“ነፍጠኛ” – “ትምክህተኛ” – እየመጡ ላሉት መጽሐፎቼ መንደርደሪያነት !


(መላኩ አላምረው)

የዛሬ ሦስት ዓምት ነው። በአንድ መንግሥታዊ “የበጀት መዝጊያ” ስብሰባ ላይ (የመንግሥት ሠራተኛ በመሆኔ) ታድሜያለሁ። የስብሰባ አጀንዳው “የተቋሙ ያለፈው በጀት ዓመት አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች” የሚል ሆኖ ሳለ ክቡር ሰብሳቢ በምንም በምንም እያሳበበና እያጠጋጋ እነዚህን “ነፍጠኛ” እና “ትምክህተኛ” የሚሉ ቃላትን ደጋግሞ በመጥራት አዛገኝ። “ነፍጠኛውና ትምክህተኛው የአማራ ሥርዓት እንዲህ አድርጎን… እንዲህ ፈጥሮን… ላለፉት ሺህ ዓመታት ብቻውን ተጠቅሞ… አሁን ዕድሜ ለኢህአዴግ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ሆነ…”… በቃ ይወርድብን ጀመር። አማላክ በፈቃዱ ከአማራ ክልል የፈጠረን ኢትዮጵያውያን (ያውም ሙልጭ ያልን የድሃ ልጆች) የዚህ ትችት ሰለባ መሆናችን ግርምምም ብሎኝ ስሰማ ቆየሁ። በኋላ የጥያቄና አስተያየት ዕድል ሲሰጥ እጅ ለማውጣት የቀደመኝ አልነበረም። ተሰጠኝ። በንዴት ተናገርሁ።
.
“ሲጀመር አማራ ልዩ ተቃሚ መሆኑ ያስቃል። ሲቀጥል ‘ነፍጠኛ’ እና ‘ትምክህተኛ’ የሚሉ ቃላትን ትርጉም ሳትረዱ ብዙ በማውራታችሁ ማፈር ነበረባችሁ።”
ታዳሚው ፀጥ አለ።
“ፀጥ አለ በእናንተ ቤት እነዚህ ቃላት ስድብ ናቸው። ታሳዝናላችሁ። ሳያስተውሉ የሚሰሟችሁን የእናንተ ቢጤዎችም ታስታላችሁ። ለእኔ ግን ነፍጠኝነት ጀግንነት ነው። አነጣጣሪነት፣ ኢላማ መችነት፣ ጠላት ድል ነሽነት። ምናልባት ይህ ስያሜ ለአማራው የተሰጠው በጣልያን ጊዜ ባደረገው ጠላትን ለይቶ የመምታት ጀግንነቱ ይሆናል። እናንተ እንደምትሉት በወንድሞቹ ላይ ግፍ የፈፀመ አማራ የለም። ሕዝብን በዚህ መልኩ መዝለፍ አላዋቂነት ነው። ቢገባችሁ ነፍጠኝነትን ለአሁኑ የድህነት ትግል በተጠቀማችሁበት። ሕዝቡ ሁሉ ነፍጠኛ ሆኖ ድህነትን እንዲዋጋ በሰበካችሁበት። በነፍጠኝነት አነጣጥሮ የድህነትን ጭንቅላት መትቶ መጣል ያባቶቻችን ልጆች ያደርገናል ባላችሁትና ለበጎ በተጠቀማችሁበት። ይህንን ቃል ላንድ ብሔር ስድብ ለማድረግ መሞከር ትርፉ ምን ይሆን? ነፍጠኛ ማነው? አዎ በላይ ዘለቀ ነፍጠኛ ነው። ጀግና አላሚ፣ ጠላትን አነጣጥሮ የሚመታ ነፍጠኛ። ግን በላይ ብቻ ነው? በፍጹም። ራስ አሉላ ነፍጠኛ ነው። ጠላትን ለይቶ የሚመታ ጀግና ነፍጠኛ። አብዲሳ አጋም ጀግና ነፍጠኛ ነው። ምነዋ ይህ ስም ላንድ ብሔር ተሰጠ? ለእኔ ግን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ነፍጠኞች ነን። ለጠላት የማንበረከክ አልሞ ተኳሾች። ይህ ደግሞ አኩሪ እንጅ አሳፋሪ አይደለም። ስድብ ልታደርጉት የምትደክሙ ሁሉ ባለማወቃችሁ ልክ ራሳችሁን ትሰድባላችሁ። አዎ የነፍጠኛ ልጅ ነፍጠኛ ነኝ። አያቶቼ ጥይትን ወደ ጠላት ተኩሰው ነፃ ሀገር አስረከቡኝ። እኔ ደግሞ የፍቅር ባሩድን ታጥቄ የአንድነትን ፍላፃ በጥበብ እየተኮስሁ ዘረኝነትንና ጥላቻን አነጣጥሬ የምመታ ነፍጠኛ ነኝ። መቼም በዚህ ስም አላፍርም።
ትምክህተኛም ነኝ። ትምክህት እናንተ እንደምትሉት አይደለም። የአማራ ትምክህቱ አንዲት ሀገሩ እንጅ ሌላ ምንድነው? በሀገር የማይመካ እርሱ ምንድነው? ትምክህተኛ ልቦች ናቸው ለሀገር መስዋዕት እስከመሆን የፀኑት። ካሣ (አፄ ቴዎድሮስ) ሀገሩን አንድ ለማድረግ የተነሳው በትምክህተኝነቱ ነው። ለሀገሬ እኔ አስገልጋታለሁ ማለት ነው ትምክህት። ይህ ስህተት ነው? የበላይ ዘለቀ የአርበኝነት ስንቁም ትምክህት ነው። ሀገሬን ነፃ የማደርጋት እኔ ነኝ ብሎ ጠላትን እንዲወጋ ያደረገው ትምክህቱ ነው። ግን ትምክህተኞቹ እነርሱ ብቻ አልነበሩም። በመላው ሀገሪቱ ነፍጥ አንግበው ጠላትን የተዋጉ ሁሉ ልባቸው በትምክህት የተሞላ ልበ ሙሉዎች ነበሩ። ለሀገራችን ያለናት እኛ ነን… ብለው የተመኩ ጀግኖች ናቸው ነፃ ምድርን ያወረሱን። ትምክህት እንዴት ባለ ትርጉም ስድብ ሆነ? ለትምክህት ‘እኔ ብቻ’ የሚልን ራስ ወዳድነት ማን ሰጠው? ይልቅ ምናለ ትውልዱ ሁሉ በሀገሩ እንዲመካ ብታደርጉት። ሁሉም ልቡ በትምክህት ተሞልቶ ለዚህች ሀገር ያለናት እኛ ነን… ከድህነቷ የምናወጣትም እኛ… ቢል ምናለበት? የኃያላን ሀገሮች የብልጽግና ምሥጢር ትምክህተኝት መሆኑን ሳታውቁ ነው እንዴ ሀገር የምትመሩት??? ጃፓናውያን እንዳይስቁባችሁ… ጀርመኖችም እንዳይሳለቁባችሁ። ይልቅ ይህንን ትውልድ ከአንዲት ሀገር ትምክህቱ አውርዳችሁ ዘረኛ ስታደርጉት ነው ማፈር ያለባችሁ። በአንዲት ሀገር ትምክህት ያልተሞላና የተከፋፈለ ሕዝብ ይጠፋልና። ደግሞ ከአማራ ሕዝብ ራስ ውረዱ። እኔ አንዱ የዚህ ሕዝብ ልጅ ነኝ። በጣም ደሃ ቤተሰቦቼን ተምሬ ላግዝ የምለፋ ባተሌ ሆኜ እያለ ልዩ ተጠቃሚ ነበርህ ስትሉኝ እንዴት ልስማችሁ? የዘመዶቼን የኑሮ ሁኔታ እያወቅሁት ከልዩ ተጠቃሚ ሕዝብ እንደመጣሁ ስትነግሩኝ አልሰማችሁም። እኔ የተማርሁት ወንድሞቼ ከክልላቸው ርቀው በመሄድ የቀን ሥራ እየሰሩና እናት አባቴም እየተበደሩ ነው። ይህንን ያደርጉት ተመርቄ እንደምመልስላቸው ተስፋ አድርገው ነው። ያልመለስሁት ዕዳ አለብኝ። በዚህ ዕዳ ውስጥ የምኖር ተስፈኛ ወጣት በማንም ልሰደብ አይገባኝም። ሀገሬን የምወዳት በሀብቷ አይደለም። በሀገርነቷ ብቻ እንጅ።”
.
በስሜት ብዙ ተናገርሁ። ተሰብሳቢው በጭብጨባ አገዘኝ። ልቤ በወገኔ ተመካ።
እናም ከዚያች ዕለት ጀምሮ ስለ “ነፍጠኝነት እና “ትምክህተኝነት” አብዝቼ አስብ ጀመር። እነዚህን ቃላት ለበጎ ዓላማ መጠቀም እየተቻለ ለምን ለስድብነት እንደተመረጡ አልገባህ አለኝ። ማንም ምን ቢል ግን እኔ በእነዚህ ቃላት መሸማቀቅ እንደሌለብኝ ወሰንሁ። ወስኖ መቀመጥ ብቻም ሳይሆን “ነፍጠኛ እና ትምክህተኛ” ሆኜ ለሀገር አንድነትና ለሕዝብ ፍቅር የራሴን ድርሻ ለመሥራት ተነሳሳሁ። ምንም ነገር ባይኖረኝ ቢያንስ ሀገሬ በደሃ ገበሬዎቿ ግብር አስተምራ ያስጨበጠችኝ መጠነኛ እውቀት አለችኝ። ይህንን ለበጎ መጠቀም አለብኝ።
.
አዎ አባቶቼና አያቶቼ ነፍጠኞች ነበሩ። ጠላትን ለይተው አነጣጥረው የመቱና ነፃ ምድር ያስረከቡኝ። እኔም ነፍጠኛ መሆን እችላለሁ። አሁን ላይ ሀገሬን እየበከላት ያለን “ዘረኝነት” የሚባል ጠላት ለይሼ ለመምታት የፍቅርን አረር በጥበባዊ ስንኝ መተኮስ እችላለሁ። ድህነትም በነፍጠኞች ተለይቶ ሊመታ የሚገባው አደገኛ ጠላት ነው። ይህ ሁሉ ግን ያለ አንዲት ሀገር ትምክህት አይቻልም። በሀገሬ የምመካ ትምክህተኛም ነኝ። ለሀገሬ በጣም ያማስፈልጋት ውድ ልጇ ነኝ።
ብዕሬን እንደ ነፍጥ አነሳለሁ። የፍቅርን ባሩድ እታጠቃለሁ። የሀገሬን ትምክህት እደርባለሁ። እያነጣጠርሁ እተኩሳለሁ። የሀገር ልዩ ጠላቶችም ይመታሉ። ይህንንም ለማሳካት ሁሉንም አስተባብራለሁ። ልክ እነ በላይ ዘለቀ ከመላው ሀገሪቱ የተነሱ አርበኞችን አስተባብረው ጠላትን እንዳንበረከኩ… ለእኛም ይቻላል። እነ አብዲሳ አጋ በባዕድ ሀገር ቅኝ ግዛትን እንደታዋጉ ለእኛ ይቻላል።

ዘረኝነትን ለመውጋት ነፍጠኛ መሆንን የወደደ ሁሉ ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ መነሳት አለበት። ዘረኝነት ሲሸነፍ ድህነትም እጅ ይሰጣል። በአንድነትና በፍቅር በታሰረ የተባበረ ክንድ የማይሸነፍ ጠላት የለም።
….
ይህንን ሁሉ የምለፈልፍላችሁ….. ከነገ ጀምሮ በፌስቡክ መተዋወቅ የሚጀምረው የመጀመሪያው መድበሌ “ስያሜ” ከእንዚህ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ መሆኑን ለመጠቆም ነው። (ሌላውም ቀጣይ መጽሐፌ ከእነዚህ ጉዳዮች አይርቅም።)
ርዕሱን መገመት ይቻላል….. የማይቻለው መድበሉን አለመግዛት ብቻ ነው።
መልካም ሰንበት።

“ነፍጠኛ” – “ትምክህተኛ” – እየመጡ ላሉት መጽሐፎቼ መንደርደሪያነት !

melaku alameraw

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s