Archive | March 16, 2017

እሩቅ አይደለም

qoshe 2

Alemayehu Kidanewold

ህይወት እንደቀልድ የሚቀጠፍባት ፣ ይሄም ኑሮ ተብሎ ክዚችም ላይ እድሜ ልክ ጣር ፣ ሰቆቃ፣ ለቅሶና ዋይታ….

ሃይማኖቱን ጾም ጸሎቱን በስርአት ይዘናል ባህልና ወጉን ጠብቀን ያለንን ከኛ በታች ላሉ አካፍለን መቼም አለን ከተባለ” ተከባብረን እያለን ታድያ ይሄ ሁሉ መአት ከየት ነው የሚፈልቀው

ትናንት በሊቢያ በታረዱት ስናለቅስ ከዛም በስደት ያሉ ወገኖቻችን ሲደበደቡ እና ተቀጥቅጠው ሲገደሉ ስናለቅስ በዛ ላይ በረሃብ ህጻናት ሲረግፉ እያየን ስናለቅስ በኦሮምያና በአማራ ክልል ስንቱ ሲረግፍ፥ ደሞዝ እየከፈለው ድንበር ከወራሪ ሃገርንም ከጠላት ጠብቅ የተባለው ወታደር የገዛ ወገኑ ላይ እናት ከነልጅው እንደወጡ ሲያስቀር ፣ ወጣቱን ፣ ምሁሩን፣ ገበሬውን፣ ነጋዴውን፣ተማሪውን ደመ ከልብ ሲያደርግ አረ ለማን ነው አቤት የሚባለው

ስር በሰደደ የአስተዳደር ችግር ሃገር እንደዚህ በሽፍታ መንግስት ስትመራ አለም ወደፊት ስትሄድ እኛ ወደሁዋላ ስንጎተት የኑሮው ውድነት፣ የመብራት የንጹህ ውሃና የስልክ ያለመኖር፣ የጤና ችግር፣ መሰረታዊ ለሰው ልጅ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች መጉደል፣ ሙስናው፣ የመሬት ሽያጩ ፣ ዘረኝነቱ እረ ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል

ይሄ ሁሉ ነገር ግን የሚያበቃበት ጊዜ ቅርብ ይመስለኛ መከራው ሲሞላ ግፉ ሲያንገሸግሽ አንገት መድፋቱ ሲያበቃ ሁሉም በአንድ ላይ ሆ ብሎ ሲነሳ የዛን ሰአት ኢትዮጵያ ታላቁዋን ኢትዮጵያ ትሆናለች::

ትውልድ የሚያፍርባትና የሚያለቅስባት ሃገር ሳትሆን ሁሉም የሚኮራባት በነጻንትና በደስታ የሚኖርባት ቅድስቲቱ ኢትዮጵያ

ትሆናለች::አዎ እመኑኝ እሩቅ አይደለም::

አቅመ ቢስነት ሰለቸኝ!!! ሁልጊዜ ዋይታ ሁልጊዜ ጩኸት ሁልጊዜ ወደ ውስጥ ማልቀስ!!!

qoshe

በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ በሚባል ሰፈር የደረሰውን አሰቃቂ አደጋ በተመለከተ በብዙ ኢትዮጵያውያንና የትግል አጋሮቼ ብዙ ሲባል እኔ የተዘበራረቀ ስሜት ላይ ሆኜ ምንም ማለት አልቻልኩም፡፡አደጋውን ስሰማ አቅመ ቢስነትና የበታችነት ስሜት ተሰማኝ፡፡ በሁለት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከሰው በታች ተቆጥረው በሳውዲ አረቢያ ሲታረዱ ፣በደቡብ አፍሪካ ሲታረዱ፣በሊቢያ ሲታረዱ፣በጋምቤላ ሲታረዱና ታፍነው ሲወሰዱ፣በሀገራቸው የፀጥታ ሃይል በኮንሶ፣በኦሮሚያ በአማራ ክልሎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፣ባህላቸውን ለማክበር ኤሬቻ ላይ የተገኙ ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ሲያጡ፣ በቂልንጦ ማረምያ ቤት ዜጎች በቁማቸው ሲቃጠሉ ዛሬ ደግሞ የቆሻሻ ክምር ተንዶባቸው ለመስማት በሚከብድ ሁኔታ ህይወታቸውን ሲያጡ ያደረግነው ነግር ቢኖር ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይስጥልን የሚል ሀረግ በፌስ ቡክ ገፅ ላይ መለጠፍ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ከጓዶቼ ይድነቃቸው አዲስ፣ ማዕዛ መሀመድ፣ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ወይንሸት ስለሽ፣ምዕራፍ ይመርና አዲሱ ጌታነህ ጋር በቦታው ተገኝቼ ሳየው አደጋው የደረሰባቸውን የሚያወጡበት ሁኔታ ስመለከት የማሽን ሰራተኞችና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መደበኛ ስራቸውን የሚያከናውኑ እንጅ የሰው አካል የሚያወጡ አይመስልም፡፡ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና የእርዳታ ድርጅቶች መኖር ሲገባቸው አካባቢውን የወረረው የፖሊስ ሀይልና ደህንነት ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን ስቃይ መቼ እንደሚቆም፤ መንግስት አደጋ በተከሰተ ቁጥር የሀዘን ቀን ማወጁን እኛም እስከመቼ RIP እያልን እንደምንቆይ አላውቅም፡፡ ለእኔ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የክፉ አገዛዝ ውጤቶች እንጅ መንስኤ አይደሉም፡፡ ስለሆነም መፍትሄው ኢትዮጵያን ከግፍና ከጭቆና ወደ ዴሞክራሲ ማሸጋገር እና የኢትዮጵያን ህዝብ የሀገሩ ባለቤት ማድረግ ነው፡፡ ያኔ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህ ይሰፍናል፣የኢኮኖሚ እኩል ተጠቃሚነት ይረጋገጣል፣ነፃነት በሀገራችን ማበብ ይጀምራል፣የኢትዮጵያ ልጆችም በተሰማሩበት መስክ ሁሉ የግልና የጋራ ጥቅማቸውን ሚዛን በመጠበቅ ያለመታከት ይሰራሉ፣ያኔ ኢትዮጵውያን ከገባንበት የውርደት ማጥ ተነስተን ወደ ብልፅግና ተራራ መትመም እንጀምራለን፡፡ ከዚህ ውርደት ለመውጣት የኢትዬጵያ ህዝብ በአንድነት መቆም አለበት!!!

የሞቱትን ነፍስ ይማር ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይስጥልን፡፡