Archive | April 1, 2018

እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲፈቱ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተከራካሪዎች አሳሰቡ

 

ባለፈው እሁድ በድጋሚ ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄ ቀረበ፡፡ ጥያቄው ከሀገር ውስጥ አልፎ በውጭው ዓለም የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጭምር ሲሆን፤ ስለ ጋዜጠኞች መብት የሚሟገቱ ድርጅቶችም የታሰሩት ሰዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ መግለጫ በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው እሁድ መጋቢት 16 ቀን 2010 በተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት በተሰናዳ የምስጋና ፕሮግራም ላይ ታድመው የነበሩ 12 ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ሰዎች በድጋሚ ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

eskinder free

ዓለም ዓቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ የእነ እስክንድር ነጋን መታሰር አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ለእስር የተዳረጉት ሁሉም ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ መንግስትን አሳስቧል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ የፍሎሪዳ ግዛት ሴናተር የሆኑት ማርኮ ሩቢኦ በውሸት በተመሰረተበት ክስ ለእስር ተዳርጎ ከሰባት ዓመት በኋላ በቅርቡ የተፈታው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አብረውት የታሰሩት የፖለቲካ እስረኞች መፈታት አለባቸው ሲሉ አገዛዙን አሳስበዋል፡፡ ሌላው ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ የጋዜጠኞቹ እና ፖለቲከኞቹ መታሰር አሳፋሪ መሆኑን ገልጾ፣ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ያሰራቸውን አገዛዝ አሳስቧል፡፡

የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች በተናጠል ካወጡት የእስረኞች ይፈቱ መግለጫ በተጨማሪ፤ አርባ ዓለም ዓቀፍ እና በኢትዮጵያውያን የተቋቋሙ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋዜጠኞቹ እና ፖለቲከኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ቅንጅት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፤ ሲፒጄም ይህን ስብስብ መቀላቀሉ ታውቋል፡፡ አርባዎቹ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ለሚሰየሙት ዶ/ር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ፤ ጋዜጠኞቹ እና ፖለቲከኞቹ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡ ሁሉም የታሰሩት ያለ ምንም ክስ መሆኑን የጠቀሱት አርባዎቹ የመብት ተከራካሪ ድርጅቶች፤ እነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የታሰሩትም አርብ የካቲት 23 ቀን 2010 በጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አማካይነት መሆኑንም በጋራ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

የህሊና እስረኞቹ በአሁን ሰዓት ታስረው የሚገኙት በላፍቶ ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ፖሊስ ጣብያ ሲሆን፤ የእስር ቤት አያያዛቸውም ለበሽታ እና ለመሰል ጉዳቶች የሚያጋልጥ እንደሆነ ታውቋል፡፡ 5 በስምንት በሆኑ ሶስት ክፍሎች ውስጥ ከ200 ሰዎች ጋር የታሰሩት እነ እስክንድር ነጋ፤ ክፍሏ በጣም ጠባብ በመሆኗ ለመተኛትም ሆነ ለመቀመጥ እንዳልቻሉም ተነግሯል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ የእስር ሁኔታ ላይ ከሚገኙት ታሳሪዎች አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ከዚህ ቀደም በዝዋይ እስር ቤት ሳለ ያጋጠመው የወገብ ህመም አገርሽቶበት በትላንትናው ዕለት ሆስፒታል መግባቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የእስር ቤቱ ወለል ወይም መሬት ቀዝቃዛ ሲሚንቶ መሆኑ፣ የታሳሪዎቹን የጤና ሁኔታ ለእንከን እንደሚያጋልጠው ተነግሯል፡፡

Image may contain: text

የዶክተር አቢይ መመረጥ፣ መጻኢ እድላቸውና ፈተናዎቻቸው

abiy

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)

“ምርጫችን መለያየት ወይም መበታተን ሳይሆን መደመር/አንድ መሆን ብቻ ነው። አማራና ኦሮሞ በወንፊት እንኳ እንደማይለያዩ ሠርገኛ ጤፍ ማለት ናቸው። ታሪካችን የአንድነትና በአንድነት አብሮ የመሥራት ታሪክ ነው፤ ለዚህም የፋሲል ግምብ ግምባታና አድዋ በቂ ምሣሌዎቻችን ናቸው። ይህ አገር የወረስነው ሳይሆን ከልጆቻችን የተዋስነው አገር ነው።” አቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዶክተር አቢይ አህመድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ ከላይ የተጠቀሰውን መሰል፤ በርካታ ቀስቃሽና አገር ወዳድ ንግግሮችን በማሰማታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገዝፈውና ተወዳጅ ሆነው ብቅ ያሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በአገር አቀፍ ደረጃ ስማቸው አሁን ጎልቶ ተሰማ እንጂ፤ እነ አቶ ለማ መገርሳና አዲሱ ኦህዴድ ለጀመሩት ለውጥ እንደ አንድ ዋነኛ አጋር ሆነው፤ ድምጻቸውን አጥፍተው ሲሰሩ እንደቆዩ ይነገራል።

ሸንጎ በአንድ በኩል እንዲህ ዓይነት ችሎታና አገር ወዳድነት በአያሌው የተለገሳቸው ግለሰብ ለአገር መሪነት መመረጣቸው ደስ  የሚል ዜና መሆኑን እየገለጽን፤ በሌላ በኩል አገሪቱ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ አንጻር፤ በርካታ ጠጣርና ጠመዝማዛ ፈተናውች እንደሚገጥሟቸው ከወዲሁ ማሰብ እንችላለን። ከነዚህ ውስጥ ዋነኛው የመከላከያና የጸጥታ ሀይሎች በህወሃት እዝ ስር መሆናችው ነው። ይሁን እንጂ ዶክተር አቢይ ከመመረጣቸው በፊት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ተከትለው ወደፊት ከተራመዱ (ለምሳሌ እኔ የማንም ቱቦ አልሆንም ያሉትን እናስታውሳልን) ህዝቡ ሲጠይቅና ሲዋደቅለት የቆየውን ለውጥ ለመተግበር አንዲት ቀጭን እድል ይኖራቸዋል ብለን እንገምታለን።

ይህም ቀጭን እድል ዶክተር አቢይ የሚያቋቁሙት መንግስት (ካቢኔ) ከህዝብ ጋር በተለይም ከወጣቱ ጋር የሚፈጥረው አጋርንት ነው። እስካሁን ከሰማነው ዶክተሩ በአማራና በኦሮሞ እንዲሁም በከፊል ደቡብ ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አላቸው። በቅልጥፍና ወጣቶች ተደራጅተውና ተቀናጅተው በመንቀሳቀስ የለውጡ አስተማማኝ ሃይል እንዲሆኑ መርዳት ይጠበቅባቸዋል ። ህጋዊ መድረኮችን በመጠቀም መንግስታቸው ክሌሎች ህዝቦች ጋር (ቤንሻንጉል፤ ጋምቤላ፤ ሱማሌ) የሚኖረውን ዝምድና ማጥበቅ;። አሁን በኢህአደግ ውስጥ ያለውን ወደ እርሳቸው ያጋደለውን የሃይል ሚዛን በመጠቀምና በኦሮሚያ ውስጥ ያላችውን የህዝብ ድጋፍና የለውጥ ፈለግ መሰረት በማድርግ ደፈር ያሉ የለውጥ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ በፓርላማ ውስጥ ለውጥ ፈላጊ ግዛቶች ያላቸውን የቁጥር ብልጫ በአግባቡ በመጠቀም ህዝቡ የሚጠይቃቸውን ለውጦች ሊጀምሩና ወደ ቀጣዩ የለውጥ አቅጣጫ አገሪቱን ማድረስ ይችላሉ። ይህ እንግዲህ ቀጭኑ ግን ትልቁ እድላቸው ነው።፡

ጎታችና አፋኝ ሃይሎች የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ በየደረጃው መሰናክል እንደሚፈጥሩ ሊታሰብ ይገባል። ከዚህ ውስጥ በዋናነት ሊጠቅስ የሚገባው ሰሞኑን የተጀመረው የለውጥ አራማጆችን እየለቀሙ ወደ እስር ቤት ማጎር ነው። ዓለምን ጉድ ባሰኘ የአፈና አካሄድ ከእስር ቤት ከወጡ ገና ጥቂት ቀናት ያስቆጠሩ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ መሪዎችን እንደገና መልሰው  ለእስር ሰቆቃ ዳርገዋቸዋል። ሸንጎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን እስራትና አፈና አጥብቆ ይኮንናል። የዶክቶር አቢይ ሃቀኛ የለውጥ ፈላጊነት የሚረጋገጠው ይህን በሰላማዊ ህዝብ ላይ የተቃጣ የመከራና የእስራት ጉዞ ማስቆም ሲችሉ ነው።  ህዝቡ እስካሁን የህወሃትን ደባ ተቋቁሞ ከመበተን አንድነትን፤ ከጥላቻ ፍቅርን፤ ከመራራቅ መቅረብን መርጧል። የዶክተር አቢይ መንግስት ስኬት ሊያመጣ የሚችልውና ከአደናቃፊዎቹም የሚመጣብትን ጥቃት ሊመክት የሚችለው  በህዝቡ ላይ እምነት ሲኖረውና ከህዝቡ ጋር ሲወዳጅ ብቻ ነው።

ዶ/ር አቢይ አሕመድ ይህንን አገር የመምራት ከፍተኛ ግዴታና ኃላፊነት ሲቀበሉ ከፊታቸው የተደቀኑ ብዙ ችግሮችና አማራጮች እንደሚጠብቋቸው ቢያውቁም፤ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ፤ አማራጮቹን ለማየትና ብሎም ችግሮቹን ለማስወገድ ኃላፊነቱን እንደተረከቡ ሊያደርጓቸው በሚችሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሸንጎ ሊያነሳቸው የሚሻቸው ዐበይት የፖለቲካ ኃሳቦች የሚከተለት ናቸው-

1.1         የአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዋነኛና ቀዳሚ ዓላማ መሆን የሚገባው፤ አንዳንድ መሠረታዊ ያልሆኑ ለውጦችን አድርጎ ኢሕአዴግን ከነጉድፉ ሥልጣን ላይ ማሰንበት ሳይሆን፤ ለሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት በሩን መክፈት ይሆናል። ለሽግግር ሥርዓቱ በር ከፋች የሚሆኑ ርምጃዎች የሚከተሉትን ሊያጠቃልሉ ይገባል፦

  • ሳይውል ሳያድር በአጭር ጊዜ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስወገድ
  • ለወደፊትም የመከላከያ ሰራዊት በሲቪል አስተዳደ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ በህግ መገደብ
  • ድርጅታዊ የስለላና የግድያ መዋቅሮችን ማስወገድ፤
  • ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ባስቸኳይና ያላንዳች ቅድመ-ሁኔታ መፍታት፤

1.2        ሰላማዊ የሽግግር ሥርዓት በሮችን መክፈትና የቀዳሚም ሆነ የተባባሪነት ሚና ወስዶ የሰላም ኮንፈረንስ በአገር ውስጥ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ወይም ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጥሪ ጋር መተባበር፤

1.3        ተቃዋሚ ድርጅቶች ያላንዳች ተጽዕኖ በአገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱና የየራሳቸውን ድርጅት ምልመላ እያደረጉ ለምርጫ እንዲዘጋጁ ማበረታታትና ሕጋዊ ድጋፍም እንዲያገኙ ማድረግ፤

1.4        የሕዝቡን የመናገር፣ የመጻፍ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶችን ከአሁን ጀምሮ ማስከበር።

1.5     የፍትህ ስርዓቱን ለማስተካከል አሁን ያሉትን ዳኞች በሙሉ በማባረር፤ አዲስ የዳኞች መደባ ስርዓት ማቋቋም። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶ/ር አቢይ አሕመድና በዙሪያቸው የሚያስቀምጧቸው ባለ-ራዕዮችና ዴሞክራሲያዊ አገር ወዳዶች እነዚህን ማድረግ ከቻሉ በርካታ የአገሪቱ ችግሮች ባመዛኙ ይቀረፋሉ የሚል ጽኑ ዕምነት አለን። እስካሁን በሕዝብ ላይ በአንዳንድ ወገኖች የተፈጸሙ ግፎችና ወንጀሎች ቀናቸውን ጠብቀው ፍትህ እንዲያገኙም በሩን ለውይይት መክፈት አግባብ ነው እንላለን።

ያለፍትህ ወደፊት መግፋት አይቻልምና ትውልዱ የሚጠይቀውን የፍትህ ጥያቄ በደፈናው ካሳለፍነው “አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ” እንዳይሆንብን ሸንጎ ጥብቅ ዕምነቱ ነው። ዶ/ር አቢይ ባሕር ዳር ላይ በተደረገው ስብሰባ ተገኝተው ተናገሩት የተባለውን ታሪካዊ ጥቅስ ሠፋ አድርገንና ለኢትዮጵያዊነትና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን እንዲሠራ በማድረግ፤ “ኢትዮጵያዊነት በወንፊት እንኳ ተለይቶ የማይወጣ ሠርገኛ ጤፍ ማለት ነው” ብለን በማጠቃለል ነው።

አንድነት ኃይል ነው!

ሰላምና ፍትኅ ለኢትዮጵያ ሕዝብ!