Archive | October 2017

“አንዱ ቀበሮ ሌላው ተኩላ ሁለቱም ይበሉኛል …”

የሕዝብ ፍላጎት ሁልጊዜም ሠላም ፣ ዲሞክራሲ ፣ ልማት እና ዕድገት የሕግ የበላይነት ናቸው። በተለያየ ምክንያት ሠላም ቢታወክ ሲሠሩ ውሎ በሠላም መግባት ቤተሰብን እና ንብረትን መጠበቅ አስቸጋሪ ይሆናል ። ከከፋም ሕይወት ይጠፋል ንብረት ይወድማል መኖርም አስቸጋሪ ይሆናል ። ሕዝብ ከችግር ሙሉ በሙሉ ርቆ ባይኖርም መስዋዕትነት እየከፈለም ቢሆን ችግሩን እየፈታ እና እያስወገደ ከዚህ ደረጃ ደርሷል ፤ የደረሰበት ደረጃ ግን እጅግ ውስብስብ እና ፖለቲካዊ ባህሪ ያለው በመሆኑ ለመፍታትም አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ካለፈበት ባህላዊ መንገድ የዘለለ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሻ ሆኗል።
ለዘመናት የተከማቸውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር እንፈታለን በማለት በተለያየ ጊዜ እና ለተለያየ ዓላማ የፖለቲካ ድርጅቶች ተፈጥረዋል ፤ ሻዕብያ እና ጀብሀ ክልልን ፣ ኦነግ ፣ ሕወሐት እና ኦብነግ ብሔርን ፣ ኢህአፓ እና መኤሶን አገርን (ሕብረ ብሔር ) መሠረት አድርገው ተደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል ። ከእነዚህ መካከል ሻዕቢያ እና ሕወሐት ለመንግሥት ሥልጣን በቅተዋል ፣ ያመጡትም ወጤት በግልጽ ይታወቃል ።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ለመፍጠርም ሆነ ለመፍታት የፖለቲካ ልሂቃን ከፍተኛ ሚና አላቸው ፣ ጠንካራ እና የዳበረ የፖለቲካ ባህል በሌለበት እና የህግ የበላይነት በማይከበርበት አገር የምኞት ፖለቲከኞች እድል አግኝተው የፖለቲካ መድረኩን ስለሚቆጣጠሩት ሕዝብ የሀገሩ እና የሥልጣን ባለቤትነቱ ተረጋግጦለት መምረጥ ፖለቲከኞችም በነፃነት ተወዳድረው መመረጥ አይችሉም ። የምኞት ፖለቲከኞች ፍላጎታቸው እስኪሟላ ሁኔታውን ያተራምሱታል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ድብቅ ፍላጎታቸውን በጉያቸው ይዘው በሕዝብ ሥም ነው ።
ወያኔ የኢትዮጵያ የዘመናት የፖለቲካ ችግር አከተመ ብሎ ግንቦት 20 / 1983 አውጆ ነበር ፣ ሥልጣን እንደጨበጠ የጉያውን ወደ አደባባይ አውጥቶ እስከቻልኩ ኢትዮጵያን እገዛለሁ ፣ ሲያቅተኝ ኢትዮጵያን አፈራርሼ ፣ ሐብት ንብረቷን ወደ ትግራይ አጓጉዤ የትግራይ ሪፐብሊክን እመሠርታለሁ የሚለውን አጀንዳ ወደ ተግባር መመንዘር ተያያዘ ። ሕዝብን ከሕዝብ ፣ ዕምነትን ከዕምነት በማጋጨት ፣ ሕዝብን በማሰር ፣ በማሰቃየት እና በመግደል በመጀመሪያ አማራን ፣ ቀጥሎ ኦሮሞን ከዚያም ሌሎችን ብሔረሰቦች እንደ ሥጋት ቅደም ተከተላቸው መምታት እና ማንበርከክ የሚለውን ዕቅዱን አጧጧፈው ። ማጋጨቱ ፣
ማሠሩ ፣ ማሰቃየቱ ፣ መግደሉ ቢሳካለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ግን መከፋፈል አንድነቱንም መናድ አልቻለም ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ደማችን አንድ ፣ አገራችን የጋራ ብሎ ፀረወያኔ ትግሉን አፋፍሞ ወያኔን ውጥረት እና ጭንቀት ውስጥ አስገብቷል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁርጠኛ ፀረወያኔ ትግል በሚያካሂድበት ወቅት ተረኛ ሥልጣን ጠባቂ የምኞት ፖለቲከኞች ፀረሕዝብ እና ፀርሀገር በመሆን የወያኔ ተባባሪ ሀገር አፍራሽ ግብረ ሐይል በመሆን ትግሉን እያዳከመ ለወያኔ እስትንፋስ ይሰጣል ::ወያኔ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ወያኔነትን እያውለበለበ ነው ። ወያኔነት ዘረኝነት ፣ ስግብግብነት ፣ ራስ ወዳድነት ፣ ተበቃይነት ፣ ቅጥረኛነት ፣ ፀረኢትዮጵያ እና ፀረኢትዮጵያዊነት ነው ። ተረኛ ሥልጣን ጠባቂ ፖለቲከኞች ሀገር ሕዝብ እየደማ ለላም አለኝ በሰማይ ሥልጣናቸው ወያኔነትን ይረዳሉ ፣ ያግዛሉ ፣ እንዲያውም ወያኔነትን እየተለማመዱ ነው ፤ የዘውግ እና የባዶ አንድነት ተዋንያን ተጠቃሽ ናቸው ።
የዘውግ ፖለቲከኞች ከኦሮሞ ብሔረሰብ በላይ ለብሔረሰቡ እኛ እንጨነቃለን እናስባለን በማለት ኦሮሞነትን ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን መቀስቀሻ እና ማደራጃ አድርገውታል ። ታሪክን ቆርጦ በመቀጠል ኦሮሞ ተበደለ ፣ ቋንቋው ፣ ባሕሉ እና ማንነቱ ጠፋ ፣ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ነህ ተብሎ የሌላ ማንነትን እንዲኖር ተገደደ ፣ ፈጣሪ የሰጠውን መሬት ፣ ሐብት እና
ንብረት ተነፍጎ የሌሎች መጠቀሚያ ሆነ ፣ የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብቱ ተነጥቆ በባርነት ይኖራል በማለት በደሙ እና አጥንቱ ከሰራው ቤቱ እና ሀገሩ ኢትዮጵያ ሊያስወጡት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለውን ትልቅ የታሪክ አሻራ ሊፍቁበት ፣ ኢትዮጵያዊ ማገርነቱን እና ምሰሶነቱን ሊያፈርሱበት በአጠቃላይ ኦሮሞን ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት እንዲሁም
ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሊነጥሉት ይሯሯጣሉ ።
ጃዋር የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን መጠናከር አስፈላጊነት ሲገልጽ ፣ በእኛ አካባቢ ሙስሊሞች ጠንካራ ስለሆኑ ቀና ብሎ የሚያያቸው የለም ፣ ካለም በሜንጫ አንገቱን እንለዋለን ካለ በኋላ በእስልምና እና በኦሮሞ መካከል ያለውን አንድነት ማብራራት ቀጠለ ። እንደጃዋር እምነት እስልምና ሲነካ ኦሮሞ ይነካል ፣ ኦሮሞ ሲነካም እስልምና ስለሚነካ የኦሮሞ ነፃ መውጣት የእስልምና ነፃ መውጣት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የኦሮሞን የነፃነት ትግል መደገፍ
ይገባቸዋል ባይ ነው ።፡ይህ ካልሆነ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ቀና ብለው እንደማይሄዱ እና መስጊድ መስራት እንደማይችሉ የጎንደር እና የትግራይ ሙስሊሞችን በምሳሌነት በማንሳት አስረድቷል ። ጃዋር ስለእስልምና እና ስለ ኦሮሞነት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታነት ሲያወራ እስላም ስላልሆኑ ኦሮሞዎች መኖር አለመኖር ትንፍሽ አላለም ። ጃዋር መቼም አያልቅበት ዲባባ ሁሉ ኦሮሞ አይደለም በማለት ኦሮሞ የሆኑ ኦሮሞዎች እና ኦሮሞ ያልሆኑ ኦሮሞዎች ብሎ እንደፈረጀ ሁሉ እስላም ያልሆነም ኦሮሞ አይደለም ይለን ይሆናል ።
ኦሮሞነትን በተለያዩ ፍላጎቶች እየመነዘሩ ኦሮሞነትን መሥጠት እና መንሳት ወይም ኦሮሞዎች ሁሉ እኩል አይደሉም ብሎ ማበላለጥ ጆርጅ ኦርዌል (George Orwell ) ሁሉም እንሦች እኩል ናቸው ፤ አንዳንዶቹ ግን ከሌሎቹ የበለጡ እኩል ናቸው (“All animals are equal, but some animals are more equal than others) ያለው የማረከው ይመስላል ፡ ለነገሩ ድብቅ አላማ ያለው የማይለው ነገር የለም።
የኦሮሞ ብሔርተኝነት ሥሜት የወዘወዛቸው ዘውገኞች ዛሬ የሚቀብሩት የልዩነት ፈንጂ በወቅቱ ካልተወገደ ነገ አካባቢያዊነት ፣ ኢትዮጵያዊነት እና ጎረቤትነት ተደምረውበት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለው ሰባዊ ቀውስ ከሚገመተው እና ከሚታሰበው በላይ እጅግ የከፋ ሊሆን ይችላል ። የሠራሁትን ቤቴን እና ሀገሬን ኢትዮጵያ አላፈርስም ላለ ኦሮሞ ይሄ ሁሉ
አይገባውም ፣ የሚገባው ሰላም ፣ ልማት ፣ አንድነት ፣ እኩልነት እና ነፃነት ነው ።
እነ ጃዋር ኦሮሞ እና እስልምና አንድ ናቸው ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ነፃ የሚወጡት ኦሮሞ ነፃ ሲወጣ ስለሆነ የኦሮሞን የነፃነት ትግል ይርዱ የሚሉት አባባል በኦሮሞ ማዕከልነት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ያሰባሰበ መንግሥት የመመሥረት ፍላጎት መልዕክት ነው የሚሉ በርካታ ናቸው ። ግምቱ ትክክል ከሆነ የኦርቶዶክስ ፣ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት
መንግሥት ምሥረታ ጥያቄ ቢመጣ አንደምታው ምን ሊሆን ነው ። የቋንቋ ፌዴሬሽን ወደ ድንበር እና መሬት ይገባኛል ግጭት እንዳስገባው የሐይማኖት ፌዴሬሽንም ወደ ሐይማኖት ጦርነት ያመራል ማለት ይቻላል ።
የዘውግ ፖለቲከኞች የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ማማ ላይ አውጥተው በአንድነት እና በእኩልነት አብረን መኖር እንችላለን ማለት ፣ ሐይማኖት የግል ሀገር የጋራ የሚለውን ትልቅ ኢትዮጵያዊ እሴት ዘሎ የየብሔረሰቡን ሙስሊሞች ፍለጋ መሄድ ፣ በተምታታ ፍላጎት እና ማንነት እየዳከሩ በአላማቢስ እና ግብየለሽ አቋም መናወዝ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ትግሉን
ይጎዳል ፣ ወያኔን ግን ይጠቅማል ።

እንደ ዘውገኞች ሌላው የፖለቲካ እንቅፋት የባዶ አንድነት ኃይል ነው ፤ አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ማለቱ መልካም ነው ነገር ግን በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔረሰቦች ባሉበት ሐገር የሚያስፈልጉ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ መሠረቶችን ጠንቅቆ መረዳቱ አስፈላጊ ነው። በአንድ ሀገር የግል ፣ የጋር እና የወል መብቶችን ለማስከበር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመቻች ይገባል። ይህ በሌለበት አንድ ሀገርም ሆነ አንድ ህዝብ የማይታሰብ ነው ።
የአንድ ሀገር የአንድ ሕዝብ አቀንቃኞች የቋንቋ ፣ የባህል እና ራስን በራስ የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲነሱ ክልብሽ የሚላቸው የሚዘምሩለትን ያልተረዱ ወይም መንገዱ የጠፋባቸው ናቸው ። ባዶ አንድነት ለማንም ለምንም አይበጅም ፤ አንድነት ያለእኩልነት እና ነፃነት ባዶ ጋጋታ ወይም ጩሸት ነው ። አንድነት እኩልነት እና ነፃነት ሲኖር መብቶች ያለችግር ይሟላሉ ፣ ይከበራሉ ። አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ፈላጊዎች የሁሉንም መብት በእኩልነት ተቀብላችሁ እና አክብራችሁ አብሮ ለመኖር ዝግጁነታችሁን ገልጻችሁ ከብሔረተኞች ጋር አብሮ ለመኖር ያላችሁን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ገልጻችሁ ዘውገኞችን
ለውይይት በመጥራት የአንድነት ፣ የእኩልነት እና የነፃነት ጠበቃ እና የሕዝብ ወገን መሆናችሁን አረጋግጡ ።
የዘውግ እና የባዶ አንድነት ፖለቲካ ለፍትሓዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታ እና ግንባታ በሽታ ነው ፣ በተለይም ለድህረ ወያኔ ኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ነው ። በሽታ ውጫዊ ከሆነ በክተባት ፣ በሥራዓተ ምግብ እና የአካል እንቅስቃሴ ፣ በግል እና በአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ መከላከል እንደሚቻል ፣ ይህን አልፎ በሽታው ወደ ውስጥ ቢገባ በሕክምና እንደሚፈታ ፣ በሽታው ከውስጥ በቅሎ እና አድጎ ካጠቃ ካንሰር በመሆኑ የታወከውን ክፍል
ቆርጦ መጣል እንዳለበት ያም ሆኖ መዘዙ እና መርዙ ሙሉ በሙሉ ስለማይፀዳ ቀጣይ ሕክምና እንደሚይሥፈለግ ከባለሙያዎች ይሰማል ። ከዚህ መረዳት የተቻለው ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመውረር የመጣውን የውጭ ጠላት ሁሉ በአንድነት ተሰባስበው ወራሪውን ለምን ማባረር እንዳልቸገራቸው ፣ በአንፃሩ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ በቅሎ እና አድጎ መልሶ
የወረራቸውን የውስጥ በሽታ በአንድነት ተባብረው ከአካላቸው ቆርጠው ለመጣል ለምን አስቸጋሪ እና ውስብስብ እንደሆነባቸው ነው::
በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ወያኔ ከኢትዮጵያ አካል ውስጥ በቅሎ መልሶ ኢትዮጵያን የወረረ ካንሰር ስለሆነ ኢትዮጵያን ከማፈራረሱ በፊት ተቆርጦ ሊጣል ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ያሳስቡ ነበር ፣ ሰሚ ጠፍቶ ያሉት እየደረሰ ነው ። ወያኔ በመላው ኢትዮጵያ ካንሰሩን አሰራጭቶ ከየብሔረሰቡ የፈጠራቸው የተወሰኑ የፖለቲካ ካንሰር ድዊያን በማወቅም ሆነ ባለማውቅ የወያኔን አገዛዝ ዕድሜ እና የኢትዮጵያውያንን የሰቆቃ ግዜ እያራዘሙ ነው ፣ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ እየጫረ ፣ እየአቀጣጠለና እያፋፋመ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት የሚፈሰው ደም የፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማን ሥጋት ትክክለኛነት ግልጽ አድርጎ ያሳያል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት እጦት ከገባበት የከፋ የፖለቲካ አረንቋ መውጣት አቅቶት ይላቁጣል ። ሁኔታው የቀጠለው ችግሩ ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም ። ችግሩ ወላጅ አስተምሮ ለሀላፊነት ያደረሳቸው የፖለቲካ ልሂቃን ልጆቹ ከዛሬ ነገ ይፈቱታል ተብሎ ሲጠበቅ ከህዝብ የራቁ እና ፍላጎታቸው ከሀገር በላይ የሆነባቸው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ በየግዜው ከሚፈጥሩት ውስብስብ የፖልቲካ ችግር የተነሳ ነው ።እነዚህ የዘውግ እና የባዶ አንድነት ፖለቲከኞች ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ እየፈጀ ሲያስፈጅ፣ ሀገር በላያችን ላይ ሲያፈርስ ፣ ህዝብን በገዛ ሀገሩ ተፈናቃይ ሲያደርግ ፣ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ የሚልሰው የሚቀምሰው አጥቶ በረሀብ ሲጠበስ እያዩ እና እየሰሙ ከብሔርተኘነት እና ባዶ አንድነት ጩቨት ሊወጡ አልቻሉም ። እዬዬም ሲዳላ ነው እና የማይገኝ የምኞት ስልጣን አንጋጦ ከመጠበቅ ሀገር ማዳን ይቅደም ፣ ቀሪው ጉዳይ በወቅቱ ይታያል ።
የኢትዮጵያ ህዝብ አገራዊ የነፃነት ቻርተሩን በደሙ ስለፃፈ፣ በአንድነት በእኩልነት እና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት አብሮ በጋራ ለመኖር ስለወሰነ የዘውግ የነፃነት ቻርተር አርቃቂ የባዶ አንድነት ዘማሪ ፖለቲከኞችን አይፈልግም። የሕዝብ ወገን ነኝ የሚል ፣ በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ እና ሰቆቃ ይቁም ፣ ሀገር አይፍረስ ፣ ማንነት አይጥፋ እስራት ፣ ግርፋት ፣ ግድያ ዘረኝነት ይብቃ የሚል የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ፣ ውሳኔ እና ምርጫ የሆነውን ሰላም ፣ ልማት እና ብልጽግና ፣ እኩልነት እና ነፃነት ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት መረባረቢያው ግዜ
ዛሬ ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1964 ማልኮም ኤክስ (Malcolm X) በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ንግግር ሲያደርግ በወቅቱ ለአሜሪካ ፕሬዘዳንትነት ሲወዳደሩ ከነበሩት ከቤሪ ጎልድዋተር (Barry Goldwater) እና ከሊንደን ጆንሰን (Lyndon Johnson) ማንን ትመርጣለህ ተብሎ ሲጠየቅ “አንዱ ተኩላ ሌላው ቀበሮ ስለሆኑ ሁለቱም ስለሚበሉኝ ማንኛቸውንም አልመርጥም” እንዳለው ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየፈጀ የሚያስፈጀውን ወያኔን
የሚፋለመው በዘውግ ከፋፋይ እና በባዶ አንድነት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች ለመተካት ሳይሆን በወያኔ መቃብር ላይ የሁሉም የጋራ ቤት በምትሆን ኢትዮጵያ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሐውልት ለማቆም ነው።

ለራስህ ስትል ብታርፍ ይሻልሃል !!!

ይህ እውነት የተፃፈው ላንተ ነው ።
ግጭትን ለማብረድ ከመሞከር ይልቅ በተነሳው እሳት ላይ ቤንዚን እየጨመርክ ላለኸው ላንተ ።

እንዲመጣ እየወተወትክ ያለኸው ክፉ ቀን ቢመጣ እንዲህ እንዳሁኑ ፌስቡክ ላይ ተጥዶ መዘብዘብ አይታሰብም ።

ያኔ ያንተ ምኞት ዛሬን በህይወት መክረም ብቻ ይሆናል ።
ያኔ አደለም እንደልብህ ወጥተህ መግባት ይቅርና ሱቅ ደርሶ መመለስ ቅንጦት ሊሆንብህ ይችላል ምክንያቱም እንዲነድ ያቀጣጠልከው እሳት ወላፈን. .. ከቤትህ ወጣ እንዳልክ ሊበላህ ይችላል እሳት ማንንም ስለማይመርጥ ።

ለነገሩ እያቀጣጠልክ ያለኸው እሳት ……. እቤትህም ሆነህ ከሰል አድርጎ ሊያስቀርህ ይችላል ።

ያኔ ሃገሪቱ በትናንሽ ባለጠመንጃ መንግስታት የምትመራ ስለምትሆን እንደልብ የምትተቸው መንግስት አይኖርህም ይህ ነገር አሁን አይገባህም ።፡
ምናልባት ይገባሃል ብዬ የማስበው ፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት በመድሃኒትና በምግብ እጦት ሲያልቁ ያዩ እናቶች ….. ልጆቻቸውን ለማትረፍ ወደ ስደት በሚያደርጉት ጉዞ የአውሬና የሽፍታ ሲሳይ ሆነው ሲቀሩ ፡ ያኔ ይገባሃል ብዬ አስባለሁ ።

አስፓልቶች በታንክ ታርሰው ….. ከተማይቱ በህንፃ ፍርስራሽ ተሞልታ በዘሩ ምክንያት በየቀኑ በየጎዳናው የሞተው ቀባሪ ያጣ አስከሬን ሽታው አገሩን ሲሞላው ያኔ ይገባህ ይሆናል ።

እመነኝ …… ዛሬ ላይ ለተፋሃት እያንዳንዷ ብጥብጥ ቀስቃሽ መልእክትህ መፈጠርህን እስክትረግም ዋጋ ትከፍልባታለህ ። አይንህ እያየ ሚስትህ በሌላ ጎሳ ጎረምሶች ስትደፈር ፡ ያኔ ይገባህ ይሆናል ።

ያ እንዲመጣ የምትፈልገው ቀን ሲመጣ. .. ክልልህ አያድንም ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የላካቸው ሰላም አስከባሪ ወታደሮችም ከመጣብህ መአት አያድኑህም ።

ምናለፋህ ዛሬ እንደዋዛ እያቀጣጠልክ ያለኸው እሳት ለጎረቤት ሃገራትም ይተርፋልና ክልሌ መሸሸጊያዬ ብለህ እንዳታስብ ።
ዛሬ በሃገር ሰላም በድንገት በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችን ላጋጋልክበት አንድ ቀን በቁጭት እና ፀፀት የደም እንባ እያነባህ . በህይወትህ ዋጋ ትከፍልበታለህ ።

አሁን እንጂ የዛኔ ምርጫ የለህም ፡ ስለዚህ ያች እንድትመጣ እየጠራሃት ያለኸው ቀን ሳትመጣ ፡ በዚች በመልካሟ በዛሬዋ ቀን ላይ ሳለህ ምርጫ አለህና አስብበት ።

ለራስህ ስትል ብታርፍ ይሻልሃል !!!

የሰሞኑ የኦሮሚያ ተከታታይ ሰልፎች መሪ ቃል “Down Down Weyane”

 Alemayehu Kidanewold

down do

ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ፖለቲካዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነበር። የመንግስት ሀላፊዎች ድርጅቱን ጥለው መኮብለል በአንድ በኩል፤ እንዲሁም  የኦሮሚያ ወጣቶች « Down Down Weyane » በሚል  መሪ ቃል የሚመሩ ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፎች በሌላ በኩል የህወሐትን ጎራ ድንጋጤ ውስጥ የከተቱ ይመስላል፤ በተለይ የፌስቡክ ጭፍን ደጋፊያቸውን። በእነዚህ  ጭፍን ደጋፊዎች የሚቀነቀኑ ጀግንነት ከኛ ውጪ ላሳር  እና የተሰጠህን አመስግን አይነት ስብከቶች  ረገብ ብለዋል።  እነዚህ የህወሐት የፌስቡክ አርበኞች አለቆቻቸው ነገሩ ሁሉ እየከዳቸው እንደሆነ የተረዱ ይመስላል። ይህ ያለንበት ወቅት ለአነዚህ የህወሐት ወጣቶችና ምሁር ተብዬ የፌስቡክ አርበኞች  ሁለት ምርጫዎችን አቅርቦአል። የመጀመሪያው ህወሐት በትግራይ ህዝብ  ስም የሚያካሂደውን ዘረፋና ጭቆና ያቁም የሚል አላማ ይዞ ከሰፊው ህዝብ ጋር መሰለፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቢያንስ በዝምታ መደበኛ ኑሮአቸውን መኖር ይሆናል፤ እንደሰሞኑ።  ምክንያቱም በቲፎዞነት፣ በመሳሳብና በአካባቢነት የህዝብ ሀብት የሚዘረፍበት ወቅት ቢያንስ በኦሮሚያ ክልል ላይመለስ ያከተመ በመሆኑ ። ህዝቡ ለዚህ መሰል ሰልፍ የሚወጣው ስራ አጥቶ ወይም  ከዚህ ቀደም ሲባል እንደነበረው  በሌላ ሀይል ተገፋፍቶ እይደለም። የበይ ተመልካችነቱ አንገፍግፎት እንጂ ።

እንደ እኔ ምልከታ የህዝቡን ጸረ ህወሐት ትግል ሲጎትት የነበረው ኦህዴድም ቢያንስ  በበታች መዋቅሩ  የህዝቡን ጸረ ወያኔ ትግል በዝምታ የሚደግፍበት ደረጃ  ላይ ደርሶአል። በከፍተኛ አመራሩ ውስጥም መጠነኛ ለውጦችን አይተናል፤ ግራ አጋቢና ምንጫቸው ምን እንደሆነ ባይረጋገጥም።  ምናልባት ኦህዴድ  እንደ ድርጅት ላለፉት 26 ዓመታት የህወሐት ተላለኪ በመሆን የኦሮሞንም ሆነ ሌሎች ህዝቦችን የበደለበትን ስራውን በግልጽ ተናዞ ወደ ትክክለኛ  መስመር የሚገባ ከሆነ እጅግ ብዙ የቤት ስራዎች ይጠብቁታል። ሌሎች ለኦሮሞ ህዝብ ክብር እንቆማለን የሚሉ ስብስቦችም ቢሆኑ የተግባሩ ወቅት እየመጣ ስለሆነ ፖሊሲዎቻቸውን መፈተሽና መመርመር ይገባቸዋል።

እንደ እኔ እምነት ከዚህ በፊት በአንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና ድርጅቶች ሲሰበኩ የምንሰማቸው የመገንጠል ስብከቶች  የኦሮሞን ህዝብ አሳንሶ ከማየት የመነጩ ናቸው።  ኦሮሞ ትልቅ ህዝብ እንደመሆኑ  መስዋዓት የከፈለበትን ሀገር የሚበትንበት ምክንያት አይኖርም። የሚገባውን ሚና እየተጫወተ አዲሲቱን  ኢትዮጵያ ያስተባብራል እንጂ። ሀገሪቷን በትኖ ማብቃ የሌለው የድንበርና የዘር ፍጅት በአካባቢው እንዲፈጠር የማድረግ አላማ ዞሮ ዞሮ የህወሐትን አላማ አንደ ማስፈጸም ይቆጠራል። ስለዚህ ህወሐት በእጁ የቀረው የመጨረሻ የመጫወቻ ካርታ   ( አተራምሶ መሄድ )  እኛ በመጫወት እንዳናግዘው  ደግመን ደጋግመን ማሰብ ያስፈልጋል።

ህዝብ የሚጠየፋቸው ገዢዎች እና ክፉ በሽታቸው

Alemayehu Kidanewold

በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ እንደወያኔ በህዝብ የሚጠላ ገዢ አላየሁም፤ አልሰማሁም እንዲሁም አላነበብኩም፡፡ በዚህ ወቅት ኢህአዴግን ሀገሪቱን የሚያስተዳድር መንግስት ብሎ እና ሹማምንቱን ደግሞ ህዝቡን የሚመሩ መሪዎቹን ብሎ መጥራት አይደለም መስማት ህሊናን የኮሰኩሳል፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቷ እና በህዘቧቿ ላይ ያደረጉት እና የሚያደርጉትን ስትመለከት፡፡ ከተራ ወንበዴነት እስከ ሀገርን እና ህዝብን ለዘርፍ የመጣ የውጪ ጠላት የሚፈፅመውን ፈፅመዋል፡፡

እነሱንም እንመራዋለን የሚሉት ህዘብም በተግባራቸው ይጠየፋቸዋል፡፡ ከቀንን ወደ ቀንም የፓርቲው እና የሹሞቹ ስም ሲነሳ እንደ ዛር የሚያንዘ ዜጋ ከትላንቱ ይለቅ ዛሬ ላይ ቁጥሩ የትዬለሌ አሻቅቧል፡፡ ይህ በርሃብ፣ በስራ አጥነት፣ በነፃነት እጦት፣ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት የሚሰቃይው ዜጋ ይህ ከፉ ስርአት ባመጣበት ሌላ የዘር በሽታ ዛሬ ላይ በእርስ በርስ ግጭት መታመስ ከጀመረ ውሎ አድሮአል፡፡

የኢትዮጲያ ህዝብ የሚጠየፈው አምባገነን ስርአት የዘራው ክፉ የዘር ስርአት (በሽታ) ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ የሀገሪቱ ግንባር ቀደም ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም ክፉ ስርአት በህዝብ ጫንቃ ላይ የሚቆይ ከሆነ የሀገሪቱን ህልውና እና ዘላቂ ሰላም ላይ ምን ሊያሰከትል እንደሚችል ለመገመት ጠቢብ መሆን አያስፈልግም፡፡  ወያኔ የሚከተለውን የዘር ፖለቲካ ክፉ በሽታ እያለኩ  በፅሁፉ ውሰጥ የምጠቀመው ለሀገራችን አንድነት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በአለፉት 26 አመታት አይተነዋል፡፡ በተጨማሪም አንድ ዜጋ በዘሩ ከሚያገኘው ነፃነት ይልቅ በዜግነቱ የሚያገኘው ነፃነት ሚዛን ስለሚደፋ እና የሚያኮራ በመሆኑ ነው፤ የዘር ፖለቲካቸውን ክፉ በሽታ ያልኩት፡፡

ወያኔ ስልጣል ላይ በቆየበት ሩብ ምተአመት ውስጥ ሀገራችን ላይ ከዚህ ቀደም ተከስተው የማያውቁ ነገሮች ዛሬ ላይ በስፋት ተከስተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዘር ያማከሉ ጦርነቶች እና ስደቶች ወይንም ከቦታ መፈናቀሎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ቀንን ወደ ቀን እየተባባሱ  የመጡ የክፉው በሽታ ውጤቶች ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በአጭሩ እንቃኘው፡፡

በቅርቡ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ከ50 ሺ በላይ ኦሮሞዎችን ሲያፈናቅል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ቀጥፏል። በዚህ ግጭት ታጣቂ የወያኔ ሀይሎች (የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል) ተሳትፈውበታል፡፡ ደብረ ዘይት ላይ የእሬቻ በአል ሊያከብር በወጣው ሰላማዊ ህዝብ ላይ ጥይት ያርከፈከፈው የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ወይንም የፈደራል ወታደር ከሞት ተርፎ ወደ ጅጅጋ እና አጎራባች ከተሞች የሚሰደደው ዜጋን መኪና እያስቆመ ሲገደል፣ ሲገረፍ እና አካሉ ሲጎድል የት ነበር ያስብላል፡፡ እየፈሰሰ ያለው የወገኖቻችን ደም እና የስቃይ ጩኸት የሚሰማ መጥፋቱ እጅግ የሚያሰቆጭ ቢሆንም  ግጭቱን እሰከ ዛሬ ድረስ እንዳይበርድ ለምን እንደተገለገ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

ሌላኛው የክፉ በሽታው ምሳል የሚሆኑት በቤንሻንጉል ክልል ጉራፍ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ገበሬዎች ላይ የዛሬ አምስት አመት አካባቢ የተከሰው ሞትና መፈናቀል፣ በጋንቤላ ክልል በንዌሮች እና በአኝዋክ ጎሳች መካከል የተካሄደው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ናቸው፡፡

የነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸውን ሶስት አሳዛኝ ክስተቶች ለማስረጃነት አነሳሁ እንጂ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ መሽቶ እስኪነጋ መዘርዘር ይቻላል፡፡

መታወቅ ያለበት ዋናው ጉዳይ የግጭቶች መንስኤ በህዝብ ጫናቃ ላይ የሰፈረው ክፉ ስርአት መሆኑ ነው፡፡ ስርአቱ ለመሆኑ ደግሞ እኛ ተጎጂዎቹ / የምንኖረው/ አይደለንም አልፎ ሂያጅ የተቀረው የአለም ሰው ያገነዘበዋል፡፡ እኛን የስርአቱ ገፈት ቀማሾች የሆነውን ዜጎች እያሳሰበ የመጣው ይህ ዘርንና ክልልን ያማከለ ግጭት አለም ላይ ያሉ ጥልልቅ ሚዲያዎችን ትኩረት አግኝቷል፡፡ አልጄዚራም ምን እንደሸተተው ባይታወቅም በአለም ለጋዜጠኞች በአደገኝነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ወደ ሰፈረችው ኢትዮጲያ ተጉዞ ቢሮውን ከትሟል፡፡ ቢቢሲ ኬንያ ሆኖ ጆሮውን ከቀሰረ ሰነባብቷል ለዛውም በአራት የሀገራችን ቋንቋ ስርጭችን አካቶ፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህን ሚዲያዎች እና የዘገባዎች መንፈስ በሌላ ፅሁፍ የምመለስበት በመሆኑ ለዛሬ በዚሁ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን እየተከሰተ ያለው ዘርንና ክልልን ያማከለ ግጭት ያሳሰባቸው ሁለት ኢትዮጲያዊ ምሁራን ያሉትን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡

የቀድሞው የህውሀት መስራችና አመራር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ሰሞኑን ‹‹ትውልድ ፈታኝ ቀውጥ!›› በሚል ርዕስ ባስነበቡን ፅሁፋቸው በዚህ ክፉ በሽታ  የተሰማቸውን ስጋት እንዲህ አስፍረውታል፡፡ ‹‹ይህ እየተሰራጨ ያለው ክፉ ክስተት ማቆምያ ካልተበጀለት ሃገር-አልባ ሊያደርገን ይችላል። ቀውሱን የፈጠረው የህወሓት/ኢህኣዴግ ገዢ መደብ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ይህ ሀላፊነት የማይሰማው አምባገነን ቡድን ገና ከጅምሩ የወጠናቸው ደንባራና ስግብግብ ፖሊሲዎች እንዲሁም አረመንያዊ የአገዛዝ ዘይቤዎች አሁን ከምንገኝበት አረንቋ ውስጥ ከቶናል።››

እኝህ ወያኔን ከጥንስሱ ጀምሮ የሚያቁት ሰው ስጋታቸው ‹‹አገር-አልባ›› እስከመሆን ያደረሰው የቀድሞ ወዳጆቻቸውን አላማ ሳያውቁት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዚህ በፍጥነት ስጋ ለብሶ ማየታቸው ሳያስደነግጣቸው አልቀረም፡፡ ይህ ማለት ግን ስጋቱ እና ድንጋጤው የሳቸው ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ 26 አመት ሙሉ ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው እና በሚያየው አስጨንቆታል፡፡

ሌላኛው ታዋቂ የኢኮኖሚው ዘርፍ ምሁሩ ዶ/ር አክሎክ ቢራራ በዚህ ሳምንት ‹‹በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የውጭ ኃይሎች ጫናና ሴራ እንዴት ለመቋቋም ይቻላል? በአዲሱ ዓመት ለጠባብ ብሄርተኞች እጃችን ላለመስጠት እንወስን›› በሚል ገራሚ የመጀመሪያ ክፍል  ጥናታዊ ፅሁፍ አስነብበዋል፡፡ ዶ/ሩ በፅሁፋቸው ውስጥ ‹‹የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሰራሽ ቀውሶች ለኢትዮጵያ ቀጣይነት አደጋዎች ናቸው።›› በሚል በሰጡት ንዑስ ርእስ ‹‹ዛሬ በኢትዮጵያ በመሬት ላይ የሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር–ለምሳሌ፤ ከድርቅ ረሃብ፤ ከድህነት፤ ከአገር ውስጥ የሕዝብ ፍልሰት፤ ከተስቦ በሺታዎች ወዘተ… ጋር ሲደማመር ኢትዮጵያን ወደማይመለስ ውድቀት እንድታመራ ያደርጋታል። ይህ፤ ከመጥፎ አገዛዝ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ የሚታየው ክስተት ምንን ያንጸባርቃል? ብየ ራሴን ስጠይቅ መልሱ ሆነ ተብሎ የተጸነሰውና ሊቆም የማይችል የሚመስለው የብሄር የማንነት ጥያቄ እየተስፋፋና እየከረረ መሄዱን ያሳያል የሚል ይሆናል።›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

የኢኮኖሚ ምሁሩ ወያኔ በሀገራችን ህዘቦች ውስጥ የዘራውን ክፉ የዘር ስርአት ከተፈጥሮ በሽታዎች ጋር ተዳምሮ የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የማይታከም መሆኑ ቢያሰጋቸውም የዘር ፖለቲካው ብቻ በራሱም ለሀገራችን ነቀርሳ መሆኑን ነግረውናል፡፡

በአጠቃላይ በሀገራች ላይ የተከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ፣ የንብረት ውድመቶችን ተመልክቶ እና የሙሁራኑን የስጋቶች ጥልቀን አሰተውሎ ዝም ብሎ መቀመጥ የሚችል ዜጋ ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም ሀገራችን ኢትዮጲያ እንደ ሀገር እንደትቀጥልና በህዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠነክር መስራት ያስፈልጋል፡፡ ወያኔ የዘራው ክፉ በሽታ እንዲከስም በጋራ መቆም ፍቱን መዳኒቱ፤ ስርአቱን ከስሩ ነቅሎ መጣል ደግሞ የሀገሪቱ ፈውስ ነው፡፡   ሰለዚህ ……

ስለዚህ ‹‹ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ ….›› እያልን እየዘመርን (የቀድሞው ስርአት ናፋቂዎች ብንባልም)  ለሀገችን መስራት ነው፡፡ ጥያቄህ ለሀገሬ ምን ልስራ ከሆነ ራስህን ምን መስራት እችላለሁ ብለህ ጠይቅ ያኔ መልሱን ታገኘዋለህ፡፡ እውነቱ ግን ሀገራችን የኛ የህዝቦችዋን የአንድነት ስራ ትሻለች፡፡ (አራት ነጥብ !!!)