የወያኔ የዝርፊያ ድርጊት – በኤርምያስ ለገሰ የመለስ ልቃቂት


ይገረም አለሙ

አዩትና ልቡ እንደሞተበት
አባቱ ቀየ ላይ ወርደው ጠመዱበት

የኤርምያስ ለገሰን የመለስ ልቃቂት መጽኃፍ እያነበብኩ ነው፡፡ የወያኔ የዝርፊያ ድርጅቶችን አይነትና ብዘት በተለያየ ግዜ በተለያየ መንገድ እየተነገረም እየተጻፈም ያውቃናቸው ቢሆንም ይህን ያህል ዝርፊያ መፈጸማቸውን የሚያውቅ ብዙ  ሰው የነበረ አይመስለኝም፡፡ ኤርምያስ የካድሬነት ቆይታውም ሆነ የኮሙኒኬሽን ምኒስቴር ዲኤታነቱ  ዘራፊዎቹን ድርጅቶች በቅርብ ለማወቅ ያስቻለው በመሆኑ የሚያስነብበን በመረጃ እና ማስረጃ የተረጋገጠ እውነት ልብ ያቆስላል፡፡ ከወያኔዎቹ ድፍረት የእኛ ዝም ብሎ ሀገር ማዘረፍ ጥያቄ ያጭራል ቁጭት ይፈጥራል፡፡ ግና እኛ ከህውሀት በተቃራኒ የቆምን ነን የምንል ወገኖች ከአንድ ሳምንት የሚያልፍ ቁጭት፣ ንዴት፣ ምሬት፣ ወዘተ አያውቀንም እንጂ፡፡Yemeles Likakit book cover

አቶ ኤርምያስ የገለጸውን የወያኔ ዘረፋ ሳነብ “አረሱት መተማን የእኛን የእኛን እጣ፣ አረሱት እራያን የእኛን የእኛን ዕጣ፣ እነርሱ ምን ያርጉ ከእኛ ወንድ ሲታጣ” የሚለው ቀረርቶ ታወሰኝ፡፡ በትንሽ በትንሹ አንድ ሁለት እያሉ ሞከሩ፣ አዩን፣ ገመቱን፣ ምንም የተቃውሞ ምላሽ ስላልገጠማቸው የዘረፋውን አይነቱንም ስልቱንም አሳድገው ቀጠሉ፤ ዝርፊያው ጎልቶም ጎልብቶም ሲታይም ከአንድ ሰሞን ጫጫታ ያለፈ ነገር አልገጠማቸውምና  “አዩትና ለዩትና ልቡ እንደሞተበት፣ አባቱ ቀየ ላይ ወርደው ጠመዱበት” እንደሚባለው የሀገሪቱን ሀብት በሙሉ በማግበስበስ እንድም ወደ ትግራይ ሁለትም ወደየኪሳቸው ማድረጉን ተያያዙት፡፡ ሰውየው “ሚስትህ አረገዘች ወይ ቢሉት፣ ማን ወንድ ብላ አለ እንደሚባለው ማንን ፈርተው ምንስ አስፈርቷቸው ዝርፊያውን ያቁሙ!

የአቶ ኤርሚያስ የመለስ ልቃቂት መጽኃፈ እንደሚነግረን ከዘራፊው ህውሀት በላይ አዘራፊዎቹ ለጌታ አደሮች ትልቁን ድርሻ ተጫውተዋል እየተጫወቱም ነው፡፡ እነርሱ መቼም አንዴ ህሊናና ሆዳቸው ቦታ ተለዋውጧልና ምን ተባለ ምን ላይሰማቸው ይችላል፡፡ እነዚህ በስም ተጠቅሰው፣ ጸያፍ ምግባራቸው በማስረጃ ተደግፎ የተገለጸ ሰዎች ሚስቶችና ልጆች ይህን መጽኃፍ ሲያነቡ ምን ይሰማቸው ይሆን? የልጅና የሚሰት ማፈሪያ ከመሆን ፈጣሪ ይጠብቀን፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን እውን ሆኖ የህግ የበላይነት ሊሰፍን ከቻለ የአቶ ኤርምያስ መጽኃፍ ወንጀለኞችን ለመለየትና ለወንጀላቸውም መረጃና ማስረጃ ለማሰባሰብ መንገድ መሪ ነው ፡፡

ይህን የሚያህል ህውኃቶች ኢትዮጵያን እየጋጡ ሳያላምጡ የሚውጡበትን ወንጀል የፖለቲካ ድርጅቶች በዝምታ መመልከታቸው ከተናገሩም ብለን ነበር ለማለት ያህል መሆኑ ያስገረመው ኤርምያስ በገጽ 425 ላይ “ታዲያ ኩባንያዎችን በተመለከተ በተቀዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ አመራሮቻቸው ዘንድ “ተከድኖ እየበሰለ” ያለው ጥያቄ ምንድን ነው? ይህ በግልጽ መመለስ ያለበት ግን ደግሞ በከፍተኛ ፍራቻ የማይገለጠው ቁም ነገር በእነዚህ ፋብሪካዎችን የንግድ ተቋማት የትግራይ ህዝብ ተጠቅሟል ወይ? የትግራይ ህዘዝብ ጥቅም እያገኘ እንዳልሆነ ለምን ራሱ ምስክርነት አይሰጥም የሚለው ሆኗል፡፡ ርግጥም መጠቀም ማለት ምን ማለት ነው? እውነት ትግራይ ለምታች ወይ? ተጠቅማለች ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ግልጽ ምላሽ የሚያሻቸው ናቸው፡፡ እየተነገረ ያለው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፍ በሞኖፖል የየዘ ድርጅት ስለሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጠ ድርጅትም ሆነ በህዝቡ እይታ አቋማቸው መታወቅ ይኖርበታል፣”  ይላል፡፡

የፖለቲከኞቹ ዝምታ አጠያያቂ፣ አቋማቸው መታወቁም አሰፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ነገረ ግን ኤርምያስ በስፋትና በግዝፈት ያነሳውን ዘረፋ ከትግራይ መጠቀም አለመጠቀም ጋር አያይዞ ጥያቄ ማንሳቱ ጉዳዩ የሚያሳንሰውም ዋናውን አቅጣጫ የሚያስተውም ሆኖ ታየኝ፡፡ ይህን ለማሳየት በ1992 ምርጫ ክርክር ወቅት ስለ እነዚህ ድርጅቶች የተባለውን ማስታወሱ የሚጠቅም ይሆናል፡፡በወቅቱ የእነዚህ ድርጅቶች ጉዳይ በፖለቲካ ፓርቲዎቸ ዘንድ በስፋት ይነሳ ነበር፡፡ በተለይም በወቅቱ አዲስ የተመሰረተው ኢዴፓ ዋንኛ የመከራከሪያ አጀንዳ አድርጎ ይዞት ነበር፡፡ ታዲያ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ በነበረ የክርክር መድረክ ጉዳዩ ሲነሳ በኢህአዴግ በኩል በትጥቅ ትግል ወቅት ያፈራነው ሀብት ነው መነሻው፤ ሥልጣን ስንይዝ ምን እንዳረገው እንበትነው፣ እንከፋፈለው ወዘተ የሚል የብስጭት ምላሽ ሲሰጥ፤ ከተቀዋሚው ወገን እኛ ህውሀትን የምናውቀው ጠመንጃ ይዞ ዱር ቤቴ ብሎ መዋጋቱን እንጂ በንግድ ስራ መሰማራቱን አይደለም፣ድርጅቶቹ የተመሰረቱት ጫካም እያላችሁ ወደ አዲስ አበባማ ስትጓዙ መንግስትም ከሆናችሁ በኋላ ከህዝብ በዘረፋችሁት ንብረት ነው፡፡የሚል ምላሽ ተሰጠ፡፡

በቀጣዩ ቀን ኢህአዴጎች ትንሽ የቅርጽ ለውጥ አድርገው፡ ድርጅቶቹ የህዝብ ሀብት ናቸው፣ የትግራይ ህዝብ፣ የአማራ ህዝብ የኦሮሞ ህዝብ፣ የደቡብ ህዝብ ንብረት ናቸው የሚል መከራከሪያ ይዘው ቀረቡ፤ ከተቀዋሚው ወገን ለዚህ የተሰጠው ምላሽ በመዝጋቢው መስሪያ ቤት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በተጠቀሱት ስሞች የህዝብ ንብረት ተብሎ የተመዘገበ ድርጅት የለም የሚል ነበር፡፡ በዚህ ግዜ አንድ  ከነገረ ሥራው ጉዳዩ ያልገባው መሆኑ የሚያስታውቅ የኦህዴድ ካድሬ በንዴት ስሜት በድንገት ከመቀመጫው በመነሳት የኦሮሞ ህዝብ ንብረት የሚባል የለም ብሎ ሲናገር አዳራሹ በሳቅ ተሞላ፡፡

በሶስተኛው መድረክ  አቶ በረከት ተገኘና ድርጅቶቹ ለትርፍ የማይሰሩ፣ መንግስትና የግል ባለሀብቶች ሊሸፍኑት የማይችሉትን የልማት መስክ የሚሸፍኑ ኢንዶውመንቶች ናቸው፡፡  የማን ናቸው ምንድን ናቸው የሚለው ላይ ማተኮሩ ምን ይጠቅማል፤ ምን እየሰሩ ነው የሚለውን ማየቱ ነው የሚሻለው ወዘተ በማለት ድርጅቶቹ ሰሩት እና እየሰሩ ነው ያለውን በመዘርዘር አዲስ መከራከሪያ አቀረበ፡፡ተቀዋሚዎችም ከህውሀት ድርጅቶች አንዳቸውም በኢንዶውምነት ስም እንዳልተመዘገቡ፤ተግባራቸውም ከዚህ የራቀ መሆኑን፣ ሁሉም አትራፊ ብቻ ሳይሆኑ የግል ባለሀብቱን እየተጋፉ ከገበያ የሚያስወጡ እንደሆኑ ወዘተ በመጥቀስ ተከራከሩ፡፡

የማን ናቸው እንዴት ተመሰረቱ፣ የሚለውን ትታችሁ ምን እየሰሩ ነው ብሎ መጠየቁ ነው የሚበጀው የሚለው የበረከት አቀራረብ የህውኃትን አቅጣጫ የማስቀየሪያ የተለመደና እስካሁንም የቀጠለ አካሄድ ያሳየ ነበር፡፡ ትኩረት ማስቀየር፣ አቅጣጫ ማስለውጥ አንዱን ለማድበስበስ ሌላ አጀንዳ መስጠት የተለመደ የወያኔ ተግባር ሲሆን አብዛኛው ተቀዋሚም ይህን ለምዶ ወያኔን ተከትሎ ይነጉዳል  በሚያቀብለው ኳስ ይጫወታል  እንጂ ነገሮችን አዋጭና ወያኔን መፈናፈኛ ማሳጣት በሚያስችል መልክና መንገድ ማስኬድ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ከዛ በኋላ የፖለቲካ ድርጅቶች በወያኔ የዘረፋ ድርጅቶች ጉዳይ አቋም ይዘው ሲናገሩም ሆነ ሲጠይቁ ያልተሰሙት፡፡

በእነዚህ ድርጅቶች የትግራይ ህዝብ ተጠቅሟል አልተጠቀመም የሚል ጥያቄ በአብይነት ሲነሳ ከ15 ዓመታት በፊት  በረከት አትንኩት ያለውን ዋናውን የድርጅቶቹን ማንነት፣ ምንነትና እንዴትነት ጥያቄ ወደ ጎን ማድረግና ወያኔ በሚፈልገው ስልት መጫወት ይሆናል፡፡እውነታው ይህን አያሳይም እንጂ በእነዚህ ድርጅቶች የትግራይ ህዝብ ተጠቅሟል አልተጠቀመም ለሚለው ጥያቄ ምላሹ አዎ ተጠቃሚ ነው የሚል ቢሆን ድርጅቶቹ ተቀባይነት ሊኖራቸው ነው ማለት ነው? አይመስለኝም፡

መነሳት ያለበት ጥያቄ ሆኖ የሚታየኝ፣

1–እንዴት ተመሰረቱ፤ ከዚህ ጥያቄ የሚገኘው ምላሽ እነርሱ እንደሚሉት በትጥቅ ትግል በተገኘ ገንዘብ፣ ወይንስ ሌሎች እንደምንለው ከሀገር  በተዘረፈ ሀብት የሚለውን ያሳያል፡፡ ያለጥርጥር የሚገኘው ምላሽ በማስረጃ የሚረጋገጠውም ድርጊት ሁለተኛው ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በተዘረፈ ሀብት የተቋቋመ ድርጅት ማንም ይሁን ምን፣ እንዲሁም ምንም ያድርግ ምን ከተጠያቂነት ነጻ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የህውሀት የዘረፋ ድርጅቶች ( የንግድ የሚለው መጣኝ ስም አይመስለኝም) ለአብዛኛው የትግራይ ነዋሪ ምንም ባልጠቀሙበት ሁኔታ ቀርቶ ለእግሩ መራመጃ ወርቅ ቢያነጥፉለት፣ በየ ቤቱ ወተት በቧንቧ ቢያስገቡለት እንኳን ከተጠያቂነት  ነጻ ሊሆኑ አይችሉም፡፡

2-እንዴትና ምን ሰርተው አደጉ፣ ተመነደጉ፤ በወሬ ደረጃ እናውቀው እንደነበረውና አቶ ኤርምያስ በማስረጃ እንዳረጋገጠልን እነዚህ ድርጅቶች ያደጉ የተመነደጉት በንጹህ ሰርተው በነጻነት ተወዳደረው አይደለም፡፡ የድርጅቶቹ ባለቤቶች መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው እቃዎችን ከቀረጥ ነጻ ከማስገባታቸው በላይ ከባንክ ተበድረው አለመክፈላቸው፣ ሲበዛም እዳ ማሰረዛቸው፣ የመንግስት ድርጅቶችን ንብረት ወስደው የራሳቸው ከማድረጋቸው በላይ ለባለንብረቶቹ መልሰው በማከራየት ተጠቃሚ መሆናቸው፣ ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር በሚል ሰበብ በአነስተኛ ዋጋ ድርጅቶችን ከመሰብሰባቸው ባሻገር እነርሱ ከሚያመርቱት ምርት ጋር ተመሳሳይና በገበያ ተፈላጊ የሆነ ምርት የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን መንግስታዊ ሥልጣንን በመጠቀም ከገበያ በማስወጣት ወይንም ተፎካካሪ እንዳይሆኑ በማዳከም፡ ገበያውን ለብቻቸው መያዛቸው ( የጨርቃ ጨርቅና የስሚንቶ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ) ወዘተ የከፋ ወንጀል ነው፡፡ ሌላም ሌላም ይጠቀሳል፤

ስለሆነም እነዚህን ድርጅቶች ማንነታቸው፣ ምንነታቸውና እንዴትነታቸው ላይ ሳይሆን ለትግራይ ህዝብ በመጥቀም አለመጥቀማቸው ላይ ማተኮርና በዚሁ ለመመዘን መሞከር ፖለቲካዊም ህጋዊም አካሄድ አይመስለኝም፡፡

ግን ግን  ይህ ሁሉ በአቶ ኤርምያስ የመለስ ልቃቂት መጽኃፍ የተገለጸው ዝርፊያ ሲካሄድ እኛ የት ነበርን? ብለን በየግል ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ውሻ ልጆቿን ሰብስባ ምን ቢርባችሁ እሰው ቤት ገብታች እቃ እንዳትደፉ የውሻ  ልጅ ተብላችሁ ታሰድቡኛላችሁ በማለት ትመክራቸዋለች፡፡ በዚህ ግዜ ከመሀል አንዷ ተከፍቶ ካገኘንስ በማለት ስትጠይቃት   አፍሽ እስኪከቱልሽ ልትጠብቂ ነው በማለት መለሰች እንደሚባለው ወያኔ ኢትዮጵያን ክፍቷን አገኛትና ጫካ ሆኖ ሲጎመዥበት የነበረውን ነገር ሁሉ እየዘረፈ ሳያላምጥ ዋጠ እየዋጠም ነው፡፡ ራሳችንን እንጠይቅ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s