Archive | November 2017

በግብጽ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 235 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዜና)በግብጽ ሳይናይ ግዛት በአንድ መስጊድ ላይ በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 235 ሰዎች ሲገደሉ 130 ሰዎች ቆስለዋል።

የሟቾቹም ሆነ በጥቃቱ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል መረጃዎች ጠቁመዋል።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሶስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀንም አውጀዋል።

እስካሁንም ለጥቃቱ በይፋ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም ።

በግብጽ ሳይናይ ግዛት ዛሬ በአንድ መስጊድ ላይ በደረሰው የሽብር ጥቃት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ ቢያንስ 235 ሰዎች ሲገደሉ 130 ሰዎች ላይ ደግሞ ጉዳት ደርሷል።

አርብ እኩለ ቀን ላይ በተፈጸመ በዚህ ጥቃት ቢያንስ ሁለት ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

ከፍንዳታው በኋላ በመስጊዱ በብዛት ለአርብ ስግደት የተገኙ ሰዎች ነፍሳቸውን ለማዳን በሩጫ ለመውጣት በሚሞክሩበት ጊዜ ውጪ ሆነው የሚጠብቁት ጥቃት ፈጻሚዎች ተኩስ ከፍተውባቸዋል።

ፍንዳታው በመስጊዱ ላይም ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰም ዘገባዎች አመልክተዋል።

የግብጽ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ካሊድ ሙጃሂድ ለሀገሪቱ ቴሌቪዥን ሲናገሩ ጥቃቱን የሽብር ጥቃት ነው ብለውታል።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከጥቃቱ በኋላ ከጸጥታ አማካሪዎቻቸው ጋር ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን የሶስት ቀናት ብሔራዊ ሀዘንም አውጀዋል።

እስካሁን ለጥቃቱ በይፋ ሃላፊነትን የወሰደ አካል ባይኖርም የግብጽ የጸጥታ ሃይሎች ግን በየቀኑ በሚባል ደረጃ ከአይሲስ ጋር ከወገኑ ሃይሎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ይነገራል።

ጥቃቱን ያደረሱት ሰዎችም ለጊዜው ወዴት እንደጠፉና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም።

የዛሬው ጥቃት ባሳይናይ ግዛት ከተፈጸሙት ጥቃቶች ሁሉ አስከፊው ነው ተብሏል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ በራት ተሽከርካሪዎች በመሆን ፍንዳታውን ካደረሱ በኋላ በአካባቢው ያሉ ተሽከርካሪዎችን በቦምብ በማጋየት ለአርብ ጸሎት በመስጊድ የተሰበሰቡትን ሰዎች ከአደጋው መውጫ አሳጥተዋቸዋል።

በግብጽ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 የሙስሊም ወንድማማቾች በመባል የሚታወቀው እንቅስቃሴ መሪ መሀመድ ሙርሲ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የእስልምና አክራሪዎች ጥቃት በማድረስ ላይ ናቸው።

በ2014 ፕሬዝዳንት አልሲሲ በግዛቲቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያውጁ አካባቢው የአሸባሪዎች መፈልፈያ ሆኗል ብለው ነበር።

በሳይናይ ግዛት ከ2014 ጀምሮ ለአይሲስ አጋርነታቸውን ከሚገልጹ ወገኖች በደረሰ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር አባላትና ሲቪሎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ለኢትዮጵያ የአባይ ጉዳይ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው ተባለ

(ኢሳት ዜና) የአባይ ጉዳይ ለእኛም የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገለጹ።

ቃል አቀባዩ አቶ መለስ አለም የአባይ ግድብን በተመለከተ ከግብጽ ጋር ውጥረት መከሰቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ኢትዮጵያ በራሷ አቅም አባይን መገደቧን ትቀጥላለች።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በቅርቡ አንድ የአሳ ፋብሪካን ሲመርቁ አባይ የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው የአባይ ግድብ የተነሳ ግብጽ ሰሞኑን ጠንካራና ጠጠር ያለ ቃላት በመወርወር ላይ ትገኛለች።

ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ፣ግብጽና ሱዳን መካከል የተጀመረው ውይይት እንከን ስለገጠመው መሆኑ ነው የተነገረው።

ግብጽ በሶስትዮሹ ምክክር ከዚህ ቀደሞ የነበሩ የቅኝ ግዛት ውሎች ግምት ውስጥ ይግቡልኝ ስትል ኢትዮጵያና ሱዳን ሀሳቡን አልተቀበሉትም ነበር።

እናም በዚሁ ሳቢያ እሰጣ ገባ የገቡት የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች በካይሮ ያካሄዱት ውይይት መቋረጡ ለሰጣ ገባው ምክንያት ሆኗል።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ታዲያ የውይይቱን መቋረጥ ተከትሎ ማስጠንቀቂያ አዘል ሀሳብ ሰንዝረዋል።

አልሲሲ በቅርቡ አንድ የአሳ ፋብሪካ በሀገራቸው ሲመርቁ እንዳሉት የአባይ ጉዳይ ለግብጽ የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው።

ይህ ጠንከርና ጠጠር ያለው የአልሲሲ ንግግር ታዲያ ኢትዮጵያን ተመሳሳይ ቃላት እንድትሰነዝር አስገድዷታል።

የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የአባይ ጉዳይ ለኢትዮጵያም የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው።

እናም ግብጽ የሶስቱን ሀገራት የቀድሞ ስምምነት በሚጥስ መልኩ መግለጫ መስጠቷ የተሳሳተ ነው ብለዋል።

በግብጽ በኩል እየተሰነዘረ ያለው የማስጠንቀቂያ ቃላት ኢትዮጵያ የአባይን ግድብ እውን የምታደርግ ከሆነ የውሃው መጠን ቀንሶ ህልውናችንን ስጋት ውስጥ ይከታል በሚል ነው።

የሕዳሴው ግድብ ተብሎ የሚታወቀውን ግንባታ ከ60 በመቶ በላይ ማጠናቀቋን የምትገልጸው ኢትዮጵያ ግን ስራው እንደሚቀጥል አስታውቃለች።

ሱዳን በበኩሏ ኢትዮጵያ ግድቡን መገደቧ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያስከትለው ችግር አይኖርም ባይ ነች።

በዚህ የሱዳን አቋም ሳቢያም ግብጽ የካርቱም መንግስት ለኢትዮጵያ እያደላ ነው በሚል ቅሬታዋን ገልጻለች።

ግብጽ የአባይ ግድብን ለማስቆም ወታደራዊ አማራጭ የምትከተል ከሆነ አካባቢው ወደ ከፋ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል በሚል ዘገባዎች ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።

አጠብቂኝ በቃ!

 

ጠዋ…ት ተነስቼ – እንደ ወፍ በርሬ
እመጣለሁ ያልኩሽ? ተይው በቃ ውዴ
አጠብቂኝ ይቅር! አልመጣም ጨርሶ 
ክረምቱ እስኪያበቃ – ጨለማውን ገፎ::
ይህ ጥቁር ደመና – ጉሙን ያረገዘው
ለሊቱን አርዝሞ – ቀኑን ያሳጠረው
ተበትኖ እስኪጠፋ
አጠብቂኝ በቃ!

ይህ የኔ ህይወት ቀኑን የተቀማ
እንኩዋን ላንቺ ሊሆን ለራሱም ያልቀና
ቢመጣም ችግር ነው ብሶትና ‘ሮሮ
በኑሮ ውጣውረድ ጭንቅላቱ ሰክሮ
አጠብቂኝ በቃ አ..ጠ..ብ..ቂ..ኝ በቃ!

ያ የብርሃን ንጉስ – የጸሃይቱ ጌታ
ስራዬን አይቶልኝ – አሁን አለሁ ሲለኝ!
ፍሬዬን ባርኮልኝ – ዘሬን አብዝቶልኝ
ከዛ አይሻለሁ – በንጋት ገስግሼ
ጨርቄን ማቄን ሳልል – ያለኝን ለብሼ::
እውነት… እ…ውነት ውዴ!
ለኔ በቂዬ ነው የጸሃይዋ ድምቀት
ያኔ ይታየኛል ያንቺ ምስጢርነት::

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያስከትል አዲስ የጸጥታ እና የደህንነት ዕቅድ ይፋ ተደረገ 

(ዘ-ሃበሻ) በሰብዓዊ መብት ላይ ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጽም አዲስ ዕቅድ ይፋ ተደረገ፡፡ ዕቅዱ የብሔራዊ እና የክልል ደህንነት ጸጥታ ምክር ቤቶች የጋራ ዕቅድ የሚባል ሲሆን፣ ይህን ለማስፈጸምም ራሱን የቻለ አንድ ግብር ኃይል አለው፡፡ በውጭ ዲፕሎማቶች እና በእርዳታ ሰጪ ሀገራት ጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት ተገዶ የነበረው ገዥው ፓርቲ፣ አሁን ደግሞ ቆዳውን ገልብጦ ሌላ ጸረ ህዝብ አዋጅ ይዞ ብቅ ማለቱም ተነግሯል፡፡

ትላንት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተደረገው ስበሰባ ላይ የፌደራል እና የከልል የደህንነት አባላት፣ የመከላከያ አዛዦች እና በጸትታ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ የገዥው ቡድን ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የመከላከያ ሚኒስትሩ እና የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ አዲስ የወጣው ዕቅድ ለቀጣይ አንድ ዓመት ይቆያል፡፡ ዕቅዱ በፌደራል እና በክልሎች የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚተገበር የገለጹት አቶ ሲራጅ፣ ዕቅዱም ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚተገበር ተናግረዋል፡፡

በህዝባዊ ተቃውሞ ከፍተኛ ጭንቅት ላይ የሚገኘው አገዛዙ አንዴ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የብሔራዊ እና የክልል ደህንነት ጸጥታ ምክር ቤት የጋራ ዕቅድ በማለት የህዝብን ተቃውሞ ለማፈን እየሞከረ እንደሚገኝ ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡ ሀገሪቱ ተረጋግታለች በማለት በጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንስቶ የነበረው አገዛዙ፣ አሁን ላይ በድጋሚ አዋጁን መመለስ መሳቂያ መሳለቂያ እንደሚያደርገው አምኗል የሚሉ ታዛቢዎች፣ በዚህም የተነሳ የስም ለውጥ በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚተካ አዲስ ህግ ማውጣቱንም ታዛቢዎቹ ያክላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ህዝብ እየተካሔደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ የስልጣን መናጋት የፈጠረበት አገዛዙ፣ አዲሱን የደህንነት ዕቅድ የተቃውሞ ማብረጃ ለማድረግ እንዳቀደም ታውቋል፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የተባለው ግብረ ኃይል ውስጥ የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የፌደራል እና የክልል የደህንነት አዛዦች የተካተቱበት ሲሆን፣ ግብረ ኃይሉም ህዝባዊ ተቃውሞ በተነሳበት ሰዓት ሁሉ ወታደሮችን እና ፖሊሶችን የማዘዝ ስልጣን አለው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስራ ላይ በነበረበት ሰዓት እስከ 60 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች መታሰራቸው እና በርካቶችም መገደላቸው ይታወሳል፡፡ አዲሱ ዕቅድም ተመሳሳይ ዓለማ እንዳለው ለመረዳት ተችሏል፡፡

”ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”! ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ

ኢትዮጵያዊነት ከደም አልፎ በልብ ውስጥ የተቀመጠ የተከበረ ማንነት ነው- ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ

‹‹ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ዛሬ ባየነው ትዕይንት ትርጉሙ ገብቶኛል፡፡ኢትዮጵያዊነት ልዩ ነው፡፡ አትዮጵያዊነት ሱስ ነው፡፡ከደም አልፎ ልቡ ውስጥ እንዳለ ዛሬ አይተነዋል፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ይሁን የት ፣ምን ያህል የኢትዮጵያዊነት ርሀብ እንዳለበት በመላው ዓለም የሚገኙ ሁሉ መምጣታችንን ሲሰሙ ምን ያህል በውስጣቸው እንዳደረ አይተናል፡፡ችግሮቻችንን በጋራ እየፈታን ለእድገታችን የምንሰራበት ጊዜም ነው ብለዋል፡፡ 23131890_1861009617272604_7999216097441461243_n

ለዚች ሀገር ህይወቱን አሳልፎ የሰጠው ይህ ህዝብ ለሀገሩ ፣ለአንድነቱ ነው፡፡ትናንት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ደሙን የገበረው ለኢትዮጵያ ነው፡፡ለሀገራችን አሁንም መስራት ይጠበቅብናል፡፡ወደ ኋላ እያየን ወደፊት ልንጓዝ አንችልም፡፡ያለፈውን እንርሳው ፡፡ለሀገራችን አንድነት በጋራ እንቁም ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ዛሬ አማራ ክልል የተገኘነው እንደምስታፈልጉን ፣እንደምናስፈልጋችሁ ስለምናምን ነው፡፡ለኢትዮጵያችን ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያስፈልጓታል፡፡ፍቅር ያሸንፋል፡፡ብሄሮች በጋራ ሊቆሙላት ይገባል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ ነው ያለነው፡፡በጎረቤቶቻችን ላይ ያለውን መመልከት ያስፈልጋል፡፡ለምናደርጋቸው ነገሮች ሀላፊነት ሊሰማን ይገባል፡፡

አቶ ለማ አክለውም የሀገሪቱ ተረካቢ ለሆነው ወጣት ስራ ልንፈጥርለት ይገባል፡፡ትውልዱን ለመቅረጽ ደግሞ ቅድሚያ የሚወስደው ቤተሰብ ነው፡፡በመቀጠልም ማህበረሰብ ፤ስለሆነም ለስነ-ምግባር ጉዳይ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል፡፡አባቶች ፣አባ ገዳዎች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ስነ-ምግባርን በተመለከተ ትኩረት ልትሰጡት ይገባል ብለዋል ፡፡

 

በእነ ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ ብይን ለመስጠት በሚል በድጋሜ ቀጠሮ ተሰጥቷል

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት የፍ/ቤት ትዕዛዝ አላከበረም ተብሏል

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የሽብር ክስ የቀረበባቸውን የእነ ንግስት ይርጋ የክስ መዝገብ የአቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾች የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ መከላከል ያስፈልጋቸዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ሊሰናበቱ ይገባል የሚለውን ብይን ለማሰማት ለዛሬ ጥቅምት 21/2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ የነበር ቢሆንም፣ ዳኞች መዝገቡን መርምሮ ለመስራት ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገናል በሚል በድጋሜ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡

አክቲቪስት ንግስት ይርጋን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾችን የያዘው የእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ ነሐሴ 12/2009 ዓ.ም ለብይን በሚል ቀጠሮ ከተያዘ በኋላ ብይኑ አልደረሰም በሚል ለዛሬ ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን ዛሬም መዝገቡ ተመርምሮ ብይኑ ባለመሰራቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለህዳር 01/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ቃሊቲ ማ/ቤት የምትገኘው አክቲቪስት ንግስት ይርጋ በእስር ቤት የጥየቃ ሰዓትና የጠያቂ ገደብ ተጥሎብኛል የሚሉና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አቤቱታ አቅርባ ይህ እንዲስተካከል ፍ/ቤቱ ለቃሊቲ ማ/ቤት አስተዳደር ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ማ/ቤቱ ትዕዛዝን አለማክበሩ ተገልጹዋል፡፡

‹‹ሐምሌ 21/2009 ዓ.ም ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶልኝ ነበር፡፡ ሆኖም ማ/ቤት አስተዳደሩ የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ መብቶቼን ባለማክበሩ በድጋሜ ነሃሴ 12/2009 ዓ.ም አቤቱታ አቅርቤ፣ ለዛሬ ማ/ቤት አስተዳደር ለምን ትዕዛዙን እንዳላከበረ መልስ እንዲሰጥ ታዝዞ ነበር፡፡ ይባስ ብሎ በማ/ቤቱ አስተዳደር ቢሮ እየተጠራሁ ‹አንቺ ማን ስለሆንሽ ነው ማ/ቤቱን የምትከሽው፣ አንቺ ከማን ትበልጫለሽ እየተባልሁ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠኝ ነው›› በማለት ንግስት ይርጋ ስላለው ሁኔታ አቤቱታ አሰምታለች፡፡

ሌሎችም ተከሳሾች አቤቱታ እንዳላቸው ቢገልጹም ፍ/ቤቱ አቤቱታቸውን በጽሁፍ ካቀረቡ ብቻ እንደሚቀበላቸው በመግለጽ እንዳይይገሩ ከልክሏል፡፡

ፍ/ቤቱ የቃሊቲ ማ/ቤት አስተዳደር ቀደም ሲል በንግስት ይርጋ አቤቱታ ላይ የተላለፈውን የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበረ በቀጣይ ቀጠሮ ቀርቦ እንዲያስረዳ በድጋሜ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡