Archive | July 30, 2017

ዝክረ ጴጥሮስ በሐምሌ 22

abune Peteros
አቡነ ጴጥሮስ በኢጣልያኖች በአደባባይ ሲገደሉ ሂደቱ እና በዕለቱ የታዩት ክስተቶች ምን ይመስሉ ነበር::
የጣልያንን ወረራ ለመከላከል በ1928 አዋጅ በታወጀ ጊዜ በወቅቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ ንጉሠነገሥቱን ተከትለው ወደማይጨው ዘመቱ። በ1928
ሐምሌ 21 ቀን የተባበሩት የአርበኞች ግምባር አዲስ አበባ ላይ የሠፈረውን የጠላት ጦር ለመዋጋት በአደረገው ቀጠሮ መሠረት አቡነ ጴጥሮስ በነደጃዝማች አበራ ካሣ ይመራ ከነበረው የሠላሌ ጦር አብረው ወደ አዲስ አበባ ገቡ። ይህ ጦር ግን የሚፈለገውን
ውጤት አለመምጣቱን በመገንዘብ ወደመጣበት ሢያፈገፍግ አቡነ ጴጥሮስ የአዲስ አበባን ህዝብ ሠብከው በጠላት ላይ ለማሥነሣት በማሠብ ከጦሩ ተለይተው አዲስ አበባ ቀሩ። ብዙም ሣይቆዩ አንድ ቀን ብቻ እንደቆዩ የጦር አለቆች ፊት ቀረቡ።
አቡነ ጴጥሮስ ጳጳሰ ዘምስራቅ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ
ብፁእነታቸው ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት ‘ኮርየር ዴላሴራ’ (corriere della sera) የተባለው ጋዤጣ ወኪል እና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው ‘ፖጃሌ’ የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓም አዲስ አበባ በነበረ ጊዜ ሂደቱን ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ፅፎ ነበር
“ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ ያለና መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሠየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል ‘ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም ዐምፀዋል፣ ሌሎችንም አንዲያምፁ አድርገዋል’ የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም ‘ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቂርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ አርስዎ ለምን ዐመፁ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?’ ሲል ጠየቃቸው ፡፡ አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መለሱ”፡፡
“አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ አኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተ ከርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ከርስቲያኔ አቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣረዬ ብቻ የምናገረውን አናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡
ይሀንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእከት አስተላለፉ፡፡
”አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡ እንጂ በጎ ለመሥራት፣ እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ህገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከለ። ነጸነታችሁን ከሚረክስ ሙታቹህ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን።”
እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣሊያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርገ፡ም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጎመም፡፡ አኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበበ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ሐላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቢ ተቀምጦ ስለ ነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለ ገለጠልኝ ነው፡፡ እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተስበስቡት ጣሊያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበበ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰማ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር”።
ሆኖም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረበቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ ቀረ። ቀጥሎም ብፁእነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ ርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞታቸው ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣልያ የእጅ ሰላምታ ዓይነት እጁን እንዲያነሣ ታዘዘ። በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን ዐውቀው ስዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ምንም ፍርሃት አይታይባቸውም ነበር። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ ታላቅ ፍርሃትም በፈቱ ላይ ይታይ ነበር።
ይሙት በቃ የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉኖ ደከሞአቸው ስለ ነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲ ቀመጡም ፈቀደላቸው፡፡ በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኩዋቸው። ብፁዕነታቸው እስከ መቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ የሆነ ፍጹም ቆራጥነት ይታይባቸው ነበር፡፡
የሀገራቸው በጠላት መወረር የሕዝበቸው መገደልና መታስር የቤተ ከርስቲያናቸው መደፈር እስከ ሞት ያደረሳቸው እኒህ እውነተኛ ጳጳስ ሐምሌ 22 ቀን ለመገደል ሲወስዱ ጥይት አልፎ ሌላ ሰው እንዳይጎዳ ግንብ ይፈለግ ጀመር፡፡ ሩቅ ባለመሔድ ከመካነ ፍትሑ 10 ሜትር ርቆ ግንብ ያለው መግደያ ቦታ ተገኘና ወደዚያ ተወስዱ። ከገዳዮቹም አንዱ ‘ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉገ?’ ሲል ጠየቃቸው፡፡ ‘ይህ የአንተ ሥራ ነው’ ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ’፡፡ ከመግደያውም ቦታ እንደ ደረሱ ወንበር ቀረበላቸውና ፊታቸውን ወደ ግንቡ ጀርባቸውን ወደ ሕዝቡ እድርገው እንዲቀመጡ ሆኑ።
ከዚያ በኋላ ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ ርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ ‘ተኩስ’ በማለት ትእዛዝ ሲስጥ ስምንቱም ተኩስው መቱዋቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አላመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው፡፡ የብፁዕነታቸው አሰክሬን ማንም እንዳይወስደው በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ውጭ ማንም በማያውቀው ቦታ በምሥጢር አንዲቀበር ተደሪገ። በዚያች ሌሊት በአዲስ አበባ ውስጥ በየቤቱ ልቅሶና ዋይታ ሆነ”
በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ” ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቆአቸው እርስቸውም የሚክተለውን ተናግረዋል።
“አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከ ኪሳቸው ክተቱት። ወዲያው ወታደሮች በሩምታ ተኩስው ገደሉ ዋቸው። ይህ እንደሆነ አስገድዶ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ።
ማታ ከአስገዳዩ ኮለኔል ጋር ተገኖኝተን ስንጫወት ‘በዚህ ቄስ መገደል አኮ ሕዝቡ ተደሰቷለ’ እለኝ ‘እንዴት?’ ብለው ‘አላየህም ሲያጨበጭብ’ አለኝ። እኔም ‘ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጨበጭባል’ አልኩት። ‘እንዴት?’ ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት። እሱም አሳየኝ። ከዚህ በኋላ ” የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቼአለሁ” ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ስዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተስንጥቋል። መስቀሉም ልክ በመሐከሉ ላይ ጥይት በስቶት ወጥቷል። የኪስ ስዓታቸውንም እንዳየሁት፡ እንደዚሁ ጥይት በስቶታል” ጠላት ድል ተደርጎ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የብፁዕነታቸውን አኩሪ ታሪክ ትውልድ ሲዘክርላቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓም በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት ሐውልት ቆሞላቸዋል::
አቡነ ጴጥሮስ በአደባባይ በፋሺሽት ኢጣልያ የተረሸኑት ሐምሌ 22: 1928 ዓም ነበር።
መታሰቢያ ሃውልታቸው አራዳ ይገኛል::