“አንዱ ቀበሮ ሌላው ተኩላ ሁለቱም ይበሉኛል …”


የሕዝብ ፍላጎት ሁልጊዜም ሠላም ፣ ዲሞክራሲ ፣ ልማት እና ዕድገት የሕግ የበላይነት ናቸው። በተለያየ ምክንያት ሠላም ቢታወክ ሲሠሩ ውሎ በሠላም መግባት ቤተሰብን እና ንብረትን መጠበቅ አስቸጋሪ ይሆናል ። ከከፋም ሕይወት ይጠፋል ንብረት ይወድማል መኖርም አስቸጋሪ ይሆናል ። ሕዝብ ከችግር ሙሉ በሙሉ ርቆ ባይኖርም መስዋዕትነት እየከፈለም ቢሆን ችግሩን እየፈታ እና እያስወገደ ከዚህ ደረጃ ደርሷል ፤ የደረሰበት ደረጃ ግን እጅግ ውስብስብ እና ፖለቲካዊ ባህሪ ያለው በመሆኑ ለመፍታትም አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ ካለፈበት ባህላዊ መንገድ የዘለለ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሻ ሆኗል።
ለዘመናት የተከማቸውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር እንፈታለን በማለት በተለያየ ጊዜ እና ለተለያየ ዓላማ የፖለቲካ ድርጅቶች ተፈጥረዋል ፤ ሻዕብያ እና ጀብሀ ክልልን ፣ ኦነግ ፣ ሕወሐት እና ኦብነግ ብሔርን ፣ ኢህአፓ እና መኤሶን አገርን (ሕብረ ብሔር ) መሠረት አድርገው ተደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል ። ከእነዚህ መካከል ሻዕቢያ እና ሕወሐት ለመንግሥት ሥልጣን በቅተዋል ፣ ያመጡትም ወጤት በግልጽ ይታወቃል ።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር ለመፍጠርም ሆነ ለመፍታት የፖለቲካ ልሂቃን ከፍተኛ ሚና አላቸው ፣ ጠንካራ እና የዳበረ የፖለቲካ ባህል በሌለበት እና የህግ የበላይነት በማይከበርበት አገር የምኞት ፖለቲከኞች እድል አግኝተው የፖለቲካ መድረኩን ስለሚቆጣጠሩት ሕዝብ የሀገሩ እና የሥልጣን ባለቤትነቱ ተረጋግጦለት መምረጥ ፖለቲከኞችም በነፃነት ተወዳድረው መመረጥ አይችሉም ። የምኞት ፖለቲከኞች ፍላጎታቸው እስኪሟላ ሁኔታውን ያተራምሱታል። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ድብቅ ፍላጎታቸውን በጉያቸው ይዘው በሕዝብ ሥም ነው ።
ወያኔ የኢትዮጵያ የዘመናት የፖለቲካ ችግር አከተመ ብሎ ግንቦት 20 / 1983 አውጆ ነበር ፣ ሥልጣን እንደጨበጠ የጉያውን ወደ አደባባይ አውጥቶ እስከቻልኩ ኢትዮጵያን እገዛለሁ ፣ ሲያቅተኝ ኢትዮጵያን አፈራርሼ ፣ ሐብት ንብረቷን ወደ ትግራይ አጓጉዤ የትግራይ ሪፐብሊክን እመሠርታለሁ የሚለውን አጀንዳ ወደ ተግባር መመንዘር ተያያዘ ። ሕዝብን ከሕዝብ ፣ ዕምነትን ከዕምነት በማጋጨት ፣ ሕዝብን በማሰር ፣ በማሰቃየት እና በመግደል በመጀመሪያ አማራን ፣ ቀጥሎ ኦሮሞን ከዚያም ሌሎችን ብሔረሰቦች እንደ ሥጋት ቅደም ተከተላቸው መምታት እና ማንበርከክ የሚለውን ዕቅዱን አጧጧፈው ። ማጋጨቱ ፣
ማሠሩ ፣ ማሰቃየቱ ፣ መግደሉ ቢሳካለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ግን መከፋፈል አንድነቱንም መናድ አልቻለም ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ደማችን አንድ ፣ አገራችን የጋራ ብሎ ፀረወያኔ ትግሉን አፋፍሞ ወያኔን ውጥረት እና ጭንቀት ውስጥ አስገብቷል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁርጠኛ ፀረወያኔ ትግል በሚያካሂድበት ወቅት ተረኛ ሥልጣን ጠባቂ የምኞት ፖለቲከኞች ፀረሕዝብ እና ፀርሀገር በመሆን የወያኔ ተባባሪ ሀገር አፍራሽ ግብረ ሐይል በመሆን ትግሉን እያዳከመ ለወያኔ እስትንፋስ ይሰጣል ::ወያኔ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊነት ላይ ወያኔነትን እያውለበለበ ነው ። ወያኔነት ዘረኝነት ፣ ስግብግብነት ፣ ራስ ወዳድነት ፣ ተበቃይነት ፣ ቅጥረኛነት ፣ ፀረኢትዮጵያ እና ፀረኢትዮጵያዊነት ነው ። ተረኛ ሥልጣን ጠባቂ ፖለቲከኞች ሀገር ሕዝብ እየደማ ለላም አለኝ በሰማይ ሥልጣናቸው ወያኔነትን ይረዳሉ ፣ ያግዛሉ ፣ እንዲያውም ወያኔነትን እየተለማመዱ ነው ፤ የዘውግ እና የባዶ አንድነት ተዋንያን ተጠቃሽ ናቸው ።
የዘውግ ፖለቲከኞች ከኦሮሞ ብሔረሰብ በላይ ለብሔረሰቡ እኛ እንጨነቃለን እናስባለን በማለት ኦሮሞነትን ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን መቀስቀሻ እና ማደራጃ አድርገውታል ። ታሪክን ቆርጦ በመቀጠል ኦሮሞ ተበደለ ፣ ቋንቋው ፣ ባሕሉ እና ማንነቱ ጠፋ ፣ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ነህ ተብሎ የሌላ ማንነትን እንዲኖር ተገደደ ፣ ፈጣሪ የሰጠውን መሬት ፣ ሐብት እና
ንብረት ተነፍጎ የሌሎች መጠቀሚያ ሆነ ፣ የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብቱ ተነጥቆ በባርነት ይኖራል በማለት በደሙ እና አጥንቱ ከሰራው ቤቱ እና ሀገሩ ኢትዮጵያ ሊያስወጡት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለውን ትልቅ የታሪክ አሻራ ሊፍቁበት ፣ ኢትዮጵያዊ ማገርነቱን እና ምሰሶነቱን ሊያፈርሱበት በአጠቃላይ ኦሮሞን ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት እንዲሁም
ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሊነጥሉት ይሯሯጣሉ ።
ጃዋር የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን መጠናከር አስፈላጊነት ሲገልጽ ፣ በእኛ አካባቢ ሙስሊሞች ጠንካራ ስለሆኑ ቀና ብሎ የሚያያቸው የለም ፣ ካለም በሜንጫ አንገቱን እንለዋለን ካለ በኋላ በእስልምና እና በኦሮሞ መካከል ያለውን አንድነት ማብራራት ቀጠለ ። እንደጃዋር እምነት እስልምና ሲነካ ኦሮሞ ይነካል ፣ ኦሮሞ ሲነካም እስልምና ስለሚነካ የኦሮሞ ነፃ መውጣት የእስልምና ነፃ መውጣት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የኦሮሞን የነፃነት ትግል መደገፍ
ይገባቸዋል ባይ ነው ።፡ይህ ካልሆነ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ቀና ብለው እንደማይሄዱ እና መስጊድ መስራት እንደማይችሉ የጎንደር እና የትግራይ ሙስሊሞችን በምሳሌነት በማንሳት አስረድቷል ። ጃዋር ስለእስልምና እና ስለ ኦሮሞነት የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታነት ሲያወራ እስላም ስላልሆኑ ኦሮሞዎች መኖር አለመኖር ትንፍሽ አላለም ። ጃዋር መቼም አያልቅበት ዲባባ ሁሉ ኦሮሞ አይደለም በማለት ኦሮሞ የሆኑ ኦሮሞዎች እና ኦሮሞ ያልሆኑ ኦሮሞዎች ብሎ እንደፈረጀ ሁሉ እስላም ያልሆነም ኦሮሞ አይደለም ይለን ይሆናል ።
ኦሮሞነትን በተለያዩ ፍላጎቶች እየመነዘሩ ኦሮሞነትን መሥጠት እና መንሳት ወይም ኦሮሞዎች ሁሉ እኩል አይደሉም ብሎ ማበላለጥ ጆርጅ ኦርዌል (George Orwell ) ሁሉም እንሦች እኩል ናቸው ፤ አንዳንዶቹ ግን ከሌሎቹ የበለጡ እኩል ናቸው (“All animals are equal, but some animals are more equal than others) ያለው የማረከው ይመስላል ፡ ለነገሩ ድብቅ አላማ ያለው የማይለው ነገር የለም።
የኦሮሞ ብሔርተኝነት ሥሜት የወዘወዛቸው ዘውገኞች ዛሬ የሚቀብሩት የልዩነት ፈንጂ በወቅቱ ካልተወገደ ነገ አካባቢያዊነት ፣ ኢትዮጵያዊነት እና ጎረቤትነት ተደምረውበት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሊደርስ የሚችለው ሰባዊ ቀውስ ከሚገመተው እና ከሚታሰበው በላይ እጅግ የከፋ ሊሆን ይችላል ። የሠራሁትን ቤቴን እና ሀገሬን ኢትዮጵያ አላፈርስም ላለ ኦሮሞ ይሄ ሁሉ
አይገባውም ፣ የሚገባው ሰላም ፣ ልማት ፣ አንድነት ፣ እኩልነት እና ነፃነት ነው ።
እነ ጃዋር ኦሮሞ እና እስልምና አንድ ናቸው ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ነፃ የሚወጡት ኦሮሞ ነፃ ሲወጣ ስለሆነ የኦሮሞን የነፃነት ትግል ይርዱ የሚሉት አባባል በኦሮሞ ማዕከልነት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ያሰባሰበ መንግሥት የመመሥረት ፍላጎት መልዕክት ነው የሚሉ በርካታ ናቸው ። ግምቱ ትክክል ከሆነ የኦርቶዶክስ ፣ የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት
መንግሥት ምሥረታ ጥያቄ ቢመጣ አንደምታው ምን ሊሆን ነው ። የቋንቋ ፌዴሬሽን ወደ ድንበር እና መሬት ይገባኛል ግጭት እንዳስገባው የሐይማኖት ፌዴሬሽንም ወደ ሐይማኖት ጦርነት ያመራል ማለት ይቻላል ።
የዘውግ ፖለቲከኞች የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ማማ ላይ አውጥተው በአንድነት እና በእኩልነት አብረን መኖር እንችላለን ማለት ፣ ሐይማኖት የግል ሀገር የጋራ የሚለውን ትልቅ ኢትዮጵያዊ እሴት ዘሎ የየብሔረሰቡን ሙስሊሞች ፍለጋ መሄድ ፣ በተምታታ ፍላጎት እና ማንነት እየዳከሩ በአላማቢስ እና ግብየለሽ አቋም መናወዝ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ትግሉን
ይጎዳል ፣ ወያኔን ግን ይጠቅማል ።

እንደ ዘውገኞች ሌላው የፖለቲካ እንቅፋት የባዶ አንድነት ኃይል ነው ፤ አንድ ሀገር አንድ ህዝብ ማለቱ መልካም ነው ነገር ግን በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔረሰቦች ባሉበት ሐገር የሚያስፈልጉ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ መሠረቶችን ጠንቅቆ መረዳቱ አስፈላጊ ነው። በአንድ ሀገር የግል ፣ የጋር እና የወል መብቶችን ለማስከበር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊመቻች ይገባል። ይህ በሌለበት አንድ ሀገርም ሆነ አንድ ህዝብ የማይታሰብ ነው ።
የአንድ ሀገር የአንድ ሕዝብ አቀንቃኞች የቋንቋ ፣ የባህል እና ራስን በራስ የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሲነሱ ክልብሽ የሚላቸው የሚዘምሩለትን ያልተረዱ ወይም መንገዱ የጠፋባቸው ናቸው ። ባዶ አንድነት ለማንም ለምንም አይበጅም ፤ አንድነት ያለእኩልነት እና ነፃነት ባዶ ጋጋታ ወይም ጩሸት ነው ። አንድነት እኩልነት እና ነፃነት ሲኖር መብቶች ያለችግር ይሟላሉ ፣ ይከበራሉ ። አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ፈላጊዎች የሁሉንም መብት በእኩልነት ተቀብላችሁ እና አክብራችሁ አብሮ ለመኖር ዝግጁነታችሁን ገልጻችሁ ከብሔረተኞች ጋር አብሮ ለመኖር ያላችሁን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ገልጻችሁ ዘውገኞችን
ለውይይት በመጥራት የአንድነት ፣ የእኩልነት እና የነፃነት ጠበቃ እና የሕዝብ ወገን መሆናችሁን አረጋግጡ ።
የዘውግ እና የባዶ አንድነት ፖለቲካ ለፍትሓዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምሥረታ እና ግንባታ በሽታ ነው ፣ በተለይም ለድህረ ወያኔ ኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ነው ። በሽታ ውጫዊ ከሆነ በክተባት ፣ በሥራዓተ ምግብ እና የአካል እንቅስቃሴ ፣ በግል እና በአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ መከላከል እንደሚቻል ፣ ይህን አልፎ በሽታው ወደ ውስጥ ቢገባ በሕክምና እንደሚፈታ ፣ በሽታው ከውስጥ በቅሎ እና አድጎ ካጠቃ ካንሰር በመሆኑ የታወከውን ክፍል
ቆርጦ መጣል እንዳለበት ያም ሆኖ መዘዙ እና መርዙ ሙሉ በሙሉ ስለማይፀዳ ቀጣይ ሕክምና እንደሚይሥፈለግ ከባለሙያዎች ይሰማል ። ከዚህ መረዳት የተቻለው ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመውረር የመጣውን የውጭ ጠላት ሁሉ በአንድነት ተሰባስበው ወራሪውን ለምን ማባረር እንዳልቸገራቸው ፣ በአንፃሩ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ በቅሎ እና አድጎ መልሶ
የወረራቸውን የውስጥ በሽታ በአንድነት ተባብረው ከአካላቸው ቆርጠው ለመጣል ለምን አስቸጋሪ እና ውስብስብ እንደሆነባቸው ነው::
በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ወያኔ ከኢትዮጵያ አካል ውስጥ በቅሎ መልሶ ኢትዮጵያን የወረረ ካንሰር ስለሆነ ኢትዮጵያን ከማፈራረሱ በፊት ተቆርጦ ሊጣል ይገባል በማለት በተደጋጋሚ ያሳስቡ ነበር ፣ ሰሚ ጠፍቶ ያሉት እየደረሰ ነው ። ወያኔ በመላው ኢትዮጵያ ካንሰሩን አሰራጭቶ ከየብሔረሰቡ የፈጠራቸው የተወሰኑ የፖለቲካ ካንሰር ድዊያን በማወቅም ሆነ ባለማውቅ የወያኔን አገዛዝ ዕድሜ እና የኢትዮጵያውያንን የሰቆቃ ግዜ እያራዘሙ ነው ፣ ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ እየጫረ ፣ እየአቀጣጠለና እያፋፋመ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት የሚፈሰው ደም የፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማን ሥጋት ትክክለኛነት ግልጽ አድርጎ ያሳያል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት እጦት ከገባበት የከፋ የፖለቲካ አረንቋ መውጣት አቅቶት ይላቁጣል ። ሁኔታው የቀጠለው ችግሩ ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም ። ችግሩ ወላጅ አስተምሮ ለሀላፊነት ያደረሳቸው የፖለቲካ ልሂቃን ልጆቹ ከዛሬ ነገ ይፈቱታል ተብሎ ሲጠበቅ ከህዝብ የራቁ እና ፍላጎታቸው ከሀገር በላይ የሆነባቸው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ በየግዜው ከሚፈጥሩት ውስብስብ የፖልቲካ ችግር የተነሳ ነው ።እነዚህ የዘውግ እና የባዶ አንድነት ፖለቲከኞች ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ እየፈጀ ሲያስፈጅ፣ ሀገር በላያችን ላይ ሲያፈርስ ፣ ህዝብን በገዛ ሀገሩ ተፈናቃይ ሲያደርግ ፣ በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ የሚልሰው የሚቀምሰው አጥቶ በረሀብ ሲጠበስ እያዩ እና እየሰሙ ከብሔርተኘነት እና ባዶ አንድነት ጩቨት ሊወጡ አልቻሉም ። እዬዬም ሲዳላ ነው እና የማይገኝ የምኞት ስልጣን አንጋጦ ከመጠበቅ ሀገር ማዳን ይቅደም ፣ ቀሪው ጉዳይ በወቅቱ ይታያል ።
የኢትዮጵያ ህዝብ አገራዊ የነፃነት ቻርተሩን በደሙ ስለፃፈ፣ በአንድነት በእኩልነት እና በፍትሐዊ ተጠቃሚነት አብሮ በጋራ ለመኖር ስለወሰነ የዘውግ የነፃነት ቻርተር አርቃቂ የባዶ አንድነት ዘማሪ ፖለቲከኞችን አይፈልግም። የሕዝብ ወገን ነኝ የሚል ፣ በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ እና ሰቆቃ ይቁም ፣ ሀገር አይፍረስ ፣ ማንነት አይጥፋ እስራት ፣ ግርፋት ፣ ግድያ ዘረኝነት ይብቃ የሚል የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ፣ ውሳኔ እና ምርጫ የሆነውን ሰላም ፣ ልማት እና ብልጽግና ፣ እኩልነት እና ነፃነት ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን እውን የሚያደርግ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት መረባረቢያው ግዜ
ዛሬ ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1964 ማልኮም ኤክስ (Malcolm X) በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ንግግር ሲያደርግ በወቅቱ ለአሜሪካ ፕሬዘዳንትነት ሲወዳደሩ ከነበሩት ከቤሪ ጎልድዋተር (Barry Goldwater) እና ከሊንደን ጆንሰን (Lyndon Johnson) ማንን ትመርጣለህ ተብሎ ሲጠየቅ “አንዱ ተኩላ ሌላው ቀበሮ ስለሆኑ ሁለቱም ስለሚበሉኝ ማንኛቸውንም አልመርጥም” እንዳለው ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየፈጀ የሚያስፈጀውን ወያኔን
የሚፋለመው በዘውግ ከፋፋይ እና በባዶ አንድነት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች ለመተካት ሳይሆን በወያኔ መቃብር ላይ የሁሉም የጋራ ቤት በምትሆን ኢትዮጵያ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ሐውልት ለማቆም ነው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s