Archive | August 3, 2017

ዘርፎ አደሮች Vs ሠርቶ አደሮች !

በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ እጅግ ብዙ ዘርፎ አደሮችና ጥቂት ሠርቶ አደሮች ነበሩ። ዘርፎ አደሮች በማንኛውም መንገድ የሀገሪቱን ሀብት በመዝረፍና ወደ ሌላ ሀገር በማሸሽ ሀብትን ሲያካብቱ ጥቂቶቹ ሠርቶ አደሮች ደግሞ እንደምንም እየተፍጨረጨሩና የሚያገኟትን አማራጭ ሁሉ በትጋት በመጠቀም በሐቅ ሀብት ያፈሩና ያፈሩትንም ሀብት መልሰው ለሕዝብ ጥቅም ያውሉ ነበር። የዚያች ሀገር ሕዝብም እየዘረፉ ከሚከብሩት ይልቅ በታማኝነት ለሚሠሩ ሠርቶ አደሮች ልዩ ፍቅር ይሰጥና ያከብራቸው ነበር። ይህንን ያስተዋሉ ዘርፎ አደሮችም እንዲህ ሲሉ መከሩ።
<<ጎበዝ… እነዚህን ሠርቶ አደሮች ከዚህች ሀገር ካላጠፋናቸው የእኛ ህልውና አደጋ ውስጥ ነው። ምክንያቱም… ሲጀምር በነፃነት የምንዘርፈውን ሀብት እየሠሩ እየቀነሱብን ነው። በጥቅማችን መጥተዋል። ሲቀጥል እነዚህን በመሥራት ብቻ የሚያምኑ ሰዎችን እስካላጠፋን ድረስ ሕዝቡ ሥራ ወዳድ ነውና ከእነርሱ ጎን መሰለፉ አይቀርም። እነዚህ ሠርቶ አደሮች ምንም በቁጥር ጥቂት ቢሆኑም እንኳን የሚያገኙትን ሀብት በሙሉ መልሰው ለሕዝቡ ጥቅም እያዋሉ ስለሆነ በሂደት በሀብት እንደሚነግሱብንና የምንዘርፈውን እንደሚያሳጡን ግልጽ ነው። በተለይ ሕዝቡን ከያዙብን ቀስ በቀስ እኛን ከዘረፋ ውጭ ያደርጉናል። ይህ ደግሞ የሕልውናችን ፍፃሜ ይሆናል። ስለዚህ አሁኑኑ እናጥፋቸው። እነርሱን ለማጥፋትም የሀሰት ወሬ እናስወራ። የሀሰት መረጃ እንፈጠር። ይህንን ለሚሠሩልን አካላትም ዋስትና እንስጥ። በሠርቶ አደሮች ሀገር ዘርፎ መኖር የማይታሰብ መሆኑ ግልጽ ነውና ተነሱ… ዘመቻ ሠርቶ አደሮችን ማጥፋት!>> ብለው ተነሱ። መክረውም አልቀሩ ወደ ተግባር ገቡ።
ዘርፎ አደሮቹ ይህንን ምክር መተግበር በጀመሩ ማግስት ግን ከሕዝቡ ያልጠበቁትንና ያልገመቱትን ምላሽ ማግኘት ጀመሩ። በእነርሱ ቤት ዘርፎ አደርነታቸው በሕዝቡ አይታወቅም። ዳሩ ግን ሕዝቡ እያንዳንዷን ሥራቸውን ጠንቅቆ ያውቅ ነበርና በዘመቻቸው ማሾፍና ማሽሟጠጥ ጀመረ። “ምነዋ ዘርፎ አደሮቹ ሰሞኑን ከንቱ ይደክማሉሳ… ‘ለማያውቅሽ ታጠኝ’ አሉ… እነዚህን ጥቂት ጨዋ ልጆቻችንን ስም ማጥፋት መጀመራቸው መፍራታቸውን ያሳያል… አሂሂሂ… ‘ድሮ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ’ አሉ። እኛ ማን እንደሚጠቅመን፣ ማን ሌባ እንደሆነ፣ በጨዋ ሰው ላይም ማን ስም በማጥፋት እንደሚዘምት እናውቃለን። ሌቦቹ ግን ምናለ የዘረፉትን በሰላም ቢበሉና እነዚህን ታማኝ ልጆቻችንን እንኳን ቢተውልን?” እያሉ የቡና መጠጫ ከማድረግም አልፎ በየአጋጣሚው በግልጽ ይነግሯቸው ጀመር። ይሁንና አሁንም ዘርፎ አደሮች ስልት እየቀያየሩ ሠርቶ አደሮችን ማሳደዱን ቀጠሉ።
በዚህ ነውረኛ ሥራቸው የተማረረው ሕዝብም ሰላማዊ ሰክፍ ወጣ። በብዙ መፎክሮች የታጀበው ሰልፍ እንዳበቃም የሰልፉ መሪ ይህንን መልእክት አስተላለፈ።
<<ዘርፎ አደሮች ሆይ! እናንተ የሠርቶ አደሮችን ስኬት ማየት እንደማትፈልጉ እናውቃለን። ለምን ቢባል ሠርቶ አደሮቹ እናንተ ዘርፋችሁ ልትወስዱት ያቀዳችሁትን ሠርተው ስለሚወስዱባችሁ ነው። እናም እናንተ ዘርፎ አደሮች ሠርቶ አደሮችን ከመጥላትም አልፎ በግልጽ ማሳደድ መጀመራችሁ… ምንም የሚገርም ነገር የለውም። ሠርቶ አደሮች እያሉ እናንተ ሁሉንም ለመዝረፍ ስለምትቸገሩ እነርሱን ለማጥፋት እየሞከራችሁ እንደሆነም እያየን ነው። ግን ግን… ሲያምራችሁ ይቅር። እኛ ከሠርቶ አደሮች ጎን ነን። እናንተ እነርሱን ለማጥፋት ስትነሱ በእኛም ሕልውና ላይ እየመጣችሁብን ነውና ስታጠፉን ዝም የምንል ይመስላችኋልን? ስትዘርፉ ዝም አልን… አሁን ግን እናንተ ከምትዘርፉት የምትተርፈውን ጥቂት ሀብት በትጉህነታቸው እያባዙ ለእኛና ለልጆቻችን ኑሮ እያዋሉ ያሉትን ታማኝ ልጆቻችንን ልታጠፉ ስትነሱ ዝም አንልም። ተነቃቅተናል! ከሀገራችን መወገድ ካለበት ዘርፎ አደር እንጅ ሠርቶ አደር አይደለምና… ጉድጓዳችሁን አትቆፍሩ።>>

ይህን የሕዝብ ድምጽ የሰሙ ዘርፎ አደሮችም… የዘረፉትን ይዘው……… ወዴት እንደገቡ አልታወቀም።

.
ዘርፎ አደሮች ሁሌም ሠርቶ አደሮችን ያሳድዳሉ። ብዙዎቹ ሠርቶ አደሮችን በዘርፎ አደሮች ዘመቻ ይጠፋሉ። በመጨረሻ ግን ሁሉን የሚያውቀው ሕዝብ ይነሳል። ሕዝብ ደግሞ ማንን ማጥፋት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል!!!