ የሚገኘው ለሥለላ ሥራ – አንዳንዶቹን መጠርጠር ተገቢ ቢሆንም – ወይም የልመናን “ሙያ” ለማየት ሲባል ለድሎትና ለቅንጦት እንዳይመስለን – እንደኛው ከእውነት ተቸግሮ ነው፡፡ ሁሉም በየሆዱ ይዞ “እህህ” እያለ እንጂ የወያኔ ልምጭ ያልሸነቆጠው በዘመኑ ቋንቋ አንድም ክልል የለም፡፡ አንዱን ከሌላው እየለዩ በሀብት ማክበር ወይም ማደኽየት ደግሞ ትልቁ የወያኔ የአገዛዝ ሥልት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ እውነቱን ለመናገር አጋንንት ለሥልት ካልሆነ በስተቀር በዘርና በጎሣ አያምንም፡፡ የሊቀ ሣጥናኤል ልጆች ወያኔዎች ደግሞ እንኳንስ ለመላው ትግሬ ለእናታቸውም ልጅ የማይራሩ ልዩ ጭራቆች ናቸው – እነኚህ የእፉኝት ልጆች ለአንዳንዶቻችን የክፋት ሥራ ተመጥነው በልካችን የተሠፉ የመርገምት ልብሶቻችን መሆናቸውን ደግሞ በእግረ መንገድ መጠቆምና ይህ መለኮታዊ ቅጣት ገብቶን ከልብ እንድንጸልይበትም ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡ ልብ አድርጉ – ስብሃት ነጋ አንዳች መንፈሣዊ ኃይል በአካል ተከስቶ “ልጅህን ብትገብርልኝ አሥር ዓመት ዕድሜ እጨምርልሃለሁ” ቢለው እንዲያውም “ሌላም ልጨምርልህ እችላለሁ!” ከማለት የሚመለስ አይመስለኝም – የቆረበው በክፋት ሥራ ነውና፡፡ የወያኔዎች ብቸኛ ዘመድ ሆዳቸው ነው፡፡ ለሆዳቸውና ለሥልጣናቸው ሲሉ የማያደርጉት ነገር – የማይፈነቅሉት ድንጋይ – የማይቧጥጡት ሰማይ የለም፤ ለነሱ ያልሆነች ዓለም ብታልፍም ደንታ የላቸውም፡፡ ለነሱ ሚስትና ልጅ ብርቃቸው አይደለም – ብቸኛ ብርቃቸው ሰይጣናዊ ፌሽታና ዳንኪራ ነው – እንደሚባለውም ከሆነ ለዚህ ነው በሰይጣናዊ ምች የአልጋ ላይ ደዌ ተመትተው ብዙዎቹ በመድኃኒት እገዛ የሚኖሩት፡፡ ይህ ሥርዓት ከራስ ዱሜራ እስከራስ ካሳር ሕዝበ ኢትዮጵያን እያደኸየና ለርሀብም ለሞትም ለስደትም እየዳረገ ነው፡፡ ተባብረን ካላስወገድነው እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁላችንም በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እናልቃለን፡፡ የፋሲካው በግ በገናው በግ መሣቁን ከቀጠለ አሣራችንም በዚያው ልክ ይቀጥላል፡፡ በአንዲት ሰሞነኛ ቀልድ የምትመስል እውነተኛ ገጠመኝ እንለያይ፡፡ ብሔራዊ ትያትር አካባቢ አንድ ትግሬ ወደ አንድ መኪና ጠጋ ብሎ ይለምናል፡፡ የሚለምንባት መኪና ሹፌር – ከምን ነገድ እንደሆነ አልሰማሁም – መስኮቱን ወረድ ያደርግና “ይቺን ‹ሥራ› እንኳን ለኛ አትተውልንም?” በማለት ስሙ ብቻ ያከበረውን ምሥኪኑን ትግሬ ቀልቡን በመግፈፍ ያስኮርፍና ካጠገቡ ያርቀዋል፡፡ … የኔ ቢጤው ድሃ ሰላይ ቢሆን ኖሮ የዚያችን መኪና ታርጋ በመያዝ ወዲያውኑ ይደውልና አምባሳደርን ወይም ጥቁር አንበሣ ሆስፒታልን ሳያልፍ ያ ቀልደኛ ሹፌር ሸቤ በተባለና ከዚያም የከፋ እርምጃ በተወሰደበት ነበር – ስለዚህ ምንም እንኳን ብሶት የማያደርገው ነገር ባይኖርም ከስሜት ይልቅ እውነትና ምክንያት ይበልጥ አዋጭ ናቸውና ወገናችንን የሚያስከፋ ነገር ላለማድረግ እንጠንቀቅ፤ ሁሉም ለሚያልፍ ነገር የማያልፍ ጠባሳ እንዳናስቀምጥ አማራና ትግሬ፣ ኦሮሞና ጉራጌ ሳንል ሁላችንም ወደየኅሊናችን እንመለስ፤ ያኔ ከኛ የራቀ የሚመስለን ፈጣሪም ፊቱን ወደኛ ያዞራል – The moral of the Story. ግን ግን ፈጣሪ ፊቱን ከኛ አላራቀ ይሆን እንዴ? ዘፋኙ “ዋሸሁ እንዴ” ያለው ትዝ አለኝ – አሁን፡፡ ለነገሩ ቢያርቅስ ማን ይፈርድበታል? ያንዳንዶቻችን ዕኩይ ሥራ እኮ ወደርየለሽ ነው!

በተሻለ መንግሥቱ